ከውፍረት ባሻገር ፡ ልብ ላይ ያለ ጫና
- Zebeaman Tibebu
- Dec 28, 2025
- 4 min read
በሚሊየኖች የሚሆኑ ሰዎች በአለም ዙሪያ የውፍረት ችግር አለባቸው። በፈረንጆች 2022 ይህ ቁጥር ወደ 900 ሚሊየን ይጠጋ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። ውፍረት ደግሞ በበኩሉ ልብ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ከባድ በመሆኑ ፤ ከእነኝህ መሀከል አብዛኞቹ በአመታት ውስጥ የልብ በሽተኞች ይሆናሉ።

በልብ በሽታ ምክንያት ከሚሞቱ አስር ሰዎች መሀከል አንዱ ከውፍረት ጋር በተያያዘ ምክንያት እንደሚያርፍ ከ አመት በፊት የወጣ መረጃ ይጠቁማል። በግምትም በየአመቱ 1.9 ሚሊየን የሚሞሉ ሰዎች ከውፍረት ጋር በተያይዘ ልብ ህመም ይሞታሉ።
ይህ ችላ ሊባል የማይችል እውነታ ነው!
ጠላት ከሩቅ አይመጣም አይደል እንደሚባለው....
አብሮት ያለ ሰውነትዎ ውስጥ የተደበቀ ፤ ውፍረት እና ተያይዞት ያለ የስብ ችግር ፤ በአመታት ውስጥ ልብ በሽታ ሊያስከትል ይችላል። ይህ ቫይረስ ወይም መርዝ አይደለም። ግዙፍነት/ ግርማ ብለው የሚኮሩበት ፤ እንደሰውነትዎ የሚያስቡት ውፍረት ነው ጠላትዎ!
📊 ውፍረት ምንድንነው?
በህክምና ክብደትን በተለያዩ ክፍሎች መመደብ የምንችልበት መስፈርት ሲኖር ፤ ከዚህ ውስጥ በዋነኝነት ጥቅም ላይ የሚውለው ቢኤም አይ (BMI) ይባላል። በዚህ መስፈርት መሰረትም ክብደት እንደሚከተሉት መክፈል ይቻላል።
መደበኛ/ጤናማ ክብደት የሚባለው 18.5-24.9 ያለው ነው። ይህ ጤናማ ደረጃ ተብሎ ይታሰባል።
ከመጠን በላይ ክብደት የሚባለው 25-29.9 ያለው ነው። ይህም ተያያዥ የጤና ችግሮች አሉት።
ከመጠን በላይ ውፍረት የሚባለው ከ 30 በላይ ሲሆን ፤ ይህም ለልብ ፣ ስኳር ፣ ደም ግፊት እና የተለያዩ በሽታዎች ዋነኛ መንስኤ ነው።

ከመጠን ያለፈ ውፍረት ለልብ በሽታ አንደኛ አጋላጭ ነው። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ቢኤምአያቸው ከ 30 የበለጡ ግለሰቦች ለ ልብ በሽታ የመጋለጥ እድላቸው በ 2.4 እጥፍ የጨመረ ነው። ቢኤም አያቸው ከ 25 እስከ 29.9 የሆኑ ሰዎች እራሱ የልብ በሽታ የማጋጠም እድላቸው ከጤነኛ ሰው በ 61 % ይጨምራል።
ይህ ቀላል አይደለም!
ለልብ አደጋ ለመጋለጥ የግድ ከመጠን በላይ ውፍረት መሆን አያስፈልግም። ቢኤም አይዎ ከመደበኛ ከፍ እስካለ ድረስ የመጋለጥ እድልዎ የጨመረ ነው።
🔍 ይህ በሽታ ነው !
ከመጠን በላይ መወፈር በህክምናው እንደበሽታ ነው የሚታሰበው። በልብ መዋቅር እና ኡደት ላይም ጎጂ ለውጦችን ያመጣል።
ቢኤም አይዎት ከመደበኛ መጠኑ በአንድ ሲጨምር የልብ ድካም አደጋን በወንዶች ላይ በ 5% እናም በሴቶች ላይ ደግሞ በ 7% ይጨምራል።

ሰውነትዎ ውፍረት እስካለው ድረስ ታታሪ ልብዎ መቼም ቢሆን ጤና አይደለችም። ሁልጊዜ ለአደጋ እንደተጋለጠች ነው። ታድያ በአመታት ውስጥ አንድ ቀን እጅ መስጠቷ አይቀርም። ትደክማለች ወይም የልብ ጥቃት ያጋጥማታል። ያን ጊዜ ግን አርፍደዋል።
📌አሳሳቢው ውፍረት፡ ቦርጭ
ቦርጭ የምቾት መስሎ ሊታይ ይችላል። ሆኖም ግን የሰውነት አካላት ጋር የተደበቀ የስብ ክምችት እጅ አዙር አመላካች ነው።
በድራፍት ጠጪዎች ላይ በብዛት ስለሚታይ የድራፍት ቦርጭ (beer belly) ይባላል። ውፍረት የሌለባቸው ቀጭን ሰዎች ላይ እንዲሁም ጥሩ ቁመና ያላቸው ሰዎች ላይም ይታያል። አንዳንዶች እንደውም ቢኤም አይ መስፈርታቸው ጤነኛ ሆኖ ቦርጭ ይኖራቸዋል።

ቦርጭ እስካለ ድረስ ልብዎ መቼም ሰላም አትሆንም።
በሆድ አካባቢ ውፍረት መኖር (ቦርጭ) የልብ ህመም ተጋላጭነትዎን ከግማሽ በላይ ይጨምራል። ቢኤም አያቸው ጤነኛ ሆኖ እንኳን ቦርጭ ያለባቸው ሰዎች እንኳን የልብ ህመም የመጋለጥ እድላቸው እስከ 33 ፐርሰንት የጨመረ ነው።

ያስተውሉ ይህ የመልክ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ጥያቄው የልብ ጤና ነው። ልብዎት ሁሌም አደጋ ላይ ናት!
🔥 ውፍረት ብቻውን አይመጣም።
ውፍረት ብቻውን አይመጣም። ጭፍሮች አሉት። ጀሌዎቹን አስከትሎ ነው የሚመጣው።ሰውነት ላይ በሚያደርሰው ጥቃት ብዙ በሽታዎችን ያመጣል። እነኝህም በሽታዎች በበኩላቸው ልብን ይበልጥ ያዳክማሉ።

ከመጠን በላይ መወፈር የደም ግፊትን ይጨምራል። ውፍረት በኩላሊት፣ በነርቭ ፣ በደምስሮችና በልብ ላይ በሚያደርሰው ጫና ፤ በአመታት ውስጥ ደም ግፊት እንዲከሰት ያደርጋል። ደም ግፊት በአለም ዙሪያ ለ ልብ ድካም እና ለስትሮክ ዋነኛ መንስኤ ሆኖ ይጠቀሳል።
ከመጠን በላይ ክብደት ሰውነታችን ከስኳር ጋር ግንኙነት ላለው ለ ኢንሱሊን ሆርሞን ምላሽ እንዳይሰጥ ያደርጋል። ይህም በአመታት ውስጥ የስኳር በሽታን ያስከትላል። የስኳር በሽታም በበኩሉ የልብ ድካም እና የልብ ጥቃት በማምጣት የታወቀ ነው።
ቢኤም አይዎ ከ 25 (ከመደበኛ) ከበለጠ የስኳር ተጋላጭነትዎ በ 5 እጥፍ የጨመረ ነው። ከ 30 ከበለጠ ደግሞ ተጋላጭነትዎ እስከ 28 እጥፍ ሊጨምር ይችላል።
📍 የደም ውስጥ ስብ ችግርና ውፍረት
ሲወፍሩ ቆዳዎ ስር እና አካላቶችዎ አጠገብ ሰውነትዎ ትርፍ ስብን ያከማቻል። ከዚህም አልፎ አንዳንዴ ደም ስር ግድግዳ ላይም ስብን ማስቀመጥ ይጀምራል። የተትረፈረፈው ስብም ወደ ደም እየገባ የደም ውስጥ ስብ መጠን ይጨምራል። ሚዛን ያቃውሳል።
ይህም እላይ ለጠቀስናቸው ለሁሉም በሽታዎች መንስኤ ይሆናል። አካላትን ያጠቃል። ደም ስር ያደድራል። ልብን ኩላሊትን ይጎዳል።
ይህ የተዛባ የስብ ክምችት በህክምናው ዲስሊፒደሚያ (dyslipidemia)ይባላል።

ስለ ደም ስብ ክምችት ለመረዳት ፤ ደም ውስጥ ስላሉ የስብ አይነቶች ማንሳቱ መልካም ነው። ባብዛኛው ማህበረሰብ ስለ ኮሌስትሮል በነሲብ ቢይቅም፤ የደም ውስጥ ስብ ኮሌስትሮል ብቻ አይደለም። በዋነኝነት አራት አይነት ስቦች አሉ።
የእነኝህን ስብ አይነቶች ፤ ጤናማ መጠናቸው እና ልብ አደጋ የሚያስከትሉበት ከፍተኛ መጠን እነሆ ፡
የስብ አይነት | ጤናማ መጠን | የልብ አደጋ የሚጨምረበት መጠን |
ጠቅላላ ኮሌስትሮል | <200 mg / dL | ≥240 mg / dL - ከፍተኛ አደጋ |
LDL ("መጥፎ") ኮሌስትሮል | <100 mg / dL | ≥160 mg / dL - ከፍተኛ አደጋ |
HDL ("ጥሩ") ኮሌስትሮል | ≥50 mg/dL (ሴቶች) / ≥40 mg/dL (ወንዶች) | ከእነዚህ ያነሰ - ከፍተኛ አደጋ |
ትራይግላይሴራይድ | <150 mg / dL | ≥200 mg/dL የልብ በሽታ ተጋላጭነትን ይጨምራል |
ያስተውሉ ከመጠን ባለፈ ውፍረት ጊዜ ይህ ሚዛን ይቃወሳል። የልብ ህመም ተጋላጭነትን በእጅጉ ይጨምራል።
ቀጭን መሆንስ ከዚህ አደጋ ነጻ ያወጣል?

"ቀጭን ነኝ! ስለዚህ ልቤ ጤናማ ነው።"የሚለውን አስተሳሰብ ማሰወገድ አለብን።
ለእይታ ቀጨን መምሰል ነጻ አያወጣም።
ለምን?
ለእይታ ቀጭን ቢመስሉም በሰወነትዎ ውስጥ በተለይ አካላትዎ ስር የስብ ክምችት ሊኖር ይችላል። የደም ውስጥ ስብ መዛባት ሊኖርብዎት ይችላል። በተለይ ደግሞ ቦርጭ ካለብዎ!
አዎ ! ጤናማ ክብደትን መጠበቅ ጠቃሚ ነው። ነገር ግን ከጤናማ የደም ቅባት መጠን ጋር ካልተጣመረ በስተቀር ፍጹም የልብ ጤናን አያረጋግጥም።
🍔 አመጋገቤ ምን ይምሰል ?

የሚበሉት ነገርን ማስተካከል እጅጉን ጠቃሚ ነው። የደም ውስጥ ቅባት መጠንን ይቀንሳል። የልብ በሽታ አደጋን ይቀንሳል።
🔹 በፍራፍሬ፣ በአትክልት፣ በጥራጥሬ የበለፀጉ ምግቦችን አዘውትረው ይመገቡ።
🔹 ጤናማ ስብ ይመገቡ። አለልክ የተጠበሱ ምግቦችን ፣ ጮማንና ቅቤን ይቀንሱ። በእነርሱ ፋንታ የእጽዋት ዘይቶችን ይመገቡ። አሳም የጤናም ስብ ምንጭ ስለሆነ ፤ አሳም መመገብ ይቻላሉ።
🥗 ኮሌስትሮሌን ለመቀነስ ምን ልመገብ?
የደም ውስጥ ስብ መጠንን ለማሻሻል የሚከተሉትን እንዲመገቡ ይመክራል።

✔ አጃ እና አዝእርት- የሚሟሟ አሰር (ፋይበር) ስላላቸው መጥፎ ኮሌስትሮል መጠንን ለመቀነስ ያግዛሉ።
✔ ጥራጥሬዎች (ባቄላ ፣ ምስር) - በፋይበርና በእፅዋት ፕሮቲን የበለጸጉ ስለሆኑ የመጥፎ ኮሌስትሮል መጠንን ይቀንሳሉ።
✔ የቅባት እህሎች - እንደለውዝ ያሉ የእጽዋት ቅባት ምንጮች ጤናማ ናቸው። የደም ውስጥ ስብ መጠንን ያሻሽላሉ።
✔ ዓሳ (ሳልሞን ፣ ሰርዲን) - የባህር ምግቦች በኦሚጋ 3 ዘይቶች የበለጸጉ ስለሆኑ ፤ ትራይግላይሰራይድ በመባል የሚታወቀውን የስብ አይነት ይቀንሳሉ።
✔ ቅጠላ ቅጠሎች እና ፍራፍሬዎች - አንቲኦክሲደንትስ እና አሰር (ፋይበር) ስላላቸው ፤ የደም ውስጥ ቅባት መጠንን ያሻሽላሉ።
ለዚህም እነዚህን ምግቦች ሲመገቡ የደምዎ ውስጥ ስብ መጠን ይሻሻላል።
🍟 ማስወገድ ያለብዎ ምንድነው?

❌ ቅቤና ጮማ ይቀንሱ።
❌ የታሸጉ ምግቦች አያዘውትሩ። ውስጣቸው ትራንስ ፋቲ አሲድ(TFA) ያላቸው ዘይቶች አይጠቀሙ ።
❌ ብስኩቶች እና ጣፋጮች አያዘውትሩ።
እነዚህ መጥፎ ኮሌስትሮልን አብዝተው ጥሩ ኮሌስትሮልን ይቀንሳሉ። በደም ስሮች ውስጥም ስብ እንዲከማች እድል ይፈጥራሉ።
እዚህ አመጋገብ ላይ ክብደት ቢቀንሱስ ?
ይህ እጅግ መልካም ነው!

የደም ውስጥ ስብ ክምችትዎ ይሻሻላል። ጤናማ ይሆናል። የልብ ህመም ተጋላጭነትዎ ይቀንሳል።
የቀነሱት ክብደት መጠነኛ ቢሆን እንኳን እንዳይዘናጉ። እንዳይሳነፉ ! ክብደትን በትንሹ መቀነስ እንኳን አመርቂ የሆነ ለውጥ ያመጣል። ውጤታማነቱ ከመድሀኒት ሊበልጥ እንደሚችል የሚጠቁሙ ጥናቶች አሉ።
ለውጥ የሚመጣው ቀስ በቀስ ነው። ይበርቱ!
አመጋገብዎን ያሻሽሉ። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ። ልብዎ አምዎት ሳይመጡ ፤ ዛሬውኑ እርምጃ ይውሰዱ!
መደበኛ ምርመራ ያድርጉ።
ለልብዎ ጤና ፈጽሞ ችላ እንዳይሉ!





Comments