የልጅዎ ሽፍታ አሳሳቢ መሆኑን እንዴት ይወቁ?
- Zebeaman Tibebu
- Sep 2
- 4 min read
የ ልጅዎ የሚያሳሳ ቆዳ ከልስላሴው ባሻገር ፤ የበሽታ መከላከያም አካል እንደሆነ ያውቃሉ?
ገና ይችን አለም ከተቀላቀሉባት ከመጀመሪያዋ ደቂቃ ጀምሮ ፤ የህጻናት ቆዳ አከባቢ ላይ ከሚገኙ በሽታ አምጪ ህዋሳት ጋር ግብግብ ላይ ነው።
ለዚህም ህጻናት በመጀመሪያ አመታቸው በቆዳ ህመሞች ይጠቃሉ። በብዛት ከሚታመሟቸው ህመሞች ውስጥም ሽፍታ አለበት። በአለም ዙሪያ ሽፍታ እና የቆዳ ለውጦች ህጻናትን ወደ ጤና ተቁም ከሚወስዱ ምክንያቶች መሀከል በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። ጥናቶችም እንደሚያመላክቱት ከ 40 እስከ 50 ፐርሰንት የሚሆኑት ህጻናት ፤ በተወለዱ በመጀመሪያ ወራት ውስጥ የሚስተዋል ሽፍታ ይኖራቸዋል። የጨቅላ ህጻናት ክፍተኛ ክትትል ውስጥ የሚታከሙ ህጻናት መሀልም ፤ አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ተያያዥ የቆዳ ችግር ያሳያሉ። ከዚህም ከፍተኛውን መጠን የሚወስደው ሽፍታ ነው።

በኢትዮጵያም ተቀራራቢ ቁጥር ቢገመትም ፤ ይህን የሚያሳዩ በቂ ጥናቶች የሉም። ሆኖም ግን እነኝህ ህጻናት ወደ ጤና ተቋም እንዲሄዱ ከሚያደርጉ 10 ተጠቃሽ ህመሞች ውስጥ ፤ ሽፍታና የቆዳ ኢንፌክሽን እንዳሉበት ጤና ጥበቃ ሚኒስተር ይጠቁማል።
ቢሆንም ፤ ሁሉም ሽፍታ አሳሳቢ አይደለም።
የጨቅላ ህጻናት ቆዳ ገራም እንደመሆኑና ካለመዳበሩ የተነሳ ፤ በትንሹም በትልቁም ጉዳይ ሽፍታ ሊይዛቸው ይችላል። ከሙቀት ጀምሮ እስከ ከባድ ኢንፌክሽን ድረስ ሽፍታ ሊያስከትል ይችላል።
ለዚህም ወላጆች አሳሳቢ ሽፍታዎችን ፤ ከተራ ሽፍታዎች ለይተው ማወቅ ግድ ይላቸዋል።
ይህንን ማወቅ ደግሞ ተራ የሕክምና ጉጉት ብቻ አይደለም። እንደኩፍኝ ካሉ ወረርሽኖችም ጋር ተያያዥነት ስላለው የማህበረሰብ ጤና ኃላፊነትም ነው።
ለምንድን ነው ሕጻናት ይህን ያህል ለሽፍታ የሚጋለጡት?
ሳይንሱ ቀላል ነው። ከጎልማሳ ሰው ቆዳ አንጻር የህጻናት ቆዳ ሥሥ ነው። ለዚህም በቀላሉ በከባቢያዊ ንጥረ ነገሮች እንዲሁም በበሽታ አምጪ ተህዋሳት ይጠቃሉ። ከዚህም ባሻገር ቆዳቸው በደንብ አለመዳበሩ ፤ ለሽፍታ እና ለቆዳ ኢንፌክሽኖች ተጋላጭነቱን ይጨምራል።

የተለመዱ ሽፍታ አምጪ አካላት
ከኢንፌክሽንም ባሻገር የአከባቢ ለውጥ ለሽፍታ ያጋልጣቸዋል። ለምሳሌ ሙቀት እንዲሁም ወበቅ/እርጥበት ሽፍታን ያመጣሉ። እርጥበት የበዛበት የህጻን አካል ሽፍታ ይኖረዋል። ይህም ከቆዳ መሳሳት ጋር በይበልጥ ይያዛል። አንዳንዴም እርጥበቱን ተከትሎ የሚመጡ በሽታ አምጪ ተህዋሳትም ይህንን ያስከትላሉ። ለዚህም ተጠቃሽ የሚሆነው የህጻኑ ሽንት ጨርቅ/ዳይፐር የሚሸፍንበት ቦታ ላይ የሚታይ ሽፍታ ነው። በህክምና ስሙ ዳይፐር ደርማታይተስ (የሽንት ጨርቅ አከባቢ ያለ የቆዳ ችግር/ሽፍታ) ሲባል ፤ በሕጻናት የመጀመሪያ ወራት ላይ እጅጉን የተለመደ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት አንድ አመት ያልሞላቸው ህጻናት መሀል ሁለት ሶስተኛውን ያጠቃል።
ለሞቁ አካላት ጋር ንክኪ ሲኖር ፣ ላብ የበዛባቸው ስፍራዎች ላይ ፣ አንዳንድ ሳሙናዎችንና እንዲሁም ክሬሞች ጋር ተያይዞም ሽፍታ ሊታይ ይችላል። ይህ እንደ መጠነኛ አለርጂ አይነት ሲመስል ፤ በህክምናም ኮንታክት ደርማታይተስ አልያም ከንክኪ ጋር ተያያዥነት ያለው የቆዳ መቆጣት ይባላል። በስርጭቱ ዙሪያ በኢትዮጵያ በቂ መረጃ የለም። ይህ ሽፍታ በባህሪው ንክኪ ያደረገውን የቆዳ ክፍል ብቻ የሚያጠቃ ሲሆን ፤ ያስቆጣውን አካል (ሙቀት፣ ሳሙና፣ ክሬም፣ ወ.ዘ.ተ...) ክተወገደ በቀናት ውስጥ ይጠፋል።
እላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በሽታ አምጪ ተህዋሳትም ፤ ቫይረስን ጨምሮ ሽፍታ ሊያመጡ ይችላሉ። ያልተከተቡ ህጻናት ከቫይረስ ኢንፌክሽን ጋር ተያያዥነት ላላቸው ሽፍታዎች ተጋላጭነታቸው የሰፋ ነው። በተለይ ኩፍኝ ፣ ሩቤላ እና ቺክን ፖክስ ወረርሽኝ ጊዜ ሽፍታዎች ብዙ ህጻናት ላይ ሊታዩ ይችላሉ። በቅርቡ በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍል ውስጥ የታየውን የኩፍኝ ወረርሽኝ ጋር ተያያዥነት ያለው ሽፍታ ለዚህ ዋቢ መሆን ይችላል። ከዚህም ባሻገር በቀላሉ ለባክቴሪያ እና ለፈንገስ ኢንፌክሽን ጋር ተያይዥነት ያላቸውም ሽፍታዎች ይታያሉ።
👶 የሚከተሉትን ሽፍታዎች ካዩ አይደንግጡ። ግን ይከታተሉት ።
እነዚህ ሽፍታዎች የተለመዱ፣ በራሳቸው የሚዱኑና አብዛኛውን ጊዜ ምንም ዓይነት ሕክምና የማያስፈልጋቸው ናቸው።

ጫፋቸው ነጭ/ቢጫ ነጠብጣብ ያላቸው ጥቃቅን ቀይ ሽፍታዎች ፡ እነኝህ ከፊሉን አራስ ህጻናት የሚያጠቁ ሲሆን ፤ በብዛትም በተወለዱ በመጀመሪያ ወር ላይ ይታያሉ። በታዩ ከ 1 እስከ 2 ሳምንት ይጠፋሉ። ይህም ሽፍታ እነኝህን ህጻናት የሚያጠቃ ኢራይተማ ቶክሲከም ኒዮናቶረም ምልክት ናቸው።
በአፍንጫ ፣ በጉንጭ እንዲሁም አገጭ ዙሪያ የሚታዩ ጥቃቅን ነጫጭ ሽፍታዎች ፡ እነኝህ አንዳንድ ህጻናት ላይ የሚስተአሉ ከቅባት/ወዝ አምራች ህዋሳት ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው። ሆኖም አያሳስቡም።
ብጉር የሚመሉ ሽፍታዎች ፡ እነኝህ ከእናት ሆርሞን ጋር ተያይዘው የሚመጡ የተወለዱ አራስ ህጻናት ላይ የሚታዩ ብጉር የሚመስሉ ሽፍታዎች ናቸው። ህጻናቶቹ ደም ውስጥ ያለው የእናት ሆርሞን ሲመናመን ብጉሩ ይጠፋል። ለዚህም መድሐኒት አያስፈልገውም።
ላብ እና ሙቀት የሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ የሚታዩ ቀያይ ሽፍታዎችም፡ እነኝህም አያሳስቡም። በብዛት በመጋጠሚያዎች እና የቆዳ እጥፋቶች አከባቢ ይታያሉ። ስፍራው ሲናፈስ እና ሲቀዘቅዝ ይጠፋሉ።
ዳይፐር አከባቢ የሚታዩ መጠነኛ ቀያይ የተቆጡ የዳይፐር ሽፍታዎች፡ ቦታው ካለው እርጥበት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ስለሆነ ፤ ቦታው ሲደርቅ ፣ ሲናፈስ ይጠፋሉ። እንዲሁም ቆዳ የሚጠብቁ ቅባቶችም ሽፍታዎቹ እንዲጠእፉ ያግዛሉ። ለዚህም ሊያሳስቡ አይገባም።
እነኝህ ሁሉ ሽፍታዎች የሚያሳስቡ ቢመስሉም፤ አደገኛ አይደሉም ። በመጠነኛ የቆዳ እንክብካቤ ይጠፋሉ።
🚨 መጨነቅ ያለባችሁ መቼ ነው?
ከዚህ በታች ያሉ ሽፍታዎችን ከተመለከቱ በአፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ይፈልጉ። እነዚህ ሽፍታዎች ኢንፌክሽንን ወይም ከጀርባ ያለ ሌላ ሕመምን ጠቋሚ ሊሆኑ ይችላሉ።

የማይነጣጠሉ ትናንሽ ቀይ ወይም ሐምራዊ ነጠብጣቦች ያሉት ሽፍታ ካስተዋሉ። የበለዘ ወይም የተመታ አይነት መልክ ሲኖራቸው ፤ የቆዳው ቀለም ለውጥ የተጫኑት ጊዜ አይጠፋም። ይህም ከጀርባ ለ እንደማጅራት ገትር ፣ ደም ኢንፌክሽን እንዲሁም የደም መፍሰስ አይነት ከባድ የጤና ችግሮች ጠቋሚ ሊሆን ይችላል።
ሰውነት ዙሪያ የተሰራጨ ውሀ ያዥ ሽፍታ ካለ ፤ እንዲሁም ተያይዥ የሆነ የቆዳ መላላጥ ካለ ያሳስባል። ይህም የከባድ ባክቴሪያ ኢንፌክሽን ጠቋሚ ነው። አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ያስፈልጋል እና አይዘግዩ።
ሽፍታው በፍጥነት ከተስፋፋ ፤ አብሮት የአተነፋፈስ ለውጥ እንዲሁም ሌሎች አካላዊ ለውጦች ጋር ከተያያዘ ያስተውሉ። የህክምና እርዳታ ያስፈልጋል።
ሽፍታው መግል ካዥ ፣ ትኩሳት ካለ እና የሽፍታው ስር ከቀላ የባክቴሪያ ቆዳ ኢንፌክሽን ሽፍታ ሊሆን ይችላል። ተያይዥ ሽታም ሊኖር ይችላል።
ያስተዋሉት የዳይፐር ሽፍታ ከ 3 ቀናት በላይ ከሰነበተ ሀኪም ጋር ይዘው ይሂዱ። ቦታው ጋር ያለው እርጥበት ኖሮ ፤ ንጽህና ተጠብቆ አለመሻሉ ፤ ተደራቢ የባክቴሪያ አልያም የፈንገስ ኢንፌክሽን ጠቋሚ ሊሆን ይችላል።

ያስተውሉ እነኝህ እጅጉን አሳሳቢ ሽፍታዎች ስለሆኑ ፤ የሕክምና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
ለዚህም መቼም እንዳይዘናጉ!
🛑 ከሽፍታው ባሻገር ማስተዋል ያለብዎ ምልክቶች
ከሽፍታው ጋር ተደርበው እነኝህ ምልክቶች ካዩ ፤ የትኛውም አይነት ሽፍታ ቢሆን ፤ በአቅራቢያዎ ካለ የጤና ተቋም በአፋጣኝ ይሂዱ።

ትኩሳት (>38°C)
የምግብ ፍላጎት መቀነስ (እንደወትሮው አለመጥባት )
የእንቅልፍ ለውጥ (አለመተኛት / እንቅልፍ ከወትሮ በተለየ መጠን ማብዛት)
አብዝቶ መነጫነጭ/ ማልቀስ
የአተነፋፈስ ለውጥ
የፊት/ከንፈር እብጠት
የበለዙ የሚመስሉ ሽፍታዎች
የአንገት እንቅስቃሴው መገደብ (አንገት መድረቅ)
ማስታወክ
ማንቀጥቀጥ
በፍጥነት የሚስፋፋ ሽፋታ
መግል ካዠ ፣ ከቆሰለ ፣ እንዲሁም ሽታ ካለው ያስተውሉ!
እነኝህ ምልክቶች የቆዳ ችግር ብቻ አለመሆኑን ጠቋሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ለዚህም በአፋጣኝ ልጅዎን ያሳክሙ።
🛡️ እርስዎስ ምን ማድረግ ይችላሉ?
የህጻኑን ንጽህና ይጠብቁ።
ሽንት ጨርቁን / ዳይፐሩን እንደተጠቀመ ይቀይሩ። እንደ ዚንክ ኦክሳይንድና ፔትሮሊየም ጀል (ቫዝሊን) አይነት ቆዳን የሚጠብቁ ክሬሞችን/ቅባቶች መጠቀም ይችላሉ።
ሰውነት ሲያጸዱ አይፈትጉ። በስሱ ቆዳውን ያጽዱ።
ቆዳ ሁል ጊዚ አይሸፈን ። መናፈስ እርጥበት ያጠፋል።
ክትባት ፈጽሞ እንዳይዘለል። ለሕይወት አስጊ የሆኑ የቫይረስ ኢንፌክሽኖችን ለመከላከል ክትባት እጅጉን አስፈላጊ ነው። አንዳንዶቹ ኢንፌክሽኖች ተከትሎ የሚመጣ ሽፍታንም ይከላከላል።
ማንኛውንም አሳሳቢ ሽፍታ ካዩ በአፋጣኝ የጤና ተቋም ይሂዱ። ምርመራ ይደረግ።
አይዘናጉ! ለልጅዎ ጤና ቦታ ይስጡ።





Comments