top of page

በእንቅርት ላይ...


እንቅርት በሽታን የማያውቅ አለ ማለት ዘበት ነው!

 ግን ግንዛቤዎ ምን ያህል ነው?እንቅርት በሽታ ከጨው ጋርስ  ግንኝነት እንደሌለው ያውቃሉ?

 እንቅርት በሽታ የሰውነታችን ውስጥ ዋነኛ እጢዎች መሀክል አንገታችን መሀል ከማንቁርታችን ፊትለፊት የሚገኘው የታይሮይድ እጢ ማደግ ነው።  ይህ እጢ በተፈጥሮው የቢራቢሮ ቅርጽ ያለው ሲሆን ፤ መጠኑ ካልገዘፈ በስተቀር በአይናቸን ለመለየት ያስቸግራል።

 

ስራውስ?


ስራው እጅጉን ሰፊ ነው። በዚህ እጢ የሚመረተው ሆርሞን (ታይሮይድ ሆርሞን) በአንድ በኩል ወይም በሌላ የማይነካው የሰውነት ክፍል የለም። የዚህ ሆርሞን ስራዎች ውስጥ ጥቂቶቹ፡

  • የሰውነትን ኡደት (ሜታቦሊዝም) ይከታተላል። ለዚህም ሰውነታችን ኃይል አጠቃቀም ፣ ግሉኮስ መጠቀሙን፣ ሙቀት ማምረቱን ፣ ወ.ዘ.ተ ላይ ተጽእኖ አለው።

  • እድገትን ይደግፉል - ለልጆች አካላዊ እድገት አስፈላጊ ነው።

  • የአንጎል እድገትን ያግዛል - ለፅንስ እና ለጨቅላ ህጻናት አንጎል ስራ እና እድገት አስፈላጊ ነው.

  • የልብ ሥራን ይጠብቃል - የልብ ምት እና የደም ዝውውርን ሊጨምር ይችላል።

  • የሰውነት ሙቀትን ይቆጣጠራል - ሰውነታችን መደበኛውን የሙቀት ሚዛን እንዲጠብቅ ይረዳል።

  • የምግብ መፈጨትን ይደግፉል - የምግብ ፍላጎትን እና የአንጀት እንቅስቃሴን ያበረታታል።

  • የስነ ተዋልዶ ጤና ላይ ተጽእኖ አለው - የወር አበባ ዑደትና የመውለድ መቻል ላይም ተጽእኖ አለው።

  • የቆዳ፣ የፀጉር እና የጡንቻን ጤንነት ይጠብቃል።

  • ቀይ የደም ህዋሳት ምርት ላይ ያግዛል።

  • ከሌሎች ሆርሞኖች ጋር በመተባበርም የሰውነት ስርዓቶችን ሚዛናዊነት ይጠብቃል


ree

ታድያ ይህ እጢ በተፈጥሮ ከተለመደው መጠኑ ይልቅ ሲያልፍ እንቅርት ወይንም ጎይተር አጋጠመ እንላለን።  ጎይተር በሽታ በአለም በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን በአለም ዙሪያ እንደሚያጠቃ የዓለም ጤና ድርጅት ይገልጻል። ወደ 30 ፐርሰንት የሚጠጋው የአለም ህዝብ የአዮዲን እጥረት ባለባቸው አከባቢዎች ይኖራል። 


የአዮዲን እጥረት ደግሞ የእንቅርት በሽታ ዋነኛ አጋላጭ ተደርጎ ይገለጻል። በአለም ዙሪያ ወደ 2 ቢሊየን የሚጠጋ ህዝብ ለዚህ እጥረት እንደተጋለጠ ከዚህም ውስጥ ወደ 241 ሚሊየን የሚጠጉት ልጆች እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።


ሀገራችን ኢትዮጵያም እንቅርት በሽታ በስፋት ካሉባቸው ሀገራት ተርታ ትጠቀሳለች። የዚህ በሽታ መጠን ከ 40 እስከ 43 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎችን እንደሚያጠቃ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

ለምን?


በአንድ በኩል ለዚህ ተጠቃሽ የሚደረገው የምንጠቀመው ጨው ውስጥ ያለው የአዮዲን መጠን ነው። በመልካም ጎኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ለቤት ውስጥ ፍጆታ የምንጠቀመው ጨው ውስጥ እስከ 89 ፐርሰንት የሚጠጋው አዮዲን አለው። ሆኖም ግን ይህ ጨው ውስጥ ያለው የአዮዲን መጠን በቂነት አጠራጣሪ ነው።


የህጻናት ተማሪዎች የሽንት ምርመራ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ይህንን ይጠቁማሉ። ምርመራ የተደረገላቸው ተማሪዎች ሽንታቸው ውስጥ ከ 25 ማይክሮ ግራም ያነሰ አዮዲን ተገኝቷል። ይህ ደግም ሰሞኑን የተመገቡት የአዮዲን መጠን አነሰተኛ መሆኑን ጠቋሚ ነው። የአለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠው ደረጃ በቂ አዮዲን የሚወስድ ሰው ቢያንስ በሽንቱ ውስጥ ከ100 ማይክሮ ግራም በላይ አዮዲን መገኘት አለበት።

 

ree

ይህ ደግሞ አዮዲን ያለው ጨው ተደራሽነት በሚቀንስባት በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ለሚኖሩ ሰዎች እና ለእርጉዝ ሴቶች እጅጉን አሳሳቢ ነው።


ያስተውሉ እንቅርትን የሚያስከትለው የጨው ሳይሆን የአዮዲን ማነስ ነው ።

 


ለምንድነው አዮዲን ማነስ ይህንን ችግር እያስከተለ ያለው?


እላይ እንደተገለጸው የዚህ እጢ ስራ ታይሮይድ ሆርሞን ማምረት ነው። ይህ ሆርሞን የተለያዩ አይነቶች ቢኖሩትም (T3 & T4) ፤ ይህ ሆርሞን አካል ውስጥ አዮዲን አለ። ፌሮ የህንጻ አካል እንደሚሆነው የአዮዲን ንጥረ ነገርም የዚህ ሆርሞን አካል ነው።


ታድያ ይህ  ንጥረ ነገር ሲያንስ ሰውነታችን የሚረዳው የታይሮይድ ሆርሞን ምርት ማነሱን ነው። ያነሰውን ምርትም ለማሻሻል ሰውነት አምራች አካሉን (እጢውን) ማስፋት ይጀምራል። ምርት እንዲጨምር ፋብሪካ እንደማስፋት ማለት ነው።  ይህ ደግሞ ታይሮይድ እጢ እንዲገዝፍ ወይም መጠኑ እንዲጨምር ያደርጋል።


ree

ችግሩ የምርት ማነስ ስላልሆነ ፤ የአዮዲን እጥረት እስኪስተካከል ድረስ ሰውነት እጢውን መጠን ለመጨመር ይሞክራል። ለዚህም ነው ትላልቅ እንቅርት ያላቸው ታማሚዎች የምናየው።


አዮዲን እጥረቱ ቢስተካከልም ሰውነት አንዴ እጢውን ስላሳደገው መልሶ አያፈርሰውም። ለዚህም አንዴ እንቅርት ከታየ ያለ ህክምና እርዳታ ሊጠፋ አይችልም።


👉 በቀላል አነጋገር ጎይተር/ እንቅርት የታይሮይድ እጢዎ የድረሱልኝ ጥሪ ምልክት ነው። ይህ ምልክት ሰውነትዎ በአዮዲን እየቀነሰ መሆኑን ሊያመላክት ይችላል።


⚠️ በዋነኝነት ተጋላጮች ማናቸው?

  1. ዝቅተኛ የአዮዲን የሚመገቡ ግለሰቦች፡ የባህር ምግቦችን ፣ የወተት ተዋጽኦዎችን ፣ እንዲሁም አዮዲን ያለበት ጨውን የማይመገቡ ግለሰቦች ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ነው።


  2. በገጠሪቷ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ግለሰቦች ፡ አዮዲን ያለው ጨው ተደራሽ ባልሆነባቸው አከባቢዎች እንዲሁም አፈር ውስጥ ያለው አዮዲን መጠን ዝቅተኛ በሆኑ አከባቢዎች (አንዳንድ ትግራይ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ያሉ ስፍራዎች) የሚኖሩ ግለሰቦች ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ነው።


    ree

  3. ሴቶች በተለይም በጉርምስና እድሜያቸው፣ በእርግዝና ወቅት  እና ጡት በማጥባት ወቅት የአዮዲን ፍላጎታቸው ከፍ ይላል። ይህ ደግሞ ተጋላጨንታቸውን ይጨምራል።



  4.  እንቅርት የሚያባብሱ/ የሚያመጡ ምግቦችን አዘውትረው የሚመገቡ ሰዎች፡ ለምሳሌ ጥቅል ጎመን፣ ማሽላ፣ ብሮክሊ፣ ስፒናች፣ ካሳቫ፣ ወ.ዘ.ተ አብዝተው የሚመገቡ ሰዎች ተጋላጭነታቸው የጨመረ ነው። 

ለምን?
ree
እነኝህ ምግቦች ውስጣቸው አዮዲንን የሚቃወም አልያም ታይሮይድ ሆርሞንን የሚጻረር ውህድ አላቸው። ለዚህም እጅጉን አብዝተው ከተመገቧቸው ለእንቅርት የማጋለጥ እድላቸው የሰፋ ነው። ለዚህም በህክምናው እንቅርት አምጪ (Goitrogenic) ምግቦች ይባላሉ።  ይህንን ተጽእኖአቸውን ለመቀነስ ምግቦቹን በደንብ ማብሰል ይኖርብዎታል። 
  1. የአዮዲን እጥረት ባይሆንም አንዳንድ የታይሮይድ ችግሮች በቤተሰብ ተወራራሽ ይሆናሉ። ለዚህም ቤተሰባቸው የታይሮይድ ችግር ያለባቸው ሰዎች ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ነው።


  2. አንዳንድ ከባቢያዊ ለውጦች ለእንቅርት ሊያጋልጡ ይችላሉ። ለምሳሌ አንደ ፍሎራይድ ያሉ ኬሚካሎች የአዮዲንን ኡደትን አሰናክለው ለእንቅርት ሊያጋልጡ ይችላሉ። ለዚህም ይጠንቀቁ። 


  3. የተመረተ አዮዲን ያለው ጨው አቀማመጥም ለዚህ አስተዋእጾ ያደርጋል። ይህም ሲቀመጥ ለእርጥበት እና ለጸሀይ ከተጋለጠ ውስጡ ያለውን የአዮዲን መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል። ለዚህም ቢመገቡትም ተጋላጭነት አለብዎ።


🤒 የተለመዱ ምልክቶች


የአዮዲን እጥረትን ትከትሎ የሚመጣ እንቅርት ከአንገት ፊት ላይ ከሚታይ እብጠት ባሻገር ምልክት ላያሳይ ይችላል።


ree

ሆኖም ግን 

እንቅርቱ ከፍተኛ ከሆነ፡

  • በሚዋጥበት ጊዜ የአንገት መወጠር

  •  የመዋጥ ወይም የመተንፈስ ችግር

  • የድምጽ መጎርነን ወይም የድምፅ ለውጦች ሊያሳይ ይችላል

 

ከታይሮይድ ሆርሞን መብዛት ወይም ማነስ ጋር ግንኙነት ካለው ደግሞ

  • አብዝቶ መድክመ

  • የክብደት ለውጥቅ

  • ቅዝቃዜ አለመቻል (ሆርሞኑ ካነሰ)

  • መቀት አለመቻል (ሆርሞኑ ከበዛ)

  • ማላብ

  • እረፍት ማጣት ሊያሳይ ይችላል።


በልጆች ላይ

  • እድገት መዘግየት

  • የትኩረት አለመኖር እንዲሁም 

  • የመማር ችግሮች ሊያሳይ ይችላል


በነፍሰ ጡር ሴቶች ላይ  ደግሞ

 

  • የጽንስ እድገት መገታት፣

  •  ማህጸን ውስጥ የጽንስ መሞት፣ 

  • እንዲሁም የጽንሱ የአንጎል እድገት መዘግየት ሊያመጣ ይችላል። 


🧭 እንዴት ይመረመራል?


ree
  1. ዶክተሩ በአካላዊ ምርመራ የእጢውን እድገት እና አካላዊ ለውጦችን ሊያስተውል ይችላል።

  2. የደም ምርመራዎች የታይሮይድ እጢ ስራን ሊፈትሹ ይችላሉ (TSH፣ T3 እና T4 የሆርሞን መጠንን መለካት)።

  3. የሽንት አዮዲን ምርመራ በቅርቡ ያለ የአዮዲን አወሳሰድን ያሳያል።

  4. አልትራሳውንድ የእጢውን አቀማመጥ እና አወቃቀር ያሳያል።

  5. ሌሎች የኢሜጂንግ ምርመራዎች የእጢውን ስራ እና አቀማመጥ በጥልቀት ያሳያሉ።

  6. ካጠራጠረ በናሙና የእጢውን ባህሪ መለየት ይቻላል። 


💊 ህክምናውስ?

የእንቅርት ሕክምና እንደ መንስኤው፣ እንደግዝፈቱ እና እንደ እጢው የአሰራር መጠን ይወሰናል።


ree

1. በአዮዲን እጥረት ምክንያት ከሆነ አመጋገብን ማስተካከል ይኖርብዎታል።

  • በጣም ርካሹ እና በጣም ውጤታማው ህክምና አዮዲን ያለው ጨው መመገብ ነው

  • እጥረቱ ከፍ ካለ አዮዲን ያለባቸው እንክብሎች ወይም መድሀኒቶችን በተጨማሪነት በመውሰድ ማገዝ ይቻላል። 

2. የታይሮይድ ሆርሞን ሕክምና

  • ተያይዞ የሆርሞን መዛባት ችግር ካለ ፤ የሆርሞን መጠኑን ለማስተካከል መድሀኒቶች ሊታዘዙ ይችላሉ። 

3. ቀዶ ጥገና

  • የመተንፈስ/የመዋጥ ችግር ካለ ፣ በጣም ትልቅ ከሆነ ፣ ካንሰር ከተጠረጠረ በቀዶ ህክምና ሊታከም ይችላል። 

  • ውበትም ባለው ተጸእኖ ቀዶ ህክምና ሊመረጥ ይችላል።

5. ክትትል

  • ህክምናው ከተደረገ በኋላም ክትትል እጅጉን አስፈላጊ ነው።  በተለይም ለሴቶች እና ለህጻናት።


🛡️ መፍትሔው በእጅዎ ነው። 


መከላከል ታላቁ የህክምና አማራጭ ነው ። አሁኑኑ አመጋገብዎን ያስተካክሉ። አዮዲን ያለበት ጨው ብቻ ይመገቡ።

 እንቅርት የማምጣት ባህሪ ያላቸውን ምግቦች አያዘውትሩ። አብስለው ይመገቡ። 


ከተጠራጠሩ / ማንኛውም እብጠት ካለ ዛሬውን በፍጥነት ሀኪምዎን ያማክሩ።


ተግባራዊ ለውጥ ዛሬውኑ ያምጡ፣

 

Comments


bottom of page