top of page

ዳቦ ወይም ሌሎች የስንዴ ምግቦች ለምን አንዳንድ ሰዎችን ያሳምማሉ?

12 minutes ago
3 min read
ዳቦ ከበሉ በኋላ የሆድ መነፋት፤ ተቅማጥ ወይም የሆድ ሕመም ይሰማዎታል?

አንዳንድ ጊዜ ይህ ችግር የስንዴ ዳቦ ከበሉ በኋላ በተደጋጋሚ ሊከሰት ይችላል። ብዙዎች ይህንን በቀላሉ የምግብ አለመስማማት ብለው ያልፉታል።


ነገር ግን የስንዴ ምግቦች በአንዳንድ ሰዎች ላይ ከቀላል የሆድ መረበሽ የበለጠ ከባድ የሆነ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ። ይህም በህክምናው የ ሴሊያክ በሽታ (Celiac disease) ይባላል።


ሴሊያክ በሽታ ምንድን ነው?

ሴሊያክ በሽታ ሰውነት በስህተት የራሱን አንጀት (ትንሹን አንጀት) እንዲያጠቃ የሚያደርግ የመከላከያ ሥርዓት ችግር (Autoimmune disease) ነው።

ይህ ችግር ከግሉተን (Gluten) ከሚባል ፕሮቲን ጋር ይያያዛል። ግሉተን በስንዴ፣ በገብስና በጥምዠ ውስጥ የሚገኝ ፕሮቲን ነው። ከእነኝህ እህሎች የተዘጋጁ ዳቦ፣ ፓስታ፣ ቆሎ፣ ገንፎ፣ ኬክና ሌሎች ምግቦችም በውስጣቸው ይህን ግሉተን የሚሰኝ ፕሮቲን ሊይዙ ይችላሉ።


ይህ በሽታ ያለበት ሰው ታድያ ግሉተን የያዘ ምግብ ሲመገብ፤ የሰውነቱ መከላከያ ሥርዓት ግሉተንን ለመከላከል ሲል ትንሹን አንጀት ይጎዳል። በትንሹ አንጀት ውስጥ ምግብን የሚመጡት ትንንሽ ጣት መሰል ክፍሎች (Villi)፤ በሰውነታችን መከላከያ ስርአት ይጠቃሉ። እነሱም ሲጎዱ ሰውነት ብረት፣ ካልሲየምና ሌሎች አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን በበቂ ሁኔታ መምጠጥ ይቸገራል። የዚህን ጊዜ ሰውነት የእነኝህ ንጥረ ነገሮች እጥረት ያጋጥመዋል።


ስለዚህ ሴሊያክ በሽታ የሆድ ሕመም ብቻ ሳይሆን የሰውነትን አጠቃላይ ጤና ሊጎዳ የሚችል በሽታ ነው።


ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

ሴሊያክ በሽታ በሰዎች ላይ በተለያየ መንገድ ይታያል። አንዳንዶች የሆድ ምልክቶች ሲኖሯቸው፤ ሌሎች የሆድ ችግር ሳይኖራቸው ከምግብ ንጥረ ነገሮች እጥረት ጋር የተያያዙ ምልክቶች ሊታዩባቸው ይችላሉ።


የሆድና የአንጀት ምልክቶች፦

  • በተደጋጋሚ የሚከሰት ተቅማጥ፣

  • የሆድ መነፋትና ጋዝ፣

  • የሆድ ሕመም/ቁርጠት፣

  • ማቅለሽለሽ/ ማስታወክና፣

  • ሳይፈልጉ የሰውነት ክብደት መቀነስ ሊታዩ ይችላሉ።


ከሆድ ውጭ የሚታዩ ምልክቶች፦

  • የብረት እጥረትን ተከትሎ የሚመጣ የደም ማነስ (Anemia)፣

  • በቂ እንቅልፍ ቢወስዱም የሚሰማ ድካም።

  • የአጥንት ድክመትና የአጥንት ጥንካሬ መቀነስ( ከካልሲየም እጥረት ጋር ተያይዞ)፣

  • ከባድ ማሳከክ ያለው ሽፍታና፣

  • በልጆች ላይ የእድገት መዘግየት ሊታይ ይችላል።


አስገራሚው ነገር አንዳንድ ሰዎች ግልጽ የሆነ የሆድ ምልክት ሳይኖራቸውም፤ በሽታው ሊኖርባቸው መቻሉ ነው። ለምሳሌ በተደጋጋሚ የብረት እጥረት ማነስ የሚያጋጥማቸው ሰዎች ምክንያቱ ሴሊያክ በሽታ ሊሆን ይችላል።


ለምን አንዳንድ ሰዎችን ብቻ ይያዛል?

ሴሊያክ በሽታ ከዘረመል (Genetic) ጋር የተያያዘ ነው። ማለትም በቤተሰብ ውስጥ በሽታው ያለበት ሰው ካለ፤ በተለይም ወላጅ፣ ወንድም፣ እህት ወይም ልጅ ከሆነ፣ ሌሎች የቤተሰቡ አባላትም የመያዝ እድላቸው ከፍ ያለ ነው።


ነገር ግን ሴሊያክ በሽታ ያለባቸው ቤተሰቦች አሉ ማለት በሽታው ይይዛል ማለት አይደለም። በበሽታው የመያዝ እድልን ያሳድጋል እንጂ ብቻውን በሽታውን አያረጋግጥም።


እዚህ ላይ አንድ አስፈላጊ ነገር መለየት ያስፈልጋል። ዳቦ ከበሉ በኋላ የሆድ ሕመም መኖሩ ብቻ ሴሊያክ በሽታ አለብዎት ማለት አይደለም። የስንዴ አለርጂን ጨምሮ ሌሎች አንዳንድ በሽታዎች አንዳንድ ተመሳሳይ ምልክቶች ሊያሳዩ ይችላሉ። ለዚህም ከስንዴ ምግብ በኋላ ምልክት መኖሩን ብቻ ተመልክቶ ሴሊያክ በሽታ ነው ብሎ መደምደም አይቻልም።

ሴሊያክ በሽታ እንዴት ይመረመራል?

ምልክቶቹ ከተደጋገሙ ወይም ያልታወቀ የብረት እጥረት፣ የክብደት መቀነስና የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት ካለ የሕክምና ባለሙያን ማማከር ያስፈልጋል።


የጤና ባለሙያውም በመጀመሪያ የደም ምርመራ በማድረግ ሴሊያክ በሽታን የሚያመለክቱ አንቲቦዲዎችን (Antibodies) ሊመለከት ይችላል። በተለይም የtTG-IgA ምርመራ በብዛት ጥቅም ላይ ይውላል።


የደም ምርመራው በሽታውን የሚያመለክት ከሆነ በተጨማሪ ከትንሹ አንጀት ናሙና በመውሰድ ምርመራ ሊያደርግ ይችላል።


ከዚህም ባሻገር የምርመራው ውጤትና የሕመምተኛው ሁኔታ ተመልክቶ ዶክተሩ ተጨማሪ ምርመራ ሊያዝ ይችላል።


አስፈላጊ ማሳሰቢያ!

ሴሊያክ በሽታ እንዳለብዎት ከጠረጠሩ ምርመራ ከማድረግዎ በፊት ዳቦንና ሌሎች ግሉተን የያዙ ምግቦችን በራስዎ ውሳኔ አያቁሙ። ከምርመራ በፊት ግሉተንን ማቆም የደምና የአንጀት ምርመራ ውጤቶችን ሊያዛባ ይችላል።


ሕክምናው ምንድን ነው?

እስካሁን ሴሊያክ በሽታን ሙሉ በሙሉ የሚያጠፋ መድኃኒት የለም። ዋናው ሕክምና ግሉተን የያዙ ምግቦችን ከምግብ ዝርዝር ሙሉ በሙሉ ማስወገድ (Gluten-free diet) ነው።

ይህም ማለት፦

  • ከስንዴ የተዘጋጁ ዳቦ፣ ፓስታና ሌሎች ምግቦችን ማስወገድ።

  • ገብስና  ጥምዠ የያዙ ምግቦችን አለመመገብ።

  • በምግብ ውስጥ የተደበቀ ግሉተን እንዳይኖር የታሸጉ ምግቦችን ሲገዙ ይዘታቸውን ማንበብ።

  • ምግብ ሲዘጋጅ ግሉተን ካላቸው እህሎች ጋር እንዳይነካካ መጠንቀቅ ነው።


በአንፃሩ ጤፍ፣ ሩዝ፣ በቆሎና ማሽላ በተፈጥሮ በውስጣቸው ግሉተን አይይዙም። ስለዚህ ሴሊያክ በሽታ ያለባቸው ሰዎች እነዚህን መመገብ ይችላሉ። ነገር ግን ሲፈጩ ወይም ሲዘጋጁ ከስንዴ ጋር ከተቀላቀሉ በውስጣቸው ግሉተን ሊኖር ይችላል። ለዚህም የበሽታውን ምልክቶች ሊያሳዩ ይችላሉ።


በተጨማሪም የብረት፣ የካልሲየምና የሌሎች ቫይታሚኖች እጥረት ካለም በምርመራ ተለይቶ ተገቢው ሕክምና ይሰጣል።


አመጋገብ ላይ መጠንቀቅ (ግሉተን ነጻ የሆነ ምግብ መመገብ)፤ ምልክቶቹ እንዲቀንሱ ከማድረግም ባሻገር የተጎዳውን የአንጀት ክፍል እንዲያገግም ይረዳል።

ይህ የሴሊያክ በሽታ ያለባቸው ሰዎች የሕይወት ዘመን ሁሉ መከተል ያለባቸው ነው።

በመጨረሻ...

የስንዴ ምግቦችን ከበሉ በኋላ የሆድ ሕመም፣ ተቅማጥ ወይም መነፋት በተደጋጋሚ ካጋጠመዎት፤ ችላ ብለው አይለፉ።


ትክክለኛውን ምክንያት ለማወቅ የሕክምና ምርመራ ያድርጉ። ምርመራ ሳያደርጉ የስንዴ ምግቦችን በሙሉ ማቆም ትክክለኛውን በሽታ ለመለየት እንቅፋት ሊሆን ይችላል።


ጤናዎን ይጠብቁ፤ ምልክቶችን ከማስታገስ በፊት መንስኤያቸውን ይወቁ!

Comments


bottom of page