top of page

የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ፡ማድረግ ያለብዎ እና የሌለብዎ

የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ የሚፈልግ ሰው በየመንገዱ ማየት የተለመደ ነው። ምናልባት ዛሬ ራሱ በመንገድ ላይ አንድ ሰው ወድቆ በሰዎች ተከቦ አይተው ይሆናል።


ሰው እንደመሆናችን ባልታሰበ ቦታ እና ጊዜ ላይ አደጋ ማጋጠሙ አይቀርም። ምናልባት በስራ ቦታ ፣ በትምህርት ቤት ፣ በትራስፖርት፣ እንዲሁም በቤትዎ ድንገተኛ አደጋ ሊያጋጥ ይችላል። አንድ ግለሰብ ራሱን ስቶ ሊወድቅ ፣ ግራ ሊጋባ ፣ ደም ሊፈስ ይችል ይሆናል።

ree
ታድያ ይህን ጊዜ ምን ያደርጋሉ?

አንዳንዶች ከበው መታዘብ ሲመርጡ ፤ ሌሎች የታመመውን ሰው ከጭንቅ ለማውጣት ሲተራመሱ ይስተዋላል።


ለዚህም አፍንጫ ስር ክርቢት መለኮስ ፣ ውሀ/ለስላሳ መስጠት የሚሯሯጥ ሰው ማየት የተለመደ ነው። የተጎዳውን ሰውንም እፍስፍስ አድርገው አንስተው ከሆስፒታል ይዘው የሚሄዱ ደግ ሳምራዊያንም አይጠፉም።


ታድይ ይህ ምን ጥፋት አለው ይሉ ይሆን?

ልቦናቸው በመልካም የተነሳሳ ቢሆንም ፤ ብዙዎች ግን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ፈጽሞ አያውቁም። በተለምዶ ሌላ ሲያደርግ ያዩትን ነው የሚያደርጉት። ተስፋቸው መልካም ውጤት ማየት ነው።


ታድያ እዚህ ላይ ትክክለኛ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ክህሎት ቢኖርበት ምን ነበረበት። በትንሹ አንድ ህይወት ይድናል።


አንድ ታሪክ እናውጋ እስቲ ...


በአዲስ አበባ ከተማ ነው። አንድ ጠይም ዘለግ ያለ በ20ዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ ያለ ወጣት በድንገት እንደ ዛፍ ተገንድሶ ይወድቃል። ወድቆም አላበቃ መንቀጥቀጥ ይጀምራል።


ታድያ ድንገት ይጓዝ የነበረ ወጣት እንዲህ መሆን ያስደነገጣቸው ይከቡታል። አንዱ ከእግሩ ሊያስጠጋው ሲሞክር ፤ ሌላኛው ጭንቅላቱን ይደግፋል። አንዲት ተመሳሳይ እድሜ ያለች ሴት በሀዘን እያማተረች የተሰበሰበው ሰው እንዲያስረዳት ትጠይቃለች። በዚህ ሁሉ ትርምስ መህል ወጣቱ ሰውነቱ ግትር ብሎ ይርዳል። ጥርሱን ነክሶ ቢያወሩት አይመልስም። አንዱ 'ክብሪት ክብሪት...' እያለ ሮጠ። ሌላ መልካም ሴት ሚሪንዳ ልትገዛ ሱቅ ፍለጋ ላይ ናት ። "ስኳር ይሆናል" የሚልም አለ

ree

ታድያ የዚህን ጊዜ ነው አንድ የጤና ባለሙያ ስታልፍ ፤ ሚሪንዳ ሊያጠጡት የሚታገሉ ሰዎችን "በጎኑ አድርጉት" አለቻቸው። ቀርባም ያለውን ስታስተውል ፤ ቀኝ እጁ ኪሱን እየጠቆመ እንዳለ ተመለከተች። የሚያመላክተው ኪሱ ስትገባ ፤ ኪሱ ውስጥ የማንቀጥቀጥ መድሀኒት አገኘች። በጎን ባለበት ፤ በጥርሶቹ መሀል መድሀኒቱን ሰጥታ አዋጥቸው። በዋጠም በደቂቃዎች ውስጥ መንቅጥቀጡ ቀንሶ አቆመ።


ልጁ የማንቀጥቀጥ ህመም ያለበት ታካሚ ሆኖ ሳለ ፤ የጠዋት መድሀኒቱን ቁርስ ስላልበላ ሳይውጥ ወጥቶ ነው እንዲህ የሆነው ። አንዳንዴ የሚያስፈልገው የመጀመሪያ እርዳታ አብሮ ማስተዋል ሊሆን ይችላል። እንዲህ አይነት ታማሚዎች ፤ ለድንገተኛ እንዲሆን የሚይዙት መረጃ/መድሀኒት ኪሳቸው ውስጥ ይኖራል።


የመጀመሪያ እርዳታ ለምን አስፈላጊ ነው

ድንገተኛ አደጋ ብዙ ጊዜ አፍታ አይሰጥም አምቡላንስ በቅጽበት አይደርስም። ደቂቃዎች አልያም ሰዓታት ሊወስድ ይችላል። መንገዶች ሊዚጋጉ ይችላሉ። ጤና ተቋማት በ ታካሚዎች ተጣበው ሊሆኑ ይችላሉ።


የዚህን ጊዜ የ መጀመሪያ እርዳታ የአንድን ግለሰብ መኖር የሚወስን ብቸኛው የህይወት መስመር ነው።

ree

ይህም ደግሞ በመረጃ የተደገፈ ነው።

በገጠራማ ባንግላዲሽ ካሉ 1.2 ሚሊዮን ሰዎች መሀል 9 በመቶ የሚሆንት በስድስት ወር ውስጥ አንድም ይሁን ሌላ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ታድያ ከእነኝህም መሀከል ከ 80% በላይ የሚሆኑት የመጀመሪያ እርዳታ አግኝተዋል። የመጀመሪያ እርዳታ ስልጠና ባላቸው ሰዎች እርዳታ ያገኙት ታድያ በንጽጽር በተሻለ ደረጃ አገግመዋል።


በታንዛኒያ ደግሞ ለትራፊክ ፖሊስ መኮንኖች በተሰጠ የ16 ሰአታት የመጀመሪያ እርዳታ ስልጠና የብዙዎችን ህይወት ሊያተርፍ ችሏል።


ይህ ረቂቅ ምርምር አይደለም። ትምህርት ነው!


ማንኛውም ሰው የመጀመሪያ እርዳታን መማር ይችላል። ትምህርቱም ውጤታማ ነው።

በብዛት የሚደረጉ የተሳሳቱ ነገሮች


በመልካም ልቦና ተነሳስተን ቢሆንም በዘልማድ የምናደርጋቸው ድርጊቶች ብዙውን ጊዜ ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዝናል።


ለምሳሌ፡

  • ንቃተ ህሊና ለሌለው ሰው በተንጋለለበት ፤ በአፍ ውሀ ወይም መጠጥ መስጠት ፤ ፈሳሽ ወደ ሳንባ እንዲገባ ያደጋል። ይህ ደግሞ ህይወትን አደጋ ላይ ይጥላል።

  • በእሳት/በጋለ/ በፈላ ነገር የተቃጠለ ቆዳን ቅቤ/ዘይት/ የጥርስ ሳሙና መቀባት ፤ ጉዳቱ እንዲቀጥል ያደርጋል። አካል ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ያብሳል።

  • አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ከወደቁበት ቦታ ማንቀሳቀስ ፤ ስብራትን ሊያብስ፤ የአከርካሪ አጥንት ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ይህ ደግሞ ባይገል አካል ጉዳተኛ ያደርጋል።


እነዚህ ልምምዶች ከመልካም ዓላማ የመጡ ቢሆንም ሊገድሉ እንደሚችሉ መረዳት ያስፈልጋል።


መፍትሄው። ከዘልማድ ይልቅ በመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ በኩል እውቀት ይኑርዎ ። ትምህርት ይውሰዱ። ክህሎት ያዳብሩ።

ሳይንስ ምን ይላል? የተወሰኑ የሳይንስ ምሳሌዎች


 ማንም ሰው ሊማራቸው የሚችላቸው አምስት ቀላል፣ በማስረጃ የተደገፉ የመጀመሪያ እርዳታ እርምጃዎች እነሆ፡


ree

አደጋ

ምን ይደረግ

ለምን አስፈላጊ ነው

ደም መፍሰስ

የሚደማው ቦታ ላይ በንጹህ ጨርቅ ግፊት ያድርጉ። የቆሰለውን ስፍራ ከተቻለ ከፍ ያድርጉት።

ይህ የደም መፍሰስን ያቆማል። ደም መፍሰስ ደግሞ ብዙዎችን የሚቀጥፍ ነውና፤ ፈጽሞ ችላ አይበሉ።

እሳት አደጋ/ የፈላ/የጋለ አካል አደጋ

የተጎዳውን ስፍራ ላይ ቢያንስ ለ 20 ደቂቃዎች ንጹህ ውሃ ያፍሱበት። ይህ ወዲያውኑ ያቀዘቅዘዋል። በስሱ ይሸፍኑ።

ይህ ቆዳን ስለሚያቀዘቅዝ ፤ የጉዳቱን መጠን ይገድባል። ጥልቅ ጉዳትን ይከላከላል። ለዚህም ቶሎ ያገግማሉ።

በምግብ መታነቅ/ ትንታ

የታነቀው ስው እንዲያስል አበረታቱ። ከታነቀው ሰው ጀርባ በመሆን እጅን ሆድ ላይ በማድረግ፤ ሆድን በመግፋት ገፍትሮ እንዲወጣ ማገዝ ይኖርብዎታል (ከሰለጠኑ)።

አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ፤ የአየር ቱቦ በቶሎ እንዲጸዳ ያደርጋል። ይህ ህይወትን ያተርፋል። .

ስብራት / የተጠረጠረ የአከርካሪ ጉዳት

ዝም ብለው ይቆዩ። ታካሚውን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ቀጣይነት ያለው ጉዳት ከሌለ (ለምሳሌ፡ የሚቆርጥ ነገር፤ የሚናድ ድንጋይ፣ አስፋልት ላይ ከወደቀ በመኪና እንዳይመታ፣ ወ.ዘ.ተ ካልሆነ) አያንቀሳቅሱ። ፈጽሞ አያንቀሳቅሱ።

ይህ ስብራቱ እንዳይባባስ ያደርጋል። የአንገት አከርካሪ አጥንት ጋር ጉዳት ካለ ስናንቀሳቅሳቸው ሊሞቱ ይችላሉ። የጀርባ አከርካሪ አጥንት ከሆነ ደግሞ ሽባ ሊሆን ይችላል።

የደም ግፊት መቀነስ / ድንጋጤ

ግለሰቡን ቀጥ ያለ ቦታ ላይ እንዲተኛ ያድርጉ። እግሮችን ከፍ ያድርጉ። እንዳይበርድ ወፍራም ልብስ ያድርጉ።

ይህ የደም ፍሰትን ያሻሽላል። ወደ ከፋ ሁኔታ ከመውደቅ ይከላከላል።።


ሁሉም ላይ አምቡላንስ መጥራት ፈጽሞ አይረሳ።


እነዚህ ውስብስብ አይደሉም። ውድ መሣሪያ አያስፈልጋቸውም ። ግንዛቤ እና ልምምድ ብቻ!

ታድያ ሰዎች ለምን አስፈላጊውን የመጀመሪያ እርዳታ አይማሩም?


ree

ለዚህ አንደኛ የሚጠቀስ የሚሆነው የትምህርቱ ተደራሽነት ችግር ነው። በተለይም በገጠር አካባቢዎች ስልጠናዎች እምብዛም የሉም። ይህ ደግሞ በማህበረሰብ ደረጃ የመጀመሪያ እርዳት እውቀት ያላቸው ሰዎች መጠን ዝቅተኛ እንዲሆን ያደርጋል።

ከዚህ ባሻገር ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ፍርሀት አለባቸው። እንደዚህ አይነት ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎችን በሚረዱበት ጊዜ የሚያጋጥም ህጋዊ ተጠያቂነት ይፈራሉ። ይህም ትምህርቱንም እንዳይወስዱ ፤ ሰው መርዳት እንዳይፈልጉ ሲያደርጋቸው ይታያል። ሌሎች ከሳይንስ ይልቅ በልምድ /በዘልማድ ድርጊቶች ይተማመናሉ። ለዚህም ትምህርቱን ለመማር ተነሳሽነት የላቸውም።


ነገር ግን እነዚህ ሁሉ መሰናክሎች በቀላሉ መፈታት ይችላሉ። የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት መፍትታት ይቻላል። እዳው ገብስ ነው!


በሀገር ደረጃ ምን መደረግ አለበት?

የመጀመሪያ እርዳታ ህይወትን የሚያድን እስከከሆነ ድረስ፤ በአጋጣሚ መተው የለበትም። ሁላችንም የመፍትሔው አካል መሆን አለብን።

ree
  • ሹፌሮች፣ አስተማሪዎች፣ ባለሱቆች፣ ተማሪዎች፣ ወ.ዘ.ተ በመንግስትና ባለድርሻ አካላት የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ መሰልጠን አለባቸው።

  • ቀጣዩ ትውልድ እያወቀ እንዲያድግ የመጀመሪያ እርዳታ በትምህርትቤቶች ካሬኩለም መዋሀዱ መልካም ነው።

  • የመጀመሪያ እርዳታ ክህሎቶችዎን በመደበኛነት ያድሱ። አጫጭር ስልጠናዎችን ይውሰዱ።

  • ሊረዱ ያሰቡ በጎ ሰዎች ህጋዊ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል። ህግን እያስከበሩ መልካምነትእንዳይጠፋ ፤ እዚህ ጋር የህግ አካላት ቅንጅት ያስፈልጋል።

  • በሚዲያ አካላት፣ በማህበራዊ ድህረ ገጽ እንዲሁም በበራሪ ወረቀቶች ትምህርት ሰጪ የመጀመሪያ እርዳታ እውቀቶች መሰራጨት እውቀት/ክህሎቱን ያስፋፋሉ።


ያስተውሉ

የመጀመሪያ እርዳታ ለዶክተሮች ብቻ አይደለም። ለሁላችንም ነው።

በሚቀጥለው ጊዜ አንድ ሰው በመንገድ ላይ ሲወድቅ ምን ያደርጋሉ? ልማድ ወይስ ሳይንስ?


ምክንያቱም በእነዚያ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ውስጥ እርስዎ አምቡላንስ ነዎት። ሆስፒታሉ ነዎት። በሕይወትና በሞት መካከል ያለው ልዩነት አንተ/አንቺ ነህ/ሽ።

 


Comments


bottom of page