top of page

ከእድሜ ጋር የሚያያዘው የአጥንት መሳሳት ህመም

Updated: Jul 11

ለመሆኑ ሰው ወለም ብሎት የቁርጭምጭሚት ቀዶ ህክምና ሊያስፈልገው ይችላልን? ምን ይመስልዎታል? ያጋጠመው ሰውስ ያውቃሉ?


ይህ የምታውቁት ሰው ወንድ ነው ሴት? እድሜውስ?


የወለምታ ስብራት

(እውነተኛ ታሪክ)

ree
እናት እጅጉን ታታሪ በመሆናቸው ፤ በ80 አመታቸው እንኳን ይሰሩ ነበር። ታድያ አንድ ጠማማ ቀን ላይ ከስራ ሲመለሱ ፤  ታክሲ ሊይዙ ሲሉ ፤ ድንገት ወለም ብሏቸው ወደቁ። ላለፉት ስንት አስርት አመታት እላይ እታች ብለው ፤ ልጆቿቸውን ለቁም ነገር ላበቁ እናት ወለምታ ተራ ነበር። ከዚህ በላይ አሸን ጊዜ ወድቀው ተነስተዋል። እንዳሳለፉት ህይወት ፤ እንደተጋፈጡት ችግር ፤ ለእኝህ እናት ወለምታ ምናቸው?
ሆኖም ግን ያሁኑ ወለምታ ለየት ያለ ሆነባቸው። ምንም ልባቸው ቢጀግንም የዚህ ወለምታ ቁስል የሚሽር አልሆን አላቸው። የዚህን ጊዜ ልጆቻቸው ተሯሩጠው ሀኪም ቤት ይዘዋቸው ሄዱ። እና እዛም የተደረገው የኤክስ ሬይ ምርመራው ፈጽሞ ያልጠበቁት ሆነ። 
አንድ አጥንት አይደለም። የግራ እግራቸው ሁለቱም አጥንቶች ቁርጭምጭሚታቸው አከባቢ ተሰብረዋል። ልጆች ማመን ከበዳቸው። "ወለም ነው እኮ ያላት!" ይላሉ ህመሙን ሲያስረዱ ። 
ይህ ስብራት በህክምናው የፖትስ ስብራት (Potts fracture) ሲባል፤ በእዚህ የእድሜ ክልል የተለመደ ነው። እኝህ እናትም በቀጣይ ቀን በቀዶ ህክምና ስብራታቸው ተስተካከለላቸው ። ሆስፒታል ውስጥ ለ ሁለት ሳምንት ከቆዩ በኋላ ወደ ቤት ተመለሱ።  
ከሆስፒታል ከወጡም በኋላ ፈጽሞ ለማገገም ረዥም ጊዜ ወሰደባቸው። ሆኖም ግን ሙሉ ፈውስ አላገኙም።  እንደድሮው ተሳፍረው ሩቅ ሄደው ስራ ሰርቶ መምጣት ተሳናቸው። እንቅስቃሴያቸው ተገደበ። ከ ቀዶ ህክምናው በኋላ መጣ ሄድ የሚል፤ በቅዝቃዜ የሚብስ ህመም ነበረባቸው።  

ታድያ ግን ይህ ታሪክ የእኝህ እናት ብቻ አይደለም። ብዙ እድሜያቸው የገፋ እናቶቻችን ፤ አንዳንድ ህመም ያለባቸው ፤ ደካማ አመጋገብ ያለባቸው ቤተሰቦቻችን ተመሳሳይ እክል አጋጥሟቸዋል።


እንኳን ወለም ብሏቸው አልያም አደናቅፏቸው ይቅርና ፤ ዘለው ሲያርፉ አጥንታቸው የተሰበረም አይጠፉም።

ይህ የሚፈጠረው በአጥንት መሳሳት የተነሳ ነው። በዚህም ትምህርታዊ ጽሁፍ ፤ በይበልጥ ሴቶችን ስለሚያጠቃው የአጥንት መሳሳት አይነት በትኩረት እናነሳለን።


🌪 የአጥንት መሳሳት ምንድን ነው?

የአጥንት መሳሳት ህመም ፡በግራ በኩል የሚታየው ጤናማ አጥንትነው። በመሀል እና በቀኝ ያሉት የሳሱ አጥንቶች ናቸው።
የአጥንት መሳሳት ህመም ፡በግራ በኩል የሚታየው ጤናማ አጥንትነው። በመሀል እና በቀኝ ያሉት የሳሱ አጥንቶች ናቸው።

የአጥንት መሳሳት በህክምና ስሙ ኦስቲዮፖሮሲስ ሲባል ፤ የ አጥንታችን ጥንካሬ ከቀን ወደቀን እየተመናመነ ሲመጣ የሚከሰት ነው። ይህ ሲያጋጥም አጥንታችን በመገንባት ፋንታ እየፈረሰ ይመጣል። አጥንታችንን ጥንካሬ የሚሰጡት የካልሺየም እና የ ፎስፌት ማእድናት ፤ አጥንት ውስጥ ያላቸው መጠን ይቀንሳል። ለዚህም አጥንታችን ይሳሳል። ስለሳሳም በቀላል ኃይል ይሰበራል።


ለዚህም ሲዘሉ ፤ ድንገት ፈጣን እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ፤ ወለም ሲላቸው ፤ ሲያደናቅፋቸው ፤ አጥንታቸው ይሰበራል። አጥንታቻው ስለሳሳ ፤ አሁን ትንሿ ኃይል ያይለ ጉዳቷ ታደርሳለች።


አዳልጧቸው ወድቀው ፤ በመኪና እንደተገጩ ደረጃ የዳሌ ስብራት ጋጥማቸዋል።

ይህም ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች አሉት። ከእድሜ ጋር የሚያያዝ ቢሆንም ፤ በሁሉም የእድሜ ክልል ይከሰታል። እድሜ ሲገፋ ሰውነት እራሱን የመገንባት አቅሙ ስለሚዳከም ፤ የአጥንት መሳሳትም በይበልጥ ይከሰታል። ከወንዶች ይልቅ ሴቶችን አብዝቶ ያጠቃል።


👩🏽‍🦳 ሴቶችን ለምን በይበልጥ ያጠቃሉ?


አጥንት መሳሳት ሴቶች ላይ ማየሉ ፤ በዋነኝነት ከሆርሞን ጋር ይያዛል። ሴቶች በመውለጃ እድሚያቸው ላይ ሆነው ፤ ያላቸው የ ኢስትሮጅን ሆሮሞን (Estrogen) መጠን ከፍተኛ ነው። ይህ ሆርሞን ደግሞ አጥንት ውስጡ ገንቢ የሆኑ ማእድናትን እንዲያስቀምጥ ስለሚያደርግ ፤ አጥንት ጥንካሬው እንዲጠበቅ ያደርጋል። ለዚህም በሴቶች አጥንት ጥንካሬ ላይ ከፍተኛ የሆነ ሚና ይጫወታል።

የሴቶች የ ኢስትሮጅን ሆርሞን መጠን ከእድሜ ጋር
የሴቶች የ ኢስትሮጅን ሆርሞን መጠን ከእድሜ ጋር

ሴቶች የመውለጃ እድሜያቸው ካለፈ በኋላ የዚህ ሆርሞን መጠን እየቀነሰ ይመጣል። ይህም ሆርሞን መጠን መቀነሱ ፤ ሙሉ የሰውነት አካላት ላይ ተጽእኖ ያሳድራል። በመቀነሱ አጥንት ላይ ያለው ተጽእኖ እንዲሁ ይዳከማል። አሁን አጥንት ውስጥ ገንቢ የሆኑ ማእድናት አይቆዩም። ይህም በመሆኑ የአጥንትን ጥንካሬን መጠበቅ ይሳነዋል።


መረጃዎች እንደሚያሳይቱ ከሆነ ፤ ሴቶች ማረጥ ከጀመሩ በኋላ ባሉ ከ5-7 ዓመታት ውስጥ ፤ እስከ 20% የሚሆነውን የአጥንት ክብደት ሊያጡ ይችላሉ።

እድሜ በገፋ ቁጥር ፤ የዚህ ሆርሞን መጠንም እጅጉን እየቀነሰ ይመጣል። የአጥንትም መሳሳትም እንዲሁ። ለዚህም እድሜ ሲጨምር ፤ አጥንት በቀላል እንቅስቃሴ የመሰበር እድሉ እያየለ ይመጣል።


በአለም አቀፍ ደረጃ እድሜያቸው ከ50 በላይ ከሆናቸው ሶስት ሴቶች አንዷ አንዷ የአጥንት ስብራት ያጋጥማታል።

ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?


የአጥንት መሳሳት ማስጠንቀቂያ ምልክቶች የሉትም።
ree
  • አጥንት ሲሳሳ ምንም አይሰማም። በመስታወት ውስጥ አያዩትም። ጉዳቱ ቀስበቀስ የሚደረጅ ነው።


  • ቁመት ይቀንሳል (ብዙውን ጊዜ ከ3-5 ሴ.ሜ ወይም ከዚያ በላይ)


  • አቋም ይለወጣል። ሰውነት ይጎብጣል።


  • የአከርካሪ አጥንትን ከተጠቃ ፤ ጥቃቅን የአከርካሪ አጥንት ስብራቶች ያጋጥማሉ። ለዚህም በጀርባ ህመም ይሰቃያሉ።


  • በቀላል እንቅስቃሴዎች ከባድ የሆነ ጉዳት ያጋጥማል።


የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ


የአጥንት መሳሳት ተከትሎ የሚመጡ ስብራቶችን የሚያሳይ ሀገር አቀፍ መረጃ የለንም። ስለ አጥንት መሳሳት ሰምተው የማያውቁ ሴቶችም ጥቂት አይደሉም። አንዳንዶች ስብራት ሲያጋጥማቸው ነው ስለ አጥንት መሳሳት የሚያውቁት። በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ ደረጃ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከሆነ፡


  • እስራኤል አገር ከሄዱ ኢትዮጵያዊ ቤተ እስራኤላውያን መሀከል 38.7% የአጥንት መሳሳት አለባቸው። ይህ እስራኤል ሀገር ከተወለዱ ኢትዮጵያዊ ቤተ እስራኤላውያን አንጻር በ 33.6 % (5.2% ነው) ይበልጣል። ይህም የሚያመላክተው ከአኗኗራችን እና ከአመጋገባችን ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ነው።


  • በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከታከሙ አስር የአጥንት ስብራት ህሙማን መሀከል ፤ አንዱ ስብራት በአጥንት መሳሳት የተነሳ የመጣ ነው። እድሜያቸው ከ 40 አመት በላይ ከሆኑ አስር የአጥንት ስብራት ታማሚዎች መሀከል ደግሞ ፤ ሶስቱ ስብራት ያጋጠማቸው በአጥንት መሳሳት የተነሳ ነው ።


  • በትግራይ ውስጥ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ደግሞ ፤ ከ አጥንት ስብራት ታካሚዎች መሀከል 9.3% የሚሆኑት የአጥንት መሳሳት አለባቸው። አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት እድሜያቸው ከ40-49 የሚሆኑ ሴቶች ናቸው።


  • ከከተማ አንጻር በገጠሯ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ግለሰቦች ለአጥንት መሳሳት ያላቸው ተጋላጭነት በእጥፍ ይጨምራል።


ለምን እንዲህ ተንሰራፋ?


በሀገራችን ኢትዮጵያ የአጥንት መሳሳት ህመም ደረጃ ከፍ ለማለቱ የተለያዩ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ። ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ግን አኗኗራችን እና አመጋገባችን ነው። ለዚህም በቤተ እስራኤላውያን ዘንድ የተሰራውን ጥናት ዋቢ አድርጎ መጥቀስ ይቻላል። ለዚህ መንስኤ ሊሆኑ ከሚችሉ ልማዶቻችን በጥቂቱ፡

ree

  • በካልስየም የበለጸጉ የወተት ተዋጽኦዎች ተዘውትረው አይወሰዱም። ይህን አዘውትረው ከወሰዱ የሚወስዱት ህጻናት ናቸው። የመውለጃ እድሜያቸው ያለፈ ሴቶችም ፤ በደንብ አዘውትረው መውሰድ አለባቸው።


  • ብዙ ሴቶች (በተለይ በገጠሪቷ ኢትዮጵያ) አብዛኛውን ጊዜ ሲንቀሳቀሱ ፤ ከላይ እስከታች ቆዳቸውን የሚሸፍኑ ልብሶችን ይለብሳሉ። የጸሀይ ብርሀን የሚያገኘው ሰውነታቸው እጅጉን ውስን ነው። ይህ ደግሞ የቫይታሚን ዲ ደማቸው ውስጥ እንዳይጎለብት ይገድበዋል። ይህም ለአጥንት መሳሳት ያጋልጣል።


  • አካል እንቅስቃሴ አዘውትሮ መስራት የተለመደ አይደለም። አካል እንቅስቃሴን ከወጣትነት ጋር የማያያዝ ብሂል አለ። እድሜ ሲገፋ አጥንትን ማጠንከር የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች ቢያስፈልጉም ፤ ይህ ፈጽሞ አልተለመደም። በእርጅና ዘመን ማን አስቦበት?!


  • እድሜ ሲገፋ ከሚመጡ የጀርባ ህመም መንስኤዎች ውስጥ አንዱ የጀርባ አጥንት መሳሳት ይኖርበታል። ታድያ ግን ሴቶች ቁመታቸው ሲያጥር ፤ የጀርባ ህመም ሲያይል ፤ ሲጎብጡ የአጥንት መሳሳት ተብሎ አይታሰብም።


  • መደበኛ ምርመራ አልተለመደም። በተለይ የማረጫ እድሜ ያለፉ ሴቶች የአጥንታቸውን ጤና መከታተል ቢኖርባቸውም ፤ ማን አስተውሎት ?


የ ችግሩ መጠን


የአጥንት መሳሳትን ፈጽሞ እንደቀላል ማየት የለብንም። የአጥንት መሳሳት ዳፋው ከአጥንት አልፎ ፤ ህይወትን ያሰናክላል። የአልጋ ቁራኛ ያደርጋል። ከከፋም እስከሞት ሊያደርስ ይችላል።


  • በአለም አቀፍ ደረጃ የዳሌ ስብራት ካጋጠማቸው 5 ሴቶች አንዷ ፤ ዳሌ ስብራት በአጋጠማት በአመቱ ውስጥ ትሞታለች።


  • የዳሌ ስብራት ካጋጠማቸው እስከ 40% የሚሆኑት ሴቶች ለተረፈው ህይወታቸው ጥገኛ ይሆናሉ። ንጽህናቸውን ለመጠበቅ ፤ መጸዳጃ ቤት ለመጠቀም ፤ ለመንቀሳቀስ የሌላ ሰው እገዛን ይፈልጋሉ።


  • ቤተሰብን ቀጥ አድርገው ያስተዳድሩ የነበሩ እናቶች ፤ ሸክም ሲሆኑ ይጨነቃሉ ። ስብራቱን ተከትሎ ከማህበራዊ ቁርኝት መራቃቸው ፤ ይህንን ጭንቀት ያብሰዋል። በገንዘብም ጥገኛ ይሆናሉ።


  • በህክምናው በኩል ካየነው ደግሞ ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው ደረጃ ለህክምና በብዙ ሺዎች ያስፈልጋል። ታድያ አንድ ከእጀ ወደ አፍ ኑሮ የምትኖር እናት እጣዋ ምን ይሆን ?


ለ እነኝህ ስብራቶች በሀገር ደረጃ ብዙ ትኩረት የተሰጠ ባለመሆኑ ፤ ታካሚዎች ህክምና ለማግኘት ይዘገያሉ። የማገገሚያ ህክምናም የተሟላ ባለመሆኑ ብዙዎች ከጉዳት ጋር ህይወትን ይመራሉ።

መልካሙ ዜና ግን ፈጽሞ መከላከል ይቻላል።


💪🏽ከዛሬ ጀምሮ ምን ማድረግ ይችላሉ?


ከዚህ በኋላ የአጥንት መሳሳት ህመምን ችላ ማለት የለብዎትም። ልማዶትን በመለወጥ ፤ አኗኗሮትን በማስተካከል መከላከል ይችላሉ። ለዚህም የሚከተሉትን ተግባራዊ ለውጥ ያድርጉ።


እድሜዎ ከ 40 አመት በላይ ያለ ሴት ነዎት? እድሜው የገፋ የቤተሰብ አባል አለዎት?መልስዎ አዎ ከሆነ እነኝህ ምክሮች በይበልጥ እርስዎን ይመለከታሉ።
ree
  1. አበላልን ያስተካክሉ፡ በካልሽየም የበለጸጉ ምግቦችን ፤ በተለይ የወተት ተዋጽኦዎችን ፤ ቢያንስ በሳምንት 4 ጊዜ መጠቀም የ አጥንት መሳሳት ተጋላጭነት በደንብ ይቀንሳል (ኢትዮጵያ ውስጥ የተደረገ ጥናት ይህን አረጋግጧል)።


  2. እንቅስቃሴ ያዘውትሩ ፡ ለጉልበት ስራ አይቦዝኑ። አጥንት የሚያጠነክሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን (መራመድ፣ ቀላል ሸክሞችን መሸከም፣ ደረጃዎችን መውጣት፣ መደነስ) ያዘውትሩ።


  3. ሲጋራ አያጭሱ ። አጥንት ያሳሳል።


  4. የተመጣጠነ ምግብ ይመገቡ።


  5. ኮካኮላ መጠጣት አያዘውትሩ። ውስጥ ያለው ፎስፎሪክ አሲድ ከአጥንት መሳሳት ጋር ይያዛልና ፤ ተጋላጭነት ካለብዎ ፤ ኮካኮላ መጠጣት አያዘውትሩ።

  6. ክብደትዎ ጤናማ ደረጃ ያድርጉ። መክሳት ወይም ዝቅተኛ ቢኤም አይ ከ አጥንት መሳሳት ጋር ቁርኝት አለው።


  7. አለባበስዎን ያሻሽሉ። ጸሀይን አብዝቶ የሚከልል አለባበስ አይኑርዎ። በቂ የጸሀይ ብርሀን ለአጥንትዎ ጤና አስፈላጊ ነው። ቢያንስ በቀን ከ 15 እስከ 30 ደቂቃ በቂ የጸሀይ ብርሀን ማግኘት አለብዎ።


  8. በተለይ ሴቶች እድሜያቸው ከ 40 አመት በላይ ከሆነ ፤ መደበኛ የአጥንት ምርመራ ማድረግ አለባቸው።


  9. በምግብ በቂ ካልሽየም መጠን መውሰድ ካልተቻለ በእንክብል ይወሰዱ (Calcium and vitamin D supplement)። በተለይ ሴቶች የመውለጃ እደሜያቸው ካለፈ ዶክተር አማክረው ይውሰዱ።



🎯 ስለ አጥንትዎ ጤና እንነጋገር።


አጥንትዎ እስኪሳሳ አይጠብቁ። አስቀድመው ይከላከሉ። አጥንትዎን ይገንቡ።


ዛሬ የሚያደርጉት ተግባራዊ ለውጥ የአጥንትዎን ጤና ይወስናል።





.




.

Comments


bottom of page