top of page

መንጋጋ መቆለፍ ብቻ አይደለም! ስለ ቴታነስ ማወቅ ያለብዎት እውነታ

አንድ ሰው በዛገ ብረት ቢወጋ፤ ብዙዎቻችን ወዲያውኑ “ቴታነስ ይይዘዋል!” ብለን እናስባለን። ይህ ፍርሃት በብዙዎቻችን አእምሮ ውስጥ የታተመ ከመሆኑ የተነሳ፤ ዝገት እና መንጋጋ ቆልፍ የማይነጣጠሉ ጠላቶች መስለው ይታዩናል።



ይህ ግን ትክክል አይደለም!

ዝገቱ ራሱ የብረትና የኦክስጅን መስተጋብር ውጤት እንጂ፤ በሽታውን ሊያመጣ አይችልም።  ታዲያ ለዘመናት የዛገ ብረትን የፍርሃታችን ምንጭ ያደረግነው ለምንድነው? ከዚህ የተሳሳተ ማኅበራዊ ግንዛቤ በስተጀርባ ምን ዓይነት ሳይንሳዊ እውነታ ተደብቋል?


ዛሬ ስለቴታነስ ምንነት፣ በምን እንደሚመጣ እና መከላከያ መንገዶቹ እናነሳለን።


ቴታነስ ምንድነው?

የቴታነስ ባክቴሪያ የሚያሳይ ምስል
የቴታነስ ባክቴሪያ የሚያሳይ ምስል

ቴታነስ ክሎስትሪዲየም ቴታኒ (Clostridium tetani) በሚሰኝ ባክቴሪያ የሚመጣ፤ ማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓትን የሚያጠቃ እጅግ ከባድ በሽታ ነው። የዚህ ባክቴሪያ ጠንካራ እንቁላላሎች (spores) በብዛት የሚኖሩት በምንረግጠው አፈር፣ በአቧራ እና በእንስሳት ሰገራ ውስጥ ነው። ለዚህም ነው ከአፈር ጋር ቀጥተኛ ንክኪ የነበረው ብረት ወይንም ስለት እንደተወጉ ወይም እንደቆሰሉ፤ በላዩ ላይ የሚገኙት ባክቴሪያዎች ቆዳን አልፈው፤ ወደ ሰውነት ይገባሉ።


በቁስሉ ውስጥ ኦክስጅን ዝቅተኛ የሆነ ምቹ ሁኔታ ካገኘ ባክቴሪያው ማደግ ይጀምራል። ይህን ጊዜ ቴታኖስፓዝሚን (tetanospasmin) የተባለ እጅግ ኃይለኛ መርዛማ ንጥረ ነገር ያመነጫል። ይህ መርዝ በቀጥታ የነርቭ ሥርዓትን በመቆጣጠር፤ ለመተንፈስና ለመንቀሳቀስ የሚያስፈልጉንን ዋና ዋና የሰውነት ጡንቻዎች በኃይል እንዲወጠሩ ያደርጋል። ይህም ከባድ የጡንቻ መጠንከርና መኮማተር ያስከትላል።


ታድያ ዝገት ያለው ሚስማር ሲወጋን ለምን ቴታነስ ይይዛል?

በቴታነስ እና በዝገት መካከል ያለው ቁርኝት በማኅበረሰባችን ውስጥ የተለመደ፤ ሆኖም ግን የተሳሳተ ግንዛቤ ነው። እላይ እንደገለጸነው፤ ዝገቱ ራሱ ቴታነስን አያመጣም።


ነገር ግን አንድ ሚስማር ሜዳ ላይ፣ አፈርና ጭቃ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ወድቆ ሲዝግ፤ በዚያው ልክ በባክቴሪያው የመበከል ዕድሉ እጅግ ከፍተኛ ይሆናል። ይህ የዛገ ስለት ቆዳችንን ሲወጋን፣ በቆሻሻው ውስጥ የተሸሸገው ባክቴሪያ በቀጥታ ወደ ሰውነታችን በመግባቱ አደጋው ይበረታል።


ለዚህም ነው ከዛገ ብረት ባሻገር፣ አፈር የነካው ማንኛውም ስለት ሲያቆስለን፣ በዕንጨት/ እሾህ ስንወጋ፣ ወይም በባዶ እግራችን ስንሄድ ድንጋይ ሲያደማን፤ ይህ አደገኛ ባክቴሪያ ወደ ሰውነታችን የመግባት ሰፊ ዕድል አለው።


በህክምናው በእነኝህ ሁሉ ጊዜ ለቴታነስ መታከም ይመከራል።

በእንስሳት ንክሻ የሚፈጠር ቁስልም የቴታነስ መከላከያ ህክምና ሊያስፈልገው ይችላል።


ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

የቴታነስ ባክቴሪያ ወደ ሰውነት ውስጥ በገባበት ቅጽበት በቀጥታ ምልክት ማሳየት አይጀምርም። ለመራባትና መርዙን ለማሰራጨት ጊዜ ይወስዳል። ምልክቶቹ የሚታዩበት ጊዜ፤ እንደ ቁስሉ ጥልቀትና ሁኔታ በጣም ሊለያይ ይችላል። ከተወጉ በኋላ በጥቂት ቀናት ውስጥ አልያም እስከ 3 ሳምንታት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ ቀስ በቀስ ሊታዩ ይችላሉ።


በሽታው የሚያሳያቸው 4 ዋና ዋና ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፦


1️⃣ መንጋጋ መቆለፍ፦ ይህ ቴታነስ በግልጽ ከሚታወቅባቸው ቀዳሚ ምልክቶች አንዱ ነው። መንጋጋ ቆልፍ የሚለውን ስያሜውንም ያገኘው በዚህ ነው። የመንጋጋ ጡንቻዎች ያለምንም ምክንያት በድንገት መኮማተር/መደደር ስለሚጀምሩ፤ አፍን ለመክፈትና ምግብ ለማኘክ በከፍተኛ ሁኔታ መቸገር ይከሰታል። ይህም በሕክምናው ዓለም “lockjaw” ተብሎ ይጠራል።

የጀርባ እና የሰውነት ጡንቻዎች በመኮማተራቸው የሚመጣ የቲታነስ በሽታ ምልክት። በህክምናው ኦፒስቶቶነስ (opisthotonus) ይሰኛል።
የጀርባ እና የሰውነት ጡንቻዎች በመኮማተራቸው የሚመጣ የቲታነስ በሽታ ምልክት። በህክምናው ኦፒስቶቶነስ (opisthotonus) ይሰኛል።

2️⃣ የጡንቻዎች መኮማተር፦ ይህ የጡንቻዎች መኮማተር በመንጋጋ ብቻ ተወስኖ አይቀርም።  ባክቴሪያው ያመነጨው መርዝ በነርቭ ሥርዓት ውስጥ እየተሰራጨ ሲሄድ፤ መላው የሰውነታችን ጡንቻዎች ቁጥጥር ማጣት ይጀምራሉ። መኮማተሩ እየተስፋፋ በመሄድ የአንገትን፣ የጀርባን እና ሌሎች የሰውነት ዋና ዋና ጡንቻዎችን መቆጣጠር ይጀምራል። ይህ መኮማተር ዝም ብሎ የጡንቻ መደደር አይደለም።  የጡንቻ መኮማተሩ እጅግ ኃይለኛ፣ ድንገተኛ እና በሚያሰቃይ ከፍተኛ ሕመም የታጀበ ነው። ከላይ ያለውን ምስል ይመልከቱ።


3️⃣ የመዋጥ ችግር፦ እየባሰም ሲሄድ የጉሮሮ ጡንቻዎች በመኮማተራቸው፤ መዋጥ ያስቸግራል። ለዚህም ታማሚዎች ምራቅ እንኳን መዋጥ ይከብዳቸዋል።


4️⃣ የመተንፈስ ችግር፦ የዓለም ጤና ድርጅት (World Health Organization) እንደሚያስጠነቅቀው፤ በሽታው እየበረታ ሲሄድ፤ ሕይወትን ለማቆየት የሚያስፈልጉት ዋና ዋና የመተንፈሻ ጡንቻዎች ጭምር ሊጎዱ ይችላሉ። ለዚህም የታካሚው የመተንፈስ አቅም በእጅጉ ሊዳከም ይችላል። ይህ በራሱ ለሞት ሊዳርግ ይችላል።


ከዚህም ባለፈ፣ የልብ ምትና የደም ግፊት መዛባትን ጨምሮ ሌሎች መላውን አካል የሚያናጉ ከባድ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ።


ለዚህም ነው ቴታነስ አደገኛ በሽታ የሆነው!

ስለዚህ የቴታነስ ምልክቶች ከታዩ በቤት ውስጥ ለመጠበቅ የሚመች ሕመም አይደለም። አስቸኳይ የሕክምና ግምገማ ያስፈልጋል።

ታድያ መፍትሔው ምንድነው?

ይህንን በሽታ ለመግታት የሚመከረው ዋነኛ መፍትሔ መከላከል ነው። ለዚህም ዋና መሠረት ደግሞ ክትባት ነው።


የቴታነስ ክትባት በጣም ውጤታማ ጥበቃን ይሰጣል። ነገር ግን የሕይወት ዘመን ሙሉ ጥበቃን ለማረጋገጥ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በአጠቃላይ 3 የመጀመሪያ ዶዞች እና 3 የማጠናከሪያ ዶዞች (booster doses) እንዲሰጡ ይመክራል። የመጀመሪያው ክትባት ከ6 ሳምንት ዕድሜ ጀምሮ ሊሰጥ ይችላል ። ቀጣዮቹ ክትባቶች በየ 4 ሳምንት ልዩነት መሰጠት ሲኖርባቸው፤ በተቻለ መጠን  3ኛው ክትባት በ6 ወር ዕድሜ ላይ ተጠናቆ መሰጠት ይኖርበታል። የማጠናከሪያ ክትባቶቹ ደግሞ የሚሰጡት እንደሚከተለው ነው፦


  • 1ኛ ማጠናከሪያ፦ 12–23 ወር

  • 2ኛ ማጠናከሪያ፦ 4–7 ዓመት

  • 3ኛ ማጠናከሪያ ፦ 9–15 ዓመት

በማጠናከሪያ ክትባቶች መካከል፤ በተቻለ መጠን ቢያንስ 4 ዓመት ልዩነት እንዲኖር ይመከራል።



ስለዚህ “አንድ ጊዜ ተከትቤያለሁ” ብሎ መደምደም ብቻ በቂ አይደለም።

እዚህ ጋር ማስተዋል ያለብዎ ነገር፤ ቴታነስ የልጆች ብቻ በሽታ አይደለም። አዋቂዎችንም ሊያጠቃ ስለሚችል፤ ክትባቱ ለአዋቂዎችም ይሰጣል።


ታድያ አዋቂ ሰው መቼ የቴታነስ ክትባት ያስፈልገዋል?

ይህ በአንድ ቀላል ቁጥር ብቻ የሚወሰን አይደለም። የሚወሰነው በቀድሞ በተከተቡት መጠን፣ የመጨረሻው ክትባት መቼ እንደተሰጠ፣ እና የቁስሉ አይነት ላይ ነው።



አዋቂ ሰው በልጅነቱ የቴታነስ ክትባት በተሟላ ሁኔታ ካልወሰደ ወይም የተከተበበትን ታሪክ ካላወቀ፤ የክትባት ታሪኩ በጤና ባለሙያ ተገምግሞ የሚያስፈልጉት የቴታነስ ክትባት ዶዞች እንዲሟሉ ይደረጋል። የተሟላ የመጀመሪያ ተከታታይ ክትባት ያልወሰደ አዋቂ በአጠቃላይ 3 የመጀመሪያ ተከታታይ ክትባት ይሰጠዋል። 1ኛው ክትባት Tdap ሲሆን፤ 2ኛው ቢያንስ ከ4 ሳምንት በኋላ፤ 3ኛው ደግሞ ከ2ኛው ከ6–12 ወር በኋላ ይሰጣል። ከዚያ በኋላ Td ወይም Tdap በየ10 ዓመቱ ለማጠናከር ይሰጣል።


ከዚህም ባለፈ ነፍሰ ጡር እናቶች በቅድመ ወሊድ ክትትል (ANC) ጊዜ፤ ይህንን ክትባት እንዲወስዱ ይደረጋል። ይህም እናቲቱን ከማዳኑም በላይ፤ የሚወለደው ጨቅላ ሕፃን ገና ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ለድንገተኛ የቴታነስ በሽታ (Neonatal Tetanus) እንዳይጋለጥ ጋሻ ሆኖ ይጠብቀዋል።


ስለት ባለው ነገር ከተወጉ በኋላ ማድረግ ያለብዎ!


ስለት ባለው፣ ለአፈር፣ አቧራ እና ቆሻሻ በተጋለጠ ነገር እንደተወጉ ወይም እንደቆሰሉ፤ ወዲያውኑ የሚከተሉትን ወሳኝ እርምጃዎች ይውሰዱ፦


በመጀመሪያ ቁስሉን ያጽዱ። ቁስል ከተፈጠረ በኋላ በተቻለ ፍጥነት በውሃና በሳሙና በመታጠብ፤ በቁስሉ ውስጥ ያለውን ቆሻሻና ባክቴሪያ ጠራርጎ ማስወገድ ይገባል። ከዚያም አቅራቢያዎ ወደሚገኝ የጤና ተቋም በአስቸኳይ በመሄድ ምርመራ ያድርጉ።


ወደ ሕክምና ቦታ ሲሄዱ ከዚህ በፊት ተከትበው የነበረበትን ጊዜ ለጤና ባለሙያው ማማከር ያስፈልጋል። በተሟላ ሁኔታ የተከተበ አዋቂ ሰው ቁስል ከደረሰበት በኋላ ተጨማሪ ክትባት ያስፈልገዋል ወይስ አያስፈልገውም የሚለው በቁስሉ አይነት እና ከመጨረሻው የቴታነስ ክትባት ጀምሮ ባለው ጊዜ ይወሰናል። ይህ በጤና ባለሙያው የሚወሰን ይሆናል።


ለአንዳንድ ጥልቀት ላላቸው እና እጅግ ለተበከሉ ቁስሎች ደግሞ፤ የጤና ባለሙያው ከክትባቱ በተጨማሪ ፈጣን መከላከያ (Tetanus Immune Globulin) ሊሰጥዎ ይችላል። የቁስሉ መበከል ካለ ወይም ሌላ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ከተጠረጠረ ሐኪም አንቲባዮቲክ ሊያዝል ይችላል። ነገር ግን አንቲባዮቲክ መውሰድ ለቴታነስ መከላከያ ምትክ አይደለም።


ስለዚህ ማንኛውም ዓይነት ቁስል ከደረሰብዎ በኋላ፤ “ክትባት አልፈልግም” ወይም “በልጅነቴ ተከትቤ ነበር” ብለው ብቻ በራስዎ አይወስኑ።


የቴታነስ አደጋን የሚወስነው ዝገቱ ሳይሆን፤ የቁስሉ አይነትና መከተብዎ ነው!

ሙሉ በሙሉ ይከተቡ። ቁስልዎን በአግባቡ ይንከባከቡ። ሕይወትዎን በጊዜ ይታደጉ።


Comments


bottom of page