top of page

ብጉር እና መከላከያ መንገዶቹ

ብጉር በአብዛኞቻችን የለመድነው ፤ በብዛት የሚታይ የቆዳ በሽታ ነው። በአለም ዙሪያ ከ 200 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ያጠቃል። ከ16 እስከ 24 እድሜ ክልል ውስጥ ካሉ 5 ወጣቶች መሀል ፤ ቢያንስ አንዱ ብጉር እንደሚኖርበት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ለዚህም በተለምዶ የጉርምስና ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። ሆኖም ግን ከጉርምስና አልፎ ፤ እስከ ጎልማሳነት እድሜ ሊታይ የሚችል የቆዳ ችግር ነው።


ree

በኢትዮጵያ አገር አቀፍ መረጃ ባይኖርም ፤ ብጉር የተለመደ የቆዳ ችግር ነው። በመቀሌ አይደር ሪፈራል ሆስፒታል የተደረገ ጥናት ፤ ከቆዳ ታካሚዎች ውስጥ 19.4 በመቶ የሚገመቱት ብጉር አለባቸው። ከፊሎቹም ብጉር ማየት የጀመሩት ከ 17 አመታቸው ወዲህ ነው ። ከእነኝህም ውስጥ ጥቂት የማይባሉት ላይ ፤ ለመዋቢያ ከሚጠቀሟቸው ቅባቶች ጋር ግንኙነት አለው ። ይህም ቅባቶቹ ካላቸው ንጥረ ነገር ጋር ተያያዥነት አለው። ለምሳሌ ፡ ስቴሮይድ ያላቸው ቅባቶች ብጉር ያመጣሉ። ቆዳን ያሳሳሉ።


ታድያ ችግሩ የቆዳ ቢሆንም ፤ ጉዳቱ ግን በቆዳ ብቻ አይገደብም ። ውብት ላይ በሚኖረው እክልም ፤ የስነ ልቦና ችግር ሊያስከትል ይችላል። ከዚህም አልፎ የማህበራዊ ኑሮም ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል ።


ታድያ ግን በህክምና እርዳታ እና በባህሪ/ልማድ ለውጥ መቆጣጠር እና ማጥፋት ይቻላል።

ብጉር ምንድን ነው?


ብጉር  ከፀጉር ስር(hair follicles) እና የቆዳ ቅባት አምራች ህዋሳት (sebaceous glands) ጋር ተይያዥነት አለው። የሚከሰትባቸውን መንገዶች በአራት መክፈል እንችላለን።

የብጉር አከሳሰት ደረጃዎች፡ በግራ ያለው ምስል የቆዳ ቀዳዳ መደፈኑን ያመላክታል። መሀል ያለው ምስል የቆዳ ቅባት ክምችትን ያመላክታል። በስተቀኝ ያለው ምስል የተቆጣ ብጉርን ያሳያል።
የብጉር አከሳሰት ደረጃዎች፡ በግራ ያለው ምስል የቆዳ ቀዳዳ መደፈኑን ያመላክታል። መሀል ያለው ምስል የቆዳ ቅባት ክምችትን ያመላክታል። በስተቀኝ ያለው ምስል የተቆጣ ብጉርን ያሳያል።

አንደኛ፡ ቆዳ ወዛም መሆን ጋር ይያዛል። ይህም የቆዳ ቅባት አምራች ህዋሳት በሆርሞን ቀስቃሽነት ፤ በብዛት የቆዳ ቅባትን (ሴበምን) ፤ በማምረታቸው ሊከሰት ይችላል። ይህም የሚከሰተው ፤ የበዛው ቅባት የቆዳን ቀዳዳን ስለሚደፍን ነው።


ሁለተኛ፡ የቆዳ ያልተለመደ ለውጥን ተከትሎ ፤ የቆዳ ቀዳዳ ሲደፈን ሊከሰት ይችላል።


ሶስተኛ፡ የቆዳ ቀዳዳዎች ውስጥ የሚገኘው ባክቴሪያ (Cutibacterium acne) ፤ የተደፈነውን ቀዳዳ ሲያጠቃ ፤ ብጉር ነጭ ጫፍ ይኖረዋል። አልያም መግል ያዣል። አንዳንዴም ጥቁር ሊሆን ይችላል።


አራተኛ፡ የቆዳ ቀዳዳ መደፈንን ተከትሎ ፤ ያ አከባቢ ከተቆጣ ሊያብጥ እና ሊቀላ ይችላል።


ታድያ ህክምናውም እነኝህን አራት መንገዶች ላይ የተመሰረተ ነው። 
ree

የአሜሪካ የቆዳ ሀኪሞች አካዳሚ የሚከተለውን ይመክራል።

  • የቆዳ ቆዳዳዎች ውስጥ ሊኖር የሚችል ያልተለመደ እድገትን ለመግታት ሬቲኖይድስ (retinoids) መስጠት  

  • ባክቴሪያውን ለመቃወም እንዲሁም የቆዳ መቆጣትን ለመቀነስ ፤ ቤንዞይል ፐርኦክሳይድን (Benzoyl peroxide) መስጠት እንዲሁም

  • እንደ በሽታው መስፋፋት እና እንዳደረሰው የቆዳ ቁስለት/ጠባሳ ተጨማሪ ህክምናዎችን ይመከራል።


ብጉርን ተከትሎ የአእምሮ ጤና ቀውስ የሚያጋጥማቸው ታካሚዎች ደግሞ ፤ ለብጉሩ ከሚያደርጉት ህክምና ባሻገር ፤ የሰነ ልቦና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

መንስኤዎች

ለብጉር አጋላጭ መንስኤዎች መሀከል ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸው።


ree
  • ሆርሞኖች እና የሕይወት ደረጃ -  ከሆርሞኖች ውስጥ በተለይ አንድሮጅን ሆርሞኖች የቆዳን ወዝ ይጨምራሉ። ይህም በጉርምስና ጊዜ እና ወር አበባን ጋር ተያይዞ ብጉር እንዲበዛ ያደርጋል። ይህም የሚታይባቸው ታካሚዎች የሆርሞን መቃወሚያ ህክምና ( የ ፀረ-አንድሮጅን ሕክምና (spironolactone) ) ያስፈልጋቸዋል።


  • አመጋገብ ፡ አመጋገብ ብጉር ላይ ተጽእኖ እንዳለው የሚያሳዩ መረጃዎች ቢኖሩም ፤ አስረግጦ ለመናገር ገና ብዙ ጥናቶች ይቀራሉ። ሆኖም ግን ስኳር የበዛባቸው ምግቦች አብዝቶ መመገብ ብጉርን እንደሚያባባስ ጠቋሚ ጥናቶች አሉ። ለዚህም ብጉርን ለመቀነስ የምንመገበውን የስኳር መጠን መገደብ ይኖርብናል።


  • ባክቴሪያዎች - ከብጉር ጋር ተያያዥነት ያላቸው ባክቴሪያዎች አሉ። ለዚህም የሚቀባ የባክቴሪያ መቃወሚያ በዚህ በኩል ጠቀሜታ አለው። ታድያ ግን እንዳይላመዱ መጠንቀቁ መልካም ነው።


  • መዋቢያዎች ፡ የቆዳ ቀዳዳን የሚደፍኑ መዋቢያዎች፤ እንዲሁም በውስጣቸው ስቴሮይድ ያላቸው ክሬሞች ብጉርን ያመጣሉ።


  • ውጥረትና እንቅልፍ፦ ውጥረትና እንቅልፍ ማጣት የቆዳ ቅባት ምርትን ከማዛባቱ አልፎ ፤ ቆዳ እንዲቆጣ ያደርጋል። ለዚህም ብጉር ያመጣል።



ብጉር በዋነኝነት የሚያጠቃቸው አካላት፡


ብጉር እንደዘፈቀደ ማንኛውንም የሰውነት ክፍል አያጠቃም። በቅባት አምራች ህዋሳት ላይ ስለሚመሰረት ፤ እነኝህ ህዋሳት የተከማቹበት የሰውነት ክፍሎችን በይበልጥ ያጠቃል። ለዚህም በዋነኝነት የሚጠቁ የሰውነት ክፍሎች የሚከተሉት ናቸው።


ree
  • ፊት ፡ እጅጉን የተለመደ ሲሆን ፤ በአማካይ ከ 95 በመቶ በላይ የሚሆኑ ታማሚዎች ፊታቸው ላይ ብጉር ይኖራቸዋል። በዋነኝነትም ግንባር ፣ አፍንጫ ፣ አገጭ እና ጉንጭ ላይ ይታያል ። እነኝህ የፊታችን ክፍሎች ከፍተኛ የቅባት አምራች ህዋሳት ክምችት ስላላቸው ፤ እንዲሁም ለአቧራ እና ለተመሳሳይ ነገሮች ተጋላጭ ስለሆኑ ፤ በይበልጥ በብጉር ይጠቃሉ። የውበት መጠበቂያ ቅባቶች ፣ ሜካፖችም በብዛት ፊት ላይ ስለሚደረጉ ፤ የቆዳ ቀዳዳን ደፍነው ብጉር ሊያመጡ ይችላሉ። ስቴሮይድ ያላቸው ቅባቶች በበኩላቸው ፤ የቆዳ ቅባት ምርት እንዲጨምር በማድረጋቸው ፊት ላይ ብጉር እንዲበራከት ያደርጋሉ።

  • ጀርባ፡ በግምት ወደ 60 ፐርሰንት የሚሆኑ ታካሚዎች ጀርባቸው ላይ ብጉር ይታይባቸዋል። በብዛት የላይኛው ጀርባ እና ትከሻ ላይ ያጋጥማል። እዚህ አከባቢ ያለው ቆዳ ወፍራም ከመሆኑ ባሻገር ፤ ብዙ ቅባት አምራች ህዋሳት ስላሉት ፤በብጉር አብዝቶ ይጠቃል።

  • ደረት፡ ቢያንስ አንድ ሶስተኛ የሚጠጉ ታካሚዎች ደረታቸው ላይ ብጉር ይኖራቸዋል። ይህም በሙቀት እና ጠበቅ ያለ ልብስ በመልበስ ሊባባስ ይችላል።


  • አንገት እና አገጭ ፡ ይህ በዋነኝነት ወጣት እና ጎልማሳ ሴቶች ላይ የሚታይ ሲሆን ፤ ከሆርሞን ጋር ግንኙነት አለው።


  • ከዚህም ባሻገር የራስ ቅል ቆዳየታችኛው ጀርባ ፣ መቀመጫ እና ከክርን በላይ ብጉር ሊታይ ይችላል።



📊 ብጉር የሚያጠቃበት መንገድ እንድ እድሜ እና ጾታ ሊለያይ ይቻላል!
  • በጉርምስና እድሜ ላይ ብጉር በብዛት የሚታይ ሲሆን ፤ ስርጭቱም በይበልጥ ፊት ላይ ነው። ለዚህም ግንባር ፣አፍንጫ እና ጉንጭ ላይ ይታያል። ይህም ጉርምስናን ተከትሎ በሚመጣ ለውጥ ፤ ቆዳችን ወዛም ስለሚሆን ነው። ብዙ ጊዜ መግል ሊያዥ፣ ውሀ ሊቋጥር እንዲሁም ጥቁር ጫፍ ሊኖረው ይችላል። ከጉርምስና ባሻገር ፤ ከጭንቀት እና ከምግብ ጋር ሊባባስ ይችላል።


  • በወጣትነት እና በጎልማሳ እድሜ ፤ ከወንዶች ይልቅ በብዛት በሴቶች ይታያል። ይህም በዋነኝነት የታችኛው የፊት ክፍል ላይ በተለይም አገጭ ፣ መንገጭላ እና አንገት ላይ ይስተዋላል። ይህም ከሆርምን መዋዠቅ ጋር ሲያያዝ ፤ አንዳንድ ሴቶች ላይ ከወር አበባ ቀድሞ ይስተዋላል። ብዙ ጊዜ እብጠት ብቻ ሊሆን አልያም ሊቆጣ ይችላል።


    ree

  • ከአርባ አመት በኋላ ብጉር ብዙም የተለመደ አይደለም። ከታየ ከሆርሞን ጋር ተያይዥነት ያለቸው በሽታዎች ጋር ፤ አልያም ከመድሐኒት ጋር ግንኙነት አለው።


  • ወንዶች ላይ ብዙ ጊዜ ጀርባ እና ደረት ላይ የሚታይ ሲሆን ፤ ጉዳቱም ትንሽ ያይላል።


  • ብጉር መጣ ሄደት የሚልባችው ታካሚዎችም አሉ። ይህ ደግሞ ከ ወር አበባ፣ ከወቅቶች ጋር ፣ አልያም ህይወት ላይ ከሚያጋጥሙ ወጥረቶች ጋር ግንኙነት አለው።


 🌿 በቤትዎ ምን ማድረግ ይችላሉ?


ለብጉር ተመራጭ ህክምና በሀኪምዎ የሚታዘዙ እንደ ሬቲኖይድና ቤንዞይል ፐሮክሳይድ ያሉ መድኃኒቶች ናቸው። ሆኖም ግን በቤትዎ እነኝህን በማድረግ ቡግርን መቀነስ እንዲሁም መከላከል ይችላሉ።

ree

1.    መደበኛ እንክብካቤ ለቆዳዎያድርጉ። 


  • ፊትዎን በቀን ሁለት ጊዜ ለብ ባለ ውሀ ይታጠቡ።

  • አብዝቶ ቆዳ ማሸት ወይም ደጋግሞ መታጠብ ቆዳን ይጎዳል። ለቆዳ ድርቀት ይዳርጋል። ለዚህ አብዝተው አይታጠቡ። መዓዛ በሌለው ሳሙና ይታጠቡ።  

  • ጠንካራ ማሻዎችን፣ አልኮል ያላችው መታጠቢያዎች/ቅባቶችን አይጠቀሙ። መቆጣትን ሊያባብሱ ይችላሉ። 

  • የሚስማማዎትን ግብአቶች ለይተው ይወቁ።


2.    ማር 🍯

  • ንጽሁ ማር ጀርሞችን የመከላከል እና መቆጣትን የመቀነስ ባህሪ አለው። ለዚህም በየሳምንቱ ለተወሰኑ ቀናት ከ10 እስከ 15 ደቂቃ የማር ስክረብ ያድርጉ። ይህ በተለይ ለተቆጡ መጠነኛ ቡግሮች ይጠቅማል።


3.     ግሪን ቲ (አረንጓዴ ሻይ)

  • ግሪን ቲ በውስጡ ፖሊፌኖል (EGCG) ይዟል። ይህም ውህድ የቆዳን ቅባት ምርትን ከመገደቡም ባሻገር ፤ የቆዳ መቆጣትን  ይቀንሳል። 

  • ለዚህም አረንጓዴ ሻይ አፍልተው፤ አቀዝቅዘው ፤ ቆዳ ላይ በመቀባት መጠቀም ይችላሉ። አልያም ከግሪን ቲ የሚሰሩ የቆዳ ቅባቶችን/ግብአቶችን መጠቀም ይችላሉ።


4.    ሬት🌱

  • ሬት ለቆዳ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ  አለው። ቆዳን ያለሰልሳል ፤ ባክቴሪያን ይቃወማል። ብጉርን ይቀንሳል።

  • ለዚህም ሬት ይቀቡ። ታድያ ግን አልኮል ያለውን የሬት ምርት አይጠቀሙ። ንጽህ ሬት ይጠቀሙ።

  • ይህም የቆዳን መቆጣት ይቀንሳል። በተለይ ሬቲኖይድ መድሀኒት ከመጀመርዎ በፊት መጠቀሙ ይመከራል።


5.    የኑሮ ዘይቤዎን ያስተካክሉ።

  •  ከፍተኛ የስኳር መጠን ያላቸው ምግቦች አይመገቡ። ጣፋጭ መጠጦችና ምግቦችን ይቀንሱ። አዝእርቶችን፣ ፍራፍሬዎችን እና አትክልቶችን ይመገቡ።

  • አይጨነቁ። ህይወትዎ ውስጥ ያለ ውጥረትን ይቀንሱ።

  • የሰውነትዎን ንጽህና ይጠብቁ። እንዳላብዎ ወዲያውኑ ይታጠቡ።

  • ሜካፕ አብዝተው አይጠቀሙ። በተለይ ጭምብል፣ ሔልመት እና ኮፍያ የሚጠቀሙ ከሆነ።

  • በውስጣቸው ስቴሮይድ ያላቸውን የቆዳ ቅባቶች አይጠቀሙ።

  • መደበኛ የእንቅልፍ ሰአት ይኑርዎ። ቢያንስ ለ ስድስት ሰአት በቀን ይተኙ።

  • መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ።


6.    ብጉሩን በእጅዎ አይንኩት። አያፍርጡት! ይተዉት!


7.    ህመም ያለው እና ያዠ ብጉር ካለ ፤ በረዶ በጨርቅ ጠቅልለው ያድርጉበት። ይህም መቆጣትን ይቀንሳል።


8.   ከዚህም ባሻገር ቅባት የሌለው ፤ ኮሞዶጅን የሌለው የጸሀይ ጨረር መከላከያ የቆዳ ክሬም (non-comedogenic sun screen ) ይጠቀሙ። የብጉር ጠባሳዎች ቶሎ እንዲጠፉ ያደርጋል።

 

እነኝህን ተግባራዊ ለውጦች በማድረግ፤ የቆዳዎን ጤና ይጠብቁ!


 

Comments


bottom of page