🩸 የደም አይነት እና አመጋገብ፡ ሳይንስ ወይስ ተረት ?
- Zebeaman Tibebu
- Jul 4
- 5 min read
ለበርካታ ዓመታት በአለም ዙሪያ የምግብ ገበታዎችን፣ የአመጋገብ ስርአቶችን ፣ የስነ ምግብ ክሊኒኮችን ያዳረሰ ሀሳብ አለ። ይህ ሀሳብ አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል አስተሳሰብንም ተጠናውቶታል። በማህበራዊ ድህረ ገጾች ያለገደብ ተሰራጭቷል።
ይህም የደም አይነት እና የአመጋገብ ቁርኝት ነው።

ከዚህ በፊት ሰምተውት ከነበረ ፤ የሚገርም አሳማኝ ይመስላል አይደል? ሳይንሳዊ ሀሳብ ሆኖ ከመቅረቡም ባሻገር ፣ ምስክርነት የሚሰጡለት ሰዎችን በማህበራዊ ድህረገጾች አይተናል።
ደምዎት ኦ አይነት ከሆነ ስጋ ያለባቸውን ምግቦች እንዲያዘውትሩ ፤ ኤ ከሆነ ደግሞ የእጽዋት ምግቦችን እንዲመገቡ ይመከራል።
ይህ ግን በሳይንስ የሚደገፈው ምን ያህል ነው ብለው ያስባሉ? ያሉን ሳይንሳዊ ጥናቶችስ ምን ይላሉ?
🧬 የደም ዓይነት ምንድን ነው?

ይህንን ለመረዳት የደም ዓይነት ምንድን ነው የሚለውን ማወቅ ይኖርብናል።
ሰውነታችን በውስጡ ካሉ በትሪሊየን ከሚጠጉ ህዋሳት መሀከል ፤ የደም ህዋሳት ከፍተኛ መጠኑን ይወስዳሉ። የቀይ የደም ህዋሳት ዋነኛ ስራቸው ኦክስጅን ማመመላለስ ሲሆን ፤ በአንድ አንድሚሊየነኛ ሊትር ውስጥ በአማካይ ወድ 5 ሚሊየን የቀይ ደም ህዋሳት ይገኛሉ።
እኛ ስራ ቦታ ላይ እንደምናጠልቀው መታወቂያ ወይም ባጅ እነኝህ ቀይ የደም ህዋሳት የ ፕሮቲን መለያ ባጅ (አንቲጅን) አላቸው። ያላቸውንም የአንቲጅን/መታወቂያ አይነት መሰረት በማድረግ ፤ የደም አይነትን እንለያለን። በዚህም ተመስርቶ ብዙ አይነት ስርአቶች ቢኖሩም ፤ በዋነኝነት የምንጠቀማቸው የደም አይነት መለያ ስርአቶች ሁለት ናችው።
ኤቢኦ (ABO) ስርአት ፡ ይህም የ ኤ፣ ቢ፣ ኤቢ እና ኦ አንቲጅኖች ተጠቅሞ ይለያል።
የ አር ኤች (Rh) ስርአት፦ ይህም አር ኤች መታወቂያ (አንቲጅን) የያዙትን ፖዘቲቭ ስንል (Rh-positive (+) ) ፤ ያልያዙትን ኔጌቲቭ (Rh-negative (−)) በማለት እንለያለን።
ታድያ በመደበኛነት ሁለቱን የደም አይነት ስርአቶች አቆራኝተን የደም አይነትን ኤ+ ፣ ኦ−፣ ወ.ዘ.ተ... በማለት ልንለይ እንችላለን።
👉 ያስተውሉ እነዚህ አንቲጂኖች እያንዳንዱ ቀይ የደም ሴል ላይ ያሉ ጥቃቅን ባጅ/መታወቂያ አይነት ምልክት ናቸው። በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት የሰውነታችንን ህዋሳት እና ከእንግዳ ህዋሳትን ለመለየት እነዚህን ባጅዎች ይጠቀማሉ።
💡 ይሁን እንጂ ነገሩ ይህ ነው፦ እነኝህ ልዩ ባጆች/መታወቂያዎች የቀይ የደም ህዋስ ላይ ብቻ የሚገኙ ምልክቶች ናቸው። ሌላ የሰውነት ህዋሳት ላይ የሉም ። የምግብ መፈጨትን፣ የምግብ መዋሃድን ወይም ስውነታችን ገንቢ ንጥረ ነገሮችን የመቀበል/ የመቃወም ሂደት አይቆጣጠሩም።
ታድያስ የቀይ የደም ህዋስ ላይ ያለ መታወቂያ ላይ ተመስርቶ ፤ አመጋገብ ስርአትን መወሰን ይቻላልን?
🌱 የደም ዓይነትና አመጋገብን ያቆራኘው መላምት የመጣው ከየት ነው?
ይህ ሀሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበው እንደፈረንጆቹ በ1996 በ ዶክተር ጴጥሮስ ዲ'አዳሞ መፅሃፍ ነው። የመጽሀፉ ርዕስ ለደምዎ አይነት በስርአት ይመገቡ (eat right for your type) የሚል ሲሆን፤ ፅንሰ ሃሳቡ የአመጋገብና የደም አይነትን ቁርኝት ያመላክታል።

የመጽሀፉ መላምት እንደሚያመላክተው ከሆነ
"እያንዳንዱ የደም አይነት ከሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ (evolution) ጋር የተቆራኘ ነው። በተለያየ ጊዜ የመጡ የዘረመል (ጄኔቲካዊ) ለውጦች የተለያዩ በሰው ልጆች መሀል የተለያዩ የደም አይነቶች እንዲፈጠሩ አስችለዋል። ታድያ ይህ የዘረመል ለውጥ የመጣባቸው ወቅት ላይ ፤ አባቶቻችንን ሲመገቧቸው የነበሩትን ምግቦች ብንመገብ ለሰውነታችን ጠቃሚ ነው። ይህም ከምንመገበው ምግብ ውስጥ ፤ ያሉትን ንጥረ ነገሮች ሰውነታችን በይበልጥ እንዲጠቀም ያስችለዋል። በዚህ የተነሳ አበላላችን ከደም አይነታችን ጋር መመሳሰል አለበት። " ብለው መላምታቸውን ያሰፍራሉ።
በመጽሐፉ መሰረት -
🩸 አይነት O "አዳኙ"፡ የመጀመሪያው የደም አይነት ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን። የዛን ጊዜ የሰው ልጅ የእንሰሳት ተዋእጾን አብዝቶ ይመገብ ነበር። ለዚህም ይህ ደም ያለባቸው ሰዎች፤ የከፍተኛ-ፕሮቲን ያላቸው ምግቦችን መመገብ ይኖርባቸዋል። ስጋ ቢያዘውትሩ ይመከራል።
🩸 አይነት A "ገበሬው"፡ ይህ ደግሞ የሰው ልጅ ከ አድን እና ከጫካ ወጥቶ አርሶ መብላት የጀመረ ሰአት የመጣ የደም አይነት ነው ተብሎ ይታሰባል። ለዚህም ይህንን የደም አይነት ያለባቸው ሰዎች ፤አዝእርቶችን ቢያዘውትሩ ይመከራል።
🩸 ዓይነት B ፦ "ዘላኑ" : ይህ ደግሞ የሰው ልጅ ፍልሰት የጀመረበት ሰአት ላይ የመጣ የደም አይነት ነው ተብሎ ይታሰባል። ስለዚህ የዘላኖች አይነት አመጋገብ ማለትም የእንሰሳትም የ እጽዋትም ምግብ ቢመገቡ መልካም ነው። ይህ ደም ያላቸው ሰዎች ከወተት ተዋጽኦ ማዘውተራቸው ጠቃሚ ነው።
🩸 አይነት AB "ዘመናዊ" - ይህ በዝግመት ለውጥ በቅርብ ጊዜ የመጣ የደም አይነት ሲሆን ፤ የ A እና B ድብልቅ ነው። ይህም በፍልሰት ወቅት ኤ እና ቢ የደም አይነት ያላቸው ህዝቦች ሲደባለቁ የመጣ ነው ተብሎ ይታሰባል።
የእነኝህ የደም አይነቶች መብላት፣ መጠጣት እንዲሁም ማስወገድ ያለባቸው የምግብ አይነቶች ዝርዝር ሰፊ ነው። ይህ የ ዶክተር ዲ አዳሞ ጥንሥሥ ሀሳብ የያዘ መጽሐፍ ሲሆን ፤ በተጽእኖ ፈጣሪዎች እና አንዳንድ ግለሰቦች ይህ ዝርዝር በተለያየ መልኩ ተለውጦ ሊገኝ ይችላል።
በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ይህንን መላምት ተቀብለዋል ። በጤና ላይ ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችም አሞግሰውታል ። እንደውም ይህ አመጋገብ ሕይወታቸውን እንደለወጠ ሲምሉ ሲገዘቱ የሚታዩም አሉ ።
ማንኛውም ሀሳብ ከመላምት ወደ ሳይንሳዊ እውነታ ለመሻገር በ ጥናታዊ ጽሁፎች መደገፍ ይኖርበታል።
እዚህ ጋር ግን ጥያቂ እንጠይቅ
እንደ አለም አቀፍ የደም ልገሳ ማህበረሰብ ከሆነ 47 የደም መለያ ስርአቶች አሉ (ሁለቱን እላይ ጠቅሰናቸዋል)። ታድያ ከእነኝህ ሁሉ የ መለያ ስርአቶች እንዴት አንዱ ብቻ የዚህ መላምት መሰረት ሆነ? ሌሎቹ በዝግመታዊ ለውጥ የመጡ አይደለምን?
አንድ የወተት አለርጂ ያለበት የ ቢ የደም አይነት ያለው ሰውስ አመጋገብ ምን ላይ ይመስረት?
እንዴትስ ምግብን ከማይቆጣጠር ኦክስጅንን ብቻ ከሚሸከም ህዋስ ላይ ያለ ባጅ ፣ የምግብ መፈጨት ስርአትን ሊወስን ቻለ?
ይህ ማለት የጎረቤትዎን መልክ አይቶ ስለ እርስዎ ቤተሰብ ማውራት አይሆንምን?
🔬 ጥናቶች ምን ይላሉ?
ይህ አስተሳሰብ ምንም ያህል የተወደደ ቢሆንም ፤ ጥናታዊ ጽሁፎች ይህንን አይደግፉም። ከተደረጉ ጥናቶች ውስጥ ትልቁ ፤ የዛሬ አስር አመት በፊት በፕሎስ ዋን (PLOS ONE (2014) የታተመ ፤ በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተገኘ ነው። ይህ ጥናት 1,400 ሰዎች ላይ የተደረገ ሲሆን ፤ ዋነኛ ግኝቶቹ የሚከተሎት ናቸው።
ይህ አስተሳሰብ የሚመክረው ፤ የጤናማ የአመጋገብ ልማድን (እንደ አትክልት፣ አዝዕርት፣ አነስተኛ የታሸጉ ምግቦችን) የተከተሉ ሰዎች፤ የደም ዓይነት ምንም ይሁን ምን የተሻለ ጤንነት አሳይተዋል።
ሆኖም ግን የተሻለ የጤና ደረጃ መሆናቸው ፤ በደም ዓይነት ላይ ከተመሰረተ የአመጋገብ ሥርዓት ጋር አልተገናኘም።
በሃርቫርድ የሕክምና ትምህርት ቤት፣ በብሪታንያ የስነ ምግብ ማኅበርም የተደረጉ ጥናቶች ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።
የደም ዓይነት አመጋገብን ለመወሰን እንደሚችል የሚያሳይ ሳይንሳዊ ማስረጃ የለም።
🧙🏾 ♀️ ትርክቶች እና የህክምና እውነታዎች
በዚህ ዙሪያ የተነሱ ጥቂት ሀሳቦችን እንመርምር።
ሀሳብ | ተረት ወይስ እውነታ? |
አአይነት O ሰዎች ስጋን በተሻለ መንገድ ይፈጫሉ | ❌ ተረት |
አይነት A ህዝብ አነስተኛ የሆድ አሲድ አለው | ❌ ተረት |
በብዙ ምግቦች ውስጥ የሚገኙት ሌክቲን (የፕሮቲን አይነት) የሚባሉት ንጥረነገሮች አፈጫጨት ፤ እንደየደም አይነቱ ይለያያል። | ⚠️ በከፊል እውነታ አለው። የሌክቲን ፕሮቲኖች ከደም አይነቶች ጋር የተለያየ መስተጋብር አላቸው። ሆኖም ግን ይህ አመጋገብ ጋር አይያዝም። አመጋገብን አይወስንም። |
አይነት AB በባህሪው መንፈሳዊ/ስሜታዊ አይነት ነው | ❌ ተረት |
🍽️ ታዲያ አንዳንድ ሰዎች በእነዚህ የአመጋገብ ዓይነቶች የተሻለ ስሜት የሚሰማቸው ለምንድን ነው?

ምላሹ ቀላል ነው። ይህ መላምት የሚመክራቸው አመጋገቦች ጤናማ አመጋገብ ስርአት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። የታሸገ ምግብ እንዲቀንሱ ፣ የተፈጥሮ ግብአቶችን እንዲጠቀሙ ፣ አለመጠን የበሰሉ ምግቦችንና የዘይት አይነታቸው ጤናማ ያልሆኑ የተጠበሱ ፈጣን ምግቦችን (fast foods) እንዲያስወግዱ ይመክራል። እንዲሁም በቤት ውስጥ የሚዘጋጁ ተጨማሪ ምግቦችን እንዲያዘወትሩ ይመክራል።
ይህንን አመጋገብ ስርአት ከተጠቀሙ ጤናማ ይሆናሉ። አመጋገብ ስርአቱ የተወገዱ የምግብ አማራጮች (ለምሳሌ ቀይ ስጋ)ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮችን መተኪያ የምግብ አማራጮችንም (ለምሳሌ የእጽዋት የፕሮቲን ምንጭ) ይመክራል። ለዚህም ጤናማ ምግብ እንዲመገቡ ያደርጋል።
መልካሙ ውጤቱ ፤ ከደምዎ ጋር ሳይሆን ከልማድዎ ጋር የተያያዘ ነው።
⚖️ ታድያ የአመጋገብ ስርአትዎን በምን ላይ የተመሰረተ ይሁን?
የአመጋገብ ስርአትዎን ቀይ የደም ህዋስ ላይ የሚገኝ መለያ ባጅ (አንቲጅን) ላይ ከመመስረት ይልቅ ፤ በሚከተሉት ላይ ያስመርኩዙ፡
🧬 ጀነቲክስ/ዘረመል
🦠 የምግብ ቱቦ ላይ ያሉ መልካም ባክቴሪያዎች ስርጭት
🍽️ የሰውነቶት ኡደት ፍጥነት (ሜታቦሊክ)
🧪 ባለብዎ የህክምና ሁኔታዎች (ለምሳሌ የስኳር በሽታ፣ የደም ግፊት፣ የሴሊያክ ህመም ፣ የ ወተት አለርጂ ፣ የሀሞት በሽታ ፣ ወ.ዘ.ተ...)
🎯 በአኗኗር ዘይቤዎት እና የሕይወት ግብዎ
👩 ⚕️ በስነ ምግብ እና የሕክምና ባሉሙያ የተሰጠ የአመጋገብ ምክር
የደም ዓይነትስ?
የደም አይነት ደም በመስጠት ረገድ በጣም አስፈላጊ ነው ። በምግብ እቅድዎ ውስጥ ግን አይደለም።
🩺ማሳረጊያ ሃሳብ
ይህ አስገራሚ መላምት እንጂ የህክምና እውነታ አይደለም።
የደም ዓይነትዎ ለሰውነትዎ የሚገባውን ፍጹም የአመጋገብ ልማድ እንደሚወስን ለማመን ቀላል ነው።
የደምዎ አይነት በ ድንገተኛ ክፍል ፣ በአይሲዩ ፣ በ ቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ ሊጠቅም ይችላል። በገበታዎ ላይ ግን ትርጉም የላቸውም።
ጤና ደግሞ ፈጽሞ ስለ አቋራጭ መፍትሔ አይደለም።
በማስረጃ ላይ የተደገፉ ፣ በሳይንስ የሚመከሩ የጤና መፍትሔዎች ያስቡ።
እንደ ንፋስ ገነው በሚጠፉ ኢ፟ሳይንሳዊ የጤና መፍትሔዎች(ፋሽኖች) አይታለሉ።
Comments