top of page

ስለ ማይግሬን ራስምታት ማወቅ ያለብዎ

ያልታሰበው ውሎ


እንደዚህ አይነት ቀን ቢያሳልፉስ ...


አዘቦት ቀን ነው እንበል። የእለት ተግባርዎት ላይ ተጠምደዋል።


ታድያ ሰሞኑን የነበረብዎት የስራ ጫና ሆነ ማህበራዊ ውጥረት ፤ በድንገት ቀኑን ወደ አልታሰበ አቅጣጫ ቢወስደውስ?


ቡና አብዝተው መጠጣትዎ ፣ ጠንካራ ሽታ መሽተቱ፣ ከፍተኛ ድምጽ መስማትዎ ፣ ደማቅ ብርሀን ማየትዎ አልያም ፣ ከባድ ቅዝቃዜ መኖሩም ይህንን አዙሪት ሊያስጀምር ይችላል። ድንገት ምግብ ሳይበሉ ከቆዩም እንዲሁ።


ታድያ ሲጀምር ድካም፣ ደስ የማይል ስሜት(መክበድ)፣ የባህሪ ለውጥ፣ ሀሳብ መበተን አይነት ሊሰማዎት ይችላል። ራስ ቅልን /ማጅራትዎን ጨምድዶ ሊይዝዎት ይችላል። እይታዎ ሊረበሽ አልያም ብዥ ሊልብዎም ይችላል።


ይህ ማኮብኮቢያው እንጂ ዋነኛ የበሽታው ምልክት አይደለም።  ይሄ የማስጠንቀቂያው ደውል ነው።

ትንሽ ቆይቶ ከዓይንዎ ጀርባ እንደመርፌ የሚጠረቁስ ህመም ሊሰማዎት፣ በከባዱ ሊያቅለሸልሽዎ ፤ ከማቅለሽለሽም አልፎ ሊያስታውክዎ ይችላል። ብርሀን መቋቋም ያቅትዎታል። ጮክ ያለ ድምጽም እንዲሁ።


እነኝህ ግን አጃቢ ምልክቶቹ ናቸው።

 

ከእነኝህ ጀርባ የሚሰነጥቅ አልያም የሚቀጠቅጥ (throbbing headache) አይነት ከባድ ራስ ምታት አለ። የማያቆም እረፍት የሚነሳ ራስ ምታት! ሀሳብ መሰብሰብ ፈጽሞ ያዳግትዎታል።

ree

ይህ የመጨረሻው ነው ብለው ካሰቡ ተሳስተዋል!

 

ስልክ ሲጠቀሙ የስልኩ ብርሀን ከጨመረ ፤ ከባድ ድምጽ ከሰሙ ፣ ታክሲ ውስጥ ተሳፋሪ ያደረገው ሽቶ ጠንካራ ጠረን ካለው ፤ ህመሙ እጥፍ ድርብ ይሆናል።


ቀንዎ በሙሉ በድርድር ይሞላል።  ሁሉ ነገር በቋፍ ነው ያለው። ቡና ከጠጡበትማ፤ አይታሰብም።

 

ይህ ተራ ራስ ምታት አይደለም!

ከዛ ሽሽት ይጀመራል! ከህመሙ ሽሽት! ወዴት?


ወደ ጨለማ ክፍል። ወደ መኝታ። ወደ ዝምታ መሸሽ። ብርሀን፣ ድምጽና እንቅስቃሴ ወደሌለበት ማፈግፈግ። 


ሁሉን ትቶ ለማገገም ከአለም ለጊዜው መመሸግ።


ከሰአታት በኋላ ህመሙ እየቀነስ ይመጣል። በጭጋግ የተከለለው እይታ ሆነ ትኩረት እያዘገመ ይመለሳል።

 

ይሄ ግን ጊዜያዊ ነው!

ጠንካራ ጠረን ፣ ከባድ ድምጽ አልያም እንቅልፍ ማጣት በቅጽበት ይህንን አዙሪት ዳግም ያስነሳል።


ቀድመው መቆጣጠር ካልቻሉማ ፤ ጉዞው ቁልቁለት ነው!

 

በዚህ መሀል ፣ ከማህበራዊ ህይወት ራስዎን ያገላሉ። ስራ ይስተጓጎላል።

 

ይህ ለተወሰኑ ሰአታት አልያም ለአንድ ቀን ከሆነ ፤ ላያሳስብዎ ይችል ነበር። ሆኖም ግን ደጋግሞ የሚመጣ ለቀናት የሚቆይ ቢሆንስ?


ይህ የማይግሬን ታማሚዎች ያልታሰበ ውሎ ነው። በድንገት ተቀስቅሶ ቀናችውን የሚያቃውስ ፤ ህይወታቸውን የሚያስተጓጉል ከባድ ራስ ምታት ነው።

 

ማይግሬን ምንድነው?

ree

ማይግሬን "ራስ ምታት ብቻ" አይደለም። ይህ የነርቭ በሽታም ነው። በአለም ዙሪያ ከአንድ ቢሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በማይግሬን እንደሚጠቁ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ስርጭቱም ባለፉት 30 አመታት ውስጥ ጨምሯል። በየአመቱም በመቶ ሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ያስተጓጉላል።


እንደየጥናቶች ቢለያይም በኢትዮጵያ ስርጭቱ ከ 3 በመቶ እስከ 18 በመቶ ይደርሳል። ጥቂት የማይባሉ የማይግሬን ታማሚዎች ፤ በሽታው እንዳለባቸው እራሱ ላያውቁ ይችላሉ። በተለይ የህክምና እርዳታ ውስን በሆነበት በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ደግሞ ይህ ቁጥር ከፍ ሊል ይችላል። በአዲስ አእበባ የተደረገ የማህበረሰብ ጥናት በበኩሉ ፤ ከ5 ሰዎች አንዱ የራስ ምታት ህመም ሲኖርበት ፤ ከዚህ ከፊሉ የማይግሬን በሽታ ተጠቂ መሆኑን ይጠቁማል። ይህ ስርጭት ከፍተኛ ነው።  



ምልክቶቹ


  • ማስጠንቀቂያ ምልክቶቹ፡ አንዳንድ ጊዜ ከሕመሙ ከ 5 እሰከ 60 ደቂቃ ቀድመው የሚታዩ ምልክቶች ሊኖሩ ይችላሉ። እነኝህ ህመሙ መቀስቀሱን ማመላከቻ ናቸው። እንደማንቂያ ደውል የማይግሬን ራስ ምታት ሊጀምር መሆኑን ይጠቁማሉ። በብዛት የሚታዩት ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው።

    • የማየት ችሎታ መቀነስ/ የእይታ መደብዘዝ፣

    • እይታ መሀል የሚኖሩ ተምዘግዛጊ መስመሮች፣ ብልጭልጭ ነገሮች

    • ሰውነት ላይ መደንዘዝ፣ መብላት፣ ማቃጠል፣ መጠዝጠዝ፣ መቆጥቆጥ

    • ቃላት መጥፋት

    • ባህሪ ለውጥ

    • ድካም 


የማይግሬን ህመምን ተከትሎ ሊመጡ ከሚችሉ የእይታ ለውጦች አንዱ
የማይግሬን ህመምን ተከትሎ ሊመጡ ከሚችሉ የእይታ ለውጦች አንዱ
  • ዋነኛ ምልክቶቹ

    • ከመጠነኛ– እስከ ከባድ ራስ ምታት። ራስ ምታቱ የሚቀጠቅጥ/የሚጠዘጥዝ (በስከንዶች ውስጥ ከፍ ዝቅ እያለ የሚዋዥቅ) አልያም የሚሰነጥቅ አይነት ሊሆን ይችላል። ህክምና ካልተደረገለት ህመሙ ከ 4 ሰአት አንስቶ እስከ 3 ቀን ሊቆይ ይችላል።

    • ይህም ራስ ምታት በተለመዱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችም ሊባባስ ይችላል። 

    • ማቅለሽለሽ/ማስመለስና እንዲሁም ብርሃን/ድምፅ መቋቋም አለመቻል አብሮት ሊኖር ይችላል። አንዳንድ የማይግሬን አይነቶች ላይ እነኝህ ምልክቶች ብቻ (እይታ መለውጥና ድምጽ አለመቻል ብቻ) ሊታዩ ይችላሉ።


  • ከህመሙ በኋላ የሚታዩ ምልክቶች

    • ከህመሙ በኋላ  ለሰአታት ድካም ሊኖር ይችላል። ከዚህም ባሻገር የሀሳብ ጭጋት/ ትኩረት ማጣት ሊኖር ይችላል።

 

ለምን ያጋጥማል?


የማይግሬን በሽታን ሳይንስ ሙሉ በሙሉ አልተረዳውም። ሆኖም ግን የማይግሬን ራስ ምታት ከነርቭ መቆጣት እና ከአንጎል አስራር ለውጥ ጋር ተያያዥነት እንዳለው ጥናቶች ይጠቁማሉ። ለበሽታውም አጋላጭ መንስኤዎች የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው።


  1. ጀነቲክስ/ዘረመል፡ የማይግሬን ህመም ያለበትየቤተሰብ አባል ካለዎ፤ የማይግሬን ህመም የማጋጠም እድሉ ከፍተኛ ነው።

  2. የሆርሞን ለውጥ፡ ማይግሬን ከሆርሞን ለውጥ ጋር ተያይዞ ሊከሰት ይችላል። የወር አበባ ኡደትን ተከትሎ ያለው የሴቶች የኢስትሮጅን ሆርሞን መዋዠቅ ማይግሬን እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል። ለዚህም ሴቶች ወር አበባ በሚያዩባቸው ጊዜያት ላይ ማይግሬን ተደርቦ ሊታመሙ ይችላሉ።

  3. የነርቭ አሰራርን የሚለውጡ ማንኛውም ክስተቶች ማይግሬን ሊያመጡ ይችላሉ። ለምሳሌ ጭንቅላት ላይ የሚደርስ ጥቃትን ተከትሎ የሚያጋጥም ለውጥ ማይግሬን ሊያመጣ ይችላል።


ቀስቃሽ አካላት


ከላይ የተጠቀሱት ለማይግሬን ያጋልጣሉ። ቢሆንም ማይግሬን ራስ ምታት እንዲያጋጥም ፤ ቀስቃሽ አካላት ያስፈልጋሉ። እነኝህ ቀስቃሽ አካላት ሰውነት ላይ የሚፈጥሩት ለውጥ ፤ የነርቭ መቆጣት እንዲጨምር ፤ ማይግሬን ራስ ምታት እንዲከሰት ያደርጋል። በጣም የተለመዱት ማይግሬንን የሚያስከትሉ ቀስቃሽ አካላት የሚከተሉት ናቸው።


ree
  1. የእንቅልፍ መዛባት፣

  2. በቂ ውሀ አለመጠጣት /ሰውነት ውስጥ ውሀ ማነስ

  3. መራብ / በቂ ምግብ አለመመገብ

  4. ውጥረት/ጭንቀት

  5. የስሜት ሕዋሶችን የሚፈትሹ ነግሮች

    • ደማቅ ብርሃን፣

    • ጠንካራ ሽታ፣

    • ጮክ ያለ ድምጽ

    • የአየር ለውጥ 

  6. ህመም ማስታገሻ  መድኃኒቶችን አብዝቶ መጠቀምም ፤ ይህንን ሊያስከትል ይችላል። ለዚህም የማይግሬን ታማሚዎች የሚወስዷቸውን ማስታገሻ መድሀኒቶች እና የራስ ምታቱን ለውጥ በማስታወሻ ቢመዘግቡ ይመከራል።


የመፍትሔ አቅጣጫዎችስ ?


ጊዜያዊ የማይግሬን ህመም ለማሻሻል እና ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት የምንጠቀማቸው የህክምና አማራጮች ይለያያሉ።


  • ለአጭር ጊዜ ከ ዳይክሎፌናክ እና ፓራሴታሞል ጀምሮ ህመም ማስታገሻ መውሰድ ይችላል። እንደ ህመሙ እና ምላሹ የሚወሰዱት ማስታገሻዎች ሊለያዩ ይችላሉ። የትውከት እና ማቅለሽለሽ መከላከያ መድሀኒትም ሊያስፈልግ ይችላል።


ይህ ግን የህመሙን ምልክት መቀነስ እና ጊዜያዊ ማስታገስ ላይ ያተኮረ ህክምና ነው። ለዚህም መፍትሔው ጊዜያዊ ነው።

  • ዘላቂ መፍትሔ ከፈለጉ ፤ በቅድሚያ ዶክተርዎን ያማክሩ። እንደአስፈላጊነቱ አይቶ ህመሙን እንዳይቀሰቀስ የሚያደርጉ መድሀኒቶች ሊያዝልዎት ይችላል።  እንደ ፕሮፕራኖሎል ያሉ የሚዋጡ ፤ አልያም ነርቭን የሚቀሰቅሱ አማራጮች አሉ።

 

ማንኛውም ሰው ሊያደርጋቸው የሚችላቸው  ተግባሮች 


  1. በመጀመሪያ ልማዶችን ይገንቡ።

    • የሚተኙበትን ፤ ከእንቅልፍ የሚነቁበትን ሰአት ተመሳሳይ ያድርጉ። በቀን ቢያንስ ለስደስት ሰአት ይተኙ።

    • በቂ ውሀ መጠጣ ልማድዎ ይሁን። በቀን ከ 2 እስከ 3 ሊትር ውሀ ይጠጡ።

    • በሳምንት ከ 3 እስከ 4 ጊዜ መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ። ኤሮቢክ እንዲሁም የአንገት እና ጀርባ ጡንቻን የሚያጠነክሩ ስፖርቶች ይመረጣሉ።

    • የኢኮኖሚ ደረጃ ቢወሰንውም ፤ በቂ የተመጣጠነ ምግብ ለመመገብ ጥረት ያድርጉ።

  2. የእርስዎን ማይግሬን ህመም ቀስቃሽ አካላት ይወቁ። ማስታወሻ ይያዙ።

    • ምንድነው የሚቀሰቅሰው? ምግብ፣ እንቅልፍ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ ወ.ዘ.ተ... ይመዝግቡ። 

    • ስንት ሰአት ላይ ተቀሰቀሰ? አሁንም ይመዝግቡ።

    • ምንስ መድሀኒት ወሰዱ? ምንስ ለውጥ አመጣ? ይህንንም ይመዝግቡ።



ree
  1. ከደማቅ ብርሀን እና ከከፍተኛ ድምጽ ይራቁ። ካስፈለገ የጸሀይ መነጽር ያድርጉ። የጸሀይ ኮፍያ ማድረግም ይችላሉ። ስክሪን ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ ይገድቡ። ጸጥታ የሰፈነበት ቦታ ጊዜዎን ያሳልፉ። ይረፉ!


  1. በህይወትዎ ያለ ውጥረትን ለመቀነስ ይሞክሩ። በየእለቱ ዘና የሚያደርጉ ተግባራትን ይፈጽሙ። 


  2. የጤና ባለሙያ አማክረው እንዲያግዝዎ መውሰድ የሚችሏቸው መድሀኒቶችም አሉ። የቪታሚን ቢ ፣ የማግኒዚየም ማዕድን ያለባቸውን እንክብሎችን እንደ ደጋፊ መውሰድ ይችላሉ። እነኝህም መድሀኒቶች የማይግሬን ራስ ምታት የመቀስቀስ እድልን ይቀንሳሉ።


ያስታውሉ

ተግባራዊ ለውጥ በማምጣት ጤናዎን ይጠብቁ።


ማይግሬንን እንደ ተራ ራስ ምታት ወስደው ፈጽመው እንዳይዘናጉ።


ፈጠን ብሎ ጊዜያዊ ህመም ማስታገሻ ህክምናን ማድረግ ህመሙን ቢያጠፋም፤ ቋሚ የህክምና አማራጮችን አብሮ መውሰድ ያስፈልጋል።


እርሶም በበኩልዎ ልማድዎን መለወጥ ፤ ባህሪዎን ማስተካከል ፤ እንዲሁም የህመሙ ማስታወሻ መውሰድ ያስፈልግዎታል።


ማይግሬን "ራስ ምታት ብቻ ነው" ብሎ ለሚያስብ ሰው ይህን አካፍል።

Comments


bottom of page