ትምባሆና የኤሌክትሪክ ሲጋራ ያላቸው የጤና እክል
- Zebeaman Tibebu
- Aug 13
- 5 min read
አዙሪቱ በዝምታ ይጀምራል!
አንዱ አውቶብስ እየጠበቀ ሲጋራ ይለኩሳል።
ከዩንቨርስቲ ዶርም ጀርባ ሌላኛው ፤ መልካም መአዛ ያለው ቬፕ ይስባል።
ለተመልካች አንደኛው እንደሚቃጠል ቅጠል ሲሸት ፤ ሌላኛው የከረሜላ መአዛ አለው። አንደኛው ብቻ አጫሽ ይመስላል።
ታድያ ግን ሁለቱም የሰውነት ኡደታቸው እየተለወጠ ፤ ለበሽታ፣ ለሱስና እንዲሁም ለካንሰር ያጋልጣሉ።
ትምባሆ በኢትዮጵያ
ብዙ ኢትዮጵያውያን ትምባሆ አያጨሱም። ሆኖም ግን የአጫሽ ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። አሁን ባለው መረጃ ትንባሆ በየዓመቱ ከ17,000 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት እየቀጠፈ ነው ። ብሔራዊ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከአዋቂዎች መካከል 5 በመቶ የሚሆኑት ትንባሆ የሚያጨሱ ሲሆን ፤ ከእነኝህ ውስጥ አብዛኞቹ ወንዶች ናቸው። ይህ ቁጥር ትንሽ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን 120 ሚሊየን በላይ ሰዎች ባሉባት በሚኖሩባት ሀገር ፤ የአጫሾች ቁጥር በሚሊየኖች ይገባል።

እነሱም ሲያጨሱ ፤ በ አስር ሚሊየኖች ለሲጋራ ጭስ ይጋለጣሉ። ሁለተኛ ዙር አጫሽ ይሆናሉ። ምናልባት ይህ የአንድ ጊዜ አጋጣሚ ከሆነ ላያሳስብ ይችላል። ከተደጋገመ ግን ሁለተኛ ዙር አጫሾች ፤ ከአጫሾች ይበልጥ ለብዙ የጤና እክል ይጋለጣሉ። በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ 1.3 ሚሊዮን የማያጨሱ ሰዎች ፤ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች በማጨሳቸው ለሞት ይዳረጋሉ።
እዚህ ላይ አዲሶችን የኤሌክትሪክ ሲጋራዎች ወይሞ ቬፖችን እንጨምር...
በውስጣቸው በዋነኝነት ኒኮቲንን ከተለያዩ ውህዶች ጋር ያያዙ ፤ በባትሪ የሚሰሩ ዘመናዊ ሲጋራዎች ናቸው። ታድያ በኢትዮጵያ የእነኝህ ሲጋራዎች አጫሽ መጠን የሚጠቁም መረጃ የለም። ሆኖም ግን በተማሪዎች እና በወጣቶች ዘንድ እንደ ፋሽን እየተለመዱ እየመጡ ነው።

"ሲጋራ አይደለም።"
አልያም ደግሞ
"የሲጋራ መርዛማ ኬሚካል የወጣላቸውና የተጣሩ ስለሆኑ ፤ እንደ ሲጋራ አይጎዱም። " በሚል ማሳመኛ እየተሸጡ ይገኛሉ።
በማህበራዊ ድህረ ገጾችም ከመሸጥ አልፈው ፤ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንደጌጥ አንጠልጥለዋቸው የታዩበትም ጊዜ አለ። ጣእማቸው ሳቢ ስለሆነ ፤ ብዙዎች እንደሲጋራ ላያስቧቸው ይችላሉ።
እውነታው ግን ጎጂነታቸው ከሲጋራ ጋር ተቀራራቢ ነው። መርዛማ ኬሚካሎችን የቀነሱ ቢሆንም ፤ ለህክምና አዲስ የሆኑ ፤ ለማከም የሚያስቸግሩ ፤ የጤና እክሎች እያመጡ መሆኑን ጥናቶች ያመላክታሉ።
የትንባሆ ጭስም ይሁን ቬፕ ፤ ውስጣቸው ያለው ኬሚካል ለሰውነት ጎጂ ነው።
ሲጋራ በውስጡ ከ7,000 የሚበልጡ ኬሚካሎችን ሲኖሩት ፤ ከዚህ ውስጥ ቢያንስ ሰባዎቹ ካንሰር አምጪ ናቸው። ለምሳሌ ፡ ፒ ኤ ኤች(PAH) ፣ ናይትሮሳሚን (Nitrosamine) ፣ እና አሮማቲክ አማይን (Aromatic amine) የሚባሉት ውህዶች ዘረመላችን ላይ ስለሚጣበቁ ፤ ካንሰርን ያመጣሉ።
እርግጥ ሲጋራ ውስጥ የሚገኙ በጣም መርዛማ ንጥረ ነገሮች ቬፕ ውስጥ ባይኖሩትም ፤ በምትኩ አዳዲስ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ይገኙበታል። ለምሳሌ እንደ ክሮሚየም ፣ ኒኬል እና ሊድ አይነት ከባድ ብረት አስተኔዎች (Heavy Metals) እንዲሁም ኦርጋኒክ ውህዶች (volatile organic compounds) በውስጡ አሉ። ከዚህም ባሻገር የኢሌክቶሮኒክ ሲጋራዎች ፤ በከፍተኛ ሙቀት የሲጋራውን ፈሳሽ ሲያገሉ ፤ ፎርማልዲሃይድ (በተለምዶ ፎርማሊን) ይፈጠራል። ይህም ከጭሱ ጋር አብሮ ወደ ሳንባ ይገባል።
ከዚህ ባሻገር ሁለቱም ላይ ኒኮቲን አለ። እንደውም በኒኮቲን መጠን ቬፕ ሊበልጥ ይችላል። ኒኮቲን በበኩሉ የነርቭ ስርአትን ፣ አቀማመጥን ፤ እንዲሁም አሰራርን በቋሚነት ይለውጣል። ለሱስም ያጋልጣል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት በጉርምስና ወቅት ለኒኮቲን መጋለጥ ፤ የአንጎልን እድገት በቋሚነት ሊለውጥ ይችላል። ለሌሎች ሱሶች በይበልጥ የመጋለጥ እድልንም ይጨምራል ።ለዚህም በተለይ የኤሌክትሪክ ሲጋራ ለወጣቶች በጣም አደገኛ ነው ።
የሲጋራ ጠንቅ በየሰውነት ክፍል
ሲጋራ የማይነካው የሰውነት ክፍል የለም። ሁሉም የሰውነታችን ህዋስ ፣ ከጸጉር ጀምሮ ማህጸን ውስጥ እስካለ ጽንስ በሲጋራ ይነካል።
ለዚህም አንድ በአንድ እንይ፡
የመተንፈሻ አካሎቻችን ፡ ሲጋራ ሲጨስ በመጀመሪያ የሚጋለጡት የመተንፈሻ አካሎች ናቸው። ለዚህም ከፍተኛ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ሳንባ የቻለውን ያህል አጣርቶ ወደ ደም ቢያስገባም ፤ እንደ ጥላሸት ተጣብቀው የሚቆዩት ውህዶች አሉ። በዚህም የተነሳ ሲጋራ ማጨስ ለተለያዩ የሳንባ ህመሞች ያጋልጣል። በዓለም ዙሪያ ከሚያጋጥሙ 10 የሳንባ ካንሰር ህመሞች ፤ በትንሹ ስምንቱ ከሲጋራ ጋር የተያያዙ ናቸው። በተጨማሪም ረዥም ጊዜ ለሚቆዩ የሳንባ መቆጣት ህመሞች (ለምሳሌ ኢምፋይሴማ እና ሲኦፒዲ) ያጋልጣል። ለ ትንፋሽ ቧንቧ ኢንፌክሽን ተጋላጭነትንም ይጨምራል።

ቬፕ ተመሳሳይ ጉዳት ከማስከተሉ አልፎ ፤ ለየት ያለ የሳንባ ህመምን ያመጣል። እነኝህ በሽታዎች ቬፕን ተከትለው የሚመጡ የሳንባ ጥቃቶች (EVALI/ E-cigarrete or Vaping Product Associated Lung Injury) ተብለው ይጠራሉ። ከዚህም ውስጥ ጣእሞኡን ለማሻሻል ተብሎ የሚከተተው ዳይ አሴታይል (diacetyl) የሚባለውን ውህድ ተክትሎ የሚመጣው ሳንባን እንደፈንዲሻ የሚያስመስለው (Pop corn LUng) ህመም ተጠቃሽ ነው። ከዚህም ባሻገር ቬፕም ለሳንባ ካንሰር ያጋልጣል።
የልብ እና የደም ስሮቻችን፡ ማጨስ ልብ ድካም የማጋጠም እድልን በ እጥፍ ይጨምራል። የስትሮክ አጋጣሚን በ 50 በመቶ ይጨምራል። ኒኮቲን የልብ ምትና የደም ግፊት እንዲጨምር ሲያደርግ ፤ ጭሱ ውስጥ የሚገኝው ካርቦን ሞኖ ኦክሳይድ ደግሞ ሰውነት ኦክስጅን እንዳይጠቀም ያሰናክላል። ሲጋራ ሆነ ቬፕ የደምስር ግድግዳዎችን ይጎዳሉ። ደም መርጋት እንዲያጋጥም ያደርጋሉ። ለደም ስር ህመሞችም ዋነኛ ተጠቃሽ መንስኤ ናቸው።

የምግብ መፍጫ ስርዓት፡ በጭሱ ውስጥ ያሉ ኬሚካሎች ጉሮሮን፣ ጨጓራን፣ አንጀትን፣ ጉበትንና፣ ቆሽትን አብዝተው ይጎዳሉ። ጨጓራ ህመምም ያባብሳሉ። የአሲድ ምርት ጨምረው ፤ ጉሮሮን ያስቆጣሉ። በረዥም ጊዜም ለጉሮሮ፣ ለጨጓራ ፣ እንዲሁም ለአንጀት ካንሰር ያጋልጣሉ።
ኩላሊት እና የመሽኛ አካላት ፡ ከጭሱ ውስጥ ካንሰር አምጪ የሆኑት አሮማቲክ አማይን ውህዶች ኩላሊት አጣርቶ ወደ ፊኛ ስለሚልካቸው ፤ እስኪሸና ፊኛው ውስጥ ይከማቻሉ። ለዚህም ማጨስ ለፊኛ ካንሰር ያጋልጣል። በሲጋራ አጫሾች ዘንድ የፊኛ ካንስር በሶስት እጥፍ ከፍ ያለ ነው። እንዲሁም በኩላሊት ካንሰር የመያዝ እድልም ይጨምራል።

በእርግዝና ወቅት ፡ ማጨስ የፅንስ መጨንገፍ ፣ ጽንስ ማህጸን ውስጥ እንዲሞት፣ ምጥ ያለጊዜ እንዲመጣ፣ እንዲሁም ክብደቱ ያነስ ልጅ እንዲወለድ ያደርጋል። ከዚህም ባሻገር ሲጋራ ውስጥ ያለው ኒኮቲን ፣ የጽንስን የአእምሮ እድገት ያስተጓጉላል። ለዚህም የሚወለደው ልጅ የአእምሮ ዝግመት ሊያጋጥመው ወይም የማሰብ አቅሙ ሊዳከም ይችላል። እናትም በእርግዝና ጊዜ ታጨስ ከነበረ ፤ ከወሊድ በኋላ ልጅ በድንገት የመሞት እድሉ ያየለ ነው።
የመራቢያ አካላት፡ ማጨስ የመራቢያ አካላት ካንሰር እንዲያጋጥም እድል ይከፍታል። የሚያጨሱ ሴቶች የማህጸን ጫፍ ካንሰር የማጋጠም እድላቸው ከፍተኛ ነው።
ሲጋራ ማጨስ በሽታ የመከላከል አቅምን ያዳክማል። አጫሽ ሰዎች ለሳንባ ኢንፌክሽኖች የተጋለጡ ከመሆናችውም ባሻገር ፤ የህክምና ውጤታማነትም እነሱ ላይ የቀነሰ ነው።
ማጨስ ደም ስሮችን ስለሚያዳክም ፤ የደም ዝውውርን ይቀንሳል። በቂ ኦክስጅን እና ምግብ ለህዋሳት ስለማይደርስ ፤ ከቀዶ ጥገና በኋላ ቁስል ቶሎ አይጠግንም።
አጫሾች ከሳንባ ካንሰር ባሻገር ቢያንስ ለ14 ካንሰር አይነቶች ተጋላጭነታቸው የጨመረ ነው። አለማጨስ ይህንን ተጋላጭነት ይቀንሳል። የሚያጨሱ ከሆነ ማቆሚያ ጊዜው አሁን ነው። ቶሎ ማጨስ ካቆሙ ፤ ተጋላጭነትዎን ይቀንሳሉ።

አንዴ ማጨስ ካቆሙ በኋላ ፤ ሰውነት ወደ ነበረበት ተፈጥሮአዊ ደረጃ እስኪደርስ አመታት ይወስዳል። ለዚህም አንዴ ማጨስ ካቆሙ ፤ መጽናቱ ያስፈልጋል።
ብዙዎች ማጨስ እንዳያቆሙ ፤ ካቆሙም በኋላ እንዲመለሱ የሚያደርገው የሲጋራ ሱስ ነው።
የሲጋራ ሱስ
ሱስ የሚያስይዘው የትምባሆ ቅጠሉ ፤ አልያም ጭሱ ፤ አልያም የቬፕ እንፋሎት አይደለም። ሲጋራ እንዳጨሱ ኒኮትን በሰከንድ ነርቭዎት ጋር ይደርሳል። ደርሶም ነርቮችን ያነቃቃል። ሰውነት ደስ የሚል ስሜት እንዲሰማው ያደርጋል።
ሰውነትም ይህንን የመነቃቃት ደረጃ እና ደስታ ይፈልጋል። እንደዚህ እንድንነቃቃ ይገፋፋል። ይህንንም ለማስቀጠል አንድ ሲጋራ ብቻ በቂ ነው!
ከዛም አንድ ሲጋራ ብቻ ...።
እያለ... እያለ... ሰውነት ይላመዳል።
የተለመደ ስራውን ለመፈጸም ሲጋራ ይፈልጋል። ለዚህም ያለሲጋራ መስራት፣ መንቃት፣ መልካም መስተጋብር ያዳግታል።
የቬፕማ ይብሳል!!
ኒኮቲን አብዝቶ ስላለው ፤ ሱስ የመያዝ እድል ይጨምራል።
ለዛ ይሆን እንዴ ወጣቶች በቬፕ ተጠምደው የሚታዩት ?
ከሱሱ ግን ነፃ መውጣት ይቻላል!

ሲጋራ ማጨስ ማቆም ከባህሪ ጥንካሬ ጋር ብቻ አይገናኝም!
የአጫሾች የአእምሮ አሰራር ተለውጧል። ሰውነታቸው ለመደበኛ ስራው ሲጋራ ከመፈለጉም በላይ ፤ የአእምሮ ቅርጹ ፣ ስርአቱ ፣ አቀማመጡ ተለውጧል። ለዚህም "አታጭስ!" የሚለው ቃል ብቻ ለውጥ ላያመጣ ይችላል።
ሱስ እንዲያቆሙ ለማድረግ የባህሪ እገዛ ፤ እንዲሁም የመድሐኒት ድጋፍ ያስፈልጋል። እነኝህ አንድ ላይ ሲደመሩ ማጨስ የማቆም እድልን በእጥፍ ይጨምራሉ።
የኢትዮጵያስ አቋም ምን ይመስላል?
አገራችን ኢትዮጵያ ያላት የአጫሽ መጠን አነስተኛ ቢሆንም ፤ የአጫሽ ቁጥርን ለመቀነስ እየሰራች ትገኛለች። የአፈጻጸም ክፍተት ቢኖርም ፤ የትንባሆ ማስታወቂያ ፣ በሕዝብ ፊት ማጨስና ፣ ሺሻ ማጨስ በህግ እገዳ ተጥሎባቸዋል። እንዲሁም የሲጃራ ፍጆታን ለመግታት ታስቦ ፤ ከፍተኛ የትምባሆ ግብር (በፈረንጆች 2020) ተጥሏል። አዲሱ የብሔራዊ የትምባሆ ቁጥጥር ስትራቴጂክ ፕላን (2023–2031) ሲጋራ ማጨስን ለማስቆም እቅድ አድርጓል። ይህም የሲጋራ ማጨስ ማቆም አገልግሎትን ለማስፋፋት ፤ እንደ ደም ግፊት ልኬት በየጤና ተቋማቱ አገልግሎቱን ለማዳረስ ታቅዷል።
ታድያ ግን በቂ በጀት ያለመኖርና ፣ የህግ አፈጻጸም እክሎች ይህንን እቅድ እያሰናከሉት ይገኛሉ። ከሱሱም ለመውጣት የሚያግዙ መድሀኒቶችን አቅራቦት ችግርም አለ።

የኤሌክትሮኒክ ሲጋራም በአሁኑ ጊዜ በሰፊው ቁጥጥር እየተደረገበት አይደለም። እድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ ልጆች ማጨስ የቻሉበት ክፍተት ተፈጥሯል። ይህ ደግሞ አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልገዋል።
መደምደሚያ ሀሳብ
ሲጋራ የሚገድለው በካንሰር ብቻ አይደለም። በልብ በሽታ፣ በደም ስር ህመም ፣ በስትሮክ፣ በሳንባ ምች፣ በኢንፍልዌንዛ፣ በስኳር በሽታ፣ በደም ግፊት፣ ወ.ዘ.ተ...
የእኛ የማጨስ ውሳኔ ፤ ከእኛ አልፎ በዙሪያችን ያሉትን ይጎዳል። ስለዚህ ቆም ብለን እናስተውል!
እርስዎ ያገኙትን ግንዛቤ ለሌላ ያጋሩ። የአንድ ሰው ህይወት ያድኑ።
በቀጣይ ትምህርታዊ ጽሁፎቻችን ውስጥ ሲጋራ ማጨስን ለማቆም ፤ ከሱሱ ለመገላገል የሚመከሩ ሳይንሳዊ መንገዶች ዙሪያ ፤ ስለማናነሳ ይከተሉን።
Comments