የደም ካንሰር ምንድን ነው?
- Zebeaman Tibebu
- Jan 24
- 3 min read

ፊልም ወዳጅ ከሆኑ ፤ ከእነኝህ ሁለት ተዋናዮች ውስጥ አንዱን ያውቁታል። በግራ ያለው በስፓርታከስ የሚታወቀው አንዲ ዋይትፊልድ (Andy Whitfield) ሲሆን በቀኝ በኩል ደግሞ በዴክስተር ፊልም የሚታወቀው ማይክል ሆል (Michael C. Hall) ነው። ከ ፊልም ተዋናይነታቸው ባሻገር ሁለቱንም አንድ የሚያደርጋቸው ቢኖር የደም ካንሰር ነው።
ታድያ ግን የስፓርታከሱ አክተር በ 39 አመቱ ከዚህ አመት በሞት ሲለይ ፤ ማይክል ግን ከካንሰሩ አገግሞ አሁንም በህይወት አለ።
ይህ የደም ካንሰርን እውነታ ያሳያል። አንዳንዶች ሲያገግሙ ሌሎች ይሞታሉ። በዚህ ጽሁፍ ስለ ደም ካንሰር እናነሳለን። ስለ ደም ካንሰር ከመወያየታችን በፊት ፤ የደም ህዋሳት ምንጭ ስለሆነው መቅኔ መረዳት ይኖርብናል።
የአጥንት መቅኔዎ እጅጉን ታታሪ አካልዎ ነው።
መቅኔዎ በቀን ውስጥ ወደ 500 ቢሊዮን የሚጠጉ የደም ሕዋሳትን ይሠራል። ይህም ለእርስዎ ጤናማ ህይወት እጅጉን አስፈላጊ ነው። የተመረቱት የደም ህዋሳትም በስርአት ተግባራቸውን ይፈጽማሉ። እድገታቸው፣ ስራቸው እና ሞታቸው እጅጉን ስርአት የጠበቀ ነው። መቅኔዎ አዲስ ህዋሳት የሚሠራው ፤ የሞቱ እና የደከሙ ህዋሳትን ለመተካት ነው። ከሚያስፈልገው በላይ ሆነ በታች ህዋሳትን አያመርትም።

ታድያ ይህ ሚዛን ሲዛባ ፤ የደም ህዋሳትዎ መጠን ይቃወሳል። አለልክ መመረት ይጀምራሉ ፤ ይህን ጊዜ የደም ካንሰር አለ ይባላል።
30 ትሪሊየን በላይ የሚገመቱ የደም ህዋሳት ውስጥ ፤ በሺ የሚቆጠሩ ካንሰር ህዋሳት ለእርሶ ምንም ለውጥ ላያመጡ ይችላሉ።
ችግሩ ግን ካንሰር ሕዋሳት መራባት አያቆሙም። በሺ የነበሩት ሚሊየን ይሆናሉ ፤ ሚሊየን የነበሩት በቢሊየን ይቆጠራሉ። ከራሳቸውም አልፎ የጤነኛ ህዋሳትን ስራ ያስተጓጉላሉ። ይህን ጊዜ ምልክት ሊያዩ ይችላሉ።
ምልክት ባዩ ጊዜ ከሚሊዮን እስከ ቢሊዮን የሚቆጠሩ የካንሰር ሕዋሳት ደምዎት ውስጥ እየተዘዋወሩ ሊሆን ይችላሉ።
የደም ካንሰሮች በብዛት አይታዩም ፤ ሲያጋጥሙ ግን ገዳይ ናቸው።

በበአለም ዙሪያ ካሉ ካንሰሮች ውስጥ የደም ካንሰሮች 6 በመቶ የሚሆነውን ይወክላሉ። በየአመቱ ወደ 1.3 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች በደም ካንሰር ሲያዙ ፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ይቀጥፋሉ። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ይህ ጎልቶ ይታያል።
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የተደረገ አንድ ጥናት ሊዩኬሚያ የሚባለው የደም ካንሰር ካለባችው አምስት ታማሚዎች ውስጥ አንዱ ብቻ (21%) የአምስት አመት እድሜ ይኖረዋል። ባደጉ አገራት ግን ከ60 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት ታካሚዎች ከአምስት አመት በላይ ይኖራሉ።
ታድያ ይህ ለምን ሆነ?

ይህ እውነታ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ይያዛል። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ታማሚ ዘግይቶ ነው የሚታከመው። ህክምና ቦታ ሲደርሱም ፤ ባለ የጤና መሰረተ ልማት እጥረት ፤ የተሟላ የላብራቶሪ ምርመራ ሳይደረግ ይቀራል። በሽታው መኖሩ በታወቀ ጊዜ ፤ ደርጅቶ ይገኛል። ህክምናውም ሁሉም የጤና ተቋማት በቀላሉ ስለማይገኝ ፤ ብዙዎች ህክምናውን በስርአት ለመከታተል ይቸገራሉ። ኢንፌክሽን ህመሞች በተንሰራፉባት ሀገራችን ደግሞ ፤ በስርአት ህክምና አለመከታተል የከፋ ደረጃ ላይ ይጥላል።
ለዚህም የደም ካንሰር ለብዙዎች ሳይታለም የተፈታ እውነታ ይሆናል።
ለምንስ ዘግይቶ ይታወቃል?
የደም ካንሰሮች ቀድመው ህመም አያስከትሉም። መጠናቸው በዝቶ የጤናማ የደም ህዋሳትን ሲያስተጓጉሉ አብዛኖቹ ምልክቶቹ ይስተዋላሉ። ምልክቶቹ ግን የተለመዱ ስለሆኑ ፤ችላ ይባላሉ።

ለምሳሌ፡
ድካም/ምክንያት የለሽ ድካም፡ ይህ ምልክት የቀይ የደም ህዋስ ስራ መስተጓጎል ጋር ይገናኛል።
ደጋግሞ በኢንፌክሽን መያዝ ፡ ይህ የነጭ የደም ህዋስ ስራ ከመስተጓጎል ጋር የተያያዘ ነው።
በቀላሉ መበለዝ እና መድማት ፡ ይህ ምልክት ከፕሌትሌት ስራ መስተጋጎል ይመጣል።
ትኩሳት፡ ይህ ሰውነት የካንሰር ህዋሳትን ለማስወገድ በሚያደርገው ጥረት እንዲሁም በኢንፌክሽኖች ሊመጣ ይችላል።
ክብደት መቀነስ ፡ ይህም የምግብ ፍላጎት ከመቀነስ ጋር ሊያያዝ ይችላል።
እርስዎ ለመሆኑ እነኝህን ምልክቶች አይተው ካንሰር ብለው ያስባሉን?
አዎ! የብዙዎችም እውነታ እንደ እርስዎ ነው።
የድካማቸው ምንጭ እረፍት ማጣት፣ እድሜ ፣ ወይም ደም ማነስ ብለው ይዘናጋሉ። ትኩሳት ሲሰማቸውና ኢንፌክሽን ደጋግሞ ሲይዛቸው አንቲባዮቲክስ ደጋግመው ይወስዳሉ። ከኋላ ስለሚኖር በሽታ ፈጽሞ አይጠረጥሩም። ደግሞስ ኢንፌክሽን በሽታዎች በበዙባት ኢትዮጵያ ባይጠረጠር አይደንቅም።

ኢንፌክሽን ህመሞች በበዙባት ኢትዮጵያ እነኝህ ምልክቶች አያሳስቡም። በሽታ ተችሎ እንዲታለፍ በሚያበረታታ ማህበረሰብ ውስጥ ችላ ተብለው ይታለፋሉ።
ለዚህም ምልክቶቹን መቋቋም ያቃታቸው ጊዜ ጤና ተቋም ይሄዳሉ። ያን ጊዜ ዘግይተዋል።
ለዚህም በኢትዮጵያ ውስጥ የደም ካንሰሮች ዋነኛ ገዳይ በሽታዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።
አ.ኤ.አ 2019 ዓም የተደረገ ጥናት ይህን ይደግፋል። ሊዩኬሚያ የሚባለው የደም ካንሰር በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም አራት ገዳይ ካንሰሮች ውስጥ ተጠቅሷል።
በምንስ ይመጣል?

ለደም ካንሰር አጋላጭ የሚባሉ መንስኤዎች መሀከል ዋነኛ የሚባሉት፡
የቤተሰብ ታሪክ ፡በቤተሰብ የደም ካንሰር ታማሚ ካለ የደም ካንሰር የማጋጠም እድሉ ከፍተኛ ነው።
በጊዜ ውስጥ የሚመጡ የዘረመል ለውጦች፡ እነኝህ የዘረመል ለውጦች ህዋሳት ወደ ካንሰር እንዲለወጡ ያደርጋሉ። ለዚህም እድሜ በገፋ ቁጥር እነኝህ ካንሰሮች የማጋጠም እድል እየጨመረ ይመጣል።
ለጨረር መጋለጥ፡ ደጋግሞ መጋለጥ ተጋላጭነትን ይጨምራል።
ለኬሚካሎች መጋለጥ። ቤንዜን ለ ሊዩኬሚያ እንደሚያጋልጥ መረጃዎች ይጠቁማሉ። እንዲሁም አንዳንድ ኬሚካሎች መቅኔ ላይ ባላቸው መርዛማነት እነኝህን ካንሰሮች ሊያመጡ ይችላሉ።
ቫይረሶች ፡ አንዳንድ ቫይረሶችም እነኝህን ካንሰሮች ሊያስከትሉ ይችላሉ።
የበሽታ መከላከያ ስርአት ችግር፡ በተፈጥሮ ሆነ በመድሐኒት የሚመጥ የበሽታ መከላከያ ስርአት መዛባት እነኝህ ካንሰሮችን ሊያስከትል ይችላል።
እናስ ምን ይሻላል?

መደበኛ ምርመራ ያድርጉ!
በሲቢሲ (CBC) መጀመር ይችላሉ።
እንደ ሀኪምዎ ትዕዛዝ የደም ማይኮርሶፕ ምርመራ (peripheral smear) እና የመቅኔ ናሙና ምርመራ (bone marrow examination) ሊያስፈልግ ይችላል።
የደም ካንሰር አይነቶቹን ለመለየት ላቅ ያሉ ምርመራዎችም ሊታዘዝልዎትም ይችላሉ።
በጊዜ ካወቁ የህክምና አማራጮች አሎት ። እንደ ካንሰር አይነቱ እና ደረጃው :
ኬሞቴራፒ (Chemotherapy)፣
ታርጌትድ ቴራፒ (Targeted Therapy)
እንዲሁም ኢምዩኖ ቴራፒ (Immunotherapy) ሊታዘዝ ይችላል።
እንደ ካንሰር አይነቱ ለአንዳንድ ታካሚዎች የመቅኔ ንቅለ ተከላ ሊደረግ ይችላል። እነኝህ ታካሚዎች ከበሽታው ፈጽሞ ሊያገግሙ ይችላሉ።
ይህ ሁሉ የህክምና አማራጭ ውጤታማ የሚሆነው፤ ቀድመው ህክምና ከጀመሩ ነው። ለዚህም ድካም ነው ብለው ፈጽሞ ችላ አይበሉ።
መዘግየትዎ ዋጋ ያስከፍላል!

