የህመም ማስታገሻ እና የኩላሊት ጠንቁ
- Zebeaman Tibebu
- 3 days ago
- 3 min read
ብዙ ጊዜ ህመም ሲሰማዎ የሚወስዱት ምንድንነው?
አይቡፕሮፌን ፣ ዳይክሎፌናክ / ኢንዶሜታሲን ፣ ወይስ የትኛውን የህመም ማስታገሻ?

ብቻዎትን አይደሉም! በአለም ዙሪያ ብዙዎች ለህመም ማስታገሻ የሚጠቀሟቸው መድሀኒቶች ናቸው። በስራቸው ህመምን ያስታግሳሉ፤ ትኩሳትን ይቀንሳሉ፤ የሰውነንት መቆጣት ያረጋጋሉ። ለዚህም በፍጥነት እፎይታ ይሰጣሉ። ዋናውን በሽታ ባይሽሉም ... ህመሙን እንዳይሰማዎ ያደርጋሉ።
በፍጥነት ስለሚሰሩ፣ ርካሽ ስለሆኑ እና ብዙ ጊዜ ያለ ማዘዣ ስለሚገኙ በዓለም ዙሪያ ተወዳጅ ናቸው።
እነኝህ የህመም ማስታገሻዎች ምንድን ናቸው?
በዚህ ትምህርታዊ ጽሁፍ የምናነሳው ኤን ኤስ ኤድ( NSAIDs ) በመባል ስለሚታወቁት የህመም ማስታገሻ መድሀኒቶች ነው። እነኝህ መድሀኒቶች
ለራስ ምታት
ለጀርባ ህመም
ለትኩሳት
ለመገጣጠሚያ ወይም ለጡንቻ ህመም
ለሰውነት መቆጣት ጥቅም ላይ ይውላሉ።

እነኝህ መድሀኒቶች በብዙ አገሮች ያለ ያለ ማዘዣ የሚገዙ ሲሆኑ በዝቅተኛ ዋጋ ፈጣን እፎይታ ይሰጣሉ። ለዚህም በብዙዎች ተመራጭ ናቸው።
ከ 20 በላይ አይነት መድሀኒቶች ቢኖሩም ፤በኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት የተለመዱት አይቦፕሮፌን(Ibuprofen) ፣ ዳይክሎፌናክ (diclofenac)፣ ኢንዶሜታሲን(indomethacin) እና አስፕሪን (Aspirin)(በከፍተኛ መጠን ከተወሰደ) ናቸው።
ታድያ እነኝህ መድሃኒቶች ለአጭር ጊዜ እና በትክክል ጥቅም ላይ ሲውሉ ውጤታማ እና ለጤና ጠቃሚ ናቸው። ታድያ እነርሱን በከፍተኛ መጠን ወይም በተደጋጋሚ ሁኔታ መጠቀም አደጋ አለው። በዶክተር ትእዛዝ እንደ አስፈላጊነቱ ታዞ ካልሆነ ፤ በየዕለቱ እነርሱን መጠቀም አይመከርም።
ኩላሊት ላይ ለምን ጉዳት ይደርሳል? (ማወቅ ከፈለጉ )

እነኝህ መድሀኒቶች ከኩላሊት ጉዳት ባሻገር ፣ የጨጓራ ህመም ፣ የልብ ድካም ፣ የደም ግፊት፣ ስትሮክ ሊያባብሱ ይችላሉ። በእርግዝና ጊዜም እነርሱን ከመውሰድዎ በፊት ዶክተርዎን ማማከር ይኖብዎታል። ከዚህም መሀል ለይተን የምናተኩረው ኩላሊት ላይ ስለሚያደርሱት ጉዳት ይሆናል።
እነኝህ መድሀኒቶች ህመምን የሚያስታግሱት ፕሮስታግላንዲን የሚባለውን ውህድ ስራ በመቀነስ/በማገድ ነው። ይህ ውህድ ደግሞ ኩላሊት ጋር ላለው የደም ዝውውር አስፈላጊ ነው። ደምስሮች በአግባቡ ተክፍተው ደም ዝውውር እንዲኖር ያደርጋል። ታድያ እነኝህን መድሀኒቶች በብዛት ያለ ገደብ ሲወስዱ ፤ ይህን ውህድ በከፍተኛ ሁኔታ ይቃወሙታል። ለዚህም ኩላሊት ጋር ያለው የደም ዝውውር ይዳከማል። ይህም የኩላሊትን ስራ ያሰናክለዋል። ይህም ጉዳትን ያመጣል።
ጉዳቱ መድሀኒቶቹን በወሰዱ በሰአታት ውስጥ ሊያጋጥም ይችላል።
ከዚህም ባሻገር መድሀኒቶቹ በቀጥታ የኩላሊት ህዋሳትን ሊጎዱ ይችላሉ። ለኩላሊት ህዋሳት መርዛማነት ባህሪ አላቸው። ለዚህም የኩላሊት ህዋሳት ስራቸውን በአግባቡ መስራት እንዲሳናቸው ያደርጋሉ።
ለዚህም ረዥም ጊዜ የሚጠቀሙ ታካሚዎችን ፤ ስር የሰደደ የኩላሊት በሽታ (CKD) እሱንም ተከትሎ የኩላሊት ድክመት ያጋጥማል።
ምልክቶቹስ ምንድን ናቸው?
ኩላሊት ላይ ያለው ጉዳት ከፍተኛ እስካልሆነ ድረስ መጀመሪያ ላይ ምንም ምልክቶችን አያሳይም። ይህም አደገኛ ያደርገዋል። ሆኖም ግን እነኝህን ምልክቶች ካዩ ያስተውሉ፡

የእግሮች፣ የእግሮች ወይም የፊት እብጠት
የሽንት መጠን መቀነስ
ሽንት መቅላት/መጥቆር/ደም መቀላቀል
ድካም
ማቅለሽለሽ
በድንገተኛ የደም ግፊት መጨመር
የጀርባ ህመም (ኩላሊት ያለበት አከባቢ)
ጉዳቱ እጅጉን ከፍ ካለ
የደረት ህመም
ትንፋሽ ማጠር
ግራ መጋባት
እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት
ኮማ ሊያመጣ ይችላል።
ቶሎ ካልታከመ አጣዳፊ የኩላሊት ድክመት ሊያመጣ አልያም ዘላቂ የኩላሊት ጉዳት ሊያመጣ ይችላል። ይህን ጊዜም የኩላሊት እጥበት ህክምና ሊያስፈልግ ይችላል። አንዳንዴም እስከሞት ሊያደርስ ይችላል።
ማን በይበልጥ ይጋለጣል?
እነኝህን የህመም ማስታገሻዎች ተከትሎ ለሚመጣ የኩላሊት ጉዳት ተጋላጭነታቸው ለሚከተሉት ከፍ ያለ ነው።
ከ 60 ዓመት በላይ የሆኑ አዋቂዎች
የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች
የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች
የኩላሊት ችግር ያለበት ማንኛውም ሰው
ዳይሬቲክስ (የሚያሸና ክኒን) የሚወስዱ ታካሚዎች
እርጉዝ ሴቶች
እንዲሁም የሰውነታቸው ውሀ ያነሰ ሰዎችም ተጋላጭነታቸው ከፍ ይላል። ትውከት ያለባቸው ፣ ተቅማጥ ያለባቸው ፣ ከፍተኛ የአካል እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ፣ ትኩሳት ያለባቸውና፣ እጅጉን የሚያልብ ሞቃታማ ስፍራ የሚኖሩ ሰዎች የአካላቸው የውሀ መጠን ስለሚመናመን ተጋላጭነታቸው ይጨምራል። ለዚህም ውሀ አብዝተው እንዲጠጡ ይመከራል።
የኢትዮጵያስ እውነታ ምን ይመስላል?

በኢትዮጵያም እነዚህ መድኃኒቶች ብዙውን ጊዜ ያለ ማዘዣ ጥቅም ላይ ይውላሉ። ለራስ ምታት፣ ለጀርባ ህመም፣ ለትኩሳት፣ ለመገጣጠሚያ ህመም፣ ወ.ዘ.ተ... ከፋርማሲ ተገዝተው በብዙዎች ይወሰዳሉ። ይህም ብዙዎችን ለኩላሊት በሽታ እያጋለጠ ይገኛል። በዚህ ዙሪያ ላይ ከተደረጉ ጥናቶች ውስጥ ፡
በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የተደረገ አንድ ጥናት እነኝህን ህመም ማስታገሻ የተጠቀሙ ታካሚዎች ስር የሰደደ የኩላሊት ህመም የማጋጠም እድላቸው በ 2.4 እጥፍ ጨምሯል።
በመላው ኢትዮጵያ የተደረገ የዳሰሳ ጥናት በበኩሉ ደግሞ ፤ በአጭር ጊዜ ለሚያጋጥም ለኩላሊት ህመም/ጉዳት እነኝህ የህመም ማስታገሻዎች አጋላጭ መሆናቸውን ገልጿል።
ይህም ጥቂት የማይባል የማህበረሰብ ክፍልን ለተደበቀ የኩላሊት ጉዳት ከፍተኛ ተጋላጭነት ላይ ይጥለዋል።
ምን ማድረግ አለብዎ?

ለራስዎ ህመም ማስታገሻ አይዘዙ። እጅጉን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ይጠቀሙ። ግድ ካልሆነ በቀር ደጋግመው በየቀኑ አይጠቀሙ።
ሰውነትዎ ውሀ በሚያንስበት ጊዜ ባይወስዱ ይመከራል። በሞቃታማ ስፍራ እየሰሩ ከሆነ፣ ተቅማጥ፣ ማስታወክ ወይም ትኩሳት ካለብዎ ይጠንቀቁ። ውሀ አብዝተው ይጠጡ።
የደም ግፊት ወይም የስኳር በሽታ ካለብዎ በመጀመሪያ ባለሙያ ያማክሩ።
ከአንድ በላይ ህመመ ማስታገሻዎችን አይደባልቁ። ይህ ጉዳት የማጋጠም እድልን ይጨምራል።
በቂ ውሃ ይጠጡ ። ኩላሊት ለመስራት እና እራሳቸውን ለመጠበቅ ፈሳሽ ያስፈልጋቸዋል።
ሌሎች አይነት የህመም ማስተገሻዎችን አልፎ አልፎ ይውሰዱ።
የኩላሊትዎን ጤና ያረጋግጡ። መደበኛ ምርመራ ያድርጉ።
ያስተውሉ!
ህመም ማስታገሻዎች ፍቱን የሚሆኑት በትክክል ጥቅም ላይ ሲውሉ ነው።
ከህመም ማስታገሻ ጋር የተያያዙ የኩላሊት ጉዳቶች ሙሉ በሙሉ መከላከል ይቻላል።
በዝምታ ኩላሊትዎ ሳይደክም ዛሬውኑ እርምጃ ይውሰዱ።





Comments