top of page

ካንሰር በኢትዮጵያ ፡ ለመሆኑ ዝግጁ ነን?

ድሮ... ድሮ

ካንሰር የሀብታም አገሮች በሽታ ተደርጎ ይታሰብ ነበር።

ለነገሩ እንዲያ ቢታሰብም አይደንቅም።


ለምን ካሉ ጥሩ?


በማህበረሰባችን ዘንድ የካንሰር አጋላጭ ተብሎ የሚታሰበው ፤ ከዘመናዊነት ጋር ተይያዥነት ያለው የአኗኗር ዘይቤ ነበር። ይህ አኗኗር ደግሞ ብዙውን ጊዜ ከሀብታም ሀገራት ጋር እና ከሀብታም ግለሰቦች ጋር ብቻ ይታሰብ ነበር። ለዚህም ካንሰር የእነሱ ህመም ተደርጎ ይወሰድ ነበር።

ree

ሆኖም ግን... ባለፉት አመታት ፤ በኢትዮጵያ ካንሰር ያለማቋረጥ እየጨመረ ይገኛል። ይህ ደግሞ አብዛኛው ማህበረሰቧ በዝቅተኛ ኑሮ ላይ ለሚገኝ ሀገራችን አሳሳቢ ጉዳይ ነው። እንዲሁ ጫና ለበዛበት የጤና ስርአት ላይ ትርፍ ሽክም ይሆናል።


ይህንን በመረጃ እንደግፈው

በኢትዮጵያ በየአመቱ ወደ 80,000 የሚጠጉ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በካንሰር ይታመማሉ። ከእነኝህ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር የሚወስዱት በሴቶች የማኅጸን ጫፍ ካንሰር እና የጡት ካንሰር ሲሆን በወንዶች ደግሞ የትልቁ አንጀት ካንሰር እና የፕሮስቴት ካንሰር ናቸው። ከዚህ ውስጥም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ካንሰሩ ከተሰራጨ ወይም ከደረጀ በኋላ ነው እንዳለባቸው የሚያውቁት። ይህም ደግሞ የካንሰርን ገዳይነት በኢትዮጵያ ከፍ እንዲል አድርጎታል። ለዚህም በየአመቱ ከ 50,000 የሚበልጡ ወገኖቻችን በካንሰር የተነሳ ህይወታቸውን እንደሚያጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ree

ይህንን አሳሳቢ ወረርሽኝን ለመግታት በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር በኩል የካንሰር ክትትል እና መከላከል ላይ ስትራተጂክ ፕላን ተነድፎ መሰራት ከተጀመረ ሰንበትበት ብሏል። ይህንን ተከትሎ የካንሰር ምዝገባ እየተሻሻለ ቢሆንም ፤ የተሟላ አይደለም። ይህ ደግሞ ያለውን የካንሰር ታማሚ ዙሪያ የተሟላ መረጃ እንዳይኖር መሰናክል ሆኗል።


📊 ኢትዮጵያ ውስጥ ስለተለመዱት ካንሰሮች አንድ በአንድ እናውራ

አሁን ያለው መረጃ እንደሚያሳየው


ree
  • የጡት ካንሰር - የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ እጅግ ከተለመዱ ካንሰሮች ውስጥ ይጠቀሳል። ከ10 የካንሰር ታማሚዎች ውስጥ በአማካይ ሶስቱ የጡት ካንሰር ታማሚ ናቸው። ይህ ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ነው። ከአፍሪካም አንጻር በፍጥነት እያደገ ነው። አሳሳቢው ደግሞ ከዚህ ታማሚዎች ውስጥ አብዛኞቹ በመጀመሪያ 5 አመት ውስጥ ይሞታሉ። ለዚህም ዘግይቶ በሽታቸውን ማወቃቸውን አስተዋእጾ አለው።



ree

የማኅጸን ጫፍ ካንሰር - ከጡት ካንሰር ቀጥሎ ሴቶችን በብዛት የሚያጠቃ ካንሰር ሲሆን ከአጠቃላይ ካንሰሮችም 13 በመቶ የሚጠጋውን ይወስዳል። ይህ ካንሰር በዋነንኝነት ኤችፒ ቪ በሚባል የቫይረስ አይነት የሚመጣ ነው። ለዚህም ይህንን ካንሰር በክትባት መከላከልም ፤ በቅድመ ካንሰር ምርመራም ቀድሞ መያዝ ይችላል። ሆኖም ግን ብዙዎችበመደበኛ ምርመራ ባለማድረጋቸው ፤ ክትባት መውሰድ በሚችሉበት እድሜ ባለመውሰዳቸው በሽታውን የሚያውቁት አርፍደው ነው። ለዚህም የኢትዮጵያ ሴቶች ላይ ህይወት በመቅጠፍ ዋና ተጠቃሽ ነው።


የማህፀን ካንሰር -  ይህ ደግሞ የማህጸን ዋና አካል ካንሰር ሲሆን ፤ ብዙ ጊዜ እድሜ መግፋትን ተከትሎ ፣ ከሆርሞን ስርአት እና ከውፍረት ጋር ተያይዞ ይከሰታል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህም አርፍዶ በመገኘቱ ብዙ ታማሚዎችን ለሞት እየዳረገ ይገኛል።



ree

የጉበት ካንሰር - በጣም ገዳይ ከሆኑ የካንሰር አይነቶች አንዱ ሲሆን ፤ በኢትዮጵያ በይበልጥ የሚታየው ከጉበት ቫይረሶች ኢንፌክሽን ጋር ተያያዥነት ያለው ነው። ቀድሞ ከታወቀ ቀዶ ጥገናን ጨምሮ የተለያዩ አማራጮች ቢኖሩም ፤ አብዛኛውን ጊዜ ዘግይቶ ስለሚታወቅ ፤ የሕክምና አማራጩ አነስተኛ ነው።

የኮሎሬክታል ካንሰር - የትልቁ አንጀት የታችኛው ክፍል ካንሰር ሲሆን ፤ ከጌዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ ይገኛል። በወንዶችም ዘንድ ቀዳሚ የካንሰር አይነት ሲሆን ፤ ካንስሩ ከአመጋገብ ስርዐት ጋር ተያያዥነት አለው። በተለይም ዝቅተኛ አሰር ያላቸውንና ከፍተኛ ስብ ያላቸውን ምግቦች የሚመገቡ ሰዎች ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ነው።


ree

የጨጓራ ካንሰር - ቁጥሩ ከሌሎች አንጻር ያነሰ ቢመስልም ፤ ገዳይነቱ ከፍ ያለ ነው። ይህም ካንስር ደጋግሞ የጨጓራ ባክቴሪያ የሚያማቸውን ሰዎች፣ የሚያጨሱ ሰዎች እንዲሁም እድሜያቸው የገፉ ሰዎች ላይ በብዛት ይታያል።


የጉሮሮ ካንሰር ፡ ይህ ካንሰር መጠኑ ከሌሎች ካንሰሮች ያነስ ቢመስልም ፤ ኢትዮጵያ ይህ ካንሰር በከፍተኛ ቁጥር ከሚገኝባቸው አገራት ተርታ ትገኛለች። ትኩስ ምግብ በሚመገቡ አከባቢዎች ላይ በብዛት የሚታይ በመሆኑ ፤ ስርጭቱ በሰሜን እና በምስራቅ ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ነው።

ree

የሳንባ ካንሰር - ሀገራችን ኢትዮጵያ ከአለም አንጻር አነስ ያለ የሳንባ ካንሰር ታማሚ ቁጥር ያላት ቢሆንም ፤ በኢትዮጵያ የዚህ ካንሰር ተጠቂዎች አጭሰው የማያውቁ እናቶች ናቸው። የአጫሽ ቁጥሯ ያነስ ቢሆንም ፤ እየተባባሰ ያለው የአየር ብክለት እና እየጨመረ ያለው የትምባሆ ተጠቃሚ ቁጥር የዚህን ካንሰር መጠን በቀጣይ አመታት ሊጨምር እንደሚችል ጠቋሚ ነው።


የፕሮስቴት ካንሰር - ወንዶችን ከሚያጠቁ ግንባር ቀደም ካንሰር አይነቶች ውስጥ ተጠቃሽ ነው። እ.ኤ.አ. በ 2022 የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ከ አመስት አመት በፊት በኢትዮጵያ 2,720 የፕሮስቴት በሽተኞች ሲገኙ ፤ በዚሁ አመት ወደ 1,600 ሰዎች ከዚህ ካንሰር ጋር ተያያዥነት ባለው ምክንያት ሞተዋል። የተሟላ ግንዛቤ ኖሯቸው ፣ ምልክቶቹን ለይተው ፣ ቅድመ ምርመራ አድርገው ቢሆን ፣ ብዙዎቹን ማትረፍ ይቻል ነበር።

ree

በህጻንነት እድሜ የሚያጋጥም ካንሰሮች በአመት በግምት ከ5,000-6,000 ልጆችን የሚታመሙ ሲሆን ፤ ከዚህ ውስጥ ባለን የህክምና አቅም ልናተርፍ የቻልነው አንዱን ብቻ ነው።


ምን አዲስ ነገር ቢኖር ነው ካንሰር እንዲህ እየጨምረ የሚገኘው?


ባለፉት ጥቂት አስርት አመታት ውስጥ ያመጣነው የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። ይህም የከተሞች መስፋፋትን ተከትሎ በመጣው ዘመናዊነት ፤ አመጋገባችን ተለውጧል። ባህሪያችን ተለውጧል። ተንቀሳቅሶ ስራ መስራት ፈንታ አብዛኛውን ቀናችንን የምናሳልፈው በቢሮ፣ በሱቅ፣ በቤት ውስጥ ተገድበን ነው። እንቅስቃሴያችንም በ መኪና ነው። አልኮል መጠጣት እና ትምባሆ ማጨስም እየተስፋፋ ይገኛል።

ree

ሲኖረን ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች አብዝተን እንመገባለን። የታሸጉ ምግቦችማ የቅንጦት ስለሆኑ ፤ ባገኘው እድል ይዘወተራሉ! ገበታ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችም በአንድ መንገድ ይሁን በሌላ ለኬሚካሎች ተጋላጭነት አላቸው። ገበሬዎች ብዙ ምርት ለማግኘት ማዳበሪያ ይጠቀማሉ፣ አረም ማጥፊያ ይረጫሉ።


ከዚህ በተጨማሪም አከባቢያችን እጅጉን እየተለወጠ ይገኛል። የኦዞን መሳሳትን ተከትሎ የጸሀይ ብርሀን ጎጂነት አቅም ጨምሯል። በከተሞች ከፍተኛ የሆነ የአየር መበከል አለ።

ree

የህክምና ተደራሽነትም ውስን ነው። ማህበረሰቡ ባለበት የኑሮ ጫና መደበኛ የጤና ምርመራ ማድረግ ይቸገራል። ይህ ደግሞ ብዙው ካንሰር አርፍዶ እንዲገኝ ያደርገዋል። የህክምና ወጪን ችሎ ሙሉ ምርመራ እና ህክምና ማድረግ የሚሳነው የማህበረሰብ ክፍልም ጥቂት አይደለም። እነሱ ምልክቱን ቢያውቁም እንኳን ፤ አስፈላጊውን ህክምና እስኪያደርጉ እጅጉን ይዘገያሉ።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ ተላላፊ በሽታዎች ስላሉ ፤ በኢንፌክሽን የተነሳ የሚከሰቱ የካንሰር አይነቶችም እየጨመሩ ይገኛሉ። እላይ የተጠቀሱት የጨጓራ ካንሰር፣ የማህጸን ጫፍ ካንሰር፣ የጉበት ካንሰርን ለዚህ ዋቢ አድርጎ መጥቀስ ይቻላል። እነኝህን ኢንፌክሽኖችን መከላከልም እጅጉን ወሳኝ እርምጃ ቢሆንም ፤ይህን ለመከላከል የማህበረሰቡ ግንዛቤ ማደግ ይኖርበታል።


በመልካም ጎኑ ደግሞ ከድሮው አንጻር የህክምና አቅማችን በማደጉ ፤ ድሮ መለየት የማንችላቸውን የበሽታ አይነቶች በቀላሉ መለየት ማወቅ እና ማከም ችለናል። ለዚህም ከድሮው አንጻር የካንሰር ቁጥሩ በመጠኑ ጨምሮ ሊታይ ይችላል። ይህንን የህክምና እመርታ ተከትሎ ፤ ብዙ ሰዎች ካንሰር የሚያጋጥምበት እድሜ ክልል ላይ ይደርሳሉ። ሆኖም ግን ይህ ያለውን የካንሰር ስርጭት የሚጨምርበት ፍጥነትን ብቻውን አይገልጽም።



እርስዎ እንደግለሰብ ሊወስዷቸው የሚችሏቸው ተግባራዊ እርምጃዎች

የዓለም ጤና ድርጅት እንደገለጸው በኢትዮጵያ ከሚገኙት ካንሰሮች ውስጥ እስከ 40 በመቶ የሚደርሱትን መከላከል ይቻላል።እንዴት እንደሆነ እነሆ ፡


  • ክትባት ይውሰዱ እርስዎ ወይም ልጆችዎ ለ ክትባቶች ብቁ ከሆኑ ዛሬውኑ ይውሰዱ። ክትባቶች ካንሰርን ይከላከላሉ።

    • የ ማህጸን ጫፍ ካንሰር የሚያመጣው ቫይረስ (HPV) ክትባት በመውሰድ ይህንን ካንሰር መከላከል ይችላል።

    • የጉበት ቫይረስ (ሄፐታይተስ ቢ) ክትባት እና ህክምና በማድረግ አብዛኛዎቹን የጉበት ካንሰሮችን መከላከል ይቻላል።

ree
  • አሳሳቢ የካንሰር ጠቋሚ ምልክቶችን ይወቁ።  

    • ያልታወቀ ክብደት መቀነስ፣

    • በጡት ውስጥ ያለ እብጠት፣

    • ያልተለመደ ከሴት ብልት የሚወጣ የደም መፍሰስ፣

    • የማያቋርጥ ሳል፣

    • ደም የቀላቀለ ሽንት ካዩ ቶሎ ምርመራ ያድርጉ።

    • ቀደም ብሎ ከተያዘ ሕይወትዎን ማትረፍ ይቻላል።

ree

  • አኗኗር ዘይቤዎን ያስተካክሉ።

    • የታሸጉ ምግቦችን ይቀንሱ።

    • የተፈጥሮ ምርት ይመገቡ።

    • ቅባት ይቀንሱ።

    • ውፍረትዎን ይቆጣጠሩ።

    • መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ።

    • አትክልት እና ፍራፍሬ አዘውትረው ይመገቡ።

    • ትኩስ ነገር አቀዝቅዞ በመመገብ የጉሮሮ ካንሰር ተጋላጭነትን መቀነስ ይቻላል።

    • ትምባሆን ያስወግዱ እና አልኮልን ይገድቡ - እነዚህ ለብዙ ነቀርሳዎች ሊወገዱ የሚችሉ ዋነኛ መንስኤዎች ናቸው።


  • ቀደም ብሎ ማወቅ እና መደበኛ ምርመራ ማድረግ ለብዙ ካንሰሮች መፍትሔ ነው። ከበሽታው የማገገሚያ ፍጥነትን በእጥፍ ሊጨምር ይችላል። ለዚህም የቅድመ ካንሰር ምርመራዎችን ያድርጉ። ጤናዎን በመደበኛ ምርመራ ይወቁ።

ree

  • የካንሰር ታካሚዎችን ይደግፉ። ያበርቷቸው!  ስለበሽታው ግዝፈት ሳይሆን ስለእነርሱ ጥንካሬ በማንሳት አጠንክሯቸው። ያስተውሉ ተግባራዊ ድጋፍ ተገዢነትን እና ውጤቶችን ያሻሽላል።



በመከላከል ብቻ በየአመቱ በ አስር ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወትን መታደግ ይችላል።

ሆኖም ግን አሁንም ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ ነው።

እንደ ሀገርስ ዝግጁ ነን?


አጭር መልሱ ፡ ገና አይደለንም ! ግን መሆን እንችላለን።


ኢትዮጵያ ካንሰርን ለመቆጣጠር ብዙ እርምጃዎችን ወስዳለች። ጤናጥበቃና ባለድርሻ አካላት በዚህ ላይ እየሰሩ ይገኛሉ። የኤች ፒቪ ክትባት ለሁሉተኛ ደረጃ ተማሪ ሴቶች እየቀረበ ይገኛል። የጉበት ቫይረስ ክትባት የህጻንት ክትባቶች ውስጥ ከተካተተ ቆይቷል። የተለያዩ የቅድመ ምርመራ እንቅስቃሴዎች በየአከባቢው ይታያሉ። የሰው ሀይል አቅምን ለማጎልበት የካንሰር ስፔሻሊስት ስልጠና በትላልቅ ሆስፒታሎች እየተካሄደ ይገኛል። የመመርመሪያ እና የህክምና አቅምን ለማጎልበት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርጸ እየተሰሩ ነው።

ree

ቢሆንም በቂ የካንሰር መድህኔቶች አሁንም የሉም። የጨረር ህክምና አቅም ያላቸው ተቋማት ጥቂት ናቸው። የካንሰር ምርመራ አቅም የተሟላ አይደለም። ብዙ መደረግ የሚችሉ የካንሰር ምርመራዎች አይካሄዱም።


ለካንሰር ታማሚዎች የአቅም ድጋፍ ፕሮግራሞች እምብዛም ናቸው። ታማሚዎች በቂ ማህበራዊ ድጋፍ የላቸውም።


ስለዚህ በዚህ ዙሪያ ስራዎች ይቀራሉ።


አንኳር ሀሳቡ!

ካንሰር እየጨመረ ቢሆንም ፤ ይህንን ለመቆጣጠር የተለያዩ ስራዎች በመንግስት እና ባለድርሻ አካላት በኩል እየተሰሩ ቢሆንም ፤ መቆጣጠር እስክንችል ብዙዎች ህይወታቸውን ያጣሉ። ብዙ የካንሰር ዓይነቶችን መከላከል የሚቻል ሲሆን ፤ የተቀሩትን ቀድሞ በማወቅ በውጤታማነት ሊታከሙ ይችላሉ። ለዚህም ደግሞ እርስዎ የበኩልዎን ድርሻ ይወጡ። እርምጃ ከወሰድን። መንግስት እና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እያደረጉ ነው። እርስዎስ!?

በዚህ ወር እነኝህን ያድርጉ -

  • እላይ የተጠቀሱት የካንሰር መከላከያ ክትባቶች  መገኘት በአከባቢዎ ያለ የጤና ተቋም ይጠይቁ። ካለና ከተመለከትዎ ክትባቱን ይውሰዱ፤ የቤተሰብ አባልዎንም ያስወስዱ።

  • የማኅጸን ጫፍ ምርመራ ምርመራ ያለበትን ተቋም አጣርተው ፤ ከተመለከትዎ ይመርመሩ። ቤተሰብ አባልዎንም ያስመርምሩ።

  • የካንሰር ጠቋሚ ምልክቶችን ለይተው ይወቁ ። ቢያንስ ሶስት ሰዎች ያካፍሉ። ይህንን ትምህርታዊ ጽሁፍም ለሌሎች ያጋሩ።

  • በአካባቢዎ ያሉ የካንስር ታማሚዎች ፤የአቅም ችግር ካለባቸው ይደግፏቸው። በዚህ ላይ የሚሰሩ የምግባረ ሰናይ ድርጅትን ይርዱ።


ያስተውሉ! የሚያደርጓቸው ትናንሽ እርምጃዎች ተደምረው ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ።

 

1 Comment


thomasjoe604
Oct 23

ทุกวันนี้การหาคู่หรือเพื่อนใหม่ผ่านโลกออนไลน์กลายเป็นเรื่องง่ายและปลอดภัยขึ้นมาก โดยเฉพาะการเข้าร่วมเว็บไซต์ที่ช่วยให้คุณพบปะผู้คนใหม่ ๆ ได้อย่างสะดวกและมั่นใจ โดยไม่จำเป็นต้องออกจากบ้าน หากคุณกำลังมองหาความสัมพันธ์ที่จริงจัง หรือเพียงแค่คนคุยสนุก ๆ เว็บไซต์ที่ให้บริการในการ รับงานคู่ ก็เป็นทางเลือกที่ช่วยให้คุณได้พบคนที่มีความสนใจคล้ายกันในบรรยากาศที่เป็นกันเองและปลอดภัย

Like
bottom of page