🦴 ስብራት ወይስ ውልቃት?
- Zebeaman Tibebu
- Sep 25
- 4 min read
ድንገት በመውደቅ / በምጋጨት ይጀምራል....።
ምክንያቱ አዳልጦን አልያም አደናቅፎ ሊሆን ይችላል። አንዳንዱ ደረጃ ሲወጣ ተንሸራቶ ሲወድቅ ፤ ሌላው በሚመራው ከብት ይመታል። ገጠር ያለው ከፈረስ ወድቆ ሲጎዳ ፤ የከተማው በመኪና ግጭት አጥንታቸው ይጎዳል።
ታድያ ይህ የችግሩ መጀመሪያ እንጂ ማብቂያ አይደለም።
ጥቂቶች ወደ ሐኪም ቤት ሲሄዱ ፤ የተቀሩት ወጌሻ ይመርጣሉ። አይን ያወጣ ጉዳት አልያም ቆዳን ቀዶ የሚወጣ ስብራት እስከሌለ ድረስ የሚያሳስብ የማይመስላቸውም አይጠፉም።

እርስዎስ የቱን ይመርጣሉ? ምርመራ ከሚያበዛው/ ኪስ ከሚያከሳው ከሃኪም ቤት ወይስ ዳሶ ፈውሱን ከሚያውቀው ወጌሻ(እንደ አንዳንዶች አስተሳሰብ)?
...የቱን ይመርጣሉ?
ወጌሻው የተጎዳውን አካል አሽቶ ፤ በጨርቅ አጅሎ ፤ በእንጨት ወጥሮ ፤ ሙያዊ ምክር ሰጥቶ ይልካል። ለሳምንት አልያም ከዛ በላይ ክትትል ያዛል?
ሀኪሙም ኤክስ ሬይ አይቶ ፤ እንደአስፈላጊነቱ ሲቲ ስካን አዞ ፤ ስብራት ይሁን ውልቃት ለይቶ ፤ ወደ ቀዶ ጥገና አልያም እዛው ወደ ማስተካከል ይገባል። እሱም በበኩሉ በየሳምንት/ በየ2 ሳምንት ይቀጥራል።
ታድያ ሁልጊዜ ብዙ ኢትዮጵያውያን በሁለቱ መሀከል ለምርጫ ሲቸገሩ / ሲመላለሱ ማየት የተለመደ ነው።
በይበልጥ ግራ የሚያጋባው አንዱ ወጌሻ ስብራት ሲል ፤ ሌላኛው' ቀላል ነው ውልቃት ነው' ሲል ይገኛል። ለዚህም ታካሚ ዛሬ ቅጥቅጥ ነው ሲል የነበረ ፤ ሳይሻለው ቀርቶ ሌላ ወጌሻ ጋር አይ ውልቃት ነው ተስተካክሏል ይባላል። ታድያ ይህው ታካሚ ሌላ ወጌሻ ጋር ስብራት ነው ሊባል ይችላል።

ይህ ያልተለመደ ታሪክ አይደለም። የኢትዮጵያ ዝምተኛ ወረርሽኝ ነው። ብዙዎች በጊዜ ቢታከም ለሚድን ስብራት ፤ በዚህ ግራ መጋባት ውስጥ ታስረው ፤ ዘላቂ ጉዳት ያጋጥማቸዋል። አጥንት መሳሳት ህመም የሚለው ጽሁፍ ላይ የገለጽነውን እውነተኛ ታሪክ ለዚህ ዋቢ አድርጎ ማየት ይችላል።
📊 አሳሳቢው እውነታ
በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚደርሱት የአካል ጉዳቶች ውስጥ ስብራት ከ10-15% የሚያህለውን እንደሚይዝ የአለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ 2022 ባወጣው ሪፖርት ገልጿል። ታድያ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ፤ የህክምና አቅማቸው ባልጠነከረ አገራት ይህ ቁጥር ሊጭመር ይችላል። አንድም ለጉዳቱ የሚያስፈልገውን ህክምና በጊዜ ባለማግኘት ሌላም በባህላዊ ወጌሻዎች የደረሰባቸው ጉዳት ሊባባስ ይችላል።
እ.ኤ.አ. በ 2021 በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ከ 50% በላይ የሚሆኑት የአጥንት ስብራት ያጋጠምቸው ታካሚዎች ህክምና ቦታ ከመምጣታቸው በፊት ወጌሻ ጋር ሄደው ነበር። ከነዚህም መካከል ከአስሩ ውስጥ ወደ ሶስት የሚጠጉት በኢንፌክሽን፣ የተወሳሰበ የአጥንት ጉዳት እና ቋሚ የአካል ጉዳት ያጋጥምቸዋል።
ቀድመው ቢመጡ ምን ነበረበት? ወጌሻ ጋር ከመሄዳቸው በፊት ቢያንስ ኤክስሬይ ቢነሱስ?
የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያደረገው ጥናት ደግሞ አብዛኞቹ በገጠራማ ኢትዮጵያ የሚያጋጥሙ ስብራቶች "ከህክምና" በፊት የኤክስሬይ ማረጋገጫ አያገኙም። ታድይ ይህ ችግሩ እንዲበራከት ያደርጋል።
የዚህ መሰረታዊ ችግር ፤ ወጌሻና ዘመናዊ ህክምናን ቀንደኛ ጠላት አድርጎ ማሰብ ነው። ወጌሻ ጋር ከመሄድዎ በፊት በሰው አይን የማይታይ ከቆዳ ስር ያለ የአጥንት ጉዳትን ለመመልከት ኤክስሪይ ቢጠቀሙ ፤ ብዙዎች አካል ጉዳት ባላጋጠማቸው ነበር።

ሆኖም ግን እውነታው ከዚህ የራቀ ነው!
ይህ ከግንዛቤ ጉድለት የመጣ ነው። የተሻለ ግንዛቤ ቢኖር ስንት ኢትዮጵያውያን በድጋፍ ከመራመድ፣ ከከባድ ህመም ጋር ከመኖር አልያም መተዳደሪያቸውን ከማጣት ሊተርፉ ይችሉ ነበር።
ለዚህም ለመለየት እንዲችሉ በስብራት እና በውልቃት መሀከል ያለውን ልዩነት እናንሳ።
🧬 ስብራት ወይስ ውልቃት
ስብራት የሚባለው አጥንት ሲሰበር አልያም የውጭ ግድግዳው ሲሰነጠቅ ነው። ደረጃው ሊለያይ ይችላል። አንዳንዴ ተሰብሮ አጥንቶቹ ግን ተደጋግፈው ሊቆዩ ሲችሉ ፤ ሌላ ጊዜ ከተሰበረው ክፍል ውስጥ አንዱ ቆዳን ቀዶ አፈንግጦ ሊወጣ ይችላል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ደቃቅ ትናንሽ አጥንቶች ሊኖሩት ይችላሉ።
ከዚህ ቀጣይ ውልቃት ሲሆን ፤ ውልቃት አጥንት ቦታውን ሲስት የሚፈጥረ ነው። ይህም አንድ አጥንት ከመደበኛ ቦታው ሲያፈነግጥ አልያም አቀማመጡ ሲለወጥ ነው። ይህም መለውጥ መጋጠሚያ ላይ ጫና ስለሚያሳድር ፤ እንቅስቃሴ ሊገደብ ይችላል።

ያጋጠመ ጉዳትን በስርአት ሳይመረምሩ ከሁለቱ የትኛው እንደሆነ መገመት አደገኝነት አለው።
ለምን?
የሁለቱ ህክምና ፈጽሞ የተለያየ ነው። ስብራት በጀሶ አልያም በመደገፊያ አካል ማስተካከል አልያም በቀዶ ጥገና ማበጀት ሊፈልግ ይችላል። ውልቃት በበኩሉ ከስብራት ይልቅ ድንገተኛ ህክምና የሚያስፈልገው ነው። በአፋጣኝ የሳተው አጥንት ወደ ቦታው መመለስ ያስፈልገዋል።
ውልቃትን ስብራት አድርጎ መውሰድ ውልቃቱ መስተካከያ ወርቃማ ጊዜ ያባክናል። ይህም መባከን አጥንት እንዲራብ እና ጉዳቱ እንዲያይል ያደርጋል። አንድ ውልቃት በ 6 ሰአት ውስጥ ካልታከመ ይህ ሊያጋጥም ይችላል።

አሳዛኙ እውነታ... ብዙዎች ከ ቀናት/ከሳምንታት በኋላ ነው ወደ ህክምና ቦታ የሚሄዱት። ይህን ጊዜ አጥንት የደረሰበት ቀላል ጉዳት ደርጅቷል።
ምልክቶቻቸው አንዳንዴ ፍጹም ተመሳሳይ ሊመስሉ ይችላሉ። ሁለቱም እብጠት፣ከባድ ህመም፣ የእንቅስቃሴ መገደብ ሊያሳዩ ይችላሉ። ሆኖም ግን አንድ አይደሉም።
ታድያ በኤክስሬይ እንኳን ለመለየት የሚያስቸግርበት ሁኔታ ባለበት ላይ ፤ በወጌሻ ግምት ላይ መታመን በጤናዎ እንድመቆመር ነው!
⚠️ ችግሩ ምንድንነው ታድያ?
በሰአቱ አግባብ ያለው ህክምና ካልተደረገ ፤
የተሰበረው የአጥንት ክፍል ባለበት የራሱን ጉዳት ለመፈወስ ይሞክራል። በትክክል ሳይሆን ፤ ተጣሞ ይገጥማል። ይህ ደግሞ የራሱ ብዙ ችግር አለው። አጥንት ጥንካሬውን ያጣል። ደጋግሞ ለመሰበርም ቅርብ ይሆናል
የወለቀው የአጥንት ክፍል የተጫነው የደምስር የሚመገበው የአጥንት ክፍል ይሞታል። ይህም ብዙ ዳፋ ይዞ ይመጣል።

በጊዜው ህክምና ባለማድረግ የሚመጣውን ዳፋ/እክል እንደሚከተለው መጠቅለል እንችላለን።
የአጥንት ኢንፌክሽን (ኦስቲኦሜይላይትስ) → ጉዳት የደረሰበት አጥንት ንጽህናው ካልተጠበቀ ፤ የሚታሰርበት መሳሪያዎችም ንጽሁ ካልሆኑ ለበሽታ አምጪ ተህዋሳት ይጋለጣል። ይህም ጠንከር ያለ የአጥንት ኢንፌክሽን እንዲያጋጥም እድል ይከፍታል። ይህም ቁጥጥር ስር ካልዋለ አካል እስከመቆረጥ የሚደርስ ህክምና ሊያስፈልገው ይችላል።
የነርቭ እና የደም ቧንቧ ጉዳት → አጥንት በሚደርስበት ጉዳት ጊዜ አጠገብ ያሉ ነርቮችን እና የደም ቧንቧዎችን ሊጫን እና ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። እንዲሁም የደምስር አቀማመጥ እውቀት የሌለው ባለሙያ አጥንቱን ሊያስተካክል በሚሞክርበት ጊዜ የደም ዝውውርን ሊያቋርጥ ይችላል። ይህ የደምስር መቋረጥ ደግሞ ጋንግሪን ያስከትላል።
በልጆች ላይ የእድገት ችግሮች → አጥንት ሰውነታችን የሚያድግበት ፤ ቁመት የሚጨምርበት አካል ነው። እድገታቸውን ባልጨረሱ ልጆች ላይ የሚደርስ የአጥንት ጉዳት በጊዜ ካልታከመ ፤ እነኝህን ህጻናት እድገት በቋሚነት ሊያደናቅፍ ይችላል።
👉 ይህን ሲያስረግጥ ፤ እ.ኤ.አ በ 2019 በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የተደረገ አንድ ጥናት ፤ በባህላዊ ፈዋሾች ከሚታከሙ ህጻናት መሀከል ከ25% በላይ የሚሆኑት ዘላቂ አካል ጉዳተኝነት ያጋጥማቸዋል።
ታድያ ይህ የሕክምና ጉዳይ ብቻ አይደለም። የኢኮኖሚም ተግዳሮት ነው። የወጣቱ ገበሬ መራመድ አለመቻል የምርት መጥፋት ነው። እጁን መጠቀም ያቃተው ተማሪ ፤ የትምህርት ውጤታማነቱ ፈተና ላይ ይወድቃል። አባት ባልታከመ ስብራት ስራ መስራት አለመቻሉ ፤ ሙሉ ቤተሰብ ያስርባል። ለዚህ ይህ የማህበረሰብ ኪሳራ ነው።
🏥 ባህላዊ ወጌሻ ወይስ ዘመናዊ ህክምና?
ባህላዊ ወጌሻዎች በማህበረሰቡ ዘንድ የተከበሩ ቢሆኑም ፤ ክፍተት ግን አለባቸው። ከሚታዩባቸው ክፍተቶች ውስጥ ጥቂቶቹ
ኤክስሬይ ይጎድላቸዋል → ይህ ማለት ስብራት እና መነቀልን መለየት አይችሉም ማለት ነው።
የጸዳ መሳሪያዎች የላቸውም → ይህም ማለት ኢንፌክሽኑን የማሰራጨት እድላቸው ሰፊ ነው።
የሕክምና ስልጠና ይጎድላቸዋል → ይህም ማለት እንደ ውስጣዊ ደም መፍሰስ ወይም የአከርካሪ ጉዳት ያሉ የተደበቁ ጉዳቶችን ላይለይዋቸው ይችላሉ።
ለዚህም ብዙ ጉዳት ሊያስከትሎ ይችላሉ።
ታድያ በዘመናዊ ሕክምና እና በባህላዊ ወጌሻ መሀከል ያለውን ርቀት ማጥበብ ይኖርብናል። ጤና ጥበቃ በበኩሉ ባህላዊ ህክምናን ከዘመናዊ ህክምና ጋር አቆራኝቶ ውጤታማነት ለማሻሻል እየሰራ ይገኛል።
እርስዎም በበኩልዎ ደግሞ ፤ ስብራት እና ውልቃት በአይን ለመለየት እንደሚያዳግቱ ተረድተው ፤ ህክምናዎን ከመላምት ይልቅ በኤሚጂንግ/ኤክስሬይ ምርመራዎች ላይ ይመስርቱ።
ያስተውሉ ! ዘመናዊ ሕክምና ከባህላዊ ህክምና ጋር ፍጽም ተቃርኖ የለውም። ይልቁኑ የባህላዊ ህክምናን ድክመት የሚያግዝ ነው።
ለዚህም ስብራትና ውልቃትን ለመለየት አይን ማየት የማይችለውን በሚያሳዩት የዘመናዊ ህክምና መሳሪያዎች ይመርኮዙ።
የአጥንትዎን ጤና ይጠብቁ! በመጀመሪያ ሆስፒታል ይሂዱ።

ለማገገም በሀኪምዎ ምክር እንደአስፈላጊነቱ ከዘመናዊ ወጌሻዎች (ፊዚዮቴራፒስት) ጋር ይከታተሉ።
💡ተግባራዊ አንድምታው!
ይህን በማድረጋቸው በአለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ አገሮች የአካል ጉዳትን መጠን ከ40-60 በመቶ መቀነስ ችለዋል። ይህንን ካሻሻልን ኢትዮጵያም ተመሳሳይ ነገር ማሳካት ትችላለች።





Comments