ልጅዎን ያመመው ቀላል ሕመም ነው ወይስ ሌላ?
- Zebeaman Tibebu
- 3 minutes ago
- 5 min read
ትላንት በደስታ ሲቦርቅ፤ ሳቁ ቤቱን ሲሞላው የዋለ ልጅ፤ ዛሬ ጠዋት ግን ከአልጋው መነሳት አቅቶት ይደፋል። ከሰዓት በኋላ ደረቅ ሳል ይጀምረዋል። ምሽት ላይ ደግሞ ተቅማጥ ይጨመርበታል።
ይህ ትዕይንት በብዙ ቤቶች የተለመደ ነው። እንዲህ ያሉ ድንገተኛ መታመሞች ሲከሰቱ፤ ቤተሰብ "ምን ይሻላል?" ብሎ መጨነቁ አይቀሬ ነው። በዚያው ልክ ደግሞ ምክሮች ከያሉበት ይዘንባሉ፦
“ፈሳሽ አጠጡትና ይተኛው፤ ይለቀዋል”
“ብርድ እንዳይገባው ደርብቡለት። ሙቅ ነገር ስጡት።”
“ትንሽ ታሞ ነው። ነገ ይነሳል...”

በአብዛኛው ሁኔታዎች ይህ የቤት ውስጥ ጥበብ ይሰራል። ህፃኑ አገግሞ ወደ ጨዋታው ይመለሳል፤ ህይወትም በለመደችው መስመር ትቀጥላለች።
ነገር ግን... ነገሮች ሁልጊዜ እንዲህ ቀላል አይሆኑም።
አንዳንዴ ያ ቀላል የመሰለው ሳል ሳይታወቅ ወደ ፈጣንና አጣዳፊ አተነፋፈስ ይቀየራል። ያ ተራ ተቅማጥ ሰውነትን የሚያፈዝ አደገኛ የፈሳሽ እጥረት (Dehydration) ይወልዳል። "ትንሽ ትኩሳት ነው" ያልነው ጉዳይ ህፃኑን ራሱን እስከማሳት ሊያደርሰው ይችላል።
በእነዚህ ወሳኝ ሰከንዶች ውስጥ በልበ ሙሉነት የምንሰጣቸው የቤት ውስጥ ምክሮች ብቻቸውን በቂ አይደሉም። እንዲያውም አንዳንዴ በህይወትና በሞት መካከል ያለውን ጠባብ መስመር ሊያጠፉት ይችላሉ።
ታዲያ ልዩነቱን እንዴት እንወቀው?
ይህ ጥያቄ ስለ ፍርሃት ሳይሆን ስለ ንቃት ነው። "አልጋው ላይ ይዋል" በሚባለው ህመም እና "አሁኑኑ ሆስፒታል!" በሚያስባለው አደገኛ ምልክት መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ ያስፈልጋል። የልጅዎ የነገ ሳቅ የሚመሰረተው ይህንን በመለየትዎ ላይ ተመስርቶ ነው።
የልጅነት ሕመሞች ተፈጥሮአዊነት

የልጅነት ሕመም እንግዳ ነገር አይደለም፤ እንዲያውም የማደግ አንዱ አካል ነው። የሕክምና መጽሐፍት እንደሚነግሩን፤ ትናንሽ ልጆች በዓመት ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት በመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን ሊያጠቁ ይችላሉ። ይህ ሂደት በራሱ አንድ ትልቅ ትምህርት ቤት ነው፤ የበሽታ መከላከል አቅማቸው ገና በማደግ ላይ ስለሆነ፤ ሰውነታቸው አዳዲስ ረቂቅ ተህዋሲያንን መለየትና መቋቋም እየተለማመደበት ያለ መንገድ ነው።
ልጅዎ ከአካባቢው ጋር በተገናኘ ቁጥር የተለያዩ ምልክቶችን ያሳያል። እያንዳንዱ ትኩሳት፤ እያንዳንዱ ሳል፤ እና እያንዳንዱ ጉንፋን የሰውነቱ የመከላከያ ሰራዊት እየተገነባ መሆኑን የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው። ስለዚህ ትኩሳት፣ ሳል ፣እና ተቅማጥ ያልተለመዱ ክስተቶች አይደሉም፤ የሚጠበቁ ናቸው። እንዲያውም አብዛኛዎቹ እነዚህ ሕመሞች ቀለል ያሉና በቤት ውስጥ በሚደረግ ጥንቃቄ የሚሻገሩ ናቸው።
ሆኖም ግን፤ ይህ “ተራነት” አታላይ ሊሆን ይችላል።
ምክንያቱም አደገኛና ከባድ ሕመሞች መጀመሪያ ላይ ማንነታቸውን በግልጽ አያሳውቁም። እንደ ቀላል ህመም መስለው፤ በኋላ ላይ እየተባባሱ ሊመጡ ይችላሉ። ውስጣዊ አጥፊነታቸውን በቀላል ምልክቶች ጀርባ ሊደበቅ ይችላል።
ምልክቶቻቸው ተመሳሳይ ሲሆኑ—ግን ሕመሙ ሲለያይ
ለወላጆች ትልቁ ፈተና ይሄ ነው። ሕመሞች መጀመሪያ “ተመሳሳይ ፊት” ይዘው ብቅ ማለታቸው ያሳስባቸዋል። ቀላል ጉንፋን እና ሳንባ ምች (Pneumonia) መጀመሪያ ተመሳሳይ ምልክት ሊያሳዩ ይችላሉ። ሁለቱም ትኩሳት ይላቸዋል፤ ያስላቸዋል፤ ድካምም ይታይባቸዋል። በተመሳሳይ ተራ የሆድ መረበሽ እና ለሕይወት አስጊ የሆነ ተቅማጥ መነሻቸው አንድ ዓይነት ሊሆን ይችላል።

ይህም የሆነው ሰውነታችን ጉዳቱን መግለጽ የሚችልበት ምልክቶች የተገደቡ ስለሆኑ ነው። እንደምሳሌ ትኩሳት፣ ሕመም መሰማት (pain)፣ ድካም እና የምግብ ፍላጎት መቀነስ ብዙ በሽታዎች ላይ ይስተዋላሉ። በበሽታዎች መሀል ለመለየት ግን የእነዚህ ምልክቶች መኖር ብቻ ሳይሆን፤ ከሰዓት ወደ ሰዓት የሚያሳዩት የባሕሪ ለውጥና አብረዋቸው ያሉ ምልክቶችን ማየት ያስፈልጋል። እውነተኛውን ታሪክ የሚነግረን ያ የለውጥ ሂደት ነው።
ትኩሳትን እንደምሳሌ እንውሰድ። ትኩሳት ሰውነት በሽታን እየተከላከለ መሆኑን የሚያሳይ የበሽታ መከላከያ ስርአታችን የመታገል ምልክት ነው። በቫይረስ የሚመጡ ሕመሞች ላይ ትኩሳት ቢኖርም፣ ሰውነት ራሱ ሊያስወግደው ይችላል። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነጥብ ከትኩሳቱ መጠን (ቁጥር) ባሻገር የልጁ አጠቃላይ ሁኔታ ነው። ትኩሳት ኖሮትም የሚጠጣ፣ የሚጫወትና፣ ንቁ የሆነ ልጅ፤ ትኩሳት ኖሮት ዝልፍልፍ ከሚል ከሚነጫነጭ ወይም ጭልጥ ያለ ዝምታ ውስጥ ከሚሰምጥ ልጅ ጋር ፈጽሞ እኩል አይደለም። ይህ ትኩሳት ያለበት ልጅ የሚኖረው የወባ በሽታ የተስፋፋበት አከባቢ ከሆነ ደግሞ፤ ማንኛውም ትኩሳት እንደ ድንገተኛ አደጋ ታይቶ ወዲያውኑ ምርመራ መደረግ አለበት።
ሕመሙ መልክ ሲቀይር
አብዛኛዎቹ የተለመዱ ሕመሞች የሚታወቅ ጉዞ አላቸው፦ ምልክቶች ይታያሉ፤ ይበረታሉ ከዚያም ቀስ በቀስ ይሻላሉ። ነገር ግን ያ ሂደት ሲስተጓጎል ትኩረት ይሻል።
ለምሳሌ፡ ወደ ፈጣን ወይም አስቸጋሪ አተነፋፈስ የተቀየረ ሳል ከእንግዲህ ተራ ጉንፋን አይደለም።
ፈጣን አተነፋፈስ የምንለው ዕድሜያቸው ከ2-11 ወር ለሆኑ ህፃናት በደቂቃ 50 እና ከዚያ በላይ ሲሆን፤ ከ1 እስከ 5 ዓመት ለሆኑ ደግሞ በደቂቃ 40 እና ከዚያ በላይ ሲሆን ነው። ከ 6 እስከ 12 እድሜ ላሉ ህጻናት ደግሞ ከ30 በላይ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር (IMNCI) መመሪያዎች፤ አንድ ሕመም ከተለመደው መስመር ወጥቶ ወደ አደገኛ ደረጃ መሸጋገሩን የሚያሳዩ "ቀይ መስመሮችን" በግልጽ ያስቀምጣሉ። እነዚህ ምልክቶች የታዩበት ሕፃን በቤት ውስጥ ሊታከም የሚችልበት ደረጃ ላይ አይደለም፤ ይልቁንም አስቸኳይ የሕክምና ዕርዳታ ይሻል።
ልጅዎ ላይ የሚከተሉትን ምልክቶች ካዩ በሽታው ቀላል እንዳልሆነ ተረድተው ሳይዘገዩ እርምጃ ይውሰዱ፦
የአተነፋፈስ ለውጥ፦ መተንፈስ መቸገር (የደረት መጎዝጎዝ) ወይም ያልተለመደ ፈጣን አተነፋፈስ።
የቆየ ትኩሳት፦ ዕድሜያቸው ከ2 ዓመት በታች ለሆኑ ልጆች ትኩሳቱ ከ1 ቀን በላይ፤ ከ2 ዓመት በላይ ለሆኑ ደግሞ ከ2 ቀናት በላይ ከቆየ።
ከፍተኛ ሙቀት፦ የሙቀት መጠኑ ከ38.5 ዲግሪ ሴልሺየስ (በብብት ሲለካ) በላይ ከሆነ።
የአቅም ማጣት፦ ጡት መጥባት ወይም ምግብ መውሰድ በፍጹም አለመቻል።
የማያቋርጥ ትውከት፦ የወሰዱትን ማንኛውንም ነገር ወዲያውኑ መመለስ።
የንቃት መቀነስ፦ ከመጠን ያለፈ እንቅልፍ ወይም በፍጹም መንቃት አለመቻል።
የአንገት መገተር፦ የአንገት መድረቅ ወይም መደደር (Stiff neck) ካለ።
መንቀጥቀጥ (Convulsions)፦ ድንገተኛና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የሰውነት መንቀጥቀጥ።
አደገኛ የፈሳሽ እጥረት፦ የዓይን መሰርጎድ፣ የከንፈርና የምላስ መድረቅ፣ እንዲሁም ከፍተኛ ድካም ወይም ዝልፍልፍ ማለት።
እነዚህ ምልክቶች ካዩ በሽታው ቀላል አይደልም። መጠበቅ አደጋ አለው። አቅራቢያዎ ያለ የጤና ተቋም ይሂዱ።
መዘግየት የሚያስከትለው ጉዳት
በሕፃናት ሕክምና ውስጥ "ጊዜ" ቁጥር ብቻ አይደለም፤ የሕይወት መትረፊያ ዕድል እንጂ። አደገኛ ምልክቶች ታይተው ሆስፒታል ለመድረስ የሚባክን እያንዳንዱ ደቂቃ፤ በሕፃኑ ሰውነት ውስጥ ያለውን የሕመም ኃይል ያበረታዋል።

አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች ወደ ሕክምና ለመሄድ የሚዘገዩት በቸልተኝነት ሳይሆን "ይሻለዋል" በሚል ተስፋ ወይም ነገሮችን ባለመረዳት ነው። ሆኖም ይህ መዘግየት ከባድ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል። ለምሳሌ፦
የበሽታው መሰራጨት፦ እንደ ሳንባ ምች ያሉ ሕመሞች በሰዓታት ውስጥ ከአንድ የሳንባ ክፍል ወደ ሌላው በመዛመት አተነፋፈስን ሙሉ በሙሉ ሊያስተጓጉሉ ይችላሉ።
የሰውነት መዛል፦ ህፃናት እንደ ትልቅ ሰው መጠባበቂያ ኃይል የላቸውም። ተቅማጥና ትውከት የሚያስከትሉት የፈሳሽ እጥረት በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የልብና የኩላሊት ሥራ ላይ ከባድ ጫና ሊያሳድሩ ይችላሉ።
የሕክምናው መወሳሰብ፦ ቀድሞ ቢደረስ በቀላል መድኃኒት ሊድን የሚችል ሕመም፤ ሲዘገይ ግን ከፍተኛ የቀዶ ጥገና ወይም የፅኑ ሕክምና ክትትል (ICU) ሊያስፈልገው ይችላል።
በሕይወት እና በሞት መካከል ያለው ልዩነት ብዙ ጊዜ ሆስፒታል መድረሳችን ሳይሆን፤ መቼ ደረስን የሚለው ነው።
ልጅዎ ላይ ከላይ የተጠቀሱትን አደገኛ ምልክቶች ካዩ፤ "እስቲ ልይ" የሚለው ውሳኔ ለነገ የማይባል የሕይወት መስዋዕትነት እንዳያስከፍልዎት አሁኑኑ እርምጃ ይውሰዱ።
ትክክለኛ የቤት ውስጥ እንክብካቤ ምንድነው?
ሁሉም የልጅነት ሕመሞች ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል መሄድን ላይጠይቁ ይችላሉ። እንደውም አንዳንድ ሕመሞች ቀለል ያሉ በመሆናቸው በቤት ውስጥ በሚደረግ ጥንቃቄ ሊታለፉ ይችላሉ። ምናልባትም በተለያየ ምክንያት አቅራቢያዎ ያለ ጤና ተቋም መሄድ ተቸግረው ሊሆን ይችላል። በእርስዎ ዘንድ ቆራጥ ውሳኔ የሚያስፈልገው የአደጋ ምልክቶችን ለይቶ በማወቅ እንጂ፤ ሁሉንም ሕመም በመፍራት መሆን የለበትም።

ልጅዎ ከላይ የጠቀስናቸውን የከፋ አደጋ ምልክት ሳይታይበት ከታመመ፤ የሚከተሉት እርምጃዎችን ቢያደርጉ በፈጣን እንዲያገግም ያግዙታል።
ትኩሳት ወይም ተቅማጥ ካለ በቂ ፈሳሽ መስጠት የሕክምናው ቀዳሚ ተግባር ነው። የኦአርኤስ (ORS) ጨው የፈሳሽ እጥረትን በመከላከል ረገድ ሕይወት አዳኝ ነው።
በኢትዮጵያ የጤና መመሪያ መሠረት፤ ተቅማጥ ላለባቸው ሕፃናት ከኦአርኤስ ባሻገር የዚንክ ኪኒን መስጠት፤ የሕመሙን ቆይታና ጥንካሬ በእጅጉ ይቀንሳል።
ሕፃኑ በሕመም ወቅት የምግብ ፍላጎቱ ቢቀንስም፤ በተደጋጋሚ ትንሽ ትንሽ ምግብ እንዲወስድ ማድረግ ኃይል እንዲያገኝና ማገገሙ እንዲፋጠን ይረዳል።
ትኩሳት ካስተዋሉ የሕፃኑን ምቾት ለመጠበቅ እንደ ፓራሴታሞል ያሉ መድኃኒቶችን በሐኪም ወይም በፋርማሲ ባለሙያ በሚታዘዘው ትክክለኛ መጠን መጠቀም ይቻላል።
እዚህ ጋር ሊያስተውሉ የሚገባው፦
ያለ ሐኪም ትዕዛዝ አንቲባዮቲክ (Antibiotics) መጠቀም ጉዳት አለው። ሰውነት ላይ ሊያደርስ ከሚችለው ጎንዮሽ ጉዳት ባሻገር፤ በሽታውንም ላያክም ይችላል። ለምሳሌ ለቫይረስ ሕመሞች አንቲባዮቲክ ምንም ዓይነት ጠቀሜታ የለውም። እንዲያውም ለወደፊት መድኃኒት የመላመድ (Resistance) ችግርን ሊፈጥር ይችላል።
ሁሉንም ነገር የሚቀይረው አንድ ጥያቄ
በመጨረሻም፤ ዋናውና ወሳኙ ጥያቄ “ይህ ምን ዓይነት ሕመም ነው?” የሚለው ሳይሆን ይልቁንም፦
“ልጄ እየተሻለው ነው ወይስ እየባሰበት?” የሚለው ነው።
ንቁ የሆነ፤ ፈሳሽ የሚወስድና ቀስ በቀስ የሚሻለው ልጅ በቤት ውስጥ ሊከታተሉት ይችላሉ። እየዛለ የሚሄድ፤ ስሜቱ የማይታወቅ ወይም አዳዲስ አሳሳቢ ምልክቶች የታዩበት ልጅ ግን በአስቸኳይ መታየት አለበት።
አብዛኛዎቹ የልጅነት ሕመሞች ቀላል ቢሆኑም፤ ጥቂቶቹ በወቅቱ ትኩረት ይሻሉ። የልጅዎ ሕይወት የሚተርፈው በሰዓቱ በሚያደርጉት ውሳኔ ነው።
ምልክቶቹን ያስተውሉ። በአፋጣኝ ይወስኑ።





Comments