top of page

🌸የወር አበባ ጊዜውን ጠብቆ ባይመጣስ?

ለብዙ ሴቶች የወር አበባ ዑደት ፤ ስርአቱን የጠበቀ፤ በቀን መቁጠሪያ ሊተመን የሚችል ነው። ለአንዳንድ ሴቶች ግን ፤ የሚታይበትን ቀን ለምገመት አዳጋች ሲሆን ይታያል። አንድ ወር ላይ በሳምንታት ውስጥ ሲታይ ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከወራት በኋላ ይታያል። አንዳንዴማ ጨርሶ ጥፍት ይላል።


ree

ግን ለምን?


ይህ መደበኛ ነውን?


ይህንን ለማወቅ በመጀመሪያ ፤ ስለ የወር አበባ እንነጋገር።


የወር አበባ በእርግጥ ምንድን ነው?


የወር አበባ እርግዛና ባልተከሰተ ጊዜ የሚያጋጥም ፤ የማህፀን ግድግዳ መፍረስ ነው።  ይህም የሚፈጠረው ፤ የሴት ልጅ ሰውነት እርግዝና አለመኖሩን ሲረዳ ነው። ለዚህም ሰውነቷ የእርግዝና ጠባቂ የሆነው ፕሮጀስትሮን ሆርሞን መጠን ዝቅ ያደጋል። ይህንንም ተከትሎ ፤ ጽንስ ለመያዝ ተዘጋጅቶ የነበረው የማህጸን ግድግዳ ይፈርሳል። የፈረሰውም ግድግዳ በወር አበባ መልክ ይወጣል።


ree

በአኗኗር ላይ ቢመሰረትም በአለም ዙሪያ ሴቶች ከ12/13 አመት ጀምሮ የወር አበባ ያያሉ። ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከሆነ በኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ ያሉ ሴቶች ከ 13 - 14 ዓመት ጀምሮ የወር አበባ የሚያዩ ሲሆን ፤ በገጠሯ ኢትዮጵያ የሚኖሩት ደግሞ ከ14 -15 ዓመት እድሜ ጀምሮ ያያሉ። ሴት ልጅ መውለድ በምትችልባቸው አመታት ሁሉ ፤ ይህ ዑደት ይቀጥላል። ወደ አርባዎች መጨረሻ ገደማ ደግሞ ፤ የወር አበባ ማየት ታቆማለች። ይህም በተለምዶ ማረጥ ይባላል።


ወርሀዊ ግዴታ ይባል እንጂ በየወሩ 30ን ጠብቆ የሚፈጠር አይደለም።ከሰው ሰው ቢለያይም ቢለያይም በአማካይ ከ 3 ሳምንት እስከ 5 ሳምንት ድረስ ባለው ጊዜ (21 እስከ35 ቀናት) ይታያል። አልፎ አልፎ እስከ 6 ሳምንት ሊቆይ ይችላል። አንዲት ሴት የወር አበባ ከ 3 እስከ 7 ቀን ድረስ ልታይ ትችላለች። እንደ አጠቃቀሟ ከ 2 እስከ 4 ፓድ በቀን ልትጠቀም ትችላለች።


ይህም መደበኛ የወር አበባ ስርአት ነው!



🔍 ታድያ መቼ ያሳስባል?


ከመደበኛው ከወጣ፤ አልያም የወር አበባ ኡደቱ ከተስተጓጎለ፤ ማስተዋል ያስፈልጋል። ለዚህም

  • አንዲት ሴት ልጅ በ15 አመቷ የወር አበባ ካላየች፤

  • የወር አበባ ለአጭር ጊዜ (ከ 3 ቀን በታች) ወይም ለረጅም ጊዜ ( ከ 7 ቀን በላይ) ከቆየ ፤🌀

  • በየወሩ ጊዜውን/ቀመሩን ጠብቆ የሚመጣ ካልሆነ፤⏳

  • የሚታየው የወር አበባ መጠኑ ካነሰ አልያም ከበዛ (በቀን ከ 4 ፓድ በላይ ከተጠቀምሽ) ፤🌊

  • የወር አበባ የማይታይባቸው ወራቶች ካሉ፤ 🚫

ማስተዋል ያስፈልጋል።


የዚህን ጊዜ ሰውነትሽን ማዳመጥ ፤ ሀኪምሽን ማማከር ይኖርብሻል!
ree

🌍 ደሞም ብቻሽን አይደለሽም!


 ከ4 ሴቶች መካከል አንዷ በሕይወት ዘመኗ ከመደበኛ የተለየ የወር አበባ ታያለች። ይህም ደግሞ በተለይ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በሚገኙ ወጣቶችና ወደ ማረጥ እድሜ እየተቃረቡ ባሉ ሴቶች ላይ በይበልጥ ይስተዋላል። 


ቢሆንም ፤ ይህን ከመደበኛ የተለወጠ የወር አበባ ስርዐት ማስተዋል ያስፈልጋል።

አንዳንዴም ከውስጥ የተደበቀ በሽታን አመላካች ሊሆን ይችላል።

እነኝህ ለውጦች ለተወሰነ ጊዜ የሚቆዩ ፤ የማያሳስቡ ሊሆኑ ይችላሉ።

እነኝህ ለውጦች

  • ለረዥም ጊዜ ከቆዩ ፤ እንዲሁም

  • እነኝህን ለውጦች ተከትሎ እንደ ድካም፣ ማቅለሽለሽ ፣ ጆሮ ላይ መጮሕ ፣ የገረጣ ቆዳ አይነት የደም ማነስ ምልክቶች ከታዩ ፤


በይበልጥ አጽንኦት መስጠት ያስፈልጋል። ይህም ስር የሰደደ ችግር አመላካች ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ፡ ከጀርባ መሀንነት ፣ ደም ማነስና፣ የሆርሞን ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ከዚህም ባሻገር የኢንዶሜትርዮሲስ፣ የማህጸን አከባቢ ካንሰሮች እና የማህጸን እጢዎችም ፤ ለየት ያለ የወር አበባ ኡደት ሊያሳዩ ይችላሉ።


የወር አበባ ከተለመደው ጊዜ ከቆየ እርግዝና አለመኖሩን ፤ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

የወር አበባሽ ኡደት ስለ መውለድ መቻልሽን ብቻ አያመላክትም። የጤንነትሽም ምልክት ነው።

⚠️ ለምን ይከሰታል?


ree

ከመደበኛው የተለወጠ የወር አበባ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል። ከእነኝህም መሀል


ውጥረትና የአኗኗር ዘይቤ – እንቅልፍ ማጣት፣ ከባድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና፣ የተመጣጠነ ምግብ አለመመገብ ፤ የሰውነት ሆርሞኖችን ሚዛን ያዛባል። የወር አበባ ለውጥን ያመጣል። 


ፖሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድሮም (PCOS) – ፒኮስ ለማህንነት ሊያጋልጥ የሚችል ፤ ብዙ ወጣት ሴቶችን የሚያጠቃ በሽታ ነው። ይህም በሽታ የሆርሞን መዛባት ስለሚያስከትል ፤ የወር አበባ ስርአትን ሊቀይር ይቻላል።


የታይሮይድ በሽታ ችግር — ከመጠን በላይ እየሰራ ያለ ፤ አልያም ስራው የቀነሰ የታይሮይድ እጢ ፤ የወር አበባን ሊያስተጓጉል ይችላል ።


የክብደት መለዋወጥ – መወፈርም ሆነ መክሳት ሆርሞኖች ላይ በሚያሳድረው ተጽእኖ ፤ የወር አበባን ሊለውጥ ይችላል። ለዚህም ድንገተኛ የሰውነት ክብደት ለውጥ ካለ ፤ የወር አበባ ከተለመደው ሊለውጥ ይቻላል።


✨ ብዙዎቹ የእርግዝና መከላከያዎችም ሆርሞኖች ከመሆናቸው የተነሳ ፤ የወር አበባን ዑደቶች ሊለውጡ ይችላሉ ።


ሥር የሰደደ በሽታ — የስኳር በሽታ ፣ የጉበት በሽታ ወይም ሌሎች የጤና ችግሮች ፤ የወር አበባን ስርአት ሊለውጡ ይችላሉ።


ሆኖም ግን እነኝህ ለውጦች ብዙ ጊዜ አሳሳቢ አይደሉም።

እዚህ ጋር የወር አበባ ጊዜ የሚታየው ህመምም መረሳት የለበትም።


ree

አንዲት ሴት የወር አበባ በምታይበት ወቅት ፤ የማህጸን ጡንቻ መኮማተሩን ተከትሎ ፤ የወር አበባ ህመም ይሰማታል። ይህ ህመም የታችኛውን የሆድ ክፍል ላይ የሚሰማ ሲሆን ፤ የህመሙ መጠን እንደየሰዉ ይለያያል። ሆኖም ግን ብዙ ጊዜ በህመም ማስታገሻ የሚመለስ ነው። ከሥራ ፣ ከትምህርት እንዲሁም ከማህበራዊ ቁርኝቶች ሊያስተጓጉል የሚችልብቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ።


ሆኖም ግን ይህ ህመም

  • እጅጉን ካየለ /ከጠነከረ፣

  • ከወር አበባ በኋላም ከቆየ ፤

  • በህመም ማስታገሻ ቁጥጥር ስር ካልዋለ ፤

  • በግንኙነት ጊዜም ካለ ፤

  • ሥራ፣ትምህርትን፣ ማህበራዊ ቁርኝትን በከፍተኛ ሁኔታ ካስተጓጎለ

  • አብረውት ሌሎች የህመም ምልክቶቹ ካሉ ሊያሳስብ ይገባል።


ህመሙ እነኝህን ለውጦች ካሳየ ፤ አቅራቢያሽ ወዳለ ጤና ተቋም ሄደው ፤ ምርመራ ማድረጉ መልካም ነው።


🌱 ምን ማድረግ ትችያለሽ


ree

የወር አበባ ለውጥ በጥንቃቄ እና በህክምና እርዳታ ሊስተካከል የሚችል ነው። ለዚህም


💡የወር አበባ ዑደትሽን ተከታተይ - የሞባይል መተግበሪያ፣ ካላንደሮችን፣ እንዲሁም ማስታወሻዎችን ያዥ። 


💡 የአኗኗር ለውጥ አድርጊ– ለጤናሽ ቦታ ስጪ ፣ እንቅልፍ በአግባቡ ተኚ ፣ የተመጣጠነ ምግብ ተመገቢ፣ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርጊ ።


💡 የህክምና ምርመራ አድርጊ – የወር አበባ ስርአቱ ዙሪያ አሳሳቢ ለውጥ ካየሽ ፤  ቅርብ ያለ የጤና ተቋም ሂጂ። ዶክተር አማክሪ።


 💡 ውጥረት –  አትጨነቂ፣ ውጥረት ቀንሺ። ውጥረት ለመቀነስ የሚጠቅሙ እንቅስቃሴዎችን (እንደ ዮጋ እና የአተነፋፈስ እንቅስቃሴዎች) አድርጊ።


💡 ለፒኮስ፣ ለታይሮይድ ህመም ምርመራ አድርጊ። መደበኛ የጤና ምርመራ ይኑርሽ። 


 

🌸 የመጨረሻ ሃሳብ

መደበኛ ያልሆነ የወር አበባ የቀን መቁጠሪያ ችግር ብቻ አይደለም።


ሰውነትሽን በጥሞና አዳምጪ። 


ሲለወጥ አትጠብቂ። የጤና ባለሙያ አማክሪ። 

 

Comments


bottom of page