top of page

እንጥል መቆረጥ ወይስ?


አብዛኞቻችን በህጻንነታችን ቶንሲል ታመን እናውቃለን!

ታሞ መርፌውን የተወጋማ ፤ የማይረሳ ትውስታ አለው።

የቶንሲል መቆጣት በተለይ በህጻንነት አብዝቶ የሚያጋጥም በሽታ ነው። አንዳንዱ ደጋግሞ ይታመማል። አንዳንድ እናቶች በጨው፣ ሎሚ ፣ እና እንደ ቁንደበርበሬ ያሉ ግብእቶችን አፍልተው እንዲግሞጠሞጡ በማረግ ወይ በማስዋጥ ለማከም ይሞክራሉ። ከዚ ባስ ሲል ደግሞ በባህላዊ እንጥልን ማስወገድ እንደ ዋነኛ እና ብቸኛ መፍትሔ አድርገው ፤ በመውሰድ እንጥል ወደ ማስቆረጥ ያመራሉ


የጨነቀ እለት....አይደል የሚባለው!


ree

በሌላ በኩል የሰለጠኑትማ ... ብልሀታቸው ከዚህም የረቀቀ ነው። በዘመናዊት ኢትዮጵያ በመሀል ከተማ አዲስ አበባ እንኳን እንጥል ለማስቆረጥ ያስባሉ። ከሀኪም ቤት ሄዶ ለማስቆረጥ ያቅዳሉ። በዘመናዊ ህክምና ባህላዊ መፍትሔ እንዲህ ነው!


ልምድ የቀሰሙ ብልህ እናቶች በበኩላቸው፤ ጉሮሮ ህመም ሲጀምር በጨው ውሀ አድርገው ያጉመጠምጣሉ።


ለምን ብለን ብንጠይቅ ሁሉም ማስረጃ አላቸው።

 

ከልምዳቸውን ይጀምራሉ። "ደግሞም የእከሌ ልጅ እኮ ቶንሲል  ስትታመም እንጥሏን ከተቆረጠች በኋላ ተሽሏታል" ብለው ያስረግጣሉ።

 

የእነኝህ ወላጆች መፍትሔያቸው ለየቅሉ ቢሆንም ፤ ህመሙ እና ጭንቃቸው ግን አንድ ነው። ምርጫቸው ታድያ ብዙ ጓዝ ይዞ ይመጣል።


የጨነቃት አንድ ምስኪን እናት ፤ በግንዛቤዋ ልክ ዘላቂ መፍትሔ ብትፈልግ እንዴት ይፈረድባታል።

እነኝህን የመፍትሔ አማራጮች እና የተሻለውን መንገድ ለመረዳት ፤ ስለ ቶንሲል በሽታ እና ህክምናው በጥልቀት እንወያይ።

 

የመጀመሪያ ግንዛቤ


ከምላስ ጀርባ በግራና ቀኝ ያለው ነው ቶንሲል። እንጥል ከላንቃ ግርጌ መህል ላይ ያለው ነው።
ከምላስ ጀርባ በግራና ቀኝ ያለው ነው ቶንሲል። እንጥል ከላንቃ ግርጌ መህል ላይ ያለው ነው።

ቶንሲል እና እንጥል አንድ አይደሉም። እንጥል ላንቃችን ጀርባ መሀል ላይ ተንጠልጥሎ ያለ ስጋ/አካል ነው። ስራው ምግብ ወደ አፍንጫች እንዳይገባ መከላከል እና አፍን ለማረስረስ የሚጠቅም ፈሳሽ (ምራቅ) ማምረት ነው። በህክምና ስሙ ኡቩላ (uvula) ይባላል።

ቶንሲልስ?


ቶንሲል ደግሞ የሚባለው ከ እንጥል ጀርባ በጉሮሮ መግቢያ ጋር በግራ እና በቀኝ ዘብ የቆመ አካል/ስጋ ነው። በቀላሉ ጉሮሮአችን ጋር ያለ ንፍፊት ነው። ይህም አካል/ንፍፊት እውነትም ዘብ ነው! አፋችንና ጉሮሮአችን አከባቢ ያሉ ህዋሳት በበሽታ አምጪ ተህዋስ እንዳይጠቁ የሚጠብቁ ነጭ የደም ሴል ህዋሳት መከማቻ ካምፕ ነው። ወራሪ ሀይልን መከላከያ የወታደር ካምፕ!


ለዚህም የቶንሲል መቆጣት እና የ እንጥል መቆጣት አንድ ላይ ሊያጋጥሙ ቢችሉም እንኳን ፈጽሞ ይለያያሉ።


በግልጽ ቋንቋ የቶንሲል በሽታ ምንድን ነው - በግልጽ ቋንቋ?


የቶንሲል በሽታ ቀለል ባሉ ቃላት ስንገልጸው የቶንሲል መቆጣት ነው። የሚቆጣውም በበሽታ አምጪ ህዋሳት በመጠቃቱ ነው። ለእይታም ፍም ይመስላል (ይቀላል)። ያብጣል።


ታድያ እነኝህ አጥቂ ህዋሳት እነማን ናቸው?

አንደኛ እና ዋነኛዎቹ ቫይረሶች ናቸው። ቫይረሶች በብዛት ቶንሲልን የሚወሩ ጠላት ናቸው። ከእነኝህም መካከል ኮሮና ቫይረስ፣ አዴኖ ቫይረስ ፣ ራይኖ ቫይረስ እና ኢፒስተን ባር ቫይረስ የሚባሉት ይጠቀሱበታል።

ree

ባክቴሪያዎችስ? እነርሱም እንደ ቫይረሶች አብዝተው ባይለመዱም ፤ ቶንሲልን ይወራሉ። ከእነኝህም መሀክል በተለይ ስትሬፕቶኮከስ ፓዮጅነስ የሚባለው (Streptococcus pyogenes /Group A strep)  ዋነኛ ተጠቃሽ ነው። ከባይረሶች አንጻር የባክቴሪያ መጠኑ ቢቀንስም ፤ በመድሃኒት ህክምና ያስፈልገዋል። 


ምልክቶቹ


ታድያ ይህ ቶንሲል በተወረረ ጊዜ የሚመለከቱን ምልክቶች ያሳያል።

በግራና በቀኝ ያበጡና የቀሉ ቶንሲሎች ይታያሉ። መህል ላይ እንጥል አለ።
በግራና በቀኝ ያበጡና የቀሉ ቶንሲሎች ይታያሉ። መህል ላይ እንጥል አለ።
  • የጉሮሮ መቁሰል - ለዚህም ሲውጡ ማመም/መሰቃየት

  • ትኩሳት

  • መጥፎ የአፍ ጠረን

  • ድምጽ መታፈን

  • ጉሮሮ አከባቢ መቅላት፣ መቆጣት፣ ማበጥ 

  • አንዳንዴ መግል ያዘሉ ነጭ ነጠብጣቦች  ሊታዩ ይችላሉ። 

  • አንገት አከባቢ ያሉ ንፍፊቶች ይህን ተከትለው ሊያብጡ ይችላሉ። 

  • ህጻናት ላይ የሆድ ህመም እና ማስታወክ ሊያሳይ ይችላል። አይንም እንባ ሊይዝ/ሊሞጨሙጭ ይችላል።


ከዚህ ባሻገር የመተንፈስ ችግር፣  ከባድ የመዋጥ ችግር፣ እንዲሁም ራስ ስቶ መውደቅ ካለ ፈጽሞ አይዘግዩ። አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ያስፈልጋል።


ምናልባት ! ምናልባት! ኢንፌክሽኑ ደርጅቶ አጠገብ አከባቢ ያሉ አካላትን አስቆጥቶ ሊሆን ይችላል።

ሕክምናውም ቀላል እና ውጤታማ ነው!


  1. በአብዛኛውን ጊዜ በመደገፍ ህክምና ብቻ ሊሻሻል ይችላል። ቫይረስ ከሆነ ይህ ብቻ ሊበቃ ይችላል። ለዚህም እረፈት በማድረግ፣ ፈሳሽ አብዝቶ በመውሰድ፣ ለጉሮሮ ህመም የሚዋጡ እንክብሎች (ሎዜኝስ) በመውሰድ ፤ እንዲሁም ትኩሳት እና ህመምን የሚያስታግሱ መድሀኒቶችን በመውሰድ ሊስተካከል ይችላል። ከዚህም ባሻገር ጉሮሮ ህመም ባለ ጊዜ ፤ ፈልቶ በቀዘቀዘ የጨው ውሀ መጉመጥመጥ ይመከራል።


  2. ባክቴሪያ መሆኑ ከተረጋገጠ ወይም ከተጠረጠረ ደግሞ ፤ የባክቴሪያ መቃወሚያ መድሀኒቶችን መውሰድ ያስፈልጋል። ታድያ ግን ዶክተርን ሳያማክሩ አይውሰዱ። መድሀኒቶቹ ተጓዳኝ የአለርጂ/የአለመስማማት ምልክቶችን ሊያመጡ ይችላሉ።


በሽታው በስርአት መታከም እንዳለበት ማወቅ ይኖርብዎታል። ይህ ካልሆነ ኢንፌክሽኑ ሊስፋፋ አልያም ሊደረጅ ይችላል። ይህን ጊዜ ከአጠገብ ያሉ አካላት ሊቆጡ ይችላሉ። ቶንሲሉ አጠገብም ባለ ስፍራ መግል ክምችት ሊፈጠር ሁሉ ይችላል። በስርአት ካልታከመ ለልብ ህመም ሊዳርግ ስለሚችል እዚህ ጋር ፈጽሞ መዘናጋት የለብዎትም።


ቀዶ ጥገናስ ?


የቶንሲል ቀዶ ሕክምና
የቶንሲል ቀዶ ሕክምና

ለዚህ የቶንሲል በሽታ ግድ ካላለ በስተቀር የቀዶ ጥገና አይደረግም። ታድያ እነኝህ አስገዳጅ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?


አንደኛ ቶንሲሉ በሽታው ተደጋጋሚ መሆን አለበት። ይህ ተደጋጋሚ የሚለው በቁጥር እና በጊዜ የተገደበ ነው።


ሁለተኛው በሽታው ጠንካራ መሆን አለበት። አጠገብ ያሉ አካላት ሲጠቁ ፤ አንገት አከባቢ ተጨማሪ ኢንፌክሽን ሲፈጠር ቀዶ ጥገና ያስፈልጋል።


እንዲሁም በቶንሲል የተነሳ የአየር መወረጃ እየታፈነ በእንቅልፍ መታፈን ሲፈጠር ቀዶ ጥገና ይመረጣል።


ከዚህም ባሻገር የቶንሲል አከባቢ እጢ/ካንሰር ከተጠረጠረ ቶንሲልን መቆረጥ ይመከራል።


ሆኖም እነኝህ አስገዳጅ ሁኔታዎች እስካልተፈጠሩ ቀዶ ጥገና አይመከርም። ለምን?


በቀዶ ጥገና ቶንሲሎቹ መውጣታቸው ታካሚን ለዛ አከባቢ ኢንፌክሽን ተጋላጭ ያደርገዋል። ቀዶ ጥገናው ጋር ተያይዘው የሚኖሩ ተጓዳኝ ጉዳቶችም ሊኖሩ ይችላሉ።


ዘመናዊ የቶንሲል ቀዶ ጥገና እና ባህላዊ እንጥል መቁረጥ?


አብዛኛው ሰው እንደሚያስበው ፤ ዘመናዊ የቶንሲል ቀዶ ጥገና እንጥል መቁረጥ አይደለም።

እላይ እንደገለጽነው አካላቶቹ ስለሚለያዩ ፤ በዘመናዊ ቀዶ ጥገና የሚወጣው እንጥል ሳይሆን ቶንሲል ነው። እንጥል እራሱን የቻለ አካል ስለሆነ በዘመናዊ ቀዶ ጥገና እንጥል የሚቆረጥበት የራሱ ምክንያቶች አሉት። ዘመናዊ ቀዶ ጥገና የሚደረገውም በ ሰመመን መድሀኒት ተደርጎ ፤ ንጽህናው በተጠበቀ ስፍራ በሰለጠኑ ባለሙያዎች ስለሆነ ተጓዳኝ ጉዳቱ እጅጉን መጠነኛ ነው።

ተቆርጦ የወጣ ቶንሲል
ተቆርጦ የወጣ ቶንሲል

ባህላዊስ?


ባህላዊው ደግሞ ብዙ ጊዜ ደህንነቱ ባልተጠበቀ ቦታ በልምዱ ላይ በተመረኮዘ ልዩ ስልጠና በሌለው ግለሰብ የሚሰራ ነው። በባህላዊ የሚደረገውም ቶንሲል መቁረጥ ሳይሆን እንጥል መቁረጥ ነው።


አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ ማለት ይህ ነው።

የታመመው ቶንሲል ፤ የሚቆረጠው እንጥል። ይህ ደግሞ በህክምናው ወይም በዘመናዊ ሳይንስ በተደረጉ ጥናቶች፤ ጥቅሙ ፈጽሞ ያልተረጋገጠ ነው። እውነትም እንጥል ሲቆረጥ እንጥል ላይወርድ ይችላል። ሆኖም ግን የቶንሲል በሽታ ከመኖር ምንም አይገድበውም። ለዚህም ባህላዊው ፈጽሞ አይመከርም!


ከዚህም በላይ ባህላዊውን አሳሳቢ የሚያደርገው ነገር ቢኖር የሚካሄድበት ስፍራ እና መሳርያ ነው። የሚካሄደበት ስፍራ ከባክቴሪያ ያልጸዳ ሲሆን ፤ መሳሪያውም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ተደርጎ የማይዘጋጅ ፤ በቅርብ የሚገኝ የስለት መሳርያ ነው። ይህ ደግሞ ለዛ አከባቢ ኢንፌክሽን ፣ ለደም ውስጥ ኢንፌክሽን እንዲሁም ለከባድ ደም መፍሰስ ሊያጋልጥ ይችላል። አከባቢ ያሉ አካላት ላይ ጉዳት ሊይደርስም ይችላል። ለዚህም አይመከርም።


እጅጉን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ቀዶ ህክምናው መደረግ ያለበት ፤ ከባክቴሪያ በጸዳ አከባቢ በዘመናዊ ህክምና በሰለጠነ ባለሙያ ብቻ ነው።


አንዳንድ ወላጆች ህመሙ ባስጨነቃቸው ጊዜ ወደ ባህላዊ እንጥል ማስቆረጥ መሄዳቸው የተለመደ እውነታ ቢሆንም ፤ ከዚህ በኋላ መቆም አለበት። ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።


ጎጂ ባህላዊ ልማዶች ውስጥ በመካተቱም ባለፉት አመታት ውስጥ በመንግስት እና ባለድርሻ አካላት ትብብር እንዲቀንስ ማድረግ ተችሏል። ሆኖም ግን አሁንም ይህንን አማራጭ የሚወስዱ ወላጆች አይጠፉም። በተለይም በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ይህ ይታያል።


ለዚህም እያንዳንዱ ወላጅ ፈጽሞ ችላ ማለት የለበትም። በግንዛቤ ጉድለት ልናድናቸው ያሰብናቸውን ልጆቻችንን መጉዳት የለብንም።


ባህላዊ ማስታገሻዎችስ?

ree

አንዳንድ ከእጽዋት የሚቀመሙ መድኃኒቶች አንዳንድ ምልክቶቹን ሊያስታግስየሚችል አቅም ቢኖራቸውም እንኳን ፤ አስፈላጊውን ህክምና ከማድረግ ሊያዘገዩ ይችላሉ። ተጓዳኝ ጉዳታቸው ሆነ የህክምና መጠናቸው ስለማይታወቅ ጉዳት ሊያመጡ ይችላሉ። በዘመናዊ ህክምናም ፈጽሞ አይመከሩም።


ለዚህም ፈጽሞ ችላ አይበሉ። ልጅዎን ቶንሲል ካመመው እቤትዎ ከማቆየት የዘመናዊ ህክምና እርዳታ ይፈልጉ።


እርስዎ እንደወላጅ ምን ያድርጉ ?

  1. ግንዛቤዎን ያሻሻሉ። ስለ ቶንሲል ምልክቶች ህክምናዎች እና አላስፈላጊ ባህላዊ ስርአቶች ለይተው ይወቁ። የተሻለውን ይምረጡ ።

  2. በሀኪምዎ ትእዛዝ ብቻ ህክምና ይውሰዱ። በተለምዶ መድሀኒት መውሰድ ጠንከር ላለ ለተላመደ ባክቴሪያ ያጋልጣል።


ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ለውጥ ያምጡ !

Comments


bottom of page