top of page

የኩላሊት ህመም እና ዳፋው

Updated: Mar 6



” ጤነኛ ነበር እኮ ፤ ምን እንደነካው አናቅም”

ነበር አብሮ አደግ ጓደኛዬ  ያለኝ፤ የቤተሰቡ አባል እጅጉን በጠና ታሞ ሃኪምቤት የገባ ጊዜ። 


ታማሚው በሃያዎቹ መጀመሪያ ያለ በወንደላጤነት የሚኖር አፍላ ወጣት ነበር።  ለቀናት ከስራ ቦታ ሲጠፋ እና ስልክ መመለስ ሲያቆም ፤ ያሳሰባቸው ጓደኞቹ ሊፈጉት ወደመኖሪያ ቤቱ ይሄዳሉ። ምላሽ ሊሰጣቸው ባለመቻሉ በር ሰብረው ሲገቡ ፤ ራሱን ስቶ ከመሬት ወድቆ ያገኙትና ፤  አፋፍሰው ወደ ሆስፒታል ይዘውት ይሄዳሉ።  ያለበት የጤና ሁኔታ እጅጉን አስጊ ስለነበር ፤ ወዲያውኑ ከፍተኛ ክትትል ክፍል ይገባል። በተደረገለት ምርመራም ሁለቱም ኩላሊቱ እጅጉን ከመዳከሙ አልፎ ጭንቅላት ላይ ለውጥ ስላመጣ ኮማ (comma) ውስጥ መግባቱን ፤ እንዲሁም ስኳር እና ደም ግፊትም እንደተገኘበት ይነገራቸዋል። በዚህ ለማመን በሚያዳግት ዜና ቤተሰብ ከባድ ጭንቀት ላይ ይወድቃል። ይህን ጊዜ ነበር ጓደኛዬ ስላለው ሁኔታ ለኔ ያማከረኝ።


በሰሙት ዱብዳ እየተደናገሩ ያሉት ቤተሰቦችም ፤ የኩላሊት እጥበት (ዲያሊሲስ) ከተጓዳኝ ህክምናዎች ጋር እየተደረገ ፤ በከፍተኛ ህክምና ክፍል ክትትሉን እንዲቀጥል ይፈቅዳሉ። ሆኖም ግን ከህመሙ ሊያገግም ባለመቻሉ ፤ በሃኪም ቤት በገባ በ ሳምንቱ ከዚህ አለም በሞት ይለያል።


እላይ ታች ሮጦ ፤ ቤተሰብ መስርቶ ፤ ህይወትን ለመግፋት ህልም የነበረው ወጣት ፤ ገና ሳይጀምረው ሁሉም በአፍላነት ተቋጨ!  


እንዴት እዚህ ደረጃ እስኪደርስ አንዴም እንኳን ሀኪም ቤት አልሄደም ፤ የሚለው ጥያቄ በወቅቱ በውስጤ ይመላለስ ነበር።  እንዴት?


ይሄ ታሪክ የብዙ ኢትዮጵያውያን ታሪክ ነው። በወጣትነታቸው ኩላሊታቸው አስጊ ደረጃ ደርሶ በኩላሊት እጥበት ላይ ያሉ ፤ አልያም መታከሚያ አቅም ሳይኖራቸው የከፋ ደረጃ የደረሱ ኢትዮጵያውያን ጥቂት አይደሉም።


የኩላሊት ህመም በለሆሳስ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ቤት እየጎበኘ ይገኛል። የሱን መርዶ የመስማት ፍራቻ አድሮባቸውስ ሆስፒታል የሚፈሩ ኢትዮጵያውያንስ ስንት ናቸው? ጉዳዩን ህልም ተፈርቶ...  ያደርገዋል።


ሆኖም ግን መፍትሔ ልናገኝለት ግድ ይለናል። መፍትሔ ደግሞ ከትክክለኛ ጥያቄ ይጀምራል።


ቆም ብለን እንጠይቅ እስቲ...



ለምንድነው ማህበረሰባችን እንዲህ በኩላሊት ድክመት  እየተጠቃ ያለው?

ለምንድነው ወጣቱ በአፍላነት እድሜው እንዲህ እየታመመ ያለው?

ምንስ ማድረግ ይቻላል?


የኩላሊት ሕመም በኢትዮጵያ መስፋፋት




ከ ዛሬ ሰላሳ አርባ አመት በፊት የነበረ አንድን ግለሰብ ስለኩላሊት ህመም እና ስለኩላሊት ድክመት  ብንጠይቀው ምን የሚለን ይመስላችኋል? ያኔ በነበረው ነባራዊ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ የኩላሊት ህመም/ ድክመት ጥቂት የማህበረሰብ ክፍልን የሚያጠቃ የደዌ አይነት መሆኑን ያስረዳን ነበር። ባሳለፍናቸው አስርት አመታት ግን እውነታው ተለውጧል። የኩላሊት ድክመት እጅጉን ተስፋፍቷል። ከመብዛቱም የተነሳ የኩላሊት እጥበት ማዕከሎች ሞልተው ፤ የኩላሊት እጥበት በወረፋ እየተካሄደ ይገኛል።


ታድያ ምን ተለውጦ እዚህ ደረጃ መንሰራፋት ጀመረ?


በዚህ ዙሪያ ሁለት ምላሾች ሊሰጡ ይችላሉ። አንደኛ የሀገሪቷ የምርመራ እና የህክምና አቅም በማደጉ፤ አሁን በተሻለ ሁኔታ ደዌን መለየት እና ማከም  እንድንችል አድርጎናል። ይህም የኩላሊት ህመም ቁጥሩን እንዲጨምር አርጎት ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን ፤ ይሄ አሁን ለምናየው የመንሰራፋት ደረጃ አመርቂ ምላሽ ሊሆን አይችልም።


በቅርብ አመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከሆነ ፤  በዋነኝነት ለዚህ መጨመር ተጠያቂ የሚሆኑት ያልታወቁ ወይም ተመርምረው ቁጥጥር  ስር ያልዋሉ  የስኳር ህመም እና የደም ግፊት ህመሞች ናቸው።  እነኚህ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ፤ በ ሀገሪቷ እንደስኳር፣ ደም ግፊት፣ የስብ መዛባት ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች (ነን ኮምኒዩኬብል ዲዚዝስ) እየተበራከቱ ይገኛሉ።  የነኚህም ህመሞች መበራከት ለሚታየው የኩላሊት ድክመት/ህመም መጨመር የአንበሳውን ድርሻ እየወሰደ ይገኛል።

 

ለምንስ እነኚህ ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች ተበራከቱ?



ባለፉት አመታት ውስጥ ያሳየናቸው የአኗኗር ፣ የአመጋገገብ እንዲሁም የባህሪ ለውጦች ፤ ለነኚህ በሽታዎች ያለንን ተጋላጭነት ጨምረውታል።  እነኚህ ህመሞች ብዙ ጊዜ ምንም አይነት የበሽታ ምልክት ፊትለፊት የማያሳዩ ቢሆንም ፤ ኩላሊትን ውስጥ ለውስጥ ይጎዳሉ። ይህ የኩላሊት ጉዳት በአንድ ጀምበር የሚመጣ አይደለም። ሰውነታችን ራሱን ወዲያውኑ ስለሚጠግን ፤  እነኚህ ህመሞች ቋሚ ጉዳት ለማምጣት አመታት ይፈጅባቸዋል። ከዚህም ባሻገር የኩላሊታችንን አንድ ሶስተኛ አቅም ያህል ብቻ ስለምንጠቀም ፤ ኩላሊት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ያየለ እስካልሆነ ድረስ የላብራቶሪ ምርመራ ላይ ራሱ ኩላሊት ጤነኛ መስሎ ሊታይ ይችላል። ታማሚም በዚህ ወቅት ህመም ስለማይሰማው ጤነኛ ነኝ ብሎ ያስባል።  የሁለቱንም ኩላሊታችንን ሙሉ አቅም የሚያሟጥጥ ጉዳት ሲደርስ ግን ፤ ያኔ  ኩላሊት ይደክማል። ኩላሊት በውጤታማነት ስራውን ስለማይሰራም ፤ በኩላሊት ማጠቢያ ማሽን (ዲያሊሲስ ማሽን) መታገዝ ግድ ይለዋል።  በዚህም ባህሪያቸው የተነሳ እነኚህ ህመሞች ድምጽ አልባ ነፍሰ ገዳይ የሚባል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።

 



መልካሙ ዜና


ይህንን ሁሉ ማስቆም ይቻላል።

 

እንዴት?


ከዚህ በታች የተጠቀሱትን በማድረግ የኩላሊት ድክመትን/ ህመምን መከላከል እንዲሁም የኩላሊትን ጤና መጠበቅ ይቻላል።



ከህክምና ጋር የተያያዙ መንገዶች


  • በየተወሰነ ጊዜ የተሟላ የህክምና ክትትል (ቼክ አፕ) በማድረግ ጤናዎን ማረጋገጥ፤ ህመም ከማጋጠሙም በፊት መከላከል ይችላሉ።

  • የደም ግፊት፣ የስኳር መጠን እና የደም ውስጥ የስብ ክምችትን በየተወሰነ ጊዜ መከታተል። እነዚህ ኩላሊትን ሊጎዱ የሚችሉ ተቀዳሚ መንስኤዎች ውስጥ ናቸው ።

  • ማንኛውንም መድሀኒት ከመጠቀምዎ በፊት ኩላሊት ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ ማረጋገጥ /የህክምና ባለሙያ ምክር ማግኘት መልካም ነው።


የኩላሊትን ጤና የሚጠብቁ የ አኗኗር ዘዴዎች


  • በየቀኑ በቂ ውሃ መጠጣት – ይህም ኩላሊት በቀላሉ ስራውን እንዲሰራ ያግዘዋል።  ለዚህም አንዲት ሴት በቀን ቢያንስ 2 ሊትር ፤ አንድ ወንድ በቀን ቢያንስ 2.5 ሊትር ውሃ እንዲጠጡ ይመከራል። የተጣራ ውሃ የሌለበት አከባቢ የሚኖሩ ግለሰቦች ፈልቶ የቀዝቀዘ የመጠጥ ውሃ እንዲጠቀሙ ይመከራል።

  • አትክልትና እና ፍራፍሬ  ማዘውተር – የዕለት  ምግባችን ላይ የ ቅባት መጠናችው የቀነሰ ኩላሊትን የሚያግዙ ምግቦችን ማዘውተር ይመከራል።  

  • አካል እንቅስቃሴ ማድረግ – ይህም የደም ፍሰትን ያሻሽላል፤ የኩላሊትን ስራ ያሳልጣል፤ እንዲሁም  የሰውነትን ክብደት ለመቆጣጠር ያግዛል።

  • በምግብ ውስጥ ያለውን የጨው መጠን መቀነስ – በሶዲየም የበለፀጉ ምግቦች ኩላሊትን ላይ ተጽእኖ ስለሚኖራችው የምንመገበው ምግብ መጠነኛ ጨው ቢኖረው ይመከራል። ከዚህም ባሻገር የታሸጉ ምግቦች የ ሶዲየም መጠናቸው የበዛ ስለሚሆን አለማዘውተር ይመረጣል።



አሁንም አልረፈደም!

 

የኩላሊት ድክመትን በቀላሉ መከላከል እየቻልን ለምን ብዙ ቤተሰቦች የ ገፈቱ ቀማሽ ይሁኑ? 

 

መፍትሔው ያለው እጃችን ላይ ነው።

 

ጤናችንን እንጠብቅ ኩላሊታችንን እንታደግ።


1 Comment


selesetachun meker keleb enamesegenalen

Like
bottom of page