🔥ስለ ጨጓራ ቁስለት ማወቅ ያለብዎ ነገሮች?
- Zebeaman Tibebu
- 4 days ago
- 3 min read
በብዙዎች ዘንድ ከእንብርት በላይ ያለ የሚቃጠል የሆድ ህመም ይህን ያህልም ቦታ አይሰጠውም።
“ቡና አብዝተህ ይሆናል”
“ጭንቀት ነው” ተብሎ ይታለፋል።
የበላሁት ምግብ ነው ብለውም የሚበሉትን የምግብ አይነት የሚለውጡም አሉ። ለእንደዚህ አይነት ህመም ደግሞ ፤ ሽሮ ፍትፍትማ ፍቱን ነው!

እነኝህ አስተሳሰቦች እውነታ ቢኖራቸውም ፤ ከዚህ ተራ ከሚመስል ምቾት ማጣት በስተጀርባ ፣ ጠለቅ ያለ ነገር እየተፈጠረ ቢሆንስ?
ጨጓራ እየቆሰለ ሊሆን ይችላል!
በጨጓራ ወይም በትንሹ አንጀት ግድግዳ ላይ በዝምታ የሚፈጠር ቁስል ሊሆን ይችላል። ይህ ቁስል በህክምና "ፔፕቲክ አልሰር" (PUD) ይባላል። ስለ እርሱ ማወቅ ለጤናዎ እጅግ ጠቃሚ ነው።
ለመሆኑ የጨጓራ ቁስለት ምንድን ነው?
በሰውነታችን ውስጥ ጨጓራ ስጋን ማድቀቅ የሚችል ጠንካራ አሲድ ያመነጫል። ይህ አሲድም በጨጓራ ውስጥ የሚገባውን ምግብ ዱቄት ያደርጋል፤ ያልማል። አሲዱም ምግቡን እያላመ ከጨጓራም ባሻገር ፤ ወደ ትንሹ አንጀት የመጀመሪያ ክፍል (ዱዎዲነም) ይደርሳል።
ስጋን የሚያደቅ ፤ ይህ ጠንካራ አሲድ ለምን ራሱን ጨጓራን አይበላውም?
ይህ ኃይለኛ አሲድ ከምግቡ አልፎ እራሱን እንዳይበላው ሰውነታችን በተፈጥሮ ራሱን የሚከላከለበት ብልሀት አለው። ይህም ፦
ጨጓራችን በወፍራም ንፍጥ በመሰለ (Mucus) ሽፋን የተከለለ ነው። ይህም አሲዱ የጨጓራ ግድግዳ ጋር እንዳይደርስ ይከልለዋል።
አንጀት ጋር ደርሶ አንጀትን እንዳይበላ ደግሞ አንጀት አከባቢ ያሉ ህዋሳት ባይካርቦኔት የሚባል አሲዱን የሚቃረን ውህድ ያመነጫሉ።
ከዚህም ባሻገር ጨጓራ አከባቢ ያሉ ህዋሳትን ቶሎ ማደስ እንዲቻል በአከባቢው ተገቢ የደም ዝውውር አለ።

ታድያ ቁስል የሚፈጠረው ፤ ይህ የመከላከያ ሥርዓት ሲፈርስ ነው። አሲዱ የጨጓራን ግድግዳ በቀጥታ ሲያገኘው ያስቆጣዋል። ከመቆጣትም አልፎ ይቆስላል። ይህን ጊዜ የጨጓራ ቁስለት አጋጠመ ይባላል።
ይህ ቁስል በሁለት ዋና ቦታዎች ይከሰታል፦
በጨጓራ ግድግዳ ውስጥ → የጨጓራ ቁስለት(Gastric ulcer) ይባላል።
በትንሹ አንጀት መጀመሪያ ክፍል → የዱዎዲነም(ልዩ ስሙ) ቁስለት (Duodenal ulcer) ወይም "የአንጀት ቁስል" ይባላል።
ሁለቱም በአንድ ላይ የጨጓራ አሲድን ተከትሎ የሚመጣ ቁስለት(peptic ulcer disease/ pud) ይሰኛሉ። በተለምዶ በወል የጨጉራ ቁስለት ይባላሉ።
ጨጓራ ወይስ የትንሹ አንጀት ቁስለት? የቱ ነው ያለብኝ?

ሁለቱም በአሲድ ጉዳት ቢከሰቱም፣ በሰውነት ላይ ያላቸው ባህሪ ይለያያል።
የጨጓራ ቁስል (Gastric ulcer)፦
ምግብ እንደበሉ ወዲያው ያማል። ምግብ መብላት አሲድ እንዲመነጭ ስለሚያደርግ የቆሰለውን የጨጓራ ግድግዳ ያቃጥለዋል። ታካሚዎች ምግብ ከበሉ ከ30 ደቂቃ በኋላ ህመሙ እንደሚብስባቸው ይገልጻሉ። ምግብ መብላት ህመም ስለሚያመጣባቸው፤ ምግብ መመገብ ይቀንሳሉ። ለዚህም የክብደት መቀነስ የተለመደ ምልክት ነው።
የትንሹ አንጀት ቁስል (Duodenal ulcer)፦
በተቃራኒው ጨጓራ ባዶ ሲሆን (ከተመገቡ ከ2-3 ሰዓት በኋላ ወይም እኩለ ሌሊት ላይ) ያማል። ምግብ ሲበሉ ህመሙ ለጊዜው ይጠፋል። አንዳንድ ታካሚዎች ህመሙን ለማስታገስ በተደጋጋሚ ስለሚበሉ ክብደት ሊጨምሩ ይችላሉ።
ምን ያህል የተለመደ ነው?
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ5-10% የሚሆኑ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ በሆነ ወቅት ለጨጓራ ቁስለት ይጋለጣሉ። በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በበሽታው ይጠቃሉ።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የአፍሪካ አገሮች የበሽታውን ጫና ከፍ ያለ ነው። ይህም የጨጓራ የባክቴሪያ ስርጭት ከፍተኛ ከመሆኑ ፤ ያለ ሀኪም ትእዛዝ የህመም ማስታገሻዎች በስፋት ጥቅም ላይ ከመዋላቸው እና የጨጓራ ኢንዶስኮፒ ምርመራ አገልግሎት በቀላሉ ካለመገኘቱ ጋር የተያያዘ ነው።
መንስኤዎቹ
ለብዙ አሥርተ ዓመታት የጨጓራ ቁስለት በጭንቀትና በሚያቃጥል ቅመም ብቻ ይመጣል ተብሎ ይታመን ነበር። ዘመናዊ ሕክምና ያንን ግንዛቤ ቀይሮታል። ለብዙ ታማሚዎች ሁለት ዋና መንስኤዎች አሉ፦
1. የጨጓራ ባክቴሪያ (H. pylori)

ይህ ባክቴሪያ በጨጓራ ግድግዳ ላይ ይኖራል። የጨጓራን መከላከያ ሽፋንን በመብላቱ፤ ጨጓራ በቀጥታ ለአሲድ ጥቃት ያጋልጣል። ይህንን ባክቴሪያ ኢንፌክሽን በማከም ጨጓራ ቁስለትን በቋሚነት መፈወስ ይቻላል።
2. የህመም ማስታገሻዎች (NSAIDs)

እንደ ኢቡፕሮፌን (Ibuprofen)፣ ዲክሎፌናክ (Diclofenac) እና አስፒሪን (Aspirin) ያሉ መድኃኒቶች የጨጓራን ግድግዳ የሚጠብቁ ንጥረ ነገሮችን (Prostaglandins) ያግዳሉ። በዚህ ጊዜ አሲድ በቀላሉ ቁስል ይፈጥራል። ለዚህም እነዚህን መድኃኒቶች ለረጅም ጊዜ መጠቀም ለጨጓራ አደገኛ ሊሆን ይችላል።
ይህ ቁስለት ምን ዓይነት ስሜት አለው?

ዋነኛው ምልክት በሆድ የላይኛው ክፍል ላይ የሚሰማ የሚቃጠል ስሜት ነው። ህመሙ አንዳድ ጊዜ ትከሻ ላይ አልያም መሀል ጀርባ ላይ ሊሰማ ይችላል። ከዚህም ባሻገር የሚከተሉት ምልክቶችም ሊኖሩት ይችላሉ፦
የሆድ መነፋት
ማቅለሽለሽና ትውከት
ቶሎ የመጥገብ ስሜት
ቀላልክ ክብደት መቀነስ
ምክንያቱ ያልታወቀ ድካም
እላይ እንዳየነው ፤ ምልክቱ እንደ ቁስለቱ አይነት ሊለያይ ይችላል።
ቁስሉ መቼ እጅጉን አሳስቢ ይሆናል?

ያልታከመ ቁስል ወደ ሦስት ዋና አደጋዎች ሊያመራ ይችላል፦
ደም መፍሰስ፦ ቁስሉ ሲደማ የሚከሰት ነው። ምልክቶቹም ጥቁር ሰገራ፣ እንደ ቡና የጠቆረ ትውከት እና ራስን መሳት ናቸው።
የጨጓራ መበሳት (Perforation)፦ ቁስሉ ሲብስ የጨጓራ ግድግዳን ሊበሳ/ሊሸነቁር ይችላል። ይህ አስቸኳይ ቀዶ ጥገና የሚያስፈልገው የሕክምና ድንገተኛ አደጋ ነው። ይህን ጊዜ ድንገተኛ እና ከፍተኛ የሆድ ህመም ይሰማል።
የምግብ መንገድ መዘጋት (Obstruction)፦ በቁስሉ ምክንያት የሚፈጠር ጠባሳ ምግብ የሚያልፍበትን መንገድ ሊዘጋው/ሊያጠበው ይችላል። ይህ ሲያጋጥም ምልክቶቹ የበሉትን ምግብ እንዳለ መልሶ ማስታወክ ፣ ትንሽ እንደበሉ መጥገብ እና የሆድ መነፋት ናቸው።
ከ አምስት ታማሚዎች አንዱ ችግሩ እጅጉን እስኪባባስ አነስተኛ ምልክቶች ብቻ ሊኖረው ይችላል።
ለዚህም ችላ ይባላል። ይህ ደግሞ አደገኛ ነው!
እንዲሁም የጨጓራ ቁስለት ተደጋግሞ የሚያጋጥም ከሆነ ፤ በአመታት ውስጥ ለ ጨጓራ ካንሰር ሊያጋልጥ ይችላል።
ለዚህም አሁኑኑ መፍትሔ ይፈልጉለት!
እንዴት ማወቅ ይችላል?

የጨጓራ ቁስለት በተለያዩ ምርመራዎች ሊታወቅ ይችላል።
በዶክተር አካላዊ ምርመራ ጨጓራ ላይ ቁስለት መኖሩ ሊታወቅ ይችላል።
ባክቴሪያ መኖሩንም በደም ወይም ሰገራ ምርመራ መለየት ይቻላል።
እየደማ መሆኑን ለማወቅ የሰገራ የደም ምርመራ ሊታዘዝ ይችላል።
ከዚህም ባሻገር ቁስለቱን በቀጥታ ለመመልከት እና ጨጓራ ላይ ያለውን ለውጥ በአይን ለማየት የ ኢንዶስኮፒ (Endoscopy) ምርመራ ማድረግም ግድ ሊል ይችላል።
ሕክምናው ምንድነው?

የጨጓራ ቁስለትን በሚዋጥ መድሀኒቶች ማከም ይችላል። እነኝህም መድሀኒቶች ቁስለቱ እንዳይባባስ እና ጨጓራ እንዲድን አሲዱን የሚቀንሱ ናቸው። ከዚህም ባሻገር ባክቴሪያው ከተገኘ ባክቴሪያውን የሚቃወሙ መድሀኒቶች ሊጨመሩ ይችላሉ።
እንዴት መከላከል ይቻላል?
የጨጓራ ቁስለትን ለመከላከል የሚከተሉትን ያድርጉ።
ያለ አስፈላጊ ምክንያት የህመም ማስታገሻዎችን አይውሰዱ።
የህመም ማስታገሻዎችን መጠቀም ካለብዎ በዝቅተኛው መጠን ይጠቀሙ። አብዝተው አይጠቀሙ።
ሲጋራ አያጭሱ።
አልኮል ይቀንሱ/ያስወግዱ ።
የማያቋርጥ የሆድ ህመም ካለ በፍጥነት ምርመራ ያድርጉ።
ያስተውሉ!
የሚያቃጥል ቅመም (ቃሪያ/በርበሬ) በራሱ ለጨጓራ ቁስለት መንስኤ አይሆንም።
ጭንቀት ብቻውን ለጨጓራ ቁስለት መንስኤ አይሆንም።
ይህ ሊታከምና ሊከላከል የሚችል የውስጥ ቁስል ነው።
ምልክቶቹን ይወቁ! ይከላከሉ! ጤናዎን ይጠብቁ !





Comments