ውሻ ነክሶዎታል? ማወቅ ያለብዎት እውነታዎች!
- Zebeaman Tibebu
- 1 day ago
- 5 min read
Updated: 4 hours ago
ከውሻ ንክሻ በኋላ የሚወስዱት የመጀመሪያ 15 ደቂቃ ሕይወትዎን ሊያድን ይችላል!
"ትንሽ ነክሶኛል... ምንም አይሆንም!" ብለው ይሆን?

አንድ ቀትር ላይ የ9 ዓመት ልጅ ከትምህርት ቤት ወደ ቤቱ እየተመለሰ ነው። በመንገድ ላይ ያለ ውሻ በድንገት ቀርቦ እግሩን ነከሰው። ደሙ ትንሽ ፈሰሰ፤ በቤተሰቡም "ትንሽ ቁስል ነው" ተባለ። ቁስሉ ታጥቦ ተሸፈነ፤ ሕክምና ግን አልተፈለገም።
ቀናት አለፉ። ሳምንታትም አለፉ። ልጁ ጤናማ ይመስል ነበር።
ከዚያ በኋላ ግን ትኩሳት ጀመረ። በተነከሰበት ቦታ ህመምና መኮማተር ተሰማው። በቀጣዮቹ ቀናት ውሃ ለመጠጣት መፍራት፣ መናደድ፣ ግራ መጋባት እና የመተንፈስ ችግር ተከተሉ።
ይህን ጊዜ ሐኪም ቤት ቢሄድም ፤ በዚህ ደረጃ የተጀመረ ሕክምና ሕይወቱን ማዳን አልቻለም።
ይህ ታሪክ የአንድ ሰው ብቻ አይደለም። በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከውሻ ንክሻ በኋላ በሚከሰት እብድ ውሻ (Rabies)በሽታ ሕይወታቸውን ያጣሉ። አብዛኞቹ ግን በጊዜው ተገቢውን ሕክምና ቢያገኙ ሊድኑ ይችሉ ነበር።
ይህም ሬቢስን ከሌሎች በሽታዎች የሚለየው ትልቁ እውነታ ነው። ምልክቶቹ ከመጀመራቸው በፊት ሙሉ በሙሉ በሽታውን መከላከል የሚቻል ቢሆንም ፤ ምልክቶቹ ከታዩ በኋላ ግን በአብዛኛው ጊዜ ለሞት የሚያበቃ በሽታ ነው።
ሬቢስ (Rabies) ምንድን ነው?

ሬቢስ በሬቢስ ቫይረስ (Rabies virus) የሚከሰት እጅግ አደገኛ የቫይረስ በሽታ ነው። ቫይረሱ ከተያዘ እንስሳ ወደ ሰው በብዛት በንክሻ ይተላለፋል። ከሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ ወዲያውኑ ከፍተኛ ህመም አያስከትልም። በመጀመሪያ በጡንቻዎች አካባቢ ይቆያል፤ ከዚያም በነርቮች በኩል በቀስታ ወደ አንጎል ይጓዛል።
ቫይረሱ አንጎልን ከደረሰ በኋላ የአንጎልና የነርቭ ሥርዓት ከባድ እብጠት (encephalitis) ያስከትላል። በዚህ ደረጃ በሽታው በጣም ከባድ ይሆናል።
በዓለም ምን ያህል ችግር ነው?

የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እንደሚያሳየው፤ በየዓመቱ ወደ 59,000 የሚጠጉ ሰዎች በራቢስ ይሞታሉ። ከእነዚህ ሞቶች 95% በእስያና በአፍሪካ ይከሰታሉ። ወደ 40% የሚሆኑት ተጎጂዎች ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው። አብዛኞቹ የሬቢስ በሽታዎች 99% የሚሆኑት በውሻ ንክሻ የሚተላለፉ ናቸው።
ይህም አንድ ነገር ያመላክታል!
ሬቢስ ዛሬም የሕዝብ ጤና ችግር ሆኖ ቀጥሏል።
ኢትዮጵያም ሬቢስ አሁንም በተደጋጋሚ ከሚታይባቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል ትገኛለች። ለምን?
ያልተከተቡ ውሾች መብዛት
ከቤት ውጭ የሚኖሩ ውሾች መበራከት
የተነከሰ ሰው ብዙውን ጊዜ ሕክምናን በፍጥነት አለመፈለጉ
በሽታውን ለማከም ባህላዊ ሕክምና ብቻን መመርኮዙ
የሬቢስ ክትባት አገልግሎት አገልግሎት በሁሉም ቦታ በቀላሉ አለመገኘቱ ፤ በሽታው እንዲቀጥል ከሚያደርጉ ዋና ምክንያቶች መካከል ይገኛሉ።
ስለዚህ ማንኛውም የውሻ ንክሻ "ቀላል ቁስል" ብሎ መተው ትክክል አይደለም።
ሬቢስ እንዴት ይተላለፋል?

የሬቢስ ቫይረስ በበሽታው የተያዘ እንስሳ ምራቅ (Saliva) ውስጥ በብዛት ይገኛል። ለዚህም ወደ ሰው በሚከተሉት መንገዶች ይተላለፋል።
በንክሻ
ይህ ዋናውና በጣም ብዙ ጊዜ የሚከሰተው መንገድ ነው። በሽታው የተያዘ ውሻ ሰውን ሲነክስ በምራቁ ውስጥ ያለው ቫይረስ ወደ ቁስሉ ይገባል። በሽታውንም ያስከትላል።
በሽታው ያለበት እንሰሳ ምራቅ ቁስል ላይ አልያም አፍ፣ አይን፣ ወይም የአፍንጫ ውስጥ ሲያርፍ
በሽታው ያለበት እንሰሳ ክፍት ቁስልን ከላሰ፣ አልያም ምራ አይን፣ አፍ ወይም አፍንጫ ቢደርስ ኢንፌክሽን ሊፈጠር ይችላል።
መቧጨር
በምራቅ የተበከሉ ጥፍሮች ቆዳን ካቆሰሉ ቫይረሱ ሊገባ ይችላል።
ውሻ በመንካት ወይም ከውሻ አጠገብ በመሆን ይተላለፋል?
ይህ ስህተት ነው!
ሬቢስ ውሻን በመንካት፣ አንድ ክፍል ውስጥ ከውሻ ጋር መኖር፣ ጤናማ ቆዳ ላይ ምራቅ በመንካት አይተላለፍም።
ሬቢስን የሚያስተላልፉ እንስሳት

በአገራችን በሰዎች ላይ ለሚያጋጥሙ የሬቢስ ኢንፌክሽኖች አንደኛ ተጠያቂ ውሻ ነው። ሆኖም ግን ይህ በሽታ በውሻ ብቻ አይመጣም/አይተላለፍም። ሌሎች አጥቢ እንስሳትም ቫይረሱን ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ለምሳሌ፦ ድመት፣ ቀበሮ፣ ተኩላ፣ የለሊት ወፍ፣ እና ሌሎች የዱር አጥቢ እንስሳት ሊያስተላልፉ ይችላሉ።
ያስተውሉ! አጥቢ ያልሆኑ እንሰሳት ሬቢስን አያስተላልፉም።
ከንክሻ በኋላ ቫይረሱ ምን ያመጣል?

ይህ ሬቢስን ከሌሎች ቫይረሶች የሚለየው አስገራሚ ባህሪ ነው። ብዙ ቫይረሶች በቀጥታ ወደ ደም ቢገቡም፤ ሬቢስ ግን በብዛት በነርቭ መስመሮችን ተከትሎ ወደ አንጎል ይጓዛል። አንጎል ከደረሰ በኋላም ወደ ምራቅ እጢዎች ይሄዳል። እዚያም በብዛት ተከማችቶ ይቆያል። በንክሻ ጊዜ ወደ ሌላ ሰው ወይም እንስሳ ሊተላለፍ ይችላል።
ከንክሻ በኋላ በሽታው ወዲያውኑ አይታይም።
በአብዛኛው ሰዎች ላይ ምልክቶቹ ከ1 እስከ 3 ወራት በኋላ ይጀምራሉ። ነገር ግን ይህ ጊዜ በጣም ሊለያይ ይችላል፤ አንዳንድ ሰዎች ላይ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሲታይ፣ በሌሎች ደግሞ ከአንድ ዓመት በላይ ሊዘገይ ይችላል።
በተለይ ፊት፣ አንገት ወይም ራስ ላይ የሚደርሱ ንክሻዎች ቫይረሱ ወደ አንጎል አጭር መንገድ ስለሚያገኝ ከፍተኛ አደጋ ይኖራቸዋል። ለዚህም ተጋላጭነቱ እና አደጋው በህጻናት ላይ ያይላል።
ሬቢስ ሲጀምር የሚታዩ የመጀመሪያ ምልክቶች

ብዙ ጊዜ እንደ ጉንፋን የሚመስሉ ምልክቶች ይጀምራሉ።
እነዚህም፦
ትኩሳት
ድካም
ራስ ምታት
የምግብ ፍላጎት መቀነስ
በተነከሰበት ቦታ ህመም፣ ማሳከክ፣ መኮማተር ወይም መቃጠል
ይህ የመጨረሻው ምልክት ሬቢስን ለመጠርጠር ጠቃሚ ፍንጭ ሊሆን ይችላል።
በኋላ የሚከሰቱ ከባድ ምልክቶች

ቫይረሱ አንጎልን ሲያጠቃ የነርቭ ሥርዓቱ እየተበላሸ ይሄዳል።ከዚያም የሚከተሉት ከባድ ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ፦
ውሃን በማየት ወይም ለመጠጣት ሲሞክሩ የሚከሰት ከባድ የጉሮሮ ጡንቻ መጨማደድ (Hydrophobia)
ነፋስ ሲመታ የሚከሰት ከባድ የጡንቻ መጨማደድ (Aerophobia)
መረበሽ
የባህሪ ለውጥ
ግራ መጋባት
ጠበኝነት
ቅዠት (Hallucinations)
የጡንቻ መጨማደድ
ኮማ
የሬቢስ ቫይረስ አንጎልንና የነርቭ ሥርዓቱን በከፍተኛ ሁኔታ ካጠቃ በኋላ ለማስቆም የተረጋገጠ ውጤታማ ሕክምና የለም። ስለዚህ የሬቢስ ሕክምና ዋናው ግብ "ከምልክት በፊት መከላከል" ፤ እንጂ "ከታመመ በኋላ ማከም" አይደለም። ይህንን እውነታ እጅግ አስፈላጊ ነው።ሁሉም ታካሚዎች ውሃን ይፈራሉ?
አይ! ይህ የሚያጋጥመው አደገኛ በሆነው የሬቢስ አይነት (Furious Rabies) ነው። ይህ በብዛት የሚታየው አይነት ሲሆን የውሃ ፍርሃት፣ የነፋስ ፍርሃት፣ መረበሽ እና የባህሪ ለውጦች ይታያሉ።
ሆኖም ግን በሌላኛው የሬቢስ አይነት(Paralytic Rabies) ደግሞ ፤ በዋነኝነት የጡንቻ ድካምና ሽባነት ቀስ በቀስ እየተባባሰ ይመጣል። ስለዚህ ከሌሎች የነርቭ በሽታዎች ጋር ሊምታታ ይችላል።
ለሕይወትዎ ወሳኝ የሆኑ 15 ደቂቃዎች
ብዙ ሰዎች አንድ ስህተት ይሰራሉ። "ውሻው የቤት ውሻ ነው፤ ምንም አይሆንም..." ብለው ያስባሉ።

ውሻው የቤት ውሻ መሆኑ፤ በደንብ የሚያውቁት መሆኑ፤ ወይም ጸጥ ያለ መምሰሉ ብቻ ሬቢስ እንደሌለበት አያረጋግጥም።
እንዲሁም ንክሻው ትንሽ መሆኑ ወይም ደም ብዙ አለመፍሰሱ አደጋው ትንሽ ነው ማለት አይደለም። የሬቢስ ቫይረስ በዓይን አይታይም። በቁስሉ መጠንም አይመዘንም። ለዚህም እነኝህን በአፋጣኝ ያድርጉ
① ቁስሉን ወዲያውኑ ያጠቡ
ቁስሉን ቢያንስ ለ15 ደቂቃ በብዙ ውሃና በሳሙና በደንብ ያጠቡ። ይህ ቀላል የሚመስለው እርምጃ በቁስሉ ውስጥ ያለውን ቫይረስ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስ ይችላል።
② የባክቴሪያ ማጥፊያ ያለው የንጽህና መጠበቂያ(አንቲሴፕቲክ) ካለ ይጠቀሙ
እንደ አዮዲን አልያም አልኮል አይነት ኬሚካሎች ካሉ ቁስሉን ካጸዱ በኋላ ቁስሉ ላይ ያፍስሱበት!
③ ቁስሉን አይሸፍኑ
የጤና ባለሙያ ሳያየው ቁስሉን በጥብቅ መሸፈን አይመከርም።
④ ወዲያውኑ ወደ ጤና ተቋም ይሂዱ
"እስቲ እንየው " ብለው ቀናትን አይጠብቁ። የሬቢስ መከላከያ ሕክምና በተቻለ ፍጥነት መጀመር አለበት።
በፍጹም የሚከተሉትን እንዳያደርጉ!
❌ ቁስሉ ላይ ቅጠል ወይም ባህላዊ መድኃኒት መቀባት
❌ ቁስሉን በአመድ፣ ቅቤ፣ ቅጠል ወይም ኬሚካል መሸፈን
❌ ቁስሉን ማቃጠል
❌ ሕክምናን በማዘግየት ውሻውን ብቻ መጠበቅ
እነዚህ ሁሉ ሕይወትን ሊያሳጡ የሚችሉ ስህተቶች ናቸው።
የሬቢስ መከላከያ ሕክምና ምንድን ነው?

ይህ ለሬቢስ ለተጋለጠ ሰው ፤ በሽታው እንዳይከሰት የሚሰጥ የመከላከያ ሕክምና ነው። ይህ ህክምና የሚከተሉትን ያካትታል።
ቁስሉን በትክክል ማጠብ
የሬቢስ ክትባት
የሬቢስ ክትባት ቫይረሱ ወደ አንጎል ከመድረሱ በፊት ሰውነት በቂ መከላከያ እንዲፈጥር ይረዳል። የተጋላጭነት አደጋ ካለ፤ ክትባቱ በተቻለ ፍጥነት መጀመር አለበት። በአሁኑ ጊዜ የሚጠቀሙት የሬቢስ ክትባቶች ደህንነታቸውና ውጤታማነታቸው በጥናቶች የተረጋገጠ ነው።
የሬቢስ መቃወሚያ መድሀኔት (Rabies Immunoglobulin (RIG)) እንደ አስፈላጊነቱ
ይህ ከክትባቱ የተለየ መድኃኒት ነው። ክትባቱ ሰውነት ፀረ-እንግዳ አካላት (Antibodies) እንዲያመነጭ ብዙ ቀናት ይፈልጋል።
ይህ መድሀኒት ግን እነዚህን ፀረ-እንግዳ አካላት ወዲያውኑ ያቀርባል። በተለይ ከባድ ተጋላጭነት ባለባቸው ሰዎች ውስጥ ክትባቱ እስኪሰራ ድረስ ጊዜያዊ ጥበቃ ይሰጣል።
የቴታነስ መከላከያ እና ሌሎች የቁስል ሕክምናዎች እንደ አመላካችነቱ
ውሻው ጤናማ ቢመስልስ?

የአለም ጤና ድርጅት እና የእንስሳት ጤና መመሪያዎች በሚያሳዩት መሰረት፤ ንክሻውን የፈጸመው ውሻ ጤናማ ከሆነ፣ ሊገኝና ሊከታተል የሚችል ከሆነ፣ ለ10 ቀናት በባለሙያ ምክር መሰረት ሊከታተል ይችላል።
እነዚህ 10 ቀናት ውስጥ፦ ውሻው ጤናማ ቢቆይ፣ ወይም ቢታመም፣ ወይም ቢሞት የተጎጂውን የሕክምና ውሳኔ ለመወሰን ይረዳል።
ነገር ግን ይህ ማለት "ክትባት ሳይጀመር 10 ቀናት ይጠብቁ" ማለት አይደለም።
ሬቢስን እንዴት መከላከል እንችላለን?

ሬቢስ ሊከሰት ቢችልም በትክክለኛ መከላከያ በአብዛኛው ሙሉ በሙሉ ሊከለከል የሚችል በሽታ ነው።
የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች ያድርጉ፦
የቤት ውሾችንና ድመቶችን በየጊዜው በራቢስ ክትባት ማስከተብ።
የማይታወቁ ውሾችን አለመንካት።
ሕፃናትን ከውሾች ጋር ሲጫወቱ መቆጣጠር።
ማንኛውም ንክሻ ከተፈጠረ ወዲያውኑ ቁስሉን በሳሙናና በብዙ ውሃ ማጠብ።
ንክሻ ካጋጠመ ያለምንም መዘግየት ወደ ጤና ተቋም መሄድ።
ያስተውሉ!
ራቢስ ከዓለም ላይ በጣም አስፈሪ ከሆኑ የቫይረስ በሽታዎች አንዱ ቢሆንም፣ በጊዜው ትክክለኛ እርምጃ ከተወሰደ ግን በሙሉ ሊከለከል ይችላል።
ለዚህም የውሻ ንክሻን በፍጹም ቀላል አይበሉ። ቁስሉን ወዲያውኑ ይጠቡ። በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም ይሂዱ። የጤና ባለሙያው የሚመክረውን ሕክምና በሙሉ ያጠናቅቁ።
አንድ ፈጣን እርምጃ ሕይወትን ሊያድን ይችላል።




Comments