top of page

የቢጫ ወባ ክትባት፡ ሳልከተብ ካርዱ ቢኖረኝስ?

ቦታው የቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ጣቢያ ነው።የሰዎች ግርግር፣ የሻንጣዎች ድምፅ፣ የሀገር ቤት ናፍቆትና ፣ የጉዞ ጉጉት እንዲሁም ጭንቀት አየሩን ሞልቶታል። እርስዎ በዚህ መሀል ቆመዋል። ፓስፖርትዎን በእጅዎ ጨብጠዋል። የፓስፖርትዎ ገጾች ላይ አዲስ ቪዛ ታትሞ ይታያል። ከፓስፖርትዎ ጀርባ ደግሞ በጉጉት የሚጠብቁትን ያንን ዓለም አቀፍ ጉዞ እውን የሚያደርገውን፣ ያለ እርሱ መንቀሳቀስ የማይታሰበውን ቢጫ ወረቀት(የቢጫ ወባ (Yellow Fever) የክትባት ሰርተፍኬት) አጣምረው ይዘዋል።


የቢጫ ወባ ሰርተፍኬት ሰነዱ ሙሉ ነው። ስምዎ፣ የፓስፖርት ቁጥርዎ እና ህጋዊ የሚመስሉ ደማቅ ማህተሞች አርፈውበታል።

ነገር ግን እርስዎ ብቻ የሚያውቁት አንድ ትልቅ ሚስጥር አለ። የክትባት መርፌው ፈጽሞ ክንድዎን አልነካውም።

ሆኖም ግን አስፈላጊውን ሰነድ በመያዝዎ የድንበር ፍተሻ መኮንኑ ፤ እንደሚያሳልፍዎት እርግጠኛ ነዎት!


በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ዓለም አቀፍ ተጓዦች መርፌ ሳይወጉ፤ የኢሚግሬሽንን ፍተሻን ለማለፍ ብቻ ሀሰተኛ የየሎ ፌቨር (የቢጫ ወባ) ክትባት ሰርተፍኬት እንደሚገዙ የአደባባይ ሚስጥር ነው።


ይሁን እንጂ አንድ ወረቀት የድንበር ፍተሻ መኮንን ሊያታልል ቢችልም፤ ቫይረሱን ግን ሊሸውድ አይችልም።የሀሰት ካርድ ይዘው ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ወይም በሐሩራማው የደቡብ አሜሪካ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች ውስጥ ሲረግጡ፣ የሚጋፈጡት የሚጠብቅዎትን የኢሚግሬሽን መኮንን ሳይሆን፤ በትንኝ ንክሻ አማካኝነት ወደ ደምዎ ውስጥ ሰርጎ ለመግባት ዝግጁ የሆነውን ገዳይ ቫይረስ ነው። ትክክለኛውን የሕክምና ጥበቃ ሳይዙ ይህንን ካርድ መያዝ፤ በራስዎ የሞት ፍርድ እንደመፍረድ ይቆጠራል።


በዛሬው ጽሁፋችን ስለ የሎ ፌቨር በሽታ ምንነት፣ የሕክምና ጥበቃው እንዴት እንደሚሰራ እና የሀሰተኛ ካርድ አደገኝነት እናነሳለን።


የየሎ ፌቨር በሽታ ምንድን ነው? አደጋዎቹስ?

የየሎ ፌቨር በበከሉ የኤደስ (Aedes) እና ሄማጎገስ (Haemagogus) በሚሰኙ የትንኝ ዝርያዎች አማካኝነት የሚተላለፍ ከባድ የቫይረስ በሽታ ነው። ይህ እንደ ኢቦላና ማርበርግ ቫይረሶች ከባድ የደም መፍሰስ (hemorrhagic fever) የሚያመጣ የቫይረስ ነው።


በሽታው በሰውነት ውስጥ የሚያስከትለው ጉዳት እጅግ በጣም አስከፊ ሲሆን፤ ሂደቱም የሚከተሉትን ደረጃዎች አልፎ ይጓዛል፦


  • የመጀመሪያው ደረጃ : በድንገት ምልክቶቹ ይታያሉ። በድንገት በከፍተኛ ትኩሳት፣ በከባድ የጡንቻና የጀርባ ህመም፣ ፅኑ ራስ ምታት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት እና ማቅለሽለሽ ይጀምራሉ። 

  • አደገኛው የሽግግር ደረጃ : ምልክቶቹ ይጠፋሉ፤ ታካሚዎች እፎይታን ያገኛሉ። ብዙዎች ሕመምተኞች በቋሚነት ያገግማሉ። ታድያ ይህ 15 በመቶ ለሚሆኑት  ታካሚዎች የሚያዘናጋ ደረጃ ነው።ይህ ደረጃ ከ24 እስከ 48 ሰዓታት ብቻ የሚቆይ ሲሆን፤ ጥቂት ታካሚዎች ወደ ቀጣዩ ከባድ ደረጃ ይሸጋገራሉ።

  • ከባድና ገዳይ ችግሮች :  እዚህ ደረጃ ላይ ቫይረሱ ወሳኝ የሰውነት ክፍሎችን በፍጥነት ያጠቃል፤ ያፈርሳል። ሕመምተኞች በሰውነታቸው ውስጥ የደም መፍሰስ ያጋጥማቸዋል። ጥቁር ደም ያስታውካሉ። ኩላሊታቸው ሙሉ በሙሉ ሥራ ያቆማል። ጉበት ጉዳት ስለሚደርስበት ፤ አይን እና ቆዳ ቢጫ መሆን ( jaundice)ይጀምራል ። ቢጫ ወባ የሚለውን ስያሜውንም ያገኘው፤ በዚህ ባህሪው ነው። 

  • የመጨረሻው አስከፊ አደጋ: የሕክምና መጻሕፍት እንደሚያረጋግጡት፤ ወደዚህ ደረጃ ከሚገቡት ሕመምተኞች መካከል እስከ ከፊሉ ከ7 እስከ 10 ቀናት ባለው አጭር ጊዜ ውስጥ ሕይወታቸው ያልፋል።

ለቢጫ ወባ በሽታ ምንም ዓይነት የቫይረስ ማጥፊያ መድኃኒት (Antiviral) የሌለው ሲሆን፤ በሽታው አንዴ ካጋጠመ የሚደረገው ምልክቶቹን ለመቀነስ የሚደረግ የድጋፍ ሕክምና ብቻ ነው።  ያለው ብቸኛ አማራጩ ክትባት ነው።


ይህንን እውነታ ስንረዳ፤ያንን ወረቀት በጥቁር ገበያ መግዛት የድንበር ፍተሻን ለማለፍ ሳይሆን፤ ለሞት ቀጠሮ ለመያዝ መሆኑ ቁልጭ ብሎ ይታየናል።


ክትባቱ እንዴት ይሠራል?

እውነተኛው የየሎ ፌቨር ክትባት (በተለይም 17D የተባለው) በሕክምና ታሪክ ውስጥ ከተሰሩት ሁሉ እጅግ በጣም ስኬታማ እና ከፍተኛ ውጤት ያለው ክትባት ነው።ይህ ክትባት በሽታ ማምጣት የማይችል፤ ነገር ግን የሰውነትን የመከላከያ ኃይል ማንቃት የሚችል፤ እጅግ የደከመ ቫይረስን በውስጡ ይዟል። የተዳከመው ቫይረስ በሰውነታችን የመከላከያ ሥርዓት በቀላሉ የሚደመሰስ ቢሆንም፤ የሰውነታችንን ነጭ የደም ህዋሳት ለትክክለኛው ቫይረስ ቀድመው እንዲዘጋጁ እና ጠላታቸውን ለይተው እንዲያውቁ ዕድል ይሰጣቸዋል።


 መደበኛ የክሊኒካዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ክትባቱ ከ95% እስከ 99% ከቢጫ ወባ በሽታ ይከላከላል። ይህ ማለት ክትባቱን በወሰዱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ፤ የሰውነትዎ በሽታ የመከላከል ሥርዓት ቫይረሱን ሙሉ በሙሉ ሊያጠፉ የሚችሉ መርዞችን (antibodies) ያዘጋጃል። ለበሽታው ብቁ ዝግጅት ያደርጋል።

ክትባቱን አንዴ ከተወጉ ለዕድሜ ልክ ይሆናል።  ይህንን ክትባት በተደጋጋሚ መውሰድ አያስፈልግዎትም። የዓለም ጤና ድርጅት ከ12 ዓመታት በፊት በ2014፤ ለዚህ ክትባት በየ10 ዓመቱ ይወሰድ የነበረውን የማጠናከሪያ መርፌ(booster dose) አስቀርቷል። አንድ መርፌ ዕድሜ ልክዎን እንደሚጠበቅም አረጋግጧል።


ከጉዞ ስንት ቀናት በፊት መከተብ አለብዎት?

ለጉዞዎ በሚዘጋጁበት ጊዜ ቀናትን መቁጠር በጣም አስፈላጊ ነው። ከበረራዎ አንድ ወይም ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ክትባቱን መውሰድ በሕግ ፊትም ሆነ በሕክምናው ዓለም ምንም ዓይነት ዋጋ የለውም። በድንበር ፍተሻዎች ላይ እንግልት እንዳይገጥምዎትና ሰውነትዎም አስተማማኝ ከላላ እንዲያገኝ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ያስቀመጠውን የ10 ቀናት ጥብቅ ሕግ ማክበር ይኖርብዎታል።


ይህ የጊዜ ገደብ ዝም ብሎ የተቀመጠ ሳይሆን የራሱ የሆነ ጥልቅ ባዮሎጂያዊ ምክንያት አለው። የቢጫ ወባ ክትባት ወደ ሰውነትዎ ከገባ በኋላ፤ በሽታ የመከላከል ሥርዓትዎ ቫይረሱን ተዋግቶ ሙሉ በሙሉ ሊያጠፉ የሚችሉ በቂ መቃወሚያ መርዝ (Antibodies) ለማምረት በትንሹ 10 ቀናት ይፈጅበታል።


ከተከተቡ በኋላ ያሉት የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ቀናት ውስጥ ሰውነትዎ ለቫይረሱ የተጋለጠ ነው።

በዚህ ሳይንሳዊ ምክንያት የተነሳ፣ የቢጫ ወባ ክትባት ደብተርዎ በሕግ ፊት ፀንቶ መሥራት የሚጀምረውና ተቀባይነት የሚያገኘው መርፌው ከተወጉበት ዕለት ጀምሮ በትክክል አሥር ቀናት ሲሞላው ብቻ ነው። ከእነዚህ አሥር ቀናት በፊት ወደ ባዕድ አገር ድንበር ከደረሱ፤ ሰርተፍኬትዎ ውድቅ ተደርጎ ወደ መጡበት ሊመለሱ ወይም ለይቶ ማቆያ ማዕከል (quarantine) ውስጥ ለብቻዎ እንዲቆዩ ይችላሉ። ስለዚህ ቢያንስ ከጉዞዎ ሁለት ሳምንት በፊት መከተብን የዕቅድዎ መጀመሪያ ማድረግ አለብዎት።


የክትባቱ የጎንዮሽ ጉዳትስ?

ብዙ ሰዎች ክትባቱን ለመውሰድ ወደ ኋላ የሚሉበት ዋነኛው ምክንያት የጎንዮሽ ጉዳቱን በመፍራት ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን የዓለም አቀፍ የሕክምና መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ የቢጫ ወባ ክትባት የጎንዮሽ ጉዳቶች እጅግ በጣም ቀላል እና በጥቂት ቀናት ውስጥ በራሳቸው ጊዜ የሚጠፉ ናቸው። የሚጠበቁ የጎንዮሽ ጉዳቶች የሚከተሉት ናቸው ፦

  • ቀላል ምልክቶች፦ ክትባቱን ከወሰዱ በኋላ መርፌው በተወጋበት ቦታ ላይ መጠነኛ ማበጥ፣ መቅላት እና ህመም ሊሰማዎት ይችላል። አልፎ አልፎም መለስተኛ ራስ ምታት፣ መጠነኛ ትኩሳት ወይም የጡንቻ ሕመም ሊከሰት ይችላል። እነዚህ ምልክቶች በሽታ ሳይሆኑ፤ ሰውነትዎ ለክትባቱ ምላሽ እየሰጠ እና አስተማማኝ የመከላከያ ስርአት እየገነባ መሆኑን የሚያሳዩ ተፈጥሯዊና ጤናማ ምልክቶች ናቸው።

  • ከባድ የጎንዮሽ ጉዳቶች፦ እጅግ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ሲሆን፤ በግምት ከ1 ሚሊዮን ሰዎች ውስጥ 4–8 ሰዎች ላይ ብቻ ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ክትባቱ የሚሰጠው የዕድሜ ልክ ጥበቃም ከበሽታው አስከፊ ሞት አንጻር ሲለካ ጥቅሙ እጅግ የላቀ ነው።


ክትባቱን መውሰድ የማይችሉ እነማን ናቸው?

አንዳንድ ሰዎች በህክምና ምክንያት ክትባቱን መውሰድ የለባቸውም። እነዚህም፦

  • ዕድሜያቸው ከ9 ወር በታች የሆኑ ህጻናት፣

  • ነፍሰ ጡር ሴቶች፣

  • ለእንቁላል ፕሮቲን ጽኑ አለርጂ ያለባቸው እና

  • የሰውነት መከላከል አቅማቸው በከፍተኛ ደረጃ የደከመ ታካሚዎች ናቸው። 


እነዚህ ወገኖች የሀሰት ካርድ መግዛት አያስፈልጋቸውም። ምክንያቱም በአለም አቀፍ ህግ መሰረት ከህክምና ተቋማት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት (Medical Waiver/Exemption Certificate) ማግኘት ይችላሉ። ይህ ደብተር በትክክለኛ ማህተም ተረጋግጦ ሲቀርብ በአብዛኛዎቹ የዓለም አገራት የድንበር ፍተሻዎች ላይ እንደ ቢጫው ካርድ ሁሉ ሙሉ ሕጋዊ ተቀባይነት አለው። ሆኖም ግን የሀገር ውስጥ ደንቦች ሊለያዩ ስለሚችሉ በቅድሚያ ማረጋገጥ ይመከራል።


የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ አዲስ መመሪያ

የዚህ በሽታ ስጋት እና አደገኝነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የተረዳው የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር፤ በዚህ ዙሪያ ትልቅ ውሳኔ ላይ ደርሷል። በሽታው በሀገሪቱ ውስጥ በድንገት ተከስቶ ማኅበረሰቡን እንዳያናጋ እና የዜጎችን ሕይወት እንዳይቀጥፍ አስቀድሞ ለመከላከል፤ የቢጫ ወባ ክትባት በሕፃናት መደበኛ የክትባት መርሃ ግብር (Routine Immunization Schedule) ውስጥ እንዲካተት ከ አለም አቀፍ ክትባት አስተባባሪ ኮሚቴ (ICC) ጋር በመሆን ወስኗል። ሆኖም ግን ክትባቱ ገና በመላው ሀገሪቱ በመደበኛ የክትባት ፕሮግራም ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አልሆነም።


ምርጡ ውሳኔ


የሕክምና ሰነድን ማጭበርበር በክሊኒክ ውስጥ የሚባክን አንድ ሰዓት ሊያድንዎት ይችላል። ነገር ግን ለሞት ሊዳርግ የሚችል የደም መፍሰስ በሽታ ተጋላጭ ያደርግዎታል። በተጨማሪም የሀሰት ካርድ መያዝዎ ድንበር ቢታወቅ አልያም የ10 ቀኑ ህግ ሳይሞላ ቢጓዙ፤ በርካታ ሀገራት ተጓዦችን ለ6 ቀናት በራሳቸው ወጪ ለይቶ ማቆያ (Quarantine) ውስጥ የማቆየት ወይም ወደ መጡበት ሀገር የመመለስ እርምጃ ይወስዳሉ። 

ለዚህም ምርጡ ውሳኔ እውነተኛውን ክትባት ወዲያውኑ መውሰድ ነው።

ተጓዦች አራት ኪሎ በሚገኘው በምግብና መድሐኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ሄደው መውሰድ ይችላሉ። ይህን ክትባት እንዲሰጥ በሕጋዊ መንገድ የተፈቀደለትን የሕክምና ተቋም መሄድዎ ፤ ለእርስዎ መንታ ጥቅም አለው።

  1. ሙሉ በሙሉ ሕጋዊ የሆነ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕድሜ ልክ የሚያገለግል እውነተኛ ቢጫ ካርድ ያገኛሉ።

  2. በመከተብ በደምዎ ውስጥ ጠንካራ እና ቋሚ የሰውነት መከላከያ አቅም ይገነባሉ። ጉዞዎ በቢጫ ወባ በሽታ እንደማይሰናከል ዋስትና ያገኛሉ።


ሀሰተኛ ካርድ ከበሽታው አይጠብቅዎትም። ጤናዎን ይጠብቁ!
ከበረራዎ ቢያንስ 10 ቀናት ቀደም ብለው ያቅዱ! ክትባቱን በአግባቡ ይውሰዱ!





1 Comment


Guest
41 minutes ago

Great info thanks!

Like
bottom of page