top of page

🌱 አዲስ ዓመት ለጤንነትዎ አዲስ ጅማሬ

አሮጌውን ትተን አዲስ አመት የምንቀበልበት የዘመን መለወጫ ይኸው ደረሰ!


እንኳን አደረስዎ!!!


ይህንንም ለማብሰር ሰማይ በርችት ሲደምቅ ፤ ቤታችን አውደ አመት አውደ አመት ሲሸት ፤ እኛም በበኩላችን ጤናማ አመት ለማሳለፍ እቅድ ይዘን ይሆናል። ለራሳችን ብቻ ሹክ ያልናቸውው ቃላቶች ይኖራሉ።


ree

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ወደ 80% የሚሆኑት የአዲስ ዓመት ውሳኔዎች ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይተዋሉ። መልሶ ወደማይበጀን አሮጌው ባህሪያችን እንመለሳለን። በ 2018 ይህ መቆም አለበት! ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ታድያ የአንድቀን ውሳኔ ብቻ አለመሆኑን ይገንዘቡ። በአመት ውስጥ ባሉ በእያንዳንዱ ቀናት ጤናዎን መምረጥ ይኖርቦታል።

ለመሆኑ ግን ምን የባህሪ ለውጥ ቢያመጡ ይመከራል?

🥗 የተመጣጠነ ምግብ መመገብ።

ጤናማ አመጋገብ አመጋገብን ስለመቆጠብ (dieting) ብቻ አይደለም።


ሰውነትዎ የሚፈልጋቸውን ግብአቶች በበቂ ሁኔታ በማቅረብ ፤ የሰውነትዎን አቅም/ኃይል መገንባት ነው። እንዲህ አድርገው ያስቡት

" አንድ አናጢ አንድ የእንጨት ስራ ለመስራት ከ እንጨት ባሻገር የሚያስፈልጉት የተለያዩ ግብአቶች አሉ። እንደ ቀለም፣ ቫርኒሽ፣ ሚስማር፣ ኮላ አይነት ነገሮች ባይኖሩ አልያም ቢያንሱ ፤ ስራው ይበላሻል አልያም ይስተጓጎላል። ሁሉም የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ስላለው ፤ በበቂ መጠን መገኘት አለበት። አመጋገብም እንዲሁ።" 

የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እ.ኤ.አ 2020 እንደዘገበው በየአመቱ በአለም ዙሪያ ከ11 ሚሊየን በላይ የሚገመቱ ሰዎች ከአመጋገብ ጉድለት ጋር በሚያያዙ ምክንያቶች ይሞታሉ። ይህ ቁጥር እጅጉን ከፍተኛ ነው። ሆኖም ግን አመጋገብ በማስተካከል ልንከላከለው እንችላለን።

ree

አገራችን ኢትዮጵያም ይህ የአመጋገብ ጉድለት በብዛት ይስተዋላል። እ.ኤ.አ. በ 2019 የተደረገ የኢትዮጵያ የስነ ሕዝብ አወቃቀር እና ጤና ጥናት (EDHS) በከተሞች ውስጥ ከመጠን ያለፈ ውፍረት እየጨመረ ሲመጣ ፤ በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ደግሞ የምግብ እጥረት እያስቸገረ እንደሚገኝ ጠቁማል። ለዚህም አቅማችን በፈቀደው መሰረት አመጋገባችን ማስተካከል ግድ ይለናል።


የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ከፍተኛ ወጪ አይፈልግም። ቅባት፣ አሰር፣ አትክልቶች ፣ ፍራፍሬዎች እና ጥራጥሬዎች ስራዬ ብለን መመገብ ይኖርብናል።


🏃 ♀️  የሐኪም ማዘዣ የማያስፈልገው መድሃኒት ፡ እንቅስቃሴ

በሳምንት ለ150 ደቂቃ መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ለልብ ህመም፣ ለስኳር በሽታ እና ለአንዳንድ ካንሰሮች የመጋለጥ እድልን እንደሚቀንስ ያውቃሉ  ?

ይህ ማለት በቀን 30 ደቂቃ ብቻ በሳምንት አምስት ቀናት ውስጥ መጠነኛ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህም ትልቅ የአካል እንቅስቃሴ አያስቡ። ፈጣን የእግር ጉዞ ማድረግ፣ መደነስ፣ ብስክሌት መንዳት ወይም ግቢ በደንብ ማጽዳት አይነት እንቅስቃሴ በቂ ይሆናል።


ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ማህበረሰብ እጅጉን አስፈላጊ ነው። በተለይ በከተሞች ውስጥ ብዙ እንቅስቃሴ የሌለው አኗኗር እየጨመረ መምጣቱን በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የተደረገ ጥናት ይጠቁማል። ይህ አኗኗር ደግሞ በቢሮ ሰራተኞች ላይ በብዛት ይታያል።


ያስተውሉ! ጤናማ እንቅስቃሴ ያድርጉ ማለት የጂም አባልነት ይኑርዎት ማለት አይደለም።
ree

ታክሲ በመሳፈር ፋንታ ቢራመዱ ፤ ከሊፍት ይልቅ ደረጃን ቢጠቀሙ ፤ ሰንበት ላይ ሰፈር ውስጥ እግር ኳስ ቢጫወቱ ፤ ለጤናዎ ብዙ ለውጦችን ያመጣል።


ታድያ ምን አስቡ?


😴የሚረሳው የጤና ምሰሶ ፡ እንቅልፍ

ሩጫ በበዛበት ህይወት ውስጥ እንቅልፍ ይዘነጋል። ለዚህም እንቅልፍ ለድርደር የሚቀርብ አማራጭ ሆኖ በብዙዎቻችን ይቀርባል።


ስራ ሲበዛ እንቅልፋችንን መስዋእት እናደርጋለን። ስንፈልግ እንቅልፍን ተሰርዞ እስከ ንጋት እንዝናናለን። ስልካችንን እየተጠቀምን ክሆነ ፤ እንቅልፍን ገሸሽ እናደርጋለን። ስንጨነቅ ወይ እንቅልፍ እናጣለን አልያም አልጋ ላይ እንሰነብታለን።

ree

ይህ ሁሉ ጤናማ ባህሪ አይደለም ። እንቅልፍ ከጤናችን ጋር የተቆራኘ ትልቅ የጤና ምሶሶ ነው።በቀን ከ7 ሰአት ያነሰ እንቅልፍ መተኛት ከመጠን ላለፈ ውፍረት ከማጋለጡ አልፎ ፤ የበሽታ መከላከል አቅምን ያዳክማል። የማስታወስ ችግርን ይቀንሳል። ለሥር የሰደዱ በሽታዎች የመጋለጥ እድልን ይጨምራል።


ይህ ዛሬ ላይ መቆም አለበት። በ 2018 ዓ.ም በየቀኑ ከ 6 እስከ 8 ሰአት እንቅልፍ ሊተኙ ይገባል። ከመተኛትዎ በፊት ራስዎን ዘና ያድርጉ። ሞባይል አይጠቀሙ! ይጸልዩ! ሰውነትዎን ያሳስቡ! ይህን ጊዜ በደንብ ይተኛሉ። ሰውነትዎም ራሱን የሚጠግንበት ጤናውን የሚመልስበት እረፍትን ያገኛል።


🧘 የአእምሮ ጤንነት

ጤና አካላዊ ብቻ አይደለም። በአለም አቀፍ ደረጃ ከ 8 ሰዎች አንዱ የአእምሮ ጤና መታወክ ይታይበታል።። እ.ኤ.አ በ2018 የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው ከ22% በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በህይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ የአእምሮ ጤና ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል።


ሆኖም ግን ብዙዎች ይላቸው የተሳሳተ እይታ አስፈላጊውን ህክምና እንዳያደርጉ ይይዛቸዋል። እነርሱም የአእምሮ ህመም እንዳለባቸው እንዲታወቅ አይፈልጉም።


ለዚህም ብዙዎች በዝምታ ይማቅቃሉ። ድምጻቸው ሳይሰማ ይሰቃያሉ።
ree

በዚህ አመት ስለ አእምሮ ህመም መነጋገር መደበኛ መሆን ይኖርበታል። የአእምሮ ህመም ማለት እብደት አለመሆኑን ማወቅ ይኖርብዎታል። እርሶም ከልክ ያለፈ ውጥረት ካለብዎ የጤና ባለሙያ ያማክሩ።


እርስዎን እንጠይቅዎ፡

ለእርስዎ አለኝ የሚሉት ሁነኛ ሰው ማን ነው? ህይወት ጫናዋ ሲበዛ ሊያዋዩት የሚችሉት ሰው ማነው?

እስካሁን ከሌለዎት። በዚህ አመት ይኑርዎ። ሲነጋገሩ የችግርዎ ሸክም ይቀላል። መፍትሔ ይገኛል።


🚭 መጥፎ ልማዶችን ይተዉ

አልኮል፣ ትምባሆ እና የአደንዛዥ ዕፅ መጠቀም አሁንም አሳሳቢ የማህበረሰብ ጤና ችግሮች ናቸው። በየአመት የሚሊየኖችን ህይወት ይቀጥፋሉ። ሀገራችን ኢትዮጵያ በፖሊሲ ረገድ መሻሻል ብታሳይም ፤ ወጣቶች ዙሪያ አሁኑም ተግዳሮቶች ይታያሉ።

ree

ስለዚህ ጤናዎን ጠንቅ የሆኑ እነኝህን ልማዶች ፤ በአዲስ ጤናማ ልማዶች ለመተካት ይኖርብዎታል። ሁሉንም በአንዴ እርግፍ አድርገው ማቆም አይችሉ ይሆናል። ሆኖም ግን አንድ በአንድ ባህሪዎን ይለውጡ።


እንዲህ ካላሰቡ የባህሪ ለውጥ ማምጫ ዘመን አሁን ነው። ለራስዎ ቦታ ይስጡ። ሁል ጊዜ ጤናዎን ይምረጡ።


❤️ ሁል ጊዜ መከላከል ከፈውስ ይሻላል


መደበኛ የጤና ምርመራ/ቼክ አፕ ያድርጉ። አስፈላጊ ክትባቶች ይከተቡ። ጨቅላ ህጻን ካለዎት ምንም ክትባት አያምልጠው። ይህ ሁልጊዜ የሚሰሙት ምክር ቢሆንም ፤ ህይወት አድን ነው። እንዴት?


በአገራችን ኢትዮጵያ በአሳዛኝ ሁኔታ ፤ ወጣቶች በትልቅ ሰው ህመም እየታመሙ ፣ በልጅነታቸው ኩላሊታቸውና ጉበታቸው እየደከመ ፤ ልባቸው እጅጉን ተጎድቶ ፤ የተሰራጨ ካንሰር ተገኝቶባቸው ፤ የህክምና እርዳታ ሲጠይቁ በየከተሞቹ ይታያል። በፈረንጆች 2021 የጤና ጥበቃ ሚኒስተር እንዳወጣው መረጃ ከሆነ በኢትዮጵያ የስኳር በሽታ፣ ደም ግፊት እና ካንሰር ህመሞች እየጨመሩ ይገኛሉ።


ree

መደበኛ ምርመራ በማድረግ ይህንን ሁሉ መከላከል እንደሚቻል ያውቃሉን?


ሆኖም ግን በየአመቱ ወገኖቻችንን እያጣን እንገኛለን።


ታድያ እርስዎስ መቼ ነው ለመጨረሻ ጊዜ ሳይታመሙ፤ ለ መደበኛ የጤና ምርመራ የሄዱት?


ህመም አልተሰማዎትም ማለት ጤነኛ ነዎት ማለት አይደለም። መሄድ አያስፈልግዎትምን?


ያስተውሉ መከላከል ከፈውስ ይሻላል። ማንንም አይጠብቁ ዛሬውኑ እርምጃ ይውሰዱ። ህይወትዎን ያሻሽሉ።

✨ያስተውሉ!

በዚህ አዲስ አመት ፤ ተግባራዊ ለውጥ እናምጣ። ጤናችንን እንምረጥ ። ግልጽ የሆኑ ጤናማ ግቦችን እናስቀምጥ ። ዛሬውኑ እርምጃ እንውሰድ።


  • በቀን ምግብዎት ውስጥ አንድ ተጨማሪ ፍራፍሬ ወይም አትክልት ይጨምሩ።.

  • በሳምንት አምስት ጊዜ ለ 30 ደቂቃዎች በእግር ይራመዱ።

  • በቀን ከ 7-8 ሰአታት ይተኙ።

  • ስለ አእምሮ ጤንነት በግልጽ ይናገሩ።

  • በዚህ አመት አንድ ጎጂ ልማድ ያቁሙ።

  • ህመም ጥልዎት ሀኪምቤት ከመሄድዎ በፊት ይመርመሩ።

ጤናዎ መስከረም ላይ አይገነባም። ከዚህ በኋላ በሚወስዷቸው ሺ ጥቃቅን ምርጫዎች ውስጥ እንጂ።


እያንዳንዷ ቀን ጤናዎን ለማደስ እድል ናት።


2018 ጤናዎን የሚያድሱብት አመት ይሁንልዎ።



 

Comments


bottom of page