top of page

የልብ ድካም በሽታ፡ ለምን? እንዴት?

ከመወለዳችን በፊት በእናታችን ማህጸን ውስጥ ስራ የሚጀምረው ታታሪው ልብ ፤ እስከ መጨረሻ ደቂቃችን ድረስ ይተጋል።


ሆኖም በመላው ኢትዮጵያ ባሉ ሆስፒታሎች ተኝተው ከሚታከሙ አስር ታካሚዎች አንዱ የልብ ችግር እንዳለበት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህም ውስጥ የልብ ድክመት ከፍተኛውን ይወስዳል።

ለመሆኑ የልብ ድካም ምንድን ነው?


መረረኝ ሰለቸኝ የማይለው ታታሪ ልብ እንዴትስ ደከመ?

እዚህ ጋር የልብ ድካም የሚለውን ቃል ቀድመን መለየት ይኖርብናል። በተለምዶ ሁለት የልብ በሽታዎች የልብ ድካም ተብለው ይጠራሉ።


አንደኛ፡ ልብ አቅም ሲያጣ እና የተለምዶ ስራውን መስራት ሲያቅተው ልብ ደከመ እንላለን። ይህ በህክምናው ኸርት ፌለር (Heart Failure) ይባላል።

ሁለተኛ፡ የልብ መጋቢ ደም ስር ሲደፈን ፤ እርሱን የተመረኮዘው የልብ ጡንቻ ይሞታል/ ይታፈናል/ይራባል። ይህ ደግሞ በህክምና ማዮካርዲያል ኢንፍራክሽን (myocardial infraction) ይባላል። ይህን ብዙ ጊዜ ፊልሞች ላይ ያሉ ገጸ ባህሪያት ልባቸውን ይዘው ሲወድቁ የምናየው ህመም ነው። ይህ በተለምዶ ልብ ድካም ይባል እንጂ ስያሜው በሽታውን በትክክል አይገልጽም። ይልቁኑ የልብ ጥቃት (Heart attack) አቻ የሚለው ትርጓሜ ይሻላል።


በዚህ ጽሁፍ የምናወራው ስለመጀመሪያው ነው።

     

የልብ ድካምን እንደ አንድ በሽታ አያስቡት። የልብ ድካም የብዙ የልብ በሽታዎች መጨረሻ መዳረሻ ነው። ያልታከሙ አልያም በህክምና ቁጥጥር ስር ያልዋሉ ብዙ በሽታዎች የልብ ድካም ያመጣሉ።


ልብ "ሲደክም" ማለት ምን ማለት ነው?


በሕክምና አነጋገር የልብ ድካም የሚከሰተው ልብ የሰውነትን  ፍላጎት ለማሟላት በቂ ደም መርጨት/ መግፋት ሲሳነው ነው። አልያም ይህንን ለማድረግ ልብ ከፍተኛ ጉልበት የሚያወጣ / ግፊት የሚያሳድር ከሆነ ልብ ደክሟል ይባላል።


ይህንን ለመረዳት አንድ የጉልበት ሰራተኛን በምናብዎ ይሳሉ። ይህ የጉልበት ሰራተኛ ቀኑን ሙሉ ሳያሰልስ በቀላሉ ሲሸከም ውሏል። ወደ ኋላ ግን ሲደክም ፤ ተመሳሳይ ስራ ለመስራት በጣም ኃይል ማውጣት ፤ ወይም የሚሸከመውን ክብደት መቀነስ ይጀምራል።


ልብም ላይ እንዲሁ...

ታድያ ልብ ሲደክም የወትሮ ስራውን መስራት ይሳነዋል። ይህን ስራውን መስራት በመሳኑ ፤ በተለያዩ አካላት ላይ ምልክቶቹ ይስተዋላሉ።



  • ሳንባ ውሀ ይይዛል። ለዚህም ትንፋሽ ማጠር ሊታይ ይችላል።

  • ወደ ሰውነት በቂ ደም እየተዳረስ ስላልሆነ ፤ በትንሽ እንቅስቃሴ ቶል ድካም ይኖራል።

  • ጉበትም ይቆጣል/ ያብጣል።

  • እግሮች እንዲሁም ሆድ እብጠት ሊኖራቸው ይችላል።


ከዚህም ባሻገር የምግብ ፍላጎት ሊቀንስ ፤ የደረት ህመም ሊሰማ፣ የልብ አመታት ሊለወጥ፣ ወ.ዘ.ተ... ይችላል።


ከባድ ድንገተኛ ጥቃት ካልደረሰበት በቀር ፤ ታታሪው ልብ እስኪደክም አመታት ይፈጅበታል። ልብዎ ግን እጅ በቶሎ አይሰጥም ። ጉድለቱን ለማስተካከል ፤ በቂ ደም ለሰውነት ለማድረስ ይታገላል። ለዚህም እንዲረዳው የልብ ጡንቻውን ያወፍራል፣ ግድግዳዎቹን ያሰፋል፣ በፍጥነት መስራት ይጀምራል።


ታድያ ግን ይህም አይበቃም። እነኝህ ማካካሻ እርምጃዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የልብ ስራን ቢያሻሽሉም ፤ በጊዜ ሂደት ውስጥ ልብን በይበልጥ ይጎዳሉ። ስራውን ያስተጓጉላሉ። ለዚህም ልብ ይበልጡኑ ይዳከማል።


ልብ ሰውነትን ለማዳን በሚያደርገው ትግል ውስጥ ፤ ራሱን ቀስ በቀስ ያጠፋል።

ለምን የልብ ድካም ያጋጥማል?


የልብ ድካም በሽታ በተለያዩ ምክንያቶች የሚመጣ ቢሆንም ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ዋነኛ ምክንያት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።


1. ከፍተኛ የደም ግፊት

ይህ እጅጉን የተለመደና በጣም ችላ የሚባል የልብ ድካም ምክንያት ነው። ከአምስት ጎልማሳ መሀል አንዱ የደም ግፊት ህመም አለበት በሚባልባት ኢትዮጵያም አሳሳቢ ነው። ብዙዎቹም 'ጤነኛ ነኝ 'ብሎ በማመን ቁጥጥር ስር ያልዋለ የደም ግፊት በሽታ  ይዘው ይኖራሉ።



የደም ግፊት ቁጥጥር ላይ ሳይውል ከፍ ብሎ ከቆየ ፤ ልብ ላይ ጫና ያሳድራል። ልብ መደበኛ ስራውን ለመስራት ፤ ይህንን የደም ግፊት ተቃርኖ መግፋት አለበት። ይህም የልብን ጡንቻ ያወፍራል።


አንድ ስፖርተኛ ጂም ገብቶ ክብደት አንስቶ እንደሚገዝፈው ፤የልብ ጡንቻዎች ከፍተኛ ግፊት እየተቃወሙ ስለሚሰሩ ይገዝፋሉ፤ ይደነድናሉ። ይህም ልብ የሚሸከመውን ደም መጠን ይቀንሳል። ስራውን ያስተጓጉላል።


ለአመታት ልብዎት በጸጥታ ታግሎ ፤ በመጨረሻ እጅ ይሰጣል። ይዳከማል።

ይህን ጊዜ ምልክቱን ያያሉ። ነገር ግን ልብ ቀድሞውኑ ጉዳት ደርሶበታል።

 


2. የሩማቲክ የልብ ሕመም

ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የልብ ድካም ምክንያቶች ውስጥ ይህ ከፍተኛ ቦታው ይወስዳል።  በሽታው በህክምና ስሙ የሪዩማቲክ የልብ ህመም ይባላል። ስለዚህ በሽታ በጥልቅ ለማወቅ ፤ ከዚህ በፈት የጻፍነውን ጽሁፍ ያንብቡ።


ይህ ህመም የሚጀምረው ፤ በልጅነት ጊዜ ባልታከመ የጉሮሮ ኢንፌክሽን ነው። ኢንፌክሽኑ ቢጠፋም የበሽታ መከላከያ ስርአታችን የልብ ቧንቧን ያጠቃል። ይህም ቧንቧዎቹንም ያጠባል።


የእነኝህ ቧንቧዎች በስርአት አለመስራት ፤ ልብ ላይ ስራን ይጨምራል። ልብም ስራው እንዳይስተጓጎል ፤ ጉልበት አሳድሮ በይበልጥ ይሰራል።  ታድያ ለአመታት ሲተጋ የነበረው ልብም መዛል ይጀምራል። ይዳከማል።


ብዙ ኢትዮጵያውያን የልብ ህመምተኞችን የሚያጋጥመው አሳዛኝ እውነታም ይሄ ነው።

በሚዋጥ ባክቴሪያ መቃወሚያ (antibiotics) መከላከል ግን ይቻል ነበር።


  1. ከኦክስጅን ማነስ ጋር የተያያዙ የልብ በሽታዎች


ልብ ጡንቻ ነው። ልክ እንደ ሁሉም ጡንቻዎች  ኦክስጅን  እና ምግብ ያስፈልገዋል። ይህ ደግሞ በልብ መጋቢ ደም ስሮች በኩል ይደርሳል። ታድያ የእነኝህ ደም ስሮች መቋረጥ/ መጥበብ ለልብ ጡንቻዎች የሚደርሰውን የደም አቅርቦት ይቀንሳል። ልብም በቂ ኦክስጅን ስለማይደርሰው ይታፈናል። ለዚህም የልብ ጡንቻ መታፈን የሚያመጡ በሽታዎች (Ischemic Heart Disease)ይባላሉ።


በኦክስጅን እጥረት የተነሳ የልብ ጡንቻዎች ስራቸውን በአግባቡ መስራት ይሳናቸዋል። ይሞታሉ። ይህም የልብ ስራን ይበልጥ ያስተጓጉላል። የተቀረው የልብ ክፍልም በተጎዱ ጡንቻዎች ፋንታ ለመስራት ስለሚሞክር ፤ ጫናው ይበዛበታል።


ይህም ልብን ያዳክማል። 


ይህ በሽታ  በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ይገኛል።

ለመስፋፋቱ ባለፉት አመታት ያሳየናቸው የአኗኗር ለውጦች እንደመንስኤነት ይጠቀሳሉ።


4. የስኳር በሽታ

በብዛት እንደሚታወቀው የስኳር በሽታ ልብ ላይ ብዙ ጉዳት ያሰከትላል። ስኳር ልብን በተለያዩ መንገዶች ሊጎዳ ይችላል።

  • ከላይ ባየነው መሰረት ፤ የልብ ደምስሮችን በማጥበብ ፤ ጡንቻዎችን ሊያስርብ ይችላል። 

  • የደምስሮች መደደርን ሊያመጣ ስለሚችል ፤ ልብ ላይ ስራ ሊጨምርም ይችላል። 

  • የልብን ትናንሽ የደም ስሮችንም  ያጠቃል። 

  • ከዚህም ባሻገር የልብ ጡንቻ ላይም ተጽእኖ ያሳድራል።


እነኝህም በጊዜ ሂደት ውስጥ ልብ ድካም ያመጣሉ። ለዚህ የደምዎን የስኳር መጠን ዛሬውኑ ይቆጣጠሩ።

 

5. ሌሎች በሽታዎች

ከዚህም ባሻገር

  • ረዥም ጊዜ የቆየ የደም ማነስ ኦክስጅን መጠንን ስለሚቀንስ ልብ ብዙ እንዲሰራ ያስገድደዋል። ይህም በጊዜ ውስጥ ልብን ሊያዳክም ይችላል። ለዚህም ደም ማነስ ነው ብለው አይዘናጉ።

  • የሳንባ በሽታዎች ሳንባ ጋር ያለውን ግፊት ሊጭምሩ ስለሚችሉ ፤ ከሳንባ ጋር ግንኙነት ያለው የቀኝ ልብ ይዳከማል።

  • ለረዥም ጊዜ የቆዩ ኢንፌክሽኖችም በቀጥታ ልብን በመጉዳት አልያም ልብ ላይ ስራ በመጨመር ያዳክማሉ።

 

የልብ ድካም ለምን አሳስቢ ሆነ?


የልብ ድካም የደም ዝውውር በሽታ ብቻ አይደለም። የዕለት ተዕለት ኑሮ ተግዳሮት ነው።

ታካሚዎች በተለምዶ የሚሰሯቸውን ስራዎች ለመስራት ይቸገራሉ።  ቤት ማስተካከል፣ ርቆ መራመድ ፣ መስገድና መጸለይ  እንኳን ሊሳናቸው ይቻላል። እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መድከም/ ትንፋሽ ማጠር ሊያጋጥማቸው ይችላል።

እንቅስቃሴ ያለው ስራ በአግባቡ ለመስራት ስለሚቸገሩ ፤ ከስራ ቦታ ሊፈናቀሉ ይችላሉ። በሌላ ሰው ላይ ጥገኛ ይሆናሉ።

ሆስፒታልም ደግመው ደጋግመው ይሄዳሉ።


የኢትዮጵያስ እውነታ ምን ይመስላል?  


በኢትዮጵያ የተደረጉ ጥናቶችም ይህንን ይደግፋሉ። የልብ ድካም በሽተኞች ብዙ ተግዳሮቶች ይገጡማቸዋል። ይህም በገጠሪቷ ኢትዮጵያ በሚኖሩ፣ በሴቶች እንዲሁም ዝቀተኛ ገቢ ባላቸው  የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ይሰተዋላል።



በሽታው ለእነኝህ ማህበረሰብ ክፍሎች ኑሮን ያከብድባቸዋል። ድህነትንም ያባብሳል። ድህነትም በበኩሉ ደግሞ በሽታውን ያባብሰዋል። ። 

ይህ አስከፊ አዙሪት ነው!

  

የልብ ድካም ለምን ረፍዶ ይታወቃል?

የልብ ድካም ብዙ ጊዜ አያስታውቅም። የመጀመሪያዎቹ ምልክቶች በእለት ተእለት ህይወት የሚያጋጥሙንን ያስመስላሉ። ታካሚዎች


"በቃ ደክሞኛል"

"እያረጀሁ ነው"

"ውጥረት ነው"ይላሉ። 

በተለይ የህክምና ተደራሽነት ዝቀተኛ በሆነባቸው አከባቢዎች እነኝህ ምልክቶች ቦታ አይሰጣቸውም። ለዚህም በኢትዮጵያ የልብ ድካም ብዙ ጊዜ ዘግይቶ፣ ከብዶ እና ተወሳሰቦ ይደረስበታል።

 

ይህንን ታሪክ መለወጥ ግን ይችላሉ።


  • ቀድመው የደም ግፊትዎን ከተቆጣጠሩ

  • በአፋጣኝ የጉሮሮ የኢንፌክሽን ህክምና ካደረጉ

  • የደምዎን የስኳር መጠን ከተቆጣጠሩ

  • መደበኛ የጤና ምርመራ ካደረጉ


መከላከል ይችላሉ!


ፍቱኑ መድሀኒትም መከላከል ነውና ፤ ፈጽሞ አይዘናጉ። ዛሬውኑ እርምጃ ይውሰዱ። 


ጤና ተኮር ትምህርታዊ መረጃዎችን በመከታተል ግንዛቤዎን ያስፉ።

 

Comments


bottom of page