ትርፍ አንጀት በሽታ: ምልክቶቹ እና አደጋዎቹ
- Zebeaman Tibebu
- 8 hours ago
- 4 min read
እስቲ አስቡት ... ተራ ያሉት የሆድ ህመም በድንገት ሲያጣድፍዎ!
ሲጀምር መለስተኛ የሆድ ህመም ይመስላል። ህመሙም እምብርት አከባቢ ይሰማል....በሰአታት ውስጥ ህመሙ እየጠነከረ /እየባሰ ይመጣል። ቀስፎ ይይዛል።
እምብርትዎ ጋር ያለው ህመም ጋብ ሲል ፤ በቀኝ በኩል ታችኛው ሆድዎ ላይ ቀስሮ ይይዛል!
ይህን ህመም ችለው ለማሳለፍ የሚሞክሩ ብዙዎች አሉ። ሆኖም ግን ድንገተኛ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ህመሞች ውስጥ አንዱ ነው። ህይወት እስከማጣት ሊያደርስ ይችላል።
ይህ ተጓዥ ህመም ፤ አሁንም ችላ ካሉት ፤ ህክምና እርዳታ ካላገኙ ፤ በሰአታት ውስጥ የቀኝ የታችኛውን ሆድ ክፍል ትቶ መላ ሆድን ወጥሮ ይይዛል። ሙሉ ሆድዎ ይደድራል። ህመሙ ከባድ ስለሆነ ሆድም አያስነካም!
እዚህ ጋር ሳይደርስ ህክምና ማድረግ ነበረብዎ። አሁን አደገኛ ደረጃ ደርሷል! በህይወት ለመቆየት ያለዎት ሰአታት ሊሆን ይችላል። እጅጉን አፋጣኝ የሆነ ህክምና ያስፈልግዎታል።
ፈጽመው እንዳይዘናጉ! እያንዳንዷ ድቂቃ ለእርስዎ ህይወት ዋጋ አላት።
አዎ! ቀላል የመሰለ የሆድ ህመም ፤ በድንገት እንዲህ የከፋ ደረጃ ያደርሳል። ይህ የትርፍ አንጀት በሽታ ነው። ብዙዎችም ህመሙን ለይተው ስለማያውቁት ይዘናጋሉ። ታዋቂዋ የፖፕ ሙዚቃ ዘፋኙዋ ኬሊ ክላርክሰንም ህመሟን ችላ ብላው ነበር።

ታሪኩ እንዲህ ነው።
ይህች እውቅ ዘፋኝ የአሜሪካ የዘፈን ደረጃ ሰንጠረዥን (ቢል ቦርድን) ሽልማት ፕሮግራምን እንድትመራ በ2019 ተመርጣ ነበር። ታድያ ግን መድረኩን በመራችባቸው ሶስት ሰአታት ውስጥ ከፍተኛ የሆድ ህመም ላይ ነበረች። ህመሙም ቀድም ብሎ የጀመራት ቢሆንም ፤ እምብዝም ቦታ አልሰጠቸውም ነበር። ታድያ መድረኩን በምትመራበት እለት እጅጉን ባሰባት።
መደረኩን እንደምንም ብላ ጨርሳ ፤ በአፋጣኝ በሎሳንጀለስ ግዛት በሚገኘውየሴዳር ሳይናይ ሜዲካል ሴንተር ለምርመራ ሄደች። ምርምራውም ትርፍ አንጀት በማሳየቱ ፤ መድረኩን በመራች በማግስቱም ጠዋት ድንገተኛ የቀዶ ህክምና ተደረገላት። በቀጣይ ቀናትም ከበሽታዋ ልታገግም ችላለች። ቆየት ብላ በመሄዷ ግን የማገገም ጊዜዋ የተራዘመ እና እክል የሞላበት ሆኖ ነበር።
ታድያ ለ መረጃ ቅርብ ይሆናሉ ብለን የምናስባቸው ታዋቂ ሰዎች እንኳን እንደዚህ ዝንጉ ከሆኑ እርስዎ ላይ ላይፈረድ ይችል ይሆን?
ጉዳዩ ግን የመፍረድ አይደለም። ችላ ያሉት የሆድ ህመም ፤ ህይወትዎን ሊያስከፍል ይችላል። ተፈረድብዎ... አልተፈረደብዎ ህመሙን የሚችሉት ፤ የሚሰቃዩት እርስዎ ነዎት። ስለዚህም ዛሬውኑ ግንዛቤዎን ያስፉ።
እስቲ ፤ ስለትርፍ አንጀት በጥልቀት እናንሳ።
👉ትርፍ አንጀት ምንድን ነው?
ትርፍ አንጀት የትንሹ አንጀት ማብቂያ ፤ የትልቁ አንጀት መጀመሪያ ላይ ፤ እንደ ጉጠት(ወይም ጣት) አፈንግጦ የወጣ የአንጀት ክፍል ነው። ለዚህም ስሙ ትርፍ አንጀት (appendix)ይሰኛል።
ይህም ክፍል ስራው ምግብ መፍጨት አይደለም። ይልቁኑ ቅርብ ላይ ያሉ የአንጀት ክፍሎችን የሚጠብቁ ፤ የበሽታ መከላከያ ስርአቶች መከማቻ ስፍራ ነው። እርሱም ብዙ የበሽታ መከላከያ ስርአት ህዋሳት በውስጡ ስላሉት ፤ በቀላሉ ይቆጣል።

አንጀት ደግሞ በባህሪው ብዙ በሽታ አምጪ ተህዋሳትን የያዘ የሰውነት ክፍል ነው። ታድያ እነኝህ በሽታ አምጪ ተህዋሳት ወደ ትርፍ አንጀት ከደረሱ ትርፍ አንጀት ይቆጣል።
አንዳንድ ጊዜ ደግም በምግብ ቁራጮች ፤ አልያም በአንጀት ተረፈ ምርቶች የትርፍ አንጀት ጫፍ ሊደፈን ይችላል። ይህን ጊዜ ትርፍ አንጀት አብዝቶ ይቆጣል።
ይሄኔ ነው የትርፍ አንጀት በሽታ አለ የምንለው።
📊 ስርጭቱ ምን ይመስላል?
በአለም ዙሪያ በየአመቱ ወደ 17 ሚሊየን ሰዎች በዚህ በሽታ ይጠቃሉ። ከ10 ሰዎች ውስጥ አንዱም በህይወት ዘመኑ የትርፍ አንጀት በሽታ ያጋጥመዋል ተብሎ ይገመታል። ህሉንም የእድሜ ክልል ሊያም ቢችልም ፤ ይህ በሽታ ብዙ ጊዜ የሚታየው 10 እስከ 30 አመት እድሜ ያሉ ሰዎች ላይ ነው። ከሴቶችም አንጻር በወንዶች ላይም በብዛት ይስተዋላል።
😣 ችላ ሊሏቸው የማይችሏቸው የተለመዱ ምልክቶች
ትርፍ አንጀት ብዙውን ጊዜ ምልክቶቹ ይህን ይመስላሉ።
✔ ሲጀምር እምብርት አከባቢ የሚሰማ መለስተኛ የሆድ ህመም
✔ ከሰአታት በኋላ ይህ የሆድ ህመም በቀኝ በኩል ወደ ታችኛው የሆድ ክፍል ያመራል። (ይህ ህመሙ መባሱን አመላካች ነው።)
✔ ከዚህ የሆድ ህመም ጋርም አብሮ
ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ
የምግብ ፍላጎት ማጣት
ትኩሳት /ብርድ ብርድ ማለት
ራስ ምታት
ቀኝ ታችኛው ሆድ ላይ ሲነካ ማመም ሊኖር ይችላል።
ህመሙ ሲባባስም ✔ ሙሉ ሆድ ይደድራል።
✔ ሆድ የማያስነካ እጅጉን ከባድ ህመም
✔ እንዲሁም ራስ መሳት ሊኖር ይችላል።
እነኝህን ምልክቶች ካዩ በአፋጣኝ የህክምና እርዳታ ይፈልጉ። መቼም እንዳይዘናጉ። ህይወትዎን ለማትረፍ ያለዎት ሰአታት ብቻ ሊሆን ይችላል።
🚨 አፋጣኝ ህክምና ለምን ያስፈልጋል?

ትርፍ አንጀት በሽታ ቀደም ብሎ ከታከመ በቀዶ ጥገና ወይም አንዳንድ ጊዜ በአንቲባዮቲኮች ሊድን ይችላል። መዘግየት የትርፍ አንጀት መቆጣት እንዲባባስ ያደርጋል።
ይህም የተቆጣ ትርፍ አንጀት ሊፈነዳ ይችላል። ሆድ ውስጥ ሲፈነዳ ፤ በሽታውን ያመጡት ባክቴሪያዎች እና የቤዝ ባህሪ ያላቸው የአንጀት ፈሳሾች ወደ ሆድ እቃ ይፈሳሉ። እነኝህም የሆድ እቃ ኢንፌክሽን ያመጣሉ። ሀሞትን ጨምሮ ሌሎች የአንጀት ኬሚካሎችም በራሳቸው የሆድ እቃ መሸፈኛን ያስቆጣሉ። በሽታው እጅጉን ይባባሳል።
ባክቴሪያዎችም ከሆድም አልፈው ወደ ደም ውስጥ ይገባሉ። ይህን ጊዜ የደም ውስጥ ኢንፌክሽን ያመጣሉ። ይህም ከፍተኛ የሞት አደጋ ያለው በሽታ ነው።
ታድያ ይህ ሁሉ ሳያጋጥም ፤ ቀድሞ ህክምና ቢያደርጉስ? ህይወትዎን አያድኑም?
🔬 የትርፍ አንጀት በሽታን እንዴት ማወቅ ይቻላል?
ትርፍ አንጀት በሽታን ለማወቅ በይበልጥ የሚከተሉትን ምርመራዎች ያስፈልጋሉ።
✔ የዶክተር አካላዊ ምርመራ (ይህ ዋነኛውና ፤ እጅግ ጠቋሚ የሆነው ምርመራ ነው።)
✔ ኢንፌክሽን መኖሩን ለመመልከት የሙሉ ደም ምርመራም (CBC) ያስፈልጋል።
ለወንዶች እነኝህ ሁለቱ ብቻ በቂ ሊሆኑ ይችላሉ። ለሴቶች እና አንዳንድ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ፤ አልትራሳውንድ ምርመራ ሊታዘዝም ይችላል።
🛠 የህክምና አማራጮቹስ ምን ይመስላሉ?
የትርፍ አንጀት በሽታ የሚከተሉት የህክምና አማራጮች አሉት።

🔹 ትርፍ አንጀትን በቀዶ ህክምና ማስወገድ (Appendectomy)
ይህ ተመራጩ ህክምና ነው። ይህ የተቆጣውን ትርፍ አንጀት በቀዶ ህክምና በምስሉ እንደሚታየው ቆርጦ ማውጣት ነው።
ቀዶ ህክምናውም ቀላል ሲሆን ፤ ታካሚም ቢበዛ በሁለተኛ አልያም ሶስተኛ ቀን ከሆስፒታል አገግሞ ይወጣል። ይህም የቀዶ ጥገና የተለያዩ አይነቶች አሉት።
🔹 የባክቴሪያ መቃወሚያ (አንቲባዮቲክስ) እና የድጋፍ ህክምና
አንዳንዴ እንደ ዶክተሩ እይታ ፤ ትርፍ አንጀት የተጠረጠሩ ታካሚዎች ሆስፒታል ውስጥ ተኝተው ፤ አንቲባዮቲክስ እና የድጋፍ ህክምና ሊደረግላቸው ይችላል። ይህ ግን የሚደረገው የቀዶ ጥገና በአፋጣኝ ማድረግ የሚቻልበት ሆስፒታል ውስጥ ብቻ ነው። ይህም ውሳኔ በዶክተሩ ህክምናዊ እይታ ላይ ይወሰናል።
💥 በቀዶ ጥገና ጊዜ ምን ሊያጋጥም ይችላል?

የቀዶ ህክምናውን ተከትሎ የሚከተሉት ተጓዳኝ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። እነኝህ ችግሮች የማጋጠም እድላቸው እጅጉን አናሳ ነው። ታድያ ግን ዘግይተው ህክምና እርዳታ ለሚያገኙ ሰዎች ፤ የማጋጠም እድላቸው ያየለ ይሆናል። የተለመዱትም ተጓዳኝ ችግሮች የሚከተሉት ናቸው።
🔹 የቀዶ ጥገና ቦታ ኢንፌክሽን (በጣም የተለመደ ነው)
🔹 የሆድ ድርቀት ወይም ሆድ ውስጥ የሚከማቹ ፈሳሾች
🔹 አንጀት መስራት ማቆም (ileus) (ይህ ጊዜያዊ ሲሆን ፤ አንጀት ወደ ቀድሞ ስራው ይመለሳል።)
🔹 አርፍደው ሄደው ከሆነ ፤ ደም ውስጥ የተሰራጨ ኢንፌክሽን (sepsis) ሊያጋጥምም ይችላል።
🧠ፈጽሞ ማድረግ የሌለብዎ ነገሮች
እነኝህን ፈጽመው እንዳያደርጉ!
👉ፈጽሞ ችላ አይበሉ። እንደ ቀላል የሆድ ህመም ጀምሮ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን ፈጽሞ እንዳይዘናጉ። ከተጠራጠሩ እንኳን ፤ ሳይውሉ ሳያድሩ የሕክምና ዕርዳታ ይፈልጉ።
👉 ምልክቶቹን ካዩ የህመም ማስታገሻ ፈጽሞ እንዳይወስዱ። በሽታውን ደብቀው ህክምናን ያዘገያሉ። ለዚህም ከምርመራ በፊት ህመም ማስታገሻ መውሰድ የተከለከለ ነው።
💡 መቼም እንዳይዘናጉ!
የሆድ ህመም ሁሉ ቀላል አይደለም። አንዳንዴ ህይወት ያስክፍላል!
ግንዛቤው ህይወታቸውን ሊያድን ይችላልና ፤ በዙሪያዎ ላሉ ሰዎች ይህንን ትምርታዊ ጽሁፍ ያጋሩ።





Comments