top of page

ሰዎች በድንገት ለምን ይሞታሉ?

"ትላንት ደህና ነበር…"

ይህ አረፍተ ነገር በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ብርቅ አይደለም። የብዙዎቻችንን ቤት ያንኳኳ፣ በሐዘንና በግራ መጋባት መሃል የምንደጋግመው መርዶ ነው።


ትዕይንቱን በዓይነ ሕሊናዎ ይሳሉት፦


አንድ ሰው ውሎውን እንደወትሮው በሥራ ያሳልፋል። ከጓደኞቹ ጋር በሳቅ ተጫውቶ ይለያያል። ማምሻውን ደግሞ ከቤተሰቡ ጋር እራት ተመግቦ፣ መልካም ሌሊት ተመኝቶ ወደ አልጋው ያመራል።


በማግስቱ ግን ዓለም ትገላበጣለች። በመንደሩ ውስጥ መርዶው እንደ ሰደድ እሳት ይሰራጫል፦


“አልጋው ላይ እንደሞተ ተገኘ!”


ምንም ዓይነት አደጋ አልደረሰም። የሚታወቅ ሕመምም አልነበረም። አስቀድሞ የሰጠው ማስጠንቀቂያም ሆነ የተናዘዘው ኑዛዜ የለም። በቃ፣ በድንገት “ተወሰደ።”


ለቤተሰቦች ይህ ቅጽበት ልብ ሰባሪ ነው። ለማኅበረሰቡ ደግሞ አንድ የሚያስጨንቅ ጥያቄ ይጭራል፦ ትላንት ጤነኛ መስሎ የታየ ሰው፣ ዛሬ እንዴት በድንገት ሊሞት ይችላል?


ከሰማይ የወረደ ድንገተኛ መቅሰፍት ወይስ የጤና ቀውስ?

ብዙዎቻችን ይህንን ክስተት ከዕጣ ፈንታ ወይም ከማይታወቁ ምስጢራት ጋር እናያይዘዋለን። በሕክምናው ዓለም ይህ ክስተት “ድንገተኛ ሞት” (Sudden Death) ይሰኛል። ይህም አንድ ጤነኛ የሚመስል እና የተረጋጋ ግለሰብ በ24 ሰዓታት ውስጥ፣ ወይም ምልክቶች በታዩ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የሚከሰት ያልተጠበቀ ሞት ነው።


እውነታው ይሄ ነው፦ ይህ ክስተት ምስጢራዊ አይደለም። ሳይንስ ከጀርባው ያሉትን መንስኤዎች ጠንቅቆ ያውቃቸዋል። እነዚህን መንስኤዎች መረዳት ደግሞ ይህንን ለመታደግ ብቸኛው መንገድ ነው።


በምን ይከሰታል?


ድንገተኛ ሞት ያለ ምክንያት አይመጣም። “ደህና ነበር” ያልነው ሰው ከጀርባ ለሞት የሚያጋልጡ መንስኤዎች ይኖሩታል። ሆስፒታል ሄዶ አይመርመር እንጂ ፤ የማይታወቅ በሽታ ኖሮበት ሊሆን ይችላል። እነኝህ መንስኤዎች በዝምታ ተከስተው ፤ ህይወትን ይነጥቃሉ። ይህንን ከሚያስከትሉ መንስኤዎች ውስጥ ዋነኛ የሚባሉት አምስቱን እንመልከት።


1. ድንገተኛ የልብ መቆም

ይህ በጣም የተለመደ ምክንያት ሲሆን ፤ አዋቂዎች ላይ ከሚከሰቱ ድንገተኛ ሞቶች ውስጥ ከ80–90% ለሚሆኑት ምክንያት እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ይህንም ከልብ ቧንቧዎች መጥበብ/መዘጋት እስከ ልብ አመታት ለውጥ/፣መዛባት (arrhythmia) ሊያመጡት ይችላሉ


ልብም በድንገት ደምን የመርጨት ሥራውን ያቆማል። ይህን ጊዜ በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ ፤ ወደ አንጎል የሚሄደው የደም ፍሰት ይቆማል።ለዚህም ራስዎን ይስታሉ። ካልታከመ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሞት ይከተላል።


ይህ በድንገት እስኪከሰት ድረስ ግለሰቡ ምንም ዓይነት ግልጽ ምልክት ላያሳይ ይችላል።


2. ያልታወቀ የልብ ሕመም

አንዳንድ ሰዎች የልብ ጡንቻ ችግሮች (Cardiomyopathy) ወይም የተፈጥሮ የልብ ቅርጽ መዛባት ሊኖርባቸው ይችላል። አንዳንዶች ይህን ችግር ይዘው ይወለዳሉ። ይህ ችግር እንደ ተቀበረ ፈንጂ ነው። ለዓመታት ምንም ዓይነት ሕመም ሳያሳይ ይቆያል። ታድያ አንድ ቀን በድንገት ለሞት ይዳርጋል። በተለይ በወጣቶች ላይ ለሚከሰት ድንገተኛ ሞት ዋነኛው ምክንያት ይሄው ስውር ጠላት ነው። የካሜሮን ተጫዋቹ ፎኤ (Foe) እናሌሎች አትሌቶችም ለዚህ ተጠቃሽ ሊሆኑ ይችላሉ።


3. ስትሮክ ወይም በአንጎል ውስጥ የደም መፍሰስ


አንዳንድ ጊዜ ድንገተኛ ሞት የሚከሰተው በአንጎል ውስጥ ያለ የደም ሥር ሲፈነዳ ወይም ሲደፈን ነው። ቁጥጥር ያልተደረገበት ከፍተኛ የደም ግፊት በአንጎል ውስጥ ያለን የደም ሥር በድንገት እንዲፈነዳ ሊያደርገው ይችላል። ይህም በአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ አስከትሎ ሊገድል ይችላል።


ስኳር እና የስብ መዛባት ችግሮች በበኩላቸው ወደ አንጎል የሚሄዱ ደምስሮችን በድንገት እንዲደፈኑ ሊያደርጉ ይችላሉ። በዚህም ምክንያት አንጎል ኦክስጅንና ምግብ በማጣቱ ሕዋሳቱ በደቂቃዎች ውስጥ ይሞታሉ። ይህም ግለሰቡን ለህልፈት ይዳርገዋል።


4. የሳምባ ደም መርጋት (Pulmonary Embolism)



ይህ ድንገተኛ የሳምባ ደም ስር መዘጋት ነው። ይህ መንስኤ ብዙ ጊዜ አይጠበቅም። በአደጋ፣ በሕመም ወይም ረጅም ሰዓት ባለመንቀሳቀስ ምክንያት በእግር ውስጥ የደም መርጋት (Clot) ሊፈጠር ይችላል። ይህ የረጋ ደም ተላቆ በደም ሥር ውስጥ በመጓዝ ሳምባ ላይ ይደርሳል። እዚያም ዋናውን የደም መተላለፊያ በድንገት ይዘጋዋል።


ይህን ጊዜ ሳምባ ኦክስጅን መሳብ ያቅተዋል። ስራውን ያቆማል። ሰውነት ይታፈናል። ልብም ስራዋን ታቆማለች። ይህ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የሚከሰት አደጋ ነው። ህይወትንም በቅጽበት ይነጥቃል።


5. የሰውነት ማዕድናት/ ስኳር ሚዛን መቃወስ


አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ድንገተኛ ሞት የሚከሰተው የሰውነት ማእድናት መዛባት ጋር ተያይዞ ሊሆን ይችላል። ሰውነታችን እንዲሠራ የደም ውስጥ ማእድናት ሚዛን ያስፈልገዋል። በተለያዩ ምክንያቶች የእነኝህ ማእድናት መጠን ከተቃወሰ ለድንገተኛ ሞት ይዳርጋል። ለዚህም አጋላጭ ምክንያቶች መሀከል ፣ ያልታወቅ ኢንፌክሽን እና ያልታወቀ ኩላሊት በሽታ ሊጠቀሱ ይችላሉ።


ከዚህም ባሻገር ሰውነት ውስጥ ያለ የስኳር መጠን በድንገት ሊወርድ/ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል። ይህም ካልተስተካከለ በደቂቃዎች ውስጥ ለሞትሊዳርግ ይችላል።


በኢትዮጵያስ ?


ከፍተኛ ገቢ ካላቸው አገራት በተለየ በኢትዮጵያ ስለ ድንገተኛ ሞት ያለው የአገራዊ መረጃ ውስን ነው። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የአስከሬን ምርመራ ባህላችን ዝቅተኛ መሆኑና የሞት ምዝገባ ሥርዓታችን አሁንም ድረስ በጅምር ላይ በመሆኑ ነው።


ነገር ግን የቅርብ ጊዜ ሳይንሳዊ ጥናቶችና የጤና ባለሥልጣናት ሪፖርቶች ይህንን ይነግሩናል። “ትላንት ደህና የነበረው” ሰው፣ ለዓመታት በዝምታ ሲገነባ የቆየ የጤና ቀውስ ሰለባ ቢሆንስ? ለዚህም ተጠቃሽ ከሚሆኑት ምክንያቶች መሀከል የሚከተሉት ዋነኞች ናቸው።


  • በሀገር አቀፍ ደረጃ የተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እየጨመሩ ነው፦ ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት በኢትዮጵያ የደም ግፊት፣ የልብ ሕመም፣ ስኳር እና ውፍረት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከሚከሰቱ ሞቶች መካከል 43% የሚሆኑት በእነዚህ በሽታዎች ሳቢያ የሚከሰቱ ናቸው። በየሰዓቱ 25 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በልብ ሕመም፣ በስኳርና በደም ግፊት ምክንያት ሕይወታቸውን ያጣሉ

  • የደም ግፊት የተለመደ ቢሆንም ብዙ ጊዜ አይታወቅም፦ ብዙ ኢትዮጵያውያን የደም ግፊት እንዳለባቸው ሳያውቁ ይኖራሉ። ይህም ለድንገተኛ የልብ ሞት ዋነኛው መንስኤ ነው። ለድንገተኛ ስትሮክ ሞትም ተጠያቂ ነው። ትላንት ደህና ነበር” የተባለው ግለሰብ፣ ለዓመታት ያልታወቀ እና ቁጥጥር ያልተደረገበት የደም ግፊት ሰለባ ቢሆንስ?

  • የድንገተኛ ጊዜ እርዳታ ተደራሽነት ውስንነት፦ አንድ ሰው ልቡ በድንገት ሲቆም፣ ሕልውናው በሰከንዶች ውስጥ ይወሰናል። በበለጸጉት አገራት ፈጣን የመጀመሪያ እርዳታ (CPR) እና አምቡላንስ ሕይወትን ይታደጋሉ። በኢትዮጵያ ግን አብዛኛው ድንገተኛ ሞት የሚከሰተው ከሆስፒታል ውጭ ነው። አምቡላንሶች እስኪደርሱ ወይም ግለሰቡ ሆስፒታል እስኪገባ ድረስ የሚጠፋው ወርቃማ ጊዜ፣ የመትረፍ ዕድሉን እጅግ አነስተኛ ያደርገዋል።


እነኝህ ግለሰቦች ለምን ጤነኛ ይመስላሉ?


ድንገተኛ ሞት ግራ የሚያጋባው ሰውየው ከዚያ በፊት ፍጹም ደህና ስለሚመስል ነው። በሕክምና “ጤነኛ መምሰል” እና “በእርግጥም ጤነኛ መሆን” የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ይህ ከሚሆንባቸው ምክንያቶች መሀከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ።


  • የተደበቀ በሽታ፦ ብዙ የልብ ሕመሞች በዝምታ ነው የሚከሰቱት።


  • የመጀመሪያው ምልክት ሞት ሊሆን ይችላል፦ በአንዳንድ ሰዎች ላይ የልብ ሕመም መኖሩን የሚጠቁም ምንም ዓይነት ቅድመ ማስጠንቀቂያ አይኖርም። ይልቁንም የመጀመሪያውና ብቸኛው የበሽታው ምልክት ድንገተኛ የልብ ትርታ መዛባት ይሆናል። ይህም በድንገት ሕይወት ይነጥቃል።


  • የመደበኛ ምርመራ እጥረት፦ ያለ ምርመራ እንደ ከፍተኛ ደም ግፊት ወይም ስኳር ያሉ ችግሮች ተደብቀው ይቆያሉ። እነዚህ በሽታዎች በሰውነት ውስጥ ጉዳት እያደረሱ ለረጅም ጊዜ ምንም ምልክት አያሳዩም። በኢትዮጵያ ደግሞ ሕመም ሳይሰማን የመታየትና የመመርመር ባህላችን ደካማ በመሆኑ፣ ብዙዎቻችን በውስጣችን ያለውን ስጋት ሳናውቅ እንቀራለን። ያለ ምርመራ በውስጣችን ያለውን እውነተኛ የጤና ሁኔታ ማወቅ አይቻልም፤ ይህም ሞት ሲከሰት “ያለ ምክንያት የመጣ” እንዲመስል ያደርገዋል።

ማስተዋል ያለብዎ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች

ድንገተኛ ሞት ያለ ማስጠንቀቂያ ሊከሰት ቢችልም፣ አንዳንድ ምልክቶች አስቀድመው ሊታዩ ይችላሉ፦


  • ምንም ዓይነት ግልጽ ምክንያት ሳይኖር (ለምሳሌ፦ ረሃብ ወይም ድካም ሳይኖር) በድንገት ራስን መሳት አልያም ሰውነት መቅለል ስሜት ካለ በአፋጣኝ ምርመራ ያድርጉ። የልብ ችግር ሊሆን ይችላል።

  • በደረትዎ ላይ የመጫን፣ የመጨመቅ ወይም የማቃጠል ስሜት ከተሰማዎት፤ በተለይም ሕመሙ ወደ ትከሻዎ፣ ወደ አንገትዎ ወይም ወደ እጅዎ የሚሰራጭ ከሆነ የሕክምና እርዳታ ይፈልጉ። ይህ ሕመም ተከስቶ ቢጠፋ እንኳ “ደህና ነኝ” ብለው ችላ ሊሉት አይገባም። የልብ ችግር ሊኖር ይችላል።

  • ደረጃ ሲወጡ ወይም ትንሽ ሲራመዱ ከወትሮው በተለየ ትንፋሽዎ ቁርጥ ቁርጥ የሚል ከሆነ፣ ድካም ከተሰማዎ ያስተውሉ። ይህ የልብ ወይም የሳምባ ችግር ምልክት ሊሆን ይችላል።

  • የአንዱ እግርዎ ባት/ታፋ በድንገት አብጦና ቀልቶ ካዩት፣ ይህ የእግር ደም ስር መርጋት ምልክት ሊሆን ይችላል። ወደ ሳምባዎ ከመጓዙ በፊት በአስቸኳይ ወደ ሕክምና መሄድ ይኖርብዎታል

  • በበድንገት ለመሳቅ ሲሞክሩ የፊትዎ አንድ ወገን ካልታዘዘልዎት ወይም እጅዎን ወይ እግርዎ ድንገት ከሰነፈ ይፍጠኑ። ከዚህም ባሻገር ድንገተኛ የባህሪ ለውጥ የንግግር ለውጥ ካዩም በአፋጣኝ ወደ አቅራቢያዎ ወዳለ ጤና ተቋም ይሂዱ።

  • ያለምንም ሙቀት ወይም እንቅስቃሴ በድንገት የሚመጣ ላብና የሰውነት መንቀጥቀጥ፣ በሰውነት ውስጥ የስኳር መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ማነሱን ሊያመለክት ይችላል። ይህም በፍጥነት ካልተስተካከለ ራስን ወደ መሳትና ለህልፈት ይዳርጋል። ለዚህም ችላ እንዳይሉ


እንዴት ይከላከላሉ?

ድንገተኛ ሞትን አስቀድሞ መከላከል ይቻላል። እነዚህን ቀላል የአኗኗር ዘይቤዎች በመከተል የራስዎንና የወዳጅዎን ሕይወት ይታደጉ፦


  1. የደም ግፊትን በየጊዜው መለካት፦ የደም ግፊት "ጸጥተኛ ገዳይ" በመሆኑ፣ ምልክት ባይሰማዎትም እንኳ በየጊዜው በመለካት ይቆጣጠሩ። ይህም ለድንገተኛ ስትሮክና ለልብ ሕመም ያለዎትን ተጋላጭነት በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል።

  2. ለስኳር በሽታ መመርመር፦ በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን መዛባት ለልብና ለደም ሥር ጤና ጠንቅ ነው። በሽታው መኖሩን አስቀድሞ ማወቅና ተገቢውን ሕክምና መጀመር ድንገተኛ አደጋዎችን ይከላከላል።

  3. ከአልኮልና ከሲጋራ መራቅ፦ ሲጋራ የደም ሥሮችን በማጥበብና በማደደር ለልብ ድንገተኛ መቆም ዋነኛው መንስኤ ነው። አልኮልን ማቆም ወይም መቀነስ ደግሞ የልብን ሥራ ያቀልላል።

  4. ጤናማ አመጋገብና እንቅስቃሴ፦ በምግብ ውስጥ የጨው መጠንን መቀነስ፣ አትክልትና ፍራፍሬን ማዘውተር እንዲሁም በቀን ቢያንስ ለ30 ደቂቃ በእግር መጓዝ የልብን ጤንነት ይጠብቃል።

  5. እላይ የተዘረዘሩትን ምልክቶች ካዩ ቀጠሮ ሳይሰጡ በአስቸኳይ ወደ ሕክምና ይሂዱ።


ያስታውሱ!

ከብዙ ድንገተኛ ሞቶች በስተጀርባ የተደበቁ በሽታዎች፣ ያልታወቁ የጤና እክሎች አሉ።

መከላከል ያለዎት ብቸኛ አማራጭ ነው!


Comments


bottom of page