የሐሞት ጠጠር ምልክቶቹና ህክምናው
- Zebeaman Tibebu
- Sep 21
- 3 min read
መቼም አብዛኞቻችን ሀሞት እናውቃለን?
ሀሞት በባህላችን በንግግራችን በእምነታችን ጋር የተለያየ ትርጉም አለው።
ሀሞትን በተለምዶ ኮምጣጣነትን ፣ ጀግንነትን ለመግለጽ እንጠቀመዋለን። 'ሀሞቴ ፈሠሠ' የሚለውን ቃል እንኳን ተነሳሽነት ማጣታችንን ለመግለጽ ፤ በንግግራችን መሀል እንጠቀማለን።
አባቶቻችንም ጮማ የበዛበት ጥሬ ስጋ ሲበሉም እንዲስማማምቸው በሀሞት ይበላሉ።
በህክምናስ ሀሞት ምንድነው?

ሀሞት ከፈረሰ የቀይ የደምህዋስ በጉበት ውስጥ የሚሰራ ፤ ሰውነታችን ምግብ ለመፍጨት የሚጠቀመው ውህድ (ኤንዛይም)ነው። ይህም ውህድ በጉበት ቢመረትም ፤ ስራው አንጀት ላይ ነው። ታድያ ስራ እስኪውል ድረስ በጊዜያዊነት ከጉበት ስር ባለ ከረጢት ውስጥ ይከማቻል። ለዚህም ይህንን ከረጢት የሀሞት ከረጢት እንለዋለን።
ታድያ ሀሞት በዋነኝነት የሚሰራው ቅባት/ ስብ ለመፍጨት ነው። ቅባት ያለው ምግብ በብዛት ሲበላ ሰውነት በከረጢት ያስቀመጠውን ይህን ሀሞት ይጠቀማል።
ታድያ እንዴት እዚህ ከረጢት ውስጥ ጠጠር ሊገኝ ቻለ?
ዛሬ ስለ ሀሞት ጠጠር በጥልቀት እናነሳለን።
የሀሞት ጠጠር ምንድነው?
ይሄ ጊዜያዊ ማከማቻ የሆነው የሀሞት ከረጢት ውስጥ ፤ ጠጠር ሲከማች የሀሞት ጠጠር ይባላል። እነኝህም ጠጠሮች መጠናቸው ይለያያል። አንዳንዶቹ እንደ አሸዋ ደቃቅ ሲሆኑ ፤ ሌሎች ደግሞ ብይ ያህል ሊገዝፉ ይችላሉ። መልካቸውም እንደመንስኤያቸው ይለያያል።

ታድያ የሀሞት ጠጠር እንዴት ይፈጠራል?
አንድ ወፍራም ውህድ/ፈሳሽ ውሀ ለረዥም ጊዜ ረግቶ ሲቆይ ፤ ዝቃጭ ወይም አሸዋ እንደሚፈጥረው ሁሉ ፤ የሀሞት ሚዛን ሲዛባ የሀሞት ጠጠር ይፈጠራል። ይህም እንዲፈጠር የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። በዚህ ላይ ተመስርተን በሶስት ልንመድበው እንችላለን።

ሀሞት ውስጥ በኮሌስትሮል መብዛት የሚመጣው የኮሌስትሮል ጠጠር አንዱ ሲሆን ፤ በመልኩም ነጭ ነው።
ለሀሞት ምርት ግብአት የሚሆነው የቀይ የደም ህዋስ በብዛት ሲሞት አልያም የጉበት ጠባሳ ካለ ጥቁር የሀሞት ጠጠር ይፈጠራል።
ኢንፌክሽንን ተከትሎ የሚፈጠረው የሀሞት ጠጠር ደግሞ ቡናማ ቀለም ይኖረዋል።
ታድያ ይህ ጠጠር ከአንጀት ጋር በሚያገናኘው ቀጭን ቱቦ ለማለፍ ሲሞክር በሀሞት ጠጠር ጊዜ የሚታወቀው ከባድ ህመም ይሰማል።
የሀሞት ጠጠር አጋላጭ መንስኤዎቹም የሚከተሉት ናቸው።
ዕድሜ መጨመር(ከ40 ዓመት በኋላ አደጋው ይጨምራል)፣
ከመጠን ያለፈ ውፍረት እና ፈጣን ክብደት መቀነስ፣
የስኳር በሽታ ፣
የደም ስብ/ኮሌስትሮል ችግርና (dyslipidemia)፣
እርግዝና ይጠቀሳሉ።
ሴቶች ደግሞ በተፈጥሮ የኢስትሮጅን ሆርሞን ስላላቸው ፤ ተጋላጭነታቸው ከወንዶች የበለጠ ነው። የኢስትሮጅን መብዛት አልያም ኢስትሮጅን ያለበት መድሀኒት ወይም ግብአት መውሰድም ተጋላጭነትን ይጨምራል።
ነባራዊ ሁኔታ/ ስርጭቱ
በቅርብ ጊዜ የተደረጉ የሐተታ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የሀሞት ጠጠር ከ ከ6-10% የሚሆነው የአለም ህዝብ ያጠቃል። በይበልጥም በሴቶች ይታያል።
በኢትዮጵያ ያሉ ጥናቶችም የሀሞት ጠጠር ስርጭት ከ 5 እስከ 8 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል ይጠቁማሉ። በተለይም ስርጭቱ ከ 30ዎቹ እስከ 50 ዎቹ የእድሜ ክልል ላይ ያሉ ሴቶች ላይ ይታያል።
ማን ይታመማል - እና ማንስ ህመም አይሰማውም?
ግራ የሚያጋባው ነገሩ ይህ ነው!
አንዳንዶች የሀሞት ጠጠር ኖሮባቸው ምንም ህመም ሳያሳዩ ለአመታት ሲቆዩ ሌሎች በሀሞት ጠጠር ህመም አብዝተው ይሰቃይሉ። ለምን እንዲህ እንደሚያጋጥም በስርአት አይታወቅም።
የሐሞት ጠጠር ምልክቶች

የሀሞት ጠጠር ሲኖርብዎ የሚሰማዎት ምልክቶች እኝህን ይመስላሉ።
ከእንብርትዎ በላይ በቀኝ በኩል/መሀል ላይ የሚሰማ ድንገተኛ ኃይለኛ የሆድ ቁርጠት ህመም ይሰማል። ይህ ህመም ከሆድዎ አልፎ ወደ ጀርባዎ እና ወደ ቀኝ ትከሻዎ ሊሄድ ይችላል። ብዙ ጊዜ ይህ ህመም የሚሰማዎ ቅባት የበዛበት ምግብ ከበሉ በኋላ ነው።
ሀሞት ጠጠሩ ላይ ተደርቦ የሀሞት ከረጢት መቆጣት በሽታ ( Acute Cholecystitis) ሊይዝዎ ይችላል። ይህን ጊዜም የማያቋርጥ ህመም፣ ትኩሳት፣ ምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ድካም በተጨማሪ ሊሰማዎ ይችላል። ይሄኔ አፋጣኝ የሆነ ህክምና ያስፈልጋል።
የመውጫ ቱቦን ከዘጋ የቆዳ እና የአይን ቢጫ መሆን ምልክቶችን ሊያሳይም ይችላል።
ሽንትም ሊጠቁር ፤ ሰገራም ሊነጣ ይችላል።
ከዚህ ባሻገር ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክና የምግብ ፍላጎት መቀነስ ሊታይ ይችላል።
እንዲሁም ለሌሎች በሽታዎች ሊይጋልጥ ይችላል። ለምሳሌ የቆሽት መቆጣት፣ የሀሞት ቱቦ መቆጣት፣ ወ.ዘ.ተ..
ምርመራውና ህክምናው
እንደ ሀሞት ጠጠሩ ሁኔታ የ አልትራሳውንድ ምርመራ ፣ ኢራሲፒ (ERCP)፣ ኤምአር ሲፒ (MRCP)፣ የ ኤም አር አይ (MRI) ምርመራዎች ሊታዘዙ ይችላሉ።

እነሱንም ለማገዝ የደም ምርመራም ይደረጋል።
ህክምናውም እንደአለው ምልክት ይወሰናል።
ምንም ምልክቶች ከሌሉ /ጠጠሮቹ መጠነኛ ከሆኑ/ ሀሞት ከረጢት ካልተቆጣ ፤ ቀዶ ጥገና አያስፈልግም። የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ብቻ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
ምልክቶች ካሉ ፣ ሀሞት ከረጢት ከተቆጣ ፣ ትላልቅ ድንጋዮች ከሆኑ ፣ ኢንፌክሽን ካለ ፣ ከጎን ያሉ አካላትም ከተጎዱ/ከተቆጡ ፣ የሀሞት መውጫ ቱቦ ከተዘጋ አፋጣኝ ህክምና ያስፈልጋል። የሀሞት ከረጢት በቀዶ ጥገና እንዲወጣ ይደረጋል።
መከላከል- የተሻለው አማራጭ

የሀሞት ጠጠር እንዳያጋጥም ለመከላከል አልያም ፤ ያለብዎ የሀሞት ጠጠር እንዳይገዝፍ እንዲህ ያደርጉ።
ጤናማ ክብደትን ይጠብቁ። ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች አያዘውትሩ።
የአካል እንቅስቃሴ ያድርጉ።
አትክልት እና ፍራፍሬ አብዝተው ይመገቡ።
የደምዎን የስኳር መጠን እና የኮሌስትሮል መጠን ይቆጣጠሩ።
መደበኛ የጤና ምርመራ ያደርጉ። ህመም አልተሰማዎትም ማለት የሀሞት ጠጠር የለብዎትም ማለት አይደለም።
የጤና ግንዛቤዎን ያሻሽሉ። በሆስፒታሎች አልያም በጤና ባለሙያዎች ብቻ የሚለቀቁ የጤና ትምህርቶችን ይከታተሉ።
ያስተውሉ!
ለሀሞትዎና ለጉበትዎ ጤና ቦታ ይስጡ ። ታመው እስኪመጡ አይጠብቁ።
ምልክቶቹን ካስተዋሉ አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ይፈልጉ።
መዘግየትዎ በሽታው እንዲወሳሰብ ያደርገዋልና በቅድሚያ ህክምና ያድርጉ።




Comments