top of page

🎀 የጡት ካንሰር ምን? በምን? እንዴት? 🎀

እስኪ ስለ ጡት ካንሰር እንነጋገር...


ስለ ጡት ካንሰር ሰምተው ይሆናል። ለመሆኑ በቂ ግንዛቤ አለዎት?


ጡት ካንሰር ምንድነው?


እንዴትስ ይመጣል?


በምንስ መከላከል ይቻላል?


ree

የጡት ካንሰር ሴቶችን ከሚያጠቁ ካንሰሮች ዋነኛ ሲሆን ፤ ከ 8 ሴቶች ውስጥ አንዷ በጡት ካንሰር ትታመማለች ተብሎ ይገመታል።


 🚨 የኢትዮጵያ ሴቶች ከሌላው አለም ቀድመው በጡት ካንሰር እየታመሙ ፤ አርፍደው እየታከሙ ፤ በቶሎ እየሞቱ ይገኛሉ።  

ለምን?

ይህንን ለመረዳት መጀምሪያ ስለ ጡት ካንሰር እንረዳ።


 🔍 የጡት ካንሰር ምንድን ነው?


ካንሰር በባህሪው የሰውነታችን ህዋሳት ያለልክ የሚያድጉበት በሽታ ነው። የጡት አከባቢ ያሉ ህዋሳት እንደዚህ ያለገደብ ሲያድጉ የጡት ካንሰር ይባላል።  እነኝህ ህዋሳት መጠናቸው ሲበዛ ፤ ጡት ውስጥ የምናስተውለው እብጠት ይፈጥራሉ። እነኝህ ካንሰር የሆኑ ህዋሳት ቀደም ብለው ካልተያዙ ፤ ወደ ቅርብ አካላት (የጡት ቆዳ፣ የደረት አጥንት ፣ ጡት አከባቢ ወዳሉ ንፍፊቶች) አልያም ፤ ወደ ሩቅ አካላት (አጥንትን፣ ጉበትን፣ ሳንባንና አንጎልን ጭምር) ሊዛመቱ ይችላሉ።

የጡት ካንሰርን እድገት የሚያሳይ ምሳሌያዊ ሰእል። ቢጫው የጡት ካንሰር ነው።
የጡት ካንሰርን እድገት የሚያሳይ ምሳሌያዊ ሰእል። ቢጫው የጡት ካንሰር ነው።

ጡትን የሚሰሩ የተለያዩ ህዋሳት እንዳሉ ፤ በዚሁ ልክ የተለያዩ የጡት ካንሰር ዓይነቶች አሉ። ባህሪያቸውም ለየቅል ነው። አንዳንዶቹ ቀስ በቀስ ያድጋሉ። ሌሎቹ ደግሞ ቁጡ ናቸው። በፍጥነት ያጠቃሉ። ይሰራጫሉ። 


 በጣም የተለመዱት ሶስት የጡት ካንስር አይነቶች እነሆ፡


  • ኢንቬዚቭ ደክታል ካርሲኖማ (Invasive ductal carcinoma (IDC)) – ይህ ካንሰር ከወተት ማምረቻ ቱቦ ህዋሳት ይመነጫል። ብዙ ጊዜ እብጠት/ እባጭ ጡት ላይ ያሳያል። ወደ አጠገቡ ወዳሉ ህዋሳት ፤ እንዲሁም ንፍፊት እና ቆዳም ይሰራጫል።


  • ኢንቬይዚቭ ሎብዩላር ካርሲኖማ (Invasive Lobular Carcinoma (ILC)) -ይህ ወተት ከማምረቻ ክፍል (lobules) ይመነጫል። አጠገብ ወዳሉ ህዋሳት ሲሰራጭ በረድፍ ስለሆነ ፤ በጣም ካልተስፋፋ እባጭ ላያሳይ ይችላል።  


  • ትሪፕል ኔጌቴቭ ብረስት ካንሰር (Triple Negative Breast Cancer)- ይህ የአፍሪካ ዘር ባላቸው ሴቶች ላይ የተለመደ ሲሆን ፤ ለህክምና ከባድ ውጤቱም የከፋ ነው።


እነኝህ በጣም የተለመዱ ይሁኑ እንጂ የተለያዩ የጡት ካንሰር አይነቶች አሉ።


💣 የጡት ካንሰር በምን ምክንያት ይመጣል ? መንስኤው 


ጡት ካንሰር በተለያዩ ምክንያቶች ይመጣል። ለመረዳት እነኝህን ምክንያቶቹን በሶስት መጠቅለል እንችላለን ፡-ዘረመል (ጂኖች/ genes)፣ ሆርሞን እንዲሁም አኗኗር ዘይቤ። እነኝህን አንድ በአንድ እንይ


ree

ዘረመል፦የጡት ካንሰር ከ5 እስከ 10 ፐርሰንት ያህል በዘር ይተላለፋል። ለዚህም ዋነኛ ተጠቃሽ የዘረመል ለውጦች ናቸው። በተለይም ብርካ የሚባለው የዘረመል ክፍል( BRCA1 & BRCA2 ጂኖች) ጋር የተያያዘ ለውጥ ይህ እንዲከሰት ያደርጋል። ይህ ለውጥ ያለባቸው ሴቶች በህይወት ዘመናቸው የጡት ካንሰር የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ ስለሆነ ፤ መደበኛ የጡት ምርመራ ያስፈልጋቸዋል።


ሆርሞኖች፦ የጡት ካንስር ታማሚነት ከ ኢስትሮጅን ሆርሞን ጋር ይያዛል። ለዚህም ይህ ሆርሞን ደማቸው ውስጥ ከፍ ብሎ ለረዥም ጊዜ የቆየ ሴቶች ተጋላጭነት ያይላል። ለዚህም

  • ከ 30 አመት በኋላ የመጀመሪያ ልጃቸውን የወለዱ ሴቶች

  • የወሊድ መቆጣጠሪያ ለረዥም ጊዜ የወሰዱ ሴቶች (እነኝህ ሴቶች በተቃራኒው ከ ማህጸን ካንሰር የተጠበቁ ናቸው)

  • ቀድመው የወር አበባ የሚያዩ ሴቶች

  • ቆይተው የሚያርጡ ሴቶች

  • የሆርሞን ህክምና የሚወስዱ ሴቶች ለዚህ ተጋላጭነታቸው ያየለ ነው። 


የአኗኗር ዘይቤ

ከአኗኗር ዘይቤ ውስጥ ተጠቃሾቹ

  • ውፍረት እና ከፍተኛ-ቅባት አመጋገብ

  • የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ

  • ከመጠን በላይ አልኮል  መጠጣትና ማጨስ ተጠቃሽ ናቸው።

ጡት ማጥባት እና ልጅ መውለድ ደግሞ ተጋላጭነት ይቀንሳል።

🚩 ታድያ ለዚህ ተጋላጭ እነማን ናቸው ?


እላይ በተጠቀሰው መሰረት ፤ ለጡት ካንሰር ተጋላጭነት ያለባቸው የሚከተሉት ናቸው።


  • እድሜያቸው ከ40 በላይ የሆኑ ሴቶች (  ወንዶችም ጡት ካንሰር ሊይዛቸው ቢችልም እጅጉን ያልተለመደ ነው።) ፤

  • በቤተሰብ የጡት ወይም የማህጸን ካንስር ታሪክ ካለ ፤

  •  ዘረመል ለውጥ ካለ ፤

  • 30 ዓመት በኋላ የመጀመሪያ ልጅ የወለዱ ሴቶች ፤

  •  ደረታቸው አከባቢ የጨረር ሕክምና የተደረገላቸው ሴቶች ፤ ተጋላጭነታችው ይጨምራል።


🛑 መረጃዎች እንደሚያሳዩት የጡት ካንሰር ካለባቸው ሴቶች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት የሚታወቅ የቤተሰብ ታሪክ የላቸውም።  ለዚህም ሁሏም ሴት ንቁ መሆን አለባት። 

🛡️ በምን መከላከል ይቻል ይሆን?

ree

ለጡት ካንሰር አጋላጭ ምክንያቶች መሀከል ፤ የተወሰኑትን መቆጣጠር ይቻላል። አኗኗር ዘይቤን  በማስተካከል ተጋላጭነትን  መቀነስ ይቻላል።  ለዚህም


🥗ጤናማ ክብደት ይኑርሽ።

🏃 አካል እንቅስቃሴ አዘውትሪ።

🍷 አልኮል አዘውትረሽ አትጠጪ።

🚭  ሲጋራ አታጭሽ።

🍼 ከተቻለ ልጅሽን ጡት አጥቢ።

🍎 ቅባት መመገብ ቀንሺ። ፍራፊሬ አትክልትና አዝእርት ዘውትሪ። 

🧬 በቤተሰብሽ የጡት /የማህጸን ካንሰር ታሪክ ካለ ፤ መደበኛ የጡት ምርመራ አድርጊ።

🩺 በንቃት አዘውትረሽ ጡቶችሽን መመርመር ልመጂ። በእጆችሽ እየዳሰሽ እብጠት መኖሩን አስተውይ። አተር የሚያክል እንኳን እብጠት ካየሽ ፤ በአፋጣኝ ጤና ባለሙያን አማክሪ።


⚠️ መታወቅ ያለባቸው ምልክቶች


የጡት ካንሰር  ሲጀምር ብዙ ጊዜ በባህሪው በህመም አያሰቃይም። የህመም ምልክት ላያሳይ ይችላል። ለዚህም ቀደም ብሎ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ለዚህ ነው ተጠራጣሪ መሆን የሚመከረው። ህመም የሚኖረው ሲደረጅ፣ ሌሎች አካላትን ሲወር ነው።

 

ree

ሆኖም ግን እነኝህን ምልክቶች ፈጽሞ ችላ እንዳትይ!

✅ ጡቶች ላይ ወይም ብብት ስር ያለ ማንኛውንም እብጠት ፤

✅የጡት ቅርጽ ፣ መጠን እና ያለው ልስላሴ ለውጥ ፤

✅የጡት ቆዳ ከቀላ፣ ከሰረጎደ እንዲሁም እንደቡርትካን ልጣጭ ካደበደበ ፤

✅ከጡት ጫፍ ወተት ያልሆነ ፈሳሽ ከወጣ (ደም ሊቀላልቅል ይችላል)፤

✅ የጡት ጫፍ ወደ ውስጥ መግባት ወይም መገልበጥ ፤

✅ ጡት ላይ የማያቋርጥ ህመም ካለ ፤ አስተውይ ።


ከእነዚህ ምልክቶች መካከል የትኛውንም ካስተዋልሽ ፈጽሞ ጊዜ እንዳትሰጭ። ወዲያውኑ የሕክምና ምርመራ አድርጊ።

🛑የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ


የጡት ካንሰር በኢትዮጵያም ሴቶችን የሚያጠቃ ግንባር ቀደም የካንሰር አይነት ነው። በብዛትም ሴቶችን ከሚያጠቁ የካንሰር አይነቶች አንድ ሶስተኛውን ይወስዳል። እ.ኤ.አ በ 2020 ብቻ በኢትዮጵያ 16,133 አዲስ የጡት ካንሰር በሽተኞች ተገኝተዋል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ይህ ካንሰር እየተስፋፋ ይገኛል።


አሳዛኙ ሁኔታ ደግሞ አብዛኞቹ የጡት ካንሰር ታማሚዎች ወደ ህክምና የሚመጡት ፤ አርፍደው ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ደርሶ ነው። በዚህም የተነሳ የህክምናው ውጤታማነት ዝቅተኛ ይሆና። ከሌላው አለም አንጻርም የጡት ካንሰር ኢትዮጵያ ላይ ጎልማሳዎችን ያጠቃል። በሌላው አለም አብዝቶ ከ 50 አመት በኋላ ሲያጋጥም ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኞቹ ታማሚዎች በሰላሳዎቹ እና በአርባዎቹ እድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው።


ree

በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሴቶች በጡት ካንሰር ይሞታሉ። የአብዛኞቹ ሴቶች የሞት ምክንያት የህክምና ጉድለት ሳይሆን ፤ ዘግይቶ መታወቁ ነው። አንዳንድ ሴቶች ካወቁም በኋላ ፤ ህክምና ለመውሰድ ወራት ሲፈጁ ይስተዋላል።  ይህም በሽታው  ከሚያመጣው  ህመም  አልፎ የህይወታቸውን ዋጋ ያስከፍላቸዋል። 


🛑ለምንድነው የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ እየተስፋፋ እና አርፍዶ እየተገኘ ያለው?


የጡት ካንሰር መስፋፋት እና አርፍዶ መታከም ጋር የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ከእነኝህም መሀክል ጥቂቶቹ


  1. ግንዛቤ ማጣት። አንዳንድ ሴቶች የጡት ካንሰር ዙርያ ያላቸው ግንዛቤ የተሟላ ስላልሆነ ፤ ችላ ይላሉ። በሐኪም የሚመከሩትንም ህክምና ለመውሰድ ያመነታሉ። ህክምናውን ለመውሰድ እስኪወስኑ በሽታው ይሰራጫል። አንዳንዶችም የባህል ህክምና ሲሞክሩ ሰንብተው ፤ በሽታው ሲደረጅ ወደ ጤና ተቋም ተመልሰው ይመጣሉ።  ይህም ህመሙን ማከም የሚቻልበትን ወርቃማ ጊዜ ይሰርቃል።

     

  2. አንዳንድ ሴቶች የጡት ካንሰር እንዳለባቸው እንዲታወቅ አይፈልጉም። ለዚህም የህክምና ክትትሉን ችላ ይላሉ። እንደ ፈጣሪ ቁጣ/ቅጣትም ተደርጎ ስለሚወሰድ ፤ በሽታውን ይደብቁታል። ካንሰሩ ግን ከጀርባ ስለሚደረጅ ፤ መደበቅ የማይቻልበት ጊዜ ይደርሳል። የዚህን ጊዜ የጤና ተቋም ይጎበኛሉ።


  3. የአቅም ጉዳይም ሌላኛው ምክንያት ነው። አብዛኞቹ ሴቶች የሕክምና ክትትል በሚፈልጉበት ጊዜ ካንሰሩ ስለሚዛመት ከፍተኛው ወጪ ይጠይቃል። ኬሞቴራፒ መድሐኒቶች በቀላሉ በመንግስት ሆስፒታሎች አይገኙም። ከገበያ ሲገዙም ሒሳባቸው ክፍተኛ ነው። ተጨማሪ መድሐኒቶች እና ምርመራዎች ሲታሰብ ሂሳቡ ይንራል። ይህ ደግሞ ለታችኛው የማህበረሰብ ክፍል ለምትመጣ ሴት ፈታኝ ነው። መታከም ብትፈልግም ፤ የገንዘብ እጥረት በአፋጣኝ እንዳትታከም ያደርጋታል።


  4. የራዲዮ ቴራፒ ህክምና የሚሰጡ ቦታዎች እጅጉን ውስን ስለሆኑ ፤ ወረፋ እስኪደርሳቸው በሽታቸው የሚደረጅም አሉ።


  5. በተጨማሪም የስፔሻሊስት ሐኪሞች እና መመርመሪያ መሳሪያዎች ውስንነትም አለ። አሁን ኢትዮጵያ ባላት አቅም የተሟላ ምርመራ ማድረግ አይቻልም። ለዚህ ህክምና አስፈላጊ የሆኑ ልዩ ምርመራዎችን (ለምሳሌ የዘረመል ምርመራ ፣ የ ፔት ስካን (PET CT Scan)) የሉም።


 

💬 ዝምታን እንስበር!


ree

የጡት ካንሰር "የሴቶች ጉዳይ" ብቻ አይደለም። የማህበረሰብ ጉዳይ ነው። እናቶችን ፣ ሴቶች ልጆችን ፣ ሚስቶችንና እህቶችን ይነካል ።


በግንዛቤ ጉድለት ፈጽሞ ማንም ሴት መሞት የለባትም!

አሁኑኑ ይህንን ተግባራዊ ለውጥ እናምጣ፡


✅ ስለ ጡት ካንሰር እንነጋገር።

✅ ያለንን ሳይንሳዊ ግንዛቤ ለሌሎች እናጋራ።

✅ ሴቶች ምልክቶችን እንዲያስተውሉ እና እራሳቸውን እንዲመረመሩ እናበረታታ። 

✅ ምንም አይነት ለውጥ ካየች አንዲች ሴት ሀኪም እንድታማክር እናበረታታት/

 

በዚህም ህይወት እናድናለን! አንዲት ሴት ትተርፋለች።

Comments


bottom of page