top of page

አንድ እግር ብቻ በድንገት ሲያብጥ ምን ማለት ነው?

5 hours ago
4 min read

አንድ ቀን ጠዋት ከእንቅልፍዎ ሲነሱ፤ የእርስዎ ወይም የቅርብ የቤተሰብዎ አንድ እግር ባልተለመደ ሁኔታ አብጦ አገኙት እንበል...

በመጀመሪያ ወደ አእምሮዎ የሚመጣው ምንድን ነው?

"ኩላሊት ፣ የልብ ችግር፣ አልያም ጉበት ይሆን ብለው ይጨነቃሉን?

ወይም ደግሞ ነገሩን ለማቀለል “ትናንት ረጅም ሰዓት ቆሜ ስለዋልኩ ይሆናል” ብለው ሊያልፉት ይሞክሩ ይሆናል።


ግን ቆም ብለው አንድ ወሳኝ ጥያቄ ራስዎን ይጠይቁ፦

ለምን አንድ እግር ብቻ ተለይቶ አበጠ?

ለዚህ የሚሰጡት ምላሽ፤ የሚያስፈልጎትን ሕክምና ይወስናልና በደንብ ያስተውሉ!


ምናልባትም እኮ "አይ... ይሄማ ተራ ነገር ነው” ብለው እግርዎን አሽተው ሊተኙ ወይም ወደ ስራዎ ሊሄዱ ያስቡ ይሆናል።

ግን ፈጽሞ እንዳያደርጉት!

ለምን ካሉ.... ይህ እብጠት የመጣው እግር ውስጥ ያለ የደም ስር መርጋት ጋር ተያይዞ ከሆነ፤ ማሸት ሊሰሯቸው ከሚችሏቸው ትልቅ ስሐተቶች ውስጥ አንዱ ነው።


ለዚህም ዋቢ እንዲሆንዎት፤ በሕክምናው አለም ያጋጠሙ እና በሕክምና ምርምር መጽሄት ላይ የተለቀቁ 2 ታሪኮችን እንጥቀስልዎ፦

አንድ የ23 ዓመት ወጣት ከእግር ስብራት በኋላ እግሩ በጀሶ ታስሮ ነበር። በኋላም በእግሩ ላይ ሕመምና እብጠት ተከሰተ። እናቱም ይህንን ህመም ለማስታገስ በሚል ባቱን አሸችለት።


ከዚያ በኋላ ግን ነገሩ በድንገት ተቀየረ። ወጣቱ የትንፋሽ ማጠር፣ ከባድ የደረት ሕመምና የልብ ምት መዛባት አጋጠመው። ወደ ጤና ተቋም ተወስዶ የአደጋ ጊዜ ሕክምና ቢደረግለትም፤ በሳንባው የደም ሥር ውስጥ በተፈጠረ መዘጋት ምክንያት ሕይወቱ ሊተርፍ አልቻለም። ታሪኩን እዚህ ያገኙታል


በሌላ ተመሳሳይ ታሪክ፤ ቀደም ሲል የእግር ጥልቅ የደም ሥር መርጋት (DVT) የነበረበት የ56 ዓመት ግለሰብ እግሩ ከታሸ በኋላ፤ ከባድ የትንፋሽ ማጠር አጋጠመው።  ዕድለኛ ሆኖ በፍጥነት ወደ ድንገተኛ ክፍል ተወስዶ ፤ በተደረገለት ከፍተኛ የነፍስ አድን ሕክምና ሊተርፍ ችሏል። ታሪኩን እዚህ ያገኙታል


እነዚህ ታሪኮች አንድ ወሳኝ ጥያቄ ያስነሳሉ፦

እግር ውስጥ የሚፈጠር የደም መርጋት እንዴት ለሕይወት አስጊ ሊሆን ይችላል?

በእግርዎ ውስጥ ያለ የደም መርጋት ምንድነው?

ስንቆስል ወይም ስንጎዳ ደማችን መርጋቱ የተፈጥሮ የሰውነት ምላሽ ነው። ይህም ቁስሉን በመዝጋት ከመጠን በላይ ደም እንዳይፈስ ይረዳል። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ምንም ቁስል ሳይኖር፤ በደም ሥር ውስጥ የደም መርጋት ሊፈጠር ይችላል። ይህ መርጋት ደም በደም ሥሩ ውስጥ በተለመደው ሁኔታ እንዳይፈስ ሊያደርግ ይችላል።


ወደ ልብ በሚመልሱ (ደም መልስ/viens ) የደም ሥሮች ውስጥም ደም ሊረጋ ይችላል። ይህ ክስተት በሕክምናው ዓለም Deep Vein Thrombosis (DVT) ወይም የጥልቅ ደም ሥር የደም መርጋት ይባላል። ይህ መርጋት በአብዛኛው በእግር ጥልቅ የደም ሥሮች ውስጥ ቢፈጠርም በእጅ ውስጥ ባሉ ጥልቅ የደም ሥሮችም ሊከሰት ይችላል።

ለዚህ ጽሁፍ በዋነኝነት እግርን ብንጠቀምም፤ የሚነሳው ሃሳብ ወይም ምክር አንድ እጅ ለይቶ ለሚያጋጥም እብጠትም ሊሆን እንደሚችል መታወቅ ይኖርበታል። 

የደም መርጋትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ምክንያቶች

የደም መርጋት ከሚከሰትባቸው ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ለረጅም ጊዜ እንቅስቃሴ መቀነስ/አለማድረግ ነው።


ለምሳሌ፦ ለረጅም ሰዓታት ሳይንቀሳቀሱ መቀመጥ፣ በሕመም ምክንያት አልጋ ላይ መቆየት ወይም ረጅም የመኪናና የአውሮፕላን ጉዞ ማድረግ በእግር ውስጥ ያለው ደም ወደ ልብ የሚመለስበትን ፍጥነት ሊቀንስ ይችላል። ይህም የመርጋት ዕድልን ያሳድጋል።


ሌላው ምክንያት ጉዳት ነው። በአደጋ፣ በከባድ ስብራት ወይም በትልቅ ቀዶ ጥገና ምክንያት የደም ሥሮች ሲጎዱ፣ የደም መርጋት ዕድል ሊጨምር ይችላል።


ከዚህም በተጨማሪ፤ በጄኔቲክ ተጽዕኖ፣ በእርግዝናና ከወሊድ በኋላ፣ በአንዳንድ መድኃኒቶች ወይም በካንሰር ምክንያት የደም የመርጋት ባህሪ ሊጨምር ይችላል።


ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

በጥልቅ ደምስሮች ውስጥ ደም መርጋቱን ተከትሎም የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያስተውሉ ይችላሉ።


  • ድንገተኛ የአንድ እግር ማበጥ፦ ይህ እላይ ያነሳነው ዋነኛው ምልክት ነው። ሁለቱም እግሮች ሳይሆኑ አንደኛው እግርዎ ብቻ (በተለይ ከጉልበትዎ በታች) በድንገት ከሌላው ተለይቶ ያብጣል ።

  • ያበጠው እግር ላይ ከባድ የሆነ ህመም ያስተውላሉ።   ይህ ሕመም ሲቆሙ ወይም ሲራመዱ ይበልጥ እየባሰ ይሄዳል።

  • ያበጠው እግር ሙቀት መጨመር፦ ያበጠውን እግር በእጅዎ ሲነኩ፤ ከሌላኛው እግርዎ ይበልጥ የትኩሳት ወይም የሙቀት ስሜት ሊሰማዎት ይችላል።

  • የቆዳ ቀለም መለወጥ፦ እብጠቱ ባለበት አካባቢ ያለው የቆዳ ቀለም ሊቀላ፣ ሊጠቁር ወይም ወደ ሰማያዊነት ሊያደላ ይችላል።


እዚህ ጋር ያስተውሉ!

ይህ የጤና እክል አለ ለማለት እነዚህ ምልክቶች ሁሉ በአንድ ላይ መታየት የለባቸውም ። እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች በእግራቸው ውስጥ ገዳይ የደም መርጋት ቢኖርባቸውም እንኳን፤ ምንም ዓይነት ግልጽ ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ። ለዚህም የአንድ እግር ለይቶ ማበጥ ካለ፤ ነገሩን አቅልሎ ከማየት ወደ ሕክምና ተቋም ሄዶ መመርመር እጅጉን ይመከራል።


የደም መርጋት ለምን አደገኛ ነው?

እዚህ ጋ ነው እንግዲህ ጉዳዩ አሳሳቢ የሚሆነው!

በእግርዎ ጥልቅ የደም ሥር ውስጥ የተፈጠረው የደም መርጋት እዚያው ባለበት ብቻ አርፎ ላይቀመጥ ይችላል። ይህ የደም መርጋት ካለበት ቦታ ተላቆ፤ በደም ፍሰት አማካኝነት በቀጥታ ወደ ሳንባዎ በመጓዝ የሳምባን ዋና የደም ሥር ሊዘጋ ይችላል። በሕክምናው ዓለም ይህ የሳንባ የደም ሥር መዘጋት (pulmonary embolism/PE) ገዳይ የሆነ የጤና እክል ነው። በደቂቃዎች ውስጥ ለህልፈት ሊዳርግ የሚችል ለሕይወት አስጊ የሆነ የጤና ቀውስ ነው!

እግርን ማሸትም የሚከለከለው ለዚህ ነው።

ለምን?


እግሩ በደም መርጋት ምክንያት ያበጠ ከሆነ፤ ማሸት ተገቢ የሕክምና መፍትሔ አይደለም። ሲያሹ በግፊቱ ምክንያት በእግር ጥልቅ የደም ሥር ውስጥ ተጣብቆ ተቀምጦ የነበረው የደም መርጋት ከቦታው እንዲለቅ እድል ይፈጠራል። ካለበት ቦታ ከተላቀቀ ደግሞ፤ ወደ ሳንባ በመጓዝ ከላይ የገለጽነውን ገዳይ ሁኔታ ያስከትላል።


ለዚህም እግርዎን ማሸት አደገኛ ሊሆን ይችላል!


ታዲያ እግር ማበጥ ሁልጊዜ የደም መርጋት ማለት ነው?

ፍጹም አይደለም!

አንድ እግር ብቻውን ሊያብጥ የሚችለው በደም መርጋት ምክንያት ብቻ አይደለም። በተለያዩ የጤና ችግሮች ሳቢያ ሊከሰት ይችላል።


ለምሳሌ፦ እግር ላይ የሚደርስ ድንገተኛ ጉዳት( መመታት፣ መውደቅ፣ ወይም ከባድ የጡንቻ መጋጨትና መጎዳት) የአንድ እግር እብጠት ሊያስከትል ይችላል። በቆዳ ላይ በሚፈጠር የባክቴሪያ ኢንፌክሽንም ቆዳው እንዲቀላ፣ ሙቀት እንዲጨምር፣ ከፍተኛ ሕመም እንዲያሳይ ሊያደርግ ይችላል። ከንፍፊት ጋር የተያያዙ ችግሮችም የእግር እብጠት ሊያስከትሉ ይችላሉ።


በተጨማሪም የልብ፣ የኩላሊት ወይም የጉበት ድካም ችግሮችም እግርን ሊያሳብጡ ይችላሉ። ሆኖም ግን በእነዚህ የውስጥ አካላት በሽታዎች ምክንያት የሚመጣ እብጠት፤ ብዙውን ጊዜ በሁለቱም እግሮች ላይ እኩል ነው የሚታየው (ይህ ግን ሁልጊዜ እንደዚያ ነው ማለት አይደለም)።


ዋናው ቁምነገር ምንድነው!?

በአንድ እግር ላይ በድንገት ያጋጠም እብጠትን ምክንያት በራስዎ ከመገመት፤ አቅራቢያዎ ያለ የጤና ተቋም ሄደው አስፈላጊውን ምርመራ አድርጎ መለየት ይሻላል።


ለዚህ ተጋላጭ እነማን ናቸው?

የደም መርጋት አደጋ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኝ ለማንኛውም ሰው ሊከሰት ይችላል። ሆኖም ግን፤ የሚከተሉት ሁኔታዎች ካሉብዎ፤ ይህ ችግር የመከሰት ዕድሉ ለእርስዎ እጅግ ከፍተኛ ይሆናል፦

  • ከመጠን በላይ የሰውነት ክብደት ካለብዎ፣

  • ለረጅም ሰዓታት ሳይንቀሳቀሱ በሥራ ጠረጴዛ ላይ የሚቀመጡ ከሆነ፣

  • በበሽታ ምክንያት አልጋ ቁራኛ የሆኑ ሰዎችን፣

  • ረጅም የባቡር፣ የመኪናና የአውሮፕላን ጉዞ በተደጋጋሚ ካደረጉ፣

  • በቅርብ ጊዜ ትልቅ ቀዶ ሕክምና ካደረጉ ወይም ከባድ ስብራት ካጋጠምዎ፣

  • በእርግዝና ወቅት እና ከወሊድ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ወራት ላይ ከሆኑ ፣

  • የካንሰር በሽታ ካለብዎ ፣

  • በቤተሰብዎ ውስጥ የደም መርጋት ታሪክ ካለ ፣ እና

  • ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ ፤ ተጋላጭነትዎ ከፍ ይላል።


እግርዎ በድንገት ካበጠ ማድረግ የሌለብዎ 3 ወሳኝ ነገሮች!

አንድ እግርዎ ብቻ በድንገት ሲያብጥ፤ ነገሩ በቤት ውስጥ መፍትሔ የሚተው ስላልሆነ እባክዎ እነዚህን ሦስት ነገሮች ፍጹም እንዳያደርጉ፦

  1. እግሩን ማሸት የለብዎትም !

ከላይ እንደገለጽነው፤ የበሽታው ምክንያት ሳይታወቅ እግር ማሸት ተገቢ አይደለም። ይህም ሕይወትን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።


  1. እብጠቱን ለመቀነስ በረዶ/ ሞቅ ያለ ነገር አያድርጉበት!

የእብጠቱ ምክንያት ሳይታወቅ በቤት ውስጥ ባሉ መፍትሔዎች ብቻ መተማመን፤ የሚያስፈልገውን ምርመራ ሊያዘገይ ይችላል።


  1. በራስዎ የደም ማቅጠኛ መድኃኒት አይውሰዱ!

እነዚህ መድኃኒቶች ደም መፍሰስን ጨምሮ ከባድ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። መድኃኒቱ የሚያስፈልግ መሆኑንና መጠኑን (Dose) መወሰን ያለበት የሕክምና ባለሙያ ብቻ ነው። ስለዚህ ለራስዎ ፈጽመው አይዘዙ!


በዋነኝነት ዛሬውኑ የሕክምና ምርመራ ያድርጉ !

አንድ እግርዎ በድንገት ካበጠ፣ በተለይም ከሕመም፣ ከሙቀት መጨመር ወይም ከቆዳ ቀለም ለውጥ ጋር ከተያያዘ፤ ዛሬውኑ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን ምርመራ ያድርጉ።  “እስኪ እስከ ነገ ልየው” ብሎ መጠበቅ ሕይወትዎን አደጋ ላይ መጣል እና በሽታው እስኪባባስ ዕድል መስጠት ነው።



በተለይም የሳንባ ደም ስር መዘጋት ምልክት ሊሆኑ የሚችሉት፤ የደረት ሕመም ፣ ድንገተኛ የትንፋሽ ማጠር፣ ሳል፣ ወይም ራስ መሳት ካጋጠምዎት፤ በአፋጣኝ ድንገተኛ የሕክምና እርዳታ ያግኙ።



ፈጽሞ ችላ አይበሉ! ለጤናዎ ቦታ ይስጡ!

Comments


bottom of page