ራሰ በራነት እንዴት ያጋጥማል? እንዴት እንከላከል?
- Zebeaman Tibebu
- Sep 15
- 5 min read
በአለም ዙሪያ ራሰ በርሀነትን ለማሰብ የተሰየሙ የተለያዩ ቀኖች አሉ። ያለፈው ቅዳሜ በአሜሪካ የተከበረው የብሄራዊ የመላጣነት ውበት ቀን ለዚህ ተጠቃሽ ነው። ለመሆኑ አክብረዋል?

እንዲሁም አለም አቀፍ የራሰ በርሀነት ቀን በፈረንጆች የኦገስት ወር ላይ የመጀመሪያ ቅዳሜ ይከበራል።
እነኝህ ቀናቶች ታድያ መላጣነትን የሚያሞግሱ ፤ መላጣነት ጉድለት ሳይሆን ውበት መሆኑን የሚያወሱ ቀናቶች ናቸው።
በሀገራችን ኢትዮጵያ ይህንን የሚያወሳ ቀን እስከ አሁን የለም። ቢኖርስ ያከብሩ ነበር?
ስለመላጣነት ያለዎት አስተያየት ምንድነው?
በመጀመሪያ ስለጸጉር እናውራ
ከልጅነታችን ጀምሮ ጸጉራችንን እንደማናወልቀው አክሊል አድርገን እናስበዋለን። ሳይንስ ጸጉርን እንደፕሮቲንክ ክር አድርጎ ቢረዳውም ፤ በአለም ዙሪያ ያሉ የተለያዩ ባህሎች ለጸጉር የሚሰጡት ትርጉም ሰፊ ነው።
በአሜሪካ የሚኖሩት ህንዶች ውስጥ ባለ ሶስት ጸጉር ቁጥርጥር ጥንካሬን እና የሀሳብ ጽናትን ያመላክታል። በኢሲያ ሀገራት እንዲሁም በህንድ ደግሞ ወደ መንፈሳዊ ህይወት ለመቅረብ ራስን ለማጽዳት ጸጉር መላጨት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ሀገራት ጸጉር እንደ አሰራሩ ፤ እድሜን ፣ የትዳር ሁኔታን እንዲሁም በማህበረሰብ ውስጥ የሚሰጥ ቦታን ያመላክታል። ወደ ጃማይካ እና ራስ ተፈሪ እምነት ትከታዮች ከሄድን ደግሞ የጸጉር ትርጉሙ እየሰፋ ይሄዳል።
ለዚህ ባህልና ኋላ ቀር አስተሳሰብ የተነሳ ለጸጉር የምንሰጠው እይታ ካለው ተፈጥሮአዊ ጠቀሜታ ያለፈ ነው። ለብዙ ወጣቶች ከማንነት ጋር ይያዛል። ለዚህም የጸጉር አቆራረጥ ፋሽን ፉክክሩም ቀላል አይደለም።

ወንዱም ዞማ ወገብ የደረሰ ጸጉር ያላት ሴት ፤ ሴቷም ጸጉሩ ሙሉ የሆነ ያልሸሸ ወንድ ይፈልጋሉ በሚል እሳቤ በወጣቶች ላይ ያለው ጫና ቀላል አይደለም። ይህ ግን የተሳሳተ ነው! መላጣነት/ራሰበራነት በራሱ ውበት አለው። ለዚህም በአለም ዙሪያ አማላይ ተብለው የተሰየሙ ታዋቂ ግለሰቦች ምስክር ሊሆኑ ይችላሉ።
በተሳሳተ አስተሳሰብ የተነሳ ፤ አንዳንዶች ፀጉራቸውን ማጣት ማንነታቸውን ከማጣት ጋር ሊያስተካክሉት ይችላሉ። ካለፉት አመታት አሁን የተሻለ አስተሳሰብ ቢኖርም ፤ ስለ ራሰ በራነት ያለ አስተሳሰብ አሁንም መስተካከል ያስፈልጋል። ለዚህም ነው እነኝህ ቀናት በአለም ዙሪያ ያስፈለጉት።
የእርስዎስ ጸጉርዎት መሳሳት ጀምሯል? ጸጉሩ መሳሳት የጀመረ ሰው ያውቃሉን?
እውነታው ግን ከዚህ የራቀ ነው። ራሰ በራነት በጣም ከተለመዱት የሕክምና ችግሮች አንዱ ነው። ከምን ጊዜም በላይ ሳይንስ አሁን በደንብ ተረድቶታል። በጥልቅ እንየው።
የራሰ በራነት ስርጭት
ራሰ በራነት ከተወለድን በኋላ የሚያጋጥም የጸጉር መሳሳት ሲሆን ፤ በአለም ዙሪያ እጅጉን የተለመደ ነው። እሱም በተፈጥሮ እድሜን ተከትሎ ፣ ኢንፌክሽኖችንና አንዳንድ በሽታዎችን ተከትሎ ፣ እንዲሁም እንደ ኪሞቴራፒ ያሉ ህክምናዎችን ተከትሎ ሊመጣ ይችላል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአለምአቀፍ ደረጃ
30 ዓመት ከሞላቸው 3 ወንዶች ውስጥ አንዱ የጸጉር መሳሳት ይጋጥመዋል።
50 ዓመት ከሞላቸው ወንዶች ውስጥ ግማሹ በራሰ በራነት ይጠቃሉ።
እንደወንዶች ባይሆንም ሴቶችም በዚህ ችግር ይጠቃሉ። እስከ 40% የሚደርሱ ሴቶች በጎልማሳነት እድሜያቸው ውስጥ ጸጉራቸው ይቀጭጫል። ይህም ደግሞ በይበልጥ የመውለጃ እድሜያቸው ያለፈ ሴቶች ላይ ይስተዋላል።

አንዳንድ ጥናቶች ራሰ በራነት በይበልጥ በ አውሮፓ እና በእስያ ህዝቦች ውስጥ እንደሚታይ ይጠቁማሉ። ሆኖም ግን በአፍሪካ ያለው የተሳሳተ የባህላዊ እይታ ፤ መጠኑ በስርአት እንዳይታወቅ አግዶት ሊሆን ይችላል።
ኢትዮጵያ ለዚህ ምርጥ ምሳሌ መሆን ትችላለች። የራሰበራነት ስርጭት የሚያሳይ ሀገር አቀፍ መረጃ ባይኖረንም ፤ ቁጥሩ ከፍ ያለ እንደሚሆን ለመገመት አያዳግትም። የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት አዋቂዎች በብዛት የሚያጋጥማቸው ከ ሆርሞን ጋር የሚያይዘው ሲሆን ህጻናት ደግሞ ከፈንገስ ኢንፌክሽን ጋር ተያይዞ የሚመጣው ነው። ሆኖም ግን ብዙውን ጊዜ ራሰ በራነት በስርአት ሪፖርት አይደረግም። አንድም እንደ እድሜ አመላካች ተደርጎ ስለሚወሰድ ሌላም ፤ ባለ ማህበረሰባዊ ጫና ብዙዎች አስፈላጊውን ህክምና አያደርጉም።
የፀጉር መሰረታዊ ሳይንስ
ስለ ራሰ በራነት ለመረዳት ስለ ፀጉር እድገት እናውራ። የፀጉር እድገት ዑደት አለው።
የመጀመሪያው የዑደት ደረጃ አናጀን (anagen) ይባላል። ይህም ጸጉር የሚያድግበት ደረጃ ሲሆን ከ 2 እስከ 6 ዓመት ሊፈጅ ይችላል። ትልቁን ጊዜ (90 በመቶ የሚሆነውን) ይወስዳል።
ሁለተኛው ደረጃ ካታጀን (catagen) ሲባል ፤ ይህም መሸጋገሪያ ደረጃ ተደርጎ ይወሰዳል። ይህም ከ 2 እስከ 3 ሳምንታት ሲፈጅ ፤ ያደገው ጸጉር እረፍት የሚወስድበት ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ጸጉር እድገት ያቆምና፣ የጸጉር ሥር መቀጨጭ ይጀምራል። ለቀጣይ ደረጃም ይዘጋጃል።
ሶስተኛውና የመጨረሻው ደረጃ ቴሎጅን (telogen) ይባላ። ይህም አድጎ የጨረሰው ጸጉር የሚረግፍበት ጊዜ ነው። መርገፉ መልካም ባይመስልም አስፈላጊ ነው። ያረጁት ጸጉሮች ሲረግፉ ፤ ከስር ለአዲስ ጸጉር ቦታ ይሰጣሉ።
በጤናማ የራስ ቅል ቆዳ ውስጥ፤ ይህ ዑደት ሁሌ ሚዛናዊ ነው።
ነገር ግን ራሰ በራነት ጊዜ ይህ ዑደት ይዛባል/ይቋረጣል። ምክንያቱም እንደ አይነቱ ሊለያይ ይችላል።
የራሰበራነት አይነቶች
የወንዶች አይነት ራሰበራነት (አንድሮጀነቲክ አሎፒሺያ / MPB/ Androgenetic alopecia)
ይህ አይነት ከዘረመል (ጂኖች) ጋር እንዲሁም ከ ወንድ ልጅ ሆርሞን ጋር (በተለይ DHT ከሚሰኘው) ጋር ያያዛል። ይህም ሆርሞን የጸጉር ሥር ላይ ባለው ተጽእኖ ጸጉር ይሳሳል። ያለው ተጽእኖ ቅድም ያነሳነው የጸጉር ማደጊያ ጊዜ (አናጀንን) ያሳጥራል። የጸጉር ውፍረቱ እጅጉን ይቀንሳል። እየባሰ ሲመጣም ጸጉር እጅጉን ቀጭጮ በተወለዱ ህጻናት ላይ እንደሚታየው አይነት ጸጉር ሊመስል ይችላል።

ይህን ጊዜ ጸጉር ይሳሳል። ሲታይ ጸጉር ወደውስጥ የሸሸ ይመስላል። አሸሻሹ ደግሞ አይነት አለው። በዋነኝነት የግምባር ጠርዝ ጋራ ያሉት ጸጉሮች እና የመሀል ጭንቅላት ጋር ያሉት ጸጉሮች ይሳሳሉ።
አኗኗርን ተከትሎ የሚመጣ ራሰበራነት (ቴሎጅን ኤፍለቪየም / Telogen effluvium )
ይህ ደግሞ ህመምን ፣ ውጥረትን ፣ አመጋገባችን ተከትሎ የሚመጣ ነው። አንዳንዴ የወለዱ ሴቶችም ላይ ሊታይ ይችላል። ሁሉም የራስ ቅል ጸጉሮች በአንዴ ወደ ሁለተኛው የእረፍት ደረጃ ይገባሉ። ለዚህም እላይ ያየነውን የጸጉር ኡደት በቀጣይ ሳምንታት/ ወራት ውስጥ ጸጉር በብዛት ይረግፋል።
ሲታይ ይህ አስደንጋጭ ቢመስልም ፤ አስፈላጊውን እርዳታ (ውጥረት መቀነስ ፣ ህመምን መታከም ፣ አመጋገብ ማስተካከልን) ተከትሎ ሊመለስ ይችላል። ዘላቂ አይደለም።
በበሽታ መከላከያ ስርአት የሚመጣ ራሰ በራነት (አሎፔሺያ ኤርያታ/ alopecia areata)
ይህ ደግሞ የራሳችን የበሽታ መከላከያ ስርዓት በስህተት የጸጉር ስሮችን ሲያጠቃ የሚፈጠር ነው። ለዚህም ጸጉር መሀል የሚታዩ ክብ መላጣ ቦታዎች ይኖሩታል። ከባሰ ሙሉ ጸጉር ሊረግፍ ይችላል።

የፈንገስ ኢንፌክሽን ተከትሎ የሚመጣ ራሰበራነት (ስካሪንግ አሎፒሺያ / Scarring alopecia)
ይህ በልጅነት እድሜ በሚያጋጥሙ ከባድ ኢንፌክሽኖች ፣ ባልታከሙ የራስ ቅል ቆዳ ፈንገስ ህመሞች የሚመጣ ነው። እነኝህ ኢንፌክሽኖች የጸጉር ስርን ሊያጠቁ ይችላሉ። የጸጉር ስርን በጣም ካጠቁ ጠባሳ ይፈጥራል። ጠባሳ ከፍጠረ ደግሞ ራሰበራነቱ ቋሚ ይሆናል። ለዚህም አፋጣኝ ህክምና አስፈላጊ ነው።
ህክምናን ተከሎ የሚመጣ ራሰበራነት (አናጀን ኢፍለቪየም / anagen effluvium)
ይህ እንደኬሞ ቴራፒ ያሉ ህክምናዎችን ተከትሎ የሚመጣ ራሰበራነት ነው። ስሙ እንደሚናገውም ጸጉር በሚያድግበት ደረጃ ላይ (አናጀን) ጊዜ በመድሀኒቶች የሚደርስበት ጥቃት ጸጉር እድገቱን እንዲቁረጥ ያደርጋል። መድሀኒቱን በወሰዱ በሳምንታት ውስጥ ጸጉር በብዛት ይረግፋል።
ውጤታማ ሕክምናዎች የትኞቹ ናቸው?
ነገሮች አስቸጋሪ የሚሆኑት እዚህ ጋር ነው። ራሰበራነት ለመቃወም የሚሰሩ የጸጉር ግብአቶች ብዙ ናቸው። በአለም ዙሪያ በቢሊየኖች ገቢ ያስገኛሉ። አምራች ድርጅቶቻቸውም እንደ ተአምራዊ መፍትሔዎች ያስተዋውቋቸዋል። በማህበራዊ ድህረገጽ ቢፈልጉም አሸን ያገኛሉ። ምስክርነት የሚሰጡ አስተዋዋቂዎችም ጥቂት አይደሉም
ብዙዎች ይወስዱዋቸዋል። ሆኖም ግን ምንም ለውጥ አያሳዩም። ዘላቂ መፍትሔ የላቸውም።
ሳይንስስ ምን ይላል?
በዘመናዊ ህክምና የሚሻሉ የሚባሉት አማራጮች እነሆ፡
ለ ወንድ አይነት ራሰ በራነት (MPB) ያሉ የህክምና አማራጮች
የሚኖክሲድል(minoxidil) ቅባት /ክሬም

ይህ በሰፊው ሲገኝ ፤ ለወንዶችም ለሴቶችም ግልጋሎት ላይ ሊውል ይችላል። ጥቂት የማይባሉ የጸጉር ማሳደጊያ ቅባቶችም በውስጣቸው ይህንን ውህድ አላቸው። ይህ ውህድ የጸጉር ስርን ያነቃቃል። ጸጉር እንዲወፍር ፤ ችምችም ብሎ እንዲያድግ ያደርጋል። የጸጉር መርገፍን ይቀንሳል።
ሆኖም ግን በየቀኑ ሳይቋረጥ መወሰድ አለበት። ከተቋረጠ የመጣው ለውጥ ይጠፋል። መወሰድ ያለበትም የሚቀባው ብቻ ነው። የሚዋጥ እንዳይወስዱ!
የሚዋጥ ፊናስተራይድ(Finasteride) እንክብል
ይህ ለወንዶች ብቻ የሚሆን ሲሆን ፤ የጸጉር ስርን የሚያሳሳውን ዲኤችቲ (DHT) የተባለውን ሆርሞን ይቀንሳል።
ለዚህም ራሰበራነትን ይገታል።ጸጉር በድጋሜ እንዲያድግ ያስችላል።
ሆኖም ግን የጎንዮሽ ጉዳት ስላለው የሕክምና ክትትል ያስፈልገዋል።
ፕሌትሌት ያለው የፕላዝማ መድሀኒት (platelet rich plasma)
ይህ ደግሞ ደም ውስጥ ያሉ የእድገት ኬሚካሎችን ይጠቀማል። እነኝህ ኬሚካሎች ከደምዎ ተወስደው ራስ ቅልዎ ላይ ጸጉርዎን እንዲያሳድጉ ይወጋሉ። ይህ ህክምናም አመርቂ ውጤት አሳይቷል። የጸጉር ውፍረት እና ብዛትን ያሻሽላል።

የጨረር ህክምና (low level laser therapy)
ይህ የጸጉር ስርን የሚያነቃቁ ጨረሮች ይጠቀማል። ከሌሎች ሕክምናዎች ጋር ከተጣመረ አስተማማኝ ከመሆኑም ባሻገር ተጓዳኝ ጉዳቱ ይቀንሳል።
የፀጉር ንቅለ ተከላ
ይህ ከለጋሽ የተወስዱ የጸጉር ስሮች ራሰበራነት ያጠቃበት ቦታ በቀዶ ጥገና የሚተከሉበት ነው። ጥሩ ጤና ላይ ያለ የፀጉር ስር ከተገኘ ውጤቱ አርኪ ነው። ሆኖም ግን የህክምናው ሂሳብ ውድ ነው። በዚህ የሰለጠነ የጤና ባለሙያ እና ልዩ የህክምና እቃዎች ይፈልጋል።

በበሽታ መከላከያ ስርአት ለሚመጣ ራሰ በራነት ያሉ የህክምና አማራጮች
ይህንን ለማከም የበሽታ መከላከያ ስርአትን የሚያረጋጋ መድሀኒቶችን በራሰበራነት የተጠቃው ስፍራ ላይ መውጋት ያስፈልጋል። ይህንን በተሻለ መልኩ የሚያክሙ አዳዲስ መድሀኒቶች አሁን ገበያ ላይ ውለዋል ።
ኢንፌክሽኖችን ተከትሎ ለሚመጣ ራሰ በራነት ያሉ የህክምና አማራጮች
የጭንቅላት የፈንገስ ህመም ላለበቸው ህጻናት የፀረ-ፈንገስ መድሃኒቶች (በአፍ የሚወሰድ ፣ የሚቀቡ መድሀኒቶች ) በመጠቀም መከላከል ይቻላል። ዘላቂ ራሰ በራነትን ለመከላከል ቀድሞ ህክምና ማድረግ አስፈላጊ ነው።
እንዴት ይከላከሉ?
መቼም የዘር ጉዳይን መቆጣጠር ባይቻልም ፣ አኗናር ለውጥ በማድረግ የጸጉርዎን ጤና መጠበቅ ይችላሉ። ለዚህም

የራስ ቅል ቆዳ ኢንፌክሽኖች ጠባሳ ከማምጣታቸው በፊት ቀድመው ህክምና ያድርጉ።
የተመጣጠነ ምግብ ይመገቡ። የሚመገቡት ውስጥ የ ፕሮቲን ፣ ብረት፣ ዚንክና ፣ ቫይታሚን ዲ ማነስ ጸጉር እንዲረግፍ ያደርጋል።
ጸጉርዎን ይንከባከቡ። ጸጉርዎን አጥብቀው አይሰሩ፣ ቁጥርጥር አይሰሩ። ደጋግመው የጸጉር ቀለም አይጠቀሙ። እንደ ፐርም ያሉ የጸጉር ኬሚካሎች አይጠቀሙ።
የራስ ቆዳ ንፅህና ይጠብቁ። ጸጉርዎን ካሳስከክዎ ወይም ቆዳዎ ከተላላጠ ችላ አይበሉ። ፎሮፎር ካለ ክምና ያደርጉ።
ላለብዎ በሽታ በአስቸኳይ ህክምና ያድርጉ። ከባድ ጭንቀት ፣ የታይሮይድ በሽታ፣ ወይም ከባድ ኢንፌክሽኖች ካለብዎ የህክምና እርዳታ ይፈልጉ።
ዶክተር ማየት መቼ ያስፈልጋል?
ለጸጉር መሸሽ ወይም ራሰ በራነት ሀኪም ጋር መሄድ የተለመደ አይደለም። ታድያ ግን መቼ ዶክተር ያማክሩ?
ጸጉርዎ በድንገት መርገፍ ከጨመረ
በአንድ ጀምበር ጭንቅላትዎ ላይ ክብ መላጣ ስፍራዎች ካዩ
ራስቅልዎ ከቀላ፣ ካስከከ፣ ወይም ህመም ካለው
በራስ የመተማመን ስሜትዎ እየቀነሰ ከመጣ ፣
ራሰበራነቱ በራሱ ስሜትዎን ከበጠበጠ ወይም ውጥረት ካመጣ
የጤና ባለሙያውም ቀላል የራስ ቆዳ ምርመራ እንዲሁም የደም ምርመራዎችን ሊያደርግ ይችላል። ይህም ለእርስዎ ተመራጭ ህክምናውን ለመለየት ያግዛልና ሀሳብ እንዳይገባዎ።




Comments