የጨረር አይን ህክምና ፈዋሽነት ከምን እስከ ምን?
- Zebeaman Tibebu
- Oct 13
- 5 min read
ከፊልም የወጡ የሚመስሉ የሚመስሉ ብዙ የህክምና ግኝቶችን በዘመናችን ለማየት ታድለናል።
ሰንሰማቸው “እውነት ነውን?” ያስባሉ ግኝቶች ሰራ ላይ ከመዋላቸውም አልፎ ተርፎ እንደኛ ባሉት ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ሃገራቶች ተስፋፍተው ማየታችን ይበል የሚያስብል ነው።
ሆኖም ግን አንዳንዶቹ ከእውነታ በራቀ መልኩ ተጋነው ሲቀርቡ ማየትም የተለመደ ነው። ይህ ታድያ የህክምና ግኝቶች ላይ ሲሆን ጉዳት ሊኖረው ይችላል።

በዚህ መልኩ ከሚቀርቡ ግኝቶች ውስጥ አንዱ ጨረርን በመጠቀም የሚደረግ የአይን ህክምና ነው። ብዙዎችም ይህንን ህክምና እንደ ተአምር አድርገው ይወስዱታል።
እርግጥም ብርሀንን ተጠቅሞ የአይንን ጤና በመመለሱ አስደማሚ ግኝት ቢያደርገውም ፤ በአንዳንዶች ሁሉን የአይን ህመም እንደሚፈውስ ምትሀታዊ ህክምና ተደርጎ መወሰዱ ግን አሳሳች ነው።
እርስዎም በበኩልዎ ምናልባት አይተው ወይም ሰምተው ይሆናል። ይህ ህክምና የሚሰጡ ተቋማትም ምናልባት አግነው አቅርበውት ፤ ተመልካቾችም እንደ ተአምር ወስደውት ይሆናል። ይህ ደግሞ ማስታወቂያ ነው።
የህክምና እውነታ ግን አይደለም።
ይህ የኢትዮጵያ እውነታ ብቻ አይደለም። በአለም ዙሪያ ራሱ ባለፉት አመታት የሚደረጉ ማስተዋወቂያዎች በማህበረሰቡ ዘንድ ከእውነታ የራቀ ግምት እንዲኖረው አድርገዋል።
አንዳንድ ክሊኒኮች በፍጥነት የእይታ መመለስን ቃል ሲገቡ ፤ ሊሎች በዘላቂነት ከመነጽር ነጻ መሆንን በተስፋ ይሰጣሉ። ይህ የሚያድናቸው ታካሚዎች ቢኖሩም ፤ ለብዙዎች ግን ቀቢጸ ተስፋ ሊሆን ይችላል።
በዚህ ሁሉ ግርግር መሀል ፤ አንድ የምይካድ እውነታ አለ።
የአይን የጨረር ህክምና የሚደነቅ ፤ አመርቂ ውጤት ያሳየ ምርጥ የዘመናችን ህክምና ነው። ሆኖም ግን እንደማንኛውም ህክምና አቅሙ የተገደበ እንጂ ፤ ፈጽሞ ተአምራዊ አይደለም።
ስለ ሌዘር ህክምና በጥልቅ እናንሳ
የሌዘር ህክምና ምንድነው?
የሌዘር ህክምና የብርሀን ጨረርን የሚጠቀም የህክምና አማራጭ ነው። የእንግሊዘኛ ስሙም ምህጻረ ቃል ሲሆን ፤ በግርድፉ ሲተነተን አቅሙ የጎለበተ የብርሀን ጨረር (LASER ፡Light Amplification by Stimulated Emission of Radiation ) ህክምና ነው። ይህንን ስያሜ ያገኘው በአስራሩ ላይ ተመስርቶ ነው። የሚሰራውም የብርሀንን ሞገድ አቀናጅቶ ፣ መጥኖና አጠናክሮ በአንድ አቅጣጫ መትሮ በመልቀቅ ነው። ብርሀኑም በተመራው መሰረት ረድፉን ጠብቆ ከታለመበት ስፍራ ያርፋል። የብርሀን ሞገዱ ያረፈበት አከባቢም ፤ እንደጨረሩ አይነት የሚጠበቀውን ለውጥ ያመጣል።

በህጻንነት ምብራቅ/ሌንስ ይዞ ወረቀት እያቃጠለ ላደገ የዚህ ጨረር አሰራር መረዳት ላይክብድ ይችላል።
ይህ ተሰብስቦ ተመጥኖ የሚለቀቅ ጨረር ከህክምና ባሻገር ዳይመንድን ለመቁረጥና መንኮራኩሮችን ለመጠንገም ይውላል። በህክምናም ተመሳሳይ አቅም ያለው ጨረር ባይሆንም ፤ ይህ የሌዘር ህክምና ብዙ ጠቀሜታ አለው።
በህክምና ዘርፍም ለተለያዩ ችግሮችን ለማከም ጥቅም ላይ ይውላል። በአይንም ዘንድ እይታን የማስተካከል እንዲሁም እይታን የማጥራት አቅም አሳይቷል።
ታድያ ግን ለሁሉም የእይታ ችግሮች መፍትሔ አይደለም።
ለአይን ህክምና የሚውሉ የሌዘር ህክምና አይነቶች

ለአይን ህክምና የሚውሉ የሌዘር ህክምና አይነቶች ውስጥ አራቱን እንይ። እነኝህም
የአይን የፊት መስታወት የሆነ
ውን ኮርኒያን (cornea) ለማስተካከል ጥቅም ላይ የሚውለው ኤክሳይመር (Excimer) የ ሌዘር ህክምና ፤
የአይን ግርዶሽ/ሞራ ቀዶ ጥገና ከተካሄደ በኋላ የሚደረገው የ ዋያኤጂ (YAG laser) የጨረር ህክምና ፤
የስኳር ህመምን ተከትሎ የሚመጣው የአይን ጥቃቅን ደምስሮች መድማት እና መጎዳትን የሚያክመው አርጎን ሊዜር (Argon Laser) ህክምና እንዲሁም
በአይን ውስጥ ያለ ግፊትን ለመቀነስ (ግላኮማን ለማከም) የምንጠቀመው ዳዮድ ሌዘር (diode laser) ህክምና ናቸው።
ታድያ እነኝህን የጨረር ህክምና አማራጮች በመጠቀም ፤ ለተለያዩ የአይን በሽታዎች መፍትሔ መስጠት ተችሏል።
የአይን የጨረር ህክምና የሚሰጠው የህክምና ጥቅሞች ጥቂቶቹ
ኮርንያ ጋር በተያያዘ የሚመጡ እይታ ችግሮችን ማስተካከል
ይህ ህክምና የአይን ፊት መስታወት (ኮርንያን) ቅርጽ በማስተካከል ፤ ብርሃን ተመጥኖ ሬቲና ላይ እንዲያልፍ በማድረግ እይታን ያስተካክላል። ለዚህም የቅርብ ርቀት እና ሩቅ ርቀት እይታ ችግሮች ያለባቸውን ታካሚዎች የአንጸባራቂው ኮርኒያን ቅርጽ በማስተካከል ሊያክም ይችላል። lለዚህም ይህንን ጨረር መሰረት ያደረጉት እንደ ላሲክ (LASIK) እና ፒአርኬ (PRK) አይነት ህክምናዎች ተጠቅሽ ናቸው። ህክምናው ደቂቃዎች የሚፈጅ ፤ ህመም የሌለው ዘላቂ የህክምና አማራጭ ነው። ሆኖም ግን ይህ ህክምና በኮርንያ ቅርጽ እይታቸው ለተስተጓጎለ ታካሚዎች ብቻ የሚሆን ነው።

ያስተውሉ !
ኮርንያ በጣም ከሳሳ ፣
ተለዋዋጭ እይታ ካለ
እንዲሁም የአይን ድርቀት ካለ፤
ይህ ህክምና ፈጽሞ አይመከርም። ህክምናው ከተደረገ ግን አይን ይብሱኑ ጉዳት ሊያጋጥመው ይችላል።
ግላኮማ ለመቆጣጠር ይረዳል።
የአይን ግላኮማ በሽታ የሚባለው ፤ የአይን ውስጥ ግፊት ሲጨምር ነው። የዚህም ግፊት መጨመር ፤ የእይታ ነርቭ የሆነውን የኦፕቲክ ነርቭ ይጫነዋል። ጫና ያደረበትም የኦፕቲክ ነርቭ ስራውን በስርአት መስራት ስለሚሳነው፤ እይታ ችግር ይፈጠራል። ግላኮማ በሽታ ካለብዎ ፤ የዐይን ግፊትዎ ከፍተኛ ነው። ይህም ግፊት መጨመር ደግሞ የእይታ ዋነኛ ነርቭ ኦፕቲክ ነርቭን ይጫነዋል። የሚመግቡትንም ጥቃቅን ደምስሮች ያፍናል። ያለ ህክምና እርዳታ ይህ ነርቭ ሊሞት እይታ ሊጠፋ ይችላል።
ታድያ ይህንን ግፊት ለመቀነስ የሌዘር ህክምናን በመጠቀም ፤ የአይን ውስጥ ግፊትን ማስተንፈስ ይችላል። ጨረሩ የአይን ፈሳሽ መንሸራሸር እንዲችል ቱቦ ይከፍትለታል። ይህም ግፊቱን ለመቆጣጠር ያስችለዋል።

እዚህ ጋር ያስተውሉ ፤ ግፊቱን መቆጣጠር እንጂ ግላኮማ ፈጽሞ መፈወስ አይደለም።
ያለ ከበድ ያለ ቀዶ ጥገና ራሱ ይህንን ግፊት መቀንስ መቻሉ እጅጉን አስደሳች ዜና ነው።
ከስኳር ጋር ተያይዞ ለሚመጣ የዕይታ ችግር አማራጭ መፍትሔ ነው።
ስኳር ህመም ስር ሲሰድ ጥቃቅን ደም ስሮች ላይ ጉዳት ያደርሳል። ታድያ ከሚጎዱ ጥቃቅን ደም ስሮች ውስጥ አይን ጀርባ ሬቲና ጋር ያሉት ደምስሮች አንዶቹ ናቸው። እነኝህ ደምስሮች በሚደርስባቸው ጉዳት ይደማሉ ፣ ይቀደዳሉ /ይሰነጠቃሉ ። ይህም ታድያ እየጨመረ ሲመጣ እይታ ላይ ችግር ይፈጥራል። ደም ፍሰቱም ከፍ ያለ ከሆነ ሬቲናን ከስሩ ነጥሎ እይታን ሊያቋርጥ ይችላል።
ታድይ ይህ የጨረር ህክምና የደምስሮቹን ግድግዳ በመጠገን ፤እንዳይደሙ ይከላከላል። ይህንን ለስኳር ታማሚዎች ዘላቂ ጉዳት ከማጋጠሙ በፊት ይከላከላል።

እዚህም ጋር ያስተውሉ ፤ የተጎዱ /የተቀደዱ ደምስሮችን ጠገናቸው እንጂ ፤
ይህ የጨረር ህክምና ስኳር በሽታን ሆነ ከሱ ጋር ተያይዘው ያሉ ሌሎች ጉዳቶችን አይለውጥም።
ሆኖም ግን ይህ የረቀቀ ህክምና በአለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከዐይነ ስውርነት ታድጓል።
ከሞራ መግፈፍ(cataract Surgery) ቀዶ ጥገና በኋላ
ሞራ አይናቸውን ለጋረዳቸው ታካሚዎች የሞራ መግፈፍ በቀዶ ጥገና ተድርጎም እንኳንድ ከሌንስ ጀርባ ጉም አይነት ምልክት ሊኖር ይችላል። ይህም እይታን እንደ ቆሸሸ መስታወት ሊያደበዝዝ ይችላል። ይህንንም ለማጥራት የጨረር ህክምና መጠቀም ይችላል። የጨረር ህክምናም በስከንዶች ውስጥ ፤ በቀላሉ ውጤት ያሳያል።

ታድያ እነኝህ በሽታ አይነቶች ውጭስ ?
ጨረር ህክምና ያለው ውጤት እጅጉን የተገደበ ነው።
በአይን ሌዘር ህክምና ዙሪያ መረዳት ያለብዎ
ያለ ጠባሳ በደቂቃዎች ውስጥ የሚያክም ፤ በፍጥነት የሚያገግም ይህ የዘመናችን ሳይንስ ግኝት ህክምና ያለውን ገደብ መረዳት ይኖርብናል። ለምሳሌ፡
ሁሉንም የዕይታ ችግር ማከም አይችልም
የሌዘር ህክምና ሁሉንም የእይታ ችግር ፈጽሞ አይፈታም።ሁሉም የአይን በሽታ አንድ አይደለም። ሁሉም ዐይን — ትንሽ ወይም ትልቅ፣ ቡኒ ወይም ጥቁር — ቅርጹ እና ቀለሙ ልዩ እንደሆነው ችግሩም እንዲሁ ለየቅሉ ነው ። የአይን በሽታም ደግሞ ብዙ አይነት ነው ያለው። የእይታ ችግር አለ ማለት በሽታው አንድ ነው ማለት አይደለም። ለዚህም፡
የኦፒቲክ ነርቭ ጉዳትን ፣ የሬቲና ጉዳትን ሊመልስ አይችልም። ከዚህ ጋር የሚመጣ የእይታ ችግር በሌዘር ህክምና አይታከመምም።
እንዲሁም በጣም የተባባሰ ግላኮማን እንዲሁም ፣ ማኩላ (macula) የተሰኘው የአይን ክፍልን ጉዳትንም አይመልስም።
የሞተ ነርቭን አያስነሳም። የደከመ አካልን አይቀስቀስም።
ለዚህም ከእነኝህ ጋር የተያያዘ ችግር ላለባቸው ታካሚዎች ጠቀሜታ አይኖረውም።

ለሁሉም ሰው ህክምናው አይሰጥም
ህክምናውም ለሁሉም ሰው አይሰጥም።
የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅሙ ለተዳከመ ሰው ፤
ኮርንያው ስስ ለሆነ ሰው፣
የሚዋዥቅ የእይታ መጠን ላለው ሰው ይህ ህክምና ውጤታማ አይሆንም።
ከአደጋ ነጻ አይደለም
ማንኛውም የህክምና አማራጭ እንዳለው አደጋ ፤ የሌዘር ህክምናም ተጓዳኝ ጉዳቶች ይኖሩታል።
እይታን ብዥ ማድረግ ፤
የማታ እይታን ማጣት (ዳፍንት በሽታ) እንዲሁም
የአይን ድርቀት ሊያመጣ ይችላል።
አንዳንዴም የሚኖረው ጉዳት ዕይታን እስከመጨረሻው ሊያሳጣ ይችላል።

ከዚህም ባሻገር መሳሪያው ምንም የረቀቀ ቢሆንም፣ ውጤታማነቱ እንደ ሃኪሙ ብቃት፣ ልምድ እና ጥንቃቄ ይወሰናል። የዶክተሩ ክህሎት ደረጃም ግንዛቤ ውስጥም መግባት አለበት።
ትክክለኛው ተአምር በእውቀት እና በስነምግባር ላይ ይመሰረታል።
የሌዘር ህክምና እውነተኛው ምትሃታዊ ተግባር እና ውጤት ያለው መሳርያው ላይ ሳይሆን፤ መቼ፣ለምን እና ለማን መጠቀም እንዳለብን ማወቅ ላይ ነው።
በትከክለኛው ምርመራ፣ሙያዊ ስነምግባር እና ክህሎት ሲመራ እና ሲታጀብ መሳርያው አስደናቂ ስኬትን ያመጣል።
የገንዘብ ትርፍ ላይ ብቻ ያተኮረ እና ከመጠን ባለፈ የራስ መተማመን የሚድረግ ህክምና መቼም ቢሆን ጉዳት እንጂ ጠቀሜታ አይኖረውም።
ያስተውሉ። ውሳኔዎ በጥንቃቄ የተሞላ መሆን ይኖርበታል።
ግንዛቤዎን ያሻሽሉ። የጨረር ህክምና ተአምራዊ ሳይሆን ፤ አቅሙ የተገደበ አምርቂ ውጤት ያሳየ የህክምና አማራጭ መሆኑን ያስተውሉ።
የሚፈውስዎት ብርሀን ሊያሳውር ስለሚችል ፤ ያስተውሉ።




Comments