top of page

ታዋቂዋ አርቲስት ለምን ንቅለ ተከላ አስፈለጋት?

ለዓመታት፣ በአለም ዙሪያ ባሉ አድናቂዎቿ በድምጿ ስርቅርቅነት ፣ በፊልሞቿ ሳቢነት እና በሚማርክ ፈገግታዋ የምትታወቀው ሴሌና ጎሜዝን ምን አጋጥሟት ነበር?


ree

ከተለመደው የዝና መድረክ ወደ ኋላ ስታፈገፍግ ፤ በወቅቱ ብዙ ጥያቄዎች ተነስተው ነበር።


እውነታው፣ በመጨረሻ ስትገልጽ፣ የበለጠ አሳሳቢ ነበር። 

ሴሌና ጎሜዝ ከሲስተሚክ ሉፐስ ኤራይቲማቶሰስ (SLE) ጋር ትኖር ነበር

 

ይህ በሽታ ምንድን ነው?

 

የእርሷ ታሪክ እጅጉን መነጋገሪያ ከመሆኑም በላይ በአለም ዙሪያ ሚሊየኖች የሚያሳልፉትን ተግዳሮት ማሳያ መስታወት ሆነ። በሽታው እንዳለባቸው ሳያውቁ የሚሰቃዩም ብዙዎች ናቸው።


 

ታሪኩ እንዲህ ነው...


ሰሌና ጎሜዝ ከህጻንነቷ ጀምሮ የዝና ጣሪያ ላይ የወጣች ፤ የፊልም አክተር ፣ ተዋናይ ነበረች። ፊልሞቿን ዘፈኖቿ በአለም ዙሪያ በብዙዎች ታየተው ተወደዋል።


ታድያ ይህች ተዋናይ ለአመታት ይደክማት እንደነበር ገልጻለች። ከድካሟ ባሻገር ከባድ የመገጣጠሚያ ህመም እንደንበረባት እና መገጣጠሚያዎቿም እንደሚያብጡ አስረድታ ነበር። አእምሮዬ እና እኔ (My Mind & Me) በሚለው ዶክመንተሪዋ ላይ እንደውም ... " ከ እንቅልፌ እንደነቃው የማለቅስባቸው ቀናቶች ነበሩ። ህመሙ ከባድ ነበር።" ብላ ገልጻለች።

ree

ታድያ ከ አስር አመት በፊት እ.ኤ.አ በ2015 ሉፐስ በሽታ (SLE) እንደተገኘባት ለአለም ይፋ አደረገች። በሽታው ጤነኛ ህዋሳት በበሽታ መከላከያ ስርአት ሲጠቁ የሚመጣ ነው። ከመጋጠሚያዎቿ ባሻገር ፤ በሽታው በኩላሊቶቿ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ጀምሮ ነበር። እግሮቿ እና እጆቿ ማበጥ ጀመሩ። በህክምናው ይህን በሽታ ተከትሎ የሚመጣው የኩላሊት መቆጣት ሉፐስ ኒፍራይተስ (Lupus Nephritis) ይባላል። 


ታድያ በጥቃት ስር ያለው ኩላሊቷ መዳከም ጀመረ። እ.ኤ.አ. በ 2017 የኩላሊት ሥራዋ በአደገኛ ሁኔታ መቀነሱ ታወቀ። ይህን ጊዜ ዶክተሮች በአስቸኳይ ንቅለ ተከላ እንደሚያስፈልጋት ነገሯት።


ኩላሊት የለገሰችው ጓደኛ
ኩላሊት የለገሰችው ጓደኛ

ታድያ በዚህ ጭንቅ ጊዜዋ የቅርብ ጓደኛዋ ደረሰችላት። ይህንን እጅግ አስደናቂ ተግባር ሰሌና አመስግናለች። በወቅቱ ጓደኛዋ ፍራንሲያ ራይሳ ኩላሊቷን በመለገሷ ፤ የሰሌና ህይወት ሊድን ቻለ። 

 

ይህን ፈታኝና ከባድ ጊዜ ካለፈች በኋላ ሰሌና ማስታወሻ ዶክመንተሪ ሰርታለች። እዚህም ዶክመንተሪ ላይ ከእንደዚህ አይነት ስር የሰደደ ህመም ጋር መኖር የሚፈጥረው የ አእምሮ ቀውስ እና ተከትሎት ስለሚመጣ ውጥረትም ዘርዝራለች።


በአሁኑ ወቅት በሽታዋ በቁጥጥር ስር ሆኖ ፤ ንቅለ ተከላ የተደረገው ኩላሊቷ በጥሩ ደረጃ እየሰራ ይገኛል። ሆኖም ግን በሽታው ጋር ተያይዘው ያሉ የረዥም ጊዜ የጤን እክሎች እያስታመመች ፤ ውጤታማ ህይወት እየመራች ትገኛለች።


ኤስ አሌ ኢ(SLE) ወይም ሉፐስ ምንድነው?


ይህ ሥር የሰደደ ራስን የመከላከል በሽታ ነው።  በዚህ በሽታ ጊዜ የሰውነት በሽታ የመከላከል ስርአት ሰውነትን እንደመጠበቅ ፈንታ ፤ በስህተት ጤነኛ ህዋሳትን ያጠቃል። ይህም በሰውነት ዙሪያ የተስፋፋ መቆጣት እና ህመም ያመጣል። ሁሉንም የሰውነት አካል የሚያጠቃ ሲኦን በብዛት መጋጠሚያዎችን ፣ ቆዳን፣ ኩላሊቶችን እንዲሁም አንጎልን ያጠቃል። ምልክቶቹ እና የህመሙ ደረጃ ከሰው ሰው ፈጽሞ ይለያያል።

ree

ስርጭቱ ምን ይመስላል?


  • በዓለም ዙሪያ ወደ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሉፐስ አለባቸው።

  • ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ በይበልጥ ይታያል። በተለይ በመውለጃ እድሜ (ከ15-44 ዓመት) ያሉ ሴቶችን ያጠቃል።

  • የአፍሪካ ዝርያ ያላቸው ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ከመሆኑም በላይ ፤ በሽታው ሲያጋጥማቸው ከባድ ሊሆን ይችላል።

  • በሽታውን ቀድሞ ማወቅ ውጤታማነቱን በእጅጉ ያሻሽላል።


ምልክቶቹ ምን ይመስላሉ?

ሉፐስን በባህሪው "ታላቁ አስመሳይ" ብሎ መጥራት ይቻላል።

ለምን?


ምክንያቱም ምልክቶቹ ከሌሎች ብዙ በሽታዎች ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ለሉፐስ ተብሎ ካልተመረመሩ ፤ ታካሚዎች ለሌላ በሽታ ሲታከሙ አመታት ሊቆዩ ይችላሉ።


ree

የተለመዱ ምልክቶቹ የሚከተሉትን ያካትታሉ

  • የማያቋርጥ ድካም

  • የመገጣጠሚያ ህመም ፣ መደደር/ መድረቅ ፣ እና እብጠት

  • የቆዳ ሽፍታ (በተለይ በጉንጮቹ ላይ የሚታወቀውን የቢራቢሮ ሽፍታ የዚህ በሽታ ምልክት ነው)

  • ጸህይ ብርሀንን አለመቻል (ቆዳ ጸሀይ ሲነካው በቀላሉ ይቆጣል/ ሽፍታ ያመጣል)

  • ትኩሳት

  • ፀጉር መሳሳት

  • የአፍ ቁስል

  • ያልታወቀ የክብደት ለውጦች (መጨመር/መቀነስ)

  • የኩላሊት ችግሮች

  • የደረት ሕመም/ የትንፋሽ እጥረት፣ ወ.ዘ.ተ...


እያንዳንዱ ታካሚ ሁሉም ምልክቶች የሉትም። ሉፐስ ምልክቶቹ ከሰው ወደ ሰው በጣም ይለያያል።

ሐኪሞች ታድያ ሉፐስን እንዴት ይለያሉ?


ree

ሉፐስን ለመለየት ባለሙያዎች የሚከተሉትን ምርመራዎች በጥምረት ይጠቀማሉ።

  • የደም ምርመራዎች(ANA &anti-dsDNA)

  •  የኩላሊት ተሳትፎን ለመፈተሽ የሽንት ምርመራዎች

  •  የሚታዩ የሕመም ምልክቶች ላይ የተመሰረተ አካላዊ ምርመራ

  •  የተጎዱ አካላትን ለማየት የኢሚጂንግ ምርመራ

  • እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱ ናሙና ሊታዘዝ ይችላል።


ምልክቶቹ ስውር እና በቀላሉ ሊለዩ የማይችሉ በመሆናቸው ፤ ሉፐስን ለመመርመር ዓመታት ሊወስድ ይችላል። በተዋናይዋም ይህን አይተናል።


ህክምናውስ ምን ይመስላል?


ሉፐስ ፈውስ የለውም!

ሆኖም ግን የበሽታውን ምልክቶቹ የሚያክሙ ፤ የሰውነት መከላከያ ስርአትን የሚያረጋጉ ፤ ዘመናዊ ሕክምና አማራጮች አሉ። እነኝህም አማራጮች ታካሚዎች ውጤታማ እና ደስተኛ ህይወት እንዲመሩ ያስችሉዋቸዋል።


ree

ከመድሀኒቶቹም ባሻገር የሚከተሉት ያስፈልጋሉ።


  • መደበኛ የሕክምና ክትትል

  • የፀሐይ መከላከያ ማድረግ (የፀሐይ መከላከያ ክሬም (Sun Screen) ፣ጥላ፣ እንዲሁም ቆዳን የሚከልል ልብስ ማድረግ)

  • የተመጣጠነ አመጋገብ መመገብ

  • መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ

  • በቂ እረፍት

  • የአእምሮ ጤና ድጋፍ



ቀደም ብሎ ህክምና ማድረግ ፤ አካል ጉዳት እንዳይደርስ ይከላከላልና ፈጽሞ እንዳይዘናጉ።

በሽታውንም ቀድመው ይቆጣጠሩ።


በግንዛቤ፣ በቅድመ ምርመራ እና በተገቢው እንክብካቤ፣ ታማሚዎች የተሟላ ህይወት እየቻሉ ፤ በስቃይ መኖር የለባቸውም።


ለዚህም ምልክቶቹን ያስተውሉ ፤ ቀድመው ህክምና ያድርጉ። ለሌሎች ያጋሩ።


 

 

Comments


bottom of page