117 results found with an empty search
- የህመም ማስታገሻ እና የኩላሊት ጠንቁ
ብዙ ጊዜ ህመም ሲሰማዎ የሚወስዱት ምንድንነው? አይቡፕሮፌን ፣ ዳይክሎፌናክ / ኢንዶሜታሲን ፣ ወይስ የትኛውን የህመም ማስታገሻ? ብቻዎትን አይደሉም! በአለም ዙሪያ ብዙዎች ለህመም ማስታገሻ የሚጠቀሟቸው መድሀኒቶች ናቸው። በስራቸው ህመምን ያስታግሳሉ፤ ትኩሳትን ይቀንሳሉ፤ የሰውነንት መቆጣት ያረጋጋሉ። ለዚህም በፍጥነት እፎይታ ይሰጣሉ። ዋናውን በሽታ ባይሽሉም ... ህመሙን እንዳይሰማዎ ያደርጋሉ። በፍጥነት ስለሚሰሩ፣ ርካሽ ስለሆኑ እና ብዙ ጊዜ ያለ ማዘዣ ስለሚገኙ በዓለም ዙሪያ ተወዳጅ ናቸው። እነኝህ የህመም ማስታገሻዎች ምንድን ናቸው? በዚህ ትምህርታዊ ጽሁፍ የምናነሳው ኤን ኤስ ኤድ( NSAIDs ) በመባል ስለሚታወቁት የህመም ማስታገሻ መድሀኒቶች ነው። እነኝህ መድሀኒቶች ለራስ ምታት ለጀርባ ህመም ለትኩሳት ለመገጣጠሚያ ወይም ለጡንቻ ህመም ለሰውነት መቆጣት ጥቅም ላይ ይውላሉ። እነኝህ መድሀኒቶች በብዙ አገሮች ያለ ያለ ማዘዣ የሚገዙ ሲሆኑ በዝቅተኛ ዋጋ ፈጣን እፎይታ ይሰጣሉ። ለዚህም በብዙዎች ተመራጭ ናቸው። ከ 20 በላይ አይነት መድሀኒቶች ቢኖሩም ፤በኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት የተለመዱት አይቦፕሮፌን(Ibuprofen) ፣ ዳይክሎፌናክ (diclofenac)፣ ኢንዶሜታሲን(indomethacin) እና አስፕሪን (Aspirin)(በከፍተኛ መጠን ከተወሰደ) ናቸው። ታድያ እነኝህ መድሃኒቶች ለአጭር ጊዜ እና በትክክል ጥቅም ላይ ሲውሉ ውጤታማ እና ለጤና ጠቃሚ ናቸው። ታድያ እነርሱን በከፍተኛ መጠን ወይም በተደጋጋሚ ሁኔታ መጠቀም አደጋ አለው። በዶክተር ትእዛዝ እንደ አስፈላጊነቱ ታዞ ካልሆነ ፤ በየዕለቱ እነርሱን መጠቀም አይመከርም። ኩላሊት ላይ ለምን ጉዳት ይደርሳል? (ማወቅ ከፈለጉ ) እነኝህ መድሀኒቶች ከኩላሊት ጉዳት ባሻገር ፣ የጨጓራ ህመም ፣ የልብ ድካም ፣ የደም ግፊት፣ ስትሮክ ሊያባብሱ ይችላሉ። በእርግዝና ጊዜም እነርሱን ከመውሰድዎ በፊት ዶክተርዎን ማማከር ይኖብዎታል። ከዚህም መሀል ለይተን የምናተኩረው ኩላሊት ላይ ስለሚያደርሱት ጉዳት ይሆናል። እነኝህ መድሀኒቶች ህመምን የሚያስታግሱት ፕሮስታግላንዲን የሚባለውን ውህድ ስራ በመቀነስ/በማገድ ነው። ይህ ውህድ ደግሞ ኩላሊት ጋር ላለው የደም ዝውውር አስፈላጊ ነው። ደምስሮች በአግባቡ ተክፍተው ደም ዝውውር እንዲኖር ያደርጋል። ታድያ እነኝህን መድሀኒቶች በብዛት ያለ ገደብ ሲወስዱ ፤ ይህን ውህድ በከፍተኛ ሁኔታ ይቃወሙታል። ለዚህም ኩላሊት ጋር ያለው የደም ዝውውር ይዳከማል። ይህም የኩላሊትን ስራ ያሰናክለዋል። ይህም ጉዳትን ያመጣል። ጉዳቱ መድሀኒቶቹን በወሰዱ በሰአታት ውስጥ ሊያጋጥም ይችላል። ከዚህም ባሻገር መድሀኒቶቹ በቀጥታ የኩላሊት ህዋሳትን ሊጎዱ ይችላሉ። ለኩላሊት ህዋሳት መርዛማነት ባህሪ አላቸው። ለዚህም የኩላሊት ህዋሳት ስራቸውን በአግባቡ መስራት እንዲሳናቸው ያደርጋሉ። ለዚህም ረዥም ጊዜ የሚጠቀሙ ታካሚዎችን ፤ ስር የሰደደ የኩላሊት በሽታ (CKD) እሱንም ተከትሎ የኩላሊት ድክመት ያጋጥማል። ምልክቶቹስ ምንድን ናቸው? ኩላሊት ላይ ያለው ጉዳት ከፍተኛ እስካልሆነ ድረስ መጀመሪያ ላይ ምንም ምልክቶችን አያሳይም። ይህም አደገኛ ያደርገዋል። ሆኖም ግን እነኝህን ምልክቶች ካዩ ያስተውሉ፡ የእግሮች፣ የእግሮች ወይም የፊት እብጠት የሽንት መጠን መቀነስ ሽንት መቅላት/መጥቆር/ደም መቀላቀል ድካም ማቅለሽለሽ በድንገተኛ የደም ግፊት መጨመር የጀርባ ህመም (ኩላሊት ያለበት አከባቢ) ጉዳቱ እጅጉን ከፍ ካለ የደረት ህመም ትንፋሽ ማጠር ግራ መጋባት እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት ኮማ ሊያመጣ ይችላል። ቶሎ ካልታከመ አጣዳፊ የኩላሊት ድክመት ሊያመጣ አልያም ዘላቂ የኩላሊት ጉዳት ሊያመጣ ይችላል። ይህን ጊዜም የኩላሊት እጥበት ህክምና ሊያስፈልግ ይችላል። አንዳንዴም እስከሞት ሊያደርስ ይችላል። ማን በይበልጥ ይጋለጣል? እነኝህን የህመም ማስታገሻዎች ተከትሎ ለሚመጣ የኩላሊት ጉዳት ተጋላጭነታቸው ለሚከተሉት ከፍ ያለ ነው። ከ 60 ዓመት በላይ የሆኑ አዋቂዎች የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች የኩላሊት ችግር ያለበት ማንኛውም ሰው ዳይሬቲክስ (የሚያሸና ክኒን) የሚወስዱ ታካሚዎች እርጉዝ ሴቶች እንዲሁም የሰውነታቸው ውሀ ያነሰ ሰዎችም ተጋላጭነታቸው ከፍ ይላል። ትውከት ያለባቸው ፣ ተቅማጥ ያለባቸው ፣ ከፍተኛ የአካል እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ፣ ትኩሳት ያለባቸውና፣ እጅጉን የሚያልብ ሞቃታማ ስፍራ የሚኖሩ ሰዎች የአካላቸው የውሀ መጠን ስለሚመናመን ተጋላጭነታቸው ይጨምራል። ለዚህም ውሀ አብዝተው እንዲጠጡ ይመከራል። የኢትዮጵያስ እውነታ ምን ይመስላል? በኢትዮጵያም እነዚህ መድኃኒቶች ብዙውን ጊዜ ያለ ማዘዣ ጥቅም ላይ ይውላሉ። ለራስ ምታት፣ ለጀርባ ህመም፣ ለትኩሳት፣ ለመገጣጠሚያ ህመም፣ ወ.ዘ.ተ... ከፋርማሲ ተገዝተው በብዙዎች ይወሰዳሉ። ይህም ብዙዎችን ለኩላሊት በሽታ እያጋለጠ ይገኛል። በዚህ ዙሪያ ላይ ከተደረጉ ጥናቶች ውስጥ ፡ በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የተደረገ አንድ ጥናት እነኝህን ህመም ማስታገሻ የተጠቀሙ ታካሚዎች ስር የሰደደ የኩላሊት ህመም የማጋጠም እድላቸው በ 2.4 እጥፍ ጨምሯል። በመላው ኢትዮጵያ የተደረገ የዳሰሳ ጥናት በበኩሉ ደግሞ ፤ በአጭር ጊዜ ለሚያጋጥም ለኩላሊት ህመም/ጉዳት እነኝህ የህመም ማስታገሻዎች አጋላጭ መሆናቸውን ገልጿል። ይህም ጥቂት የማይባል የማህበረሰብ ክፍልን ለተደበቀ የኩላሊት ጉዳት ከፍተኛ ተጋላጭነት ላይ ይጥለዋል። ምን ማድረግ አለብዎ? ለራስዎ ህመም ማስታገሻ አይዘዙ። እጅጉን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ይጠቀሙ። ግድ ካልሆነ በቀር ደጋግመው በየቀኑ አይጠቀሙ። ሰውነትዎ ውሀ በሚያንስበት ጊዜ ባይወስዱ ይመከራል። በሞቃታማ ስፍራ እየሰሩ ከሆነ፣ ተቅማጥ፣ ማስታወክ ወይም ትኩሳት ካለብዎ ይጠንቀቁ። ውሀ አብዝተው ይጠጡ። የደም ግፊት ወይም የስኳር በሽታ ካለብዎ በመጀመሪያ ባለሙያ ያማክሩ። ከአንድ በላይ ህመመ ማስታገሻዎችን አይደባልቁ። ይህ ጉዳት የማጋጠም እድልን ይጨምራል። በቂ ውሃ ይጠጡ ። ኩላሊት ለመስራት እና እራሳቸውን ለመጠበቅ ፈሳሽ ያስፈልጋቸዋል። ሌሎች አይነት የህመም ማስተገሻዎችን አልፎ አልፎ ይውሰዱ። የኩላሊትዎን ጤና ያረጋግጡ። መደበኛ ምርመራ ያድርጉ። ያስተውሉ! ህመም ማስታገሻዎች ፍቱን የሚሆኑት በትክክል ጥቅም ላይ ሲውሉ ነው። ከህመም ማስታገሻ ጋር የተያያዙ የኩላሊት ጉዳቶች ሙሉ በሙሉ መከላከል ይቻላል ። በዝምታ ኩላሊትዎ ሳይደክም ዛሬውኑ እርምጃ ይውሰዱ።
- ታዋቂዋ አርቲስት ለምን ንቅለ ተከላ አስፈለጋት?
ለዓመታት፣ በአለም ዙሪያ ባሉ አድናቂዎቿ በድምጿ ስርቅርቅነት ፣ በፊልሞቿ ሳቢነት እና በሚማርክ ፈገግታዋ የምትታወቀው ሴሌና ጎሜዝን ምን አጋጥሟት ነበር? ከተለመደው የዝና መድረክ ወደ ኋላ ስታፈገፍግ ፤ በወቅቱ ብዙ ጥያቄዎች ተነስተው ነበር። እውነታው፣ በመጨረሻ ስትገልጽ፣ የበለጠ አሳሳቢ ነበር። ሴሌና ጎሜዝ ከሲስተሚክ ሉፐስ ኤራይቲማቶሰስ (SLE) ጋር ትኖር ነበር ። ይህ በሽታ ምንድን ነው? የእርሷ ታሪክ እጅጉን መነጋገሪያ ከመሆኑም በላይ በአለም ዙሪያ ሚሊየኖች የሚያሳልፉትን ተግዳሮት ማሳያ መስታወት ሆነ። በሽታው እንዳለባቸው ሳያውቁ የሚሰቃዩም ብዙዎች ናቸው። ታሪኩ እንዲህ ነው... ሰሌና ጎሜዝ ከህጻንነቷ ጀምሮ የዝና ጣሪያ ላይ የወጣች ፤ የፊልም አክተር ፣ ተዋናይ ነበረች። ፊልሞቿን ዘፈኖቿ በአለም ዙሪያ በብዙዎች ታየተው ተወደዋል። ታድያ ይህች ተዋናይ ለአመታት ይደክማት እንደነበር ገልጻለች። ከድካሟ ባሻገር ከባድ የመገጣጠሚያ ህመም እንደንበረባት እና መገጣጠሚያዎቿም እንደሚያብጡ አስረድታ ነበር። አእምሮዬ እና እኔ (My Mind & Me) በሚለው ዶክመንተሪዋ ላይ እንደውም ... " ከ እንቅልፌ እንደነቃው የማለቅስባቸው ቀናቶች ነበሩ። ህመሙ ከባድ ነበር።" ብላ ገልጻለች። ታድያ ከ አስር አመት በፊት እ.ኤ.አ በ2015 ሉፐስ በሽታ (SLE) እንደተገኘባት ለአለም ይፋ አደረገች ። በሽታው ጤነኛ ህዋሳት በበሽታ መከላከያ ስርአት ሲጠቁ የሚመጣ ነው። ከመጋጠሚያዎቿ ባሻገር ፤ በሽታው በኩላሊቶቿ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ጀምሮ ነበር። እግሮቿ እና እጆቿ ማበጥ ጀመሩ። በህክምናው ይህን በሽታ ተከትሎ የሚመጣው የኩላሊት መቆጣት ሉፐስ ኒፍራይተስ (Lupus Nephritis) ይባላል። ታድያ በጥቃት ስር ያለው ኩላሊቷ መዳከም ጀመረ። እ.ኤ.አ. በ 2017 የኩላሊት ሥራዋ በአደገኛ ሁኔታ መቀነሱ ታወቀ። ይህን ጊዜ ዶክተሮች በአስቸኳይ ንቅለ ተከላ እንደሚያስፈልጋት ነገሯት። ኩላሊት የለገሰችው ጓደኛ ታድያ በዚህ ጭንቅ ጊዜዋ የቅርብ ጓደኛዋ ደረሰችላት። ይህንን እጅግ አስደናቂ ተግባር ሰሌና አመስግናለች። በወቅቱ ጓደኛዋ ፍራንሲያ ራይሳ ኩላሊቷን በመለገሷ ፤ የሰሌና ህይወት ሊድን ቻለ። ይህን ፈታኝና ከባድ ጊዜ ካለፈች በኋላ ሰሌና ማስታወሻ ዶክመንተሪ ሰርታለች። እዚህም ዶክመንተሪ ላይ ከእንደዚህ አይነት ስር የሰደደ ህመም ጋር መኖር የሚፈጥረው የ አእምሮ ቀውስ እና ተከትሎት ስለሚመጣ ውጥረትም ዘርዝራለች። በአሁኑ ወቅት በሽታዋ በቁጥጥር ስር ሆኖ ፤ ንቅለ ተከላ የተደረገው ኩላሊቷ በጥሩ ደረጃ እየሰራ ይገኛል። ሆኖም ግን በሽታው ጋር ተያይዘው ያሉ የረዥም ጊዜ የጤን እክሎች እያስታመመች ፤ ውጤታማ ህይወት እየመራች ትገኛለች። ኤስ አሌ ኢ(SLE) ወይም ሉፐስ ምንድነው? ይህ ሥር የሰደደ ራስን የመከላከል በሽታ ነው። በዚህ በሽታ ጊዜ የሰውነት በሽታ የመከላከል ስርአት ሰውነትን እንደመጠበቅ ፈንታ ፤ በስህተት ጤነኛ ህዋሳትን ያጠቃል። ይህም በሰውነት ዙሪያ የተስፋፋ መቆጣት እና ህመም ያመጣል። ሁሉንም የሰውነት አካል የሚያጠቃ ሲኦን በብዛት መጋጠሚያዎችን ፣ ቆዳን፣ ኩላሊቶችን እንዲሁም አንጎልን ያጠቃል። ምልክቶቹ እና የህመሙ ደረጃ ከሰው ሰው ፈጽሞ ይለያያል። ስርጭቱ ምን ይመስላል? በዓለም ዙሪያ ወደ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሉፐስ አለባቸው። ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ በይበልጥ ይታያል። በተለይ በመውለጃ እድሜ (ከ15-44 ዓመት) ያሉ ሴቶችን ያጠቃል። የአፍሪካ ዝርያ ያላቸው ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ከመሆኑም በላይ ፤ በሽታው ሲያጋጥማቸው ከባድ ሊሆን ይችላል። በሽታውን ቀድሞ ማወቅ ውጤታማነቱን በእጅጉ ያሻሽላል። ምልክቶቹ ምን ይመስላሉ? ሉፐስን በባህሪው "ታላቁ አስመሳይ" ብሎ መጥራት ይቻላል። ለምን? ምክንያቱም ምልክቶቹ ከሌሎች ብዙ በሽታዎች ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ለሉፐስ ተብሎ ካልተመረመሩ ፤ ታካሚዎች ለሌላ በሽታ ሲታከሙ አመታት ሊቆዩ ይችላሉ። የተለመዱ ምልክቶቹ የሚከተሉትን ያካትታሉ የማያቋርጥ ድካም የመገጣጠሚያ ህመም ፣ መደደር/ መድረቅ ፣ እና እብጠት የቆዳ ሽፍታ (በተለይ በጉንጮቹ ላይ የሚታወቀውን የቢራቢሮ ሽፍታ የዚህ በሽታ ምልክት ነው) ጸህይ ብርሀንን አለመቻል (ቆዳ ጸሀይ ሲነካው በቀላሉ ይቆጣል/ ሽፍታ ያመጣል) ትኩሳት ፀጉር መሳሳት የአፍ ቁስል ያልታወቀ የክብደት ለውጦች (መጨመር/መቀነስ) የኩላሊት ችግሮች የደረት ሕመም/ የትንፋሽ እጥረት፣ ወ.ዘ.ተ... እያንዳንዱ ታካሚ ሁሉም ምልክቶች የሉትም። ሉፐስ ምልክቶቹ ከሰው ወደ ሰው በጣም ይለያያል። ሐኪሞች ታድያ ሉፐስን እንዴት ይለያሉ? ሉፐስን ለመለየት ባለሙያዎች የሚከተሉትን ምርመራዎች በጥምረት ይጠቀማሉ። የደም ምርመራዎች (ANA &anti-dsDNA) የኩላሊት ተሳትፎን ለመፈተሽ የሽንት ምርመራዎች የሚታዩ የሕመም ምልክቶች ላይ የተመሰረተ አካላዊ ምርመራ የተጎዱ አካላትን ለማየት የኢሚጂንግ ምርመራ እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱ ናሙና ሊታዘዝ ይችላል። ምልክቶቹ ስውር እና በቀላሉ ሊለዩ የማይችሉ በመሆናቸው ፤ ሉፐስን ለመመርመር ዓመታት ሊወስድ ይችላል። በተዋናይዋም ይህን አይተናል። ህክምናውስ ምን ይመስላል? ሉፐስ ፈውስ የለውም! ሆኖም ግን የበሽታውን ምልክቶቹ የሚያክሙ ፤ የሰውነት መከላከያ ስርአትን የሚያረጋጉ ፤ ዘመናዊ ሕክምና አማራጮች አሉ። እነኝህም አማራጮች ታካሚዎች ውጤታማ እና ደስተኛ ህይወት እንዲመሩ ያስችሉዋቸዋል። ከመድሀኒቶቹም ባሻገር የሚከተሉት ያስፈልጋሉ። መደበኛ የሕክምና ክትትል የፀሐይ መከላከያ ማድረግ (የፀሐይ መከላከያ ክሬም (Sun Screen) ፣ጥላ፣ እንዲሁም ቆዳን የሚከልል ልብስ ማድረግ) የተመጣጠነ አመጋገብ መመገብ መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በቂ እረፍት የአእምሮ ጤና ድጋፍ ቀደም ብሎ ህክምና ማድረግ ፤ አካል ጉዳት እንዳይደርስ ይከላከላልና ፈጽሞ እንዳይዘናጉ። በሽታውንም ቀድመው ይቆጣጠሩ። በግንዛቤ፣ በቅድመ ምርመራ እና በተገቢው እንክብካቤ፣ ታማሚዎች የተሟላ ህይወት እየቻሉ ፤ በስቃይ መኖር የለባቸውም። ለዚህም ምልክቶቹን ያስተውሉ ፤ ቀድመው ህክምና ያድርጉ። ለሌሎች ያጋሩ።
- ስለ ኩላሊት ጤና ማወቅ ያለብዎ?
በአንድ ወቅት (እ.ኤ.አ1990ዓ.ም.) በዓለም ዙሪያ ወደ 378 ሚሊዮን የሚገመቱ ጎልማሶች የኩላሊት ጤና እክል ነበረባቸው። ታድያ አሁንስ? ቀንሷል ብለው ካሰቡ... ተሳስተዋል! ከሠላሳ ዓመት በኋላ - ይህ ቁጥር ከእጥፍ በላይ ጨምሯል። በአሁኑ ወቅት በአለም ዙሪያ ወደ 788 ሚሊየን የሚጠጉ ጎልማሶች ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ (CKD ) አለባቸው። ይህ ማለት በአለም ላይ ካሉ 7 ጎልማሶች ውስጥ አንዱ ኩላሊቱ ሙሉ ጤና ላይ አይደለም ። ምን ያህሉስ ይሆን ይህ ችግር እንዳለበት የሚያውቀው? እርስዎስ የኩላሊትዎ ጤና ያለበት ሁኔታ ያውቃሉ? እ.ኤ.አ በ 2012 (ከ 13 አመት በፊት) የኩላሊት ህመም አለም አቀፍ ካርታ በ 30 አመት ውስጥ ለታየው መጨመር ዋነኛ ምክንያት ተደርገው ስኳር፣ ደም ግፊት፣ ውፍረት እና የተመጣጠነ ምግብ ጉድለት ይጠቀሳሉ። የእነርሱ መጠን በአለም ዙሪያ መጨመር ቁጥሩን አሳድጎታል ተብሎ ይታመናል። በዚህም የተነሳ ከሁለት አመት በፊት በፈረንጆች 2023ዓ.ም ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ዘጠነኛው ገዳይ በሽታ ሆኖ ተመዝግቧል። በዛ አመት ብቻ ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። በሀገራችን ኢትዮጵያስ? በኢትዮጵያም ይህ ችግር በደንብ ይስተዋላል። ሀገር አቀፍ ጠቋሚ ቁጥሮች ባይኖሩም ፤ አንዳንድ በሆስፒታል ላይ የተመሰረቱ ጥናቶች ይህን ይመሰክራሉ። ለምሳሌ፡ በአማራ ክልል በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ፤ ከ 5 ታካሚዎች አንዱ ስር የሰደደ የኩላሊት ህመም አለበት። ለዚህም አጋላጭ ሆነው የተዘረዘሩት የደም ግፊት በሽታ፣ ማጨስ፣ እና የህመም ማስታገሻ መድሀኒቶችን መውሰድ ናቸው። ከ 5 አመት በፊት በስኳር በሽተኞች መሀከል የተደረገ የዳሰሳ ጥናት በበኩሉ ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 3 የስኳር በሽተኞች አንዱ ( 35-36% ) ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ተገኝቶበታል። በዚህ አመት የወጣ አንድ ጥናት ሥር የሰደደ የኩላሊት ህመም በኢትዮጵያ እጅጉን እየጨምረ እንደሚገኝ ጠቁሟል። በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ (እ.ኤ.አ 2019 - 2022) ቁጥሩ በእጥፍ ጨምሯል። ይህም በተለይ በወንዶች ላይ ተስተውሏል። አሁንስ አያሳስብም ? ሀገር አቀፍ መረጃ አለመኖሩ ፤ ችግሩን ሙሉ በሙሉ እንዳንረዳ አድርጎን ይሆናል። ባለን መረጃ እራሱ ችግሩ አሳሳቢ ነው። የተሟላ የኩላሊት ህክምና መስጠት የሚችሉ ተቁሞች በሌሉባት በኢትዮጵያ ከማሳሰብ አልፎ ሊያስፈራን ይገባል። በሀገር ደረጃ የሚመጣ ለውጥ እንዳለ ሆነ ፤ በእርሶ ደረጃ ማድረግ ያለብዎ ላይ ማተኮር አለብዎ። እንደ ማህበረሰብ ዛሬውኑ ለውጥ ማውጣት አለብን። ይህ ደግሞ የኩላሊትዎን የጤና ከማወቅ ይጀምራል። ኩላሊት ሙሉ በሙሉ እስኪዳከም የኩላሊት ምርመራ የማያደርጉ ብዙዎች ናቸው። ስለሚያስፈልግዎ ምርመራ ለማወቅ ይህንን ቪድዮ ይመልከቱ! አስቸጋሪው እውነታ እነሆ... በመጀመሪያዎቹ ደረጃዎች ጊዜ ሥር የሰደደ የኩላሊት ህመም ምንም ግልጽ ምልክቶች ሉትም። የኩላሊትዎ ስራ እያሽቆለቆለ ፤ ብዙዎች የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን ይቀጥላሉ። ለምን? ጤነኛ ናቸው! ሕመም እስካልተሰማቸው ድረስ ፤ ምንም የሚያሳስባቸው ነገር የለም። እውነታው! ብዙ ዲያሊሲስ ላይ ያሉ አልያም ንቅለ ተከላ የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች አስተሳሰብ ከአመታት በፊት እንዲህ ነበረ። ጤነኛ ነበሩ። ምናለበት ያኔ ቀድመው ቢመረመሩ ኖሮ ፤ ሁሉንም መመለስ በቻሉ ነበር። ቻዩ ኩላሊታቸው ታድያ ...ጉዳቱ እያየለ ሲመጣ እና ስራውን መስራት ሲሳነው... ያኔ ምልክቶች ይታያሉ። ታድያ ግን ኩላሊት ስራው ቀድሞውኑ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ ሊሆን ይችላል። የኩላሊት እጥበት ሊያስፈግ ይችል ይሆናል። ብዙዎች ከእርስዎ በፊት የተሳሳቱትን ስእተት እርሶም አይድገሙ። ቀድመው ይከላከሉ። ለመሆኑስ ኩላሊትዎን ጤና እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉስ ያውቃሉ? የኩላሊትዎን ጤና ለመጠበቅ ማድረግ ያለብዎን ለማቅ ይህንን ቪድዮ ይመልከቱ። ምልክቶቹስ ምን ይመስላሉ? የኩላሊት ጉዳት ምልክቶች እንደደረሰው ጉዳት መጠን ይለያያል። መለስተኛ የኩላሊት ጉዳት ይህ የኩላሊት ጉዳቱ መጠን ዝቅተኛ ነው። ጉዳቱን አልፎ ኩላሊት ስራውን መስራት ስለሚችል ፤ የዚህን ጊዜ ምንም ምልክት አይታይም። ታድያ በምርመራ ቢታወቅ ፤ የኩላሊት ጉዳትን ማቆም አልያም እንዳይባባስ ማድረግ ይቻላል። የገፋ ደረጃ የኩላሊት ጉዳት የዚህን ጊዜ ያለው የኩላሊት ጉዳት መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ፤ ኩላሊት ስራውን በትክክል እንዳይሰራ ይስተጓጎላል። የኩላሊት ስራ በመሰናከሉ የሚከተሉት ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ። ክብደት መቀነስ የምግብ ፍላጎት ማጣትም ማቅለሽለሽ ቁርጭምጭሚቶች፣ እግሮች ፣ እጆች፣ አይኖች ላይ እብጠት ትንፋሽ ማጠር ድካም የሽንት ባህሪ ለውጥ ሽንት ደም መቀላቀል ሽንት አረፋ መደባለቅ ደግም ደጋግሞ መሽናት መሀል ለሊት ራሱ ሽንት አዘውትሮ መምጣት የእንቅልፍ መረበሽ/ እንቅልፍ ማጣት የቆዳ ማሳከክ የጡንቻ ህመም ራስ ምታት ምልክቶች ሊኖሩት ይችላል። በወንዶች ስንፈተ ወሲብ (ብልት መቆም ችግር) ሊያመጣም ይችላል። ጉዳቱ እጅጉን አይሎ ኩላሊት ስራውን መስራት ፈጽሞ ሲያቅተው ፡ ሽንት ፈጽሞ አለመውጣት / መሽናት ሊያቅት ይችላል። አእምሮ ላይ በሚኖረው ተጽእኖ ደግሞ የባህሪ ለውጥና ኃይለኝነት ሊያመጣ ይችላል። ደም ማነስ እንዲሁም የኢንፌክሽን ተጋላጭነትም ይጨምራል። ይህን ጊዜ በኩላሊት እጥበት አልያም በንቅለ ተከላ ካልታገዘ ኮማ እንዲሁም ሞት ማብቂያው ይሆናል። ምልክቶቹን እንዳዩ ህክምና ማድረጉ የደረሰው የኩላሊት ጉዳትን ባለበት ለመቆጣጠር ይረዳል። ለዚህም ምልክቶቹን ካስተዋሉ በአፋጣኝ አቅራቢያዎ ወዳለው ጤና ተቋም ይሂዱ። ያስተውሉ! ከሁሉም ከሁሉም መከላከል ይመረጣልና ዛሬውኑ ለኩላሊትዎ ጤና ቦታ ይስጡ። በነሲብ ጤነኛ ነኝ ከማለት ይልቅ አስፈላጊውን ምርመራ አድርገው ዛሬውኑ የኩላሊትዎን ጤና ይጠብቁ። ኩላሊቶችዎ ሲዳከሙ ድምጽ የላቸውምና ያስተውሉ! ዝምታው ወደ ስቃይ ከመቀየሩ በፊት ዛሬውኑ እርምጃ ይውሰዱ።
- የተልባ ጤና ጥቅም: ሳይንስ ወይስ ባህል
ለመሆኑ ተልባ ወስደው ያውቃሉ? በምን መልክ? ተልባ በአለም ዙሪያ ለዘመናት ጥቅም ላይ ውሏል። ከግንዱ እና ቅርንጫፎቹ የሚወጣው ቃጫ ለአልባሳት መስሪያ ሲያገለግል ፤ የተልባ ፍሬ (ዘር) ደግሞ በምግብነት እና በመድሀኒትነት ውሏል። ለምሳሌ ፡ ከ 5000 አመታት በፊት በጥንታዊቷ ግብጽ ለመድሀኒትነት ጥቅም ላይ ዉሏል። ተልባ ንጽህናን እና ህይወትን ያሳያል ብለው ያምኑ ስለነበር ፤ በሱ የሚሰሩ አልባሳትን ለአምልኮ ጊዜ ይጠቀሟቸው ነበር። የህክምና አባት በመባል የሚታወቀው ሂፖክራተስም የተልባ ፍሬ የሆድ ህመሞችን እና አንጀት ችግሮችን እንዲያድን ያዝ ነበር። በአውሮፓ፣ በኢሲያ እንዲሁም በአፍሪካም ተልባ ውስጡ ላለው ዘይት እንዲሁም ለልብስነት ጥቅም ላይ ይውል ነበር። በኢትዮጵያ ተልባ ብዙ ባህላዊ ጥቅም አለው። ለዘይትነት፣ ለምግብነት፣ ለመድሀኒትነት ሲውል ቆይቷል። እናቶቻችን እና አያቶቻችን ለጨጓራ ህመም ፣ ለሆድ ድርቀት እንዲሁም ማህጸንን ለመክፈት (ባህላዊ አባባል) አውለውታል። ታድያ ይህ እውነት ወይስ ትውፊት ? በሳይንስ እና በባህል መሀል ያለውን እንመርምር። ባህላዊ ጥቅሙ በይበልጥ ሊያውቁት ስለሚችሉ ፤ ስለ ሳይንሱ ብቻ እናነሳለን። ተልባ በውስጡ ምን አለ? ዘመናዊ ሳይንስ እንደሚያሳየው ተልባ በልዩ ንጥረ ነገሮች/ውህዶች የበለጸገ ነው። ውስጡ ካሉ ንጥረ ነገሮች በዋነኝነት ህክምናዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው የተረጋገጡት የሚከተሉት ናቸው። አልፋ-ሊኖሌኒክ አሲድ (ALA) - ይህ ከእጽዋት የሚገኝ እንደ ኦሜጋ 3 ፋቲ አሲድ (Omega 3) ሲሆን ፤ በይበልጥ በተልባ ዘይት ውስጥ ይገኛል። በህክምናው ኦሜጋ 3 ፋቲ አሲድ ፤ ነርቮች ላይ ባለው መልካም ተጽእኖ የአእምሮ እድገትን ያጎለብታል። ለዚህም ለህጻናት ተለይቶ ይሰጣል። ሊግናንስ (በዋነኛነት secoisolariciresinol diglucoside/ SDG የሚባለው) - ይህ እጽዋት ውስጥ ከሚገኙ ፖሊፌኖል(polyphenol) ከሚባሉ ውህድ አይነቶች ውስጥ አንዱ ነው። እነኝህ ውህዶች ሰውነት መቆጣትን ይቃወማሉ። የጸረ ኦክሲዳንት ባህሪ አላቸው። እንዲሁም የኢስትሮጅ ሆርሞን ተመሳሳይ ባህሪ አላቸው። በውስጣቸው አሰር (ፋይበር) አላቸው ፡ ይህ ደግሞ የምግብ መፈጨትን ያሻሽላል። የኮሌስቶሮል ኡደንትም ያስተካክላል። የደም ስኳር መጠንም ላይ ተጽእኖ ያሳድራል። ፕሮቲን፣ ቫይታሚኖች እና ማዕድናት አሉት - ውስጡ ፕሮቲኖች፣ ቫይታሚኖች እንዲሁም ማእድናት ቢኖሩትም ፤ መጠናቸው አነስተኛ ስለሆነ ፤ የእነሱ ዋነኛ ምንጭ መሆን አይችልም። በተጨማሪ ምግብነት ማገልገል ይችላል። ሳይንሳዊ ጥናቶችስ ስላለው የጤና ጥቅም ምን ይላሉ? ብዙ ጥናቶች በዚህ ዙሪያ የተካሄዱ ቢሆንም ፤ በይበልጥ በማስረጃ የተደገፉት የሚከተሉት ናቸው። 1) የመጥፎ ኮሌስትሮል( LDL) እና የአጠቃላይ ኮሌስትሮል(Total Cholesterol) መጠንን ይቀንሳል። ወደ መደበኛ ደረጃ ያወርዳል። የተልባ ዘር (ተፈጭቶ ሆነ ጥሬውን) የሰውነት የኮሌስትሮል መጠንን የመቀነስ አቅም አለው። የመቀነስ አቅሙ በተለይ የኮሌስትሮል መጠናቸው ከፍ ያለና ያረጡ ሴቶች ላይ በይበልጥ ይስተዋላል ። እ.ኤ.አ. በ 2009 የተለቀቀ ጥናትም ይህንን ይደግፋል። ተልባ የወሰዱ ሰዎች የኮሌስትሮል መጠናቸው ተሻሽሏል። ከዚህም ባሻገር የተደረጉ ጥናቶች የደም ውስጥ ያለ ስብን የመቀነስ አቅሙን ይጠቁማሉ። ሆኖም ግን የደም ኮሌስትሮል መጠንን የሚቀንሰው ፤ በአንድ ቀን አልያም በከፍተኛ መጠን አለመሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። የሚቀንሰው በመጠኑ ነው። 2) የደም ግፊትን ይቀንሳል(በተለይም የደም ግፊት ባለባቸው ሰዎች ላይ)። በቅርብ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ የተልባ ፍሬ የደም ግፊት ቁጥጥርን ያሻሽላል። ይህ መሻሻል በይበልጥ የሚስተዋለው የደም ግፊታቸው ከፍ ባለ ወይም የደም ግፊት በሽታ ባለባቸው ታካሚዎች ላይ ነው። ጥናቱ የተደረገባቸው ታካሚዎች ተልባ በመጠቀማቸው የላይኛው የደም ግፊት (ሲስቶሊክ) እንዲሁም የታችኛው የደም ግፊት (ዳያስቶሊክ) መጠን በአመርቂ ሁኔታ ቀንሷል። ይህ ተልባን የደምግፊት መድሀኒት መተኪያ ባያደርገውም ፤ ደም ግፊት ላለባቸው ሰዎች የደም ግፊታቸውን ለመቆጣጠር የሚረዳ የአኗኗር ዘይቤ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ለዚህም የሚያውቁት ደም ግፊት ያለበት ሰው ካለ ተልባ እንዲያዘወትር ይምከሩት። ይጠቅመዋል! 3) የሰውነት መቆጣትን ይቀንሳል። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከሆነ ተልባ ውስጥ ያሉ ውህዶች የሰውነት መቆጣትን ይቀንሳሉ። ይህም የመቆጣትን የሚያባብሱ ውህዶችን ( TNF-α, IL-1β, and IL-6 ) ከመቀነሱ ጋር እንደሚያያዝ የሚጠቁሙ ጥናቶች አሉ። ስብ ላይ እንዲሁም ኦሜጋ 3 ፋቲ አሲድ ላይ ያለው ተጽእኖ እንዲሁም የጸረ ኦክሲዳንት ባህሪውም ለዚህ ምክንያት ተደርገው ይጠቀሳሉ። በዚህ ዙሪያ ብዙ ጥናቶች አሁንም ይቀራሉ። 4) የልብ ጤናን ያሻሽላል። ተልባ ፍሬ ውስጥ ያሉት ውህዶች የልብ ጤናን ያሻሽላሉ። ይህም በተለያየ መንገድ የሚፈጠር ሲሆን ፤ ከዚህ ውስጥ ኮሌስትሮልን መጠን መቀነሱ አንዱ ነው። ከዚህም ባሻገር የደም ግፊትን መቆጣጠሩ ፣ የጸረ ኦክሲዳንት ባህሪው፣ መቆጣትን መቀነሱ እንዲሁም የደም የስኳር መጠን መቀነሱም ሊጠቀስ ይችላል። ልብ ላይ ያለው መልካም ተጽእኖ ቢረጋገጥም ፤ በዚህም ዙሪያ ጥናቶች ገና ሙሉ በሙሉ አልተደራጁም። 5) የምግብ መፈጨትን ያሳልጣል። የተልባ ዘር በፋይበር/አሰር የበለጸገ ነው። ይህ ደግሞ የአንጀትን ጤናማ እንቅስቃሴ ያበረታታል። እንዲሁም የአንጀትን ስራ ይደግፋል። በዚህ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ተልባን በየቀኑ መጠቀም ድርቀትን ይቀንሳል። ሽንትቤት በተደጋጋሚ መጠቀም እንዲችሉ ያደርጋል። ይህ ጥቅሙ ከመካከለኛ እድሜ በላይ ባሉ ሰዎች ላይ በይበልጥ ታይቷል። ውስጡ ያለውም የሚዝለገለግ የሚመስል ውህድም ፤ እንደ ተፈጥሮአዊ ጄል በመሆን ፤ የጨጓራ እና የአንጀት ግድግዳን ይሸፍናል። ይህም ሆድን ከጉዳት ከመጠበቁም ባሻገር የምግብ ቱቦን ጤና ያሻሽላል። 6) የካንሰር ተጋላጭነትን ይቀንሳል። የላብራቶሪ እና የእንስሳት ጥናቶች እንደሚያሳዩት ፤ ተልባ ውስጥ የሚገኙት ሊግናን የሚባሉት ውህዶች የዕጢን እድገት ይቀንሳ። ህዋሳት ያለ ቁጥጥር እንዳያድጉ ይከላከላሉ። ይህ ውስጡ ያሉ የኢስትሮጅን ባህሪ ካላቸው እንዲሁም መቆጣትን ከሚቀንሱት ኬሚካሎች ጋር ይያያዛል። ሆኖም ግን በዚህ ዙሪያ ያሉ ጥናቶች መጀመሪያ ላይ ናቸው ያሉት። ለዚህም ካንሰርን የመከላከል አቅሙ ሙሉ በሙሉ አልተረጋገጠም። 6) ገና ያልተረጋገጡ ጥቅሞች አንዳንድ ጥናቶች የተልባ ፍሬ ውስጡ ያለው ኤኤልኤ የሚባለው ኬሚካል የነርቭን ጤና እንደሚያሻሻል እንዲሁም የአእምሮን አቅም የማጎልበት ኃይል እንዳለው ይጠቁማሉ። ውስጡ ያለው የኢስትሮጂን ባህሪ ያለው ውህድ ላረጡ ሴቶች የማረጥ ምልክቶችን የመቀነስ አቅም እንዳለው ያሳያሉ። ሆኖም ግን እነኝህ ጥቅሞች ገና በህክምና ሙሉ በሙሉ አልተረጋገጡም። በዚህ ዙሪያ ጉዳት ባይኖራቸውም ፤ ጥቅማቸውን አፍ ሞልቶ ለመናገር የሚያስችሉ ጥናቶች የሉም። ምናልባት በቀጣይ አመታት የሚደረጉ ጥናቶች በደንብ ይህንን ያሳዩ ይሆናል። ⚖️ ስለ ተልባ ግልጽ መሆን ያለባቸው ነገሮች አንዳንድ ጊዜ የተልባ ዘር ካንሰርን "ይፈውሳል"፣ የልብ ሕመምን "ያድናል" ወይም ክብደትን የሚቀንስ ተአምራዊ ምግብ ነው የሚሉ ፤ መሰረት የለሽ መረጃዎችን ሰምተው ያውቁ ይሆናል። ይህ ግን በመረጃ የተደገፈ አይደለም። መረጃዎች የሚናገሩትን ያስተውሉ። እዚህ ጋር ግልጽ መሆን አለብዎ፡ ካንሰርን "አይፈውስም።" ስብን/ቅባትን/ ኮሌስትሮልን በአንድ ሌሊት "አያጠፋም።" ቀስ በቀስ ነው የሚቀንሰው። የልብ በሽታን አያጠፋም ወይም አይፈውስም። የልብ ጤናን የሚያሻሽሉ ውህዶች ግን አሉት። ስለዚህ የልብ ጤና ይሻሻላል። የተለያዩ በሽታዎችን የሚቀንሱ ውህዶች ቢኖሩትም ፤ ለማንኛውም በሽታ የሚታዘዝ ህክምና ምትክ አይደለም። ተልባ ምግብ ነው - ገንቢ፣ ደጋፊ ምግብ ። ሆኖም ግን ተአምራዊ አይደለም። 🥄 በትክክለኛው ሁኔታ እንዴት መጠቀም ይችላሉ? ✔️ ከመመገብዎ በፊት ይፍጩት። ለምን? ያልተፈጨ ተልባ ፍሬዎች በአንጀታችን ሳይፈጩ ሊያልፉ ፤ በሰገራ ሊወጡ ይችላሉ። ✔️ በቀን 1–2 የሾርባ ማንኪያ ይውሰዱ። በሚመገቧቸው ምግቦች ውስጥ (እንደ ገንፎ፣ ጭማቂዎች ፣ ሰላጣ፣ ስሙዚ፣ ቧል፣ ወ.ዘ.ተ...) ይጨምሩ። አብዝተው መውሰድ አይመከርም። ✔️ በአግባቡ ያስቀምጡ ። የተፈጨ ተልባ በቀላሉ ስለሚበላሽ ፤ ያዘጋጁትን በማቀዝቀዣ ውስጥ ያስቀምጡ። ✔️ የደም ማቅጠኛዎችን የሚወስዱ ወይም የሆርሞን ችግሮች ካሉብዎ ፤ በቅድሚያ የጤና ባለሙያን ያማክሩ። 🧠መደምደሚያ ተልባ መመገብ ባህል ብቻ አይደለም! አያቶቻችን በባህል ተመስርተው ሰጥተውን ቢሆም ፤ አሁን በሳይንስ የተደገፈ ጥቅም አለው። እርስዎም የሚመገቡት ምግብ ውስጥ ይደባልቁ።
- የታይፈስ ወረርሽኝ እና መከላከያዎቹ
እንደ ታሪክ መዛግብት ከሆነ... ታይፈስ የሰው ልጅን ለብዙ መቶ አመታት ሲያሰቃይ የቆየ የትኩሳት ህመም ነው። ከትላልቅ ጦርነቶች ፣ ረሀቦች ፣ ስደቶች ጋር ታይፈስ አብሮ ይነሳል። ከጦርነት የተረፉትን ሰራዊት የጨረሰ ነው። በአውሮፓ በ 16ተኛው ክፍለዘመን ብዙዎችን በዚህ ወረርሽኝ አልቀዋል። በ19ኛው ክፍለዘመን በታላቋ አየር ላንድ ባጋጠመው ትልቅ ረሀብ (1846-49) ጊዜም በረሀብ ላይ ተደርቦ የብዙዎችን ህይወት ነጥቋል። በአንደኛው የአለም ጦርነት በተለይም በምስራቅ ግንባር፤ ታይፈስ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች፣ እስረኞች እና ሲቪል ማህበረሰብ ሞት ተጠያቂ ነው። በምዕራብ አውሮፓ የታይፈስ ስርጭት ሊቀንስ የቻለው ፤ በተደረገ መሰረታዊ ለውጥ ነው። የንፅህና አጠባበቅ ሲሻሻል ፣ የተባይ ቁጥጥር ሲጨምር፣ የተሻለ መኖሪያ ቤቶች ሲገነቡ ፤ በጦርነት ጊዜ እንደዲዲቲ ያሉ ፀረ-ተባዮች ሲረጩ የታይፈስ ስርጭት ቀንሷል። በመጽሐፍት ውስጥ በሹክሹክታ የተጠቀሰው ይህ በሽታ አሁንም በአለማችን ውስጥ አለ! አብዛኞቻችንም እናውቀዋለን! ይህ ታሪክ አንድ ዋና እውነትን ያሳያል። ታይፈስ በችግር ጊዜ የሚበረታ በሽታ ነው። ክፉ ቀናቶችን ጠብቆ ፤ በትሩን ሰዎች ላይ የሚያነሳ ፤ ብዙዎችን ህይወት የሚነጥቅ ነው። ከጦርነት፣ ከረሃብ፣ ከመፈናቀልና ከድህነት ጋር ተያያዥነት አለው። ለምን? ስያሜውም ከበሽታው ምልክት ጋር ቁርኝት አለው። በሽታው ሲደረጅ የሚያሳየውን ድብርት ስሜት፣ግራ መጋባትና የሀሳብ መንፈዝ ለመግለጽ ስሙም ታይፈስ ተባለ። ታይፈስ የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙም መንፈዝ/ሞኝነት አልያም ጭጋግ (ሲታመሙ የአስተሳስብ ጭጋግ/መንፈዝ ስላለ) ነው። ታይፈስ ምንድን ነው? በመጀመሪያ ታይፈስ አንድ በሽታ ብቻ አይደለም። ሪኬቲስያ እና ኦረንሺያ የሚባሉ የባክቴሪያ ዝርያዎች የሚመጣ የኢንፌክሽን በሽታ ነው። እነኝህ ባክቴሪያዎችም በቅማል ፣ ቁንጫና ቅንቅን ውስጥ መቆየት ስለሚችሉ ፤ በተባዮች የተነሳ ከታማሚ ወደ ጤነኛ ይተላለፋል። በባክቴሪያው አይነትና በመተላለፊያ መንገዱ ስንመልከት 3 አይነት ታይፈስ አለ። ከ እነኝህ ውስጥ ሁለቱ በኢትዮጵያ ላይ በብዛት ይስተዋላሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት የሚታዩ ታይፈሶች ታይፈስ ከሚያመጡ ተባዮች ውስጥ አንዱ የሆነው ቅማል ወረርሽኝ የሚያመጣው ታይፈስ - ይህ ታይፈስ ሪኬቲስያ ፕሮዋዜኪ በሚባል ባክቴሪያ አይነት የሚመጣ ነው። በቅማልም ይተላለፋል። በባህሪውም ወረርሽኝ የማምጣት አቅም አለው። ታይፈስ ከሚያመጡ ተባዮች ውስጥ አንዱ የሆነው ቁንጫ ከአይጥ ጋር ግንኙነት ያለው ታይፈስ- ይህ ታይፈስ አይጥንም ሊያጠቃ የሚችል ሲሆን ሪኬትሲያ ታይፊ በሚባል ባክቴሪያ ይመጣል። የሚተላለፈውም በቁንጫ ነው። የታመሙ ሰዎች/አይጦችን የበላ ቁንጫ በሽታውን ሊያስተላልፍ ይችላል። ኢትዮጵያ እምብዛም የሆነው ታይፈስ ታይፈስ ከሚያመጡ ተባዮች ውስጥ አንዱ የሆነው ቅንቅን ይህ በቅንቅን አማካኝነት የሚተላለፍ ታይፈስ ሲሆን ፤ በህክምና ስሙ ስክረብ ታይፈስ ይባላል። ይህ ታይፈስ ኦሪየንታ በሚባለው ባክቴሪያ አይነት የሚመጣ ሲሆን በአለም ላይ በእስያ ፓስፊክ ክልል (ከምስራቅ ኢስያ በደቡብ ምስራቅ ኢስያ እስከ ኦሽንያ ባሉ ሀገራት ) ብቻ ይታያል። በቅንቅን አማካኝነትም ሊተላለፍ ይችላል። እንዴትስ ይተላለፋል? ለመተላለፉ በመጀመሪያ የታመመ ሰው/ የአይጥ ዝርያ ያስፈልጋል። ተባዮቹ በታይፈስ የተያዘውን ሰው ሲበሉ ፤ ባክቴሪያው ወደ ሰውነታችው ይገባል። እነኝህ ባክቴሪያውን የተሸከሙ ተባዮች ጤነኛ ሰው ሲበሉ የማሳከክ ስሜት ይፈጥራሉ። ይህን ጊዜ ጤነኛው ሰው አኮ ሲገድላቸው ፤ ተባዮቹ ውስጥ ያለው ባክቴሪያ ሲታከክ በተፈጠረው የቆዳ ክፍተት ወደ ጤነኛ ሰው ደም ይገባል። ደም ውስጥ ገብቶ ሲራባ ፤ ሰውየው የኢንፌክሽን ምልክት ማሳየት ይጀምራል። ትኩሳት ይኖረዋል። ሽፍታም ያሳያል። ምልክቶቹን በደንብ ይለዩ! እንዲህ ያስቡማ....ዛሬ ጤናማ ነዎት.... ጤናዎ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዳለ በተወሰኑ ቀናት ልዩነት ውስጥ ከባድ ትኩሳት ይኖርዎታል። ትኩሳቱ ከ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሊያልፍ ይችላል። ራስ ምታት(ከባድ ሊሆን ይችላል) ብርድ ብርድ ማለት የጡንቻ ህመምና የሰውነት ድካም ሊያሳዩ ይችላሉ። የታይፈስ ሽፍታ ትኩሳቱን ባዩ በቀናቶች ውስጥ ሽፍታ ሊኖርዎት ይችላል። ሽፍታው ሲጀምር ከደረትዎ/ ሆድዎ/ ጀርባዎ ተነስቶ ፤ ወደ እጅዎ መዳፍ እና ውስጥ እግርዎ ሊስራጭ ይቻላል። ከዚም ባሻገር ከምግብ ቱቦ ጋር የተያያዙ ምልክቶች ሊያስተውሉ ይችላሉ። ለምሳሌ የ ማቅለሽለሽ ስሜት ማስታወክ፣ እንዲሁም የሆድ ህመም አይነት ምልክቶች ሊያሳዩ ይችላሉ። ሳልም ሊኖርቦት ይችላል። ህመሙ ከባሰ ግን ፡ ድብርት እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት ግራ መጋባት የአስተሳሰብ ለውጥ /መንፈዝ ሊኖርብዎት ይችላል። ታድያ ታይፈስን አስቸጋሪ የሚያደርገው... ከሌሎች የትኩሳት ህመሞች ጋር መመሳሰሉ ነው። የኢንፌክሽን ህመም ስርጭት በበዛባት ኢትዮጵያ ታይፈስ በሽታ እስኪለይ ትንሽ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል። እርስዎ እርስዎ ግን ለተባይ መጋለጥዎን መለየት ቢያቅትዎ እንኳን... በአቅራቢያዎ/በጎረቤትዎ ታይፈስ የታመመ ሰው ከነበረ ወይም እነኝህን ምልክቶች የሚያሳይ ሰው ከነበረ እና እርስዎ ከእነኝህ ምልክቶች ውስጥ ብዙዎችን ካሳዩ በአፋጣኝ ጤና ተቋም ሄደው ምርመራ ያድርጉ። ታይፈስ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ እድሉ አነስተኛ ነው። ብዙ ጊዘ አስተላላፊ የሆኑ ተባዮች ያስፈልጋሉ። ለዚህ አጋላጭ ምክንያቶች ተብለው የሚጠቀሱት እነኝህ ተባዮች እንዲሁም አይጦች እንዲራቡ የሚያስችል አከባቢዊ ሁኔታዎችን ነው። ለዚህም የተጨናነቀ አኗኗር ካለ (በትንሽ ቦታ ላይ ብዙ ሰው መኖር) የንጽህና ጉድለት ካለ ቅማል እና ቁንጫ በመኖሪያ/በመቆያ ስፍራ ከበዛ አይጦች በአከባቢው ከበዙ ተጋላጭነት ይጨምራል። ድመቶች ያሏቸውም ሰዎች ፤ ድመቶች ከአይጦች ጋር ንክኪ ስለሚኖራቸውና ቁንጫ ስለሚያመጡ እቤት ውስጥ ጸረ ተባይ ካልረጩ ፤ ሳያውቁት ሊጋለጡ ይችላሉ። እላይ በጠቀስናቸው ምክንያቶች የተነሳ የታይፈስ ወረርሽኝ በእስር ቤቶች ውስጥ፣ በስደተኞች ማቆያ ካምፖች ፣ በጦር ካምፓች ፣ በተጨናነቁ ሰፈሮች ፣ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ተሰብስበው በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ይታያል። ሕክምናውስ ምን ይመስላል? መልካሙ ዜና... ታይፈስ ሊታከም ይችላል። ታክሞም ይድናል! ታይፈስን የሚያመጡ ባክቴሪያዎችን የሚቃወም አንቲባዮቲክ (የባክቴሪያ መቃወሚያ) በመውሰድ ከ ታይፈስ መዳን ይቻላል። ክዚህም ባሻገር የድጋፍ ህክምና ያስፈልጋል። ለዚህም ትኩሳቱን ፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ ሆድ ህመም ካለ እሱን ማከም ፈሳሾት መውሰድ ፤ እረፍት ማድረግ ፤ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ይመከራል። ታይፈስ በሰውነትዎ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት መከታተል ያስፈልጋል። በሽታው ከደረጀ ኩላሊትን፣ ሳንባ እና አንጎልዎትን ጨምሮ ሊያጠቃ ይችላል። ያሰተውሉ! ቶሎ ህክምና ከተደረገ ፤ የህክምናው ውጤት እጅጉን መልካም ነው። ካልታከመ ግን ሞት ሊያደርስ ይችላል። በታሪክ እንዳየነው የብዙዎችንም ህይወት ይቀጥፋል። እንዴት መከላከል ይቻላል? መከላከል ከፈውስ በላይ ነው! ለመከላከል እነኝህን ያድርጉ፡ በሁለተኛ የአለም ጦርነት ጊዜ ታይፈስን ለመከላከል የተለቀቀ ማሳሰቢያ የአከባቢዎን እና የመኖሪያ ቤትዎን ንጽህና ይጠብቁ። ለተባዮች ያሎትን ተጋላጭነት ይቀንሱ። ተባይ በቤትዎ ከበዛ ጸረ ተባይ ይጠቀሙ። የግል ንጽህናዎን ይጠብቁ። ልብሶችዎን በአግባቡ ያጽዱ። አይጥ ከቤትዎ ያጥፉ። ቁጥቋጦዎች ከአከባቢዎ ያስወግዱ። የቤት እንሰሳ ካለ ተባዮች እንዳይኖሩባቸው ንጽህናቸውን ይጠብቁ። በተጨናነቀ ስፍራ የሚኖሩ ከሆነ ቅማል እና ቁንጫ ስርጭት እንዳይኖር ይጠንቀቁ። ከዚህም በላይ ብዙዎች በቅማል እና በቁንጫ እንደሚመጣ አያውቁምና ግንዛቤን ያስጨብጡ ። ይህንን ትምህርታዊ መረጃ ለሌሎች ያጋሩ። ስርጭቱ ምን ይመስላል? የታይፈስ ወረርሽኝ ባዳጉ ሀገራት አይታይም። በተቃራነው ጦርነት፣ ድህነት ፣ ረሀብ በተንሰራፋባቸው ሀገራት ስርጭቱ ከፍ ያለ ነው። በኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ስርጭቱን የሚያሳይ በቅርብ የተደረገ ጥናት ባይኖርም ፤ እ.ኤ.አ 1981-1990 ውስጥ 14,078 የታይፈስ በሽተኞችን መኖራቸውን ኢትዮጵያ ሪፖርት አድርጋ ነበር። ይህ መጠን በወቅቱ በአፍሪካ ከተመዘገብው ሁለት ሶስተኛውን ይወስዳል። እ.ኤ.አ ከ 2008 እስከ 2012 ባሉ አራት አመታት በአዲስ አበባ ቃሊት እስር ቤት ውስጥ የተደረገ ጥናት በበኩሉ ፤ አንድ አራተኛ የሚሆኑ እስረኞች የታይፈስ ኢንፌክሽን ምልክት ደማቸው ውስጥ ታይቷል። በአሁኑ ጊዜስ ምን ያህል ይሆን? ማጠቃለያ በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ካላት አንገብጋቢ ሁኔታዎች አንጻር ፤ ታይፈስ በሽታ አርዕስተ ዜና ሊሆን ባይችልም ፡ ትኩረት ሊሰጥው ይገባል። ቀድሞ ማወቅ ህይወት ያድናልና። ፈጠን ብለው አውቀው አፋጣኝ ህክምና ያድርጉ። ቀድመውም ይከላከሉ። የእርስዎን ጤና ጠበቁ ማለት የማህበረሰብዎን ጤና ጠበቁ ነው። በቀጣይ ከታይፈስ ጋር አብዝቶ የሚነሳው ታይፎይድ ህመም ዙሪያ ትምህርታዊ ጽሁፍ ስለምንለቅ ይከታተሉ።
- በእንቅርት ላይ...
እንቅርት በሽታን የማያውቅ አለ ማለት ዘበት ነው! ግን ግንዛቤዎ ምን ያህል ነው?እንቅርት በሽታ ከጨው ጋርስ ግንኝነት እንደሌለው ያውቃሉ? እንቅርት በሽታ የሰውነታችን ውስጥ ዋነኛ እጢዎች መሀክል አንገታችን መሀል ከማንቁርታችን ፊትለፊት የሚገኘው የታይሮይድ እጢ ማደግ ነው። ይህ እጢ በተፈጥሮው የቢራቢሮ ቅርጽ ያለው ሲሆን ፤ መጠኑ ካልገዘፈ በስተቀር በአይናቸን ለመለየት ያስቸግራል። ስራውስ? ስራው እጅጉን ሰፊ ነው። በዚህ እጢ የሚመረተው ሆርሞን (ታይሮይድ ሆርሞን) በአንድ በኩል ወይም በሌላ የማይነካው የሰውነት ክፍል የለም። የዚህ ሆርሞን ስራዎች ውስጥ ጥቂቶቹ፡ የሰውነትን ኡደት (ሜታቦሊዝም) ይከታተላል። ለዚህም ሰውነታችን ኃይል አጠቃቀም ፣ ግሉኮስ መጠቀሙን፣ ሙቀት ማምረቱን ፣ ወ.ዘ.ተ ላይ ተጽእኖ አለው። እድገትን ይደግፉል - ለልጆች አካላዊ እድገት አስፈላጊ ነው። የአንጎል እድገትን ያግዛል - ለፅንስ እና ለጨቅላ ህጻናት አንጎል ስራ እና እድገት አስፈላጊ ነው. የልብ ሥራን ይጠብቃል - የልብ ምት እና የደም ዝውውርን ሊጨምር ይችላል። የሰውነት ሙቀትን ይቆጣጠራል - ሰውነታችን መደበኛውን የሙቀት ሚዛን እንዲጠብቅ ይረዳል። የምግብ መፈጨትን ይደግፉል - የምግብ ፍላጎትን እና የአንጀት እንቅስቃሴን ያበረታታል። የስነ ተዋልዶ ጤና ላይ ተጽእኖ አለው - የወር አበባ ዑደትና የመውለድ መቻል ላይም ተጽእኖ አለው። የቆዳ፣ የፀጉር እና የጡንቻን ጤንነት ይጠብቃል። ቀይ የደም ህዋሳት ምርት ላይ ያግዛል። ከሌሎች ሆርሞኖች ጋር በመተባበርም የሰውነት ስርዓቶችን ሚዛናዊነት ይጠብቃል ። ታድያ ይህ እጢ በተፈጥሮ ከተለመደው መጠኑ ይልቅ ሲያልፍ እንቅርት ወይንም ጎይተር አጋጠመ እንላለን። ጎይተር በሽታ በአለም በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን በአለም ዙሪያ እንደሚያጠቃ የዓለም ጤና ድርጅት ይገልጻል። ወደ 30 ፐርሰንት የሚጠጋው የአለም ህዝብ የአዮዲን እጥረት ባለባቸው አከባቢዎች ይኖራል። የአዮዲን እጥረት ደግሞ የእንቅርት በሽታ ዋነኛ አጋላጭ ተደርጎ ይገለጻል። በአለም ዙሪያ ወደ 2 ቢሊየን የሚጠጋ ህዝብ ለዚህ እጥረት እንደተጋለጠ ከዚህም ውስጥ ወደ 241 ሚሊየን የሚጠጉት ልጆች እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ሀገራችን ኢትዮጵያም እንቅርት በሽታ በስፋት ካሉባቸው ሀገራት ተርታ ትጠቀሳለች። የዚህ በሽታ መጠን ከ 40 እስከ 43 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎችን እንደሚያጠቃ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ለምን? በአንድ በኩል ለዚህ ተጠቃሽ የሚደረገው የምንጠቀመው ጨው ውስጥ ያለው የአዮዲን መጠን ነው። በመልካም ጎኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ለቤት ውስጥ ፍጆታ የምንጠቀመው ጨው ውስጥ እስከ 89 ፐርሰንት የሚጠጋው አዮዲን አለው። ሆኖም ግን ይህ ጨው ውስጥ ያለው የአዮዲን መጠን በቂነት አጠራጣሪ ነው። የህጻናት ተማሪዎች የሽንት ምርመራ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ይህንን ይጠቁማሉ። ምርመራ የተደረገላቸው ተማሪዎች ሽንታቸው ውስጥ ከ 25 ማይክሮ ግራም ያነሰ አዮዲን ተገኝቷል። ይህ ደግም ሰሞኑን የተመገቡት የአዮዲን መጠን አነሰተኛ መሆኑን ጠቋሚ ነው። የአለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠው ደረጃ በቂ አዮዲን የሚወስድ ሰው ቢያንስ በሽንቱ ውስጥ ከ100 ማይክሮ ግራም በላይ አዮዲን መገኘት አለበት። ይህ ደግሞ አዮዲን ያለው ጨው ተደራሽነት በሚቀንስባት በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ለሚኖሩ ሰዎች እና ለእርጉዝ ሴቶች እጅጉን አሳሳቢ ነው። ያስተውሉ እንቅርትን የሚያስከትለው የጨው ሳይሆን የአዮዲን ማነስ ነው ። ለምንድነው አዮዲን ማነስ ይህንን ችግር እያስከተለ ያለው? እላይ እንደተገለጸው የዚህ እጢ ስራ ታይሮይድ ሆርሞን ማምረት ነው። ይህ ሆርሞን የተለያዩ አይነቶች ቢኖሩትም (T3 & T4) ፤ ይህ ሆርሞን አካል ውስጥ አዮዲን አለ። ፌሮ የህንጻ አካል እንደሚሆነው የአዮዲን ንጥረ ነገርም የዚህ ሆርሞን አካል ነው። ታድያ ይህ ንጥረ ነገር ሲያንስ ሰውነታችን የሚረዳው የታይሮይድ ሆርሞን ምርት ማነሱን ነው። ያነሰውን ምርትም ለማሻሻል ሰውነት አምራች አካሉን (እጢውን) ማስፋት ይጀምራል። ምርት እንዲጨምር ፋብሪካ እንደማስፋት ማለት ነው። ይህ ደግሞ ታይሮይድ እጢ እንዲገዝፍ ወይም መጠኑ እንዲጨምር ያደርጋል። ችግሩ የምርት ማነስ ስላልሆነ ፤ የአዮዲን እጥረት እስኪስተካከል ድረስ ሰውነት እጢውን መጠን ለመጨመር ይሞክራል። ለዚህም ነው ትላልቅ እንቅርት ያላቸው ታማሚዎች የምናየው። አዮዲን እጥረቱ ቢስተካከልም ሰውነት አንዴ እጢውን ስላሳደገው መልሶ አያፈርሰውም። ለዚህም አንዴ እንቅርት ከታየ ያለ ህክምና እርዳታ ሊጠፋ አይችልም። 👉 በቀላል አነጋገር ጎይተር/ እንቅርት የታይሮይድ እጢዎ የድረሱልኝ ጥሪ ምልክት ነው። ይህ ምልክት ሰውነትዎ በአዮዲን እየቀነሰ መሆኑን ሊያመላክት ይችላል። ⚠️ በዋነኝነት ተጋላጮች ማናቸው? ዝቅተኛ የአዮዲን የሚመገቡ ግለሰቦች፡ የባህር ምግቦችን ፣ የወተት ተዋጽኦዎችን ፣ እንዲሁም አዮዲን ያለበት ጨውን የማይመገቡ ግለሰቦች ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ነው። በገጠሪቷ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ግለሰቦች ፡ አዮዲን ያለው ጨው ተደራሽ ባልሆነባቸው አከባቢዎች እንዲሁም አፈር ውስጥ ያለው አዮዲን መጠን ዝቅተኛ በሆኑ አከባቢዎች (አንዳንድ ትግራይ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ያሉ ስፍራዎች) የሚኖሩ ግለሰቦች ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ነው። ሴቶች በተለይም በጉርምስና እድሜያቸው፣ በእርግዝና ወቅት እና ጡት በማጥባት ወቅት የአዮዲን ፍላጎታቸው ከፍ ይላል። ይህ ደግሞ ተጋላጨንታቸውን ይጨምራል። እንቅርት የሚያባብሱ/ የሚያመጡ ምግቦችን አዘውትረው የሚመገቡ ሰዎች፡ ለ ምሳሌ ጥቅል ጎመን፣ ማሽላ፣ ብሮክሊ፣ ስፒናች፣ ካሳቫ፣ ወ.ዘ.ተ አብዝተው የሚመገቡ ሰዎች ተጋላጭነታቸው የጨመረ ነው። ለምን? እነኝህ ምግቦች ውስጣቸው አዮዲንን የሚቃወም አልያም ታይሮይድ ሆርሞንን የሚጻረር ውህድ አላቸው። ለዚህም እጅጉን አብዝተው ከተመገቧቸው ለእንቅርት የማጋለጥ እድላቸው የሰፋ ነው። ለዚህም በህክምናው እንቅርት አምጪ (Goitrogenic) ምግቦች ይባላሉ። ይህንን ተጽእኖአቸውን ለመቀነስ ምግቦቹን በደንብ ማብሰል ይኖርብዎታል። የአዮዲን እጥረት ባይሆንም አንዳንድ የታይሮይድ ችግሮች በቤተሰብ ተወራራሽ ይሆናሉ ። ለዚህም ቤተሰባቸው የታይሮይድ ችግር ያለባቸው ሰዎች ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ነው። አንዳንድ ከባቢያዊ ለውጦች ለእንቅርት ሊያጋልጡ ይችላሉ። ለምሳሌ አንደ ፍሎራይድ ያሉ ኬሚካሎች የአዮዲንን ኡደትን አሰናክለው ለእንቅርት ሊያጋልጡ ይችላሉ። ለዚህም ይጠንቀቁ። የተመረተ አዮዲን ያለው ጨው አቀማመጥም ለዚህ አስተዋእጾ ያደርጋል። ይህም ሲቀመጥ ለእርጥበት እና ለጸሀይ ከተጋለጠ ውስጡ ያለውን የአዮዲን መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል። ለዚህም ቢመገቡትም ተጋላጭነት አለብዎ። 🤒 የተለመዱ ምልክቶች የአዮዲን እጥረትን ትከትሎ የሚመጣ እንቅርት ከአንገት ፊት ላይ ከሚታይ እብጠት ባሻገር ምልክት ላያሳይ ይችላል። ሆኖም ግን እንቅርቱ ከፍተኛ ከሆነ፡ በሚዋጥበት ጊዜ የአንገት መወጠር የመዋጥ ወይም የመተንፈስ ችግር የድምጽ መጎርነን ወይም የድምፅ ለውጦች ሊያሳይ ይችላል ከታይሮይድ ሆርሞን መብዛት ወይም ማነስ ጋር ግንኙነት ካለው ደግሞ አብዝቶ መድክመ የክብደት ለውጥቅ ቅዝቃዜ አለመቻል (ሆርሞኑ ካነሰ) መቀት አለመቻል (ሆርሞኑ ከበዛ) ማላብ እረፍት ማጣት ሊያሳይ ይችላል። በልጆች ላይ እድገት መዘግየት የትኩረት አለመኖር እንዲሁም የመማር ችግሮች ሊያሳይ ይችላል በነፍሰ ጡር ሴቶች ላይ ደግሞ የጽንስ እድገት መገታት፣ ማህጸን ውስጥ የጽንስ መሞት፣ እንዲሁም የጽንሱ የአንጎል እድገት መዘግየት ሊያመጣ ይችላል። 🧭 እንዴት ይመረመራል? ዶክተሩ በአካላዊ ምርመራ የእጢውን እድገት እና አካላዊ ለውጦችን ሊያስተውል ይችላል። የደም ምርመራዎች የታይሮይድ እጢ ስራን ሊፈትሹ ይችላሉ (TSH፣ T3 እና T4 የሆርሞን መጠንን መለካት)። የሽንት አዮዲን ምርመራ በቅርቡ ያለ የአዮዲን አወሳሰድን ያሳያል። አልትራሳውንድ የእጢውን አቀማመጥ እና አወቃቀር ያሳያል። ሌሎች የኢሜጂንግ ምርመራዎች የእጢውን ስራ እና አቀማመጥ በጥልቀት ያሳያሉ። ካጠራጠረ በናሙና የእጢውን ባህሪ መለየት ይቻላል። 💊 ህክምናውስ? የእንቅርት ሕክምና እንደ መንስኤው፣ እንደግዝፈቱ እና እንደ እጢው የአሰራር መጠን ይወሰናል። 1. በአዮዲን እጥረት ምክንያት ከሆነ አመጋገብን ማስተካከል ይኖርብዎታል። በጣም ርካሹ እና በጣም ውጤታማው ህክምና አዮዲን ያለው ጨው መመገብ ነው እጥረቱ ከፍ ካለ አዮዲን ያለባቸው እንክብሎች ወይም መድሀኒቶችን በተጨማሪነት በመውሰድ ማገዝ ይቻላል። 2. የታይሮይድ ሆርሞን ሕክምና ተያይዞ የሆርሞን መዛባት ችግር ካለ ፤ የሆርሞን መጠኑን ለማስተካከል መድሀኒቶች ሊታዘዙ ይችላሉ። 3. ቀዶ ጥገና የመተንፈስ/የመዋጥ ችግር ካለ ፣ በጣም ትልቅ ከሆነ ፣ ካንሰር ከተጠረጠረ በቀዶ ህክምና ሊታከም ይችላል። ውበትም ባለው ተጸእኖ ቀዶ ህክምና ሊመረጥ ይችላል። 5. ክትትል ህክምናው ከተደረገ በኋላም ክትትል እጅጉን አስፈላጊ ነው። በተለይም ለሴቶች እና ለህጻናት። 🛡️ መፍትሔው በእጅዎ ነው። መከላከል ታላቁ የህክምና አማራጭ ነው ። አሁኑኑ አመጋገብዎን ያስተካክሉ። አዮዲን ያለበት ጨው ብቻ ይመገቡ። እንቅርት የማምጣት ባህሪ ያላቸውን ምግቦች አያዘውትሩ። አብስለው ይመገቡ። ከተጠራጠሩ / ማንኛውም እብጠት ካለ ዛሬውን በፍጥነት ሀኪምዎን ያማክሩ። ተግባራዊ ለውጥ ዛሬውኑ ያምጡ፣
- ሰሞነኛው ጉንፋን ለምን መጣ?
አንድ ቀን ምሽት ላይ የሁለት አመቱ ህጻኑን እጅጉን አመመው። ሰሞኑን እንደሳል እያደረገው የቆየ ቢሆንም ፤ አብዝቶ ያተኩስ ጀመር። አተነፋፈሱ ፈጥኗል። ድክምክም ብሎታል። ትኩሳት አይሎበታል። ካመመው የተወሰኑ ቀናት ቢቆጠሩም ፤ ቤተሰብ ይሻለዋል ብሎ አስቦ ነበር። ሲያይልበት ቤተሰብ ጨነቃቸው። ከቀናት በፊት ፋርማሲ አማክረው የወሰዱት የህመም ማስታገሻ ፤ ትኩሳቱንም ህመሙንም አልተቆጣጠረም። ምን ያድርጉ? ጨነቃቸው! ሆስፒታል ይዘው ለመሄድ አሰቡ.. ይህ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ባሉት ከተሞች የሚስተዋል ታሪክ መሆን ከጀመረ ሳምንታት ተቆጥረዋል። ህመሙ ሲጀምር የወሰዱት መድሀኒት አልሰራ ብሎአቸው ክሊኒክ እየጎበኙ ያሉ ጥቂቶች አይደሉም። እንደ ተራ ጉንፋን አስበውት የሳንባ ምች የሆነባቸውም አሉ። ታድያ ግን ለምን? ለምንስ ጨመረ? ለምንስ መድሀኒቶቹ እንደሚፈለገው እየሰሩ አይደለም? መረጃዎች ምን ይላሉ? ' በጉንፋን ዙሪያ ያለ መረጃ የተሟላም ባይሆን ፤ሀገራችን ኢትዮጵያ ጉንፋንን ከሚያመጡ ቫይረሶች መሀል ሀይለኛው ኢንፍሉዌንዛን መከታተያ ስርአት ካበጀች አስርት አመታት ተቆጥረዋል። እነኝህም መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ፡ በፈረንጆች ከ 2009-2015 ባለው ጊዜ ወደ 4,800 የሚጠጉ ሰዎች ጠንከር ያለ የትንፋሽ ኢንፌክሽን የታመሙ ሲሆን። ከእነኝህም መሀል አንድ አምስተኛ የሚጠጉት (988 ሰዎች) የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል። ከኢንፍሉዌንዛ ቫይረሶችም መሀል በተለይ ኢንፍሉዌንዛ ኤ( A(H3N2)፣ A(H1N1) ፣ pdm2009) እና ኢንፍሉዌንዛ ቢ (influenza B) በብዛት ታይተዋል። በፈረንጆች ከጃንዋሪ 2021 እስከ ታህሳስ 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ 18,724 ጠንከር ያለ የትንፋሽ ቧንቧ ኢንፌክሽን ያለባቸው ሰዎች ሲገኙ ከእነኝህም ውስጥ በ1,648 ውስጥ ኢንፍሉዌንዛ ተገኝቷል። እዚህ ላይ ደግሞ የኮቪድን እና የሌሎችን ቁጥር ብንጨምር ፤ መጠኑ እጅጉን ያድጋል። ስለኮቪድ መጠን እና ባህሪው በብዛት ስለሚታወቅ መዘርዘሩ አስፈላጊ አይደለም። ሁሉም ጉንፋን መሰል በሽታ ኢንፍሉዌንዛ አለመሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል። ጉንፋንን የሚያመጡ ብዙ አይነት ቫይረሶች ሲኖሩ ከእነኝህ ውስጥ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ፣ የ ሪስፓይራቶሪ ሲንሲታል ቫይረስ ፣ አዴኖ ቫይረስ እና ኮሮና ቫይረስ በዋነኝነት በኢትዮጵያ ይጠቀሳሉ። ሆኖም ግን አሁን የምናየው የጉንፋን ስርጭት መጨመር በየትኛው ቫይረስ የመጣ መሆኑን አልያስ በባክቴሪያ መምጣቱን ለማረጋገጥ የላብራቶሪ ምርመራ ያስፈልጋል። ታድያ ይህ ለምን በ2018 ጸደይ ወቅት ላይ አጋጠመ? ይህ አጭር ምላሽ የለውም። አሁን የምናስተውለውን የጉንፋን መጠን መጨመር በሚከተሉት ምክንያት ሊሆን ይችላል። ወቅታዊነት፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ወቅትን ጠብቀው የሚመጡ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽኖች / ጉንፋን ህመሞች የተለመዱ ናቸው። ለምሳሌ ክረምት ወቅትን ተከትሎ በሚኖረው የአየር ሁኔታ ለውጥ ተከትሎ ጉንፋን መስፋፋት እንደተለመደው ፤ ጸደይ ወቅት ላይም በተለይ ወደ ህዳር አቅራቢያ የጉንፋን አይነት በሽታዎች ስርጭት ይጨምራል። ይህም ከወቅቱ ጋር በተያያዙ የከባቢ አየር ለውጦች ጋር ግንኙነት አለው። የትምህርት ቤቶች መከፈት ፡ ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ ፤ በትንፋሽ የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች በተማሪዎች መሀል በብዛት ይስፋፋሉ። ይህም አንድ ተማሪ መያዙን ተከትሎ ሙሉ ክፍል አስተማሪን ጨምሮ ስለሚያዝ ነው። እነኝህ የታመሙትም ህጻናት በሽታውን ወደቤት ይዘው ይመጣሉ። ቤተሰብም ይታመማል። የህዝብ ማመላለሻዎች እና የ ህዝብ ስፍራዎች መጨናነቅ። የተማሪን እንቅስቃሴን ተከትሎ የትምህርትቤት በተከፈተባቸው የመጀመሪያ ወራት የህዝብ ማመላለሻዎች ከወትሮ በበለጠ መጠን ይጨናነቃሉ። እዚህ ላይ ደግሞ አሁን ሀገራችን በምትከተለው ፖሊሲ የተነሳ አውቶብሶች እና ሌሎች በብዛት ህዝብን የሚይዙ ማመላለሻዎች ዋነኛ የትራንስፖርት አማራጮች እየሆኑ ይገኛሉ። ይህምም ለቫይረሱ ስርጭት ተጨማሪ በሮችን ይከፍታል። አንድ የታመመ ሰው ከገባ ሙሉ አውቶብስ ሰው በሙሉ ለጉንፋን ቫይረስ/ባክቴሪያ ይጋለጣል። ከኮቪድ በኋላ ለውጦችን መጥተዋል። ተዘናግተናል። ማስኮች/ጭምብሎች ወልቀዋል። እጆቹን በሳኒታይዘር የሚያጸዳ ሰው ዝቅተኛ ነው። ይህም ተጋላጭነትን ይጨምራል። ለዚህም የዚህ ጉንፋን መስፋፋት የአንድ ነገር ውጤት ብቻ አይደለም። ስርጭቱን የሚያስፋፉ ፣ አቅሙን የሚያደረጉ ብዙ አጋላጭ ምክንያቶች አሉ። ይህም የበለጠ ተጋላጭነት ይፈጥራል። ጉንፋኑስ ለምን ትንሽ ጠንከር አለ? ጉንፋን በሽታ የላይኛውን የትንፋሽ ቧንቧ በሚያጠቁ በሽታ አምጪ ተህዋሳት የሚከሰት ኢንፌክሽን ነው። የኢንፌክሽን በሽታ መጠንከር ደግሞ በ ሁለት ነገር ላይ ይመደባል። የበሽታ መከላከያ አቅም መዳከም። የአንድ ሰው የበሽታ መከላከል አቅም በአኗኗሩ ፣ በአበላሉ እና ባለበት ጤና ደረጃ ይመደባል። ከዚህም ባሻገር የምናደርጋቸው ባህሪያት ያለንን የበሽታ መከላከል አቅም ይወስናሉ። እንደማህበረሰብ ስናስብ በኮቪድ ሰሞን አድርገነው የነበረው ፍጹም ጥንቃቄ ፤ የበሽታ መከላከያ ስርአታችንን አግዞታል። ማገዙ መልካም ሆኖ ሳለ ይህ ጥንቃቄ የበሽታ መከላከያ ህዋሳቶቻችን እንዲዘናጉ አድርጓቸዋል። በህክምናው ይህ ኢሚዩኒቲ ጋፕ(Immunity Gap) ይባላል። ታድያ ይህን ጊዜ ለጉንፋን መሰል በሽታ ስንጋለጥ ፤ በሽታው ይደረጃል። ይህ ደግሞ ህዝቡን በይበልጥ ተጋላጭ ያደርገዋል። ሁለተኛ ደግሞ የቫይረሶቹ አቅም መደርጀት ነው። ጠንከር ያለ አቅም ያላቸው ቫይረሶች ስንታመመ ፤ በሽታውም ከበድ ያለ ይሆናል። ከዚህም ባሻገር በአንዴ ከአንድ በላይ በሆኑ ቫይረሶች ልንታመም እንችላለን። በፈረንጆቹ 2021 (ከ አራት አመት በፊት) የተደረገ ጥናት እንደሚያመላክተው ከሆነ ፤ በወቅቱ በኢትዮጵያ ከተገኙ 4989 ጉንፋን መሰል ታማሚዎች ውስጥ 9.2 በመቶ የሚሆኑት ከአንድ በላይ ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል። በሌላ በኩል ከቫይረስ ኢንፌክሽኑ ባሻገር ተደራቢ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ሊኖር ይችላል። ይህም ደግሞ ሰውነታችን በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ በሽታን እየተዋጋ ስለሆነ ፤ በሽታው ሊጠነክር ይችላል። የባክቴሪያ ኢንፌክሽን መኖሩን በባለሙያ በቀላሉ መለየት የሚቻል ሲሆን ፤ ከአመላካች ምልክቶቹ መሀል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው። ከባድ ትኩሳት (ተመላልሶ የሚመጣ አልያም የማይሄድ ሊሆን ይችላል) ከአፍንጫ የሚወጣው ፈሳሽ ቢጫ መሆን (ቢጫ ንፍጥ) የአተነፋፈስ ለውጥ/ትንፋሽ ከባድ ሳል እየባሰ የሚመጣ እንዲሁም ከባድ ድካም ይሆናሉ። በሁለቱ መሀል በደንብ ለመለየት ባለሙያ ያማክሩ። እዚህ ጋር አንድ መጨመር እና ማስተዋል ያለብን ጉንፋኑን ጠንካራ ያደረገው ነገር ቢኖር፡ አለአግባብ ያለ ዶክተር ምክር የባክቴሪያ መቃወሚያ መድሀኒቶች ከፋርማሲ እየተወሰዱ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ በሽታውን የተላመዱ ፤ አቅማቸው የደረጁ የኢንፌክሽን አምጪ ተህዋሳት እንዲስፋፉ እድል ፈጥሯል። ለዚህም መድሀኒት ወስደው እንኳን ላይሻልዎት ይችላል። ለምን? መድሀኒቱን ለምዶታል። ባክቴሪያው አሁን ጠንካራ ነው። ይህ ለእርስዎ እና ለሚወዷቸው ሰዎች ምን ማለት ነው? ይህ ማለት እቤትዎ ቁጭ ብለው ጉንፋን ሊይዝዎ ይችላል። የቤተሰብ አባልዎ ወደ ቤት ሲመጣ ከገባበት የህዝብ ማመላለሻ ፣ አልያም ከትምህርትቤት ይዞ ሊመጣ ይችላል። የመያዝ እድልዎ ባሉበት የጤና ሁኔታ ላይ ይመሰረታል። የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ የሆነ እና በሽታው የሚጠነክርባቸው የሚከተሉት ናቸው፡ ሰውነታቸው የተዳከመ ሰዎች ተደራቢ ስር የሰደደ ህመም ካላባቸው የበሽታ መከላከያ አቅም የሚያዳክም ህመም ያለባቸው። ለምሳሌ ፡ ኤችአይቪ ያለባቸው ፣ ካንሰር ያለባቸው፣ ወ.ዘ.ተ... እርጉዝ ሴቶች እድሜያቸው የገፋ አዛውንቶች ህጻናቶች ፣ ወ.ዘ.ተ... ናቸው። ለዚህም እነኝህ የማህበረሰብ ክፍሎች ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ጥንቃቄው ለእነኝህ የማህበረሰብ ክፍሎች ይብለጥ እንጂ ፤ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ለጤናው ቦታ መስጠት ይኖርበታል። ምልክቶቹን ለይተው ማወቅ ይኖርብዎታል። በተለይ በተለይ.... የሚከተሉትን ምልክቶች ካዩ በአፋጣኝ የህክምና እርዳታ ይፈልጉ። የበሽታው መጠንከርን ያመላክታሉና ያስተውሏቸው! የመተንፈስ ችግር ካለ/ ትንፋሽ ማጠር ካለ የደረት ሕመም ካለ ከፍተኛ ትኩሳት ካለ (ከ 3 ቀን በላይ ከቆየ ፣ ከ 38 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ከሆነ፣ ተመላልሶ የሚመጣ ከሆነ) ግራ መጋባት ወይም ባህሪ ለውጥ ካለ የማዞር ስሜት ካለ ከባድ ድካም ካመጣ ፣ እንቅልፍ እንቅልፍ አብዝቶ ካለ ምልክቶቹ እጅጉን እየባሱ ከመጡ የምግብ ፍላጎት ፈጽሞ ከጠፋ እጅጉን ያስተውሉ! የሕክምና እርዳታ ይፈልጉ። ሀኪም ያማክሩ። ማድረግ ያለብዎት ነገሮች የሚከተሉትን ቀላል እና ተጨባጭ እርምጃዎችን ያድርጉ። በጉንፋን ወቅት እንደ የሚከተሉትን መመሪያ ህግ አድርገው ይውሰዱ። ለመከላከል በአከባቢዎ የኢንፍሉዌንዛ ክትባት እየተሰጠ ከሆነ ፣ እድሜዎት ከፈቀደ ይውሰዱ። ክትባቱ በሽታው እንዳይከብድ፣ የሳንባ ምች አልያም የደም ኢንፌክሽን እንዳያመጣ ይከላከላል። ሥር የሰደደ የጤና ችግር ካለብዎ በህክምና ይቆጣጠሩ። አስም፣ የስኳር በሽታ፣ የልብ ሕመም ካለብዎ ወይም እርጉዝ ከሆኑ ቶሎ የጤና ባለሙያ ያማክሩ። በህኪምዎ ትእዛዝ መድሃኒቶችን ይውሰዱ። በሽታዎን ይቆጣጠሩ። እግዝናዎ ጤናማ ይሁን። ምልክቶቹን ይወቁ። አሳሳቢ ምልክቶችን ያስተውሉ። ከታመሙ በሚታመሙበት ጊዜ ከቤትዎ ይቆዩ። ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ሳል፣ የሰውነት ህመም ሲጀምርዎ እረፍት ያድርጉ። ፈሳሽ በደንብ ይጠጡ። ምግብ በስርአት ይብሉ። ቪታሚን ሲ ያለባቸው ፍራፍሬዎች ምግቦችዎ ውስጥ ይደባልቁ። የበሽታ መከላከያ ስርአትዎን ያጠናክራሉና። ትኩሳት ካለብዎ ፤ ልብስ አይደራርቡ። የረጠበ ፎጣ አልያም ውሀ ሰውነትዎ ላይ ያድርጉ። የትኩሳት ማስታገሻ መድሀኒቶችንም መውሰድ ይችላሉ። ጥሩ የአተነፋፈስ ምግባር ይኑርዎ ። ሲያስሉ አፍዎን በክርንዎ አልያም በእጅዎ ይከልሉ። በሶፍት አልያም በማህረብ ይናፈጡ። እጅዎን አዘውትረው ይታጠቡ። ሳኒታይዘር አልያም አልኮል ያለበት መታጠቢያ ቢጠቀሙ ይመረጣል። ቤተሰብዎን እና በዙሪያዎ ያሉ ሰዎችን ይጠብቁ። ላለማስተላለፍ ራስዎን ያግልሉ። በተዘጉ ክፍሎች ውስጥ ሲቆዩ /ከሰዎች ጋር ሲሆኑ ማስክ ወይም ጭምብል ያድርጉ። በተለይ ተጋላጭነታቸው ከፍ ላለ ሰዎች እጅጉን ይጠንቀቁ። በሽታው እስኪደረጅ አይጠብቁ። ቀደም ብለው የጤና ባለሙያ እንክብካቤን ይፈልጉ። ቀድመው እርምጃ ይውሰዱ። ምን ማድረግ የለብዎም? እነኝህን ባያደርጉ ይመከራል። "ጉንፋን ብቻ ነው" ብለው በማሰብ ምልክቶችን ችላ አይበሉ። በተለይ አሳሳቢ ምልክቶቹን። ከሚያስቡት በላይ ከባድ ሊሆን ይችላል። ብዙ ጊዜ በቫይረስ ስለሚመጣ የባክቴሪያ መቃወሚያ አይውሰዱ። ይህ በተላመደ ጠንካራ ባክቴሪያ እንዲታመሙ ያደርግዎታል። በሽታ ማስታገሻዎችን ብቻ ይጠቀሙ። ከፋርማሲም ቢሆን ፈጽሞ ያለ ሀኪም ትእዛዝ መድሀኒት አይውሰዱ። ብርድ ብርድ ሲለው እንዲሞቀው ልብስ አይደራርቡ። እንደውም ታማሚው ትኩሳት ሊኖርበት ይችላልና ፤ የልብስ መጠን ይቀንሱ። ተአምራዊ ፈውሶች ብለው ማንኛውንም ባህላዊ መድሀኒቶች አይውሰዱ። በጤናዎ ከመቆመር በህክምና የተረጋገጠ ጥቅም ያላቸውን እርምጃዎችን ብቻ ይውሰዱ። የመጨረሻ ቃል ጉንፋን በአሁኑ ወቅት በመዲናችን ተስፋፍቷል። ከህጻን እስከ አዋቂ እየታመመ ነው። ለዚህም ምልክቶቹን ያስተውሉ። ሀኪምዎን አማክረው ፤ መድሀኒቶችን ይውሰዱ። ላለማስተላለፍ ጥንቃቄ ያድርጉ። ለጤናዎ ቦታ ይስጡ። 2
- ካንሰር በኢትዮጵያ ፡ ለመሆኑ ዝግጁ ነን?
ድሮ... ድሮ ካንሰር የሀብታም አገሮች በሽታ ተደርጎ ይታሰብ ነበር። ለነገሩ እንዲያ ቢታሰብም አይደንቅም። ለምን ካሉ ጥሩ? በማህበረሰባችን ዘንድ የካንሰር አጋላጭ ተብሎ የሚታሰበው ፤ ከዘመናዊነት ጋር ተይያዥነት ያለው የአኗኗር ዘይቤ ነበር። ይህ አኗኗር ደግሞ ብዙውን ጊዜ ከሀብታም ሀገራት ጋር እና ከሀብታም ግለሰቦች ጋር ብቻ ይታሰብ ነበር። ለዚህም ካንሰር የእነሱ ህመም ተደርጎ ይወሰድ ነበር። ሆኖም ግን... ባለፉት አመታት ፤ በኢትዮጵያ ካንሰር ያለማቋረጥ እየጨመረ ይገኛል። ይህ ደግሞ አብዛኛው ማህበረሰቧ በዝቅተኛ ኑሮ ላይ ለሚገኝ ሀገራችን አሳሳቢ ጉዳይ ነው። እንዲሁ ጫና ለበዛበት የጤና ስርአት ላይ ትርፍ ሽክም ይሆናል። ይህንን በመረጃ እንደግፈው በኢትዮጵያ በየአመቱ ወደ 80,000 የሚጠጉ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በካንሰር ይታመማሉ። ከእነኝህ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር የሚወስዱት በሴቶች የማኅጸን ጫፍ ካንሰር እና የጡት ካንሰር ሲሆን በወንዶች ደግሞ የትልቁ አንጀት ካንሰር እና የፕሮስቴት ካንሰር ናቸው። ከዚህ ውስጥም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ካንሰሩ ከተሰራጨ ወይም ከደረጀ በኋላ ነው እንዳለባቸው የሚያውቁት። ይህም ደግሞ የካንሰርን ገዳይነት በኢትዮጵያ ከፍ እንዲል አድርጎታል። ለዚህም በየአመቱ ከ 50,000 የሚበልጡ ወገኖቻችን በካንሰር የተነሳ ህይወታቸውን እንደሚያጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህንን አሳሳቢ ወረርሽኝን ለመግታት በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር በኩል የካንሰር ክትትል እና መከላከል ላይ ስትራተጂክ ፕላን ተነድፎ መሰራት ከተጀመረ ሰንበትበት ብሏል። ይህንን ተከትሎ የካንሰር ምዝገባ እየተሻሻለ ቢሆንም ፤ የተሟላ አይደለም። ይህ ደግሞ ያለውን የካንሰር ታማሚ ዙሪያ የተሟላ መረጃ እንዳይኖር መሰናክል ሆኗል። 📊 ኢትዮጵያ ውስጥ ስለተለመዱት ካንሰሮች አንድ በአንድ እናውራ ። አሁን ያለው መረጃ እንደሚያሳየው የጡት ካንሰር - የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ እጅግ ከተለመዱ ካንሰሮች ውስጥ ይጠቀሳል። ከ10 የካንሰር ታማሚዎች ውስጥ በአማካይ ሶስቱ የጡት ካንሰር ታማሚ ናቸው። ይህ ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ነው። ከአፍሪካም አንጻር በፍጥነት እያደገ ነው። አሳሳቢው ደግሞ ከዚህ ታማሚዎች ውስጥ አብዛኞቹ በመጀመሪያ 5 አመት ውስጥ ይሞታሉ። ለዚህም ዘግይቶ በሽታቸውን ማወቃቸውን አስተዋእጾ አለው። የማኅጸን ጫፍ ካንሰር - ከጡት ካንሰር ቀጥሎ ሴቶችን በብዛት የሚያጠቃ ካንሰር ሲሆን ከአጠቃላይ ካንሰሮችም 13 በመቶ የሚጠጋውን ይወስዳል። ይህ ካንሰር በዋነንኝነት ኤችፒ ቪ በሚባል የቫይረስ አይነት የሚመጣ ነው። ለዚህም ይህንን ካንሰር በክትባት መከላከልም ፤ በቅድመ ካንሰር ምርመራም ቀድሞ መያዝ ይችላል። ሆኖም ግን ብዙዎችበመደበኛ ምርመራ ባለማድረጋቸው ፤ ክትባት መውሰድ በሚችሉበት እድሜ ባለመውሰዳቸው በሽታውን የሚያውቁት አርፍደው ነው። ለዚህም የኢትዮጵያ ሴቶች ላይ ህይወት በመቅጠፍ ዋና ተጠቃሽ ነው። የማህፀን ካንሰር - ይህ ደግሞ የማህጸን ዋና አካል ካንሰር ሲሆን ፤ ብዙ ጊዜ እድሜ መግፋትን ተከትሎ ፣ ከሆርሞን ስርአት እና ከውፍረት ጋር ተያይዞ ይከሰታል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህም አርፍዶ በመገኘቱ ብዙ ታማሚዎችን ለሞት እየዳረገ ይገኛል። የጉበት ካንሰር - በጣም ገዳይ ከሆኑ የካንሰር አይነቶች አንዱ ሲሆን ፤ በኢትዮጵያ በይበልጥ የሚታየው ከጉበት ቫይረሶች ኢንፌክሽን ጋር ተያያዥነት ያለው ነው። ቀድሞ ከታወቀ ቀዶ ጥገናን ጨምሮ የተለያዩ አማራጮች ቢኖሩም ፤ አብዛኛውን ጊዜ ዘግይቶ ስለሚታወቅ ፤ የሕክምና አማራጩ አነስተኛ ነው። የኮሎሬክታል ካንሰር - የትልቁ አንጀት የታችኛው ክፍል ካንሰር ሲሆን ፤ ከጌዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ ይገኛል። በወንዶችም ዘንድ ቀዳሚ የካንሰር አይነት ሲሆን ፤ ካንስሩ ከአመጋገብ ስርዐት ጋር ተያያዥነት አለው። በተለይም ዝቅተኛ አሰር ያላቸውንና ከፍተኛ ስብ ያላቸውን ምግቦች የሚመገቡ ሰዎች ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ነው። የጨጓራ ካንሰር - ቁጥሩ ከሌሎች አንጻር ያነሰ ቢመስልም ፤ ገዳይነቱ ከፍ ያለ ነው። ይህም ካንስር ደጋግሞ የጨጓራ ባክቴሪያ የሚያማቸውን ሰዎች፣ የሚያጨሱ ሰዎች እንዲሁም እድሜያቸው የገፉ ሰዎች ላይ በብዛት ይታያል። የጉሮሮ ካንሰር ፡ ይህ ካንሰር መጠኑ ከሌሎች ካንሰሮች ያነስ ቢመስልም ፤ ኢትዮጵያ ይህ ካንሰር በከፍተኛ ቁጥር ከሚገኝባቸው አገራት ተርታ ትገኛለች። ትኩስ ምግብ በሚመገቡ አከባቢዎች ላይ በብዛት የሚታይ በመሆኑ ፤ ስርጭቱ በሰሜን እና በምስራቅ ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ነው። የሳንባ ካንሰር - ሀገራችን ኢትዮጵያ ከአለም አንጻር አነስ ያለ የሳንባ ካንሰር ታማሚ ቁጥር ያላት ቢሆንም ፤ በኢትዮጵያ የዚህ ካንሰር ተጠቂዎች አጭሰው የማያውቁ እናቶች ናቸው። የአጫሽ ቁጥሯ ያነስ ቢሆንም ፤ እየተባባሰ ያለው የአየር ብክለት እና እየጨመረ ያለው የትምባሆ ተጠቃሚ ቁጥር የዚህን ካንሰር መጠን በቀጣይ አመታት ሊጨምር እንደሚችል ጠቋሚ ነው። የፕሮስቴት ካንሰር - ወንዶችን ከሚያጠቁ ግንባር ቀደም ካንሰር አይነቶች ውስጥ ተጠቃሽ ነው። እ.ኤ.አ. በ 2022 የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ከ አመስት አመት በፊት በኢትዮጵያ 2,720 የፕሮስቴት በሽተኞች ሲገኙ ፤ በዚሁ አመት ወደ 1,600 ሰዎች ከዚህ ካንሰር ጋር ተያያዥነት ባለው ምክንያት ሞተዋል። የተሟላ ግንዛቤ ኖሯቸው ፣ ምልክቶቹን ለይተው ፣ ቅድመ ምርመራ አድርገው ቢሆን ፣ ብዙዎቹን ማትረፍ ይቻል ነበር። በህጻንነት እድሜ የሚያጋጥም ካንሰሮች በአመት በግምት ከ 5,000-6,000 ልጆችን የሚታመሙ ሲሆን ፤ ከዚህ ውስጥ ባለን የህክምና አቅም ልናተርፍ የቻልነው አንዱን ብቻ ነው። ምን አዲስ ነገር ቢኖር ነው ካንሰር እንዲህ እየጨምረ የሚገኘው? ባለፉት ጥቂት አስርት አመታት ውስጥ ያመጣነው የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። ይህም የከተሞች መስፋፋትን ተከትሎ በመጣው ዘመናዊነት ፤ አመጋገባችን ተለውጧል። ባህሪያችን ተለውጧል። ተንቀሳቅሶ ስራ መስራት ፈንታ አብዛኛውን ቀናችንን የምናሳልፈው በቢሮ፣ በሱቅ፣ በቤት ውስጥ ተገድበን ነው። እንቅስቃሴያችንም በ መኪና ነው። አልኮል መጠጣት እና ትምባሆ ማጨስም እየተስፋፋ ይገኛል። ሲኖረን ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች አብዝተን እንመገባለን። የታሸጉ ምግቦችማ የቅንጦት ስለሆኑ ፤ ባገኘው እድል ይዘወተራሉ! ገበታ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችም በአንድ መንገድ ይሁን በሌላ ለኬሚካሎች ተጋላጭነት አላቸው። ገበሬዎች ብዙ ምርት ለማግኘት ማዳበሪያ ይጠቀማሉ፣ አረም ማጥፊያ ይረጫሉ። ከዚህ በተጨማሪም አከባቢያችን እጅጉን እየተለወጠ ይገኛል። የኦዞን መሳሳትን ተከትሎ የጸሀይ ብርሀን ጎጂነት አቅም ጨምሯል። በከተሞች ከፍተኛ የሆነ የአየር መበከል አለ። የህክምና ተደራሽነትም ውስን ነው። ማህበረሰቡ ባለበት የኑሮ ጫና መደበኛ የጤና ምርመራ ማድረግ ይቸገራል። ይህ ደግሞ ብዙው ካንሰር አርፍዶ እንዲገኝ ያደርገዋል። የህክምና ወጪን ችሎ ሙሉ ምርመራ እና ህክምና ማድረግ የሚሳነው የማህበረሰብ ክፍልም ጥቂት አይደለም። እነሱ ምልክቱን ቢያውቁም እንኳን ፤ አስፈላጊውን ህክምና እስኪያደርጉ እጅጉን ይዘገያሉ። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ ተላላፊ በሽታዎች ስላሉ ፤ በኢንፌክሽን የተነሳ የሚከሰቱ የካንሰር አይነቶችም እየጨመሩ ይገኛሉ። እላይ የተጠቀሱት የጨጓራ ካንሰር፣ የማህጸን ጫፍ ካንሰር፣ የጉበት ካንሰርን ለዚህ ዋቢ አድርጎ መጥቀስ ይቻላል። እነኝህን ኢንፌክሽኖችን መከላከልም እጅጉን ወሳኝ እርምጃ ቢሆንም ፤ይህን ለመከላከል የማህበረሰቡ ግንዛቤ ማደግ ይኖርበታል። በመልካም ጎኑ ደግሞ ከድሮው አንጻር የህክምና አቅማችን በማደጉ ፤ ድሮ መለየት የማንችላቸውን የበሽታ አይነቶች በቀላሉ መለየት ማወቅ እና ማከም ችለናል። ለዚህም ከድሮው አንጻር የካንሰር ቁጥሩ በመጠኑ ጨምሮ ሊታይ ይችላል። ይህንን የህክምና እመርታ ተከትሎ ፤ ብዙ ሰዎች ካንሰር የሚያጋጥምበት እድሜ ክልል ላይ ይደርሳሉ። ሆኖም ግን ይህ ያለውን የካንሰር ስርጭት የሚጨምርበት ፍጥነትን ብቻውን አይገልጽም። እርስዎ እንደግለሰብ ሊወስዷቸው የሚችሏቸው ተግባራዊ እርምጃዎች የዓለም ጤና ድርጅት እንደገለጸው በኢትዮጵያ ከሚገኙት ካንሰሮች ውስጥ እስከ 40 በመቶ የሚደርሱትን መከላከል ይቻላል። እንዴት እንደሆነ እነሆ ፡ ክትባት ይውሰዱ እርስዎ ወይም ልጆችዎ ለ ክትባቶች ብቁ ከሆኑ ዛሬውኑ ይውሰዱ። ክትባቶች ካንሰርን ይከላከላሉ። የ ማህጸን ጫፍ ካንሰር የሚያመጣው ቫይረስ (HPV) ክትባት በመውሰድ ይህንን ካንሰር መከላከል ይችላል። የጉበት ቫይረስ (ሄፐታይተስ ቢ) ክትባት እና ህክምና በማድረግ አብዛኛዎቹን የጉበት ካንሰሮችን መከላከል ይቻላል። አሳሳቢ የካንሰር ጠቋሚ ምልክቶችን ይወቁ። ያልታወቀ ክብደት መቀነስ፣ በጡት ውስጥ ያለ እብጠት፣ ያልተለመደ ከሴት ብልት የሚወጣ የደም መፍሰስ፣ የማያቋርጥ ሳል፣ ደም የቀላቀለ ሽንት ካዩ ቶሎ ምርመራ ያድርጉ። ቀደም ብሎ ከተያዘ ሕይወትዎን ማትረፍ ይቻላል። አኗኗር ዘይቤዎን ያስተካክሉ። የታሸጉ ምግቦችን ይቀንሱ። የተፈጥሮ ምርት ይመገቡ። ቅባት ይቀንሱ። ውፍረትዎን ይቆጣጠሩ። መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ። አትክልት እና ፍራፍሬ አዘውትረው ይመገቡ። ትኩስ ነገር አቀዝቅዞ በመመገብ የጉሮሮ ካንሰር ተጋላጭነትን መቀነስ ይቻላል። ትምባሆን ያስወግዱ እና አልኮልን ይገድቡ - እነዚህ ለብዙ ነቀርሳዎች ሊወገዱ የሚችሉ ዋነኛ መንስኤዎች ናቸው። ቀደም ብሎ ማወቅ እና መደበኛ ምርመራ ማድረግ ለብዙ ካንሰሮች መፍትሔ ነው። ከበሽታው የማገገሚያ ፍጥነትን በእጥፍ ሊጨምር ይችላል። ለዚህም የቅድመ ካንሰር ምርመራዎችን ያድርጉ። ጤናዎን በመደበኛ ምርመራ ይወቁ። የካንሰር ታካሚዎችን ይደግፉ። ያበርቷቸው! ስለበሽታው ግዝፈት ሳይሆን ስለእነርሱ ጥንካሬ በማንሳት አጠንክሯቸው። ያስተውሉ ተግባራዊ ድጋፍ ተገዢነትን እና ውጤቶችን ያሻሽላል። በመከላከል ብቻ በየአመቱ በ አስር ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወትን መታደግ ይችላል። ሆኖም ግን አሁንም ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ ነው። እንደ ሀገርስ ዝግጁ ነን? አጭር መልሱ ፡ ገና አይደለንም ! ግን መሆን እንችላለን። ኢትዮጵያ ካንሰርን ለመቆጣጠር ብዙ እርምጃዎችን ወስዳለች። ጤናጥበቃና ባለድርሻ አካላት በዚህ ላይ እየሰሩ ይገኛሉ። የኤች ፒቪ ክትባት ለሁሉተኛ ደረጃ ተማሪ ሴቶች እየቀረበ ይገኛል። የጉበት ቫይረስ ክትባት የህጻንት ክትባቶች ውስጥ ከተካተተ ቆይቷል። የተለያዩ የቅድመ ምርመራ እንቅስቃሴዎች በየአከባቢው ይታያሉ። የሰው ሀይል አቅምን ለማጎልበት የካንሰር ስፔሻሊስት ስልጠና በትላልቅ ሆስፒታሎች እየተካሄደ ይገኛል። የመመርመሪያ እና የህክምና አቅምን ለማጎልበት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርጸ እየተሰሩ ነው። ቢሆንም በቂ የካንሰር መድህኔቶች አሁንም የሉም። የጨረር ህክምና አቅም ያላቸው ተቋማት ጥቂት ናቸው። የካንሰር ምርመራ አቅም የተሟላ አይደለም። ብዙ መደረግ የሚችሉ የካንሰር ምርመራዎች አይካሄዱም። ለካንሰር ታማሚዎች የአቅም ድጋፍ ፕሮግራሞች እምብዛም ናቸው። ታማሚዎች በቂ ማህበራዊ ድጋፍ የላቸውም። ስለዚህ በዚህ ዙሪያ ስራዎች ይቀራሉ። አንኳር ሀሳቡ! ካንሰር እየጨመረ ቢሆንም ፤ ይህንን ለመቆጣጠር የተለያዩ ስራዎች በመንግስት እና ባለድርሻ አካላት በኩል እየተሰሩ ቢሆንም ፤ መቆጣጠር እስክንችል ብዙዎች ህይወታቸውን ያጣሉ። ብዙ የካንሰር ዓይነቶችን መከላከል የሚቻል ሲሆን ፤ የተቀሩትን ቀድሞ በማወቅ በውጤታማነት ሊታከሙ ይችላሉ። ለዚህም ደግሞ እርስዎ የበኩልዎን ድርሻ ይወጡ። እርምጃ ከወሰድን። መንግስት እና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እያደረጉ ነው። እርስዎስ!? በዚህ ወር እነኝህን ያድርጉ - እላይ የተጠቀሱት የካንሰር መከላከያ ክትባቶች መገኘት በአከባቢዎ ያለ የጤና ተቋም ይጠይቁ። ካለና ከተመለከትዎ ክትባቱን ይውሰዱ፤ የቤተሰብ አባልዎንም ያስወስዱ። የማኅጸን ጫፍ ምርመራ ምርመራ ያለበትን ተቋም አጣርተው ፤ ከተመለከትዎ ይመርመሩ። ቤተሰብ አባልዎንም ያስመርምሩ። የካንሰር ጠቋሚ ምልክቶችን ለይተው ይወቁ ። ቢያንስ ሶስት ሰዎች ያካፍሉ። ይህንን ትምህርታዊ ጽሁፍም ለሌሎች ያጋሩ። በአካባቢዎ ያሉ የካንስር ታማሚዎች ፤የአቅም ችግር ካለባቸው ይደግፏቸው። በዚህ ላይ የሚሰሩ የምግባረ ሰናይ ድርጅትን ይርዱ። ያስተውሉ! የሚያደርጓቸው ትናንሽ እርምጃዎች ተደምረው ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ።
- የጨረር አይን ህክምና ፈዋሽነት ከምን እስከ ምን?
ከፊልም የወጡ የሚመስሉ የሚመስሉ ብዙ የህክምና ግኝቶችን በዘመናችን ለማየት ታድለናል። ሰንሰማቸው “እውነት ነውን?” ያስባሉ ግኝቶች ሰራ ላይ ከመዋላቸውም አልፎ ተርፎ እንደኛ ባሉት ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ሃገራቶች ተስፋፍተው ማየታችን ይበል የሚያስብል ነው። ሆኖም ግን አንዳንዶቹ ከእውነታ በራቀ መልኩ ተጋነው ሲቀርቡ ማየትም የተለመደ ነው። ይህ ታድያ የህክምና ግኝቶች ላይ ሲሆን ጉዳት ሊኖረው ይችላል። በዚህ መልኩ ከሚቀርቡ ግኝቶች ውስጥ አንዱ ጨረርን በመጠቀም የሚደረግ የአይን ህክምና ነው። ብዙዎችም ይህንን ህክምና እንደ ተአምር አድርገው ይወስዱታል። እርግጥም ብርሀንን ተጠቅሞ የአይንን ጤና በመመለሱ አስደማሚ ግኝት ቢያደርገውም ፤ በአንዳንዶች ሁሉን የአይን ህመም እንደሚፈውስ ምትሀታዊ ህክምና ተደርጎ መወሰዱ ግን አሳሳች ነው። እርስዎም በበኩልዎ ምናልባት አይተው ወይም ሰምተው ይሆናል። ይህ ህክምና የሚሰጡ ተቋማትም ምናልባት አግነው አቅርበውት ፤ ተመልካቾችም እንደ ተአምር ወስደውት ይሆናል። ይህ ደግሞ ማስታወቂያ ነው። የህክምና እውነታ ግን አይደለም። ይህ የኢትዮጵያ እውነታ ብቻ አይደለም። በአለም ዙሪያ ራሱ ባለፉት አመታት የሚደረጉ ማስተዋወቂያዎች በማህበረሰቡ ዘንድ ከእውነታ የራቀ ግምት እንዲኖረው አድርገዋል። አንዳንድ ክሊኒኮች በፍጥነት የእይታ መመለስን ቃል ሲገቡ ፤ ሊሎች በዘላቂነት ከመነጽር ነጻ መሆንን በተስፋ ይሰጣሉ። ይህ የሚያድናቸው ታካሚዎች ቢኖሩም ፤ ለብዙዎች ግን ቀቢጸ ተስፋ ሊሆን ይችላል። በዚህ ሁሉ ግርግር መሀል ፤ አንድ የምይካድ እውነታ አለ። የአይን የጨረር ህክምና የሚደነቅ ፤ አመርቂ ውጤት ያሳየ ምርጥ የዘመናችን ህክምና ነው። ሆኖም ግን እንደማንኛውም ህክምና አቅሙ የተገደበ እንጂ ፤ ፈጽሞ ተአምራዊ አይደለም። ስለ ሌዘር ህክምና በጥልቅ እናንሳ የሌዘር ህክምና ምንድነው? የሌዘር ህክምና የብርሀን ጨረርን የሚጠቀም የህክምና አማራጭ ነው። የእንግሊዘኛ ስሙም ምህጻረ ቃል ሲሆን ፤ በግርድፉ ሲተነተን አቅሙ የጎለበተ የብርሀን ጨረር (LASER ፡ Light Amplification by Stimulated Emission of Radiation ) ህክምና ነው። ይህንን ስያሜ ያገኘው በአስራሩ ላይ ተመስርቶ ነው። የሚሰራውም የብርሀንን ሞገድ አቀናጅቶ ፣ መጥኖና አጠናክሮ በአንድ አቅጣጫ መትሮ በመልቀቅ ነው። ብርሀኑም በተመራው መሰረት ረድፉን ጠብቆ ከታለመበት ስፍራ ያርፋል። የብርሀን ሞገዱ ያረፈበት አከባቢም ፤ እንደጨረሩ አይነት የሚጠበቀውን ለውጥ ያመጣል። በህጻንነት ምብራቅ/ሌንስ ይዞ ወረቀት እያቃጠለ ላደገ የዚህ ጨረር አሰራር መረዳት ላይክብድ ይችላል። ይህ ተሰብስቦ ተመጥኖ የሚለቀቅ ጨረር ከህክምና ባሻገር ዳይመንድን ለመቁረጥና መንኮራኩሮችን ለመጠንገም ይውላል። በህክምናም ተመሳሳይ አቅም ያለው ጨረር ባይሆንም ፤ ይህ የሌዘር ህክምና ብዙ ጠቀሜታ አለው። በህክምና ዘርፍም ለተለያዩ ችግሮችን ለማከም ጥቅም ላይ ይውላል። በአይንም ዘንድ እይታን የማስተካከል እንዲሁም እይታን የማጥራት አቅም አሳይቷል። ታድያ ግን ለሁሉም የእይታ ችግሮች መፍትሔ አይደለም። ለአይን ህክምና የሚውሉ የሌዘር ህክምና አይነቶች ለአይን ህክምና የሚውሉ የሌዘር ህክምና አይነቶች ውስጥ አራቱን እንይ። እነኝህም የአይን የፊት መስታወት የሆነ ውን ኮርኒያን (cornea) ለማስተካከል ጥቅም ላይ የሚውለው ኤክሳይመር (Excimer) የ ሌዘር ህክምና ፤ የአይን ግርዶሽ/ሞራ ቀዶ ጥገና ከተካሄደ በኋላ የሚደረገው የ ዋያኤጂ (YAG laser) የጨረር ህክምና ፤ የስኳር ህመምን ተከትሎ የሚመጣው የአይን ጥቃቅን ደምስሮች መድማት እና መጎዳትን የሚያክመው አርጎን ሊዜር (Argon Laser) ህክምና እንዲሁም በአይን ውስጥ ያለ ግፊትን ለመቀነስ (ግላኮማን ለማከም) የምንጠቀመው ዳዮድ ሌዘር (diode laser) ህክምና ናቸው። ታድያ እነኝህን የጨረር ህክምና አማራጮች በመጠቀም ፤ ለተለያዩ የአይን በሽታዎች መፍትሔ መስጠት ተችሏል። የአይን የጨረር ህክምና የሚሰጠው የህክምና ጥቅሞች ጥቂቶቹ ኮርንያ ጋር በተያያዘ የሚመጡ እይታ ችግሮችን ማስተካከል ይህ ህክምና የአይን ፊት መስታወት (ኮርንያን) ቅርጽ በማስተካከል ፤ ብርሃን ተመጥኖ ሬቲና ላይ እንዲያልፍ በማድረግ እይታን ያስተካክላል። ለዚህም የቅርብ ርቀት እና ሩቅ ርቀት እይታ ችግሮች ያለባቸውን ታካሚዎች የአንጸባራቂው ኮርኒያን ቅርጽ በማስተካከል ሊያክም ይችላል። lለዚህም ይህንን ጨረር መሰረት ያደረጉት እንደ ላሲክ (LASIK) እና ፒአርኬ (PRK) አይነት ህክምናዎች ተጠቅሽ ናቸው። ህክምናው ደቂቃዎች የሚፈጅ ፤ ህመም የሌለው ዘላቂ የህክምና አማራጭ ነው። ሆኖም ግን ይህ ህክምና በኮርንያ ቅርጽ እይታቸው ለተስተጓጎለ ታካሚዎች ብቻ የሚሆን ነው። የላሲክ ቀዶ ህክምና ያስተውሉ ! ኮርንያ በጣም ከሳሳ ፣ ተለዋዋጭ እይታ ካለ እንዲሁም የአይን ድርቀት ካለ፤ ይህ ህክምና ፈጽሞ አይመከርም። ህክምናው ከተደረገ ግን አይን ይብሱኑ ጉዳት ሊያጋጥመው ይችላል። ግላኮማ ለመቆጣጠር ይረዳል። የአይን ግላኮማ በሽታ የሚባለው ፤ የአይን ውስጥ ግፊት ሲጨምር ነው። የዚህም ግፊት መጨመር ፤ የእይታ ነርቭ የሆነውን የኦፕቲክ ነርቭ ይጫነዋል። ጫና ያደረበትም የኦፕቲክ ነርቭ ስራውን በስርአት መስራት ስለሚሳነው፤ እይታ ችግር ይፈጠራል። ግላኮማ በሽታ ካለብዎ ፤ የዐይን ግፊትዎ ከፍተኛ ነው። ይህም ግፊት መጨመር ደግሞ የእይታ ዋነኛ ነርቭ ኦፕቲክ ነርቭን ይጫነዋል። የሚመግቡትንም ጥቃቅን ደምስሮች ያፍናል። ያለ ህክምና እርዳታ ይህ ነርቭ ሊሞት እይታ ሊጠፋ ይችላል። ታድያ ይህንን ግፊት ለመቀነስ የሌዘር ህክምናን በመጠቀም ፤ የአይን ውስጥ ግፊትን ማስተንፈስ ይችላል። ጨረሩ የአይን ፈሳሽ መንሸራሸር እንዲችል ቱቦ ይከፍትለታል። ይህም ግፊቱን ለመቆጣጠር ያስችለዋል። እዚህ ጋር ያስተውሉ ፤ ግፊቱን መቆጣጠር እንጂ ግላኮማ ፈጽሞ መፈወስ አይደለም። ያለ ከበድ ያለ ቀዶ ጥገና ራሱ ይህንን ግፊት መቀንስ መቻሉ እጅጉን አስደሳች ዜና ነው። ከስኳር ጋር ተያይዞ ለሚመጣ የዕይታ ችግር አማራጭ መፍትሔ ነው። ስኳር ህመም ስር ሲሰድ ጥቃቅን ደም ስሮች ላይ ጉዳት ያደርሳል። ታድያ ከሚጎዱ ጥቃቅን ደም ስሮች ውስጥ አይን ጀርባ ሬቲና ጋር ያሉት ደምስሮች አንዶቹ ናቸው። እነኝህ ደምስሮች በሚደርስባቸው ጉዳት ይደማሉ ፣ ይቀደዳሉ /ይሰነጠቃሉ ። ይህም ታድያ እየጨመረ ሲመጣ እይታ ላይ ችግር ይፈጥራል። ደም ፍሰቱም ከፍ ያለ ከሆነ ሬቲናን ከስሩ ነጥሎ እይታን ሊያቋርጥ ይችላል። ታድይ ይህ የጨረር ህክምና የደምስሮቹን ግድግዳ በመጠገን ፤እንዳይደሙ ይከላከላል። ይህንን ለስኳር ታማሚዎች ዘላቂ ጉዳት ከማጋጠሙ በፊት ይከላከላል። እዚህም ጋር ያስተውሉ ፤ የተጎዱ /የተቀደዱ ደምስሮችን ጠገናቸው እንጂ ፤ ይህ የጨረር ህክምና ስኳር በሽታን ሆነ ከሱ ጋር ተያይዘው ያሉ ሌሎች ጉዳቶችን አይለውጥም። ሆኖም ግን ይህ የረቀቀ ህክምና በአለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከዐይነ ስውርነት ታድጓል። ከሞራ መግፈፍ(cataract Surgery) ቀዶ ጥገና በኋላ ሞራ አይናቸውን ለጋረዳቸው ታካሚዎች የሞራ መግፈፍ በቀዶ ጥገና ተድርጎም እንኳንድ ከሌንስ ጀርባ ጉም አይነት ምልክት ሊኖር ይችላል። ይህም እይታን እንደ ቆሸሸ መስታወት ሊያደበዝዝ ይችላል። ይህንንም ለማጥራት የጨረር ህክምና መጠቀም ይችላል። የጨረር ህክምናም በስከንዶች ውስጥ ፤ በቀላሉ ውጤት ያሳያል። የአይን ሞራ ታድያ እነኝህ በሽታ አይነቶች ውጭስ ? ጨረር ህክምና ያለው ውጤት እጅጉን የተገደበ ነው። በአይን ሌዘር ህክምና ዙሪያ መረዳት ያለብዎ ያለ ጠባሳ በደቂቃዎች ውስጥ የሚያክም ፤ በፍጥነት የሚያገግም ይህ የዘመናችን ሳይንስ ግኝት ህክምና ያለውን ገደብ መረዳት ይኖርብናል። ለምሳሌ፡ ሁሉንም የዕይታ ችግር ማከም አይችልም የሌዘር ህክምና ሁሉንም የእይታ ችግር ፈጽሞ አይፈታም። ሁሉም የአይን በሽታ አንድ አይደለም። ሁሉም ዐይን — ትንሽ ወይም ትልቅ፣ ቡኒ ወይም ጥቁር — ቅርጹ እና ቀለሙ ልዩ እንደሆነው ችግሩም እንዲሁ ለየቅሉ ነው ። የአይን በሽታም ደግሞ ብዙ አይነት ነው ያለው። የእይታ ችግር አለ ማለት በሽታው አንድ ነው ማለት አይደለም። ለዚህም፡ የኦፒቲክ ነርቭ ጉዳትን ፣ የሬቲና ጉዳትን ሊመልስ አይችልም። ከዚህ ጋር የሚመጣ የእይታ ችግር በሌዘር ህክምና አይታከመምም። እንዲሁም በጣም የተባባሰ ግላኮማን እንዲሁም ፣ ማኩላ (macula) የተሰኘው የአይን ክፍልን ጉዳትንም አይመልስም። የሞተ ነርቭን አያስነሳም። የደከመ አካልን አይቀስቀስም። ለዚህም ከእነኝህ ጋር የተያያዘ ችግር ላለባቸው ታካሚዎች ጠቀሜታ አይኖረውም። ለሁሉም ሰው ህክምናው አይሰጥም ህክምናውም ለሁሉም ሰው አይሰጥም። የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅሙ ለተዳከመ ሰው ፤ ኮርንያው ስስ ለሆነ ሰው፣ የሚዋዥቅ የእይታ መጠን ላለው ሰው ይህ ህክምና ውጤታማ አይሆንም። ከአደጋ ነጻ አይደለም ማንኛውም የህክምና አማራጭ እንዳለው አደጋ ፤ የሌዘር ህክምናም ተጓዳኝ ጉዳቶች ይኖሩታል። እይታን ብዥ ማድረግ ፤ የማታ እይታን ማጣት (ዳፍንት በሽታ) እንዲሁም የአይን ድርቀት ሊያመጣ ይችላል። አንዳንዴም የሚኖረው ጉዳት ዕይታን እስከመጨረሻው ሊያሳጣ ይችላል። ከዚህም ባሻገር መሳሪያው ምንም የረቀቀ ቢሆንም፣ ውጤታማነቱ እንደ ሃኪሙ ብቃት፣ ልምድ እና ጥንቃቄ ይወሰናል። የዶክተሩ ክህሎት ደረጃም ግንዛቤ ውስጥም መግባት አለበት። ትክክለኛው ተአምር በእውቀት እና በስነምግባር ላይ ይመሰረታል። የሌዘር ህክምና እውነተኛው ምትሃታዊ ተግባር እና ውጤት ያለው መሳርያው ላይ ሳይሆን፤ መቼ፣ለምን እና ለማን መጠቀም እንዳለብን ማወቅ ላይ ነው። በትከክለኛው ምርመራ፣ሙያዊ ስነምግባር እና ክህሎት ሲመራ እና ሲታጀብ መሳርያው አስደናቂ ስኬትን ያመጣል። የገንዘብ ትርፍ ላይ ብቻ ያተኮረ እና ከመጠን ባለፈ የራስ መተማመን የሚድረግ ህክምና መቼም ቢሆን ጉዳት እንጂ ጠቀሜታ አይኖረውም። ያስተውሉ። ውሳኔዎ በጥንቃቄ የተሞላ መሆን ይኖርበታል። ግንዛቤዎን ያሻሽሉ። የጨረር ህክምና ተአምራዊ ሳይሆን ፤ አቅሙ የተገደበ አምርቂ ውጤት ያሳየ የህክምና አማራጭ መሆኑን ያስተውሉ። የሚፈውስዎት ብርሀን ሊያሳውር ስለሚችል ፤ ያስተውሉ።
- እንጥል መቆረጥ ወይስ?
አብዛኞቻችን በህጻንነታችን ቶንሲል ታመን እናውቃለን! ታሞ መርፌውን የተወጋማ ፤ የማይረሳ ትውስታ አለው። የቶንሲል መቆጣት በተለይ በህጻንነት አብዝቶ የሚያጋጥም በሽታ ነው። አንዳንዱ ደጋግሞ ይታመማል። አንዳንድ እናቶች በጨው፣ ሎሚ ፣ እና እንደ ቁንደበርበሬ ያሉ ግብእቶችን አፍልተው እንዲግሞጠሞጡ በማረግ ወይ በማስዋጥ ለማከም ይሞክራሉ። ከዚ ባስ ሲል ደግሞ በባህላዊ እንጥልን ማስወገድ እንደ ዋነኛ እና ብቸኛ መፍትሔ አድርገው ፤ በመውሰድ እንጥል ወደ ማስቆረጥ ያመራሉ የጨነቀ እለት....አይደል የሚባለው! በሌላ በኩል የሰለጠኑትማ ... ብልሀታቸው ከዚህም የረቀቀ ነው። በዘመናዊት ኢትዮጵያ በመሀል ከተማ አዲስ አበባ እንኳን እንጥል ለማስቆረጥ ያስባሉ። ከሀኪም ቤት ሄዶ ለማስቆረጥ ያቅዳሉ። በዘመናዊ ህክምና ባህላዊ መፍትሔ እንዲህ ነው! ልምድ የቀሰሙ ብልህ እናቶች በበኩላቸው፤ ጉሮሮ ህመም ሲጀምር በጨው ውሀ አድርገው ያጉመጠምጣሉ። ለምን ብለን ብንጠይቅ ሁሉም ማስረጃ አላቸው። ከልምዳቸውን ይጀምራሉ። " ደግሞም የእከሌ ልጅ እኮ ቶንሲል ስትታመም እንጥሏን ከተቆረጠች በኋላ ተሽሏታል " ብለው ያስረግጣሉ። የእነኝህ ወላጆች መፍትሔያቸው ለየቅሉ ቢሆንም ፤ ህመሙ እና ጭንቃቸው ግን አንድ ነው። ምርጫቸው ታድያ ብዙ ጓዝ ይዞ ይመጣል። የጨነቃት አንድ ምስኪን እናት ፤ በግንዛቤዋ ልክ ዘላቂ መፍትሔ ብትፈልግ እንዴት ይፈረድባታል። እነኝህን የመፍትሔ አማራጮች እና የተሻለውን መንገድ ለመረዳት ፤ ስለ ቶንሲል በሽታ እና ህክምናው በጥልቀት እንወያይ። የመጀመሪያ ግንዛቤ ከምላስ ጀርባ በግራና ቀኝ ያለው ነው ቶንሲል። እንጥል ከላንቃ ግርጌ መህል ላይ ያለው ነው። ቶንሲል እና እንጥል አንድ አይደሉም። እንጥል ላንቃችን ጀርባ መሀል ላይ ተንጠልጥሎ ያለ ስጋ/አካል ነው። ስራው ምግብ ወደ አፍንጫች እንዳይገባ መከላከል እና አፍን ለማረስረስ የሚጠቅም ፈሳሽ (ምራቅ) ማምረት ነው። በህክምና ስሙ ኡቩላ (uvula) ይባላል። ቶንሲልስ? ቶንሲል ደግሞ የሚባለው ከ እንጥል ጀርባ በጉሮሮ መግቢያ ጋር በግራ እና በቀኝ ዘብ የቆመ አካል/ስጋ ነው። በቀላሉ ጉሮሮአችን ጋር ያለ ንፍፊት ነው። ይህም አካል/ንፍፊት እውነትም ዘብ ነው! አፋችንና ጉሮሮአችን አከባቢ ያሉ ህዋሳት በበሽታ አምጪ ተህዋስ እንዳይጠቁ የሚጠብቁ ነጭ የደም ሴል ህዋሳት መከማቻ ካምፕ ነው። ወራሪ ሀይልን መከላከያ የወታደር ካምፕ! ለዚህም የቶንሲል መቆጣት እና የ እንጥል መቆጣት አንድ ላይ ሊያጋጥሙ ቢችሉም እንኳን ፈጽሞ ይለያያሉ። በግልጽ ቋንቋ የቶንሲል በሽታ ምንድን ነው - በግልጽ ቋንቋ? የቶንሲል በሽታ ቀለል ባሉ ቃላት ስንገልጸው የቶንሲል መቆጣት ነው ። የሚቆጣውም በበሽታ አምጪ ህዋሳት በመጠቃቱ ነው። ለእይታም ፍም ይመስላል (ይቀላል)። ያብጣል። ታድያ እነኝህ አጥቂ ህዋሳት እነማን ናቸው? አንደኛ እና ዋነኛዎቹ ቫይረሶች ናቸው። ቫይረሶች በብዛት ቶንሲልን የሚወሩ ጠላት ናቸው። ከእነኝህም መካከል ኮሮና ቫይረስ፣ አዴኖ ቫይረስ ፣ ራይኖ ቫይረስ እና ኢፒስተን ባር ቫይረስ የሚባሉት ይጠቀሱበታል። ባክቴሪያዎችስ? እነርሱም እንደ ቫይረሶች አብዝተው ባይለመዱም ፤ ቶንሲልን ይወራሉ። ከእነኝህም መሀክል በተለይ ስትሬፕቶኮከስ ፓዮጅነስ የሚባለው ( Streptococcus pyogenes /Group A strep) ዋነኛ ተጠቃሽ ነው። ከባይረሶች አንጻር የባክቴሪያ መጠኑ ቢቀንስም ፤ በመድሃኒት ህክምና ያስፈልገዋል። ምልክቶቹ ታድያ ይህ ቶንሲል በተወረረ ጊዜ የሚመለከቱን ምልክቶች ያሳያል። በግራና በቀኝ ያበጡና የቀሉ ቶንሲሎች ይታያሉ። መህል ላይ እንጥል አለ። የጉሮሮ መቁሰል - ለዚህም ሲውጡ ማመም/መሰቃየት ትኩሳት መጥፎ የአፍ ጠረን ድምጽ መታፈን ጉሮሮ አከባቢ መቅላት፣ መቆጣት፣ ማበጥ አንዳንዴ መግል ያዘሉ ነጭ ነጠብጣቦች ሊታዩ ይችላሉ። አንገት አከባቢ ያሉ ንፍፊቶች ይህን ተከትለው ሊያብጡ ይችላሉ። ህጻናት ላይ የሆድ ህመም እና ማስታወክ ሊያሳይ ይችላል። አይንም እንባ ሊይዝ/ሊሞጨሙጭ ይችላል። ከዚህ ባሻገር የመተንፈስ ችግር፣ ከባድ የመዋጥ ችግር፣ እንዲሁም ራስ ስቶ መውደቅ ካለ ፈጽሞ አይዘግዩ። አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ያስፈልጋል። ምናልባት ! ምናልባት! ኢንፌክሽኑ ደርጅቶ አጠገብ አከባቢ ያሉ አካላትን አስቆጥቶ ሊሆን ይችላል። ሕክምናውም ቀላል እና ውጤታማ ነው! በአብዛኛውን ጊዜ በመደገፍ ህክምና ብቻ ሊሻሻል ይችላል። ቫይረስ ከሆነ ይህ ብቻ ሊበቃ ይችላል። ለዚህም እረፈት በማድረግ፣ ፈሳሽ አብዝቶ በመውሰድ፣ ለጉሮሮ ህመም የሚዋጡ እንክብሎች (ሎዜኝስ) በመውሰድ ፤ እንዲሁም ትኩሳት እና ህመምን የሚያስታግሱ መድሀኒቶችን በመውሰድ ሊስተካከል ይችላል። ከዚህም ባሻገር ጉሮሮ ህመም ባለ ጊዜ ፤ ፈልቶ በቀዘቀዘ የጨው ውሀ መጉመጥመጥ ይመከራል። ባክቴሪያ መሆኑ ከተረጋገጠ ወይም ከተጠረጠረ ደግሞ ፤ የባክቴሪያ መቃወሚያ መድሀኒቶችን መውሰድ ያስፈልጋል። ታድያ ግን ዶክተርን ሳያማክሩ አይውሰዱ። መድሀኒቶቹ ተጓዳኝ የአለርጂ/የአለመስማማት ምልክቶችን ሊያመጡ ይችላሉ። በሽታው በስርአት መታከም እንዳለበት ማወቅ ይኖርብዎታል። ይህ ካልሆነ ኢንፌክሽኑ ሊስፋፋ አልያም ሊደረጅ ይችላል። ይህን ጊዜ ከአጠገብ ያሉ አካላት ሊቆጡ ይችላሉ። ቶንሲሉ አጠገብም ባለ ስፍራ መግል ክምችት ሊፈጠር ሁሉ ይችላል። በስርአት ካልታከመ ለልብ ህመም ሊዳርግ ስለሚችል እዚህ ጋር ፈጽሞ መዘናጋት የለብዎትም። ቀዶ ጥገናስ ? የቶንሲል ቀዶ ሕክምና ለዚህ የቶንሲል በሽታ ግድ ካላለ በስተቀር የቀዶ ጥገና አይደረግም። ታድያ እነኝህ አስገዳጅ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? አንደኛ ቶንሲሉ በሽታው ተደጋጋሚ መሆን አለበት። ይህ ተደጋጋሚ የሚለው በቁጥር እና በጊዜ የተገደበ ነው። ሁለተኛው በሽታው ጠንካራ መሆን አለበት። አጠገብ ያሉ አካላት ሲጠቁ ፤ አንገት አከባቢ ተጨማሪ ኢንፌክሽን ሲፈጠር ቀዶ ጥገና ያስፈልጋል። እንዲሁም በቶንሲል የተነሳ የአየር መወረጃ እየታፈነ በእንቅልፍ መታፈን ሲፈጠር ቀዶ ጥገና ይመረጣል። ከዚህም ባሻገር የቶንሲል አከባቢ እጢ/ካንሰር ከተጠረጠረ ቶንሲልን መቆረጥ ይመከራል። ሆኖም እነኝህ አስገዳጅ ሁኔታዎች እስካልተፈጠሩ ቀዶ ጥገና አይመከርም። ለምን? በቀዶ ጥገና ቶንሲሎቹ መውጣታቸው ታካሚን ለዛ አከባቢ ኢንፌክሽን ተጋላጭ ያደርገዋል። ቀዶ ጥገናው ጋር ተያይዘው የሚኖሩ ተጓዳኝ ጉዳቶችም ሊኖሩ ይችላሉ። ዘመናዊ የቶንሲል ቀዶ ጥገና እና ባህላዊ እንጥል መቁረጥ? አብዛኛው ሰው እንደሚያስበው ፤ ዘመናዊ የቶንሲል ቀዶ ጥገና እንጥል መቁረጥ አይደለም። እላይ እንደገለጽነው አካላቶቹ ስለሚለያዩ ፤ በዘመናዊ ቀዶ ጥገና የሚወጣው እንጥል ሳይሆን ቶንሲል ነው። እንጥል እራሱን የቻለ አካል ስለሆነ በዘመናዊ ቀዶ ጥገና እንጥል የሚቆረጥበት የራሱ ምክንያቶች አሉት። ዘመናዊ ቀዶ ጥገና የሚደረገውም በ ሰመመን መድሀኒት ተደርጎ ፤ ንጽህናው በተጠበቀ ስፍራ በሰለጠኑ ባለሙያዎች ስለሆነ ተጓዳኝ ጉዳቱ እጅጉን መጠነኛ ነው። ተቆርጦ የወጣ ቶንሲል ባህላዊስ? ባህላዊው ደግሞ ብዙ ጊዜ ደህንነቱ ባልተጠበቀ ቦታ በልምዱ ላይ በተመረኮዘ ልዩ ስልጠና በሌለው ግለሰብ የሚሰራ ነው። በባህላዊ የሚደረገውም ቶንሲል መቁረጥ ሳይሆን እንጥል መቁረጥ ነው። አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ ማለት ይህ ነው። የታመመው ቶንሲል ፤ የሚቆረጠው እንጥል። ይህ ደግሞ በህክምናው ወይም በዘመናዊ ሳይንስ በተደረጉ ጥናቶች፤ ጥቅሙ ፈጽሞ ያልተረጋገጠ ነው። እውነትም እንጥል ሲቆረጥ እንጥል ላይወርድ ይችላል። ሆኖም ግን የቶንሲል በሽታ ከመኖር ምንም አይገድበውም። ለዚህም ባህላዊው ፈጽሞ አይመከርም! ከዚህም በላይ ባህላዊውን አሳሳቢ የሚያደርገው ነገር ቢኖር የሚካሄድበት ስፍራ እና መሳርያ ነው። የሚካሄደበት ስፍራ ከባክቴሪያ ያልጸዳ ሲሆን ፤ መሳሪያውም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ተደርጎ የማይዘጋጅ ፤ በቅርብ የሚገኝ የስለት መሳርያ ነው። ይህ ደግሞ ለዛ አከባቢ ኢንፌክሽን ፣ ለደም ውስጥ ኢንፌክሽን እንዲሁም ለከባድ ደም መፍሰስ ሊያጋልጥ ይችላል። አከባቢ ያሉ አካላት ላይ ጉዳት ሊይደርስም ይችላል። ለዚህም አይመከርም። እጅጉን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ቀዶ ህክምናው መደረግ ያለበት ፤ ከባክቴሪያ በጸዳ አከባቢ በዘመናዊ ህክምና በሰለጠነ ባለሙያ ብቻ ነው። አንዳንድ ወላጆች ህመሙ ባስጨነቃቸው ጊዜ ወደ ባህላዊ እንጥል ማስቆረጥ መሄዳቸው የተለመደ እውነታ ቢሆንም ፤ ከዚህ በኋላ መቆም አለበት። ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ጎጂ ባህላዊ ልማዶች ውስጥ በመካተቱም ባለፉት አመታት ውስጥ በመንግስት እና ባለድርሻ አካላት ትብብር እንዲቀንስ ማድረግ ተችሏል። ሆኖም ግን አሁንም ይህንን አማራጭ የሚወስዱ ወላጆች አይጠፉም። በተለይም በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ይህ ይታያል። ለዚህም እያንዳንዱ ወላጅ ፈጽሞ ችላ ማለት የለበትም። በግንዛቤ ጉድለት ልናድናቸው ያሰብናቸውን ልጆቻችንን መጉዳት የለብንም። ባህላዊ ማስታገሻዎችስ? አንዳንድ ከእጽዋት የሚቀመሙ መድኃኒቶች አንዳንድ ምልክቶቹን ሊያስታግስየሚችል አቅም ቢኖራቸውም እንኳን ፤ አስፈላጊውን ህክምና ከማድረግ ሊያዘገዩ ይችላሉ። ተጓዳኝ ጉዳታቸው ሆነ የህክምና መጠናቸው ስለማይታወቅ ጉዳት ሊያመጡ ይችላሉ። በዘመናዊ ህክምናም ፈጽሞ አይመከሩም። ለዚህም ፈጽሞ ችላ አይበሉ። ልጅዎን ቶንሲል ካመመው እቤትዎ ከማቆየት የዘመናዊ ህክምና እርዳታ ይፈልጉ። እርስዎ እንደወላጅ ምን ያድርጉ ? ግንዛቤዎን ያሻሻሉ። ስለ ቶንሲል ምልክቶች ህክምናዎች እና አላስፈላጊ ባህላዊ ስርአቶች ለይተው ይወቁ። የተሻለውን ይምረጡ ። በሀኪምዎ ትእዛዝ ብቻ ህክምና ይውሰዱ ። በተለምዶ መድሀኒት መውሰድ ጠንከር ላለ ለተላመደ ባክቴሪያ ያጋልጣል። ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ለውጥ ያምጡ !
- የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ፡ማድረግ ያለብዎ እና የሌለብዎ
የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ የሚፈልግ ሰው በየመንገዱ ማየት የተለመደ ነው። ምናልባት ዛሬ ራሱ በመንገድ ላይ አንድ ሰው ወድቆ በሰዎች ተከቦ አይተው ይሆናል። ሰው እንደመሆናችን ባልታሰበ ቦታ እና ጊዜ ላይ አደጋ ማጋጠሙ አይቀርም። ምናልባት በስራ ቦታ ፣ በትምህርት ቤት ፣ በትራስፖርት፣ እንዲሁም በቤትዎ ድንገተኛ አደጋ ሊያጋጥ ይችላል። አንድ ግለሰብ ራሱን ስቶ ሊወድቅ ፣ ግራ ሊጋባ ፣ ደም ሊፈስ ይችል ይሆናል። ታድያ ይህን ጊዜ ምን ያደርጋሉ? አንዳንዶች ከበው መታዘብ ሲመርጡ ፤ ሌሎች የታመመውን ሰው ከጭንቅ ለማውጣት ሲተራመሱ ይስተዋላል። ለዚህም አፍንጫ ስር ክርቢት መለኮስ ፣ ውሀ/ለስላሳ መስጠት የሚሯሯጥ ሰው ማየት የተለመደ ነው። የተጎዳውን ሰውንም እፍስፍስ አድርገው አንስተው ከሆስፒታል ይዘው የሚሄዱ ደግ ሳምራዊያንም አይጠፉም። ታድይ ይህ ምን ጥፋት አለው ይሉ ይሆን? ልቦናቸው በመልካም የተነሳሳ ቢሆንም ፤ ብዙዎች ግን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ፈጽሞ አያውቁም። በተለምዶ ሌላ ሲያደርግ ያዩትን ነው የሚያደርጉት። ተስፋቸው መልካም ውጤት ማየት ነው። ታድያ እዚህ ላይ ትክክለኛ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ክህሎት ቢኖርበት ምን ነበረበት። በትንሹ አንድ ህይወት ይድናል። አንድ ታሪክ እናውጋ እስቲ ... በአዲስ አበባ ከተማ ነው። አንድ ጠይም ዘለግ ያለ በ20ዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ ያለ ወጣት በድንገት እንደ ዛፍ ተገንድሶ ይወድቃል። ወድቆም አላበቃ መንቀጥቀጥ ይጀምራል። ታድያ ድንገት ይጓዝ የነበረ ወጣት እንዲህ መሆን ያስደነገጣቸው ይከቡታል። አንዱ ከእግሩ ሊያስጠጋው ሲሞክር ፤ ሌላኛው ጭንቅላቱን ይደግፋል። አንዲት ተመሳሳይ እድሜ ያለች ሴት በሀዘን እያማተረች የተሰበሰበው ሰው እንዲያስረዳት ትጠይቃለች። በዚህ ሁሉ ትርምስ መህል ወጣቱ ሰውነቱ ግትር ብሎ ይርዳል። ጥርሱን ነክሶ ቢያወሩት አይመልስም። አንዱ 'ክብሪት ክብሪት...' እያለ ሮጠ። ሌላ መልካም ሴት ሚሪንዳ ልትገዛ ሱቅ ፍለጋ ላይ ናት ። "ስኳር ይሆናል" የሚልም አለ ታድያ የዚህን ጊዜ ነው አንድ የጤና ባለሙያ ስታልፍ ፤ ሚሪንዳ ሊያጠጡት የሚታገሉ ሰዎችን "በጎኑ አድርጉት" አለቻቸው። ቀርባም ያለውን ስታስተውል ፤ ቀኝ እጁ ኪሱን እየጠቆመ እንዳለ ተመለከተች። የሚያመላክተው ኪሱ ስትገባ ፤ ኪሱ ውስጥ የማንቀጥቀጥ መድሀኒት አገኘች። በጎን ባለበት ፤ በጥርሶቹ መሀል መድሀኒቱን ሰጥታ አዋጥቸው። በዋጠም በደቂቃዎች ውስጥ መንቅጥቀጡ ቀንሶ አቆመ። ልጁ የማንቀጥቀጥ ህመም ያለበት ታካሚ ሆኖ ሳለ ፤ የጠዋት መድሀኒቱን ቁርስ ስላልበላ ሳይውጥ ወጥቶ ነው እንዲህ የሆነው ። አንዳንዴ የሚያስፈልገው የመጀመሪያ እርዳታ አብሮ ማስተዋል ሊሆን ይችላል። እንዲህ አይነት ታማሚዎች ፤ ለድንገተኛ እንዲሆን የሚይዙት መረጃ/መድሀኒት ኪሳቸው ውስጥ ይኖራል። የመጀመሪያ እርዳታ ለምን አስፈላጊ ነው ድንገተኛ አደጋ ብዙ ጊዜ አፍታ አይሰጥም ። አምቡላንስ በቅጽበት አይደርስም። ደቂቃዎች አልያም ሰዓታት ሊወስድ ይችላል። መንገዶች ሊዚጋጉ ይችላሉ። ጤና ተቋማት በ ታካሚዎች ተጣበው ሊሆኑ ይችላሉ። የዚህን ጊዜ የ መጀመሪያ እርዳታ የአንድን ግለሰብ መኖር የሚወስን ብቸኛው የህይወት መስመር ነው። ይህም ደግሞ በመረጃ የተደገፈ ነው። በገጠራማ ባንግላዲሽ ካሉ 1.2 ሚሊዮን ሰዎች መሀል 9 በመቶ የሚሆንት በስድስት ወር ውስጥ አንድም ይሁን ሌላ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ታድያ ከእነኝህም መሀከል ከ 80% በላይ የሚሆኑት የመጀመሪያ እርዳታ አግኝተዋል። የመጀመሪያ እርዳታ ስልጠና ባላቸው ሰዎች እርዳታ ያገኙት ታድያ በንጽጽር በተሻለ ደረጃ አገግመዋል። በታንዛኒያ ደግሞ ለትራፊክ ፖሊስ መኮንኖች በተሰጠ የ16 ሰአታት የመጀመሪያ እርዳታ ስልጠና የብዙዎችን ህይወት ሊያተርፍ ችሏል። ይህ ረቂቅ ምርምር አይደለም። ትምህርት ነው! ማንኛውም ሰው የመጀመሪያ እርዳታን መማር ይችላል። ትምህርቱም ውጤታማ ነው። በብዛት የሚደረጉ የተሳሳቱ ነገሮች በመልካም ልቦና ተነሳስተን ቢሆንም በዘልማድ የምናደርጋቸው ድርጊቶች ብዙውን ጊዜ ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዝናል። ለምሳሌ፡ ንቃተ ህሊና ለሌለው ሰው በተንጋለለበት ፤ በአፍ ውሀ ወይም መጠጥ መስጠት ፤ ፈሳሽ ወደ ሳንባ እንዲገባ ያደጋል። ይህ ደግሞ ህይወትን አደጋ ላይ ይጥላል። በእሳት/በጋለ/ በፈላ ነገር የተቃጠለ ቆዳን ቅቤ/ዘይት/ የጥርስ ሳሙና መቀባት ፤ ጉዳቱ እንዲቀጥል ያደርጋል። አካል ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ያብሳል። አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ከወደቁበት ቦታ ማንቀሳቀስ ፤ ስብራትን ሊያብስ፤ የአከርካሪ አጥንት ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ይህ ደግሞ ባይገል አካል ጉዳተኛ ያደርጋል። እነዚህ ልምምዶች ከመልካም ዓላማ የመጡ ቢሆንም ሊገድሉ እንደሚችሉ መረዳት ያስፈልጋል። መፍትሄው። ከዘልማድ ይልቅ በመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ በኩል እውቀት ይኑርዎ ። ትምህርት ይውሰዱ። ክህሎት ያዳብሩ። ሳይንስ ምን ይላል? የተወሰኑ የሳይንስ ምሳሌዎች ማንም ሰው ሊማራቸው የሚችላቸው አምስት ቀላል፣ በማስረጃ የተደገፉ የመጀመሪያ እርዳታ እርምጃዎች እነሆ፡ አደጋ ምን ይደረግ ለምን አስፈላጊ ነው ደም መፍሰስ የሚደማው ቦታ ላይ በንጹህ ጨርቅ ግፊት ያድርጉ። የቆሰለውን ስፍራ ከተቻለ ከፍ ያድርጉት። ይህ የደም መፍሰስን ያቆማል። ደም መፍሰስ ደግሞ ብዙዎችን የሚቀጥፍ ነውና፤ ፈጽሞ ችላ አይበሉ። እሳት አደጋ/ የፈላ/የጋለ አካል አደጋ የተጎዳውን ስፍራ ላይ ቢያንስ ለ 20 ደቂቃዎች ንጹህ ውሃ ያፍሱበት። ይህ ወዲያውኑ ያቀዘቅዘዋል። በስሱ ይሸፍኑ። ይህ ቆዳን ስለሚያቀዘቅዝ ፤ የጉዳቱን መጠን ይገድባል። ጥልቅ ጉዳትን ይከላከላል። ለዚህም ቶሎ ያገግማሉ። በምግብ መታነቅ/ ትንታ የታነቀው ስው እንዲያስል አበረታቱ። ከታነቀው ሰው ጀርባ በመሆን እጅን ሆድ ላይ በማድረግ፤ ሆድን በመግፋት ገፍትሮ እንዲወጣ ማገዝ ይኖርብዎታል (ከሰለጠኑ)። አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ፤ የአየር ቱቦ በቶሎ እንዲጸዳ ያደርጋል። ይህ ህይወትን ያተርፋል። . ስብራት / የተጠረጠረ የአከርካሪ ጉዳት ዝም ብለው ይቆዩ። ታካሚውን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ቀጣይነት ያለው ጉዳት ከሌለ (ለምሳሌ፡ የሚቆርጥ ነገር፤ የሚናድ ድንጋይ፣ አስፋልት ላይ ከወደቀ በመኪና እንዳይመታ፣ ወ.ዘ.ተ ካልሆነ) አያንቀሳቅሱ። ፈጽሞ አያንቀሳቅሱ። ይህ ስብራቱ እንዳይባባስ ያደርጋል። የአንገት አከርካሪ አጥንት ጋር ጉዳት ካለ ስናንቀሳቅሳቸው ሊሞቱ ይችላሉ። የጀርባ አከርካሪ አጥንት ከሆነ ደግሞ ሽባ ሊሆን ይችላል። የደም ግፊት መቀነስ / ድንጋጤ ግለሰቡን ቀጥ ያለ ቦታ ላይ እንዲተኛ ያድርጉ። እግሮችን ከፍ ያድርጉ። እንዳይበርድ ወፍራም ልብስ ያድርጉ። ይህ የደም ፍሰትን ያሻሽላል። ወደ ከፋ ሁኔታ ከመውደቅ ይከላከላል።። ሁሉም ላይ አምቡላንስ መጥራት ፈጽሞ አይረሳ። እነዚህ ውስብስብ አይደሉም። ውድ መሣሪያ አያስፈልጋቸውም ። ግንዛቤ እና ልምምድ ብቻ! ታድያ ሰዎች ለምን አስፈላጊውን የመጀመሪያ እርዳታ አይማሩም? ለዚህ አንደኛ የሚጠቀስ የሚሆነው የትምህርቱ ተደራሽነት ችግር ነው። በተለይም በገጠር አካባቢዎች ስልጠናዎች እምብዛም የሉም። ይህ ደግሞ በማህበረሰብ ደረጃ የመጀመሪያ እርዳት እውቀት ያላቸው ሰዎች መጠን ዝቅተኛ እንዲሆን ያደርጋል። ከዚህ ባሻገር ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ፍርሀት አለባቸው። እንደዚህ አይነት ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎችን በሚረዱበት ጊዜ የሚያጋጥም ህጋዊ ተጠያቂነት ይፈራሉ። ይህም ትምህርቱንም እንዳይወስዱ ፤ ሰው መርዳት እንዳይፈልጉ ሲያደርጋቸው ይታያል። ሌሎች ከሳይንስ ይልቅ በልምድ /በዘልማድ ድርጊቶች ይተማመናሉ። ለዚህም ትምህርቱን ለመማር ተነሳሽነት የላቸውም። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ መሰናክሎች በቀላሉ መፈታት ይችላሉ። የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት መፍትታት ይቻላል። እዳው ገብስ ነው! በሀገር ደረጃ ምን መደረግ አለበት? የመጀመሪያ እርዳታ ህይወትን የሚያድን እስከከሆነ ድረስ፤ በአጋጣሚ መተው የለበትም። ሁላችንም የመፍትሔው አካል መሆን አለብን። ሹፌሮች፣ አስተማሪዎች፣ ባለሱቆች፣ ተማሪዎች፣ ወ.ዘ.ተ በመንግስትና ባለድርሻ አካላት የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ መሰልጠን አለባቸው። ቀጣዩ ትውልድ እያወቀ እንዲያድግ የመጀመሪያ እርዳታ በትምህርትቤቶች ካሬኩለም መዋሀዱ መልካም ነው። የመጀመሪያ እርዳታ ክህሎቶችዎን በመደበኛነት ያድሱ ። አጫጭር ስልጠናዎችን ይውሰዱ። ሊረዱ ያሰቡ በጎ ሰዎች ህጋዊ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል። ህግን እያስከበሩ መልካምነትእንዳይጠፋ ፤ እዚህ ጋር የህግ አካላት ቅንጅት ያስፈልጋል። በሚዲያ አካላት፣ በማህበራዊ ድህረ ገጽ እንዲሁም በበራሪ ወረቀቶች ትምህርት ሰጪ የመጀመሪያ እርዳታ እውቀቶች መሰራጨት እውቀት/ክህሎቱን ያስፋፋሉ። ያስተውሉ የመጀመሪያ እርዳታ ለዶክተሮች ብቻ አይደለም። ለሁላችንም ነው። በሚቀጥለው ጊዜ አንድ ሰው በመንገድ ላይ ሲወድቅ ምን ያደርጋሉ? ልማድ ወይስ ሳይንስ? ምክንያቱም በእነዚያ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ውስጥ እርስዎ አምቡላንስ ነዎት። ሆስፒታሉ ነዎት። በሕይወትና በሞት መካከል ያለው ልዩነት አንተ/አንቺ ነህ/ሽ።
- 🦴 ስብራት ወይስ ውልቃት?
ድንገት በመውደቅ / በምጋጨት ይጀምራል....። ምክንያቱ አዳልጦን አልያም አደናቅፎ ሊሆን ይችላል። አንዳንዱ ደረጃ ሲወጣ ተንሸራቶ ሲወድቅ ፤ ሌላው በሚመራው ከብት ይመታል። ገጠር ያለው ከፈረስ ወድቆ ሲጎዳ ፤ የከተማው በመኪና ግጭት አጥንታቸው ይጎዳል። ታድያ ይህ የችግሩ መጀመሪያ እንጂ ማብቂያ አይደለም። ጥቂቶች ወደ ሐኪም ቤት ሲሄዱ ፤ የተቀሩት ወጌሻ ይመርጣሉ። አይን ያወጣ ጉዳት አልያም ቆዳን ቀዶ የሚወጣ ስብራት እስከሌለ ድረስ የሚያሳስብ የማይመስላቸውም አይጠፉም። እርስዎስ የቱን ይመርጣሉ? ምርመራ ከሚያበዛው/ ኪስ ከሚያከሳው ከሃኪም ቤት ወይስ ዳሶ ፈውሱን ከሚያውቀው ወጌሻ(እንደ አንዳንዶች አስተሳሰብ)? ...የቱን ይመርጣሉ? ወጌሻው የተጎዳውን አካል አሽቶ ፤ በጨርቅ አጅሎ ፤ በእንጨት ወጥሮ ፤ ሙያዊ ምክር ሰጥቶ ይልካል። ለሳምንት አልያም ከዛ በላይ ክትትል ያዛል? ሀኪሙም ኤክስ ሬይ አይቶ ፤ እንደአስፈላጊነቱ ሲቲ ስካን አዞ ፤ ስብራት ይሁን ውልቃት ለይቶ ፤ ወደ ቀዶ ጥገና አልያም እዛው ወደ ማስተካከል ይገባል። እሱም በበኩሉ በየሳምንት/ በየ2 ሳምንት ይቀጥራል። ታድያ ሁልጊዜ ብዙ ኢትዮጵያውያን በሁለቱ መሀከል ለምርጫ ሲቸገሩ / ሲመላለሱ ማየት የተለመደ ነው። በይበልጥ ግራ የሚያጋባው አንዱ ወጌሻ ስብራት ሲል ፤ ሌላኛው' ቀላል ነው ውልቃት ነው' ሲል ይገኛል። ለዚህም ታካሚ ዛሬ ቅጥቅጥ ነው ሲል የነበረ ፤ ሳይሻለው ቀርቶ ሌላ ወጌሻ ጋር አይ ውልቃት ነው ተስተካክሏል ይባላል። ታድያ ይህው ታካሚ ሌላ ወጌሻ ጋር ስብራት ነው ሊባል ይችላል። ይህ ያልተለመደ ታሪክ አይደለም። የኢትዮጵያ ዝምተኛ ወረርሽኝ ነው። ብዙዎች በጊዜ ቢታከም ለሚድን ስብራት ፤ በዚህ ግራ መጋባት ውስጥ ታስረው ፤ ዘላቂ ጉዳት ያጋጥማቸዋል። አጥንት መሳሳት ህመም የሚለው ጽሁፍ ላይ የገለጽነውን እውነተኛ ታሪክ ለዚህ ዋቢ አድርጎ ማየት ይችላል። 📊 አሳሳቢው እውነታ በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚደርሱት የአካል ጉዳቶች ውስጥ ስብራት ከ10-15% የሚያህለውን እንደሚይዝ የአለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ 2022 ባወጣው ሪፖርት ገልጿል። ታድያ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ፤ የህክምና አቅማቸው ባልጠነከረ አገራት ይህ ቁጥር ሊጭመር ይችላል። አንድም ለጉዳቱ የሚያስፈልገውን ህክምና በጊዜ ባለማግኘት ሌላም በባህላዊ ወጌሻዎች የደረሰባቸው ጉዳት ሊባባስ ይችላል። እ.ኤ.አ. በ 2021 በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ከ 50% በላይ የሚሆኑት የአጥንት ስብራት ያጋጠምቸው ታካሚዎች ህክምና ቦታ ከመምጣታቸው በፊት ወጌሻ ጋር ሄደው ነበር። ከነዚህም መካከል ከአስሩ ውስጥ ወደ ሶስት የሚጠጉት በኢንፌክሽን፣ የተወሳሰበ የአጥንት ጉዳት እና ቋሚ የአካል ጉዳት ያጋጥምቸዋል። ቀድመው ቢመጡ ምን ነበረበት? ወጌሻ ጋር ከመሄዳቸው በፊት ቢያንስ ኤክስሬይ ቢነሱስ? የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያደረገው ጥናት ደግሞ አብዛኞቹ በገጠራማ ኢትዮጵያ የሚያጋጥሙ ስብራቶች "ከህክምና" በፊት የኤክስሬይ ማረጋገጫ አያገኙም። ታድይ ይህ ችግሩ እንዲበራከት ያደርጋል። የዚህ መሰረታዊ ችግር ፤ ወጌሻና ዘመናዊ ህክምናን ቀንደኛ ጠላት አድርጎ ማሰብ ነው። ወጌሻ ጋር ከመሄድዎ በፊት በሰው አይን የማይታይ ከቆዳ ስር ያለ የአጥንት ጉዳትን ለመመልከት ኤክስሪይ ቢጠቀሙ ፤ ብዙዎች አካል ጉዳት ባላጋጠማቸው ነበር። ሆኖም ግን እውነታው ከዚህ የራቀ ነው! ይህ ከግንዛቤ ጉድለት የመጣ ነው። የተሻለ ግንዛቤ ቢኖር ስንት ኢትዮጵያውያን በድጋፍ ከመራመድ፣ ከከባድ ህመም ጋር ከመኖር አልያም መተዳደሪያቸውን ከማጣት ሊተርፉ ይችሉ ነበር። ለዚህም ለመለየት እንዲችሉ በስብራት እና በውልቃት መሀከል ያለውን ልዩነት እናንሳ። 🧬 ስብራት ወይስ ውልቃት ስብራት የሚባለው አጥንት ሲሰበር አልያም የውጭ ግድግዳው ሲሰነጠቅ ነው። ደረጃው ሊለያይ ይችላል። አንዳንዴ ተሰብሮ አጥንቶቹ ግን ተደጋግፈው ሊቆዩ ሲችሉ ፤ ሌላ ጊዜ ከተሰበረው ክፍል ውስጥ አንዱ ቆዳን ቀዶ አፈንግጦ ሊወጣ ይችላል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ደቃቅ ትናንሽ አጥንቶች ሊኖሩት ይችላሉ። ከዚህ ቀጣይ ውልቃት ሲሆን ፤ ውልቃት አጥንት ቦታውን ሲስት የሚፈጥረ ነው። ይህም አንድ አጥንት ከመደበኛ ቦታው ሲያፈነግጥ አልያም አቀማመጡ ሲለወጥ ነው። ይህም መለውጥ መጋጠሚያ ላይ ጫና ስለሚያሳድር ፤ እንቅስቃሴ ሊገደብ ይችላል። ያጋጠመ ጉዳትን በስርአት ሳይመረምሩ ከሁለቱ የትኛው እንደሆነ መገመት አደገኝነት አለው። ለምን? የሁለቱ ህክምና ፈጽሞ የተለያየ ነው። ስብራት በጀሶ አልያም በመደገፊያ አካል ማስተካከል አልያም በቀዶ ጥገና ማበጀት ሊፈልግ ይችላል። ውልቃት በበኩሉ ከስብራት ይልቅ ድንገተኛ ህክምና የሚያስፈልገው ነው። በአፋጣኝ የሳተው አጥንት ወደ ቦታው መመለስ ያስፈልገዋል። ውልቃትን ስብራት አድርጎ መውሰድ ውልቃቱ መስተካከያ ወርቃማ ጊዜ ያባክናል። ይህም መባከን አጥንት እንዲራብ እና ጉዳቱ እንዲያይል ያደርጋል። አንድ ውልቃት በ 6 ሰአት ውስጥ ካልታከመ ይህ ሊያጋጥም ይችላል። አሳዛኙ እውነታ... ብዙዎች ከ ቀናት/ከሳምንታት በኋላ ነው ወደ ህክምና ቦታ የሚሄዱት። ይህን ጊዜ አጥንት የደረሰበት ቀላል ጉዳት ደርጅቷል። ምልክቶቻቸው አንዳንዴ ፍጹም ተመሳሳይ ሊመስሉ ይችላሉ። ሁለቱም እብጠት፣ከባድ ህመም፣ የእንቅስቃሴ መገደብ ሊያሳዩ ይችላሉ። ሆኖም ግን አንድ አይደሉም። ታድያ በኤክስሬይ እንኳን ለመለየት የሚያስቸግርበት ሁኔታ ባለበት ላይ ፤ በወጌሻ ግምት ላይ መታመን በጤናዎ እንድመቆመር ነው! ⚠️ ችግሩ ምንድንነው ታድያ? በሰአቱ አግባብ ያለው ህክምና ካልተደረገ ፤ የተሰበረው የአጥንት ክፍል ባለበት የራሱን ጉዳት ለመፈወስ ይሞክራል። በትክክል ሳይሆን ፤ ተጣሞ ይገጥማል ። ይህ ደግሞ የራሱ ብዙ ችግር አለው። አጥንት ጥንካሬውን ያጣል። ደጋግሞ ለመሰበርም ቅርብ ይሆናል የወለቀው የአጥንት ክፍል የተጫነው የደምስር የሚመገበው የአጥንት ክፍል ይሞታል ። ይህም ብዙ ዳፋ ይዞ ይመጣል። በጊዜው ህክምና ባለማድረግ የሚመጣውን ዳፋ/እክል እንደሚከተለው መጠቅለል እንችላለን። የአጥንት ኢንፌክሽን (ኦስቲኦሜይላይትስ) → ጉዳት የደረሰበት አጥንት ንጽህናው ካልተጠበቀ ፤ የሚታሰርበት መሳሪያዎችም ንጽሁ ካልሆኑ ለበሽታ አምጪ ተህዋሳት ይጋለጣል። ይህም ጠንከር ያለ የአጥንት ኢንፌክሽን እንዲያጋጥም እድል ይከፍታል። ይህም ቁጥጥር ስር ካልዋለ አካል እስከመቆረጥ የሚደርስ ህክምና ሊያስፈልገው ይችላል። የነርቭ እና የደም ቧንቧ ጉዳት → አጥንት በሚደርስበት ጉዳት ጊዜ አጠገብ ያሉ ነርቮችን እና የደም ቧንቧዎችን ሊጫን እና ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። እንዲሁም የደምስር አቀማመጥ እውቀት የሌለው ባለሙያ አጥንቱን ሊያስተካክል በሚሞክርበት ጊዜ የደም ዝውውርን ሊያቋርጥ ይችላል። ይህ የደምስር መቋረጥ ደግሞ ጋንግሪን ያስከትላል። በልጆች ላይ የእድገት ችግሮች → አጥንት ሰውነታችን የሚያድግበት ፤ ቁመት የሚጨምርበት አካል ነው። እድገታቸውን ባልጨረሱ ልጆች ላይ የሚደርስ የአጥንት ጉዳት በጊዜ ካልታከመ ፤ እነኝህን ህጻናት እድገት በቋሚነት ሊያደናቅፍ ይችላል። 👉 ይህን ሲያስረግጥ ፤ እ.ኤ.አ በ 2019 በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የተደረገ አንድ ጥናት ፤ በባህላዊ ፈዋሾች ከሚታከሙ ህጻናት መሀከል ከ25% በላይ የሚሆኑት ዘላቂ አካል ጉዳተኝነት ያጋጥማቸዋል። ታድያ ይህ የሕክምና ጉዳይ ብቻ አይደለም። የኢኮኖሚም ተግዳሮት ነው። የወጣቱ ገበሬ መራመድ አለመቻል የምርት መጥፋት ነው። እጁን መጠቀም ያቃተው ተማሪ ፤ የትምህርት ውጤታማነቱ ፈተና ላይ ይወድቃል። አባት ባልታከመ ስብራት ስራ መስራት አለመቻሉ ፤ ሙሉ ቤተሰብ ያስርባል። ለዚህ ይህ የማህበረሰብ ኪሳራ ነው። 🏥 ባህላዊ ወጌሻ ወይስ ዘመናዊ ህክምና? ባህላዊ ወጌሻዎች በማህበረሰቡ ዘንድ የተከበሩ ቢሆኑም ፤ ክፍተት ግን አለባቸው። ከሚታዩባቸው ክፍተቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ኤክስሬይ ይጎድላቸዋል → ይህ ማለት ስብራት እና መነቀልን መለየት አይችሉም ማለት ነው። የጸዳ መሳሪያዎች የላቸውም → ይህም ማለት ኢንፌክሽኑን የማሰራጨት እድላቸው ሰፊ ነው። የሕክምና ስልጠና ይጎድላቸዋል → ይህም ማለት እንደ ውስጣዊ ደም መፍሰስ ወይም የአከርካሪ ጉዳት ያሉ የተደበቁ ጉዳቶችን ላይለይዋቸው ይችላሉ። ለዚህም ብዙ ጉዳት ሊያስከትሎ ይችላሉ። ታድያ በዘመናዊ ሕክምና እና በባህላዊ ወጌሻ መሀከል ያለውን ርቀት ማጥበብ ይኖርብናል። ጤና ጥበቃ በበኩሉ ባህላዊ ህክምናን ከዘመናዊ ህክምና ጋር አቆራኝቶ ውጤታማነት ለማሻሻል እየሰራ ይገኛል። እርስዎም በበኩልዎ ደግሞ ፤ ስብራት እና ውልቃት በአይን ለመለየት እንደሚያዳግቱ ተረድተው ፤ ህክምናዎን ከመላምት ይልቅ በኤሚጂንግ/ኤክስሬይ ምርመራዎች ላይ ይመስርቱ። ያስተውሉ ! ዘመናዊ ሕክምና ከባህላዊ ህክምና ጋር ፍጽም ተቃርኖ የለውም። ይልቁኑ የባህላዊ ህክምናን ድክመት የሚያግዝ ነው። ለዚህም ስብራትና ውልቃትን ለመለየት አይን ማየት የማይችለውን በሚያሳዩት የዘመናዊ ህክምና መሳሪያዎች ይመርኮዙ። የአጥንትዎን ጤና ይጠብቁ! በመጀመሪያ ሆስፒታል ይሂዱ። ለማገገም በሀኪምዎ ምክር እንደአስፈላጊነቱ ከዘመናዊ ወጌሻዎች (ፊዚዮቴራፒስት) ጋር ይከታተሉ። 💡ተግባራዊ አንድምታው! ይህን በማድረጋቸው በአለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ አገሮች የአካል ጉዳትን መጠን ከ40-60 በመቶ መቀነስ ችለዋል። ይህንን ካሻሻልን ኢትዮጵያም ተመሳሳይ ነገር ማሳካት ትችላለች።












