top of page

ሰው ወድቆ ሲያገኙ ምን ማድረግ አለብዎት?

በምናብዎ ይሳሉት...


በጠራራ ጸሀይ ፤ በተጨናነቀ መንገድ ላይ እየተጓዙ ሳለ ድንገት አንድ ሰው እያዩት ይደናቀፋል።


ይወድቃል።


ከዛም አይንቀሳቀስም።


ሰዎች ይሰበሰባሉ። አንዳንዱ በትኩረት ይመለከታል። አንዳንዱ “ምናልባት ሰክሮ ይሆናል” ሲል ሌላኛው "ስኳር እንዳይኖርበት"ብሎ ያንሾካሹካል። ሌሎች ደግሞ በፍርሃት ወደ ኋላ ያፈገፍጋሉ።


በዚያች ቅጽበት እርስዎ ምን ያደርጋሉ?

ዝም ብለው የሚመለከቱ መንገደኛ ነዎት!? ወይስ በሕይወትና በሞት መካከል ያለ ድልድይ ይሆናሉ።


ልብ ከቆመ እና ኦክስጅን ካጣ በቀጣይ 5 ደቂቃ ውስጥ (ከ 4–6 ደቂቃዎች) ውስጥ የአእምሮ ጉዳት ይጀምራል። በእነዚህ ደቂቃዎች ውስጥ ሆስፒታል አይደርስም። አምቡላንስ አይደርስለትም።


ምን ማድረግ እንዳለብዎ ካወቁ ህይወቱን የሚያድኑ ደጉ ሳምራዊ ይሆናሉ።በእነኝህ ደቂቃዎች ውስጥ በአቅራቢያው ያለ ማንኛውም ሰው ፤ ከሐኪሞች በላይ ፋይዳ አለው።


ለዚህም ይህ መመሪያ ለ እርስዎ ነው።


የበሽታውን ዓይነት ማወቅ አያስፈልግዎትም። ምን ማድረግ እንዳለብዎት ማወቅ ብቻ ነው የሚጠበቅብዎት።


በመጀመሪያ እርስዎም ሁለተኛ ተጎጂ አይሁኑ

ወደ ፊት ከመሮጥዎ በፊት፣ ለጥቂት ጊዜ ቆም ይበሉ። አካባቢውን ይመልከቱ።

ትራፊክ አለ? የኤሌክትሪክ ገመዶች? እሳት? ግጭት? የጋዝ መፍሰስ?


አድናለው ብለው እርስዎ ከተጎዱ፣ ከአንድ አደጋ ይልቅ ሁለት አደጋ ይፈጠራል። ይህ ምንም ትርጉም የለውም። መጀመሪያ እራስዎን ይጠብቁ። ከአደጋው እራስዎን ያርቁ! አካባቢውን ደህንነቱ የተጠበቀ ያድርጉ። ከዛም፦


  1. የሕይወት ምልክት ይፈልጉ

አከባቢዎ አደጋ ከሌለው ፤ወደ ሰውየው ይቅረቡ። ትከሻውን በደንብ ይያዙ። በግልጽ ድምፅ ጮክ ብለው ይጥሩት/ያናግሩት፦ “ደህና ነህ/ሽ?” "የሚታወቅ ህመም አለ ወይስ የለም" ይበሉት።



ካወራ፣ ከተንቀሳቀሰ ወይም ካቃሰተ ፤ ደም ወደ አእምሮ እየደረሰ ነው ማለት ነው። ምንም ምላሽ ከሌለ ግን እንደ ከባድ አደጋ ይቁጠሩት።


  1. ይጣሩ! ዝምታውን ይሰብሩ!

በአደጋ ጊዜ ብዙ ሰው መኖሩ ጥቅም የለውም። እንደውም አደገኛ ነው። ምክንያቱም “ሁሉም ሰው ሌላ ሰው ይደውላል” ብሎ ያስባል። ስለዚህ ለይተው ይዘዙ።


አንዱን ጠቁመው፦ “ አሁኑኑ ወደ ድንገተኛ አምቡላንስ ደውል!” ይበሉ። ግልጽ ትዕዛዝ ጊዜን ይቆጥባል።


  1. ትንፋሽ ይመርምሩ። አይገምቱ! ይመልከቱ!


ደረታቸውን ይመልከቱ። ደረቱ በመደበኛ ሁኔታ ይነሳል፣ ይወርዳል?


ምላሽዎ አዎ ከሆነ እና ሰውየው ራሱን የሳተ ከሆነ ፤ ቀስ አድርገው በጎኑ ያስተኙት። ራሱን በመጠኑ ወደ ኋላ ዘመም ያድርጉት። አፉ እና ጉሮሮ ውስጥ ምንም ነገር አለመኖሩን ያረጋግጡ። እርዳታ እስኪመጣ ይቀጥሉ።

ታካሚውን በምስሉ ላይ እንደሚታየው ወደጎን ይገልብጡት
ታካሚውን በምስሉ ላይ እንደሚታየው ወደጎን ይገልብጡት

ይህ አተኛኝ አፍ ውስጥ የሚገቡ ነገሮች/ ምግቦች / ፈሳሾች ወደ ሳንባ እንዳይገቡ ያደርጋል። ቢያስታውክ እንኳን ወደ ሳንባ እንዳይገባ እና እንዳይታፈን ይረዳል።


ትንፋሽ ከሌለ ግን ወዲያውኑ እርምጃ መውሰድ አለብዎት።

አፍ ውስጥ ያለ ትንፋሽን የደፈነ አካል ካለ ይፈልጉ። ምላስ ወደ ኋላ ተኝቶ ጉሮሮን አለመድፈኑን ይመልከቱ። አፍን የደፈነ አካል ከሌለ እና እየተነፈሰ ካልሆነ ለወደቀው ሰው እርስዎ መተንፈስ ይኖብዎታል። አፍ ለአፍ ትንፋሽ ለመስጠት ይዘጋጁ።


  1. ልብን ያዳምጡ።

ልብ ከቆመ፣ ኦክስጅን ወደ አእምሮ አይደርስም። ደሙን እርስዎ በእጅዎ መግፋት/ ማዘዋወር አለብዎት።


እጅዎትን በምስሉ ላይ እንደሚታየው በደረቱ መሀል ላይ አነባብረው ይግፉ።
እጅዎትን በምስሉ ላይ እንደሚታየው በደረቱ መሀል ላይ አነባብረው ይግፉ።
  • ዘዴው፦ የአንዱን እጅዎን መዳፍ ደረት መሃል ላይ ያድርጉ። ሌላኛውን እጅ በላዩ ላይ ያድርጉ። ክንድዎን ሳያጥፉ፤ በጥልቀትና በፍጥነት ይጫኑ።

  • መጠኑ፦ እየቆጠሩ 30 ጊዜ ደረቱን ይጫኑ።ከዛም ሁለት ጊዜ ትንፋሽ አፍ ለአፍ ይስጡ።

ይህ በህክምናው ሲ ፒ አር (CPR) ይሰኛል።


እርዳታ እስኪመጣ ይህን ይቀጥሉ። አፍ ለአፍ ትንፋሽ መስጠት ካልቻሉ የደረት መጫኑን ብቻ በየ 30 ዙር እያረፉ ይቀጥሉ።


ያስተውሉ! የጎድን አጥንት ቢሰበር እንኳ ይድናል፤ የሞተ አእምሮ ግን አይድንም። ለዚህም እንዳያቆሙ!


  1. ከባድ የደም መፍሰስ ካለስ?


በምስሉ እንደምታዩት አንገት ላይ የተስካው እንጨት እንዳይነቀል ደግፈውታል እንጂ አልነቀሉትም።
በምስሉ እንደምታዩት አንገት ላይ የተስካው እንጨት እንዳይነቀል ደግፈውታል እንጂ አልነቀሉትም።

ደም በከፍተኛ ሁኔታ እየፈሰሰ ከሆነ ቁስሉን በጨርቅ ተጭነው ይያዙት። በሰውነቱ ውስጥ የተሰካ ነገር ካለ (ጩቤ፣ ቢላ፣ መስታወት፣ሆነ ማንኛውም አካል)በፍጹም አይንቀሉት!

ብዙ ደም እንዳይፈስ ዘግቶ የያዘው እርሱ ይሆናል። ከነቀሉት ከባድ ደም መፍሰስ ሊያጋጥም ይችላል።


  1. የሚጥል በሽታ ካለ/እየተንቀጠቀጠ ከሆነስ?


አንድ ሰው በሚጥል በሽታ (Seizure) ምክንያት ራሱን ሊስት፣ ሊወድቅ ወይም ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የሰውነት መንቀጥቀጥ ሊያጋጥመው ይችላል። እዚህ ላይ ማስታወስ ያለብዎት ዋናው ነገር አንዴ የጀመረን መንቀጥቀጥ ማቆም እንደማይችሉ ነው።


የእርስዎ ብቸኛ ኃላፊነት ንቅናቄው እስኪያበቃ ድረስ ሰውየው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መጠበቅ ነው። በመሆኑም ይረጋጉ ፤ አካባቢውን ከጠንካራ ወይም ከሹል/ከሚጎዱ ነገሮች ያጽዱ። እናም ጃኬት/ልብስ /ለስላሳ ጨርቅ አጥፈው ከራሳቸው ስር ያድርጉላቸው። አንተራሷቸው።


መንቀጥቀጡ ሲቆም፣ አየር በደንብ እንዲያገኙና ራሳቸውን እስኪያዉቁ ድረስ በቀላሉ እንዲተነፍሱ ቀስ አድርገው በጎናቸው ያስኝቷቸው።


በፍጹም አፋቸው ውስጥ ምንም ነገር አይክተቱ። ምላሳቸውን እንዳይነክሱ አፋቸው ውስጥ የሚከቷቸው ነገሮች ጥርሳቸውን ሊሰብር ወይም የመተንፈሻ ቱቦአቸውን ሊዘጋ ይችላል።


በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ሰውየውን ለመያዝ ወይም እጅና እግራቸውን እንዳይንቀሳቀስ ለማድረግ አይሞክሩ፤ የንቅናቄው ኃይል ከእርስዎ ግፊት ጋር ሲጋጭ የአጥንት መሰበር ወይም የጡንቻ መበጠስ ሊያስከትል ይችላል።


በመጨረሻም፣ ሙሉ በሙሉ ነቅተው በግልጽ መናገር እስኪጀምሩ ድረስ ውሃ ወይም ምግብ አይስጧቸው። ምክንያቱም ገና በትክክል መዋጥ ሊያስቸግራቸው ይችላል። ለዚህም የሚሰጣቸው ምግብ ወደ ሳንባ ገብቶ ሊያፍናቸው/ ትን ሊላቸው ይችላል።


ኪሳቸው ውስጥ የሚጥል በሽታ መድሀኒት ካለ እንዲውጡ ይስጧቸው።


  1. የአካል ጉዳት እንዳለ ከተጠረጠረ

ሰውየው፦

  • ከከፍታ ላይ የወደቀ ከሆነ

  • በተሽከርካሪ የተገጨ ከሆነ

  • ግልጽ የሆነ የአካል ጉዳት ካሳየ

ያለ አስፈላጊ ምክንያት አያንቀሳቀሷቸው። የአከርካሪ አጥንት ጉዳት ደርሶባቸው ቢሆን ፤ ማንቀሳቀስዎ ለዘላቂ ሽባነት (Paralysis) ሊዳርግ ይችላል። ከዚህም አልፎ ሲያንቀሳቅሷቸው ፤ የተጎዳ የአንገት አከርካሪ አጥንትን ሊሰብሩ/ሊቀጯቸው ይችላሉ።


ሰውየውን ማንቀሳቀስ የሚገባው ፤ እዚያው ባለበት ቢቆይ የከፋ ጉዳት ሊደርስበት የሚችል ከሆነ ብቻ ነው (ለምሳሌ እሳት ካለ፣ አስፋልት መሀል ከወደቀ፣ ወ.ዘ.ተ...)።


🚫 እነኝህን አያድርጉ!



ፊት ላይ ውሃ አይርጩ፦ የቆመ ልብን አያስነሳም፣ ጥቅም የለውም።


መጠጥ፣ ምግብ ወይም መድኃኒት በአፋቸው አይክተቱ፦ ካልነቁ ሳንባ ውስጥ ገብቶ ለሞት ይዳርጋል።


የሚጥል በሽታ ሲነሳባቸው አፋቸው ውስጥ ምንም ነገር አይክተቱ፦ ምላሳቸውን አይውጡም፤ ነገር ግን ጥርሳቸውን ሊሰብሩ ወይም ትንፋሽ ሊዘጉ ይችላሉ።


ሰክሯል ብለው አይገምቱ፦ የስኳር መውረድ፣ ስትሮክ እና የልብ አደጋ ሁሉም ከስካር ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ስክሯል ብለው ችላ ብለው እንዳይሄዱ። የተቻሎትን አድርጉላቸው።


🥤ሚሪንዳ፣ ለስላሳ መጠጦች እና ክብሪትስ?


ሰው ወድቆ ሲያገኙ ፤ ብዙ ሰዎች ሚሪንዳ ወይም ጣፋጭ መጠጥ አልያም ውሀ ያሰጣሉ። ይህ የሚደረገው በቅንነት ቢሆንም ፤ የራሱ አደጋ ይኖረዋል። ራሱን የሳተ ሰው መዋጥ አይችልም፤ ፈሳሹ ወደ ሳንባው ይገባል።



ልቡ ለቆመ ሰው ስኳር ቢሰጠው ፤ በሰውነት ውስጥ አይዘዋወርም። ችግሩ ስኳር ሳይሆን የደም ዝውውር መቆም፤ ኦክስጅን ማነስ ነው።


ለዚህም ሚሪንዳ፣ ለስላሳ መጠጦች እና ውሀ ከመስጠትዎ በፊት ይህንን ያረጋግጡ!

ሰወየው ነቅቶ ያወራል ወይ? ምላሹ አይ ከሆነ ፈጽሞ አይስጡ!

ይህን ይጠንቀቁ! ራሱን የሳተ ሰው መዋጥ አይችልም


አንድ ሰው ራሱን ሲስት ፤ የመዋጥ ስሜቱ ስለሚስተጓጎል ፤ የመተንፈሻ ቱቦው ምንም መከላከያ አይኖረውም። ያለው ፈሳሽ ወደ ጨጓራ መሄድ ሲገባው ወደ ሳንባ ይገባል ። ይህም አደገኛ ነው። ስለዚህም መንቃቱን እና መጠጣቱን ሳያቅ ምግብ እና ፈሳሽ አይስጡ!


ክብሪት ማሽተትስ?


ይህ የራሱ የሆነ ባህላዊ ትርጉም ቢኖረውም ፤ ፋይዳ የሌለው ተግባር ነው። የቆመ ልብን አያስነሳም፤ ይልቁንም ወርቃማውን ጊዜ ያባክናል።


⏳ ያስተውሉ እያንዳንዱ ሰከንድ ዋጋ አለው!

ልብ ሲቆም አእምሮ ኦክስጅን ወዲያውኑ ያጣል። ከ4-5 ደቂቃ በኋላ የአእምሮ ሕዋሳት በኦክስጅን እጦት መሞት ይጀምራሉ። በእያንዳንዱ ደቂቃ የመተርፍ እድል በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። እርስዎ ሲፒአር (CPR) ሲጀምሩ ግን ፤ የደም ዝውውር ወደ አእምሮ እንዲደርስ ያደርጋሉ። ለዚህ ጊዜ እየገዙለት መሆኑን ይወቁ። የመኖር ተስፋ እየሰጡት ነው።


ሆኖም ግን በእኛ ማህበረሰብን ጨምሮ በብዙ ቦታዎች ምንም እርዳታ ሳያገኝ ይህ ሰአት ይባክናል። ለምን?

  • ሰዎች የህግ ተጠያቂነትን ይፈራሉ።

  • ሰዎች የማያውቁትን ሰው ለመንካት ይቸገራሉ። አፍ ለአፍ ትንፋሽ ለመስጠት ይፈራሉ።

  • አንዳንዶች ከመርዳት ይልቅ በስልክ መቅረጽን ይመርጣሉ።


ነገር ግን ራስዎን ጠብቀው የሌላን ሰው ህይወት ማዳን ይችላሉ። ባይችሉ ደውለው አምቡላንስ ይጥሩ! ሰውን በደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ መርዳት የሰብአዊ ክብር መገለጫ ነው።


❤️ ማስተዋል ያለብዎ ነገር!


አንድ ቀን የወደቀው ሰው እንግዳ ላይሆን ይችላል። አባትዎ፣ እህትዎ ወይም ልጅዎ ሊሆን ይችላል።


ያን ጊዜ በህይወት እና በሞት መሀከል ያለው ለውጥ ፤ እንደርስዎ ለመርዳት በወሰነ ሩህሩህ ሰው ላይ ይወሰናል። ይህ ሰው ምን ማደረግ እንዳለበት ባያውቅስ ?


ለዚህም ይህን ትምህርታዊ ጽሁፍ ለብዙዎች እንዲዳረስ ያጋሩ።


ህይወት ያድኑበታል!



Comments


bottom of page