ሰሞነኛው ጉንፋን ለምን መጣ?
- Zebeaman Tibebu
- Oct 26
- 5 min read
አንድ ቀን ምሽት ላይ የሁለት አመቱ ህጻኑን እጅጉን አመመው። ሰሞኑን እንደሳል እያደረገው የቆየ ቢሆንም ፤ አብዝቶ ያተኩስ ጀመር። አተነፋፈሱ ፈጥኗል። ድክምክም ብሎታል። ትኩሳት አይሎበታል። ካመመው የተወሰኑ ቀናት ቢቆጠሩም ፤ ቤተሰብ ይሻለዋል ብሎ አስቦ ነበር። ሲያይልበት ቤተሰብ ጨነቃቸው። ከቀናት በፊት ፋርማሲ አማክረው የወሰዱት የህመም ማስታገሻ ፤ ትኩሳቱንም ህመሙንም አልተቆጣጠረም።
ምን ያድርጉ? ጨነቃቸው!
ሆስፒታል ይዘው ለመሄድ አሰቡ..
ይህ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ባሉት ከተሞች የሚስተዋል ታሪክ መሆን ከጀመረ ሳምንታት ተቆጥረዋል። ህመሙ ሲጀምር የወሰዱት መድሀኒት አልሰራ ብሎአቸው ክሊኒክ እየጎበኙ ያሉ ጥቂቶች አይደሉም።
እንደ ተራ ጉንፋን አስበውት የሳንባ ምች የሆነባቸውም አሉ።
ታድያ ግን ለምን?
ለምንስ ጨመረ?
ለምንስ መድሀኒቶቹ እንደሚፈለገው እየሰሩ አይደለም?
መረጃዎች ምን ይላሉ?'
በጉንፋን ዙሪያ ያለ መረጃ የተሟላም ባይሆን ፤ሀገራችን ኢትዮጵያ ጉንፋንን ከሚያመጡ ቫይረሶች መሀል ሀይለኛው ኢንፍሉዌንዛን መከታተያ ስርአት ካበጀች አስርት አመታት ተቆጥረዋል። እነኝህም መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ፡

በፈረንጆች ከ 2009-2015 ባለው ጊዜ ወደ 4,800 የሚጠጉ ሰዎች ጠንከር ያለ የትንፋሽ ኢንፌክሽን የታመሙ ሲሆን። ከእነኝህም መሀል አንድ አምስተኛ የሚጠጉት (988 ሰዎች) የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል። ከኢንፍሉዌንዛ ቫይረሶችም መሀል በተለይ ኢንፍሉዌንዛ ኤ( A(H3N2)፣ A(H1N1) ፣ pdm2009) እና ኢንፍሉዌንዛ ቢ (influenza B) በብዛት ታይተዋል።
በፈረንጆች ከጃንዋሪ 2021 እስከ ታህሳስ 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ 18,724 ጠንከር ያለ የትንፋሽ ቧንቧ ኢንፌክሽን ያለባቸው ሰዎች ሲገኙ ከእነኝህም ውስጥ በ1,648 ውስጥ ኢንፍሉዌንዛ ተገኝቷል።
እዚህ ላይ ደግሞ የኮቪድን እና የሌሎችን ቁጥር ብንጨምር ፤ መጠኑ እጅጉን ያድጋል። ስለኮቪድ መጠን እና ባህሪው በብዛት ስለሚታወቅ መዘርዘሩ አስፈላጊ አይደለም።
ሁሉም ጉንፋን መሰል በሽታ ኢንፍሉዌንዛ አለመሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል። ጉንፋንን የሚያመጡ ብዙ አይነት ቫይረሶች ሲኖሩ ከእነኝህ ውስጥ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ፣ የ ሪስፓይራቶሪ ሲንሲታል ቫይረስ ፣ አዴኖ ቫይረስ እና ኮሮና ቫይረስ በዋነኝነት በኢትዮጵያ ይጠቀሳሉ።
ሆኖም ግን አሁን የምናየው የጉንፋን ስርጭት መጨመር በየትኛው ቫይረስ የመጣ መሆኑን አልያስ በባክቴሪያ መምጣቱን ለማረጋገጥ የላብራቶሪ ምርመራ ያስፈልጋል።
ታድያ ይህ ለምን በ2018 ጸደይ ወቅት ላይ አጋጠመ?
ይህ አጭር ምላሽ የለውም። አሁን የምናስተውለውን የጉንፋን መጠን መጨመር በሚከተሉት ምክንያት ሊሆን ይችላል።
ወቅታዊነት፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ወቅትን ጠብቀው የሚመጡ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽኖች / ጉንፋን ህመሞች የተለመዱ ናቸው። ለምሳሌ ክረምት ወቅትን ተከትሎ በሚኖረው የአየር ሁኔታ ለውጥ ተከትሎ ጉንፋን መስፋፋት እንደተለመደው ፤ ጸደይ ወቅት ላይም በተለይ ወደ ህዳር አቅራቢያ የጉንፋን አይነት በሽታዎች ስርጭት ይጨምራል። ይህም ከወቅቱ ጋር በተያያዙ የከባቢ አየር ለውጦች ጋር ግንኙነት አለው።

የትምህርት ቤቶች መከፈት ፡ ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ ፤ በትንፋሽ የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች በተማሪዎች መሀል በብዛት ይስፋፋሉ። ይህም አንድ ተማሪ መያዙን ተከትሎ ሙሉ ክፍል አስተማሪን ጨምሮ ስለሚያዝ ነው። እነኝህ የታመሙትም ህጻናት በሽታውን ወደቤት ይዘው ይመጣሉ። ቤተሰብም ይታመማል።
የህዝብ ማመላለሻዎች እና የ ህዝብ ስፍራዎች መጨናነቅ። የተማሪን እንቅስቃሴን ተከትሎ የትምህርትቤት በተከፈተባቸው የመጀመሪያ ወራት የህዝብ ማመላለሻዎች ከወትሮ በበለጠ መጠን ይጨናነቃሉ። እዚህ ላይ ደግሞ አሁን ሀገራችን በምትከተለው ፖሊሲ የተነሳ አውቶብሶች እና ሌሎች በብዛት ህዝብን የሚይዙ ማመላለሻዎች ዋነኛ የትራንስፖርት አማራጮች እየሆኑ ይገኛሉ። ይህምም ለቫይረሱ ስርጭት ተጨማሪ በሮችን ይከፍታል። አንድ የታመመ ሰው ከገባ ሙሉ አውቶብስ ሰው በሙሉ ለጉንፋን ቫይረስ/ባክቴሪያ ይጋለጣል።

ከኮቪድ በኋላ ለውጦችን መጥተዋል። ተዘናግተናል። ማስኮች/ጭምብሎች ወልቀዋል። እጆቹን በሳኒታይዘር የሚያጸዳ ሰው ዝቅተኛ ነው። ይህም ተጋላጭነትን ይጨምራል።
ለዚህም የዚህ ጉንፋን መስፋፋት የአንድ ነገር ውጤት ብቻ አይደለም። ስርጭቱን የሚያስፋፉ ፣ አቅሙን የሚያደረጉ ብዙ አጋላጭ ምክንያቶች አሉ። ይህም የበለጠ ተጋላጭነት ይፈጥራል።
ጉንፋኑስ ለምን ትንሽ ጠንከር አለ?
ጉንፋን በሽታ የላይኛውን የትንፋሽ ቧንቧ በሚያጠቁ በሽታ አምጪ ተህዋሳት የሚከሰት ኢንፌክሽን ነው። የኢንፌክሽን በሽታ መጠንከር ደግሞ በ ሁለት ነገር ላይ ይመደባል።
የበሽታ መከላከያ አቅም መዳከም። የአንድ ሰው የበሽታ መከላከል አቅም በአኗኗሩ ፣ በአበላሉ እና ባለበት ጤና ደረጃ ይመደባል። ከዚህም ባሻገር የምናደርጋቸው ባህሪያት ያለንን የበሽታ መከላከል አቅም ይወስናሉ። እንደማህበረሰብ ስናስብ በኮቪድ ሰሞን አድርገነው የነበረው ፍጹም ጥንቃቄ ፤ የበሽታ መከላከያ ስርአታችንን አግዞታል። ማገዙ መልካም ሆኖ ሳለ ይህ ጥንቃቄ የበሽታ መከላከያ ህዋሳቶቻችን እንዲዘናጉ አድርጓቸዋል። በህክምናው ይህ ኢሚዩኒቲ ጋፕ(Immunity Gap) ይባላል። ታድያ ይህን ጊዜ ለጉንፋን መሰል በሽታ ስንጋለጥ ፤ በሽታው ይደረጃል። ይህ ደግሞ ህዝቡን በይበልጥ ተጋላጭ ያደርገዋል።

ሁለተኛ ደግሞ የቫይረሶቹ አቅም መደርጀት ነው። ጠንከር ያለ አቅም ያላቸው ቫይረሶች ስንታመመ ፤ በሽታውም ከበድ ያለ ይሆናል። ከዚህም ባሻገር በአንዴ ከአንድ በላይ በሆኑ ቫይረሶች ልንታመም እንችላለን። በፈረንጆቹ 2021 (ከ አራት አመት በፊት) የተደረገ ጥናት እንደሚያመላክተው ከሆነ ፤ በወቅቱ በኢትዮጵያ ከተገኙ 4989 ጉንፋን መሰል ታማሚዎች ውስጥ 9.2 በመቶ የሚሆኑት ከአንድ በላይ ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል። በሌላ በኩል ከቫይረስ ኢንፌክሽኑ ባሻገር ተደራቢ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ሊኖር ይችላል። ይህም ደግሞ ሰውነታችን በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ በሽታን እየተዋጋ ስለሆነ ፤ በሽታው ሊጠነክር ይችላል። የባክቴሪያ ኢንፌክሽን መኖሩን በባለሙያ በቀላሉ መለየት የሚቻል ሲሆን ፤ ከአመላካች ምልክቶቹ መሀል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።

ከባድ ትኩሳት (ተመላልሶ የሚመጣ አልያም የማይሄድ ሊሆን ይችላል)
ከአፍንጫ የሚወጣው ፈሳሽ ቢጫ መሆን (ቢጫ ንፍጥ)
የአተነፋፈስ ለውጥ/ትንፋሽ
ከባድ ሳል እየባሰ የሚመጣ
እንዲሁም ከባድ ድካም ይሆናሉ።
በሁለቱ መሀል በደንብ ለመለየት ባለሙያ ያማክሩ።
እዚህ ጋር አንድ መጨመር እና ማስተዋል ያለብን ጉንፋኑን ጠንካራ ያደረገው ነገር ቢኖር፡
አለአግባብ ያለ ዶክተር ምክር የባክቴሪያ መቃወሚያ መድሀኒቶች ከፋርማሲ እየተወሰዱ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ በሽታውን የተላመዱ ፤ አቅማቸው የደረጁ የኢንፌክሽን አምጪ ተህዋሳት እንዲስፋፉ እድል ፈጥሯል። ለዚህም መድሀኒት ወስደው እንኳን ላይሻልዎት ይችላል። ለምን? መድሀኒቱን ለምዶታል። ባክቴሪያው አሁን ጠንካራ ነው።
ይህ ለእርስዎ እና ለሚወዷቸው ሰዎች ምን ማለት ነው?
ይህ ማለት እቤትዎ ቁጭ ብለው ጉንፋን ሊይዝዎ ይችላል። የቤተሰብ አባልዎ ወደ ቤት ሲመጣ ከገባበት የህዝብ ማመላለሻ ፣ አልያም ከትምህርትቤት ይዞ ሊመጣ ይችላል። የመያዝ እድልዎ ባሉበት የጤና ሁኔታ ላይ ይመሰረታል። የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ የሆነ እና በሽታው የሚጠነክርባቸው የሚከተሉት ናቸው፡

ሰውነታቸው የተዳከመ ሰዎች
ተደራቢ ስር የሰደደ ህመም ካላባቸው
የበሽታ መከላከያ አቅም የሚያዳክም ህመም ያለባቸው። ለምሳሌ ፡ ኤችአይቪ ያለባቸው ፣ ካንሰር ያለባቸው፣ ወ.ዘ.ተ...
እርጉዝ ሴቶች
እድሜያቸው የገፋ አዛውንቶች
ህጻናቶች ፣ ወ.ዘ.ተ... ናቸው።
ለዚህም እነኝህ የማህበረሰብ ክፍሎች ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ጥንቃቄው ለእነኝህ የማህበረሰብ ክፍሎች ይብለጥ እንጂ ፤ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ለጤናው ቦታ መስጠት ይኖርበታል። ምልክቶቹን ለይተው ማወቅ ይኖርብዎታል። በተለይ በተለይ.... የሚከተሉትን ምልክቶች ካዩ በአፋጣኝ የህክምና እርዳታ ይፈልጉ። የበሽታው መጠንከርን ያመላክታሉና ያስተውሏቸው!
የመተንፈስ ችግር ካለ/ ትንፋሽ ማጠር ካለ
የደረት ሕመም ካለ
ከፍተኛ ትኩሳት ካለ (ከ 3 ቀን በላይ ከቆየ ፣ ከ 38 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ከሆነ፣ ተመላልሶ የሚመጣ ከሆነ)
ግራ መጋባት ወይም ባህሪ ለውጥ ካለ
የማዞር ስሜት ካለ
ከባድ ድካም ካመጣ ፣ እንቅልፍ እንቅልፍ አብዝቶ ካለ
ምልክቶቹ እጅጉን እየባሱ ከመጡ
የምግብ ፍላጎት ፈጽሞ ከጠፋ
እጅጉን ያስተውሉ! የሕክምና እርዳታ ይፈልጉ። ሀኪም ያማክሩ።
ማድረግ ያለብዎት ነገሮች
የሚከተሉትን ቀላል እና ተጨባጭ እርምጃዎችን ያድርጉ። በጉንፋን ወቅት እንደ የሚከተሉትን መመሪያ ህግ አድርገው ይውሰዱ።
ለመከላከል
በአከባቢዎ የኢንፍሉዌንዛ ክትባት እየተሰጠ ከሆነ ፣ እድሜዎት ከፈቀደ ይውሰዱ። ክትባቱ በሽታው እንዳይከብድ፣ የሳንባ ምች አልያም የደም ኢንፌክሽን እንዳያመጣ ይከላከላል።

ሥር የሰደደ የጤና ችግር ካለብዎ በህክምና ይቆጣጠሩ። አስም፣ የስኳር በሽታ፣ የልብ ሕመም ካለብዎ ወይም እርጉዝ ከሆኑ ቶሎ የጤና ባለሙያ ያማክሩ። በህኪምዎ ትእዛዝ መድሃኒቶችን ይውሰዱ። በሽታዎን ይቆጣጠሩ። እግዝናዎ ጤናማ ይሁን። ምልክቶቹን ይወቁ። አሳሳቢ ምልክቶችን ያስተውሉ።
ከታመሙ

በሚታመሙበት ጊዜ ከቤትዎ ይቆዩ። ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ሳል፣ የሰውነት ህመም ሲጀምርዎ እረፍት ያድርጉ። ፈሳሽ በደንብ ይጠጡ። ምግብ በስርአት ይብሉ። ቪታሚን ሲ ያለባቸው ፍራፍሬዎች ምግቦችዎ ውስጥ ይደባልቁ። የበሽታ መከላከያ ስርአትዎን ያጠናክራሉና።
ትኩሳት ካለብዎ ፤ ልብስ አይደራርቡ። የረጠበ ፎጣ አልያም ውሀ ሰውነትዎ ላይ ያድርጉ። የትኩሳት ማስታገሻ መድሀኒቶችንም መውሰድ ይችላሉ።
ጥሩ የአተነፋፈስ ምግባር ይኑርዎ ። ሲያስሉ አፍዎን በክርንዎ አልያም በእጅዎ ይከልሉ። በሶፍት አልያም በማህረብ ይናፈጡ። እጅዎን አዘውትረው ይታጠቡ። ሳኒታይዘር አልያም አልኮል ያለበት መታጠቢያ ቢጠቀሙ ይመረጣል።
ቤተሰብዎን እና በዙሪያዎ ያሉ ሰዎችን ይጠብቁ። ላለማስተላለፍ ራስዎን ያግልሉ። በተዘጉ ክፍሎች ውስጥ ሲቆዩ /ከሰዎች ጋር ሲሆኑ ማስክ ወይም ጭምብል ያድርጉ። በተለይ ተጋላጭነታቸው ከፍ ላለ ሰዎች እጅጉን ይጠንቀቁ።
በሽታው እስኪደረጅ አይጠብቁ። ቀደም ብለው የጤና ባለሙያ እንክብካቤን ይፈልጉ። ቀድመው እርምጃ ይውሰዱ።
ምን ማድረግ የለብዎም?
እነኝህን ባያደርጉ ይመከራል።
"ጉንፋን ብቻ ነው" ብለው በማሰብ ምልክቶችን ችላ አይበሉ። በተለይ አሳሳቢ ምልክቶቹን። ከሚያስቡት በላይ ከባድ ሊሆን ይችላል።
ብዙ ጊዜ በቫይረስ ስለሚመጣ የባክቴሪያ መቃወሚያ አይውሰዱ። ይህ በተላመደ ጠንካራ ባክቴሪያ እንዲታመሙ ያደርግዎታል። በሽታ ማስታገሻዎችን ብቻ ይጠቀሙ። ከፋርማሲም ቢሆን ፈጽሞ ያለ ሀኪም ትእዛዝ መድሀኒት አይውሰዱ።
ብርድ ብርድ ሲለው እንዲሞቀው ልብስ አይደራርቡ። እንደውም ታማሚው ትኩሳት ሊኖርበት ይችላልና ፤ የልብስ መጠን ይቀንሱ።
ተአምራዊ ፈውሶች ብለው ማንኛውንም ባህላዊ መድሀኒቶች አይውሰዱ። በጤናዎ ከመቆመር በህክምና የተረጋገጠ ጥቅም ያላቸውን እርምጃዎችን ብቻ ይውሰዱ።
የመጨረሻ ቃል
ጉንፋን በአሁኑ ወቅት በመዲናችን ተስፋፍቷል። ከህጻን እስከ አዋቂ እየታመመ ነው። ለዚህም ምልክቶቹን ያስተውሉ። ሀኪምዎን አማክረው ፤ መድሀኒቶችን ይውሰዱ። ላለማስተላለፍ ጥንቃቄ ያድርጉ። ለጤናዎ ቦታ ይስጡ።
2





Comments