top of page

117 results found with an empty search

  • የሐሞት ጠጠር ምልክቶቹና ህክምናው

    መቼም አብዛኞቻችን ሀሞት እናውቃለን?   ሀሞት በባህላችን በንግግራችን በእምነታችን ጋር የተለያየ ትርጉም አለው። ሀሞትን በተለምዶ ኮምጣጣነትን ፣ ጀግንነትን ለመግለጽ እንጠቀመዋለን። 'ሀሞቴ ፈሠሠ' የሚለውን ቃል እንኳን ተነሳሽነት ማጣታችንን ለመግለጽ ፤ በንግግራችን መሀል እንጠቀማለን። አባቶቻችንም ጮማ የበዛበት ጥሬ ስጋ ሲበሉም እንዲስማማምቸው በሀሞት ይበላሉ።   በህክምናስ ሀሞት ምንድነው?   ሀሞት ከፈረሰ የቀይ የደምህዋስ በጉበት ውስጥ የሚሰራ ፤ ሰውነታችን ምግብ ለመፍጨት የሚጠቀመው ውህድ (ኤንዛይም)ነው። ይህም ውህድ በጉበት ቢመረትም ፤ ስራው አንጀት ላይ ነው። ታድያ ስራ እስኪውል ድረስ በጊዜያዊነት ከጉበት ስር ባለ ከረጢት ውስጥ ይከማቻል። ለዚህም ይህንን ከረጢት የሀሞት ከረጢት እንለዋለን።   ታድያ ሀሞት በዋነኝነት የሚሰራው ቅባት/ ስብ ለመፍጨት ነው። ቅባት ያለው ምግብ በብዛት ሲበላ ሰውነት በከረጢት ያስቀመጠውን ይህን ሀሞት ይጠቀማል። ታድያ እንዴት እዚህ ከረጢት ውስጥ ጠጠር ሊገኝ ቻለ?   ዛሬ ስለ ሀሞት ጠጠር በጥልቀት እናነሳለን።   የሀሞት ጠጠር ምንድነው? ይሄ ጊዜያዊ ማከማቻ የሆነው የሀሞት ከረጢት ውስጥ ፤ ጠጠር ሲከማች የሀሞት ጠጠር ይባላል። እነኝህም ጠጠሮች መጠናቸው ይለያያል። አንዳንዶቹ እንደ አሸዋ ደቃቅ ሲሆኑ ፤ ሌሎች ደግሞ ብይ ያህል ሊገዝፉ ይችላሉ።  መልካቸውም እንደመንስኤያቸው ይለያያል። ታድያ የሀሞት ጠጠር እንዴት ይፈጠራል? አንድ ወፍራም ውህድ/ፈሳሽ ውሀ ለረዥም ጊዜ ረግቶ ሲቆይ ፤ ዝቃጭ ወይም አሸዋ እንደሚፈጥረው ሁሉ ፤ የሀሞት ሚዛን ሲዛባ የሀሞት ጠጠር ይፈጠራል።  ይህም እንዲፈጠር የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። በዚህ ላይ ተመስርተን በሶስት ልንመድበው እንችላለን።   ሀሞት ውስጥ በኮሌስትሮል መብዛት የሚመጣው የኮሌስትሮል ጠጠር አንዱ ሲሆን ፤ በመልኩም ነጭ ነው ። ለሀሞት ምርት ግብአት የሚሆነው የቀይ የደም ህዋስ በብዛት ሲሞት አልያም የጉበት ጠባሳ ካለ ጥቁር የሀሞት ጠጠር ይፈጠራል። ኢንፌክሽንን ተከትሎ የሚፈጠረው የሀሞት ጠጠር ደግሞ  ቡናማ ቀለም ይኖረዋል።    ታድያ ይህ ጠጠር ከአንጀት ጋር በሚያገናኘው ቀጭን ቱቦ ለማለፍ ሲሞክር በሀሞት ጠጠር ጊዜ የሚታወቀው ከባድ ህመም ይሰማል። የሀሞት ጠጠር አጋላጭ መንስኤዎቹም የሚከተሉት ናቸው። ዕድሜ መጨመር(ከ40 ዓመት በኋላ አደጋው ይጨምራል)፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት እና ፈጣን ክብደት መቀነስ፣  የስኳር በሽታ ፣ የደም ስብ/ኮሌስትሮል ችግርና (dyslipidemia)፣ እርግዝና ይጠቀሳሉ።  ሴቶች ደግሞ በተፈጥሮ የኢስትሮጅን ሆርሞን ስላላቸው ፤ ተጋላጭነታቸው ከወንዶች የበለጠ ነው። የኢስትሮጅን መብዛት አልያም ኢስትሮጅን ያለበት መድሀኒት ወይም ግብአት መውሰድም ተጋላጭነትን ይጨምራል።   ነባራዊ ሁኔታ/ ስርጭቱ በቅርብ ጊዜ የተደረጉ የሐተታ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የሀሞት ጠጠር ከ ከ6-10% የሚሆነው የአለም ህዝብ ያጠቃል። በይበልጥም በሴቶች ይታያል። በኢትዮጵያ ያሉ ጥናቶችም የሀሞት ጠጠር ስርጭት ከ 5 እስከ 8 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል ይጠቁማሉ። በተለይም ስርጭቱ ከ 30ዎቹ እስከ 50 ዎቹ የእድሜ ክልል ላይ ያሉ ሴቶች ላይ ይታያል። ማን ይታመማል - እና ማንስ ህመም አይሰማውም? ግራ የሚያጋባው ነገሩ ይህ ነው!  አንዳንዶች የሀሞት ጠጠር ኖሮባቸው ምንም ህመም ሳያሳዩ ለአመታት ሲቆዩ ሌሎች በሀሞት ጠጠር ህመም አብዝተው ይሰቃይሉ።  ለምን እንዲህ እንደሚያጋጥም በስርአት አይታወቅም። የሐሞት ጠጠር ምልክቶች የሀሞት ጠጠር ሲኖርብዎ የሚሰማዎት ምልክቶች እኝህን ይመስላሉ። ከእንብርትዎ በላይ በቀኝ በኩል/መሀል ላይ የሚሰማ ድንገተኛ ኃይለኛ የሆድ ቁርጠት ህመም ይሰማል። ይህ ህመም ከሆድዎ አልፎ ወደ ጀርባዎ እና ወደ ቀኝ ትከሻዎ ሊሄድ ይችላል። ብዙ ጊዜ ይህ ህመም የሚሰማዎ ቅባት የበዛበት ምግብ ከበሉ በኋላ ነው። ሀሞት ጠጠሩ ላይ ተደርቦ የሀሞት ከረጢት መቆጣት በሽታ ( Acute Cholecystitis) ሊይዝዎ ይችላል። ይህን ጊዜም የማያቋርጥ ህመም፣ ትኩሳት፣ ምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ድካም በተጨማሪ ሊሰማዎ ይችላል። ይሄኔ አፋጣኝ የሆነ ህክምና ያስፈልጋል። የመውጫ ቱቦን ከዘጋ የቆዳ እና የአይን ቢጫ መሆን ምልክቶችን ሊያሳይም ይችላል። ሽንትም ሊጠቁር ፤ ሰገራም ሊነጣ ይችላል። ከዚህ ባሻገር  ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክና የምግብ ፍላጎት መቀነስ ሊታይ ይችላል። እንዲሁም ለሌሎች በሽታዎች ሊይጋልጥ ይችላል። ለምሳሌ የቆሽት መቆጣት፣ የሀሞት ቱቦ መቆጣት፣ ወ.ዘ.ተ.. ምርመራውና ህክምናው እንደ ሀሞት ጠጠሩ ሁኔታ የ አልትራሳውንድ ምርመራ ፣  ኢራሲፒ (ERCP)፣ ኤምአር ሲፒ (MRCP)፣ የ ኤም አር አይ (MRI) ምርመራዎች ሊታዘዙ ይችላሉ። እነሱንም ለማገዝ የደም ምርመራም ይደረጋል። ህክምናውም እንደአለው ምልክት ይወሰናል።  ምንም ምልክቶች ከሌሉ /ጠጠሮቹ መጠነኛ ከሆኑ/ ሀሞት ከረጢት ካልተቆጣ ፤ ቀዶ ጥገና አያስፈልግም። የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ብቻ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ምልክቶች ካሉ ፣ ሀሞት ከረጢት ከተቆጣ ፣ ትላልቅ ድንጋዮች ከሆኑ ፣ ኢንፌክሽን ካለ ፣ ከጎን ያሉ አካላትም ከተጎዱ/ከተቆጡ ፣ የሀሞት መውጫ ቱቦ ከተዘጋ አፋጣኝ ህክምና ያስፈልጋል። የሀሞት ከረጢት በቀዶ ጥገና እንዲወጣ ይደረጋል። መከላከል- የተሻለው አማራጭ የሀሞት ጠጠር እንዳያጋጥም ለመከላከል አልያም ፤ ያለብዎ የሀሞት ጠጠር እንዳይገዝፍ እንዲህ ያደርጉ። ጤናማ ክብደትን ይጠብቁ።  ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች አያዘውትሩ። የአካል እንቅስቃሴ ያድርጉ። አትክልት እና ፍራፍሬ አብዝተው ይመገቡ። የደምዎን የስኳር መጠን እና የኮሌስትሮል መጠን ይቆጣጠሩ።  መደበኛ የጤና ምርመራ ያደርጉ።  ህመም አልተሰማዎትም ማለት የሀሞት ጠጠር የለብዎትም ማለት አይደለም። የጤና ግንዛቤዎን ያሻሽሉ። በሆስፒታሎች አልያም በጤና ባለሙያዎች ብቻ የሚለቀቁ የጤና ትምህርቶችን ይከታተሉ። ያስተውሉ! ለሀሞትዎና ለጉበትዎ ጤና ቦታ ይስጡ ። ታመው እስኪመጡ አይጠብቁ። ምልክቶቹን ካስተዋሉ አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ይፈልጉ። መዘግየትዎ በሽታው እንዲወሳሰብ ያደርገዋልና በቅድሚያ ህክምና ያድርጉ።

  • ራሰ በራነት እንዴት ያጋጥማል? እንዴት እንከላከል?

    በአለም ዙሪያ ራሰ በርሀነትን ለማሰብ የተሰየሙ የተለያዩ ቀኖች አሉ። ያለፈው ቅዳሜ በአሜሪካ የተከበረው የብሄራዊ የመላጣነት ውበት ቀን ለዚህ ተጠቃሽ ነው። ለመሆኑ አክብረዋል? እንዲሁም አለም አቀፍ የራሰ በርሀነት ቀን በፈረንጆች የኦገስት ወር ላይ የመጀመሪያ ቅዳሜ ይከበራል። እነኝህ ቀናቶች ታድያ መላጣነትን የሚያሞግሱ ፤ መላጣነት ጉድለት ሳይሆን ውበት መሆኑን የሚያወሱ ቀናቶች ናቸው። በሀገራችን ኢትዮጵያ ይህንን የሚያወሳ ቀን እስከ አሁን የለም። ቢኖርስ ያከብሩ ነበር? ስለመላጣነት ያለዎት አስተያየት ምንድነው? በመጀመሪያ ስለጸጉር እናውራ ከልጅነታችን ጀምሮ ጸጉራችንን እንደማናወልቀው አክሊል አድርገን እናስበዋለን። ሳይንስ ጸጉርን እንደፕሮቲንክ ክር አድርጎ ቢረዳውም ፤ በአለም ዙሪያ ያሉ የተለያዩ ባህሎች ለጸጉር የሚሰጡት ትርጉም ሰፊ ነው። በአሜሪካ የሚኖሩት ህንዶች ውስጥ ባለ ሶስት ጸጉር ቁጥርጥር ጥንካሬን እና የሀሳብ ጽናትን ያመላክታል። በኢሲያ ሀገራት እንዲሁም በህንድ ደግሞ ወደ መንፈሳዊ ህይወት ለመቅረብ ራስን ለማጽዳት ጸጉር መላጨት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ሀገራት ጸጉር እንደ አሰራሩ ፤ እድሜን ፣ የትዳር ሁኔታን እንዲሁም በማህበረሰብ ውስጥ የሚሰጥ ቦታን ያመላክታል። ወደ ጃማይካ እና ራስ ተፈሪ እምነት ትከታዮች ከሄድን ደግሞ የጸጉር ትርጉሙ እየሰፋ ይሄዳል። ለዚህ ባህልና ኋላ ቀር አስተሳሰብ የተነሳ ለጸጉር የምንሰጠው እይታ ካለው ተፈጥሮአዊ ጠቀሜታ ያለፈ ነው። ለብዙ ወጣቶች ከማንነት ጋር ይያዛል። ለዚህም የጸጉር አቆራረጥ ፋሽን ፉክክሩም ቀላል አይደለም። ወንዱም ዞማ ወገብ የደረሰ ጸጉር ያላት ሴት ፤ ሴቷም ጸጉሩ ሙሉ የሆነ ያልሸሸ ወንድ ይፈልጋሉ በሚል እሳቤ በወጣቶች ላይ ያለው ጫና ቀላል አይደለም። ይህ ግን የተሳሳተ ነው! መላጣነት/ራሰበራነት በራሱ ውበት አለው። ለዚህም በአለም ዙሪያ አማላይ ተብለው የተሰየሙ ታዋቂ ግለሰቦች ምስክር ሊሆኑ ይችላሉ። በተሳሳተ አስተሳሰብ የተነሳ ፤ አንዳንዶች ፀጉራቸውን ማጣት ማንነታቸውን ከማጣት ጋር ሊያስተካክሉት ይችላሉ። ካለፉት አመታት አሁን የተሻለ አስተሳሰብ ቢኖርም ፤ ስለ ራሰ በራነት ያለ አስተሳሰብ አሁንም መስተካከል ያስፈልጋል። ለዚህም ነው እነኝህ ቀናት በአለም ዙሪያ ያስፈለጉት። የእርስዎስ ጸጉርዎት መሳሳት ጀምሯል? ጸጉሩ መሳሳት የጀመረ ሰው ያውቃሉን? እውነታው ግን ከዚህ የራቀ ነው። ራሰ በራነት በጣም ከተለመዱት የሕክምና ችግሮች አንዱ ነው። ከምን ጊዜም በላይ ሳይንስ አሁን በደንብ ተረድቶታል። በጥልቅ እንየው። የራሰ በራነት ስርጭት ራሰ በራነት ከተወለድን በኋላ የሚያጋጥም የጸጉር መሳሳት ሲሆን ፤ በአለም ዙሪያ እጅጉን የተለመደ ነው። እሱም በተፈጥሮ እድሜን ተከትሎ ፣ ኢንፌክሽኖችንና አንዳንድ በሽታዎችን ተከትሎ ፣ እንዲሁም እንደ ኪሞቴራፒ ያሉ ህክምናዎችን ተከትሎ ሊመጣ ይችላል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአለምአቀፍ ደረጃ 30 ዓመት ከሞላቸው 3 ወንዶች ውስጥ አንዱ የጸጉር መሳሳት ይጋጥመዋል። 50 ዓመት ከሞላቸው ወንዶች ውስጥ ግማሹ በራሰ በራነት ይጠቃሉ። እንደወንዶች ባይሆንም ሴቶችም በዚህ ችግር ይጠቃሉ። እስከ 40% የሚደርሱ ሴቶች  በጎልማሳነት እድሜያቸው ውስጥ ጸጉራቸው ይቀጭጫል። ይህም ደግሞ በይበልጥ የመውለጃ እድሜያቸው ያለፈ ሴቶች ላይ ይስተዋላል። አንዳንድ ጥናቶች ራሰ በራነት በይበልጥ በ አውሮፓ እና በእስያ ህዝቦች ውስጥ እንደሚታይ ይጠቁማሉ። ሆኖም ግን በአፍሪካ ያለው የተሳሳተ የባህላዊ እይታ ፤ መጠኑ በስርአት እንዳይታወቅ አግዶት ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ ለዚህ ምርጥ ምሳሌ መሆን ትችላለች። የራሰበራነት ስርጭት የሚያሳይ ሀገር አቀፍ መረጃ ባይኖረንም ፤ ቁጥሩ ከፍ ያለ እንደሚሆን ለመገመት አያዳግትም። የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት አዋቂዎች በብዛት የሚያጋጥማቸው ከ ሆርሞን ጋር የሚያይዘው ሲሆን ህጻናት ደግሞ ከፈንገስ ኢንፌክሽን ጋር ተያይዞ የሚመጣው ነው። ሆኖም ግን ብዙውን ጊዜ ራሰ በራነት በስርአት ሪፖርት አይደረግም። አንድም እንደ እድሜ አመላካች ተደርጎ ስለሚወሰድ ሌላም ፤ ባለ ማህበረሰባዊ ጫና ብዙዎች አስፈላጊውን ህክምና አያደርጉም። የፀጉር መሰረታዊ ሳይንስ ስለ ራሰ በራነት ለመረዳት ስለ ፀጉር እድገት እናውራ። የፀጉር እድገት ዑደት አለው። የመጀመሪያው የዑደት ደረጃ አናጀን (anagen) ይባላል። ይህም ጸጉር የሚያድግበት ደረጃ ሲሆን ከ 2 እስከ 6 ዓመት ሊፈጅ ይችላል። ትልቁን ጊዜ (90 በመቶ የሚሆነውን) ይወስዳል። ሁለተኛው ደረጃ ካታጀን (catagen) ሲባል ፤ ይህም መሸጋገሪያ ደረጃ ተደርጎ ይወሰዳል። ይህም ከ 2 እስከ 3 ሳምንታት ሲፈጅ ፤ ያደገው ጸጉር እረፍት የሚወስድበት ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ጸጉር እድገት ያቆምና፣ የጸጉር ሥር መቀጨጭ ይጀምራል። ለቀጣይ ደረጃም ይዘጋጃል። ሶስተኛውና የመጨረሻው ደረጃ ቴሎጅን (telogen) ይባላ። ይህም አድጎ የጨረሰው ጸጉር የሚረግፍበት ጊዜ ነው። መርገፉ መልካም ባይመስልም አስፈላጊ ነው። ያረጁት ጸጉሮች ሲረግፉ ፤ ከስር ለአዲስ ጸጉር ቦታ ይሰጣሉ። በጤናማ የራስ ቅል ቆዳ ውስጥ፤ ይህ ዑደት ሁሌ ሚዛናዊ ነው። ነገር ግን ራሰ በራነት ጊዜ ይህ ዑደት ይዛባል/ይቋረጣል። ምክንያቱም እንደ አይነቱ ሊለያይ ይችላል። የራሰበራነት አይነቶች የወንዶች አይነት ራሰበራነት (አንድሮጀነቲክ አሎፒሺያ / MPB/ Androgenetic alopecia) ይህ አይነት ከዘረመል (ጂኖች) ጋር እንዲሁም ከ ወንድ ልጅ ሆርሞን ጋር (በተለይ DHT ከሚሰኘው) ጋር ያያዛል። ይህም ሆርሞን የጸጉር ሥር ላይ ባለው ተጽእኖ ጸጉር ይሳሳል። ያለው ተጽእኖ ቅድም ያነሳነው የጸጉር ማደጊያ ጊዜ (አናጀንን) ያሳጥራል። የጸጉር ውፍረቱ እጅጉን ይቀንሳል። እየባሰ ሲመጣም ጸጉር እጅጉን ቀጭጮ በተወለዱ ህጻናት ላይ እንደሚታየው አይነት ጸጉር ሊመስል ይችላል። ይህን ጊዜ ጸጉር ይሳሳል። ሲታይ ጸጉር ወደውስጥ የሸሸ ይመስላል። አሸሻሹ ደግሞ አይነት አለው። በዋነኝነት የግምባር ጠርዝ ጋራ ያሉት ጸጉሮች እና የመሀል ጭንቅላት ጋር ያሉት ጸጉሮች ይሳሳሉ። አኗኗርን ተከትሎ የሚመጣ ራሰበራነት (ቴሎጅን ኤፍለቪየም / Telogen effluvium ) ይህ ደግሞ ህመምን ፣ ውጥረትን ፣ አመጋገባችን ተከትሎ የሚመጣ ነው። አንዳንዴ የወለዱ ሴቶችም ላይ ሊታይ ይችላል። ሁሉም የራስ ቅል ጸጉሮች በአንዴ ወደ ሁለተኛው የእረፍት ደረጃ ይገባሉ። ለዚህም እላይ ያየነውን የጸጉር ኡደት በቀጣይ ሳምንታት/ ወራት ውስጥ ጸጉር በብዛት ይረግፋል። ሲታይ ይህ አስደንጋጭ ቢመስልም ፤ አስፈላጊውን እርዳታ (ውጥረት መቀነስ ፣ ህመምን መታከም ፣ አመጋገብ ማስተካከልን) ተከትሎ ሊመለስ ይችላል። ዘላቂ አይደለም። በበሽታ መከላከያ ስርአት የሚመጣ ራሰ በራነት (አሎፔሺያ ኤርያታ/ alopecia areata) ይህ ደግሞ የራሳችን የበሽታ መከላከያ ስርዓት በስህተት የጸጉር ስሮችን ሲያጠቃ የሚፈጠር ነው። ለዚህም ጸጉር መሀል የሚታዩ ክብ መላጣ ቦታዎች ይኖሩታል። ከባሰ ሙሉ ጸጉር ሊረግፍ ይችላል። የፈንገስ ኢንፌክሽን ተከትሎ የሚመጣ ራሰበራነት (ስካሪንግ አሎፒሺያ / Scarring alopecia) ይህ በልጅነት እድሜ በሚያጋጥሙ ከባድ ኢንፌክሽኖች ፣ ባልታከሙ የራስ ቅል ቆዳ ፈንገስ ህመሞች የሚመጣ ነው። እነኝህ ኢንፌክሽኖች የጸጉር ስርን ሊያጠቁ ይችላሉ። የጸጉር ስርን በጣም ካጠቁ ጠባሳ ይፈጥራል። ጠባሳ ከፍጠረ ደግሞ ራሰበራነቱ ቋሚ ይሆናል። ለዚህም አፋጣኝ ህክምና አስፈላጊ ነው። ህክምናን ተከሎ የሚመጣ ራሰበራነት (አናጀን ኢፍለቪየም / anagen effluvium) ይህ እንደኬሞ ቴራፒ ያሉ ህክምናዎችን ተከትሎ የሚመጣ ራሰበራነት ነው። ስሙ እንደሚናገውም ጸጉር በሚያድግበት ደረጃ ላይ (አናጀን) ጊዜ በመድሀኒቶች የሚደርስበት ጥቃት ጸጉር እድገቱን እንዲቁረጥ ያደርጋል። መድሀኒቱን በወሰዱ በሳምንታት ውስጥ ጸጉር በብዛት ይረግፋል። ውጤታማ ሕክምናዎች የትኞቹ ናቸው? ነገሮች አስቸጋሪ የሚሆኑት እዚህ ጋር ነው። ራሰበራነት ለመቃወም የሚሰሩ የጸጉር ግብአቶች ብዙ ናቸው። በአለም ዙሪያ በቢሊየኖች ገቢ ያስገኛሉ። አምራች ድርጅቶቻቸውም እንደ ተአምራዊ መፍትሔዎች ያስተዋውቋቸዋል። በማህበራዊ ድህረገጽ ቢፈልጉም አሸን ያገኛሉ። ምስክርነት የሚሰጡ አስተዋዋቂዎችም ጥቂት አይደሉም ብዙዎች ይወስዱዋቸዋል። ሆኖም ግን ምንም ለውጥ አያሳዩም። ዘላቂ መፍትሔ የላቸውም። ሳይንስስ ምን ይላል? በዘመናዊ ህክምና የሚሻሉ የሚባሉት አማራጮች እነሆ፡ ለ ወንድ አይነት ራሰ በራነት (MPB) ያሉ የህክምና አማራጮች የሚኖክሲድል(minoxidil) ቅባት /ክሬም ይህ በሰፊው ሲገኝ ፤ ለወንዶችም ለሴቶችም ግልጋሎት ላይ ሊውል ይችላል። ጥቂት የማይባሉ የጸጉር ማሳደጊያ ቅባቶችም በውስጣቸው ይህንን ውህድ አላቸው። ይህ ውህድ የጸጉር ስርን ያነቃቃል። ጸጉር እንዲወፍር ፤ ችምችም ብሎ እንዲያድግ ያደርጋል። የጸጉር መርገፍን ይቀንሳል። ሆኖም ግን በየቀኑ ሳይቋረጥ መወሰድ አለበት። ከተቋረጠ የመጣው ለውጥ ይጠፋል። መወሰድ ያለበትም የሚቀባው ብቻ ነው። የሚዋጥ እንዳይወስዱ! የሚዋጥ ፊናስተራይድ(Finasteride) እንክብል ይህ ለወንዶች ብቻ የሚሆን ሲሆን ፤ የጸጉር ስርን የሚያሳሳውን ዲኤችቲ (DHT) የተባለውን ሆርሞን ይቀንሳል። ለዚህም ራሰበራነትን ይገታል።ጸጉር በድጋሜ እንዲያድግ ያስችላል። ሆኖም ግን የጎንዮሽ ጉዳት ስላለው የሕክምና ክትትል ያስፈልገዋል። ፕሌትሌት ያለው የፕላዝማ መድሀኒት (platelet rich plasma) ይህ ደግሞ ደም ውስጥ ያሉ የእድገት ኬሚካሎችን ይጠቀማል። እነኝህ ኬሚካሎች ከደምዎ ተወስደው ራስ ቅልዎ ላይ ጸጉርዎን እንዲያሳድጉ ይወጋሉ። ይህ ህክምናም አመርቂ ውጤት አሳይቷል። የጸጉር ውፍረት እና ብዛትን ያሻሽላል። የጨረር ህክምና (low level laser therapy) ይህ የጸጉር ስርን የሚያነቃቁ ጨረሮች ይጠቀማል። ከሌሎች ሕክምናዎች ጋር ከተጣመረ አስተማማኝ ከመሆኑም ባሻገር ተጓዳኝ ጉዳቱ ይቀንሳል። የፀጉር ንቅለ ተከላ ይህ ከለጋሽ የተወስዱ የጸጉር ስሮች ራሰበራነት ያጠቃበት ቦታ በቀዶ ጥገና የሚተከሉበት ነው። ጥሩ ጤና ላይ ያለ የፀጉር ስር ከተገኘ ውጤቱ አርኪ ነው። ሆኖም ግን የህክምናው ሂሳብ ውድ ነው። በዚህ የሰለጠነ የጤና ባለሙያ እና ልዩ የህክምና እቃዎች ይፈልጋል። በበሽታ መከላከያ ስርአት ለሚመጣ ራሰ በራነት ያሉ የህክምና አማራጮች ይህንን ለማከም የበሽታ መከላከያ ስርአትን የሚያረጋጋ መድሀኒቶችን በራሰበራነት የተጠቃው ስፍራ ላይ መውጋት ያስፈልጋል። ይህንን በተሻለ መልኩ የሚያክሙ አዳዲስ መድሀኒቶች አሁን ገበያ ላይ ውለዋል ። ኢንፌክሽኖችን ተከትሎ ለሚመጣ ራሰ በራነት ያሉ የህክምና አማራጮች የጭንቅላት የፈንገስ ህመም ላለበቸው ህጻናት የፀረ-ፈንገስ መድሃኒቶች  (በአፍ የሚወሰድ ፣ የሚቀቡ መድሀኒቶች ) በመጠቀም መከላከል ይቻላል። ዘላቂ ራሰ በራነትን ለመከላከል ቀድሞ ህክምና ማድረግ አስፈላጊ ነው። እንዴት ይከላከሉ? መቼም የዘር ጉዳይን መቆጣጠር ባይቻልም ፣ አኗናር ለውጥ በማድረግ የጸጉርዎን ጤና መጠበቅ ይችላሉ። ለዚህም የራስ ቅል ቆዳ ኢንፌክሽኖች ጠባሳ ከማምጣታቸው በፊት ቀድመው ህክምና ያድርጉ። የተመጣጠነ ምግብ ይመገቡ። የሚመገቡት ውስጥ የ ፕሮቲን ፣ ብረት፣ ዚንክና ፣ ቫይታሚን ዲ ማነስ ጸጉር እንዲረግፍ ያደርጋል። ጸጉርዎን ይንከባከቡ። ጸጉርዎን አጥብቀው አይሰሩ፣ ቁጥርጥር አይሰሩ። ደጋግመው የጸጉር ቀለም አይጠቀሙ። እንደ ፐርም ያሉ የጸጉር ኬሚካሎች አይጠቀሙ። የራስ ቆዳ ንፅህና  ይጠብቁ። ጸጉርዎን ካሳስከክዎ ወይም ቆዳዎ ከተላላጠ ችላ አይበሉ። ፎሮፎር ካለ ክምና ያደርጉ። ላለብዎ በሽታ በአስቸኳይ ህክምና ያድርጉ። ከባድ ጭንቀት ፣ የታይሮይድ በሽታ፣ ወይም ከባድ ኢንፌክሽኖች ካለብዎ የህክምና እርዳታ ይፈልጉ። ዶክተር ማየት መቼ ያስፈልጋል? ለጸጉር መሸሽ ወይም ራሰ በራነት ሀኪም ጋር መሄድ የተለመደ አይደለም። ታድያ ግን መቼ ዶክተር ያማክሩ? ጸጉርዎ በድንገት መርገፍ ከጨመረ በአንድ ጀምበር ጭንቅላትዎ ላይ ክብ መላጣ ስፍራዎች ካዩ ራስቅልዎ ከቀላ፣ ካስከከ፣ ወይም ህመም ካለው በራስ የመተማመን ስሜትዎ እየቀነሰ ከመጣ ፣ ራሰበራነቱ በራሱ ስሜትዎን ከበጠበጠ ወይም ውጥረት ካመጣ የጤና ባለሙያውም ቀላል የራስ ቆዳ ምርመራ እንዲሁም የደም ምርመራዎችን ሊያደርግ ይችላል። ይህም ለእርስዎ ተመራጭ ህክምናውን ለመለየት ያግዛልና ሀሳብ እንዳይገባዎ። 👉 ለጸጉርዎ ጤና ቦታ ይስጡ! ችላ እንዳይሉ! ተግባራዊ ለውጥ ማምጫ ጊዜው ዛሬ ነው! የቆዳ ህክምና ባለሙያን ያነጋግሩ ። ከሚያስቡት በላይ ብዙ አማራጮች ሊኖሩዎት ይችላል።

  • 🌱 አዲስ ዓመት ለጤንነትዎ አዲስ ጅማሬ

    አሮጌውን ትተን አዲስ አመት የምንቀበልበት የዘመን መለወጫ ይኸው ደረሰ! እንኳን አደረስዎ!!! ይህንንም ለማብሰር ሰማይ በርችት ሲደምቅ ፤ ቤታችን አውደ አመት አውደ አመት ሲሸት ፤ እኛም በበኩላችን ጤናማ አመት ለማሳለፍ እቅድ ይዘን ይሆናል። ለራሳችን ብቻ ሹክ ያልናቸውው ቃላቶች ይኖራሉ። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ወደ 80% የሚሆኑት የአዲስ ዓመት ውሳኔዎች ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይተዋሉ። መልሶ ወደማይበጀን አሮጌው ባህሪያችን እንመለሳለን። በ 2018 ይህ መቆም አለበት! ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ታድያ የአንድቀን ውሳኔ ብቻ አለመሆኑን ይገንዘቡ። በአመት ውስጥ ባሉ በእያንዳንዱ ቀናት ጤናዎን መምረጥ ይኖርቦታል። ለመሆኑ ግን ምን የባህሪ ለውጥ ቢያመጡ ይመከራል? 🥗 የተመጣጠነ ምግብ መመገብ። ጤናማ አመጋገብ አመጋገብን ስለመቆጠብ (dieting) ብቻ አይደለም። ሰውነትዎ የሚፈልጋቸውን ግብአቶች በበቂ ሁኔታ በማቅረብ ፤ የሰውነትዎን አቅም/ኃይል መገንባት ነው። እንዲህ አድርገው ያስቡት " አንድ አናጢ አንድ የእንጨት ስራ ለመስራት ከ እንጨት ባሻገር የሚያስፈልጉት የተለያዩ ግብአቶች አሉ። እንደ ቀለም፣ ቫርኒሽ፣ ሚስማር፣ ኮላ አይነት ነገሮች ባይኖሩ አልያም ቢያንሱ ፤ ስራው ይበላሻል አልያም ይስተጓጎላል። ሁሉም የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ስላለው ፤ በበቂ መጠን መገኘት አለበት። አመጋገብም እንዲሁ።" የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እ.ኤ.አ 2020 እንደዘገበው በየአመቱ በአለም ዙሪያ ከ11 ሚሊየን በላይ የሚገመቱ ሰዎች ከአመጋገብ ጉድለት ጋር በሚያያዙ ምክንያቶች ይሞታሉ። ይህ ቁጥር እጅጉን ከፍተኛ ነው። ሆኖም ግን አመጋገብ በማስተካከል ልንከላከለው እንችላለን። አገራችን ኢትዮጵያም ይህ የአመጋገብ ጉድለት በብዛት ይስተዋላል። እ.ኤ.አ. በ 2019 የተደረገ የኢትዮጵያ የስነ ሕዝብ አወቃቀር እና ጤና ጥናት (EDHS) በከተሞች ውስጥ ከመጠን ያለፈ ውፍረት እየጨመረ ሲመጣ ፤ በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ደግሞ የምግብ እጥረት እያስቸገረ እንደሚገኝ ጠቁማል። ለዚህም አቅማችን በፈቀደው መሰረት አመጋገባችን ማስተካከል ግድ ይለናል። የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ከፍተኛ ወጪ አይፈልግም። ቅባት፣ አሰር፣ አትክልቶች ፣ ፍራፍሬዎች እና ጥራጥሬዎች ስራዬ ብለን መመገብ ይኖርብናል። 🏃 ♀️  የሐኪም ማዘዣ የማያስፈልገው መድሃኒት ፡ እንቅስቃሴ በሳምንት ለ150 ደቂቃ መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ለልብ ህመም፣ ለስኳር በሽታ እና ለአንዳንድ ካንሰሮች የመጋለጥ እድልን እንደሚቀንስ ያውቃሉ  ? ይህ ማለት በቀን 30 ደቂቃ ብቻ በሳምንት አምስት ቀናት ውስጥ መጠነኛ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህም ትልቅ የአካል እንቅስቃሴ አያስቡ። ፈጣን የእግር ጉዞ ማድረግ፣ መደነስ፣ ብስክሌት መንዳት ወይም ግቢ በደንብ ማጽዳት አይነት እንቅስቃሴ በቂ ይሆናል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ማህበረሰብ እጅጉን አስፈላጊ ነው። በተለይ በከተሞች ውስጥ ብዙ እንቅስቃሴ የሌለው አኗኗር እየጨመረ መምጣቱን በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የተደረገ ጥናት ይጠቁማል። ይህ አኗኗር ደግሞ በቢሮ ሰራተኞች ላይ በብዛት ይታያል። ያስተውሉ! ጤናማ እንቅስቃሴ ያድርጉ ማለት የጂም አባልነት ይኑርዎት ማለት አይደለም። ታክሲ በመሳፈር ፋንታ ቢራመዱ ፤ ከሊፍት ይልቅ ደረጃን ቢጠቀሙ ፤ ሰንበት ላይ ሰፈር ውስጥ እግር ኳስ ቢጫወቱ ፤ ለጤናዎ ብዙ ለውጦችን ያመጣል። ታድያ ምን አስቡ? 😴የሚረሳው የጤና ምሰሶ ፡ እንቅልፍ ሩጫ በበዛበት ህይወት ውስጥ እንቅልፍ ይዘነጋል። ለዚህም እንቅልፍ ለድርደር የሚቀርብ አማራጭ ሆኖ በብዙዎቻችን ይቀርባል። ስራ ሲበዛ እንቅልፋችንን መስዋእት እናደርጋለን። ስንፈልግ እንቅልፍን ተሰርዞ እስከ ንጋት እንዝናናለን። ስልካችንን እየተጠቀምን ክሆነ ፤ እንቅልፍን ገሸሽ እናደርጋለን። ስንጨነቅ ወይ እንቅልፍ እናጣለን አልያም አልጋ ላይ እንሰነብታለን። ይህ ሁሉ ጤናማ ባህሪ አይደለም ። እንቅልፍ ከጤናችን ጋር የተቆራኘ ትልቅ የጤና ምሶሶ ነው። በቀን ከ7 ሰአት  ያነሰ እንቅልፍ መተኛት ከመጠን ላለፈ ውፍረት ከማጋለጡ አልፎ ፤ የበሽታ መከላከል አቅምን ያዳክማል። የማስታወስ ችግርን ይቀንሳል። ለሥር የሰደዱ በሽታዎች የመጋለጥ እድልን ይጨምራል። ይህ ዛሬ ላይ መቆም አለበት። በ 2018 ዓ.ም በየቀኑ ከ 6 እስከ 8 ሰአት እንቅልፍ ሊተኙ ይገባል። ከመተኛትዎ በፊት ራስዎን ዘና ያድርጉ። ሞባይል አይጠቀሙ! ይጸልዩ! ሰውነትዎን ያሳስቡ! ይህን ጊዜ በደንብ ይተኛሉ። ሰውነትዎም ራሱን የሚጠግንበት ጤናውን የሚመልስበት እረፍትን ያገኛል። 🧘 የአእምሮ ጤንነት ጤና አካላዊ ብቻ አይደለም። በአለም አቀፍ ደረጃ ከ 8 ሰዎች አንዱ የአእምሮ ጤና መታወክ ይታይበታል።። እ.ኤ.አ በ2018 የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው ከ22% በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በህይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ የአእምሮ ጤና ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል። ሆኖም ግን ብዙዎች ይላቸው የተሳሳተ እይታ አስፈላጊውን ህክምና እንዳያደርጉ ይይዛቸዋል። እነርሱም የአእምሮ ህመም እንዳለባቸው እንዲታወቅ አይፈልጉም። ለዚህም ብዙዎች በዝምታ ይማቅቃሉ። ድምጻቸው ሳይሰማ ይሰቃያሉ። በዚህ አመት ስለ አእምሮ ህመም መነጋገር መደበኛ መሆን ይኖርበታል። የአእምሮ ህመም ማለት እብደት አለመሆኑን ማወቅ ይኖርብዎታል። እርሶም ከልክ ያለፈ ውጥረት ካለብዎ የጤና ባለሙያ ያማክሩ። እርስዎን እንጠይቅዎ፡ ለእርስዎ አለኝ የሚሉት ሁነኛ ሰው ማን ነው? ህይወት ጫናዋ ሲበዛ ሊያዋዩት የሚችሉት ሰው ማነው? እስካሁን ከሌለዎት። በዚህ አመት ይኑርዎ። ሲነጋገሩ የችግርዎ ሸክም ይቀላል። መፍትሔ ይገኛል። 🚭 መጥፎ ልማዶችን ይተዉ አልኮል፣ ትምባሆ እና የአደንዛዥ ዕፅ መጠቀም አሁንም አሳሳቢ የማህበረሰብ ጤና ችግሮች ናቸው። በየአመት የሚሊየኖችን ህይወት ይቀጥፋሉ። ሀገራችን ኢትዮጵያ በፖሊሲ ረገድ መሻሻል ብታሳይም ፤ ወጣቶች ዙሪያ አሁኑም ተግዳሮቶች ይታያሉ። ስለዚህ ጤናዎን ጠንቅ የሆኑ እነኝህን ልማዶች ፤ በአዲስ ጤናማ ልማዶች ለመተካት ይኖርብዎታል። ሁሉንም በአንዴ እርግፍ አድርገው ማቆም አይችሉ ይሆናል። ሆኖም ግን አንድ በአንድ ባህሪዎን ይለውጡ። እንዲህ ካላሰቡ የባህሪ ለውጥ ማምጫ ዘመን አሁን ነው። ለራስዎ ቦታ ይስጡ። ሁል ጊዜ ጤናዎን ይምረጡ። ❤️ ሁል ጊዜ መከላከል ከፈውስ ይሻላል መደበኛ የጤና ምርመራ/ቼክ አፕ ያድርጉ። አስፈላጊ ክትባቶች ይከተቡ። ጨቅላ ህጻን ካለዎት ምንም ክትባት አያምልጠው። ይህ ሁልጊዜ የሚሰሙት ምክር ቢሆንም ፤ ህይወት አድን ነው። እንዴት? በአገራችን ኢትዮጵያ በአሳዛኝ ሁኔታ ፤ ወጣቶች በትልቅ ሰው ህመም እየታመሙ ፣ በልጅነታቸው ኩላሊታቸውና ጉበታቸው እየደከመ ፤ ልባቸው እጅጉን ተጎድቶ ፤ የተሰራጨ ካንሰር ተገኝቶባቸው ፤ የህክምና እርዳታ ሲጠይቁ በየከተሞቹ ይታያል። በፈረንጆች 2021 የጤና ጥበቃ ሚኒስተር እንዳወጣው መረጃ ከሆነ በኢትዮጵያ የስኳር በሽታ፣ ደም ግፊት እና ካንሰር ህመሞች እየጨመሩ ይገኛሉ። መደበኛ ምርመራ በማድረግ ይህንን ሁሉ መከላከል እንደሚቻል ያውቃሉን? ሆኖም ግን በየአመቱ ወገኖቻችንን እያጣን እንገኛለን። ታድያ እርስዎስ መቼ ነው ለመጨረሻ ጊዜ ሳይታመሙ፤ ለ መደበኛ የጤና ምርመራ የሄዱት? ህመም አልተሰማዎትም ማለት ጤነኛ ነዎት ማለት አይደለም። መሄድ አያስፈልግዎትምን? ያስተውሉ መከላከል ከፈውስ ይሻላል። ማንንም አይጠብቁ ዛሬውኑ እርምጃ ይውሰዱ። ህይወትዎን ያሻሽሉ። ✨ያስተውሉ! በዚህ አዲስ አመት ፤ ተግባራዊ ለውጥ እናምጣ። ጤናችንን እንምረጥ ። ግልጽ የሆኑ ጤናማ ግቦችን እናስቀምጥ ። ዛሬውኑ እርምጃ እንውሰድ። በቀን ምግብዎት ውስጥ አንድ ተጨማሪ ፍራፍሬ ወይም አትክልት ይጨምሩ።. በሳምንት አምስት ጊዜ ለ 30 ደቂቃዎች በእግር ይራመዱ። በቀን ከ 7-8 ሰአታት ይተኙ። ስለ አእምሮ ጤንነት በግልጽ ይናገሩ። በዚህ አመት አንድ ጎጂ ልማድ ያቁሙ። ህመም ጥልዎት ሀኪምቤት ከመሄድዎ በፊት ይመርመሩ። ጤናዎ መስከረም ላይ አይገነባም። ከዚህ በኋላ በሚወስዷቸው ሺ ጥቃቅን ምርጫዎች ውስጥ እንጂ። እያንዳንዷ ቀን ጤናዎን ለማደስ እድል ናት። 2018 ጤናዎን የሚያድሱብት አመት ይሁንልዎ።

  • የልጅዎ ሽፍታ አሳሳቢ መሆኑን እንዴት ይወቁ?

    የ ልጅዎ የሚያሳሳ ቆዳ ከልስላሴው ባሻገር ፤ የበሽታ መከላከያም አካል እንደሆነ ያውቃሉ? ገና ይችን አለም ከተቀላቀሉባት ከመጀመሪያዋ ደቂቃ ጀምሮ ፤ የህጻናት ቆዳ አከባቢ ላይ ከሚገኙ በሽታ አምጪ ህዋሳት ጋር ግብግብ ላይ ነው። ለዚህም ህጻናት በመጀመሪያ አመታቸው በቆዳ ህመሞች ይጠቃሉ። በብዛት ከሚታመሟቸው ህመሞች ውስጥም ሽፍታ አለበት። በአለም ዙሪያ ሽፍታ እና የቆዳ ለውጦች ህጻናትን ወደ ጤና ተቁም ከሚወስዱ ምክንያቶች መሀከል በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። ጥናቶችም እንደሚያመላክቱት ከ 40 እስከ 50 ፐርሰንት የሚሆኑት ህጻናት ፤ በተወለዱ በመጀመሪያ ወራት ውስጥ የሚስተዋል ሽፍታ ይኖራቸዋል። የጨቅላ ህጻናት ክፍተኛ ክትትል ውስጥ የሚታከሙ ህጻናት መሀልም ፤ አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ተያያዥ የቆዳ ችግር ያሳያሉ። ከዚህም ከፍተኛውን መጠን የሚወስደው ሽፍታ ነው። በኢትዮጵያም ተቀራራቢ ቁጥር ቢገመትም ፤ ይህን የሚያሳዩ በቂ ጥናቶች የሉም። ሆኖም ግን እነኝህ ህጻናት ወደ ጤና ተቋም እንዲሄዱ ከሚያደርጉ 10 ተጠቃሽ ህመሞች ውስጥ ፤ ሽፍታና የቆዳ ኢንፌክሽን እንዳሉበት ጤና ጥበቃ ሚኒስተር ይጠቁማል። ቢሆንም ፤ ሁሉም ሽፍታ አሳሳቢ አይደለም። የጨቅላ ህጻናት ቆዳ ገራም እንደመሆኑና ካለመዳበሩ የተነሳ ፤ በትንሹም በትልቁም ጉዳይ ሽፍታ ሊይዛቸው ይችላል። ከሙቀት ጀምሮ እስከ ከባድ ኢንፌክሽን ድረስ ሽፍታ ሊያስከትል ይችላል። ለዚህም ወላጆች አሳሳቢ ሽፍታዎችን ፤ ከተራ ሽፍታዎች ለይተው ማወቅ ግድ ይላቸዋል።    ይህንን ማወቅ ደግሞ ተራ የሕክምና ጉጉት ብቻ አይደለም።  እንደኩፍኝ ካሉ ወረርሽኖችም ጋር ተያያዥነት ስላለው የማህበረሰብ ጤና ኃላፊነትም ነው። ለምንድን ነው ሕጻናት ይህን ያህል ለሽፍታ የሚጋለጡት? ሳይንሱ ቀላል ነው።  ከጎልማሳ ሰው ቆዳ አንጻር የህጻናት ቆዳ ሥሥ ነው። ለዚህም በቀላሉ በከባቢያዊ ንጥረ ነገሮች እንዲሁም በበሽታ አምጪ ተህዋሳት ይጠቃሉ። ከዚህም ባሻገር ቆዳቸው በደንብ አለመዳበሩ ፤ ለሽፍታ እና ለቆዳ ኢንፌክሽኖች ተጋላጭነቱን ይጨምራል። የተለመዱ ሽፍታ አምጪ አካላት ከኢንፌክሽንም ባሻገር የአከባቢ ለውጥ ለሽፍታ ያጋልጣቸዋል። ለምሳሌ ሙቀት እንዲሁም ወበቅ/እርጥበት ሽፍታን ያመጣሉ። እርጥበት የበዛበት የህጻን አካል ሽፍታ ይኖረዋል። ይህም ከቆዳ መሳሳት ጋር በይበልጥ ይያዛል። አንዳንዴም እርጥበቱን ተከትሎ የሚመጡ በሽታ አምጪ ተህዋሳትም ይህንን ያስከትላሉ። ለዚህም ተጠቃሽ የሚሆነው የህጻኑ ሽንት ጨርቅ/ዳይፐር የሚሸፍንበት ቦታ ላይ የሚታይ ሽፍታ ነው። በህክምና ስሙ ዳይፐር ደርማታይተስ (የሽንት ጨርቅ አከባቢ ያለ የቆዳ ችግር/ሽፍታ) ሲባል ፤ በሕጻናት የመጀመሪያ ወራት ላይ እጅጉን የተለመደ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት አንድ አመት ያልሞላቸው ህጻናት መሀል ሁለት ሶስተኛውን ያጠቃል። ለሞቁ አካላት ጋር ንክኪ ሲኖር ፣ ላብ የበዛባቸው ስፍራዎች ላይ ፣ አንዳንድ ሳሙናዎችንና እንዲሁም ክሬሞች ጋር ተያይዞም ሽፍታ ሊታይ ይችላል። ይህ እንደ መጠነኛ አለርጂ አይነት ሲመስል ፤ በህክምናም ኮንታክት ደርማታይተስ አልያም ከንክኪ ጋር ተያያዥነት ያለው የቆዳ መቆጣት ይባላል። በስርጭቱ ዙሪያ በኢትዮጵያ በቂ መረጃ የለም። ይህ ሽፍታ በባህሪው ንክኪ ያደረገውን የቆዳ ክፍል ብቻ የሚያጠቃ ሲሆን ፤ ያስቆጣውን አካል (ሙቀት፣ ሳሙና፣ ክሬም፣ ወ.ዘ.ተ...) ክተወገደ በቀናት ውስጥ ይጠፋል። እላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በሽታ አምጪ ተህዋሳትም ፤ ቫይረስን ጨምሮ ሽፍታ ሊያመጡ ይችላሉ። ያልተከተቡ ህጻናት ከቫይረስ ኢንፌክሽን ጋር ተያያዥነት ላላቸው ሽፍታዎች ተጋላጭነታቸው የሰፋ ነው። በተለይ ኩፍኝ ፣ ሩቤላ እና ቺክን ፖክስ ወረርሽኝ ጊዜ ሽፍታዎች ብዙ ህጻናት ላይ ሊታዩ ይችላሉ። በቅርቡ በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍል ውስጥ የታየውን የኩፍኝ ወረርሽኝ ጋር ተያያዥነት ያለው ሽፍታ ለዚህ ዋቢ መሆን ይችላል። ከዚህም ባሻገር በቀላሉ ለባክቴሪያ እና ለፈንገስ ኢንፌክሽን ጋር ተያይዥነት ያላቸውም ሽፍታዎች ይታያሉ። 👶 የሚከተሉትን ሽፍታዎች ካዩ አይደንግጡ። ግን ይከታተሉት ። እነዚህ ሽፍታዎች የተለመዱ፣ በራሳቸው የሚዱኑና አብዛኛውን ጊዜ ምንም ዓይነት ሕክምና የማያስፈልጋቸው ናቸው። ጫፋቸው ነጭ/ቢጫ ነጠብጣብ ያላቸው ጥቃቅን ቀይ ሽፍታዎች  ፡ እነኝህ ከፊሉን አራስ ህጻናት የሚያጠቁ ሲሆን ፤ በብዛትም በተወለዱ በመጀመሪያ ወር ላይ ይታያሉ። በታዩ ከ 1 እስከ 2 ሳምንት ይጠፋሉ። ይህም ሽፍታ እነኝህን ህጻናት የሚያጠቃ ኢራይተማ ቶክሲከም ኒዮናቶረም ምልክት ናቸው። በአፍንጫ ፣ በጉንጭ እንዲሁም አገጭ ዙሪያ የሚታዩ ጥቃቅን ነጫጭ ሽፍታዎች ፡ እነኝህ አንዳንድ ህጻናት ላይ የሚስተአሉ ከቅባት/ወዝ አምራች ህዋሳት ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው። ሆኖም አያሳስቡም። ብጉር የሚመሉ ሽፍታዎች ፡ እነኝህ ከእናት ሆርሞን ጋር ተያይዘው የሚመጡ የተወለዱ አራስ ህጻናት ላይ የሚታዩ ብጉር የሚመስሉ ሽፍታዎች ናቸው። ህጻናቶቹ ደም ውስጥ ያለው የእናት ሆርሞን ሲመናመን ብጉሩ ይጠፋል። ለዚህም መድሐኒት አያስፈልገውም። ላብ እና ሙቀት የሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ የሚታዩ ቀያይ ሽፍታዎችም፡ እነኝህም አያሳስቡም። በብዛት በመጋጠሚያዎች እና የቆዳ እጥፋቶች አከባቢ ይታያሉ። ስፍራው ሲናፈስ እና ሲቀዘቅዝ ይጠፋሉ። ዳይፐር አከባቢ የሚታዩ መጠነኛ ቀያይ የተቆጡ የዳይፐር ሽፍታዎች፡ ቦታው ካለው እርጥበት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ስለሆነ ፤ ቦታው ሲደርቅ ፣ ሲናፈስ ይጠፋሉ። እንዲሁም ቆዳ የሚጠብቁ ቅባቶችም ሽፍታዎቹ እንዲጠእፉ ያግዛሉ። ለዚህም ሊያሳስቡ አይገባም። እነኝህ ሁሉ ሽፍታዎች የሚያሳስቡ ቢመስሉም፤  አደገኛ አይደሉም ። በመጠነኛ የቆዳ እንክብካቤ ይጠፋሉ። 🚨 መጨነቅ ያለባችሁ መቼ ነው? ከዚህ በታች ያሉ ሽፍታዎችን ከተመለከቱ በአፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ይፈልጉ። እነዚህ ሽፍታዎች ኢንፌክሽንን ወይም ከጀርባ ያለ ሌላ ሕመምን ጠቋሚ ሊሆኑ ይችላሉ። የማይነጣጠሉ ትናንሽ ቀይ ወይም ሐምራዊ ነጠብጣቦች ያሉት ሽፍታ ካስተዋሉ ። የበለዘ ወይም የተመታ አይነት መልክ ሲኖራቸው ፤ የቆዳው ቀለም ለውጥ የተጫኑት ጊዜ አይጠፋም። ይህም ከጀርባ ለ እንደማጅራት ገትር ፣ ደም ኢንፌክሽን እንዲሁም የደም መፍሰስ አይነት ከባድ የጤና ችግሮች ጠቋሚ ሊሆን ይችላል። ሰውነት ዙሪያ የተሰራጨ ውሀ ያዥ ሽፍታ ካለ ፤ እንዲሁም ተያይዥ የሆነ የቆዳ መላላጥ ካለ ያሳስባል። ይህም የከባድ ባክቴሪያ ኢንፌክሽን ጠቋሚ ነው። አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ያስፈልጋል እና አይዘግዩ። ሽፍታው በፍጥነት ከተስፋፋ ፤ አብሮት የአተነፋፈስ ለውጥ  እንዲሁም ሌሎች አካላዊ ለውጦች ጋር ከተያያዘ ያስተውሉ። የህክምና እርዳታ ያስፈልጋል።   ሽፍታው መግል ካዥ ፣ ትኩሳት ካለ እና የሽፍታው ስር ከቀላ የባክቴሪያ ቆዳ ኢንፌክሽን ሽፍታ ሊሆን ይችላል። ተያይዥ ሽታም ሊኖር ይችላል። ያስተዋሉት የዳይፐር  ሽፍታ ከ 3 ቀናት በላይ ከሰነበተ ሀኪም ጋር ይዘው ይሂዱ ። ቦታው ጋር ያለው እርጥበት ኖሮ ፤ ንጽህና ተጠብቆ አለመሻሉ ፤ ተደራቢ የባክቴሪያ አልያም የፈንገስ ኢንፌክሽን ጠቋሚ ሊሆን ይችላል። ያስተውሉ እነኝህ  እጅጉን አሳሳቢ ሽፍታዎች ስለሆኑ ፤ የሕክምና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።  ለዚህም መቼም እንዳይዘናጉ! 🛑 ከሽፍታው ባሻገር ማስተዋል ያለብዎ ምልክቶች  ከሽፍታው ጋር ተደርበው እነኝህ ምልክቶች ካዩ ፤ የትኛውም አይነት ሽፍታ ቢሆን ፤ በአቅራቢያዎ ካለ የጤና ተቋም በአፋጣኝ ይሂዱ። ትኩሳት (>38°C) የምግብ ፍላጎት መቀነስ (እንደወትሮው አለመጥባት ) የእንቅልፍ ለውጥ (አለመተኛት / እንቅልፍ ከወትሮ በተለየ መጠን ማብዛት) አብዝቶ መነጫነጭ/ ማልቀስ የአተነፋፈስ ለውጥ የፊት/ከንፈር እብጠት የበለዙ የሚመስሉ ሽፍታዎች የአንገት እንቅስቃሴው መገደብ (አንገት መድረቅ) ማስታወክ ማንቀጥቀጥ በፍጥነት የሚስፋፋ ሽፋታ መግል ካዠ ፣ ከቆሰለ ፣ እንዲሁም  ሽታ ካለው ያስተውሉ! እነኝህ ምልክቶች የቆዳ ችግር ብቻ አለመሆኑን ጠቋሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ለዚህም በአፋጣኝ ልጅዎን ያሳክሙ። 🛡️ እርስዎስ ምን ማድረግ ይችላሉ? የህጻኑን ንጽህና ይጠብቁ።  ሽንት ጨርቁን / ዳይፐሩን እንደተጠቀመ ይቀይሩ። እንደ ዚንክ ኦክሳይንድና ፔትሮሊየም ጀል (ቫዝሊን) አይነት ቆዳን የሚጠብቁ ክሬሞችን/ቅባቶች መጠቀም ይችላሉ። ሰውነት ሲያጸዱ አይፈትጉ። በስሱ ቆዳውን ያጽዱ። ቆዳ ሁል ጊዚ አይሸፈን ። መናፈስ እርጥበት ያጠፋል። ክትባት ፈጽሞ እንዳይዘለል። ለሕይወት አስጊ የሆኑ የቫይረስ ኢንፌክሽኖችን ለመከላከል ክትባት እጅጉን አስፈላጊ ነው። አንዳንዶቹ ኢንፌክሽኖች ተከትሎ የሚመጣ ሽፍታንም ይከላከላል። ማንኛውንም አሳሳቢ ሽፍታ ካዩ በአፋጣኝ የጤና ተቋም ይሂዱ። ምርመራ ይደረግ። አይዘናጉ! ለልጅዎ ጤና ቦታ ይስጡ።

  • አለርጂ አለብዎ? እንዴት አወቁ?

    ስለ አለርጂ ሰምቶ የማያውቅ አለ ማለት ዘበት ነው! አብዛኞቻችን ወይ አለርጂ አለብን ፤ ወይ አለርጂ ያለበት ሰው እናውቃለን። ምናልባት አለርጂ የሚያስነሳብዎት ቀስቃሽ አካል ፤ እስከዛሬ ሳያጋጥምዎ ቀርቶ ቢሆንስ? ምናልባት አለርጂ ኖሮብዎት ፤ አለመስማማት ነው ብለው በቸልተኝነት አልፈውት ቢሆንስ? ብዙዎች "አለርጂ አለብኝ" ወይም "አለርጂ የለብኝም" ከሚለው ባሻገር የተሟላ ግንዛቤ የላቸውም። አለርጂን ለመከላከል ደግሞ ይህ ግንዛቤ እጅጉን አስፈላጊ ነው። አለርጂ ምንድን ነው? አለርጂ ቀለል አድርገን ስንወስደው የሰውነት መቆጣት ነው። ታድያ ግን እንደ ኢንፌክሽን የበሽታ አምጪ ተህዋሳትን ለማስወገድ የሚደረግ መቆጣት አይደለም። ይልቁኑ ሰውነታችን ምንም ጉዳት የማያደርሱ እንግዳ አካላትን ፤ እንደ በሽታ አምጪ ተህዋሳት ሲረዳ የሚፈጠር ነው። እነሱን ለማስወገድ በሚያደርጉት ጥረት ሰውነታችን ይቆጣል። ሰውነታችንን እንዲህ የሚያስቆጡ እንግዳ አካላት ፤ በህክምናው አለርጀን ወይም አለርጂ ቀስቃሽ አካላት ተብለው ይጠራሉ። እባብ ያየ በልጥ በረየ የሚባለው ይሄ ነው! ከአለርጂ ጀርባ ያለውን ሳይንስ ማወቅ ከፈለጉ እነሆ፡ ሰውነት እነኝህ እንግዳ አካላት  መቃወሚያ መርዞችን (IgE) ያመነጫል። ይህንን ጥቃት በፊት አውራሪነት የሚመሩት የማስት ህዋሳት እና ኢዮሲኖፊል የሚባሉት የበሽታ መከላከያ ህዋሳት ናቸው። እነኝህም ሰውነታችን እንዲቆጣ የሚያደርጉ ኬሚካሎችን (Histamine and cytokines) ያመነጫሉ። የእነኝህ ኬሚካሎች መለቀቅ የሚያመጣው መቆጣት በአለርጂ ጊዜ የምናያቸውን ምልክቶች ይፈጥራል። የአልርጂ መቆጣት ግን መጠኑ ሊለያይ ይችላል።   አንዳንዲ እጅጉን ቀላል የሆነ መቆጣት ሲሆን ፤ ሌላ ጊዜ ህይወትን አደጋ ላይ የሚጥል ሊሆን ይችላል። ስርጭቱ ምን ይመስላል? እ.ኤ.አ በ2021 በዓለም ዙሪያ ወደ 260 ሚልዮን የሚጠጉ አስም ያለባቸው እንዲሁም ወደ 129 ሚልዮን የሚጠጉ ስር የሰደደ የቆዳ አለርጂ (አቶፒክ ደርማታይተስ / Atopic Dermatitis )ያለባቸው ሰዎች ነበሩ። አለርጂ ያለባቸው ሰዎች መጠንም እየጨመረ ይገኛል። ታድያ አስም እዚህ ጋር ምን አገናኘው? አስም ከ አለርጂ ጋር ከፍ ያለ ቁርኝት አለው። አስምን በአጠቃላይ በሁለት መክፈል ይቻላል፦ *የተለመደው በቀስቃሽ አካላት የሚነሳው የአለርጂ አስም እና * ከአለርጂ ጋር ቁርኝት የሌለው አስም ተብሎ ሊከፈል ይችላል። የአስም የተለመዱ ቀስቃሽ አካላት መሀል አቧራ ፣ ቅንቅን ፣ የቤት ውስጥ ብናኞች፣ የአበባ ብናኞች፣ ሻጋታ፣ የእንሰሳት ርጋፊ ይገለጻሉ። ሲቀሰቀስም ከአለርጂ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልክ የትንፋሽ ቧንቧዎች ይቆጣሉ ፤ ያብጣሉ ፤ ይጠባሉ። ይህም የመተንፈስ ችግር ይፈጥራል። ህክምናው ውስጥም የሰውነት መቆጣትን የሚያስታግሱ መድሀኒቶች አሉ። እንዲሁም ቀስቃሽ አካላቶቹን መለየት እና ማስወገድ ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ የሚታየው ሁኔታ ይህንን የዓለም አቀፍ ሁኔታ ያንፀባርቃል። በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶችም ስርጭቱ በሀገሪቷ እየጨመረ መምጣቱን ያሳያሉ።  በምሥራቅ ኢትዮጵያ በፋብሪካ አከባቢ በሚኖሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ የተካሄደ አንድ ጥናት ከ አምስቱ አንዱ አለርጂ እንዳለባቸው ይጠቁማል ። በባህርዳር የተደረገ ጥናት በበኩሉ 17.1% የሚሆኑ ሕፃናት አቶፒክ ደርማታይተስ እንዳለባቸው ያሳያል ። የአለርጂ ዓይነቶች አለርጂን በተለያየ መንገድ ልንከፍል እንችላለን። ከዚህም መሀል በሚከተለው መንገድ ልንመድብ እንችላለን።  የመተንፈሻ አካላት አለርጂ  - ይህ የአለርጂ አይነት በቅድሚያ የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃ ሲሆን ፤ በዋነኝነት በአየር ላይ በሚገኙ አካላት ይከሰታል። ለዚህም የአበባ ብናኝ ፣ ቅንቅን ፣ ሻጋታ ፣ የእንሰሳት ርጋፊ፣ ወ.ዘ.ተ... ይጠቀሳሉ። ከዚህም ጋር በተያያዥነት የሚገለጹት የአፍንጫ መደፈን እና እንደውሀ የሚፈስ ንፍጥ የሚያስከትለው አለርጂ ራይናይተስ (Allergic Rhinitis) እና አስም ይጠቀሳሉ። የምግብ አለርጂ - አንዳንድ ምግቦች በውስጣቸው ያሉ ንጥረነግሮች አለርጂ እንዲከሰት ያደርጋሉ። እነኝህን ምግቦች ሲመገቡ ሰውነትዎ ክማሳከክ እና ሽፍታ ጀምሮ ለሕይወት አስጊ እስከሆነ መቆጣት ሊያሳይ ይችላል። የቆዳ አለርጂ  - ቆዳችን ከአንዳንድ አካላት ጋር ንክኪ ካለው ፤ አለርጂ ምላሽ ሊያሳይ ይችላል።ይህን ጊዜ የሚያሳክኩ ቀያይ ሽፍታዎች ፣ ስር ሰደድ የቆዳ ህመም (Atopic Dermatitis) ይታያል። ይህም ብዙ ጊዜ የሚከሰተው በሳሙናዎች ፣ በአንዳንድ እጽዋቶች/የእጽዋት ግብአቶች ፣ አንዳንድ ብረቶች እንዲሁም በእንደ ላቴክስ አይነት ውህዶች ነው። የመድሀኒት አለርጂ - አብዛኛው የምናቃቸው መድሀኒቶች ፤ አለርጂ የማምጣት አቅም አላቸው። ሆኖም ግን ይህ አለርጂ የሚታይባቸው የተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸው። የጤና ባለሙያዎችም እነኝህን መድሀኒቶች ሲያዙ ይህንን የጎንዮሽ ጉዳት አስተውለው ነው። ምላሹም ቀለል ካለ መቆጣት እስከ ህይወት አስጊ ደረጃ ሊደርስ ይችላል። ማወቅ ያለብዎ የተለመዱ አለርጂ አምጪ አካላት ብዙ አይነት አለርጂ አምጪ አካላት ቢኖሩም ፤ የተለመዱት የሚከተሉት ናቸው።  🕷️ ቅንቅን ፡ እነዚህ በአቧራ ፣ በምንጣፍ ውስጥ ፣ በእንሰሶች ላይ እንዲሁም ፣ በቤት ውስጥ ባሉ እንጨቶች ዙሪያ የሚገኙ ጥቃቅን ፍጡሮች ናቸው። በተለይ ደግሞ እርጥበት አዘል አከባቢ ላይ ይኖራሉ። እነኝህም አለርጂ በማምጣት እጅጉን ይታወቃሉ። በተለይም አስምን፣ ሳይነስን ፣ አለርጂ ራይናይተስን ይቀሰቅሳሉ። ያብሳሉ። 🌸 የአበባ ብናኝ፡  ንቦች የሚቀስሙት የአበባ ብናኝም አለርጂ ያስከትላል። ለዚህም አበባ በብዛት በሚያብበት በጸደይ ወቅት እንዲሁም ንፋስ አብዝቶ በሚነፍስባቸው ወራት ላይ እነኝህ የአበባ ብናኞች አየር ላይ ስለሚበዙ አለርጂ ያለባቸው ሰዎች ይቀሰቀስባቸዋል። 🦠 ሻጋታ ፦ ሻጋታም አለርጂ በመቀስቀስ ይታወቃል። በቤቶችና በሕንፃዎች ውስጥ የሚፈጠር እርጥበት አዘል ሁኔታ ፤ ሻጋታ እንዲያድግ ያደርጋል። ያደገው ሻጋታ ዘር/ብናኝ በቤቶች እና ቢሮዎች ባለ አየር ላይ ይስፋፋል። ይህም በአከባቢው ባሉ ሰዎች ላይ ተደጋጋሚ አለርጂ እንዲከሰት ያደርጋል። 🥚 የምግብ አለርጂዎች ፦ እነኝህ በብዛት የሚታወቁ ፤ ብዙ ፊልሞች ላይ ያየናቸው አለርጂ አምጪ አካላት ናቸው። ከእነኝህም መሀከል ኦቾሎኒ ፣ እንቁላል፣ የወተት ተዋጽኦዎች እንዲሁም የባህር ምግቦች ዋነኛ ተጠቃሽ ናቸው። እንደ ስንዴ ፣ አጃ እና የመሳሰሉት አይነት አዝዕርቶችም አለርጂ ሊያመጡ ይችላሉ። ይህም ውስጣቸው ባለው ግሉተን ከሚባል ንጥረ ነገር ጋር ይገናኛል። ታድያ እንዴት ኢትዮጵያ ላይ በብዛት ኣናይም ? ይህ ዘረመልን ጨምሮ ከተለያዩ ነገሮች ጋር ይያዛል። በአንድ በኩል በኢትዮጵያ ዋነኛ የምንመገበው አዝዕርት ጤፍ ሲሆን ፤ ጤፍ ደግሞ በውስጡ ይህ ፕሮቲን ስለሌለው ፤ ይህ አለርጂ ላለበቸው ሰዎች ተመራጭ ምግብ ነው። በቅርቡ በአለም ዙሪያ ተወዳጅነት እያተረፈ ያለው ከዚህ ጋር ተያይዞ ነው። ለዚህም በኢትዮጵያ ይህ አለርጂ ያለባቸው ሰዎች ቢኖሩ ፤ የስንዴ ዳቦ እንደማይስማማቸው፤ እንደሚያማቸው የገብስ ዳቦ አልያም የጤፍ እንጀራ እንደሚመርጡ ይገልጻሉ። ሳያውቁት አለርጂ ምልክት የሚያሳየውን አካል በማስወገድ እራሳቸውን ያክማሉ። 🐝 Iየነፍሳት ንድፊያ  - ንቦች ፣ ተርቦች እንዲሁም ሌሎች ተናዳፊ እንሰሳት ፤ ሲነድፉን የሚለቀቀው ኬሚካል ፤ ሰውነታችንን ያስቆጣል። የአለርጂ ምላሽ ያስከትላል። 🐾 የእንሰሳት ብናኝ ፡  ከአንዳንድ የቤት እንሰሶች ሰውነት የሚረግፉ የቆዳ ቅንጣቶች፣ የጸጉር እርጋፊዎች ፣ ምራቆቻቸው እንዲሁም ሽንቶቻቸው አለርጂ ያመጣሉ። ለዚህም ነው አንዳንድ ሰዎች የድመት አለርጂ ፤ ሌሎች የውሻ አለርጂ አለብኝ ሲሉ የምንሰማው። የእንሰሳቶቹ ጥላቻ ሳይሆን ፤ እንሰሶች አጠገብ መገኘት ጤናቸውን አደጋ ላይ ስለሚጥል ነው። አለርጂ እንዳለብዎ እንዴት ለይተው ይወቁ?   አለርጂ እንዳለብዎ ለማወቅ ፤ የአለርጂ ምልክቶች ለይተው መረዳት አስፈላጊ ነው። እንደ የሰዉ ፤ እንደ የአለርጂ አይነቱም ምልክቶቹ ቢለያዩም ፤ በይበልጥ የሚታዩት የተለመዱ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው። የመተንፈሻ አካላት አለርጂ ካለብዎ በይበልጥ ማስነጠስ ፣ ማሳል አፍንጫ መታፈን አፍንጫ ማሳከክ ከአፍንጫ እንደ ውሀ የሚወርድ ፈሳሽ አይንን ማሳከክ አይን ውሀ መቋጠር ያስተውላሉ። የቆዳ አለርጂ   ካለብዎ በይበልጥ፦  ሽፍታ፣ እብጠቶች ቆዳ መቅላት ማሳከክ ያያሉ ። የምግብ አለርጂ ካለብዎ በይበልጥ ፦ ማቅለሽለሽ/ ማስመለስ ከንፈር፣ ምላስ ወይም ጉሮሮ እብጠት የሆድ ህመም ሊያዩ ይችላሉ። የአለርጂ ምልክቶቹ ከጠነከሩ አልያም ካየሉ ፤ የአናፍላክሲስ ምልክቶች ያያሉ ። አናፊላክሲስ የምንለው ምንድነው? አናፍላክሲስ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚይጋጥም ከባዱ የአለርጂ ምልክት ነው። ይህም ለህይወት እጅጉን አስጊ ነው። በአፋጣኝ ህክምና ካልተደረገ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት ይዳርጋል። የአናፍላክሲስ ጠቋሚ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው። ·የትንፋሽ ማጠር/የመተንፈስ ችግር (አስም በሽተኛ ከሆነ ፤ የሚሳብ መድሀኒት ይውሰድ) ·የጉሮሮ እብጠት  ·ደግም ግፊት መውረድ ·ራስን መሳት ያመጣል። አለርጂ እንዴት ይታወቃል? የቆዳ ምርመራ ፦ የተለመዱ አለርጂ አምጪ አካላት ያሉበት መመርመሪያ ፤  ቆዳ ላይ ተደርጎ ፤ በሚታየው ምላሽ የትኛው አለርጂ እንዳለ መለየት ይቻላል። የአለርጂ የቆዳ ምርመራ የደም ምርመራዎች - ለተጠረጠሩ አለርጂ አምጪ አካላት በተጋለጡ ጊዜ ፤ የእነሱ መቃወሚያ ኬሚካል (IgE) መጠንን በመለካት አለርጂ መኖሩን ማወቅ ይችላል። የማስወገድ አመጋገብ - ይህ የምግብ አለርጂን ለመለየት የሚረዳ ብልህ የአመጋገብ ዘዴ ነው። ከህክምና ክትትል ጋር በማጣመር የሚጠረጠሩ አለርጂ አምጪ ምግቦችን አንድ በአንድ ከምግብዎ በማስወገድ የትኛው አለርጂ እንዳመጣ መለየት ይቻላል። አከባቢዎን ይከታተሉ ፤ ይቆጣጠሩ። የተለመዱ አለርጂ አምጪ አካላትን ከአከባቢዎ በመቀነስ ፤ የሚያሳዩትን የአለርጂ ምልክቶች በመከታተል ፤ አለርጂ አምጪ አካሉን መለየት ይቻላል። አለርጂን ለመከላከል ምን ያድርጉ? ሁሉንም አለርጂ መከላከል ባይቻልም አንዳንድ እርምጃዎች በመውሰድ አለርጂ ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ መቀነስ ይችላሉ። ለዚህም የሚከተሉትን ያድርጉ። አለርጂ ምልክቶችን ሲያዩ ዶክተርዎን አማክረው የአለርጂ መቃወሚያ መድሀኒቶችን (antihistamine, corticoseroid, immunotherapy, etc) መውሰድ ይችላሉ።  ከባድ አለርጂ ካለብዎ በራሱ የሚወጋ የኢፒነፍሪን አውቶማቲክ መርፌ(epipen/ epinephrine injection) ይዘው መንቀሳቀስ ይኖብዎታል። ምልክቶቹን እንዳዩ እራስዎን በአፋጣኝ መውጋት ይኖርብዎታል። አለርጂዎን የሚጠቁም መረጃ ይዘው መጓዝ ይኖርብዎታል። የአለርጂ ዘላቂ ህክምና ያለብዎን የአለርጂ አይነት እና ቀስቃሽ አካል ለይቶ ከማወቅ ይጀምራል። ለዚህም የጤና ባለሙያ ያማክሩ። እላይ በተገለጹት መንገዶች መለየት ይቻላል። የታወቁ/ የተለመዱ አለርጂ አምጪ አካላትን ከአከባቢዎ ያስወግዱ። አለርጂ ከሚቀሰቅሱ ንጥረ ነገሮች ራቁ። የአከባቢዎን ንጽህና ይጠብቁ።  አዘውትረው ያጽዱ። ከአቧራ፣ ከሻጋታ፣ ከእንሰሳት ያርቁ።  አቅሙ ካለዎ የአየር ማጽጃ በቤትዎ ይጠቀሙ።  አየር ላይ ያሉ አለርጂ አምጪ አካላትን ሊያጣራ ይችላል።  በአለርጂ ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ ይኑርዎ። እንደዚህ አይነት የጤና ጽሁፎችን እንዲሁም ቪድዮዎችን ያንብቡ። ሆኖም ግን ያስተውሉ በጤና ባለሙያ የሚለቀቁ ፤አልያም በጤና ተቋማት የሚለቀቁትን ብቻ ያንብቡ።   ያስተውሉ አለርጂን ችላ ማለት ሥር የሰደደ የጤና ችግር ያመጣል። ለሞት ይዳርጋል። ህይወትን ይበጠብጣል።  ምልክቶቹን ቀደም ብለን በመገንዘብ ፤ እንዲሁም የመከላከያ እርምጃዎችን በመውሰድ ፤ ተጽዕኖውን መቀነስ እንችላለን። ይህን የጤና ችግር በመፍታት ረገድ የተሟላ ግንዛቤና ንቁ ሆኖ መቆየት ወሳኝ ነው።

  • ስለ ማይግሬን ራስምታት ማወቅ ያለብዎ

    ያልታሰበው ውሎ እንደዚህ አይነት ቀን ቢያሳልፉስ ... አዘቦት ቀን ነው እንበል። የእለት ተግባርዎት ላይ ተጠምደዋል። ታድያ ሰሞኑን የነበረብዎት የስራ ጫና ሆነ ማህበራዊ ውጥረት ፤ በድንገት ቀኑን ወደ አልታሰበ አቅጣጫ ቢወስደውስ? ቡና አብዝተው መጠጣትዎ ፣ ጠንካራ ሽታ መሽተቱ፣ ከፍተኛ ድምጽ መስማትዎ ፣ ደማቅ ብርሀን ማየትዎ አልያም ፣ ከባድ ቅዝቃዜ መኖሩም ይህንን አዙሪት ሊያስጀምር ይችላል። ድንገት ምግብ ሳይበሉ ከቆዩም እንዲሁ። ታድያ ሲጀምር ድካም፣ ደስ የማይል ስሜት(መክበድ)፣ የባህሪ ለውጥ፣ ሀሳብ መበተን አይነት ሊሰማዎት ይችላል። ራስ ቅልን /ማጅራትዎን ጨምድዶ ሊይዝዎት ይችላል። እይታዎ ሊረበሽ አልያም ብዥ ሊልብዎም ይችላል። ይህ ማኮብኮቢያው እንጂ ዋነኛ የበሽታው ምልክት አይደለም።  ይሄ የማስጠንቀቂያው ደውል ነው። ትንሽ ቆይቶ ከዓይንዎ ጀርባ እንደመርፌ የሚጠረቁስ ህመም ሊሰማዎት፣ በከባዱ ሊያቅለሸልሽዎ ፤ ከማቅለሽለሽም አልፎ ሊያስታውክዎ ይችላል። ብርሀን መቋቋም ያቅትዎታል። ጮክ ያለ ድምጽም እንዲሁ። እነኝህ ግን አጃቢ ምልክቶቹ ናቸው።   ከእነኝህ ጀርባ የሚሰነጥቅ አልያም የሚቀጠቅጥ (throbbing headache) አይነት ከባድ ራስ ምታት አለ። የማያቆም እረፍት የሚነሳ ራስ ምታት! ሀሳብ መሰብሰብ ፈጽሞ ያዳግትዎታል። ይህ የመጨረሻው ነው ብለው ካሰቡ ተሳስተዋል!   ስልክ ሲጠቀሙ የስልኩ ብርሀን ከጨመረ ፤ ከባድ ድምጽ ከሰሙ ፣ ታክሲ ውስጥ ተሳፋሪ ያደረገው ሽቶ ጠንካራ ጠረን ካለው ፤ ህመሙ እጥፍ ድርብ ይሆናል። ቀንዎ በሙሉ በድርድር ይሞላል።  ሁሉ ነገር በቋፍ ነው ያለው። ቡና ከጠጡበትማ፤ አይታሰብም።   ይህ ተራ ራስ ምታት አይደለም! ከዛ ሽሽት ይጀመራል! ከህመሙ ሽሽት! ወዴት? ወደ ጨለማ ክፍል። ወደ መኝታ። ወደ ዝምታ መሸሽ። ብርሀን፣ ድምጽና እንቅስቃሴ ወደሌለበት ማፈግፈግ።  ሁሉን ትቶ ለማገገም ከአለም ለጊዜው መመሸግ። ከሰአታት በኋላ ህመሙ እየቀነስ ይመጣል። በጭጋግ የተከለለው እይታ ሆነ ትኩረት እያዘገመ ይመለሳል።   ይሄ ግን ጊዜያዊ ነው! ጠንካራ ጠረን ፣ ከባድ ድምጽ አልያም እንቅልፍ ማጣት በቅጽበት ይህንን አዙሪት ዳግም ያስነሳል። ቀድመው መቆጣጠር ካልቻሉማ ፤ ጉዞው ቁልቁለት ነው!   በዚህ መሀል ፣ ከማህበራዊ ህይወት ራስዎን ያገላሉ። ስራ ይስተጓጎላል።   ይህ ለተወሰኑ ሰአታት አልያም ለአንድ ቀን ከሆነ ፤ ላያሳስብዎ ይችል ነበር። ሆኖም ግን ደጋግሞ የሚመጣ ለቀናት የሚቆይ ቢሆንስ? ይህ የማይግሬን ታማሚዎች ያልታሰበ ውሎ ነው። በድንገት ተቀስቅሶ ቀናችውን የሚያቃውስ ፤ ህይወታቸውን የሚያስተጓጉል ከባድ ራስ ምታት ነው።   ማይግሬን ምንድነው? ማይግሬን "ራስ ምታት ብቻ" አይደለም። ይህ የነርቭ በሽታም ነው። በአለም ዙሪያ ከአንድ ቢሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በማይግሬን እንደሚጠቁ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ስርጭቱም ባለፉት 30 አመታት ውስጥ ጨምሯል። በየአመቱም በመቶ ሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ያስተጓጉላል። እንደየጥናቶች ቢለያይም በኢትዮጵያ ስርጭቱ ከ 3 በመቶ እስከ 18 በመቶ ይደርሳል። ጥቂት የማይባሉ የማይግሬን ታማሚዎች ፤ በሽታው እንዳለባቸው እራሱ ላያውቁ ይችላሉ። በተለይ የህክምና እርዳታ ውስን በሆነበት በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ደግሞ ይህ ቁጥር ከፍ ሊል ይችላል። በአዲስ አእበባ የተደረገ የማህበረሰብ ጥናት በበኩሉ ፤ ከ5 ሰዎች አንዱ የራስ ምታት ህመም ሲኖርበት ፤ ከዚህ ከፊሉ የማይግሬን በሽታ ተጠቂ መሆኑን ይጠቁማል። ይህ ስርጭት ከፍተኛ ነው።   ምልክቶቹ ማስጠንቀቂያ ምልክቶቹ፡ አንዳንድ ጊዜ ከሕመሙ ከ 5 እሰከ 60 ደቂቃ ቀድመው የሚታዩ ምልክቶች ሊኖሩ ይችላሉ። እነኝህ ህመሙ መቀስቀሱን ማመላከቻ ናቸው። እንደማንቂያ ደውል የማይግሬን ራስ ምታት ሊጀምር መሆኑን ይጠቁማሉ። በብዛት የሚታዩት ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው። የማየት ችሎታ መቀነስ/ የእይታ መደብዘዝ፣ እይታ መሀል የሚኖሩ ተምዘግዛጊ መስመሮች፣ ብልጭልጭ ነገሮች ሰውነት ላይ መደንዘዝ፣ መብላት፣ ማቃጠል፣ መጠዝጠዝ፣ መቆጥቆጥ ቃላት መጥፋት ባህሪ ለውጥ ድካም  የማይግሬን ህመምን ተከትሎ ሊመጡ ከሚችሉ የእይታ ለውጦች አንዱ ዋነኛ ምልክቶቹ ከመጠነኛ– እስከ ከባድ ራስ ምታት። ራስ ምታቱ የሚቀጠቅጥ/የሚጠዘጥዝ (በስከንዶች ውስጥ ከፍ ዝቅ እያለ የሚዋዥቅ) አልያም የሚሰነጥቅ አይነት ሊሆን ይችላል። ህክምና ካልተደረገለት ህመሙ ከ 4 ሰአት አንስቶ እስከ 3 ቀን ሊቆይ ይችላል። ይህም ራስ ምታት በተለመዱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችም ሊባባስ ይችላል።  ማቅለሽለሽ/ማስመለስና እንዲሁም ብርሃን/ድምፅ መቋቋም አለመቻል አብሮት ሊኖር ይችላል። አንዳንድ የማይግሬን አይነቶች ላይ እነኝህ ምልክቶች ብቻ (እይታ መለውጥና ድምጽ አለመቻል ብቻ) ሊታዩ ይችላሉ። ከህመሙ በኋላ የሚታዩ ምልክቶች ከህመሙ በኋላ  ለሰአታት ድካም ሊኖር ይችላል። ከዚህም ባሻገር የሀሳብ ጭጋት/ ትኩረት ማጣት ሊኖር ይችላል።   ለምን ያጋጥማል? የማይግሬን በሽታን ሳይንስ ሙሉ በሙሉ አልተረዳውም። ሆኖም ግን የማይግሬን ራስ ምታት ከነርቭ መቆጣት እና ከአንጎል አስራር ለውጥ ጋር ተያያዥነት እንዳለው ጥናቶች ይጠቁማሉ። ለበሽታውም አጋላጭ መንስኤዎች የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው። ጀነቲክስ/ዘረመል፡ የማይግሬን ህመም ያለበትየቤተሰብ አባል ካለዎ፤ የማይግሬን ህመም የማጋጠም እድሉ ከፍተኛ ነው። የሆርሞን ለውጥ፡ ማይግሬን ከሆርሞን ለውጥ ጋር ተያይዞ ሊከሰት ይችላል። የወር አበባ ኡደትን ተከትሎ ያለው የሴቶች የኢስትሮጅን ሆርሞን መዋዠቅ ማይግሬን እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል። ለዚህም ሴቶች ወር አበባ በሚያዩባቸው ጊዜያት ላይ ማይግሬን ተደርቦ ሊታመሙ ይችላሉ። የነርቭ አሰራርን የሚለውጡ ማንኛውም ክስተቶች ማይግሬን ሊያመጡ ይችላሉ። ለምሳሌ ጭንቅላት ላይ የሚደርስ ጥቃትን ተከትሎ የሚያጋጥም ለውጥ ማይግሬን ሊያመጣ ይችላል። ቀስቃሽ አካላት ከላይ የተጠቀሱት ለማይግሬን ያጋልጣሉ። ቢሆንም ማይግሬን ራስ ምታት እንዲያጋጥም ፤ ቀስቃሽ አካላት ያስፈልጋሉ ። እነኝህ ቀስቃሽ አካላት ሰውነት ላይ የሚፈጥሩት ለውጥ ፤ የነርቭ መቆጣት እንዲጨምር ፤ ማይግሬን ራስ ምታት እንዲከሰት ያደርጋል። በጣም የተለመዱት ማይግሬንን የሚያስከትሉ ቀስቃሽ አካላት የሚከተሉት ናቸው። የእንቅልፍ መዛባት፣ በቂ ውሀ አለመጠጣት /ሰውነት ውስጥ ውሀ ማነስ መራብ / በቂ ምግብ አለመመገብ ውጥረት/ጭንቀት የስሜት ሕዋሶችን የሚፈትሹ ነግሮች ደማቅ ብርሃን፣ ጠንካራ ሽታ፣ ጮክ ያለ ድምጽ የአየር ለውጥ  ህመም ማስታገሻ  መድኃኒቶችን አብዝቶ መጠቀምም ፤ ይህንን ሊያስከትል ይችላል። ለዚህም የማይግሬን ታማሚዎች የሚወስዷቸውን ማስታገሻ መድሀኒቶች እና የራስ ምታቱን ለውጥ በማስታወሻ ቢመዘግቡ ይመከራል። የመፍትሔ አቅጣጫዎችስ ? ጊዜያዊ የማይግሬን ህመም ለማሻሻል እና ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት የምንጠቀማቸው የህክምና አማራጮች ይለያያሉ። ለአጭር ጊዜ ከ ዳይክሎፌናክ እና ፓራሴታሞል ጀምሮ ህመም ማስታገሻ መውሰድ ይችላል። እንደ ህመሙ እና ምላሹ የሚወሰዱት ማስታገሻዎች ሊለያዩ ይችላሉ። የትውከት እና ማቅለሽለሽ መከላከያ መድሀኒትም ሊያስፈልግ ይችላል። ይህ ግን የህመሙን ምልክት መቀነስ እና ጊዜያዊ ማስታገስ ላይ ያተኮረ ህክምና ነው። ለዚህም መፍትሔው ጊዜያዊ ነው። ዘላቂ መፍትሔ ከፈለጉ ፤ በቅድሚያ ዶክተርዎን ያማክሩ። እንደአስፈላጊነቱ አይቶ ህመሙን እንዳይቀሰቀስ የሚያደርጉ መድሀኒቶች ሊያዝልዎት ይችላል።  እንደ ፕሮፕራኖሎል ያሉ የሚዋጡ ፤ አልያም ነርቭን የሚቀሰቅሱ አማራጮች አሉ።   ማንኛውም ሰው ሊያደርጋቸው የሚችላቸው  ተግባሮች  በመጀመሪያ ልማዶችን ይገንቡ። የሚተኙበትን ፤ ከእንቅልፍ የሚነቁበትን ሰአት ተመሳሳይ ያድርጉ። በቀን ቢያንስ ለስደስት ሰአት ይተኙ። በቂ ውሀ መጠጣ ልማድዎ ይሁን። በቀን ከ 2 እስከ 3 ሊትር ውሀ ይጠጡ። በሳምንት ከ 3 እስከ 4 ጊዜ መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ። ኤሮቢክ እንዲሁም የአንገት እና ጀርባ ጡንቻን የሚያጠነክሩ ስፖርቶች ይመረጣሉ። የኢኮኖሚ ደረጃ ቢወሰንውም ፤ በቂ የተመጣጠነ ምግብ ለመመገብ ጥረት ያድርጉ። የእርስዎን ማይግሬን ህመም ቀስቃሽ አካላት ይወቁ። ማስታወሻ ይያዙ። ምንድነው የሚቀሰቅሰው? ምግብ፣ እንቅልፍ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ ወ.ዘ.ተ... ይመዝግቡ።  ስንት ሰአት ላይ ተቀሰቀሰ? አሁንም ይመዝግቡ። ምንስ መድሀኒት ወሰዱ? ምንስ ለውጥ አመጣ? ይህንንም ይመዝግቡ። ከደማቅ ብርሀን እና ከከፍተኛ ድምጽ ይራቁ። ካስፈለገ የጸሀይ መነጽር ያድርጉ። የጸሀይ ኮፍያ ማድረግም ይችላሉ። ስክሪን ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ ይገድቡ። ጸጥታ የሰፈነበት ቦታ ጊዜዎን ያሳልፉ። ይረፉ! በህይወትዎ ያለ ውጥረትን ለመቀነስ ይሞክሩ። በየእለቱ ዘና የሚያደርጉ ተግባራትን ይፈጽሙ።  የጤና ባለሙያ አማክረው እንዲያግዝዎ መውሰድ የሚችሏቸው መድሀኒቶችም አሉ። የቪታሚን ቢ ፣ የማግኒዚየም ማዕድን ያለባቸውን እንክብሎችን እንደ ደጋፊ መውሰድ ይችላሉ። እነኝህም መድሀኒቶች የማይግሬን ራስ ምታት የመቀስቀስ እድልን ይቀንሳሉ። ያስታውሉ ተግባራዊ ለውጥ በማምጣት ጤናዎን ይጠብቁ። ማይግሬንን እንደ ተራ ራስ ምታት ወስደው ፈጽመው እንዳይዘናጉ። ፈጠን ብሎ ጊዜያዊ ህመም ማስታገሻ ህክምናን ማድረግ ህመሙን ቢያጠፋም፤ ቋሚ የህክምና አማራጮችን አብሮ መውሰድ ያስፈልጋል። እርሶም በበኩልዎ ልማድዎን መለወጥ ፤ ባህሪዎን ማስተካከል ፤ እንዲሁም የህመሙ ማስታወሻ መውሰድ ያስፈልግዎታል። ማይግሬን "ራስ ምታት ብቻ ነው" ብሎ ለሚያስብ ሰው ይህን አካፍል።

  • 🌸የወር አበባ ጊዜውን ጠብቆ ባይመጣስ?

    ለብዙ ሴቶች የወር አበባ ዑደት ፤ ስርአቱን የጠበቀ፤ በቀን መቁጠሪያ ሊተመን የሚችል ነው። ለአንዳንድ ሴቶች ግን ፤ የሚታይበትን ቀን ለምገመት አዳጋች ሲሆን ይታያል። አንድ ወር ላይ በሳምንታት ውስጥ ሲታይ ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከወራት በኋላ ይታያል። አንዳንዴማ ጨርሶ ጥፍት ይላል። ግን ለምን? ይህ መደበኛ ነውን? ይህንን ለማወቅ በመጀመሪያ ፤ ስለ የወር አበባ እንነጋገር። የወር አበባ በእርግጥ ምንድን ነው? የወር አበባ እርግዛና ባልተከሰተ ጊዜ የሚያጋጥም ፤ የማህፀን ግድግዳ መፍረስ ነው።  ይህም የሚፈጠረው ፤ የሴት ልጅ ሰውነት እርግዝና አለመኖሩን ሲረዳ ነው። ለዚህም ሰውነቷ የእርግዝና ጠባቂ የሆነው ፕሮጀስትሮን ሆርሞን መጠን ዝቅ ያደጋል። ይህንንም ተከትሎ ፤ ጽንስ ለመያዝ ተዘጋጅቶ የነበረው የማህጸን ግድግዳ ይፈርሳል። የፈረሰውም ግድግዳ በወር አበባ መልክ ይወጣል። በአኗኗር ላይ ቢመሰረትም በአለም ዙሪያ ሴቶች ከ12/13 አመት ጀምሮ የወር አበባ ያያሉ። ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከሆነ በኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ ያሉ ሴቶች ከ 13 - 14 ዓመት ጀምሮ የወር አበባ የሚያዩ ሲሆን ፤ በገጠሯ ኢትዮጵያ የሚኖሩት ደግሞ ከ14 -15 ዓመት እድሜ ጀምሮ ያያሉ። ሴት ልጅ መውለድ በምትችልባቸው አመታት ሁሉ ፤ ይህ ዑደት ይቀጥላል። ወደ አርባዎች መጨረሻ ገደማ ደግሞ ፤ የወር አበባ ማየት ታቆማለች። ይህም በተለምዶ ማረጥ ይባላል። ወርሀዊ ግዴታ ይባል እንጂ በየወሩ 30ን ጠብቆ የሚፈጠር አይደለም።ከሰው ሰው ቢለያይም ቢለያይም በአማካይ ከ 3 ሳምንት እስከ 5 ሳምንት ድረስ ባለው ጊዜ (21 እስከ35 ቀናት) ይታያል። አልፎ አልፎ እስከ 6 ሳምንት ሊቆይ ይችላል። አንዲት ሴት የወር አበባ ከ 3 እስከ 7 ቀን ድረስ ልታይ ትችላለች። እንደ አጠቃቀሟ ከ 2 እስከ 4 ፓድ በቀን ልትጠቀም ትችላለች። ይህም መደበኛ የወር አበባ ስርአት ነው! 🔍 ታድያ መቼ ያሳስባል? ከመደበኛው ከወጣ፤ አልያም የወር አበባ ኡደቱ ከተስተጓጎለ፤ ማስተዋል ያስፈልጋል። ለዚህም አንዲት ሴት ልጅ በ15 አመቷ የወር አበባ ካላየች፤ የወር አበባ ለአጭር ጊዜ (ከ 3 ቀን በታች) ወይም ለረጅም ጊዜ ( ከ 7 ቀን በላይ) ከቆየ ፤🌀 በየወሩ ጊዜውን/ቀመሩን ጠብቆ የሚመጣ ካልሆነ፤⏳ የሚታየው የወር አበባ መጠኑ ካነሰ አልያም ከበዛ (በቀን ከ 4 ፓድ በላይ ከተጠቀምሽ)  ፤🌊 የወር አበባ የማይታይባቸው ወራቶች ካሉ፤ 🚫 ማስተዋል ያስፈልጋል። የዚህን ጊዜ ሰውነትሽን ማዳመጥ ፤ ሀኪምሽን ማማከር ይኖርብሻል! 🌍 ደሞም ብቻሽን አይደለሽም!   ከ4 ሴቶች መካከል አንዷ  በሕይወት ዘመኗ ከመደበኛ የተለየ የወር አበባ ታያለች። ይህም ደግሞ በተለይ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በሚገኙ ወጣቶችና ወደ  ማረጥ እድሜ እየተቃረቡ ባሉ ሴቶች ላይ በይበልጥ ይስተዋላል።  ቢሆንም ፤ ይህን ከመደበኛ የተለወጠ የወር አበባ ስርዐት ማስተዋል ያስፈልጋል። አንዳንዴም ከውስጥ የተደበቀ በሽታን አመላካች ሊሆን ይችላል። እነኝህ ለውጦች ለተወሰነ ጊዜ የሚቆዩ ፤ የማያሳስቡ ሊሆኑ ይችላሉ። እነኝህ ለውጦች ለረዥም ጊዜ ከቆዩ ፤ እንዲሁም እነኝህን ለውጦች ተከትሎ እንደ ድካም፣ ማቅለሽለሽ ፣ ጆሮ ላይ መጮሕ ፣ የገረጣ ቆዳ አይነት የደም ማነስ ምልክቶች ከታዩ ፤ በይበልጥ አጽንኦት መስጠት ያስፈልጋል። ይህም ስር የሰደደ ችግር አመላካች ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ፡ ከጀርባ መሀንነት ፣ ደም ማነስና፣ የሆርሞን ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ከዚህም ባሻገር የኢንዶሜትርዮሲስ፣ የማህጸን አከባቢ ካንሰሮች እና የማህጸን እጢዎችም ፤ ለየት ያለ የወር አበባ ኡደት ሊያሳዩ ይችላሉ። የወር አበባ ከተለመደው ጊዜ ከቆየ እርግዝና አለመኖሩን ፤ ማረጋገጥ ያስፈልጋል። የወር አበባሽ ኡደት ስለ መውለድ መቻልሽን ብቻ አያመላክትም። የጤንነትሽም ምልክት ነው። ⚠️ ለምን ይከሰታል? ከመደበኛው የተለወጠ የወር አበባ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል። ከእነኝህም መሀል ✨ ውጥረትና የአኗኗር ዘይቤ  – እንቅልፍ ማጣት፣ ከባድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና፣ የተመጣጠነ ምግብ አለመመገብ ፤ የሰውነት ሆርሞኖችን ሚዛን ያዛባል። የወር አበባ ለውጥን ያመጣል።  ✨ ፖሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድሮም (PCOS) – ፒኮስ ለማህንነት ሊያጋልጥ የሚችል ፤ ብዙ ወጣት ሴቶችን የሚያጠቃ በሽታ ነው። ይህም በሽታ የሆርሞን መዛባት ስለሚያስከትል ፤ የወር አበባ ስርአትን ሊቀይር ይቻላል። ✨ የታይሮይድ በሽታ ችግር  — ከመጠን በላይ እየሰራ ያለ ፤ አልያም ስራው የቀነሰ የታይሮይድ እጢ ፤ የወር አበባን ሊያስተጓጉል ይችላል ። ✨ የክብደት መለዋወጥ  – መወፈርም ሆነ መክሳት ሆርሞኖች ላይ በሚያሳድረው ተጽእኖ ፤ የወር አበባን ሊለውጥ ይችላል። ለዚህም ድንገተኛ የሰውነት ክብደት ለውጥ ካለ ፤ የወር አበባ ከተለመደው ሊለውጥ ይቻላል። ✨ ብዙዎቹ የእርግዝና መከላከያዎችም ሆርሞኖች ከመሆናቸው የተነሳ ፤ የወር አበባን ዑደቶች ሊለውጡ ይችላሉ ። ✨ ሥር የሰደደ በሽታ  — የስኳር በሽታ ፣ የጉበት በሽታ ወይም ሌሎች የጤና ችግሮች ፤ የወር አበባን ስርአት ሊለውጡ ይችላሉ። ሆኖም ግን እነኝህ ለውጦች ብዙ ጊዜ አሳሳቢ አይደሉም። እዚህ ጋር የወር አበባ ጊዜ የሚታየው ህመምም መረሳት የለበትም። አንዲት ሴት የወር አበባ በምታይበት ወቅት ፤ የማህጸን ጡንቻ መኮማተሩን ተከትሎ ፤ የወር አበባ ህመም ይሰማታል። ይህ ህመም የታችኛውን የሆድ ክፍል ላይ የሚሰማ ሲሆን ፤ የህመሙ መጠን እንደየሰዉ ይለያያል። ሆኖም ግን ብዙ ጊዜ በህመም ማስታገሻ የሚመለስ ነው። ከሥራ ፣ ከትምህርት እንዲሁም ከማህበራዊ ቁርኝቶች ሊያስተጓጉል የሚችልብቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ። ሆኖም ግን ይህ ህመም እጅጉን ካየለ /ከጠነከረ፣ ከወር አበባ በኋላም ከቆየ ፤ በህመም ማስታገሻ ቁጥጥር ስር ካልዋለ ፤ በግንኙነት ጊዜም ካለ ፤ ሥራ፣ትምህርትን፣ ማህበራዊ ቁርኝትን በከፍተኛ ሁኔታ ካስተጓጎለ አብረውት ሌሎች የህመም ምልክቶቹ ካሉ ሊያሳስብ ይገባል። ህመሙ እነኝህን ለውጦች ካሳየ ፤ አቅራቢያሽ ወዳለ ጤና ተቋም ሄደው ፤ ምርመራ ማድረጉ መልካም ነው። 🌱 ምን ማድረግ ትችያለሽ የወር አበባ ለውጥ በጥንቃቄ እና በህክምና እርዳታ ሊስተካከል የሚችል ነው። ለዚህም 💡 የወር አበባ ዑደትሽን ተከታተይ  - የሞባይል መተግበሪያ፣ ካላንደሮችን፣ እንዲሁም ማስታወሻዎችን ያዥ።  💡 የአኗኗር ለውጥ አድርጊ – ለጤናሽ ቦታ ስጪ ፣ እንቅልፍ በአግባቡ ተኚ ፣ የተመጣጠነ ምግብ ተመገቢ፣ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርጊ ። 💡 የህክምና ምርመራ አድርጊ  – የወር አበባ ስርአቱ ዙሪያ አሳሳቢ ለውጥ ካየሽ ፤  ቅርብ ያለ የጤና ተቋም ሂጂ። ዶክተር አማክሪ።  💡 ውጥረት  –  አትጨነቂ፣ ውጥረት ቀንሺ። ውጥረት ለመቀነስ የሚጠቅሙ እንቅስቃሴዎችን (እንደ ዮጋ እና የአተነፋፈስ እንቅስቃሴዎች) አድርጊ። 💡 ለፒኮስ፣ ለታይሮይድ ህመም ምርመራ አድርጊ። መደበኛ የጤና ምርመራ ይኑርሽ።    🌸 የመጨረሻ ሃሳብ መደበኛ ያልሆነ የወር አበባ የቀን መቁጠሪያ ችግር ብቻ አይደለም። ሰውነትሽን በጥሞና አዳምጪ።  ሲለወጥ አትጠብቂ። የጤና ባለሙያ አማክሪ።

  • ብጉር እና መከላከያ መንገዶቹ

    ብጉር በአብዛኞቻችን የለመድነው ፤ በብዛት የሚታይ የቆዳ በሽታ ነው። በአለም ዙሪያ ከ 200 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ያጠቃል። ከ16 እስከ 24 እድሜ ክልል ውስጥ ካሉ 5 ወጣቶች መሀል ፤ ቢያንስ አንዱ ብጉር እንደሚኖርበት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ለዚህም በተለምዶ የጉርምስና ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። ሆኖም ግን ከጉርምስና አልፎ ፤ እስከ ጎልማሳነት እድሜ ሊታይ የሚችል የቆዳ ችግር ነው። በኢትዮጵያ አገር አቀፍ መረጃ ባይኖርም ፤ ብጉር የተለመደ የቆዳ ችግር ነው። በመቀሌ አይደር ሪፈራል ሆስፒታል የተደረገ ጥናት ፤ ከቆዳ ታካሚዎች ውስጥ 19.4 በመቶ የሚገመቱት ብጉር አለባቸው። ከፊሎቹም ብጉር ማየት የጀመሩት ከ 17 አመታቸው ወዲህ ነው ። ከእነኝህም ውስጥ ጥቂት የማይባሉት ላይ ፤ ለመዋቢያ ከሚጠቀሟቸው ቅባቶች ጋር ግንኙነት አለው ። ይህም ቅባቶቹ ካላቸው ንጥረ ነገር ጋር ተያያዥነት አለው። ለምሳሌ ፡ ስቴሮይድ ያላቸው ቅባቶች ብጉር ያመጣሉ። ቆዳን ያሳሳሉ። ታድያ ችግሩ የቆዳ ቢሆንም ፤ ጉዳቱ ግን በቆዳ ብቻ አይገደብም ። ውብት ላይ በሚኖረው እክልም ፤ የስነ ልቦና ችግር ሊያስከትል ይችላል። ከዚህም አልፎ የማህበራዊ ኑሮም ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል ። ታድያ ግን በህክምና እርዳታ እና በባህሪ/ልማድ ለውጥ መቆጣጠር እና ማጥፋት ይቻላል። ብጉር ምንድን ነው? ብጉር  ከፀጉር ስር(hair follicles) እና የቆዳ ቅባት አምራች ህዋሳት (sebaceous glands) ጋር ተይያዥነት አለው። የሚከሰትባቸውን መንገዶች በአራት መክፈል እንችላለን። የብጉር አከሳሰት ደረጃዎች፡ በግራ ያለው ምስል የቆዳ ቀዳዳ መደፈኑን ያመላክታል። መሀል ያለው ምስል የቆዳ ቅባት ክምችትን ያመላክታል። በስተቀኝ ያለው ምስል የተቆጣ ብጉርን ያሳያል። አንደኛ፡ ቆዳ ወዛም መሆን ጋር ይያዛል። ይህም የቆዳ ቅባት አምራች ህዋሳት በሆርሞን ቀስቃሽነት ፤ በብዛት የቆዳ ቅባትን (ሴበምን) ፤ በማምረታቸው ሊከሰት ይችላል። ይህም የሚከሰተው ፤ የበዛው ቅባት የቆዳን ቀዳዳን ስለሚደፍን ነው። ሁለተኛ፡ የቆዳ ያልተለመደ ለውጥን ተከትሎ ፤ የቆዳ ቀዳዳ ሲደፈን ሊከሰት ይችላል። ሶስተኛ፡ የቆዳ ቀዳዳዎች ውስጥ የሚገኘው ባክቴሪያ ( Cutibacterium acne ) ፤ የተደፈነውን ቀዳዳ ሲያጠቃ ፤ ብጉር ነጭ ጫፍ ይኖረዋል። አልያም መግል ያዣል። አንዳንዴም ጥቁር ሊሆን ይችላል። አራተኛ፡ የቆዳ ቀዳዳ መደፈንን ተከትሎ ፤ ያ አከባቢ ከተቆጣ ሊያብጥ እና ሊቀላ ይችላል። ታድያ ህክምናውም እነኝህን አራት መንገዶች ላይ የተመሰረተ ነው።  የአሜሪካ የቆዳ ሀኪሞች አካዳሚ የሚከተለውን ይመክራል። የቆዳ ቆዳዳዎች ውስጥ ሊኖር የሚችል ያልተለመደ እድገትን ለመግታት ሬቲኖይድስ (retinoids) መስጠት   ባክቴሪያውን ለመቃወም እንዲሁም የቆዳ መቆጣትን ለመቀነስ ፤ ቤንዞይል ፐርኦክሳይድን (Benzoyl peroxide) መስጠት እንዲሁም እንደ በሽታው መስፋፋት እና እንዳደረሰው የቆዳ ቁስለት/ጠባሳ ተጨማሪ ህክምናዎችን ይመከራል። ብጉርን ተከትሎ የአእምሮ ጤና ቀውስ የሚያጋጥማቸው ታካሚዎች ደግሞ ፤ ለብጉሩ ከሚያደርጉት ህክምና ባሻገር ፤ የሰነ ልቦና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። መንስኤዎች ለብጉር አጋላጭ መንስኤዎች መሀከል ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸው። ሆርሞኖች እና የሕይወት ደረጃ -   ከሆርሞኖች ውስጥ በተለይ አንድሮጅን ሆርሞኖች የቆዳን ወዝ ይጨምራሉ። ይህም በጉርምስና ጊዜ እና ወር አበባን ጋር ተያይዞ ብጉር እንዲበዛ ያደርጋል። ይህም የሚታይባቸው ታካሚዎች የሆርሞን መቃወሚያ ህክምና ( የ ፀረ-አንድሮጅን ሕክምና (spironolactone) ) ያስፈልጋቸዋል። አመጋገብ  ፡ አመጋገብ ብጉር ላይ ተጽእኖ እንዳለው የሚያሳዩ መረጃዎች ቢኖሩም ፤ አስረግጦ ለመናገር ገና ብዙ ጥናቶች ይቀራሉ። ሆኖም ግን ስኳር የበዛባቸው ምግቦች አብዝቶ መመገብ ብጉርን እንደሚያባባስ ጠቋሚ ጥናቶች አሉ። ለዚህም ብጉርን ለመቀነስ የምንመገበውን የስኳር መጠን መገደብ ይኖርብናል። ባክቴሪያዎች - ከብጉር ጋር ተያያዥነት ያላቸው ባክቴሪያዎች አሉ። ለዚህም የሚቀባ የባክቴሪያ መቃወሚያ በዚህ በኩል ጠቀሜታ አለው። ታድያ ግን እንዳይላመዱ መጠንቀቁ መልካም ነው። መዋቢያዎች ፡  የቆዳ ቀዳዳን የሚደፍኑ መዋቢያዎች፤ እንዲሁም በውስጣቸው ስቴሮይድ ያላቸው ክሬሞች ብጉርን ያመጣሉ። ውጥረትና እንቅልፍ፦  ውጥረትና እንቅልፍ ማጣት የቆዳ ቅባት ምርትን ከማዛባቱ አልፎ ፤ ቆዳ እንዲቆጣ ያደርጋል። ለዚህም ብጉር ያመጣል። ብጉር በዋነኝነት የሚያጠቃቸው አካላት፡ ብጉር እንደዘፈቀደ ማንኛውንም የሰውነት ክፍል አያጠቃም። በቅባት አምራች ህዋሳት ላይ ስለሚመሰረት ፤ እነኝህ ህዋሳት የተከማቹበት የሰውነት ክፍሎችን በይበልጥ ያጠቃል። ለዚህም በዋነኝነት የሚጠቁ የሰውነት ክፍሎች የሚከተሉት ናቸው። ፊት ፡ እጅጉን የተለመደ ሲሆን ፤ በአማካይ ከ 95 በመቶ በላይ የሚሆኑ ታማሚዎች ፊታቸው ላይ ብጉር ይኖራቸዋል። በዋነኝነትም ግንባር ፣ አፍንጫ ፣ አገጭ እና ጉንጭ ላይ ይታያል ። እነኝህ የፊታችን ክፍሎች ከፍተኛ የቅባት አምራች ህዋሳት ክምችት ስላላቸው ፤ እንዲሁም ለአቧራ እና ለተመሳሳይ ነገሮች ተጋላጭ ስለሆኑ ፤ በይበልጥ በብጉር ይጠቃሉ። የውበት መጠበቂያ ቅባቶች ፣ ሜካፖችም በብዛት ፊት ላይ ስለሚደረጉ ፤ የቆዳ ቀዳዳን ደፍነው ብጉር ሊያመጡ ይችላሉ። ስቴሮይድ ያላቸው ቅባቶች በበኩላቸው ፤ የቆዳ ቅባት ምርት እንዲጨምር በማድረጋቸው ፊት ላይ ብጉር እንዲበራከት ያደርጋሉ። ጀርባ፡ በግምት ወደ 60 ፐርሰንት የሚሆኑ ታካሚዎች ጀርባቸው ላይ ብጉር ይታይባቸዋል። በብዛት የላይኛው ጀርባ እና ትከሻ ላይ ያጋጥማል። እዚህ አከባቢ ያለው ቆዳ ወፍራም ከመሆኑ ባሻገር ፤ ብዙ ቅባት አምራች ህዋሳት ስላሉት ፤በብጉር አብዝቶ ይጠቃል። ደረት፡ ቢያንስ አንድ ሶስተኛ የሚጠጉ ታካሚዎች ደረታቸው ላይ ብጉር ይኖራቸዋል። ይህም በሙቀት እና ጠበቅ ያለ ልብስ በመልበስ ሊባባስ ይችላል። አንገት እና አገጭ ፡ ይህ በዋነኝነት ወጣት እና ጎልማሳ ሴቶች ላይ የሚታይ ሲሆን ፤ ከሆርሞን ጋር ግንኙነት አለው። ከዚህም ባሻገር የራስ ቅል ቆዳ ፣ የታችኛው ጀርባ ፣ መቀመጫ እና ከክርን በላይ ብጉር ሊታይ ይችላል። 📊 ብጉር የሚያጠቃበት መንገድ እንድ እድሜ እና ጾታ ሊለያይ ይቻላል! በጉርምስና እድሜ ላይ ብጉር በብዛት የሚታይ ሲሆን ፤ ስርጭቱም በይበልጥ ፊት ላይ ነው። ለዚህም ግንባር ፣አፍንጫ እና ጉንጭ ላይ ይታያል። ይህም ጉርምስናን ተከትሎ በሚመጣ ለውጥ ፤ ቆዳችን ወዛም ስለሚሆን ነው። ብዙ ጊዜ መግል ሊያዥ፣ ውሀ ሊቋጥር እንዲሁም ጥቁር ጫፍ ሊኖረው ይችላል። ከጉርምስና ባሻገር ፤ ከጭንቀት እና ከምግብ ጋር ሊባባስ ይችላል። በወጣትነት እና በጎልማሳ እድሜ ፤ ከወንዶች ይልቅ በብዛት በሴቶች ይታያል። ይህም በዋነኝነት የታችኛው የፊት ክፍል ላይ በተለይም አገጭ ፣ መንገጭላ እና አንገት ላይ ይስተዋላል። ይህም ከሆርምን መዋዠቅ ጋር ሲያያዝ ፤ አንዳንድ ሴቶች ላይ ከወር አበባ ቀድሞ ይስተዋላል። ብዙ ጊዜ እብጠት ብቻ ሊሆን አልያም ሊቆጣ ይችላል። ከአርባ አመት በኋላ ብጉር ብዙም የተለመደ አይደለም። ከታየ ከሆርሞን ጋር ተያይዥነት ያለቸው በሽታዎች ጋር ፤ አልያም ከመድሐኒት ጋር ግንኙነት አለው። ወንዶች ላይ ብዙ ጊዜ ጀርባ እና ደረት ላይ የሚታይ ሲሆን ፤ ጉዳቱም ትንሽ ያይላል። ብጉር መጣ ሄደት የሚልባችው ታካሚዎችም አሉ። ይህ ደግሞ ከ ወር አበባ፣ ከወቅቶች ጋር ፣ አልያም ህይወት ላይ ከሚያጋጥሙ ወጥረቶች ጋር ግንኙነት አለው።  🌿 በቤትዎ ምን ማድረግ ይችላሉ? ለብጉር ተመራጭ ህክምና በሀኪምዎ የሚታዘዙ እንደ ሬቲኖይድና ቤንዞይል ፐሮክሳይድ ያሉ መድኃኒቶች ናቸው። ሆኖም ግን በቤትዎ እነኝህን በማድረግ ቡግርን መቀነስ እንዲሁም መከላከል ይችላሉ። 1.    መደበኛ እንክብካቤ ለቆዳዎያድርጉ።  ፊትዎን በቀን ሁለት ጊዜ  ለብ ባለ ውሀ ይታጠቡ። አብዝቶ ቆዳ ማሸት ወይም ደጋግሞ መታጠብ ቆዳን ይጎዳል። ለቆዳ ድርቀት ይዳርጋል። ለዚህ አብዝተው አይታጠቡ። መዓዛ በሌለው ሳሙና ይታጠቡ።   ጠንካራ ማሻዎችን፣ አልኮል ያላችው መታጠቢያዎች/ቅባቶችን አይጠቀሙ። መቆጣትን ሊያባብሱ ይችላሉ።  የሚስማማዎትን ግብአቶች ለይተው ይወቁ። 2.    ማር 🍯 ንጽሁ ማር ጀርሞችን የመከላከል እና መቆጣትን የመቀነስ ባህሪ አለው። ለዚህም በየሳምንቱ ለተወሰኑ ቀናት ከ10 እስከ 15 ደቂቃ የማር ስክረብ ያድርጉ። ይህ በተለይ ለተቆጡ መጠነኛ ቡግሮች ይጠቅማል። 3.     ግሪን ቲ (አረንጓዴ ሻይ) ግሪን ቲ በውስጡ  ፖሊፌኖል (EGCG)  ይዟል። ይህም ውህድ የቆዳን ቅባት ምርትን ከመገደቡም ባሻገር ፤ የቆዳ መቆጣትን  ይቀንሳል።  ለዚህም አረንጓዴ ሻይ አፍልተው፤ አቀዝቅዘው ፤ ቆዳ ላይ በመቀባት መጠቀም ይችላሉ። አልያም ከግሪን ቲ የሚሰሩ የቆዳ ቅባቶችን/ግብአቶችን መጠቀም ይችላሉ። 4.    ሬት🌱 ሬት ለቆዳ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ  አለው። ቆዳን ያለሰልሳል ፤ ባክቴሪያን ይቃወማል። ብጉርን ይቀንሳል። ለዚህም ሬት ይቀቡ። ታድያ ግን አልኮል ያለውን የሬት ምርት አይጠቀሙ። ንጽህ ሬት ይጠቀሙ። ይህም የቆዳን መቆጣት ይቀንሳል። በተለይ ሬቲኖይድ መድሀኒት ከመጀመርዎ በፊት መጠቀሙ ይመከራል። 5.    የኑሮ ዘይቤዎን ያስተካክሉ።  ከፍተኛ የስኳር መጠን ያላቸው ምግቦች አይመገቡ። ጣፋጭ መጠጦችና ምግቦችን ይቀንሱ። አዝእርቶችን፣ ፍራፍሬዎችን እና አትክልቶችን ይመገቡ። አይጨነቁ። ህይወትዎ ውስጥ ያለ ውጥረትን ይቀንሱ። የሰውነትዎን ንጽህና ይጠብቁ። እንዳላብዎ ወዲያውኑ ይታጠቡ። ሜካፕ አብዝተው አይጠቀሙ። በተለይ ጭምብል፣ ሔልመት እና ኮፍያ የሚጠቀሙ ከሆነ። በውስጣቸው ስቴሮይድ ያላቸውን የቆዳ ቅባቶች አይጠቀሙ። መደበኛ የእንቅልፍ ሰአት ይኑርዎ። ቢያንስ ለ ስድስት ሰአት በቀን ይተኙ። መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ። 6.    ብጉሩን በእጅዎ አይንኩት። አያፍርጡት! ይተዉት! 7.    ህመም ያለው እና ያዠ ብጉር ካለ ፤ በረዶ በጨርቅ ጠቅልለው ያድርጉበት። ይህም መቆጣትን ይቀንሳል። 8.   ከዚህም ባሻገር ቅባት የሌለው ፤ ኮሞዶጅን የሌለው  የጸሀይ ጨረር መከላከያ የቆዳ ክሬም (non-comedogenic sun screen ) ይጠቀሙ። የብጉር ጠባሳዎች ቶሎ እንዲጠፉ ያደርጋል።   እነኝህን ተግባራዊ ለውጦች በማድረግ፤ የቆዳዎን ጤና ይጠብቁ!

  • ትምባሆና የኤሌክትሪክ ሲጋራ ያላቸው የጤና እክል

    አዙሪቱ በዝምታ ይጀምራል! አንዱ አውቶብስ እየጠበቀ ሲጋራ ይለኩሳል። ከዩንቨርስቲ ዶርም ጀርባ ሌላኛው ፤ መልካም መአዛ ያለው ቬፕ ይስባል። ለተመልካች አንደኛው እንደሚቃጠል ቅጠል ሲሸት ፤ ሌላኛው የከረሜላ መአዛ አለው። አንደኛው ብቻ አጫሽ ይመስላል። ታድያ ግን ሁለቱም የሰውነት ኡደታቸው እየተለወጠ ፤ ለበሽታ፣ ለሱስና እንዲሁም ለካንሰር ያጋልጣሉ። ትምባሆ በኢትዮጵያ ብዙ ኢትዮጵያውያን ትምባሆ አያጨሱም። ሆኖም ግን የአጫሽ ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። አሁን ባለው መረጃ ትንባሆ በየዓመቱ ከ17,000 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት እየቀጠፈ  ነው ። ብሔራዊ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከአዋቂዎች መካከል 5 በመቶ የሚሆኑት  ትንባሆ የሚያጨሱ ሲሆን ፤ ከእነኝህ ውስጥ አብዛኞቹ ወንዶች ናቸው። ይህ ቁጥር ትንሽ ሊመስል ይችላል።  ነገር ግን 120 ሚሊየን በላይ ሰዎች ባሉባት በሚኖሩባት ሀገር ፤ የአጫሾች ቁጥር በሚሊየኖች ይገባል። እነሱም ሲያጨሱ ፤ በ አስር ሚሊየኖች ለሲጋራ ጭስ ይጋለጣሉ። ሁለተኛ ዙር አጫሽ ይሆናሉ። ምናልባት ይህ የአንድ ጊዜ አጋጣሚ ከሆነ ላያሳስብ ይችላል። ከተደጋገመ ግን ሁለተኛ ዙር አጫሾች ፤ ከአጫሾች ይበልጥ ለብዙ የጤና እክል ይጋለጣሉ። በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ 1.3 ሚሊዮን የማያጨሱ ሰዎች ፤ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች በማጨሳቸው ለሞት ይዳረጋሉ። እዚህ ላይ አዲሶችን የኤሌክትሪክ ሲጋራዎች ወይሞ ቬፖችን እንጨምር... በውስጣቸው በዋነኝነት ኒኮቲንን ከተለያዩ ውህዶች ጋር ያያዙ ፤ በባትሪ የሚሰሩ ዘመናዊ ሲጋራዎች ናቸው። ታድያ በኢትዮጵያ የእነኝህ ሲጋራዎች አጫሽ መጠን የሚጠቁም መረጃ የለም። ሆኖም ግን በተማሪዎች እና በወጣቶች ዘንድ እንደ ፋሽን እየተለመዱ እየመጡ ነው። "ሲጋራ አይደለም። " አልያም ደግሞ " የሲጋራ መርዛማ ኬሚካል የወጣላቸውና የተጣሩ ስለሆኑ ፤ እንደ ሲጋራ አይጎዱም። " በሚል ማሳመኛ እየተሸጡ ይገኛሉ። በማህበራዊ ድህረ ገጾችም ከመሸጥ አልፈው ፤ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንደጌጥ አንጠልጥለዋቸው የታዩበትም ጊዜ አለ። ጣእማቸው ሳቢ ስለሆነ ፤ ብዙዎች እንደሲጋራ ላያስቧቸው ይችላሉ። እውነታው ግን ጎጂነታቸው ከሲጋራ ጋር ተቀራራቢ ነው። መርዛማ ኬሚካሎችን የቀነሱ ቢሆንም ፤ ለህክምና አዲስ የሆኑ ፤ ለማከም የሚያስቸግሩ ፤ የጤና እክሎች እያመጡ መሆኑን ጥናቶች ያመላክታሉ።   የትንባሆ ጭስም ይሁን ቬፕ ፤ ውስጣቸው ያለው ኬሚካል ለሰውነት ጎጂ ነው። ሲጋራ በውስጡ ከ7,000 የሚበልጡ ኬሚካሎችን ሲኖሩት  ፤ ከዚህ ውስጥ  ቢያንስ ሰባዎቹ ካንሰር አምጪ ናቸው ። ለምሳሌ ፡ ፒ ኤ ኤች(PAH) ፣ ናይትሮሳሚን (Nitrosamine) ፣ እና አሮማቲክ አማይን (Aromatic amine) የሚባሉት ውህዶች ዘረመላችን ላይ ስለሚጣበቁ ፤ ካንሰርን ያመጣሉ። እርግጥ ሲጋራ ውስጥ የሚገኙ በጣም መርዛማ ንጥረ ነገሮች ቬፕ ውስጥ ባይኖሩትም ፤ በምትኩ አዳዲስ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ይገኙበታል። ለምሳሌ እንደ ክሮሚየም ፣ ኒኬል እና ሊድ አይነት ከባድ ብረት አስተኔዎች (Heavy Metals) እንዲሁም ኦርጋኒክ ውህዶች (volatile organic compounds) በውስጡ አሉ። ከዚህም ባሻገር የኢሌክቶሮኒክ ሲጋራዎች ፤ በከፍተኛ ሙቀት የሲጋራውን ፈሳሽ ሲያገሉ ፤ ፎርማልዲሃይድ (በተለምዶ ፎርማሊን) ይፈጠራል። ይህም ከጭሱ ጋር አብሮ ወደ ሳንባ ይገባል። ከዚህ ባሻገር ሁለቱም ላይ ኒኮቲን አለ። እንደውም በኒኮቲን መጠን ቬፕ ሊበልጥ ይችላል። ኒኮቲን በበኩሉ የነርቭ ስርአትን ፣ አቀማመጥን ፤ እንዲሁም አሰራርን በቋሚነት ይለውጣል። ለሱስም ያጋልጣል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት በጉርምስና ወቅት ለኒኮቲን መጋለጥ ፤ የአንጎልን እድገት በቋሚነት ሊለውጥ ይችላል። ለሌሎች ሱሶች በይበልጥ የመጋለጥ እድልንም ይጨምራል ።ለዚህም በተለይ የኤሌክትሪክ ሲጋራ ለወጣቶች በጣም አደገኛ ነው ። የሲጋራ ጠንቅ በየሰውነት ክፍል ሲጋራ የማይነካው የሰውነት ክፍል የለም። ሁሉም የሰውነታችን ህዋስ ፣ ከጸጉር ጀምሮ ማህጸን ውስጥ እስካለ ጽንስ በሲጋራ ይነካል። ለዚህም አንድ በአንድ እንይ፡ የመተንፈሻ አካሎቻችን ፡ ሲጋራ ሲጨስ በመጀመሪያ የሚጋለጡት የመተንፈሻ አካሎች ናቸው። ለዚህም ከፍተኛ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ሳንባ የቻለውን ያህል አጣርቶ ወደ ደም ቢያስገባም ፤ እንደ ጥላሸት ተጣብቀው የሚቆዩት ውህዶች አሉ። በዚህም የተነሳ ሲጋራ ማጨስ ለተለያዩ የሳንባ ህመሞች ያጋልጣል።  በዓለም ዙሪያ ከሚያጋጥሙ 10 የሳንባ ካንሰር ህመሞች ፤ በትንሹ ስምንቱ ከሲጋራ ጋር የተያያዙ ናቸው። በተጨማሪም ረዥም ጊዜ ለሚቆዩ የሳንባ መቆጣት ህመሞች (ለምሳሌ ኢምፋይሴማ እና ሲኦፒዲ) ያጋልጣል። ለ ትንፋሽ ቧንቧ ኢንፌክሽን ተጋላጭነትንም ይጨምራል። ቬፕ ተመሳሳይ ጉዳት ከማስከተሉ አልፎ ፤ ለየት ያለ የሳንባ ህመምን ያመጣል። እነኝህ በሽታዎች ቬፕን ተከትለው የሚመጡ የሳንባ ጥቃቶች (EVALI/ E-cigarrete or Vaping Product Associated Lung Injury) ተብለው ይጠራሉ። ከዚህም ውስጥ ጣእሞኡን ለማሻሻል ተብሎ የሚከተተው ዳይ አሴታይል (diacetyl) የሚባለውን ውህድ ተክትሎ የሚመጣው ሳንባን እንደፈንዲሻ የሚያስመስለው (Pop corn LUng) ህመም ተጠቃሽ ነው። ከዚህም ባሻገር ቬፕም ለሳንባ ካንሰር ያጋልጣል። የልብ እና የደም ስሮቻችን፡ ማጨስ ልብ ድካም የማጋጠም እድልን በ እጥፍ ይጨምራል ። የስትሮክ አጋጣሚን በ 50 በመቶ ይጨምራል።  ኒኮቲን የልብ ምትና የደም ግፊት እንዲጨምር ሲያደርግ ፤ ጭሱ ውስጥ የሚገኝው ካርቦን ሞኖ ኦክሳይድ ደግሞ ሰውነት ኦክስጅን እንዳይጠቀም ያሰናክላል። ሲጋራ ሆነ ቬፕ የደምስር ግድግዳዎችን ይጎዳሉ። ደም መርጋት እንዲያጋጥም ያደርጋሉ። ለደም ስር ህመሞችም ዋነኛ ተጠቃሽ መንስኤ ናቸው። የምግብ መፍጫ ስርዓት፡ በጭሱ ውስጥ ያሉ ኬሚካሎች ጉሮሮን፣ ጨጓራን፣ አንጀትን፣ ጉበትንና፣ ቆሽትን አብዝተው ይጎዳሉ። ጨጓራ ህመምም ያባብሳሉ። የአሲድ ምርት ጨምረው ፤ ጉሮሮን ያስቆጣሉ። በረዥም ጊዜም ለጉሮሮ፣ ለጨጓራ ፣ እንዲሁም ለአንጀት ካንሰር ያጋልጣሉ። ኩላሊት እና የመሽኛ አካላት ፡  ከጭሱ ውስጥ ካንሰር አምጪ የሆኑት አሮማቲክ አማይን ውህዶች ኩላሊት አጣርቶ ወደ ፊኛ ስለሚልካቸው ፤ እስኪሸና ፊኛው ውስጥ ይከማቻሉ። ለዚህም ማጨስ ለፊኛ ካንሰር ያጋልጣል። በሲጋራ አጫሾች ዘንድ የፊኛ ካንስር በሶስት እጥፍ ከፍ ያለ ነው። እንዲሁም በኩላሊት ካንሰር የመያዝ እድልም ይጨምራል።   በእርግዝና ወቅት ፡ ማጨስ የፅንስ መጨንገፍ ፣ ጽንስ ማህጸን ውስጥ እንዲሞት፣ ምጥ ያለጊዜ እንዲመጣ፣ እንዲሁም ክብደቱ ያነስ ልጅ እንዲወለድ ያደርጋል። ከዚህም ባሻገር ሲጋራ ውስጥ ያለው ኒኮቲን ፣ የጽንስን የአእምሮ እድገት ያስተጓጉላል። ለዚህም የሚወለደው ልጅ የአእምሮ ዝግመት ሊያጋጥመው ወይም የማሰብ አቅሙ ሊዳከም ይችላል። እናትም በእርግዝና ጊዜ ታጨስ ከነበረ ፤ ከወሊድ በኋላ ልጅ በድንገት የመሞት እድሉ ያየለ ነው። የመራቢያ አካላት፡ ማጨስ የመራቢያ አካላት ካንሰር እንዲያጋጥም እድል ይከፍታል። የሚያጨሱ ሴቶች የማህጸን ጫፍ ካንሰር የማጋጠም እድላቸው ከፍተኛ ነው። ሲጋራ ማጨስ በሽታ የመከላከል አቅምን ያዳክማል።  አጫሽ ሰዎች ለሳንባ ኢንፌክሽኖች የተጋለጡ ከመሆናችውም ባሻገር ፤ የህክምና ውጤታማነትም እነሱ ላይ የቀነሰ ነው። ማጨስ ደም ስሮችን ስለሚያዳክም ፤ የደም ዝውውርን ይቀንሳል። በቂ ኦክስጅን እና ምግብ ለህዋሳት ስለማይደርስ ፤ ከቀዶ ጥገና በኋላ ቁስል ቶሎ አይጠግንም ። አጫሾች ከሳንባ ካንሰር ባሻገር  ቢያንስ ለ14 ካንሰር አይነቶች ተጋላጭነታቸው የጨመረ ነው ። አለማጨስ ይህንን ተጋላጭነት ይቀንሳል። የሚያጨሱ ከሆነ ማቆሚያ ጊዜው አሁን ነው። ቶሎ ማጨስ ካቆሙ ፤ ተጋላጭነትዎን ይቀንሳሉ። ሲጋራ ማጨስን ተከትለው የሚመጡ ካንሰሮች ውስጥ 14ቱ በዝርዝር አንዴ ማጨስ ካቆሙ በኋላ ፤ ሰውነት ወደ ነበረበት ተፈጥሮአዊ ደረጃ እስኪደርስ አመታት ይወስዳል። ለዚህም አንዴ ማጨስ ካቆሙ ፤ መጽናቱ ያስፈልጋል። ብዙዎች ማጨስ እንዳያቆሙ ፤ ካቆሙም በኋላ እንዲመለሱ የሚያደርገው የሲጋራ ሱስ ነው።   የሲጋራ ሱስ ሱስ የሚያስይዘው የትምባሆ ቅጠሉ ፤ አልያም ጭሱ ፤ አልያም የቬፕ እንፋሎት አይደለም። ሲጋራ እንዳጨሱ ኒኮትን በሰከንድ ነርቭዎት ጋር ይደርሳል። ደርሶም ነርቮችን ያነቃቃል። ሰውነት ደስ የሚል ስሜት እንዲሰማው ያደርጋል። ሰውነትም ይህንን የመነቃቃት ደረጃ እና ደስታ ይፈልጋል። እንደዚህ እንድንነቃቃ ይገፋፋል። ይህንንም ለማስቀጠል አንድ ሲጋራ ብቻ በቂ ነው! ከዛም አንድ ሲጋራ ብቻ ...። እያለ... እያለ... ሰውነት ይላመዳል። የተለመደ ስራውን ለመፈጸም ሲጋራ ይፈልጋል። ለዚህም ያለሲጋራ መስራት፣ መንቃት፣ መልካም መስተጋብር ያዳግታል። የቬፕማ ይብሳል!! ኒኮቲን አብዝቶ ስላለው ፤ ሱስ የመያዝ እድል ይጨምራል። ለዛ ይሆን እንዴ ወጣቶች በቬፕ ተጠምደው የሚታዩት ? ከሱሱ ግን ነፃ መውጣት ይቻላል! ሲጋራ ማጨስ ማቆም ከባህሪ ጥንካሬ ጋር ብቻ አይገናኝም! የአጫሾች የአእምሮ አሰራር ተለውጧል። ሰውነታቸው ለመደበኛ ስራው ሲጋራ ከመፈለጉም በላይ ፤ የአእምሮ ቅርጹ ፣ ስርአቱ ፣ አቀማመጡ ተለውጧል። ለዚህም  "አታጭስ!" የሚለው ቃል ብቻ ለውጥ ላያመጣ ይችላል። ሱስ እንዲያቆሙ ለማድረግ የባህሪ እገዛ ፤ እንዲሁም የመድሐኒት ድጋፍ ያስፈልጋል ። እነኝህ አንድ ላይ ሲደመሩ ማጨስ የማቆም እድልን በእጥፍ ይጨምራሉ።  የኢትዮጵያስ አቋም ምን ይመስላል? አገራችን ኢትዮጵያ ያላት የአጫሽ መጠን አነስተኛ ቢሆንም ፤ የአጫሽ ቁጥርን ለመቀነስ እየሰራች ትገኛለች። የአፈጻጸም ክፍተት ቢኖርም ፤ የትንባሆ ማስታወቂያ ፣ በሕዝብ ፊት ማጨስና ፣ ሺሻ ማጨስ በህግ እገዳ ተጥሎባቸዋል። እንዲሁም የሲጃራ ፍጆታን ለመግታት ታስቦ ፤ ከፍተኛ የትምባሆ ግብር (በፈረንጆች 2020) ተጥሏል።  አዲሱ የ ብሔራዊ የትምባሆ ቁጥጥር ስትራቴጂክ ፕላን (2023–2031)  ሲጋራ ማጨስን ለማስቆም እቅድ አድርጓል። ይህም የሲጋራ ማጨስ ማቆም አገልግሎትን ለማስፋፋት ፤ እንደ ደም ግፊት ልኬት በየጤና ተቋማቱ አገልግሎቱን ለማዳረስ ታቅዷል። ታድያ ግን በቂ በጀት ያለመኖርና ፣ የህግ አፈጻጸም እክሎች ይህንን እቅድ እያሰናከሉት ይገኛሉ። ከሱሱም ለመውጣት የሚያግዙ መድሀኒቶችን አቅራቦት ችግርም አለ። የኤሌክትሮኒክ ሲጋራም በአሁኑ ጊዜ በሰፊው ቁጥጥር እየተደረገበት አይደለም። እድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ ልጆች ማጨስ የቻሉበት ክፍተት ተፈጥሯል። ይህ ደግሞ አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልገዋል።   መደምደሚያ ሀሳብ ሲጋራ የሚገድለው በካንሰር ብቻ አይደለም። በልብ በሽታ፣ በደም ስር ህመም ፣ በስትሮክ፣ በሳንባ ምች፣ በኢንፍልዌንዛ፣ በስኳር በሽታ፣ በደም ግፊት፣ ወ.ዘ.ተ... የእኛ የማጨስ ውሳኔ ፤ ከእኛ አልፎ በዙሪያችን ያሉትን ይጎዳል። ስለዚህ ቆም ብለን እናስተውል! እርስዎ ያገኙትን ግንዛቤ ለሌላ ያጋሩ። የአንድ ሰው ህይወት ያድኑ። በቀጣይ ትምህርታዊ ጽሁፎቻችን ውስጥ ሲጋራ ማጨስን ለማቆም ፤ ከሱሱ ለመገላገል የሚመከሩ ሳይንሳዊ መንገዶች ዙሪያ ፤ ስለማናነሳ ይከተሉን።

  • የስኳር በሽታ አስከፊ ዳፋ የሆነው ዲኬኤ

    ከሞትን አፋፍ የተመለሰው ልጅ ታሪክ ባለታሪኩ የ 6 አመቱ አብርሀም ፤ የዛሬ ስደስት ወር ገደማ ሰውነቱ አለልክ መክሳት ይጀምራል። ውሀም አለልክ ይጠጣል። ሽንትም አብዝቶ ይሸናል። ቤተሰቦቹም ብዙም አሳሳቢ ጉዳይ አድርገው አልወሰዱትም ነበር። ታድያ ከ 3 ሳምንት በፊት ፤ ያቅለሸልሸው እና ሆዱን ይቆርጠው ጀመር። ይህን ጊዜ ወስፋት የመሰላቸው የቤተሰቡ አባሎች ፤ ከቅርብ ፋርማሲ ገዝተው የ ትላትል መድሀኒት ይሰጡታል። መድሀኒቱን ቢጨርስም ፤ ምልክቶቹ ፈጽሞ አልተሻሻሉም ነበር። ምንም ለውጥ ባያሳይም ፤ ቤተሰብም ይሻለዋል ብሎ ቤት ውስጥ ይከታተሉታል። ይልቁኑ በሰው ካዩት ምልክት ተነስተው ፤ የሽንት ኢንፌክሽን ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ። ቢገምቱም ውሀ እየጠጣ ስለሆነ ፤ እንደሚሻለው በማሰብ ፤ ፈጽሞ ሀኪም ቤት ይዘውት አልሄዱም ነበር። የትላትል መድሀኒትም ስለወሰደ ፤ የሆድ ቁርጠቱም እንደሚጠፋ ፤ የምግብ ፍላጎቱም እንደሚስተካከል አምነው ይጠብቁት ጀመር። በዚህ ሁኔታ ሁለት ሳምንታት ተቆጠሩ። ግን ምንም ለውጥ የለም! በተረዱት መንገድ እያስታመሙት ያሉት ቤተሰቦች ፤ ሀሳብ ይገባቸው ጀመረ። ይብሱኑ ምልክቶቹ ተባባሱ። ያስታውከው ጀመር። ሽንቱን ፈጽሞ መቆጣጠር ተሳነው። ነገሮች ላይ ግራ መጋባት አመጣ። ቃላቶች መንተባተብ ጀመረ። ድካሙ ስለባሰበት ፤ ከእኩዮቹ ጋር መጫወት ትቶ ፤ ከቤት መተኛት አበዛ። ቀንሶ የነበረው የምግብ ፍላጎቱም ፤ ፈጽሞ ጠፋ። ምግብ በአይኔ አታሳልፉ አለ። ህመሙ መባባስ ከጀመረ ሶስት ሳምንት አከባቢ ፤ ቤተሰቦቹ የማይልፍ ህመም ባይሆን ብለው ፈሩ። ለዚህም የተጨነቁ ወላጆቹ ሆስፒታል ይዘውት ሄዱ። ሀኪም ቤት የተደረገውም ምርመራ ፤ የስኳር በሽታ እንዳለበት አመላከተ። የደም ላይ የስኳር መጠኑ 600 mg/dl ፣ የHBA1C መጠን 12. 1 እና የሽንት የኬቶን ምርመራ ፖዘቲቭ ሆኖ ተገኘ። ይህም ቁጥጥር ላይ ያልዋለ የስኳር በሽታ ከሚያመጣቸው አስጊ ህመሞች በመሆኑ ፤ በድንገተኛ ህክምና ተጀመረለት። አርፍዶ ቢሆንም ህመሙ እጅጉን ሳይባባስ ህክምና በማድረጉ ፤ ከህመሙ ሊያገግም ችሏል። ታድይ ይህ አንድ ፍሬ ልጅ ፤ ህይወቱ አደጋ ላይ እንደነበረች ቢያውቁ ቤተሰቦቹ እንዲህ ችላ ይሉ ነበርን? ከዚህ በኋላ ቀናት እንኳን አርፍዶ ቢሆን ፤ ኮማ ውስጥ ሊገባ አልያም ለሞት ሊዳረግ እንደሚችል ቢያውቁስ? ይህ ህመም ዲያቤቲክ ኬቶ አሲዶሲስ (ዲኬኤ)ሲባል ፤ በይበልጥ የታይፕ አንድ ስኳር ህመምተኞችን የሚያጠቃ ህመም ነው። እንደብሩክ ላሉ ታማሚዎችም የመጀመሪያ የስኳር በሽታ ጠቋሚ ምልክት ሊሆን ይችላል። ህመሙ ሲጀምር ቀላል ቢመስልም ፤ እጅጉን አሳሳቢ እና እስከሞት የሚያደርስ ነው። ዛሬ የምናወራው ስለ ዲኬኤ ነው። ስለ ዲኬኤ ከማውራታችን በፊት ግን ፤ ስለ ስኳር በሽታ ጥቂት ማለት ይኖርብናል። የስኳር በሽታ ምንድን ነው? የስኳር በሽታ የኢንሱሊን መዛባትን ተከትሎ የሚያጋጥም ነው። ሰውነት እንዳሉት የኢንሱሊን አምራች ህዋሳት መጠን ፤ እንዲሁም በህመሙ ባህሪ ተመስርቶ በሁለት ይከፈላል። ታይፕ አንድ የስኳርበሽታ ብዙ ጊዜ ከህጻንነት ጀምሮ የሚያጋጥም ሲሆን ፤ ታይፕ ሁለት የስኳር በሽታ ከአኗኗር ጋር ተያይዞ ወድ ኋላ እድሜ የሚመጣ ነው። ታይፕ አንድ የስኳር ኢንሱሊን አምራች ህዋሳት ሲመናመኑ ፤ ወይም ፈጽሞ ሲጠፉ የሚከሰት ነው። እራስን በሚያጠቁ የሰውነት መከላከያ ህዋሳት ፤ እንዲሁም በአንዳንድ ህመሞች ምክንያት ሊከሰት ይችላል። የስኳር በሽታ ህክምናም የተዛባውን ኢንሱሊን ማገዝ፤ እንዲሁም ደም ላይ ያለውን የስኳር መጠን መቆጣጠር ላይ ያተኮረ ነው። 🔍 ዲያቤቲክ ኬቶአሲዶሲስ (ዲኬአ) ምንድን ነው? ዲያቤቲክ ኬቶ አሲዶሲስ የሚከሰተው የስኳር በሽታ ክትትል ሲዳከም ነው። ብዙውን ጊዜ የስኳር መድሀኒት በአግባቡ ባለመውሰድ ፤ ስኳር የበዛባቸው ምግቦችን በመመገብ ፤ እንዲሁም በኢንፌክሽን ይመጣል። ይህንን ተከትሎ ፤ ሰውነት በቂ ኢንሱሊን ስለማይኖረው ፤ የደም ስኳር (ግሉኮስ) መጠን መገደብ ይሳነዋል። ስኳር ያለልክ ደም ላይ ቢበዛም ፤ ያለ ኢንሱሊን እርዳታ ሰውነት ሊጠቀመው አይችልም። ለዚህም ሰውነት ስኳር ይራባል። ያጋጠመውን የስኳር እጥረት ለማካካስ ፤ ሰውነት ስብን ተክቶ መጠቀም ይጀምራል። ይህም ህመም የሚመጣው በዚህ የተነሳ ነው። ስብን ሲጠቀም የሚያመርታቸው አካላት ደም ላይ ተክማቸተው ፤ ደምን አሲዳማ ያደርጋሉ። የሰውነትን ኡደት ያበላሻሉ። የደም ማእድን መጠንንም (በተለይ የፓታሺየም) ያዛባሉ። ቶሎ ካልታከመ እስከ ኮማ እና ሞት ሊያደርስ ይችላል። ለዚህም ይህም ህመሙን አደገኛ ያደርገዋል !! በአፋጣኝም መታከም አለበት። በህክምናው ዲኬኤ የምንለው የደም የስኳር መጠን ከ 250 mg/dl በላይ ሲሆን የሽንት ምርመራ ላይ ኬቶን ከ +2 በላይ ሲያሳይ ዲኬኤ አለ እንላለን። ኢትዮጵያ ውስጥ በቀላሉ ባይገኙም ፤ የደም የ ካርቦኔት መጠን እንዲሁም የ ፔኤች መጠንም ይህንን ህመም ለመለየት ያስችላሉ። 📊 የ የዲኬኤ ስርጭት በኢትዮጵያ የስኳር በሽታ ስርጭት በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል። የስኳር በሽታ አሳሳቢ ህመሞች ውስጥ የሆነው የዲኬኤም እንዲሁ። ሀገር አቀፍ መረጃዎች የተሟሉ ባይሆኑም ፤ ኢትዮጵያ ላይ ያለው የ ዲኬኤ ስርጭት መጠን እጅጉን አሳሳቢ ነው። በ 2025 የተደረገ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያመላክተው ከሆነ ፤ ኢትዮጵያ ባሉ የስኳር ህመምተኞች ዘንድ ያለው የዲኬኤ መጠን 46 ፐርሰንት ይደርሳል። አንዳንድ ጥናቶች ይህንን መጠን ወደ 30 ፐርሰንት ያወርዱታል። በአዲስ አበባ ከ 5 አመት በፊት የተደረገ ጥናት በበኩሉ ፤ ከ 3 የስኳር ታማሚዎች አንዱ ዲኬኤ እንደሚያጋጥማቸው ይጠቁማል። ይህ አስደንጋጭ እና አሳሳቢ ቁጥር ነው። በሰለጠነው አለም የዚህ ህመም መጠን ከ1 ፐርሰንት ባያልፍም ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ብዙ ህመምተኞች በዲኬኤ እየተጠቁ ይገኛሉ። የጤና አገልግሎት ውስን መሆንና ስለስኳር በሽታ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን ለዚህ ተጠያቂ ናቸው። ይህም የግንዛቤ ጉድለት ብዙ የስኳር ታማሚዎች ምርመራ እንዳያደርጉ ፤ ህክምና እንዳይከታተሉ ያደርጋል። በሽታው እስኪብስ ድረስም የሚቃወሙ ጥቂቶች አይደሉም። የህመም ምልክት እስኪታይ ያልታመመ የማይመስላቸው ቤተሰቦችም ፤ መድሀኒት ለመውሰድ ያከላክላሉ። ለዚህም እንደ ዲኬኤ ህይወትን አደጋ የሚጥሉ ህመሞች እስኪያጋጥሙ ፤ ህክምናን ችላ ይላሉ። ይህ ትግል እና ክርክር ከሞት ጋር እንደሆነ ቢያውቁ ግን ፤ አብዛኞቹ ፈጽመው እንዲህ አያደርጉም። ስኳር ህመም ያልበት ልጃቸው ፤ የዲኬኤን ምልክቶች አሳይቶ እንደ አብርሀም ለሳምንታት የሚያቆዩ ጥቂቶች አይደሉም። አብዛኞቹ የልጃቸው ህይወት አደጋ ላይ እንደነበር የሚረዱት ፤ በድንገተኛ ሲታከም ነው። ይህ ቸልተኝነት ዳፋው እጅጉን ከባድ ነው። 🔥 ምልክቶቹን ለይቶ ማወቅ ግድ ያላል። የህመሙን ምልክቶች ማወቅ አስፈላጊ ነው። ያስተውሉ የመጀመሪያው መከላከያ የተሟላ ግንዛቤ ነው ። የዲኬኤ የተለመዱ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው። የማይረካ የውሀ ጥማት አብዝቶ/ ቶሎ ቶሎ መሽናት የማቅለሽለሽ ስሜትና ፣ ማስመለስ የሆድ ሕመም   ፈጣን እና ጥልቅ አተነፋፈስ ድካም ግራ በመጋባት ወይም እንቅልፍ ማብዛት ትንፋሽ ደስ የሚል የፍራፍሬ ሽታ መኖር እነኝህን ምልክቶች ካዩ ፤ ፈጽሞ አይዘናጉ! ያስተውሉ የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ቀደም ብሎ ማወቅ ሕይወት ያድናል። አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ያስፈልገዋል። ወደ ቅርብ የጤና ተቋም ይዘው ይሂዱ። 🛡️ ፈጽሞ መከላከል የሚቻል ህመም ነው! እንዴት? ይህ ህመም በቁጥጥር ስር ባልዋለ የስኳር አማካኝነት የሚመጣ ህመም በመሆኑ ፤ የስኳር በሽተኞች የኢንሱሊን እና በአፍ የሚወሰዱ የስኳር በሽታ መድሐኒቶችን ሳያቁርጡ በስርአት መውሰድ ይኖርባቸዋል። በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠንን መከታተል ያስፈልጋል። ውሀ መጠጣት። አልኮል መጠጣት እና ሲጋራ ማጨስ አይመከርም። ማንኛውንም የኢንፌክሽን ህመሞችን ጊዜ እንዳይሰጡ። ወዲያውኑ በመታከም ይቆጣጠሩ። ካልታከሙ ለዲኬኤ ያጋልጣሉ። ትክክለኛና የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖርዎ ፤ በባለሙያ እና በጤና ተቋማት የሚለቀቁ የህክምና መረጃዎችን ይከታተሉ። 🚨 የበሽታው ምልክቶች ካዩ ምን ማድረግ አለብዎት? ምልክቶቹን በራስዎ ወይም በሌላ ሰው ላይ ካስተዋሉ አፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ጥረት ያድርጉ።  በአቅራቢያ ወዳለ የጤና ተቋም ይሂዱ ። ራስዎን ለማከም ወይም ሕክምናውን ለማዘግየት ፈጽሞ አይሞክሩ።   አይጨነቁ። ረጋ ይበሉ። ሆኖም ግን አፋጣኝ እርምጃ ይውሰዱ። 📣እናስተውል የስኳር ህመምን ችላ በማለት ፤ በዚህ ህመም የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ትንሽ አይደለም። ሆኖም ማብቂያው ጊዜ አሁን ነው መከላከል ይቻላል። አፋጣኝ ህክምና በማድረግም ይታከማል። ለዚህም የተሟላ ግንዛቤ ይኑርዎ። ለሌሎች ይህንን መረጃ ያካፍሉ። የሰዎችን ህይወት ያድኑ።

  • When Work Becomes Illness

    This is about all of us! Have we considered the impact of the work we do on our individual lives? Could the chronic ailment that is not responding to medical treatment be associated with our work? Yes, this is about occupational exposure.  What is Occupational Exposure? Occupational exposure  happens when workers regularly encounter harmful physical, chemical, biological, or ergonomic hazards on the job. From dust in factories and construction sites to needle-stick injuries in hospitals, these exposures can silently damage health—and all too often, do. Sometimes it is from dealing with vibration throughout the day. For instance, road workers, wood workers, and drivers of tractors may suffer from chronic joint problems due to dealing with vibrating equipment throughout the day. The posture an office secretary maintains during work can severely impact her spine, resulting in long-lasting back pain years later.  The symptoms are not always simple and direct. Most time they are masked and hidden. They are assumed to be due to some disease of unknown etiology. However, a simple office ergonomics might solve it. The common Symptoms include Respiratory symptoms – coughing, wheezing, chest tightness, shortness of breath, chronic cough, and sputum. Traumatic injuries  – cuts, fractures, amputations, especially in construction and manufacturing. Injury prevalence reaches nearly 45% in construction  and up to 50% among metalworkers in Addis Ababa . Musculoskeletal pain , like back and shoulder pain, in kitchen and hospitality workers, is documented in Bahir Dar at high prevalence  levels, affecting quality of life. Needlestick injuries and exposure to blood-borne pathogens , estimated risks for hepatitis B, C, and HIV among health care workers are high. In Ethiopia, being a TB endemic country, the prevalence of both primary and secondary TB among healthcare workers. Ethiopian Reality The reality is that occupational health has not been properly explored in Ethiopia so far. There are limited studies. The attention and investments directed toward it are even less. A nationwide meta‑analysis across 23 studies found a pooled annual occupational injury prevalence of 44.7%  (95% CI: 43.8–45.5%) . Respiratory symptom prevalence among industry workers is about 51.6%  (95% CI: 43.6–59.6%), and among factory workers, specifically, around 55% . In textile factories, non-fatal occupational injuries fell to 11%  during the COVID‑19 era—but machinery-related incidents still dominated, often affecting the hands and fingers. What about workers from flower factories? What will the daily exposure to pesticides, pollen, and other chemicals manifest as? Are there risk factors to it? Definitely, yes! Most Ethiopians can safely assume that they have the risk factor. Office spaces are designed based on function, not human resource health. Working in challenging conditions is considered a virtue, a strength. Protection equipment might not adhere to the standards, let alone the needs of the workplace. Literatures cite the following as risk factors. Lack of PPE increases the odds of respiratory symptoms. Not using PPE can triple injury risk. No OSHA or health and safety training   Long working hours Substance abuse (khat, cigarettes), Male gender, and More than 5 years of experience Alas! There is n o national reporting system  for occupational diseases. Most results remain fragmented and local . There are very few longitudinal or cohort studies , and limited studies in mining, agriculture, and healthcare beyond major cities. To make matters worse, e nforcement of labor and safety laws  remains weak. Though Ethiopia ratified many ILO conventions, its compliance and institutional capacity lag. Why You Should Care? A Call to All Ethiopians Imagine this. It’s 5:00 a.m. in Addis Ababa. A mother wears her netela, kisses her sleeping child, and walks to a dusty garment factory. She will spend the next 10 hours hunched over a sewing machine with no proper ventilation, no mask, and no guarantee of returning home uninjured. Across town, a young man climbs scaffolding at a construction site, carrying bricks without a helmet. His hands are blistered. His future, uncertain. We have to remember this isn’t fiction. This is not a mere story depicted for the purpose of this article. This is the reality of thousands of Ethiopians. In their fight to put bread on the table and sustain their family, their health has been. pushed aside. This is one symptom of Hand Arm Vibration syndrome. It is called secondary Raynaud`s Phenomenon. It is the blanching of the fingers due to spasmodic blood vessels triggered by long-standing vibration exposure. Nurses develop varicose veins, while chauffeurs develop chronic back pain. Some gradually lose their hearing, while others face skin problems. There are those who develop cancer. However, these will not be noticed! They will not bleed nor result in agonizing pain. However, they are doomed to live life with an ailment that will not respond to medical treatment. They will keep on striving and surviving until they don`t. They are the victims of their work, their livelihood. Yet, we rarely hear their voices, let alone notice their pain. We need to fix this! How do we fix this? This is a symptom of carpal tunnel syndrome. It can be caused by repetitive wrist motion, poor posture, and prolonged use of a mouse. 1. First, we must start by listening. Occupational diseases in Ethiopia are not well-tracked because, frankly, most go unreported. It is not the absence of the ailment, but the lack of attention that makes them disappear behind the scenes. Workers are afraid to speak. Many don’t even know their shortness of breath or back pain is a “work-related illness.” Hence, we as a nation must create a national registry and surveillance system  to collect data. We can’t treat what we don’t acknowledge. 2. Enforce what already exists . Ethiopia has signed international labor conventions. The legal frameworks exist on paper, while in reality, inspections are rare, and employers face little accountability.   We need to enforce the laws to ensure a healthy workplace. Imagine if inspections were as regular and respected as tax audits. If PPE violations led to actual consequences. If a worker could report unsafe conditions anonymously—without risking their job. 3. Bring protection to the people—don’t wait for people to ask. Many injuries and illnesses could be prevented with simple personal protective equipment (PPE) —gloves, goggles, dust masks, and ear protection. But in most factories or farms, PPE is either unavailable, poor in quality, or not used correctly. in this regard, we don’t need futuristic tech. Just common sense, commitment, and compassion. 4. Educate—and not just with posters. We have to acknowledge that a few faded safety signs won’t stop a worker from lifting with their back instead of their knees. Nor will a once-a-year conference or seminar advise on occupational health. Education needs to be continuous, engaging, and adapted to real life . People need to be informed on their mobile phones, on the social platforms they frequent. We need to educate them more frequently where they are. We need creative, ongoing, community-based education  that empowers workers with knowledge—and dignity. 5. Empower health professionals to do more. Doctors and nurses in Ethiopia’s hospitals are already overburdened. Many have little training in identifying occupational diseases. Unfortunately, most occupational diseases are misdiagnosed and mistreated most time. This creates a vicious cycle. Let’s train health workers to ask the right questions : “What do you do for a living?” “Are you exposed to dust?” "Do you handle vibrating equipment?" “Do others at your job feel the same symptoms?” 6. Make this everyone’s business. At the heart of it all is this: we must care . As a society. As individuals. This issue is not about “poor workers” somewhere. It’s about our sisters in the textile industry. Our uncles are on construction sites. Our neighbors in clinics. A Final Thought: To heal Ethiopia, we must first heal her workers. And we can—if we start now

  • 🎀 የጡት ካንሰር ምን? በምን? እንዴት? 🎀

    እስኪ ስለ ጡት ካንሰር እንነጋገር... ስለ ጡት ካንሰር ሰምተው ይሆናል። ለመሆኑ በቂ ግንዛቤ አለዎት? ጡት ካንሰር ምንድነው? እንዴትስ ይመጣል? በምንስ መከላከል ይቻላል? የጡት ካንሰር ሴቶችን ከሚያጠቁ ካንሰሮች ዋነኛ ሲሆን ፤ ከ 8 ሴቶች ውስጥ አንዷ በጡት ካንሰር ትታመማለች ተብሎ ይገመታል።  🚨 የኢትዮጵያ ሴቶች ከሌላው አለም ቀድመው በጡት ካንሰር እየታመሙ ፤ አርፍደው እየታከሙ ፤ በቶሎ እየሞቱ ይገኛሉ።   ለምን? ይህንን ለመረዳት መጀምሪያ ስለ ጡት ካንሰር እንረዳ።   🔍 የጡት ካንሰር ምንድን ነው? ካንሰር በባህሪው የሰውነታችን ህዋሳት ያለልክ የሚያድጉበት በሽታ ነው። የጡት አከባቢ ያሉ ህዋሳት እንደዚህ ያለገደብ ሲያድጉ የጡት ካንሰር ይባላል።  እነኝህ ህዋሳት መጠናቸው ሲበዛ ፤ ጡት ውስጥ የምናስተውለው እብጠት ይፈጥራሉ። እነኝህ ካንሰር የሆኑ ህዋሳት ቀደም ብለው ካልተያዙ ፤ ወደ ቅርብ አካላት (የጡት ቆዳ፣ የደረት አጥንት ፣ ጡት አከባቢ ወዳሉ ንፍፊቶች) አልያም ፤ ወደ ሩቅ አካላት (አጥንትን፣ ጉበትን፣ ሳንባንና አንጎልን ጭምር) ሊዛመቱ ይችላሉ። የጡት ካንሰርን እድገት የሚያሳይ ምሳሌያዊ ሰእል። ቢጫው የጡት ካንሰር ነው። ጡትን የሚሰሩ የተለያዩ ህዋሳት እንዳሉ ፤ በዚሁ ልክ የተለያዩ የጡት ካንሰር ዓይነቶች አሉ። ባህሪያቸውም ለየቅል ነው። አንዳንዶቹ ቀስ በቀስ ያድጋሉ። ሌሎቹ ደግሞ ቁጡ ናቸው። በፍጥነት ያጠቃሉ። ይሰራጫሉ።   በጣም የተለመዱት ሶስት የጡት ካንስር አይነቶች እነሆ፡ ኢንቬዚቭ ደክታል ካርሲኖማ (Invasive ductal carcinoma (IDC))  – ይህ ካንሰር ከወተት ማምረቻ ቱቦ ህዋሳት ይመነጫል። ብዙ ጊዜ እብጠት/ እባጭ ጡት ላይ ያሳያል። ወደ አጠገቡ ወዳሉ ህዋሳት ፤ እንዲሁም ንፍፊት እና ቆዳም ይሰራጫል። ኢንቬይዚቭ ሎብዩላር ካርሲኖማ (Invasive Lobular Carcinoma (ILC))  -ይህ ወተት ከማምረቻ ክፍል (lobules) ይመነጫል። አጠገብ ወዳሉ ህዋሳት ሲሰራጭ በረድፍ ስለሆነ ፤ በጣም ካልተስፋፋ እባጭ ላያሳይ ይችላል።   ትሪፕል ኔጌቴቭ ብረስት ካንሰር (Triple Negative Breast Cancer) - ይህ የአፍሪካ ዘር ባላቸው ሴቶች ላይ የተለመደ ሲሆን ፤ ለህክምና ከባድ ውጤቱም የከፋ ነው። እነኝህ በጣም የተለመዱ ይሁኑ እንጂ የተለያዩ የጡት ካንሰር አይነቶች አሉ። 💣 የጡት ካንሰር በምን ምክንያት ይመጣል ? መንስኤው  ጡት ካንሰር በተለያዩ ምክንያቶች ይመጣል። ለመረዳት እነኝህን ምክንያቶቹን በሶስት መጠቅለል እንችላለን ፡-ዘረመል (ጂኖች/ genes)፣ ሆርሞን እንዲሁም አኗኗር ዘይቤ። እነኝህን አንድ በአንድ እንይ ✅ ዘረመል ፦የጡት ካንሰር  ከ5 እስከ 10 ፐርሰንት ያህል  በዘር ይተላለፋል። ለዚህም ዋነኛ ተጠቃሽ የዘረመል ለውጦች ናቸው። በተለይም ብርካ የሚባለው የዘረመል ክፍል( BRCA1 & BRCA2  ጂኖች) ጋር የተያያዘ ለውጥ ይህ እንዲከሰት ያደርጋል። ይህ ለውጥ ያለባቸው ሴቶች በህይወት ዘመናቸው የጡት ካንሰር የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ ስለሆነ ፤ መደበኛ የጡት ምርመራ ያስፈልጋቸዋል። ✅ ሆርሞኖች፦ የጡት ካንስር ታማሚነት ከ ኢስትሮጅን ሆርሞን ጋር ይያዛል። ለዚህም ይህ ሆርሞን ደማቸው ውስጥ ከፍ ብሎ ለረዥም ጊዜ የቆየ ሴቶች ተጋላጭነት ያይላል። ለዚህም ከ 30 አመት በኋላ የመጀመሪያ ልጃቸውን የወለዱ ሴቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ ለረዥም ጊዜ የወሰዱ ሴቶች (እነኝህ ሴቶች በተቃራኒው ከ ማህጸን ካንሰር የተጠበቁ ናቸው) ቀድመው የወር አበባ የሚያዩ ሴቶች ቆይተው የሚያርጡ ሴቶች የሆርሞን ህክምና የሚወስዱ ሴቶች ለዚህ ተጋላጭነታቸው ያየለ ነው።  ✅ የአኗኗር ዘይቤ ፦ ከአኗኗር ዘይቤ ውስጥ ተጠቃሾቹ ውፍረት  እና ከፍተኛ-ቅባት አመጋገብ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ከመጠን በላይ አልኮል  መጠጣትና ማጨስ ተጠቃሽ ናቸው። ጡት ማጥባት እና ልጅ መውለድ ደግሞ ተጋላጭነት ይቀንሳል። 🚩 ታድያ ለዚህ ተጋላጭ እነማን ናቸው ? እላይ በተጠቀሰው መሰረት ፤ ለጡት ካንሰር ተጋላጭነት ያለባቸው የሚከተሉት ናቸው። እድሜያቸው ከ40 በላይ የሆኑ ሴቶች  (  ወንዶችም ጡት ካንሰር ሊይዛቸው ቢችልም እጅጉን ያልተለመደ ነው።) ፤ በቤተሰብ የጡት ወይም የማህጸን ካንስር ታሪክ  ካለ ፤ የ  ዘረመል ለውጥ  ካለ ፤ ከ 30 ዓመት በኋላ የመጀመሪያ ልጅ የወለዱ ሴቶች ፤  ደረታቸው አከባቢ የጨረር ሕክምና የተደረገላቸው ሴቶች ፤ ተጋላጭነታችው ይጨምራል። 🛑 መረጃዎች እንደሚያሳዩት የጡት ካንሰር ካለባቸው ሴቶች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት የሚታወቅ የቤተሰብ ታሪክ የላቸውም።  ለዚህም ሁሏም ሴት ንቁ መሆን አለባት።  🛡️ በምን መከላከል ይቻል ይሆን? ለጡት ካንሰር አጋላጭ ምክንያቶች መሀከል ፤ የተወሰኑትን መቆጣጠር ይቻላል። አኗኗር ዘይቤን  በማስተካከል ተጋላጭነትን  መቀነስ ይቻላል።  ለዚህም 🥗ጤናማ ክብደት ይኑርሽ። 🏃 አካል እንቅስቃሴ አዘውትሪ። 🍷 አልኮል አዘውትረሽ አትጠጪ። 🚭   ሲጋራ አታጭሽ። 🍼 ከተቻለ ልጅሽን ጡት አጥቢ። 🍎 ቅባት መመገብ ቀንሺ። ፍራፊሬ አትክልትና አዝእርት ዘውትሪ።  🧬 በቤተሰብሽ የጡት /የማህጸን ካንሰር ታሪክ ካለ ፤ መደበኛ የጡት ምርመራ አድርጊ። 🩺 በንቃት አዘውትረሽ ጡቶችሽን መመርመር ልመጂ። በእጆችሽ እየዳሰሽ እብጠት መኖሩን አስተውይ። አተር የሚያክል እንኳን እብጠት ካየሽ ፤ በአፋጣኝ ጤና ባለሙያን አማክሪ። ⚠️ መታወቅ ያለባቸው ምልክቶች የጡት ካንሰር  ሲጀምር ብዙ ጊዜ በባህሪው በህመም አያሰቃይም። የህመም ምልክት ላያሳይ ይችላል። ለዚህም ቀደም ብሎ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ለዚህ ነው ተጠራጣሪ መሆን የሚመከረው። ህመም የሚኖረው ሲደረጅ፣ ሌሎች አካላትን ሲወር ነው።   ሆኖም ግን እነኝህን ምልክቶች ፈጽሞ ችላ እንዳትይ! ✅ ጡቶች ላይ ወይም ብብት ስር ያለ ማንኛውንም እብጠት ፤ ✅የጡት ቅርጽ ፣ መጠን እና ያለው ልስላሴ ለውጥ ፤ ✅የጡት ቆዳ ከቀላ፣ ከሰረጎደ እንዲሁም እንደቡርትካን ልጣጭ ካደበደበ ፤ ✅ከጡት ጫፍ ወተት ያልሆነ ፈሳሽ ከወጣ (ደም ሊቀላልቅል ይችላል)፤ ✅ የጡት ጫፍ ወደ ውስጥ መግባት ወይም መገልበጥ ፤ ✅ ጡት ላይ የማያቋርጥ ህመም ካለ ፤ አስተውይ ። ከእነዚህ ምልክቶች መካከል የትኛውንም ካስተዋልሽ ፈጽሞ ጊዜ እንዳትሰጭ። ወዲያውኑ የሕክምና ምርመራ አድርጊ። 🛑የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ የጡት ካንሰር በኢትዮጵያም ሴቶችን የሚያጠቃ ግንባር ቀደም የካንሰር አይነት ነው። በብዛትም ሴቶችን ከሚያጠቁ የካንሰር አይነቶች አንድ ሶስተኛውን ይወስዳል። እ.ኤ.አ በ 2020 ብቻ በኢትዮጵያ 16,133 አዲስ የጡት ካንሰር በሽተኞች ተገኝተዋል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ይህ ካንሰር እየተስፋፋ ይገኛል። አሳዛኙ ሁኔታ ደግሞ አብዛኞቹ የጡት ካንሰር ታማሚዎች ወደ ህክምና የሚመጡት ፤ አርፍደው ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ደርሶ ነው። በዚህም የተነሳ የህክምናው ውጤታማነት ዝቅተኛ ይሆና። ከሌላው አለም አንጻርም የጡት ካንሰር ኢትዮጵያ ላይ ጎልማሳዎችን ያጠቃል። በሌላው አለም አብዝቶ ከ 50 አመት በኋላ ሲያጋጥም ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኞቹ ታማሚዎች በሰላሳዎቹ እና በአርባዎቹ እድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሴቶች በጡት ካንሰር ይሞታሉ። የአብዛኞቹ ሴቶች የሞት ምክንያት የህክምና ጉድለት ሳይሆን ፤ ዘግይቶ መታወቁ ነው። አንዳንድ ሴቶች ካወቁም በኋላ ፤ ህክምና ለመውሰድ ወራት ሲፈጁ ይስተዋላል።  ይህም በሽታው  ከሚያመጣው  ህመም  አልፎ የህይወታቸውን ዋጋ ያስከፍላቸዋል።  🛑 ለምንድነው የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ እየተስፋፋ እና አርፍዶ እየተገኘ ያለው? የጡት ካንሰር መስፋፋት እና አርፍዶ መታከም ጋር የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ከእነኝህም መሀክል ጥቂቶቹ ግንዛቤ ማጣት።  አንዳንድ ሴቶች የጡት ካንሰር ዙርያ ያላቸው ግንዛቤ የተሟላ ስላልሆነ ፤ ችላ ይላሉ። በሐኪም የሚመከሩትንም ህክምና ለመውሰድ ያመነታሉ። ህክምናውን ለመውሰድ እስኪወስኑ በሽታው ይሰራጫል። አንዳንዶችም የባህል ህክምና ሲሞክሩ ሰንብተው ፤ በሽታው ሲደረጅ ወደ ጤና ተቋም ተመልሰው ይመጣሉ።  ይህም ህመሙን ማከም የሚቻልበትን ወርቃማ ጊዜ ይሰርቃል።   አንዳንድ ሴቶች የጡት ካንሰር እንዳለባቸው እንዲታወቅ አይፈልጉም ። ለዚህም የህክምና ክትትሉን ችላ ይላሉ። እንደ ፈጣሪ ቁጣ/ቅጣትም ተደርጎ ስለሚወሰድ ፤ በሽታውን ይደብቁታል። ካንሰሩ ግን ከጀርባ ስለሚደረጅ ፤ መደበቅ የማይቻልበት ጊዜ ይደርሳል። የዚህን ጊዜ የጤና ተቋም ይጎበኛሉ። የአቅም ጉዳይም ሌላኛው ምክንያት ነው።  አብዛኞቹ ሴቶች የሕክምና ክትትል በሚፈልጉበት ጊዜ ካንሰሩ ስለሚዛመት ከፍተኛው ወጪ ይጠይቃል። ኬሞቴራፒ መድሐኒቶች በቀላሉ በመንግስት ሆስፒታሎች አይገኙም። ከገበያ ሲገዙም ሒሳባቸው ክፍተኛ ነው። ተጨማሪ መድሐኒቶች እና ምርመራዎች ሲታሰብ ሂሳቡ ይንራል። ይህ ደግሞ ለታችኛው የማህበረሰብ ክፍል ለምትመጣ ሴት ፈታኝ ነው። መታከም ብትፈልግም ፤ የገንዘብ እጥረት በአፋጣኝ እንዳትታከም ያደርጋታል። የራዲዮ ቴራፒ ህክምና የሚሰጡ ቦታዎች እጅጉን ውስን ስለሆ ኑ ፤ ወረፋ እስኪደርሳቸው በሽታቸው የሚደረጅም አሉ። በተጨማሪም የስፔሻሊስት ሐኪሞች እና መመርመሪያ መሳሪያዎች ውስንነትም አለ። አሁን ኢትዮጵያ ባላት አቅም የተሟላ ምርመራ ማድረግ አይቻልም። ለዚህ ህክምና አስፈላጊ የሆኑ ልዩ ምርመራዎችን (ለምሳሌ የዘረመል ምርመራ ፣ የ ፔት ስካን (PET CT Scan)) የሉም።   💬 ዝምታን እንስበር! የጡት ካንሰር "የሴቶች ጉዳይ" ብቻ አይደለም። የማህበረሰብ ጉዳይ  ነው። እናቶችን ፣ ሴቶች ልጆችን ፣ ሚስቶችንና እህቶችን ይነካል ። በግንዛቤ ጉድለት ፈጽሞ ማንም ሴት መሞት የለባትም! አሁኑኑ ይህንን ተግባራዊ ለውጥ እናምጣ፡ ✅ ስለ ጡት ካንሰር እንነጋገር። ✅ ያለንን ሳይንሳዊ ግንዛቤ ለሌሎች እናጋራ። ✅ ሴቶች ምልክቶችን እንዲያስተውሉ እና እራሳቸውን እንዲመረመሩ እናበረታታ።  ✅ ምንም አይነት ለውጥ ካየች አንዲች ሴት ሀኪም እንድታማክር እናበረታታት/   በዚህም ህይወት እናድናለን! አንዲት ሴት ትተርፋለች።

bottom of page