top of page

ስለ ኩላሊት ጤና ማወቅ ያለብዎ?

 በአንድ ወቅት (እ.ኤ.አ1990ዓ.ም.) በዓለም ዙሪያ ወደ 378 ሚሊዮን የሚገመቱ ጎልማሶች የኩላሊት ጤና እክል ነበረባቸው።


ታድያ አሁንስ?

 ቀንሷል ብለው ካሰቡ... ተሳስተዋል!


ከሠላሳ ዓመት በኋላ - ይህ ቁጥር ከእጥፍ በላይ ጨምሯል።


በአሁኑ ወቅት በአለም ዙሪያ ወደ 788 ሚሊየን የሚጠጉ ጎልማሶች ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ (CKD) አለባቸው። 


ይህ ማለት በአለም ላይ ካሉ 7 ጎልማሶች ውስጥ አንዱ ኩላሊቱ ሙሉ ጤና ላይ አይደለም ።


 ምን ያህሉስ ይሆን ይህ ችግር እንዳለበት የሚያውቀው? እርስዎስ የኩላሊትዎ ጤና ያለበት ሁኔታ ያውቃሉ?


እ.ኤ.አ በ 2012 (ከ 13 አመት በፊት) የኩላሊት ህመም አለም አቀፍ ካርታ
እ.ኤ.አ በ 2012 (ከ 13 አመት በፊት) የኩላሊት ህመም አለም አቀፍ ካርታ

በ 30 አመት ውስጥ ለታየው መጨመር ዋነኛ ምክንያት ተደርገው ስኳር፣ ደም ግፊት፣ ውፍረት እና የተመጣጠነ ምግብ ጉድለት ይጠቀሳሉ። የእነርሱ መጠን በአለም ዙሪያ መጨመር ቁጥሩን አሳድጎታል ተብሎ ይታመናል።


በዚህም የተነሳ ከሁለት አመት በፊት በፈረንጆች 2023ዓ.ም ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ዘጠነኛው ገዳይ በሽታ ሆኖ ተመዝግቧል። በዛ አመት ብቻ ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።


በሀገራችን ኢትዮጵያስ?


ree

በኢትዮጵያም ይህ ችግር በደንብ ይስተዋላል። ሀገር አቀፍ ጠቋሚ ቁጥሮች ባይኖሩም ፤ አንዳንድ በሆስፒታል ላይ የተመሰረቱ ጥናቶች  ይህን ይመሰክራሉ። ለምሳሌ፡


  •  በአማራ ክልል በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ፤ ከ 5 ታካሚዎች አንዱ ስር የሰደደ የኩላሊት ህመም አለበት። ለዚህም አጋላጭ ሆነው የተዘረዘሩት የደም ግፊት በሽታ፣ ማጨስ፣ እና የህመም ማስታገሻ መድሀኒቶችን መውሰድ ናቸው።


  • ከ 5 አመት በፊት በስኳር በሽተኞች መሀከል የተደረገ የዳሰሳ ጥናት በበኩሉ  ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 3 የስኳር በሽተኞች አንዱ ( 35-36%) ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ተገኝቶበታል።


  • በዚህ አመት የወጣ አንድ ጥናት ሥር የሰደደ የኩላሊት ህመም በኢትዮጵያ እጅጉን እየጨምረ እንደሚገኝ ጠቁሟል። በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ (እ.ኤ.አ 2019 - 2022) ቁጥሩ በእጥፍ ጨምሯል። ይህም በተለይ በወንዶች ላይ ተስተውሏል።


አሁንስ አያሳስብም ?


ሀገር አቀፍ መረጃ አለመኖሩ ፤ ችግሩን ሙሉ በሙሉ እንዳንረዳ አድርጎን ይሆናል። ባለን መረጃ እራሱ ችግሩ አሳሳቢ ነው።  የተሟላ የኩላሊት ህክምና መስጠት የሚችሉ ተቁሞች በሌሉባት በኢትዮጵያ ከማሳሰብ አልፎ ሊያስፈራን ይገባል።


በሀገር ደረጃ የሚመጣ ለውጥ እንዳለ ሆነ ፤ በእርሶ ደረጃ ማድረግ ያለብዎ ላይ ማተኮር አለብዎ።


እንደ ማህበረሰብ ዛሬውኑ ለውጥ ማውጣት አለብን። ይህ ደግሞ የኩላሊትዎን የጤና ከማወቅ ይጀምራል።


ኩላሊት ሙሉ በሙሉ እስኪዳከም የኩላሊት ምርመራ የማያደርጉ ብዙዎች ናቸው።  



አስቸጋሪው እውነታ እነሆ...


በመጀመሪያዎቹ ደረጃዎች ጊዜ ሥር የሰደደ የኩላሊት ህመም ምንም ግልጽ ምልክቶች ሉትም። የኩላሊትዎ ስራ እያሽቆለቆለ ፤ ብዙዎች የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን ይቀጥላሉ።

 

ለምን?

ጤነኛ ናቸው! ሕመም እስካልተሰማቸው ድረስ ፤ ምንም የሚያሳስባቸው ነገር የለም።

 

እውነታው!

ብዙ ዲያሊሲስ ላይ ያሉ አልያም ንቅለ ተከላ የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች አስተሳሰብ ከአመታት በፊት እንዲህ ነበረ። ጤነኛ ነበሩ።


 ምናለበት ያኔ ቀድመው ቢመረመሩ ኖሮ ፤ ሁሉንም መመለስ በቻሉ ነበር።


ቻዩ ኩላሊታቸው ታድያ ...ጉዳቱ እያየለ ሲመጣ እና ስራውን መስራት ሲሳነው... ያኔ ምልክቶች ይታያሉ። ታድያ ግን ኩላሊት ስራው ቀድሞውኑ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ ሊሆን ይችላል። የኩላሊት እጥበት ሊያስፈግ ይችል ይሆናል።


ብዙዎች ከእርስዎ በፊት የተሳሳቱትን ስእተት እርሶም አይድገሙ። ቀድመው ይከላከሉ።  ለመሆኑስ ኩላሊትዎን ጤና እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉስ ያውቃሉ?



ምልክቶቹስ ምን ይመስላሉ?


የኩላሊት ጉዳት ምልክቶች እንደደረሰው ጉዳት መጠን ይለያያል።


መለስተኛ የኩላሊት ጉዳት

ይህ የኩላሊት ጉዳቱ መጠን ዝቅተኛ ነው። ጉዳቱን አልፎ ኩላሊት ስራውን መስራት ስለሚችል ፤ የዚህን ጊዜ ምንም ምልክት አይታይም።


ታድያ በምርመራ ቢታወቅ ፤ የኩላሊት ጉዳትን ማቆም አልያም እንዳይባባስ ማድረግ ይቻላል።


የገፋ ደረጃ የኩላሊት ጉዳት


የዚህን ጊዜ ያለው የኩላሊት ጉዳት መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ፤ ኩላሊት ስራውን በትክክል እንዳይሰራ ይስተጓጎላል። የኩላሊት ስራ በመሰናከሉ የሚከተሉት ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ።


ree
  • ክብደት መቀነስ

  • የምግብ ፍላጎት ማጣትም

  • ማቅለሽለሽ

  • ቁርጭምጭሚቶች፣ እግሮች ፣ እጆች፣ አይኖች ላይ እብጠት

  • ትንፋሽ ማጠር

  • ድካም

  • የሽንት ባህሪ ለውጥ

    • ሽንት ደም መቀላቀል

    • ሽንት አረፋ መደባለቅ

    • ደግም ደጋግሞ መሽናት

    • መሀል ለሊት ራሱ ሽንት አዘውትሮ መምጣት

  • የእንቅልፍ መረበሽ/ እንቅልፍ ማጣት

  • የቆዳ ማሳከክ

  • የጡንቻ ህመም

  • ራስ ምታት ምልክቶች ሊኖሩት ይችላል።


በወንዶች ስንፈተ ወሲብ (ብልት መቆም ችግር) ሊያመጣም ይችላል።


ree

ጉዳቱ እጅጉን አይሎ ኩላሊት ስራውን መስራት ፈጽሞ ሲያቅተው ፡

  • ሽንት ፈጽሞ አለመውጣት / መሽናት ሊያቅት ይችላል።

  • አእምሮ ላይ በሚኖረው ተጽእኖ ደግሞ የባህሪ ለውጥና ኃይለኝነት ሊያመጣ ይችላል።

  • ደም ማነስ እንዲሁም የኢንፌክሽን ተጋላጭነትም ይጨምራል።


ይህን ጊዜ በኩላሊት እጥበት አልያም በንቅለ ተከላ ካልታገዘ ኮማ እንዲሁም ሞት ማብቂያው ይሆናል።


ምልክቶቹን እንዳዩ ህክምና ማድረጉ የደረሰው የኩላሊት ጉዳትን ባለበት ለመቆጣጠር ይረዳል። ለዚህም ምልክቶቹን ካስተዋሉ በአፋጣኝ አቅራቢያዎ ወዳለው ጤና ተቋም ይሂዱ።


ያስተውሉ!


ከሁሉም ከሁሉም መከላከል ይመረጣልና ዛሬውኑ ለኩላሊትዎ ጤና ቦታ ይስጡ።


በነሲብ ጤነኛ ነኝ ከማለት ይልቅ አስፈላጊውን ምርመራ አድርገው ዛሬውኑ የኩላሊትዎን ጤና ይጠብቁ።


ኩላሊቶችዎ ሲዳከሙ ድምጽ የላቸውምና ያስተውሉ!


ዝምታው ወደ ስቃይ ከመቀየሩ በፊት ዛሬውኑ እርምጃ ይውሰዱ።

 

Comments


bottom of page