top of page

የስትሮክ ህመም ነባራዊ ሁኔታ

እስቲ አስቡት ... ዛሬ ጠዋት ከእንቅልፍዎ ሲነሱ ሰውነትዎ አልታዘዝ ቢልዎት ኖሮስ? አንደበትዎ ቢንተባተብስ? ምን ይሰማዎት ይሆን?

በእርግጠኝነት አስፈሪ የሚያስጨንቅ ስሜት ነው።


ይህ ህመም ስትሮክ ይባላል። በድንገት የሚያጋጥም ፤ ህይወትን የሚለውጥ የጤና ቀውስ ነው። የህመሙን አካላዊ ዳራ ማየት የሚቻለው ያውም ከተረፉ ነው። በተኙበት ስትሮክ አጋጥሟቸው እስከወዲያኛውም ያሸለቡም አሉ። ስትሮክ የብዙ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል ፤ እየቀጠፈም ይገኛል።  የህመሙም ስርጭት ከቀን ወደቀን እየጨመረ እየመጣ ይገኛል።


በአለም አቀፍ ደረጃ በግምት በየዓመቱ 12 ሚሊዮን ሰዎች ስትሮክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያጋጥማቸዋል። በስትሮክ የተነሳ በየዓመቱ ከ6.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይሞታሉ። በአህጉራችን አፍሪካም ከምእራቡ አለም አንጻር ስትሮክ ከሁለት እስከ ሶስት እጥፍ ተሰራጭቷል። በኢትዮጵያም ከቀዳሚ የሞት መንስኤዎች ተርታ ይገኛል። ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ2017 ከሞቱ ሰዎች ውስጥ አንድ አስራአምስተኛ የሚጠጉት ከስትሮክ ጋር በተያያዘ ምክንያት እንዳረፉ መረጃዎች ያመላክታሉ።


ስትሮክ ምንድነው?


ስትሮክ ወደተወሰነ የአንጎል ክፍል የሚሄደው የደም ዝውውር ሲቋረጥ ፤ የሚያጋጥም ህመም ነው።ከዚህ ጋር በተያያዘ በመጋቢው የደም ስር የሚሄደው ኦክስጅን እና ምግብ ለነርቭ ህዋሳቶቹ ሳይደርስ ይቀራል። ይህም ደግሞ እነኝህ ህዋሳት ምግብ እንዲራቡ እንዲሁም ፤ አየር እንዲያጥራቸው ያደርጋል። የነርቭ ህዋሳቶቻችን ተርበው እና አየር አጥሯቸው መቆየት የሚችሉት ለተወሰኑ ደቂቃዎች በመሆኑ ፤ ከቆይታ በኋላ መዳከምና መሞት ይጀምራሉ። እነኝህ የነርቭ ህዋሳት በህይወታችን አንድ ጊዜ ብቻ ስለሚሰሩ ፣ ሲሞቱ አይተኩም። በዚህም የተነሳ በእነርሱ ቁጥጥር ስር ያለው የሰውነታችን ክፍል እክል ያጋጥመዋል። እንደየጉዳቱ መጠን ይዳከማል ወይ መስራት ያቆማል። የዚህን ጊዜ የስትሮክ ህመም መለያ ምልክቶች ይታያሉ። የተጎዳው የደም ስር ትልቅ እና ዋነኛ የአንጎል ክፍሎችን መጋቢ ከሆነ ፤ ጉዳቱ ከማየሉ የተነሳ ፤ ታካሚው በድንገት እዛው ይሞታል።


እንዲህ አድርጋችሁ አስቡት ... ወደ ቤታችሁ የሚገባው የመብራት መስመር ቢቋረጥ ምን ይፈጠራል? እሱን ተከትሎ ኢሌክትሮኒክስ መጠቀም አያዳግትምን? የስልክ ግንኙነታችሁስ አይተጓጎልምን ? ለኤሌክትሮኒክስ መብራት ምግባቸው ስለሆነ መብራት ከሌለ አይሰሩም። በስትሮክ ጊዜ የተራቡት የነርቭ ህዋሳት እጣም ተመሳሳይ ነው። ልዩነቱ ግን መብራት ሲመጣ ሁሉም ኤሌክትሮኒክስ ስራ ሲጀምር ፤ የአንጎላችን ነርቭ ህዋሳት ግን ከሞቱ አይመለሱም። ጉዳታቸው ቋሚ ነው።


ኢስኬሚክ ስትሮክ (በግራ) እና ሄሞሬጂክ ስትሮክ (በቀኝ)
ኢስኬሚክ ስትሮክ (በግራ) እና ሄሞሬጂክ ስትሮክ (በቀኝ)

በህክምናው ሁለት የስትሮክ አይነቶች አሉ

  1. ኢስኬሚክ ስትሮክ ፡ የደም ስር ቱቦ በተለያየ ምክንያት ከውስጥ በመዘጋቱ የተነሳ ፤ የደም ዝውውር ስለሚቋረጥ የሚመጣ ነው።


  2. ሄሞሬጂክ ስትሮክ ፡ የደም ስር ቱቦ ሲቀደድ/ ሲፈነዳ የሚፈጠር ሲሆን ፤ እሱን ተከትሎ ደም ወደ ጭንቅላት ይፈሳል።


ከሁለቱ  የስትሮክ አይነቶች አብዝቶ የሚያጋጥመው ኢስኬሚክ ስትሮክ ነው። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ ከሚያጋጥሙ አስር ስትሮኮች ስድስቱ ኢስኬሚክ ስትሮክ ናቸው። በአለም ደረጃ ግን ፤ ከአስሩ ስምንቱ ኢስኬሚክ ስትሮክ ነው።


አይነቱ የትኛውም ይሁን ፤ አፋጣኝ ህክምና ካልተደረገ ውጤቱ ሁሌ የከፋ ነው። 


በስትሮክ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች ምን ይላሉ?


  • በሙሉ ኢትዮጵያ ሆስፒታል ተኝተው ከሚታከሙት መሀል ፤ የስትሮክ ታማሚዎች እስከ 19.3 ፐርሰንት ያህል ይሆናሉ።


  • እ.ኤ.አ በ2021 በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ደግሞ ፤ 24% የሚሆኑት የነርቭ ህመም ታካሚውች የስትሮክ ህመም አለባቸው።


  • ይብሱኑ ብሎ ስትሮክ ህመም የሚያጋጥምበት እድሜ ኢትዮጵያ ላይ እየቀነሰ መጥቷል። እንደፈረንጆቹ ሳይሆን ፤ ኢትዮጵያ ላይ ከ 60 አመት በታች የሆኑ ሰዎች አብዝተው በስትሮክ ይጠቃሉ።።


  • የአለም ጤና ድርጅት እንዳወጣው መረጃ ደግሞ ፤ በተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ከሚሞቱ 10 ህመምተኖች አራቱ የሚሞቱት በስትሮክ ነው።


  • ለስትሮክ ከሚያጋልጡ መንስኤዎች 90 ፐርሰንት የሚሆኑት መሻሻል የሚችሉ ናቸው።


መንስኤዎቹ

የስትሮክ አጋላጭ ምክንያቶች በሁለት ይከፈላሉ ፦ መለወጥ የሚቻሉ አጋላጭ መንስኤዎች እና መለወጥ የማችይሉ አጋላጭ መንስኤዎች። መለወጥ የሚችሉትን ደግሞ ፤ ከሰውነት ስርአት (ሜታቦሊክ) ጋር የሚያያዙ እና ባህሪያዊ መንስኤዎች ብለን ልንከፍላቸው እንችላለን።


ሜታቦሊክ አጋላጭ መንስኤዎች


  • ከፍተኛ የደም ግፊት፣


  • ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣


  • ደም ውስጥ ስኳር መጨመር፣


  • የልብ ሕመም ፣


  • የደም ውስጥ ያለ ስብ መዛባት ተጠቃሽ ናቸው


ባህሪያዊ አጋላጭ መንስኤዎች


  • ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ፣


  • ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ


  • አልኮል መጠጣት ጫት መቃም፣ ሲጋራ ማጨስ ና ፣ አደንዛዥ እጽ መጠቀምን ያካትታል።


የማይለወጡ አጋላጭ መንስኤዎች


  • እድሜ፡ ከ 55 አመት በላይ የስትሮክ የማጋጠም እድል ይጨምራል።


  • ጾታ፡ ስትሮክ ተጋላጭነት ሴቶች ላይ ያይላል።


  • የቤተሰብ ታሪክ፡ በቤተሰብ ውስጥ ስትሮክ ያጋጠመው ሰው ካለ ሌላ የቤተሰብ አባል ላይ የማጋጠም እድሉ ይጨምራል።


  • ነገድ ፡ ከሌሎች ነገዶች ስትሮክ ጥቁሮች ላይ ይበዛል።


ስትሮክ ከላይ የተገለጡት አጋላጭ መንስኤዎች እንደሚያመላክቱት ፤ ከአኗኗር ዘይቤ ጋር የሚገናኝ ስለሆነ ፤ ህመሙ በከተሞች ይበዛል። ይህም በከተሞች ከሚታየው የአኗኗር ዘይቤ ጋር ይያዛል። በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ቁጥሩ ያነሰ ቢሆንም ፤ በህክምና ተደራሽነት ጉድለት የተነሳ ስትሮክ ታማሚዎች በአፋጣኝ ህክምና ለማግኘት ይቸገራሉ።


በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ፤ ኢትዮጵያ ላይ የስትሮክ ታማሚዎች ምልክቱ ከታየ በ24 ሰአት ውስጥ ነው ሆስፒታል ለህክምና የሚመጡት ። ይህም ህመሙን መፈወስ የሚቻልበትን ወርቃማ ጊዜ (የመጀመሪያ ሶስት ሰአት) እንዲያጡ ያደርጋል።


የስትሮክ ህክምና ምልክቶች ምንድናቸው?


የስትሮክ ህክምናን ለማግኘት የምናጠፋው ጊዜ ብዙ ዋጋን ያስከፍላል። ምልክቶቹን ቀደም ብሎ ማወቁ አፋጣኝ ህክምናን እንድናገኝ ፤ ህይወት እንዲተርፍ ሊያደርግ ይችላል።


ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

  • ፊት ገምሶ ሊወድቅ/ ሊዳከም/ ሊደነዝዝ ይችላል። ይህም አንድ አይንን መዝጋት መችገርንና ፣ ከንፈር መጣመም እንዲያጋጥም ሊያደርግ ይችላል።  


  • የእጆቻችን ወይም እግሮቻችን በከፊል ሆነ በሙሉ ሊሰንፉ/ ሊደክሙ ይችላሉ። ይህም ደግሞ ፈጽሞ እንቅስቃሴ እንዳይቻል ወይም እንዲከብድ ወይም የተዛባ አረማመድ እንዲኖር ሊያደርግ ይችላል። 


  • የንግግር ችግር ሊያጋጥም ይችላል። ከዚህ በፊት በስርአት ያወራ ይናገር የነበረ ግለሰብ አፉን ሊይዘው፣ ሊንተባተብ፣ ማውራት ሊያቅተው ፣ ቃላቶች ሊጠፉበት ይችላሉ።


  • ያልታሰበ ድንገተኛ የባህሪ ለውጥ ሊኖር ይችላል፡ ይህ ለመለየት የሚያስቸግር ሲሆን ፤ የፊት አንጎል ክፍል ሲጠቃ የባህሪ ለውጥ ሊመጣ ይችላል። ይህም ተጫዋች የነበረ ሰውን ገራም ፣ ዝምተኛና፣ ጭምት ሊያደርገው ይችላል።


በስትሮክ ህመም የተነሳ በከፊል የተዳከም ፊት ፣ ወደ አንድ ጎን የተሳበ ከንፈር
በስትሮክ ህመም የተነሳ በከፊል የተዳከም ፊት ፣ ወደ አንድ ጎን የተሳበ ከንፈር
እነኝህን ምልክቶች ካዩ አይቆዩ። በአፋጣኝ ህክምና ይፈልጉ። ስትሮኩ ካጋጠመ በ 3 ሰአት ጊዜ ውስጥ ከደረሱ ስትሮኩን መገልበጥ ፤ ጉዳቱን መቀነስ ፤ ምልክቶቹን ማጥፋት ይቻላል።

እላይ ከተጠቀሱት ባሻገር የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያሳይ ይችላል


  • የ እይታ መደብዘዝ/ችግር ፣


  • ከባድ ራስ ምታት (በተለይ የ ደምግፊት ታማሚዎች ላይ)፣


  • ግራ መጋባት ወይም ንግግርን መረዳት አለመቻል፣


  • መራመድ ችግር፣ማዞር ፣ ሚዛን ማጣት ሊያጋጥም ይችላል።


ህክምናው ፡ ከጊዜ ጋር ውድድር


የስትሮክ ህክምና ውጤታማነቱ ከ ጊዜ ጋር የተሳሰረ ነው። ስትሮኩ እንዳጋጠመ ከ 3 እስከ 4.5 ሰአት ውስጥ ህክምና ከተደረገ ፤ በደምዝውውር መቋረጥ የተጎዱት የነርቭ ህዋሳት በቋሚነት ሳይሞቱ ልንደርስላቸው ፤ አልያም የስትሮኩን ጉዳት ልንቆጣጠረው እንችላለን። ጊዜው ከረፈደ ግን ጉዳቱ ቋሚ ይሆናል።



ከዚህ ባሻገር የስትሮክ ህክምና በኢትዮጵያ ብዙ እክሎች ያጋጥሙታል።


  • የስትሮክ ህክምና መደረግ የሚችለው ሆስፒታል ደረጃ ላይ ነው። የጤና ጣቢይ ላይ ተመርምሮ ፤ ሆስፒታል ሪፈር ተደርጎ እስኪደርስ ፤ ወርቃማ ጊዜውን የሚያጣ ብዙ ነው። የተሟላ የስትሮክ ቡድን እና አቅም ያላቸው ደግሞ ፤ እንደ ጥቁር አንበሳ እና ጳውሎስ ያሉት ከፍተኛ ሆስፒታሎች ናቸው።


  • የስትሮክ መመርመሪያ መሳሪያዎች በመንግስት ሆስፒታል ላይ እክል ብዙ ጊዜ ስለሚያጋጥማቸው ፤ የግል ቦታ ሄዶ ተመርምሮ ለመምጣት የሚገደዱ ጥቂቶች አይደሉም። የመመርመሪያ መሳሪያዎቹ ፈጽሞ የሌሉባቸው አከባቢዎችም ብዙ ናቸው።


  • በትራንስፖርት እና  በግንዛቤ ማነስ ብዙ ታካሚዎች አርፍደው ነው የሚመጡት። ከቀናት በኋላ መምጣት የተለመደ ቢሆንም ፤ ከሳምንት በኋላ የባህላዊ ህክምናን ሞክሮ የሚመጣም ትንሽ አይደለም። በዚህን ጊዜ ጉዳቱ ቋሚ ስለሚሆን ፤ የእገዛ እንጂ የማዳን ህክምና እንዳይደረግ ያስገድዳል።


  • ከስትሮክ ህመም በኋላ የማገገሚያ ህክምናውን አሟልቶ የሚከታተል ታማሚ ጥቂት ነው።


  • የንግግር ህክምና ባለሙያዎች ባለፉት አመታት የተመረቁ ቢሆንም ፤ ቁጥራቸው እጅጉን አናሳ ነው።



ለዚህም ለጤናዎት ቅድሚይ ይስጡ!

ቀድመው የስትሮክ ምልክቶችን ይለዩ፣ በአፋጣኝ ህክምና ያድርጉ።

ህይወትዎን ያድኑ።

ለሌሎችም ስለስትሮክ ያሎትን ግንዛቤ ያጋሩ።

Comentarios


bottom of page