ኮሌስትሮል፦ ወዳጅ ወይስ ጠላት? መንስኤዎቹ፣ ምልክቶቹ፣ እና መፍትሔው
- Zebeaman Tibebu
- 16 hours ago
- 5 min read
Updated: 24 minutes ago
አንድ አዘቦት ጠዋት ነው ብለው ያስቡ.... ከእንቅልፍዎ እንደተነሱ ምን ያደርጋሉ?

ከአልጋዎ ይነሳሉ.... ቁርስዎን ይመገባሉ....ከዚያም ወደ ሥራዎ ያመራሉ። ይራመዳሉ፤ ይስቃሉ፤ ያወራሉ... ፤ሙሉ በሙሉ ጤነኛ እንደሆኑ ይሰማዎታል።
ነገር ግን ከዕይታዎ ውጭ፤ በሰውነትዎ ውስጥ አንድ ሚስጥራዊ ሂደት እየተከናወነ ቢሆንስ?
በደም ሥርዎችዎ ግድግዳዎች ላይ ለዓመታት ኮሌስትሮል ሲከማች፤ ምንም ዓይነት የሕመም ስሜት አይሰማዎትም። ምንም ምልክት አያሳይም። ድምፅ የለውም!
ኮሌስትሮልን አደገኛ የሚያደርገው፤ ይህ "ጸጥተኝነት" ነው !
ብዙዎች ችግሩ ጉዳት እስኪያደርስ ፤ ህመም እስኪያሰማ አያውቁትም። ይህ ድምፅ አልባ ችግር ግን ፤ በጊዜ ሂደት ወደ ድንገተኛ የልብ ወይም ስትሮክ ሊያመራ ይችላል።
ስለ ከፍተኛ ኮሌስትሮል ማወቅ ያለብን ትልቁ እውነት ይህ ነው፦ ምልክት ስለሌለ ብቻ ጤነኛ ነዎት ማለት አይደለም።
ፈጽሞ የሚታይ ምልክት የለምን?

አብዛኛው ሰው በደም ሥሩ ውስጥ ኮሌስትሮል በአደገኛ መጠን እየተከማቸ እንኳን፤ ምንም አካላዊ ምልክት አይሳይም። ራስ ምታት መጥቶ “ኮሌስትሮልዎ ከፍ ብሏል” አይልም። የደረት ሕመምም ቢሆን “የመጥፎው ኮሌስትሮል (LDL) መጠንዎ ጨምሯል” የሚል የተለየ ምልክት ይዞ አይመጣም። ማዞር፣ ድካም ፣ ወይም የሰውነት መስነፍም ቢሆኑ የኮሌስትሮልን መናርን፤ አስረግጠው ሊነግሩዎት አይችሉም።
ባጭሩ... በስሜትዎ ብቻ ኮሌስትሮልዎን ማወቅ አይችሉም።
ታድያ ግን አንዳንዴ መጠኑ በጣም ክፍተኛ ሲሆን ፤ በተለይም በዘር በሚተላለፍ የኮሌስትሮል ችግር (Familial Hypercholesterolemia - FH) ካለ፤ ሰውነት አንዳንድ ድብቅ ምልክቶችን ማሳየት ይጀምራል።
ለምሳሌ፦

በዓይን ዙሪያ የሚታዩ ቢጫ እብጠቶች (Xanthelasma)፦ በምስሉ እንደሚታየው በዓይን ሽፋሽፍት አካባቢ (በተለይ ወደ አፍንጫው በቀረበው ክፍል) የሚስተዋሉ ጥቃቅን፤ ሲነኩ ለስላሳ የሆኑ፤ በኮሌስትሮል ክምችት የሚፈጠሩ እብጠቶች ሊታዩ ይችላሉ።

በጅማቶች ላይ የሚወጡ እብጠቶች (Tendon xanthomas)፦ በምስሉ እንደሚታየው በቋንጃ(ከቁርጭምጭሚት በስተጀርባ ባለው ወፍራም ጅማት (Achilles tendon)) እና በእጆች አንጓ አከባቢ ላይ እብጠቶች ሊወጡ ይችላሉ። እነኝህ እብጠቶች በኮሌስትሮል ክምችት የሚመጡ ሲሆን፤ ሲነኩ ጠጠር ያሉ ናቸው።

በዓይንዎ ብሌን (ኮርኒያ) ላይ የሚታይ ቀለበት (Corneal arcus)፦ በምስሉ እንደሚታየው የዓይንን ብሌን የሚከብ፤ መልኩ ነጭ፣ ግራጫ ወይም ሰማያዊ የሚመስል ፤ የኮሌስትሮል ክምችት ሊስተዋል ይችላል። እንዲህ አይነት ቀለበት ብዙ ጊዜ እድሜ በገፉ ሰዎች ላይ በተፈጥሮ ሊታይ የሚችል ቢሆንም ፤ በወጣቶች ላይ ከተሰተዋለ የከፍተኛ ኮሌስትሮል ጠቋሚ ፍንጭ ሊሆን ይችላል።
እነኝህ ምልክቶች ኮሌስትሮል መብዛቱን ጠቋሚ ሊሆኑ ይችላሉ እንጂ፤ ሊያረጋግጡ እንደማይችሉ ሊታወቅ ይገባል።
ሆኖም ግን....ምልክቶች እስኪታዩ ድረስ በፍጹም አይጠብቁ!
ታድያ ኮሌስትሮል...ጠላት ወይስ ወዳጅ?

ኮሌስትሮልን በቀላሉ “መጥፎ” ብሎ መፈረጅ ስህተት ነው።
እውነታው ሰውነታችን ያለ ኮሌስትሮል መኖር አይችልም። ኮሌስትሮል ለሰውነታችን የዕለት ተዕለት ህልውና እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ታላላቅ ተግባራትን ያከናውናል። በቢሊዮን የሚቆጠሩ የሰውነታችን ሕዋሳትን ውጫዊ ሽፋን ይገነባል(ከላይ ባለው ምስል እንደሚታየው)። ኮሌስትሮል እንደ ቴስቶስትሮን፣ ኤስትሮጅን እና ኮርቲሶል ያሉ ወሳኝ ሆርሞኖችን እንዲሁም የቫይታሚን ዲ ለመስራትም የሚያገለግል ዋነኛ ጥሬ ዕቃ ነው። በተጨማሪም ምግብን ለመፍጨት የሚያገለግለው ሐሞትም የሚሰራው በኮሌስትሮል ነው።
ለዚህም ችግሩ የኮሌስትሮል መኖር ሳይሆን፤ መጠኑ ከጤናማ ደረጃ በላይ ማለፉ ነው።
ከፍተኛ ኮሌስትሮል በምን ሊመጣ ይችላል?
ብዙዎቻችን ከፍተኛ ኮሌስትሮል የሚመጣው የቅባት ምግብ በመመገብ ብቻ ይመስለናል። እውነታው ግን ፈጽሞ የተለየ ነው።
“የቅባት ምግብ አትብላ” የሚለው ምክር፤ ብቻውን ለሁሉም ሰው በቂ መፍትሔ አይሆንም።
ለምን?

አንዳንድ ጊዜ አደጋው የሚመጣው ከዕለት ተዕለት ምግባችን ሳይሆን፤ ከቤተሰብ የዘር ሐረግ ነው። ይህ በዘር የሚተላለፍ የኮሌስትሮል ችግር በህክምናው ፋሚላል ሃይፐርኮሌስቶለሚያ (Familial Hypercholesterolemia) ይሰኛል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአለም ዙሪያ በአማካኝ ከ250 ሰዎች ውስጥ 1 ሰው ይህ ችግር ይገኝበታል ተብሎ ይታሰባል። ይህ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች፤ ምንም እንኳ ጤነኛ ምግብ ቢመገቡና፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ቢያደርጉም፤ ጉበታቸው መጥፎውን ኮሌስትሮል (LDL) በአግባቡ ማስወገድ አይችልም። ለዚህም ለከፍተኛ ኮሌስትሮል ችግር ይጋለጣሉ። እርስዎም በቤተሰብዎ ውስጥ በወጣትነት ዕድሜ (ለምሳሌ ከ50 ዓመት በታች) የልብ ጥቃት ወይም የስትሮክ ታሪክ እንዲሁም የኮሌስትሮል ችግር ካለ፤ የጤና ባለሙያ ያማክሩ። አስፈላጊውን ምርመራ ይድርጉ።

ከዚህም ባሻገር፤ የኮሌስትሮል መጠን ከፍተኛ ሁኔታ እንዲሆን የሚያደርጉ ሌሎች በርካታ ድብቅ የጤና ምክንያቶች አሉ። ለምሳሌ፦
የሰውነት ክብደት መጨመር፣
የሆርሞን መዛባት፣
የስኳር በሽታ፣
የታይሮይድ ዕጢ መቀነስ (Hypothyroidism)፣
የኩላሊት ችግሮች፣
የጉበት በሽታዎች፣
እና የአንዳንድ መድሀኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት ተጠቃሽ ሊሆኑ ይችላሉ።
ለዚህም ከፍተኛ ኮሌስትሮል ካለብዎ ፤ የአኗኗር ዘይቤ ከማስተካከል ባሻገር፤ ከጀርባ ያለ የተደበቀ የጤና ችግር አለመኖሩን ተመርምረው ማረጋገጥ ይመከራል።
ታዲያ ኮሌስትሮልዎ ከፍ ቢል እንዴት ያውቃሉ?

ታድያ ከፍተኛ ኮሌስትሮል ጸጥተኛ ከሆነ.... በምልክቶች መተማመን ካልቻለ.... ከፍተኛ ኮሌስትሮል መኖሩን የምናውቅበት አስተማማኝ መንገድ ምንድነው?
መልሱ ቀላል ነው፦ የደም ስብ ምርመራ (Lipid Profile)
የደም ስብ ምርመራ ልክ እንደ መኪና ዳሽቦርድ ፤ በደምዎ ውስጥ ስላለው የስብ/ኮሌስትሮ ሁኔታ ዝርዝር መረጃ ይሰጠናል። ነገር ግን ያስተውሉ ፤ጠቅላላ ኮሌስትሮል (Total Cholesterol) መደበኛ መሆኑ፤ ሁሉ ነገር ሰላም መሆኑን አይጠቁምም። በዚህ የደም ስብ ምርመራ ውስጥ፤ የኮሌስትሮል ችግር መኖሩን የሚጠቁሙ አራት የምርመራ አይነቶች አሉ። እነኝህም፦
Total Cholesterol (ጠቅላላ ኮሌስትሮል)፦ ይህ በደምዎ ውስጥ ያለውን አጠቃላይ የኮሌስትሮል ክምችት ያሳያል። እላይ እንደገለጽነው፤ ይህ ቁጥር ብቻውን ሙሉውን ሁኔታ አይጠቁምም።
LDL Cholesterol (መጥፎው ኮሌስትሮል)፦ ይህ ለልብ አደጋ እና ለስትሮክ የሚያጋልጠውን ኮሌስትሮል የሚለካ ነው። ይህ ቁጥር ከፍ ባለ ቁጥር በደም ሥሮችዎ ላይ አደገኛ ስብ የመከማቸት (Atherosclerosis) ሂደት ፈጣን ነው።
HDL Cholesterol (ጥሩው ኮሌስትሮል)፦ በተቃራኒው የዚህ ቁጥር ከፍ ማለት፤ ከዝቅተኛ የልብ አደጋ ጋር ይያያዛል።
Triglycerides (ሌላው የደም ስብ)፦ ይህ ኮሌስትሮል አይደሉም። ነገር ግን ከኮሌስትሮል ባሻገር ፤ ከምግብ የምናገኘው ሌላው የስብ ዓይነት ነው። መጠኑ ከፍ ማለቱ ለልብ ሕመምና እንዲሁም፤ ለድንገተኛ የቆሽት መቆጣት ይጋልጣል።
እዚህ ጋር ያስተውሉ!

የላብራቶሪ ቁጥሮችን ዝም ብሎ በደፈናው ማንበብ አይቻልም። የእርስዎ የኮሌስትሮል መጠን ትርጓሜ፤ ከሌላ ሰው ፍጹም የተለየ ሊሆን ይችላል። ሐኪሞች የላብራቶሪ ውጤትዎን የሚተረጉሙት ከእርስዎ ዕድሜ፣ ከበፊት ታሪክዎ፣ ካሉ ተጓዳኝ በሽታዎች፣ እና በቤተሰብዎ ውስጥ ካለ የልብ ሕመም ታሪክ ጋር አዛምደው ነው። ለዚህም ለትርጓሜው የጤና ባለሙያ ያማክሩ።
የኮሌስትሮል መጠን ከፍ ማለቱ ድንገተኛ ህክምና ያስፈልገዋል?
የላብራቶሪ ውጤትዎ የኮሌስትሮል መጠንዎ ከፍተኛ መሆኑን ሲጠቁም ሊፈሩ፤ አልያም “ታዲያ አሁን የልብ ድካም/ጥቃት ሊያጋጥመኝ ነው?” ብለው ሊሰጉ ይችላሉ። ይህ ምክንያታዊ ነው። ሆኖም ግን በዚያው ቅጽበት የልብ ወይም ስትሮክ ይከሰታል ማለት አይደለም።
ለምን?
ኮሌስትሮል በደም ሥሮች ውስጥ የሚከማቸው በአንድ ጀምበር ሳይሆን፤ ለዓመታት ቀስ በቀስ በመሆኑ፤ ይህ ውጤት ዛሬ ድንገተኛ አደጋን ማጋጠሙን አይጠቁምም። ይልቁኑ የነገውን ሕይወትዎን ለመጠበቅ፤ ዛሬውኑ እርምጃ እንዲወስዱ ቀስቃሽ ደወል ነው።

ስለሆነም ከፍተኛ ኮሌስትሮል ካለብዎት ፤ ወዲያውኑ ወደ ድንገተኛ ክፍል መሮጥ አያስፈልግዎትም። ነገር ግን ጉዳዩን ቸል ሳይሉ የጤና ባለሙያ ማማከር ይኖርብዎታል።
ኮሌስትሮል ከፍ ብሎ ለረጅም ጊዜ ቢቆይ ምን ይከሰታል?
ይህ ወሳኙ ጉዳይ ነው!

ኮሌስትሮል በደም ውስጥ ለረጅም ጊዜ ከፍ ብሎ ሲቆይ፤ ስብ በደም ሥር ግድግዳ ላይ ሊከማች ይችላል። ይህ አደገኛ ክምችት የአተሮስክሌሮቲክ ፕላክ (Atherosclerotic plaque) ይባላል። ይህ ክምችት በጊዜ ሂደት በደም ሥሮችዎ ውስጥ እያደገ እና እየገዘፈ ይሄዳል።
ይህ ክምችት ብዙ ሲቆይ፤ የደም ሥሮችን በከፍተኛ ሁኔታ ሊያጠብ፤ አልፎ ተርፎም ተሰብሮ ወደ ደም ሊገባ ይችላል። ይህን ጊዜ የደም ሥር መዘጋት፣ አልያም የደም ፍሰት ሙሉ በሙሉ መቋረጥ ያጋጥማል። ይህ መቋረጥ በተፈጠረበት የሰውነት ክፍል ላይ በመመስረት በሽታዎቹ ሊለያዩ ይችላሉ። ለምሳሌ ፦
ልብ ላይ ከሆነ፦ ለልብ ጡንቻዎች ኦክስጅን የሚያደርሱት ሥሮች ስለሚዘጉ፤ ድንገተኛ የልብ ጥቃት በሽታ ያጋጥማል።
አንጎል ላይ ከሆነ፦ የአንጎል የደም ሥሮች ላይ መዘጋት ሲያጋጥም ነርቮች ኦክስጅን አጥተው ይሞታሉ። ለዚህም ስትሮክ (Ischemic stroke) ይጋጥማል።
እግር ላይ ከሆነ፦ በመጋጠሚያ፣ በእጆች እና በእግሮች ላይ የሚገኙ ደም ሥሮች በዚህ የኮሌስትሮል ክምችት ሊዘጉ ይችላሉ። ይህ ከፍተኛ ሕመም ያለው ሲሆን፤ እንቅስቃሴን ይገታል። በህክምናው የደም ሥር በሽታ (Peripheral arterial disease) ይባላል።
ስለዚህ ዋናው አደጋ ቅጽበታዊ የኮሌስትሮል መጨመር ሳይሆን፤ ከፍ ብሎ መቆየቱ ነው።
የሕክምና አማራጮቹ ምንድን ናቸው?
የኮሌስትሮል ሕክምና ዋናው ዓላማ የላብራቶሪ ቁጥርን ብቻ ማስተካከል አይደለም።
ይልቁኑ የደም ሥር መጥበብን (Atherosclerosis) በመከላከል፤ እንደ የልብ ጥቃት፣ ስትሮክ፣ የእግር ደም ሥር መዘጋት እና ድንገተኛ ሞትን የመሳሰሉ አስከፊ የጤና ቀውሶችን ማስቀረት ነው። ለዚህም ኮሌስትሮልን በአኗኗር ዘይቤ ለውጥ እንዲሁም በዘመናዊ መድሀኒቶች ለመቆጣጠር ሊሞከር ይቻላል።

የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች
ኮሌትሮልን ለመቀነስ ፤ የዕለት ተዕለት ምግብዎ ውስጥ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬዎች (ባቄላ፣ አተር፣ ምስር፣ ወ.ዘ.ተ...) እና እህሎችን (የጤፍ እንጀራ፣ ገብስ እና አጃ) በብዛት ይጨምሩ። እነዚህ ምግቦች በተፈጥሯቸው በፋይበር የበለፀጉ በመሆናቸው ኮሌስትሮልን ከሰውነትዎ ለማስወገድ ይረዳሉ። በተቃራኒው በሳቹሬትድ ፋት (Saturated fat) እና ትራንስ ፋት (Trans fat) የበለፀጉ ምግቦችን (ቅቤ፣ ጮማ ሥጋ፣ የተጠበሱ ምግቦች፣ ወ.ዘ.ተ...) መቀነስ፤ መጥፎ የኮሌስትሮል መጠንን ለመቆጣጠር ይረዳል።
መደበኛ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ የደም ዝውውርን የሚያነቃቃ፤ የልብና የደም ሥር ጤናን የሚጠብቅ እና አጠቃላይ የልብ በሽታ አደጋን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ ምርጥ የተፈጥሮ መፍትሔ ነው። በሳምንት ጥቂት ቀናት ብቻ የሚደረግ የ30 ደቂቃ ፈጣን እርምጃ፤ በደም ሥሮችዎ ውስጥ የሚገኘው የስብ/ኮሌስትሮል መጠን ያሻሽላል።
ማጨስ በራሱ የደም ሥር ግድግዳዎችን በቀጥታ በማቁሰልና በማጥበብ፤ ስብ በቀላሉ እንዲከማች ስለሚያደርግ የልብ ሕመም ዋነኛ መነሻ ነው። ይህ ልማድ ቀድሞውኑ ከከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን ጋር ሲደመር፤ ለልብ ድካም ያጋልጣል። ስለዚህ በፍጹም አያጭሱ። በተመሳሳይ መልኩ ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት በተለይ የ ትራይግላይሰራይድ (triglyceride) መጠንን ሊያሳድግ ስለሚችል፤ ከመጠን በላይ መጠጣትን ያስወግዱ።። ለዚህም አልኮልንም በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሱ።

ዘመናዊ መድሀኒቶች
የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ብቻውን በቂ ላልሆነላቸው እና የደም ሥሮቻቸው ተጨማሪ ጥበቃ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ደግሞ፤ መድሀኒት (Statins) ሊሰጥ ይችላል። እነዚህ መድሀኒቶች በጉበት ውስጥ የኮሌስትሮል ምርትን በመቀነስ፤ የመጥፎ ኮሌስትሮል መጠንን ዝቅ ያደርጋሉ።
ሆኖም ግን ፤ ማንኛውንም የኮሌስትሮል መድኃኒት፤ ያለ ሕክምና ባለሙያ የቅርብ ምክርና፣ ክትትል በራስ ፈቃድ መጀመርም ሆነ ማቆም ፈጽሞ አይመከርም።።ያስታውሱ!
ምልክት ከመጠበቅ፤ ቀድሞ መከላከል ሁልጊዜም እንደሚሻል አይዘንጉ! ዛሬውን የደም ምርመራ ያድርጉ። ምልክት የለኝም ብለው እንዳይዘናጉ!
ኮሌስትሮልዎ ከፍ ካለ አይደንግጡ! ሆኖም ችላም አይበሉት። የጤና ባለሙያ ያማክሩ




Comments