አለርጂ አለብዎ? እንዴት አወቁ?
- Zebeaman Tibebu
- 4 days ago
- 5 min read
ስለ አለርጂ ሰምቶ የማያውቅ አለ ማለት ዘበት ነው!
አብዛኞቻችን ወይ አለርጂ አለብን ፤ ወይ አለርጂ ያለበት ሰው እናውቃለን። ምናልባት አለርጂ የሚያስነሳብዎት ቀስቃሽ አካል ፤ እስከዛሬ ሳያጋጥምዎ ቀርቶ ቢሆንስ? ምናልባት አለርጂ ኖሮብዎት ፤ አለመስማማት ነው ብለው በቸልተኝነት አልፈውት ቢሆንስ?
ብዙዎች "አለርጂ አለብኝ" ወይም "አለርጂ የለብኝም" ከሚለው ባሻገር የተሟላ ግንዛቤ የላቸውም።
አለርጂን ለመከላከል ደግሞ ይህ ግንዛቤ እጅጉን አስፈላጊ ነው።
አለርጂ ምንድን ነው?
አለርጂ ቀለል አድርገን ስንወስደው የሰውነት መቆጣት ነው። ታድያ ግን እንደ ኢንፌክሽን የበሽታ አምጪ ተህዋሳትን ለማስወገድ የሚደረግ መቆጣት አይደለም።
ይልቁኑ ሰውነታችን ምንም ጉዳት የማያደርሱ እንግዳ አካላትን ፤ እንደ በሽታ አምጪ ተህዋሳት ሲረዳ የሚፈጠር ነው። እነሱን ለማስወገድ በሚያደርጉት ጥረት ሰውነታችን ይቆጣል። ሰውነታችንን እንዲህ የሚያስቆጡ እንግዳ አካላት ፤ በህክምናው አለርጀን ወይም አለርጂ ቀስቃሽ አካላት ተብለው ይጠራሉ።

እባብ ያየ በልጥ በረየ የሚባለው ይሄ ነው!
ከአለርጂ ጀርባ ያለውን ሳይንስ ማወቅ ከፈለጉ እነሆ፡
ሰውነት እነኝህ እንግዳ አካላት መቃወሚያ መርዞችን (IgE) ያመነጫል። ይህንን ጥቃት በፊት አውራሪነት የሚመሩት የማስት ህዋሳት እና ኢዮሲኖፊል የሚባሉት የበሽታ መከላከያ ህዋሳት ናቸው። እነኝህም ሰውነታችን እንዲቆጣ የሚያደርጉ ኬሚካሎችን (Histamine and cytokines) ያመነጫሉ። የእነኝህ ኬሚካሎች መለቀቅ የሚያመጣው መቆጣት በአለርጂ ጊዜ የምናያቸውን ምልክቶች ይፈጥራል።
የአልርጂ መቆጣት ግን መጠኑ ሊለያይ ይችላል።
አንዳንዲ እጅጉን ቀላል የሆነ መቆጣት ሲሆን ፤ ሌላ ጊዜ ህይወትን አደጋ ላይ የሚጥል ሊሆን ይችላል።
ስርጭቱ ምን ይመስላል?

እ.ኤ.አ በ2021 በዓለም ዙሪያ ወደ 260 ሚልዮን የሚጠጉ አስም ያለባቸው እንዲሁም ወደ 129 ሚልዮን የሚጠጉ ስር የሰደደ የቆዳ አለርጂ (አቶፒክ ደርማታይተስ / Atopic Dermatitis )ያለባቸው ሰዎች ነበሩ። አለርጂ ያለባቸው ሰዎች መጠንም እየጨመረ ይገኛል።
ታድያ አስም እዚህ ጋር ምን አገናኘው?
አስም ከ አለርጂ ጋር ከፍ ያለ ቁርኝት አለው። አስምን በአጠቃላይ በሁለት መክፈል ይቻላል፦
*የተለመደው በቀስቃሽ አካላት የሚነሳው የአለርጂ አስም እና
*ከአለርጂ ጋር ቁርኝት የሌለው አስም ተብሎ ሊከፈል ይችላል።
የአስም የተለመዱ ቀስቃሽ አካላት መሀል አቧራ ፣ ቅንቅን ፣ የቤት ውስጥ ብናኞች፣ የአበባ ብናኞች፣ ሻጋታ፣ የእንሰሳት ርጋፊ ይገለጻሉ። ሲቀሰቀስም ከአለርጂ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልክ የትንፋሽ ቧንቧዎች ይቆጣሉ ፤ ያብጣሉ ፤ ይጠባሉ። ይህም የመተንፈስ ችግር ይፈጥራል። ህክምናው ውስጥም የሰውነት መቆጣትን የሚያስታግሱ መድሀኒቶች አሉ። እንዲሁም ቀስቃሽ አካላቶቹን መለየት እና ማስወገድ ያስፈልጋል።
በኢትዮጵያ የሚታየው ሁኔታ ይህንን የዓለም አቀፍ ሁኔታ ያንፀባርቃል። በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶችም ስርጭቱ በሀገሪቷ እየጨመረ መምጣቱን ያሳያሉ። በምሥራቅ ኢትዮጵያ በፋብሪካ አከባቢ በሚኖሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ የተካሄደ አንድ ጥናት ከ አምስቱ አንዱ አለርጂ እንዳለባቸው ይጠቁማል። በባህርዳር የተደረገ ጥናት በበኩሉ 17.1% የሚሆኑ ሕፃናት አቶፒክ ደርማታይተስ እንዳለባቸው ያሳያል።
የአለርጂ ዓይነቶች
አለርጂን በተለያየ መንገድ ልንከፍል እንችላለን። ከዚህም መሀል በሚከተለው መንገድ ልንመድብ እንችላለን።

የመተንፈሻ አካላት አለርጂ - ይህ የአለርጂ አይነት በቅድሚያ የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃ ሲሆን ፤ በዋነኝነት በአየር ላይ በሚገኙ አካላት ይከሰታል። ለዚህም የአበባ ብናኝ ፣ ቅንቅን ፣ ሻጋታ ፣ የእንሰሳት ርጋፊ፣ ወ.ዘ.ተ... ይጠቀሳሉ። ከዚህም ጋር በተያያዥነት የሚገለጹት የአፍንጫ መደፈን እና እንደውሀ የሚፈስ ንፍጥ የሚያስከትለው አለርጂ ራይናይተስ (Allergic Rhinitis) እና አስም ይጠቀሳሉ።
የምግብ አለርጂ - አንዳንድ ምግቦች በውስጣቸው ያሉ ንጥረነግሮች አለርጂ እንዲከሰት ያደርጋሉ። እነኝህን ምግቦች ሲመገቡ ሰውነትዎ ክማሳከክ እና ሽፍታ ጀምሮ ለሕይወት አስጊ እስከሆነ መቆጣት ሊያሳይ ይችላል።
የቆዳ አለርጂ - ቆዳችን ከአንዳንድ አካላት ጋር ንክኪ ካለው ፤ አለርጂ ምላሽ ሊያሳይ ይችላል።ይህን ጊዜ የሚያሳክኩ ቀያይ ሽፍታዎች ፣ ስር ሰደድ የቆዳ ህመም (Atopic Dermatitis) ይታያል። ይህም ብዙ ጊዜ የሚከሰተው በሳሙናዎች ፣ በአንዳንድ እጽዋቶች/የእጽዋት ግብአቶች ፣ አንዳንድ ብረቶች እንዲሁም በእንደ ላቴክስ አይነት ውህዶች ነው።
የመድሀኒት አለርጂ- አብዛኛው የምናቃቸው መድሀኒቶች ፤ አለርጂ የማምጣት አቅም አላቸው። ሆኖም ግን ይህ አለርጂ የሚታይባቸው የተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸው። የጤና ባለሙያዎችም እነኝህን መድሀኒቶች ሲያዙ ይህንን የጎንዮሽ ጉዳት አስተውለው ነው። ምላሹም ቀለል ካለ መቆጣት እስከ ህይወት አስጊ ደረጃ ሊደርስ ይችላል።
ማወቅ ያለብዎ የተለመዱ አለርጂ አምጪ አካላት
ብዙ አይነት አለርጂ አምጪ አካላት ቢኖሩም ፤ የተለመዱት የሚከተሉት ናቸው።
🕷️ቅንቅን፡ እነዚህ በአቧራ ፣ በምንጣፍ ውስጥ ፣ በእንሰሶች ላይ እንዲሁም ፣ በቤት ውስጥ ባሉ እንጨቶች ዙሪያ የሚገኙ ጥቃቅን ፍጡሮች ናቸው። በተለይ ደግሞ እርጥበት አዘል አከባቢ ላይ ይኖራሉ። እነኝህም አለርጂ በማምጣት እጅጉን ይታወቃሉ። በተለይም አስምን፣ ሳይነስን ፣ አለርጂ ራይናይተስን ይቀሰቅሳሉ። ያብሳሉ።
🌸የአበባ ብናኝ፡ ንቦች የሚቀስሙት የአበባ ብናኝም አለርጂ ያስከትላል። ለዚህም አበባ በብዛት በሚያብበት በጸደይ ወቅት እንዲሁም ንፋስ አብዝቶ በሚነፍስባቸው ወራት ላይ እነኝህ የአበባ ብናኞች አየር ላይ ስለሚበዙ አለርጂ ያለባቸው ሰዎች ይቀሰቀስባቸዋል።

🦠ሻጋታ፦ ሻጋታም አለርጂ በመቀስቀስ ይታወቃል። በቤቶችና በሕንፃዎች ውስጥ የሚፈጠር እርጥበት አዘል ሁኔታ ፤ ሻጋታ እንዲያድግ ያደርጋል። ያደገው ሻጋታ ዘር/ብናኝ በቤቶች እና ቢሮዎች ባለ አየር ላይ ይስፋፋል። ይህም በአከባቢው ባሉ ሰዎች ላይ ተደጋጋሚ አለርጂ እንዲከሰት ያደርጋል።
🥚የምግብ አለርጂዎች፦ እነኝህ በብዛት የሚታወቁ ፤ ብዙ ፊልሞች ላይ ያየናቸው አለርጂ አምጪ አካላት ናቸው። ከእነኝህም መሀከል ኦቾሎኒ ፣ እንቁላል፣ የወተት ተዋጽኦዎች እንዲሁም የባህር ምግቦች ዋነኛ ተጠቃሽ ናቸው። እንደ ስንዴ ፣ አጃ እና የመሳሰሉት አይነት አዝዕርቶችም አለርጂ ሊያመጡ ይችላሉ። ይህም ውስጣቸው ባለው ግሉተን ከሚባል ንጥረ ነገር ጋር ይገናኛል።

ታድያ እንዴት ኢትዮጵያ ላይ በብዛት ኣናይም ?
ይህ ዘረመልን ጨምሮ ከተለያዩ ነገሮች ጋር ይያዛል። በአንድ በኩል በኢትዮጵያ ዋነኛ የምንመገበው አዝዕርት ጤፍ ሲሆን ፤ ጤፍ ደግሞ በውስጡ ይህ ፕሮቲን ስለሌለው ፤ ይህ አለርጂ ላለበቸው ሰዎች ተመራጭ ምግብ ነው። በቅርቡ በአለም ዙሪያ ተወዳጅነት እያተረፈ ያለው ከዚህ ጋር ተያይዞ ነው።
ለዚህም በኢትዮጵያ ይህ አለርጂ ያለባቸው ሰዎች ቢኖሩ ፤ የስንዴ ዳቦ እንደማይስማማቸው፤ እንደሚያማቸው የገብስ ዳቦ አልያም የጤፍ እንጀራ እንደሚመርጡ ይገልጻሉ። ሳያውቁት አለርጂ ምልክት የሚያሳየውን አካል በማስወገድ እራሳቸውን ያክማሉ።
🐝 Iየነፍሳት ንድፊያ - ንቦች ፣ ተርቦች እንዲሁም ሌሎች ተናዳፊ እንሰሳት ፤ ሲነድፉን የሚለቀቀው ኬሚካል ፤ ሰውነታችንን ያስቆጣል። የአለርጂ ምላሽ ያስከትላል።
🐾የእንሰሳት ብናኝ ፡ ከአንዳንድ የቤት እንሰሶች ሰውነት የሚረግፉ የቆዳ ቅንጣቶች፣ የጸጉር እርጋፊዎች ፣ ምራቆቻቸው እንዲሁም ሽንቶቻቸው አለርጂ ያመጣሉ።

ለዚህም ነው አንዳንድ ሰዎች የድመት አለርጂ ፤ ሌሎች የውሻ አለርጂ አለብኝ ሲሉ የምንሰማው።
የእንሰሳቶቹ ጥላቻ ሳይሆን ፤ እንሰሶች አጠገብ መገኘት ጤናቸውን አደጋ ላይ ስለሚጥል ነው።
አለርጂ እንዳለብዎ እንዴት ለይተው ይወቁ?
አለርጂ እንዳለብዎ ለማወቅ ፤ የአለርጂ ምልክቶች ለይተው መረዳት አስፈላጊ ነው። እንደ የሰዉ ፤ እንደ የአለርጂ አይነቱም ምልክቶቹ ቢለያዩም ፤ በይበልጥ የሚታዩት የተለመዱ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው።

የመተንፈሻ አካላት አለርጂ ካለብዎ በይበልጥ
ማስነጠስ ፣ ማሳል
አፍንጫ መታፈን
አፍንጫ ማሳከክ
ከአፍንጫ እንደ ውሀ የሚወርድ ፈሳሽ
አይንን ማሳከክ
አይን ውሀ መቋጠር ያስተውላሉ።
የቆዳ አለርጂ ካለብዎ በይበልጥ፦
ሽፍታ፣
እብጠቶች
ቆዳ መቅላት
ማሳከክ ያያሉ ።
የምግብ አለርጂ ካለብዎ በይበልጥ ፦
ማቅለሽለሽ/ ማስመለስ
ከንፈር፣ ምላስ ወይም ጉሮሮ እብጠት
የሆድ ህመም ሊያዩ ይችላሉ።
የአለርጂ ምልክቶቹ ከጠነከሩ አልያም ካየሉ ፤ የአናፍላክሲስ ምልክቶች ያያሉ።
አናፊላክሲስ የምንለው ምንድነው?
አናፍላክሲስ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚይጋጥም ከባዱ የአለርጂ ምልክት ነው። ይህም ለህይወት እጅጉን አስጊ ነው። በአፋጣኝ ህክምና ካልተደረገ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት ይዳርጋል። የአናፍላክሲስ ጠቋሚ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው።
·የትንፋሽ ማጠር/የመተንፈስ ችግር (አስም በሽተኛ ከሆነ ፤ የሚሳብ መድሀኒት ይውሰድ)
·የጉሮሮ እብጠት
·ደግም ግፊት መውረድ
·ራስን መሳት ያመጣል።
አለርጂ እንዴት ይታወቃል?
የቆዳ ምርመራ፦ የተለመዱ አለርጂ አምጪ አካላት ያሉበት መመርመሪያ ፤ ቆዳ ላይ ተደርጎ ፤ በሚታየው ምላሽ የትኛው አለርጂ እንዳለ መለየት ይቻላል።
የአለርጂ የቆዳ ምርመራ የደም ምርመራዎች- ለተጠረጠሩ አለርጂ አምጪ አካላት በተጋለጡ ጊዜ ፤ የእነሱ መቃወሚያ ኬሚካል (IgE) መጠንን በመለካት አለርጂ መኖሩን ማወቅ ይችላል።
የማስወገድ አመጋገብ- ይህ የምግብ አለርጂን ለመለየት የሚረዳ ብልህ የአመጋገብ ዘዴ ነው። ከህክምና ክትትል ጋር በማጣመር የሚጠረጠሩ አለርጂ አምጪ ምግቦችን አንድ በአንድ ከምግብዎ በማስወገድ የትኛው አለርጂ እንዳመጣ መለየት ይቻላል።
አከባቢዎን ይከታተሉ ፤ ይቆጣጠሩ። የተለመዱ አለርጂ አምጪ አካላትን ከአከባቢዎ በመቀነስ ፤ የሚያሳዩትን የአለርጂ ምልክቶች በመከታተል ፤ አለርጂ አምጪ አካሉን መለየት ይቻላል።
አለርጂን ለመከላከል ምን ያድርጉ?
ሁሉንም አለርጂ መከላከል ባይቻልም አንዳንድ እርምጃዎች በመውሰድ አለርጂ ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ መቀነስ ይችላሉ። ለዚህም የሚከተሉትን ያድርጉ።
አለርጂ ምልክቶችን ሲያዩ ዶክተርዎን አማክረው የአለርጂ መቃወሚያ መድሀኒቶችን (antihistamine, corticoseroid, immunotherapy, etc) መውሰድ ይችላሉ።
ከባድ አለርጂ ካለብዎ በራሱ የሚወጋ የኢፒነፍሪን አውቶማቲክ መርፌ(epipen/ epinephrine injection) ይዘው መንቀሳቀስ ይኖብዎታል። ምልክቶቹን እንዳዩ እራስዎን በአፋጣኝ መውጋት ይኖርብዎታል። አለርጂዎን የሚጠቁም መረጃ ይዘው መጓዝ ይኖርብዎታል።

የአለርጂ ዘላቂ ህክምና ያለብዎን የአለርጂ አይነት እና ቀስቃሽ አካል ለይቶ ከማወቅ ይጀምራል። ለዚህም የጤና ባለሙያ ያማክሩ። እላይ በተገለጹት መንገዶች መለየት ይቻላል።
የታወቁ/ የተለመዱ አለርጂ አምጪ አካላትን ከአከባቢዎ ያስወግዱ። አለርጂ ከሚቀሰቅሱ ንጥረ ነገሮች ራቁ።
የአከባቢዎን ንጽህና ይጠብቁ። አዘውትረው ያጽዱ። ከአቧራ፣ ከሻጋታ፣ ከእንሰሳት ያርቁ።
አቅሙ ካለዎ የአየር ማጽጃ በቤትዎ ይጠቀሙ። አየር ላይ ያሉ አለርጂ አምጪ አካላትን ሊያጣራ ይችላል።
በአለርጂ ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ ይኑርዎ። እንደዚህ አይነት የጤና ጽሁፎችን እንዲሁም ቪድዮዎችን ያንብቡ። ሆኖም ግን ያስተውሉ በጤና ባለሙያ የሚለቀቁ ፤አልያም በጤና ተቋማት የሚለቀቁትን ብቻ ያንብቡ።
ያስተውሉ
አለርጂን ችላ ማለት ሥር የሰደደ የጤና ችግር ያመጣል። ለሞት ይዳርጋል። ህይወትን ይበጠብጣል።
ምልክቶቹን ቀደም ብለን በመገንዘብ ፤ እንዲሁም የመከላከያ እርምጃዎችን በመውሰድ ፤ ተጽዕኖውን መቀነስ እንችላለን።
ይህን የጤና ችግር በመፍታት ረገድ የተሟላ ግንዛቤና ንቁ ሆኖ መቆየት ወሳኝ ነው።
Comments