የስኳር በሽታ አስከፊ ዳፋ የሆነው ዲኬኤ
- Zebeaman Tibebu
- Aug 10
- 4 min read
ከሞትን አፋፍ የተመለሰው ልጅ ታሪክ
ባለታሪኩ የ6 አመቱ አብርሀም ፤ የዛሬ ስደስት ወር ገደማ ሰውነቱ አለልክ መክሳት ይጀምራል። ውሀም አለልክ ይጠጣል። ሽንትም አብዝቶ ይሸናል። ቤተሰቦቹም ብዙም አሳሳቢ ጉዳይ አድርገው አልወሰዱትም ነበር። ታድያ ከ 3 ሳምንት በፊት ፤ ያቅለሸልሸው እና ሆዱን ይቆርጠው ጀመር። ይህን ጊዜ ወስፋት የመሰላቸው የቤተሰቡ አባሎች ፤ ከቅርብ ፋርማሲ ገዝተው የ ትላትል መድሀኒት ይሰጡታል። መድሀኒቱን ቢጨርስም ፤ ምልክቶቹ ፈጽሞ አልተሻሻሉም ነበር።

ምንም ለውጥ ባያሳይም ፤ ቤተሰብም ይሻለዋል ብሎ ቤት ውስጥ ይከታተሉታል። ይልቁኑ በሰው ካዩት ምልክት ተነስተው ፤ የሽንት ኢንፌክሽን ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ። ቢገምቱም ውሀ እየጠጣ ስለሆነ ፤ እንደሚሻለው በማሰብ ፤ ፈጽሞ ሀኪም ቤት ይዘውት አልሄዱም ነበር። የትላትል መድሀኒትም ስለወሰደ ፤ የሆድ ቁርጠቱም እንደሚጠፋ ፤ የምግብ ፍላጎቱም እንደሚስተካከል አምነው ይጠብቁት ጀመር። በዚህ ሁኔታ ሁለት ሳምንታት ተቆጠሩ። ግን ምንም ለውጥ የለም!
በተረዱት መንገድ እያስታመሙት ያሉት ቤተሰቦች ፤ ሀሳብ ይገባቸው ጀመረ። ይብሱኑ ምልክቶቹ ተባባሱ። ያስታውከው ጀመር። ሽንቱን ፈጽሞ መቆጣጠር ተሳነው። ነገሮች ላይ ግራ መጋባት አመጣ። ቃላቶች መንተባተብ ጀመረ። ድካሙ ስለባሰበት ፤ ከእኩዮቹ ጋር መጫወት ትቶ ፤ ከቤት መተኛት አበዛ። ቀንሶ የነበረው የምግብ ፍላጎቱም ፤ ፈጽሞ ጠፋ። ምግብ በአይኔ አታሳልፉ አለ።
ህመሙ መባባስ ከጀመረ ሶስት ሳምንት አከባቢ ፤ ቤተሰቦቹ የማይልፍ ህመም ባይሆን ብለው ፈሩ። ለዚህም የተጨነቁ ወላጆቹ ሆስፒታል ይዘውት ሄዱ። ሀኪም ቤት የተደረገውም ምርመራ ፤ የስኳር በሽታ እንዳለበት አመላከተ። የደም ላይ የስኳር መጠኑ 600 mg/dl ፣ የHBA1C መጠን 12. 1 እና የሽንት የኬቶን ምርመራ ፖዘቲቭ ሆኖ ተገኘ። ይህም ቁጥጥር ላይ ያልዋለ የስኳር በሽታ ከሚያመጣቸው አስጊ ህመሞች በመሆኑ ፤ በድንገተኛ ህክምና ተጀመረለት።
አርፍዶ ቢሆንም ህመሙ እጅጉን ሳይባባስ ህክምና በማድረጉ ፤ ከህመሙ ሊያገግም ችሏል።
ታድይ ይህ አንድ ፍሬ ልጅ ፤ ህይወቱ አደጋ ላይ እንደነበረች ቢያውቁ ቤተሰቦቹ እንዲህ ችላ ይሉ ነበርን?
ከዚህ በኋላ ቀናት እንኳን አርፍዶ ቢሆን ፤ ኮማ ውስጥ ሊገባ አልያም ለሞት ሊዳረግ እንደሚችል ቢያውቁስ?
ይህ ህመም ዲያቤቲክ ኬቶ አሲዶሲስ (ዲኬኤ)ሲባል ፤ በይበልጥ የታይፕ አንድ ስኳር ህመምተኞችን የሚያጠቃ ህመም ነው። እንደብሩክ ላሉ ታማሚዎችም የመጀመሪያ የስኳር በሽታ ጠቋሚ ምልክት ሊሆን ይችላል።
ህመሙ ሲጀምር ቀላል ቢመስልም ፤ እጅጉን አሳሳቢ እና እስከሞት የሚያደርስ ነው።
ዛሬ የምናወራው ስለ ዲኬኤ ነው።
ስለ ዲኬኤ ከማውራታችን በፊት ግን ፤ ስለ ስኳር በሽታ ጥቂት ማለት ይኖርብናል።
የስኳር በሽታ ምንድን ነው?

የስኳር በሽታ የኢንሱሊን መዛባትን ተከትሎ የሚያጋጥም ነው። ሰውነት እንዳሉት የኢንሱሊን አምራች ህዋሳት መጠን ፤ እንዲሁም በህመሙ ባህሪ ተመስርቶ በሁለት ይከፈላል። ታይፕ አንድ የስኳርበሽታ ብዙ ጊዜ ከህጻንነት ጀምሮ የሚያጋጥም ሲሆን ፤ ታይፕ ሁለት የስኳር በሽታ ከአኗኗር ጋር ተያይዞ ወድ ኋላ እድሜ የሚመጣ ነው።
ታይፕ አንድ የስኳር ኢንሱሊን አምራች ህዋሳት ሲመናመኑ ፤ ወይም ፈጽሞ ሲጠፉ የሚከሰት ነው። እራስን በሚያጠቁ የሰውነት መከላከያ ህዋሳት ፤ እንዲሁም በአንዳንድ ህመሞች ምክንያት ሊከሰት ይችላል።
የስኳር በሽታ ህክምናም የተዛባውን ኢንሱሊን ማገዝ፤ እንዲሁም ደም ላይ ያለውን የስኳር መጠን መቆጣጠር ላይ ያተኮረ ነው።
🔍 ዲያቤቲክ ኬቶአሲዶሲስ (ዲኬአ) ምንድን ነው?
ዲያቤቲክ ኬቶ አሲዶሲስ የሚከሰተው የስኳር በሽታ ክትትል ሲዳከም ነው። ብዙውን ጊዜ የስኳር መድሀኒት በአግባቡ ባለመውሰድ ፤ ስኳር የበዛባቸው ምግቦችን በመመገብ ፤ እንዲሁም በኢንፌክሽን ይመጣል። ይህንን ተከትሎ ፤ ሰውነት በቂ ኢንሱሊን ስለማይኖረው ፤ የደም ስኳር (ግሉኮስ) መጠን መገደብ ይሳነዋል። ስኳር ያለልክ ደም ላይ ቢበዛም ፤ ያለ ኢንሱሊን እርዳታ ሰውነት ሊጠቀመው አይችልም። ለዚህም ሰውነት ስኳር ይራባል።
ያጋጠመውን የስኳር እጥረት ለማካካስ ፤ ሰውነት ስብን ተክቶ መጠቀም ይጀምራል። ይህም ህመም የሚመጣው በዚህ የተነሳ ነው።
ስብን ሲጠቀም የሚያመርታቸው አካላት ደም ላይ ተክማቸተው ፤ ደምን አሲዳማ ያደርጋሉ። የሰውነትን ኡደት ያበላሻሉ። የደም ማእድን መጠንንም (በተለይ የፓታሺየም) ያዛባሉ። ቶሎ ካልታከመ እስከ ኮማ እና ሞት ሊያደርስ ይችላል።
ለዚህም ይህም ህመሙን አደገኛ ያደርገዋል !! በአፋጣኝም መታከም አለበት።

በህክምናው ዲኬኤ የምንለው
የደም የስኳር መጠን ከ 250 mg/dl በላይ ሲሆን
የሽንት ምርመራ ላይ ኬቶን ከ +2 በላይ ሲያሳይ ዲኬኤ አለ እንላለን።
ኢትዮጵያ ውስጥ በቀላሉ ባይገኙም ፤ የደም የ ካርቦኔት መጠን እንዲሁም የ ፔኤች መጠንም ይህንን ህመም ለመለየት ያስችላሉ።
📊 የ የዲኬኤ ስርጭት በኢትዮጵያ
የስኳር በሽታ ስርጭት በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል። የስኳር በሽታ አሳሳቢ ህመሞች ውስጥ የሆነው የዲኬኤም እንዲሁ። ሀገር አቀፍ መረጃዎች የተሟሉ ባይሆኑም ፤ ኢትዮጵያ ላይ ያለው የ ዲኬኤ ስርጭት መጠን እጅጉን አሳሳቢ ነው። በ 2025 የተደረገ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያመላክተው ከሆነ ፤ ኢትዮጵያ ባሉ የስኳር ህመምተኞች ዘንድ ያለው የዲኬኤ መጠን 46 ፐርሰንት ይደርሳል። አንዳንድ ጥናቶች ይህንን መጠን ወደ 30 ፐርሰንት ያወርዱታል። በአዲስ አበባ ከ 5 አመት በፊት የተደረገ ጥናት በበኩሉ ፤ ከ 3 የስኳር ታማሚዎች አንዱ ዲኬኤ እንደሚያጋጥማቸው ይጠቁማል።
ይህ አስደንጋጭ እና አሳሳቢ ቁጥር ነው። በሰለጠነው አለም የዚህ ህመም መጠን ከ1 ፐርሰንት ባያልፍም ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ብዙ ህመምተኞች በዲኬኤ እየተጠቁ ይገኛሉ።
የጤና አገልግሎት ውስን መሆንና ስለስኳር በሽታ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን ለዚህ ተጠያቂ ናቸው። ይህም የግንዛቤ ጉድለት ብዙ የስኳር ታማሚዎች ምርመራ እንዳያደርጉ ፤ ህክምና እንዳይከታተሉ ያደርጋል። በሽታው እስኪብስ ድረስም የሚቃወሙ ጥቂቶች አይደሉም። የህመም ምልክት እስኪታይ ያልታመመ የማይመስላቸው ቤተሰቦችም ፤ መድሀኒት ለመውሰድ ያከላክላሉ።

ለዚህም እንደ ዲኬኤ ህይወትን አደጋ የሚጥሉ ህመሞች እስኪያጋጥሙ ፤ ህክምናን ችላ ይላሉ። ይህ ትግል እና ክርክር ከሞት ጋር እንደሆነ ቢያውቁ ግን ፤ አብዛኞቹ ፈጽመው እንዲህ አያደርጉም።
ስኳር ህመም ያልበት ልጃቸው ፤ የዲኬኤን ምልክቶች አሳይቶ እንደ አብርሀም ለሳምንታት የሚያቆዩ ጥቂቶች አይደሉም። አብዛኞቹ የልጃቸው ህይወት አደጋ ላይ እንደነበር የሚረዱት ፤ በድንገተኛ ሲታከም ነው።
ይህ ቸልተኝነት ዳፋው እጅጉን ከባድ ነው።
🔥 ምልክቶቹን ለይቶ ማወቅ ግድ ያላል።
የህመሙን ምልክቶች ማወቅ አስፈላጊ ነው።
ያስተውሉ የመጀመሪያው መከላከያ የተሟላ ግንዛቤ ነው ።

የዲኬኤ የተለመዱ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው።
የማይረካ የውሀ ጥማት
አብዝቶ/ ቶሎ ቶሎ መሽናት
የማቅለሽለሽ ስሜትና ፣ ማስመለስ
የሆድ ሕመም
ፈጣን እና ጥልቅ አተነፋፈስ
ድካም
ግራ በመጋባት ወይም እንቅልፍ ማብዛት
ትንፋሽ ደስ የሚል የፍራፍሬ ሽታ መኖር
እነኝህን ምልክቶች ካዩ ፤ ፈጽሞ አይዘናጉ!
ያስተውሉ የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ቀደም ብሎ ማወቅ ሕይወት ያድናል።
አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ያስፈልገዋል። ወደ ቅርብ የጤና ተቋም ይዘው ይሂዱ።
🛡️ ፈጽሞ መከላከል የሚቻል ህመም ነው! እንዴት?

ይህ ህመም በቁጥጥር ስር ባልዋለ የስኳር አማካኝነት የሚመጣ ህመም በመሆኑ ፤
የስኳር በሽተኞች የኢንሱሊን እና በአፍ የሚወሰዱ የስኳር በሽታ መድሐኒቶችን ሳያቁርጡ በስርአት መውሰድ ይኖርባቸዋል።
በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠንን መከታተል ያስፈልጋል።
ውሀ መጠጣት።
አልኮል መጠጣት እና ሲጋራ ማጨስ አይመከርም።
ማንኛውንም የኢንፌክሽን ህመሞችን ጊዜ እንዳይሰጡ። ወዲያውኑ በመታከም ይቆጣጠሩ። ካልታከሙ ለዲኬኤ ያጋልጣሉ።
ትክክለኛና የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖርዎ ፤ በባለሙያ እና በጤና ተቋማት የሚለቀቁ የህክምና መረጃዎችን ይከታተሉ።
🚨 የበሽታው ምልክቶች ካዩ ምን ማድረግ አለብዎት?
ምልክቶቹን በራስዎ ወይም በሌላ ሰው ላይ ካስተዋሉ
አፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ጥረት ያድርጉ። በአቅራቢያ ወዳለ የጤና ተቋም ይሂዱ ።
ራስዎን ለማከም ወይም ሕክምናውን ለማዘግየት ፈጽሞ አይሞክሩ።
አይጨነቁ። ረጋ ይበሉ። ሆኖም ግን አፋጣኝ እርምጃ ይውሰዱ።
Comments