የተልባ ጤና ጥቅም: ሳይንስ ወይስ ባህል
- Zebeaman Tibebu
- Nov 10
- 4 min read
ለመሆኑ ተልባ ወስደው ያውቃሉ? በምን መልክ?
ተልባ በአለም ዙሪያ ለዘመናት ጥቅም ላይ ውሏል። ከግንዱ እና ቅርንጫፎቹ የሚወጣው ቃጫ ለአልባሳት መስሪያ ሲያገለግል ፤ የተልባ ፍሬ (ዘር) ደግሞ በምግብነት እና በመድሀኒትነት ውሏል።
ለምሳሌ ፡ ከ 5000 አመታት በፊት በጥንታዊቷ ግብጽ ለመድሀኒትነት ጥቅም ላይ ዉሏል። ተልባ ንጽህናን እና ህይወትን ያሳያል ብለው ያምኑ ስለነበር ፤ በሱ የሚሰሩ አልባሳትን ለአምልኮ ጊዜ ይጠቀሟቸው ነበር።
የህክምና አባት በመባል የሚታወቀው ሂፖክራተስም የተልባ ፍሬ የሆድ ህመሞችን እና አንጀት ችግሮችን እንዲያድን ያዝ ነበር።

በአውሮፓ፣ በኢሲያ እንዲሁም በአፍሪካም ተልባ ውስጡ ላለው ዘይት እንዲሁም ለልብስነት ጥቅም ላይ ይውል ነበር።
በኢትዮጵያ ተልባ ብዙ ባህላዊ ጥቅም አለው። ለዘይትነት፣ ለምግብነት፣ ለመድሀኒትነት ሲውል ቆይቷል። እናቶቻችን እና አያቶቻችን ለጨጓራ ህመም ፣ ለሆድ ድርቀት እንዲሁም ማህጸንን ለመክፈት (ባህላዊ አባባል) አውለውታል።
ታድያ ይህ እውነት ወይስ ትውፊት ?
በሳይንስ እና በባህል መሀል ያለውን እንመርምር። ባህላዊ ጥቅሙ በይበልጥ ሊያውቁት ስለሚችሉ ፤ ስለ ሳይንሱ ብቻ እናነሳለን።
ተልባ በውስጡ ምን አለ?
ዘመናዊ ሳይንስ እንደሚያሳየው ተልባ በልዩ ንጥረ ነገሮች/ውህዶች የበለጸገ ነው። ውስጡ ካሉ ንጥረ ነገሮች በዋነኝነት ህክምናዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው የተረጋገጡት የሚከተሉት ናቸው።

አልፋ-ሊኖሌኒክ አሲድ (ALA) - ይህ ከእጽዋት የሚገኝ እንደ ኦሜጋ 3 ፋቲ አሲድ (Omega 3) ሲሆን ፤ በይበልጥ በተልባ ዘይት ውስጥ ይገኛል። በህክምናው ኦሜጋ 3 ፋቲ አሲድ ፤ ነርቮች ላይ ባለው መልካም ተጽእኖ የአእምሮ እድገትን ያጎለብታል። ለዚህም ለህጻናት ተለይቶ ይሰጣል።
ሊግናንስ (በዋነኛነት secoisolariciresinol diglucoside/ SDG የሚባለው) - ይህ እጽዋት ውስጥ ከሚገኙ ፖሊፌኖል(polyphenol) ከሚባሉ ውህድ አይነቶች ውስጥ አንዱ ነው። እነኝህ ውህዶች ሰውነት መቆጣትን ይቃወማሉ። የጸረ ኦክሲዳንት ባህሪ አላቸው። እንዲሁም የኢስትሮጅ ሆርሞን ተመሳሳይ ባህሪ አላቸው።
በውስጣቸው አሰር (ፋይበር) አላቸው ፡ ይህ ደግሞ የምግብ መፈጨትን ያሻሽላል። የኮሌስቶሮል ኡደንትም ያስተካክላል። የደም ስኳር መጠንም ላይ ተጽእኖ ያሳድራል።
ፕሮቲን፣ ቫይታሚኖች እና ማዕድናት አሉት - ውስጡ ፕሮቲኖች፣ ቫይታሚኖች እንዲሁም ማእድናት ቢኖሩትም ፤ መጠናቸው አነስተኛ ስለሆነ ፤ የእነሱ ዋነኛ ምንጭ መሆን አይችልም። በተጨማሪ ምግብነት ማገልገል ይችላል።
ሳይንሳዊ ጥናቶችስ ስላለው የጤና ጥቅም ምን ይላሉ?
ብዙ ጥናቶች በዚህ ዙሪያ የተካሄዱ ቢሆንም ፤ በይበልጥ በማስረጃ የተደገፉት የሚከተሉት ናቸው።
1) የመጥፎ ኮሌስትሮል( LDL) እና የአጠቃላይ ኮሌስትሮል(Total Cholesterol) መጠንን ይቀንሳል። ወደ መደበኛ ደረጃ ያወርዳል።

የተልባ ዘር (ተፈጭቶ ሆነ ጥሬውን) የሰውነት የኮሌስትሮል መጠንን የመቀነስ አቅም አለው። የመቀነስ አቅሙ በተለይ የኮሌስትሮል መጠናቸው ከፍ ያለና ያረጡ ሴቶች ላይ በይበልጥ ይስተዋላል ።
እ.ኤ.አ. በ 2009 የተለቀቀ ጥናትም ይህንን ይደግፋል። ተልባ የወሰዱ ሰዎች የኮሌስትሮል መጠናቸው ተሻሽሏል። ከዚህም ባሻገር የተደረጉ ጥናቶች የደም ውስጥ ያለ ስብን የመቀነስ አቅሙን ይጠቁማሉ።
ሆኖም ግን የደም ኮሌስትሮል መጠንን የሚቀንሰው ፤ በአንድ ቀን አልያም በከፍተኛ መጠን አለመሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። የሚቀንሰው በመጠኑ ነው።
2) የደም ግፊትን ይቀንሳል(በተለይም የደም ግፊት ባለባቸው ሰዎች ላይ)።

በቅርብ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ የተልባ ፍሬ የደም ግፊት ቁጥጥርን ያሻሽላል። ይህ መሻሻል በይበልጥ የሚስተዋለው የደም ግፊታቸው ከፍ ባለ ወይም የደም ግፊት በሽታ ባለባቸው ታካሚዎች ላይ ነው።
ጥናቱ የተደረገባቸው ታካሚዎች ተልባ በመጠቀማቸው የላይኛው የደም ግፊት (ሲስቶሊክ) እንዲሁም የታችኛው የደም ግፊት (ዳያስቶሊክ) መጠን በአመርቂ ሁኔታ ቀንሷል።
ይህ ተልባን የደምግፊት መድሀኒት መተኪያ ባያደርገውም ፤ ደም ግፊት ላለባቸው ሰዎች የደም ግፊታቸውን ለመቆጣጠር የሚረዳ የአኗኗር ዘይቤ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ለዚህም የሚያውቁት ደም ግፊት ያለበት ሰው ካለ ተልባ እንዲያዘወትር ይምከሩት። ይጠቅመዋል!
3) የሰውነት መቆጣትን ይቀንሳል።

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከሆነ ተልባ ውስጥ ያሉ ውህዶች የሰውነት መቆጣትን ይቀንሳሉ። ይህም የመቆጣትን የሚያባብሱ ውህዶችን (TNF-α, IL-1β, and IL-6) ከመቀነሱ ጋር እንደሚያያዝ የሚጠቁሙ ጥናቶች አሉ። ስብ ላይ እንዲሁም ኦሜጋ 3 ፋቲ አሲድ ላይ ያለው ተጽእኖ እንዲሁም የጸረ ኦክሲዳንት ባህሪውም ለዚህ ምክንያት ተደርገው ይጠቀሳሉ።
በዚህ ዙሪያ ብዙ ጥናቶች አሁንም ይቀራሉ።
4) የልብ ጤናን ያሻሽላል።

ተልባ ፍሬ ውስጥ ያሉት ውህዶች የልብ ጤናን ያሻሽላሉ። ይህም በተለያየ መንገድ የሚፈጠር ሲሆን ፤ ከዚህ ውስጥ ኮሌስትሮልን መጠን መቀነሱ አንዱ ነው። ከዚህም ባሻገር የደም ግፊትን መቆጣጠሩ ፣ የጸረ ኦክሲዳንት ባህሪው፣ መቆጣትን መቀነሱ እንዲሁም የደም የስኳር መጠን መቀነሱም ሊጠቀስ ይችላል።
ልብ ላይ ያለው መልካም ተጽእኖ ቢረጋገጥም ፤ በዚህም ዙሪያ ጥናቶች ገና ሙሉ በሙሉ አልተደራጁም።
5) የምግብ መፈጨትን ያሳልጣል።

የተልባ ዘር በፋይበር/አሰር የበለጸገ ነው። ይህ ደግሞ የአንጀትን ጤናማ እንቅስቃሴ ያበረታታል። እንዲሁም የአንጀትን ስራ ይደግፋል።
በዚህ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ተልባን በየቀኑ መጠቀም ድርቀትን ይቀንሳል። ሽንትቤት በተደጋጋሚ መጠቀም እንዲችሉ ያደርጋል። ይህ ጥቅሙ ከመካከለኛ እድሜ በላይ ባሉ ሰዎች ላይ በይበልጥ ታይቷል።
ውስጡ ያለውም የሚዝለገለግ የሚመስል ውህድም ፤ እንደ ተፈጥሮአዊ ጄል በመሆን ፤ የጨጓራ እና የአንጀት ግድግዳን ይሸፍናል። ይህም ሆድን ከጉዳት ከመጠበቁም ባሻገር የምግብ ቱቦን ጤና ያሻሽላል።
6) የካንሰር ተጋላጭነትን ይቀንሳል።

የላብራቶሪ እና የእንስሳት ጥናቶች እንደሚያሳዩት ፤ ተልባ ውስጥ የሚገኙት ሊግናን የሚባሉት ውህዶች የዕጢን እድገት ይቀንሳ። ህዋሳት ያለ ቁጥጥር እንዳያድጉ ይከላከላሉ። ይህ ውስጡ ያሉ የኢስትሮጅን ባህሪ ካላቸው እንዲሁም መቆጣትን ከሚቀንሱት ኬሚካሎች ጋር ይያያዛል።
ሆኖም ግን በዚህ ዙሪያ ያሉ ጥናቶች መጀመሪያ ላይ ናቸው ያሉት። ለዚህም ካንሰርን የመከላከል አቅሙ ሙሉ በሙሉ አልተረጋገጠም።
6) ገና ያልተረጋገጡ ጥቅሞች
አንዳንድ ጥናቶች የተልባ ፍሬ
ውስጡ ያለው ኤኤልኤ የሚባለው ኬሚካል የነርቭን ጤና እንደሚያሻሻል እንዲሁም የአእምሮን አቅም የማጎልበት ኃይል እንዳለው ይጠቁማሉ።
ውስጡ ያለው የኢስትሮጂን ባህሪ ያለው ውህድ ላረጡ ሴቶች የማረጥ ምልክቶችን የመቀነስ አቅም እንዳለው ያሳያሉ።
ሆኖም ግን እነኝህ ጥቅሞች ገና በህክምና ሙሉ በሙሉ አልተረጋገጡም። በዚህ ዙሪያ ጉዳት ባይኖራቸውም ፤ ጥቅማቸውን አፍ ሞልቶ ለመናገር የሚያስችሉ ጥናቶች የሉም። ምናልባት በቀጣይ አመታት የሚደረጉ ጥናቶች በደንብ ይህንን ያሳዩ ይሆናል።
⚖️ ስለ ተልባ ግልጽ መሆን ያለባቸው ነገሮች
አንዳንድ ጊዜ የተልባ ዘር ካንሰርን "ይፈውሳል"፣ የልብ ሕመምን "ያድናል" ወይም ክብደትን የሚቀንስ ተአምራዊ ምግብ ነው የሚሉ ፤ መሰረት የለሽ መረጃዎችን ሰምተው ያውቁ ይሆናል። ይህ ግን በመረጃ የተደገፈ አይደለም። መረጃዎች የሚናገሩትን ያስተውሉ።

እዚህ ጋር ግልጽ መሆን አለብዎ፡
ካንሰርን "አይፈውስም።"
ስብን/ቅባትን/ ኮሌስትሮልን በአንድ ሌሊት "አያጠፋም።" ቀስ በቀስ ነው የሚቀንሰው።
የልብ በሽታን አያጠፋም ወይም አይፈውስም። የልብ ጤናን የሚያሻሽሉ ውህዶች ግን አሉት። ስለዚህ የልብ ጤና ይሻሻላል።
የተለያዩ በሽታዎችን የሚቀንሱ ውህዶች ቢኖሩትም ፤ ለማንኛውም በሽታ የሚታዘዝ ህክምና ምትክ አይደለም።
ተልባ ምግብ ነው - ገንቢ፣ ደጋፊ ምግብ ። ሆኖም ግን ተአምራዊ አይደለም።
🥄 በትክክለኛው ሁኔታ እንዴት መጠቀም ይችላሉ?
✔️ ከመመገብዎ በፊት ይፍጩት። ለምን? ያልተፈጨ ተልባ ፍሬዎች በአንጀታችን ሳይፈጩ ሊያልፉ ፤ በሰገራ ሊወጡ ይችላሉ።

✔️ በቀን 1–2 የሾርባ ማንኪያ ይውሰዱ። በሚመገቧቸው ምግቦች ውስጥ (እንደ ገንፎ፣ ጭማቂዎች ፣ ሰላጣ፣ ስሙዚ፣ ቧል፣ ወ.ዘ.ተ...) ይጨምሩ። አብዝተው መውሰድ አይመከርም።
✔️ በአግባቡ ያስቀምጡ ። የተፈጨ ተልባ በቀላሉ ስለሚበላሽ ፤ ያዘጋጁትን በማቀዝቀዣ ውስጥ ያስቀምጡ።
✔️ የደም ማቅጠኛዎችን የሚወስዱ ወይም የሆርሞን ችግሮች ካሉብዎ ፤ በቅድሚያ የጤና ባለሙያን ያማክሩ።
🧠መደምደሚያ
ተልባ መመገብ ባህል ብቻ አይደለም!
አያቶቻችን በባህል ተመስርተው ሰጥተውን ቢሆም ፤ አሁን በሳይንስ የተደገፈ ጥቅም አለው።
እርስዎም የሚመገቡት ምግብ ውስጥ ይደባልቁ።





Comments