እናቶቻችን ለምንድነው በሳንባ ካንሰር እየተጠቁ ያሉት?
- Zebeaman Tibebu
- Jun 10
- 4 min read
Updated: Jun 11

ገና ወፎች ሳይጮሁ ነበር ከ እንቅልፏ የተነሳችው። ልጆቿ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ። ባለቤቷም ቀኑን ሙሉ ስራ ይውላል። ምግብ ማዘጋጀት ነበረባት። ገና የጸሀይ ጮራዋ ሳይታይ ተነስታ ከሰል አያያዘች። ምግብ አበሰለች።
ልጆቿ ሲነሱ። ቤቱ ሞቅ ብሏል። ምግብ ቀርቧል ፣ ሻይ ፈልቷል ፣ ምሳቃቸው ታስሯል። ደስ አላቸው። ባሏን ሽኝታ ወደ ማእድ ቤት ገባች። ባሏ ሰርቶ የሚያመጣው በቂ ስላልነበር ፤ ይህች እናት ሙልሙል መጋገር ጀመረች። ይህች እናት ኑሮዋን ለማገዝ እንጀራ ጋግራ ሙልሙል ሸጣ ኑሮዋን ታግዝ ነበር። የሞላላት ቀን 50 እንጀራ ፣ 100 ሙልሙል ትሸጣለች። ባሏና ልጆቿ ከስራ ሲመለሱ እራት አዘገጃጅታ ሁሉን አሟልታ ነበር የምትጠብቃቸው።
ከ 20 አመት በኋላ...
ልጆቿ ዩንቨርስቲ ጨርሰው ፤ ስራ ጀምረዋል። ታድያ ይህች እናት የሳል ህመም ሰነበተባት። መድሐኒት ወስዳለች፤ ግን አልተሻላታም። የሳንባ ምችም ተብላ ታክማ ነበር። ሌላው ህመም ሲለቃት ሳሉ ግን አልተዋትም ነበር። ከቀን ወደ ቀን ሰውነቷ እየመነመነ መጣ። ጤናዋ ጉዳይ ያሳሰባቸው ልጆች ወደ ሀኪም ቤት ይዘዋት ሄዱ። ዜናው ግን ፈጽሞ ያልጠበቁት ነበር። ሁሉቱም ሳንባዋ በሳንባ ካንሰር ተጠቅቷል።
ደነገጡ!
ቤቷን ለማቅናት ስትለፋ የተነፈሰችው የማገዶ ጭስ ፤ ይህን ይዞ እንደሚመጣ ቀድመው ቢያውቁ ምን ያደርጉ ነበር ?
ሳንባ ካንሰር ምንድነው

የሳንባ ካንሰር በዓለም ላይ ካሉት ገዳይ ነቀርሳዎች አንዱ ነው። በገዳይነቱ ከጡት፣ ከፕሮስቴት፣ እና ከአንጀት ካንሰር ይበልጣል። በህይወት ያሉ የካንሰሩ ታማሚዎችም ያለባቸው ስቃይ/ ህመም ቀላል አይደለም። ለዚህ ካንሰር አጋላጭ ምክንያቶች ተብለው የሚጠቀሱት ማጨስ፣ የአየር ብክለት፣ እንደ ራደን እና አስቤስቶስ ያሉ ኬሚካሎች ፤ እንዲሁም በቤተሰብ የሳንባ ካንሰር መኖር ናቸው።
በአብዛኛው የአለም ክፍል ይህ ካንሰር ከሲጋራ ማጨስ እንዲሁም ፤ ከኢንዱስትሪ ኬሚካሎች ተጋላጭነት ጋር የተያያዘ ነው። እንደውም በምእራቡ አለም 80 ፐርሰንት የሚሆነው ከሲጋራ ማጨስ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። ሲጋራ በውስጡ ወደ 60 የሚጠጉ ካንሰር አምጪ ኬሚካሎች ስላሉት ይህንን ካንሰር ያመጣል።
ሆኖም ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት ላይ የዚህ ካንሰር ዋነኛ ገፈት ቀማሾች ፤ ሲጋራ የማያጨሱ የቤት እመቤቶች ሆነው ይገኛሉ።
ለምን?
በእነኝህ አገራት ለዚህ ካንሰር ዋነኛ አጋላጭ ምክንያት ተደርጎ የሚገለጸው የቤት ውስጥ አየር መበከል ነው። ይህም በባህላዊ መንገድ ቤት ውስጥ ምግብ ከማብሰል ጋር ይያዛል። አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ቤቶች (ከ 85 እስከ 92 ፐርሰንት) ፤ ለአንድም ይሁን ለሌላ ግልጋሎት ለቀን የምግብ ፍጆታቸው ከሰል፣ እንጨት፣ የአዝእርት አገዳ ፣ ኩበት ፣ ወ.ዘ.ተ... ይጠቀማሉ። እነኝህ አይነት የኃይል ምንጮች ባዮ ማስ ፊዩል ሲባሉ ፤ እነሱ ሲቃጠሉ የሚወጣው ጭስ ከባድ የጤና ጠንቅ አለው። በውስጡ ብዙ ካንሰር አምጭ ኬሚካሎችን የያዘ ነው። እነኝህ ኬሚካሎች እና ጋዞች ውስጥ በጥቂቱ፡

ደማችን ውስጥ በቀላል ገብተው የሚቆዩ ብዙ ጤና ጠንቅ ያላቸው ደቃቅ ኬሚካሎች (PM10 & PM 2.5)።
ካርቦን ሞኖክሳይድ
ፎርማልዲሃይድ
የናይትሮጅን ውህዶች
ሌሎች ካንሰር አምጪ ኬሚካሎች፣ ወ.ዘ.ተ...
ይህንን ለመሸሽ የቡታ ጋዝ የሚጠቀሙ ቢኖሩም ፤ ቡታ ጋዝ ውስጥ ያለው ነጭ ጋዝ ጤና ጠንቁ የተሻለ አይደለም።
ለዚህ ተመራጭ የኤሌክትሪክ ስቶቭ አልያም ፤ ሜቴን ወይም ኢታኖል የሚጠቀሙ የሲሊንደር ስቶቮች ናቸው።
እነኝህም ነዳጆች በደንብ አየር የማይናፈስበት ቤት ውስጥ ሲቃጠሉ ፤ አብዛኛው የቤተሰብ አባላት ለጭሱ ተጋላጭ ይሆናሉ። ለዚህም ግንባር ቀደም ተጋላጭ የሚሆኑት ፤ ምግባችንን ሲያበስሉ የሚውሉ እናቶቻችን ናቸው። እነሱም ቀን በቀን ሳያቋርጡ ፤ ይህን መርዛማ ጭስ ይተነፍሱታል። ጭሱ ውስጥ ያለውም ኬሚካል ሳንባቸውን ይጎዳል ፤ ያሳምማል። ይህ ህመም በአመታት ውስጥ ሲደጋጋመ የሳንባ ካንሰር/ነቀርሳ ይሆናል።
የአለም ጤና ድርጅት እንደሚገልጸው ይህንን ጭስ የምትተነፍስ ሴት/እናት 400 ሲጋራዎች እንደሚያጨስ ሰው ተጋላጭነት አላት።
ታድያ ኢትዮጵያ ላይ ሳንባ ካንሰር ታማሚዎች እድሜ በሲጋራ ሳንባ ካንሰር ከመጣባቸው ሰዎች ቢያንስ እንዴት ይደንቅ።
📊 አሳሳቢው እውነታ

የቤት ውስጥ የአየር ብክለት በዓለም ዙሪያ በየአመቱ ከ4 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ይገድላል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በሴቶች ላይ ከሚደርሱት ስርሰደድ የሳንባ ህመሞች መካከል ፤ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በቤት ውስጥ በሚያጋጥም የአየር ብክለት የተከሰቱ ናቸው።
በኢትዮጵያ ካሉ አሰር የገጠራማ ቤቶች ዘጠኙ ፤ ለኃይል ፍጆታ በዋነኝነት እንደ ከሰል ፣ ኩበትና የማገዶ እንጨት ይጠቀማሉ።
ለዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሴቶች እና ህጻናት በቀን በአማካይ 3 ሰአታት ያህል ለጭስ ይጋለጣሉ።
በየአመቱ ከ 50,000 እስከ 67,830 ኢትዮጵያውያን በዚህ የተነሳ ይሞታሉ።
ከሌላው አለም አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ የሳንባ ካንሰር በጎልማሳነት እድሜ ያጋጥማል።
ብዙ የኢትዮጵያውያን እናቶች ምግብ ሲያበስሉ ፤ መርዛማ ጭስ ይስባሉ። ቤተሰባቸውን ለመመገብ ፤ እራሳቸውን ለአደጋ ያጋልጣሉ።
🚨 ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምልክቶች፡ ምን ማየት ይኖርቦታል?
ታድያ የሳንባ ካንሰር በአንድ ቀን የሚፈጠር ድንገተኛ ክስተት አይደሉም። ቀስበቀስ በአመታት ውስጥ የሚመጣ እንጅ። ለዚህም በመጦሪያ በማረፊያ እድሜያቸው፣ ውድ እናቶቻችን ሀኪም ቤት ይንከራተታሉ።
ከዛ በፊት በነበሩት አመታት ላይ ጠቋሚ ምልክቶች ቢኖሩም ፤ ችላ ተብለው ይታለፋሉ። ጉንፋን ወይን ከእድሜ ጋር የሚመጡ ተድርገው ይታሰባሉ።
እነኝህ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

የማያቋርጥ ደረቅ ሳል
በቀላል ተግባራት ላይ የትንፋሽ ማጠር
በተደጋጋሚ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን
የአስም አይነት ትንፋሽ ጋር ተደራቢ ድምጽ
ድካም
ደረትን መጭመቅ/ማፈን
ሰውነት መክሳት (ክብደት መቀነስ)
እነዚህ ምልክቶች ከጥቂት ሳምንታት በላይ ከቆዩ ወይም ተደጋግመው ከመጡ አይጠብቁ። ምርመራ በአፋጣኝ ያድርጉ።
💡 ታድያ ምን እናድርግ? መከላከያ መንገዶቹ ምንድን ናቸው?
በተቻለ ሁኔታ የዘመናዊ የኤሌክትሪክ ምድጃን አልያም የሲሊንደር ስቶቭ (ኢታኖል እና ሜታኖል) መጠቀም። እሱ ተያይዞ የሚመጣው የኤሌክትሪክ ክፍያ እና የስቶቭ ወጪ አብዛኛው የማህበረስብ ክፍል ሊከበደው ይችላል። ይህ ካልሆነ ግን ፡

ከተቻለ ከቤት ውጭ ማብሰል።
ቤት ውስጥ ካበሰሉ፣ መስኮቶች ይክፈቱ። አየር እንዲናፈስ ያድርጉ።
የእናቶችን ግንዛቤ ከፍ ማድረግ። ይህንን መረጃ እርስዎም ለጎረቤቶት እና ለቤተስብዎ ያካፍሉ።
ቤት ውስጥ ማብሰል ግድ ከሆነ ፤ የጭስ ማውጫ ወይም የዘመኑ (ጭስ የሚቀንሱ) ማብሰያዎችን ይጠቀሙ።
እድሜ ከ 50 አመት ካለፈ በኋላ በየአመቱ የሳንባ ካንሰር ምርመራ ቢደረግ መልካም ነው። ይህ ደግሞ ለረዥም አመት በባህላዊ መንገድ ሲያበስሉ ለነበሩ እናቶች እጅጉን አስፈላጊ ነው።
💬 እናታችን እኛን ልታበላ መሞት የለባትም።
ኢትዮጵያ ውስጥ እናቶቻችንን ብናከብርም ፤ ለእነሱ የምናደርገው ጥበቃ ከዚህ መጀመር አለበት።
ለማገዶ የምንጠቀመው እንጨት ፤ በዝምታ እናቶቻችንን በሳንባ ካንሰር እየነጠቀን መሆኑን ማየት ይኖርብናል።
👉 እናትቶቻችን፣ እህቶቻችን ወይም ጎረቤቶቻችን በከሰል ወይም በማገዶ ሲያበስሉ ስናይ እንምከራቸው። መስኮት ይክፈቱ ፤ ሳንባ ምርመራ ያድርጉ።
የነገ ጤናችን ዛሬ በምናደርገው ተግባራዊ ለውጥ የተመሰረተ ነውና ፤ ችላ አንበል።
Comments