top of page

የታይፈስ ወረርሽኝ እና መከላከያዎቹ

 እንደ ታሪክ መዛግብት ከሆነ... ታይፈስ የሰው ልጅን ለብዙ መቶ አመታት ሲያሰቃይ የቆየ የትኩሳት ህመም ነው።


ከትላልቅ ጦርነቶች ፣ ረሀቦች ፣ ስደቶች ጋር ታይፈስ አብሮ ይነሳል። ከጦርነት የተረፉትን ሰራዊት የጨረሰ ነው።

በአውሮፓ በ 16ተኛው ክፍለዘመን  ብዙዎችን በዚህ ወረርሽኝ አልቀዋል። በ19ኛው ክፍለዘመን በታላቋ አየር ላንድ ባጋጠመው ትልቅ ረሀብ (1846-49) ጊዜም በረሀብ ላይ ተደርቦ የብዙዎችን ህይወት ነጥቋል። 
ree
በአንደኛው የአለም ጦርነት በተለይም በምስራቅ ግንባር፤ ታይፈስ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች፣ እስረኞች እና ሲቪል ማህበረሰብ ሞት ተጠያቂ ነው።

በምዕራብ አውሮፓ የታይፈስ ስርጭት ሊቀንስ የቻለው ፤ በተደረገ መሰረታዊ ለውጥ ነው። የንፅህና አጠባበቅ ሲሻሻል ፣ የተባይ ቁጥጥር ሲጨምር፣ የተሻለ መኖሪያ ቤቶች ሲገነቡ ፤  በጦርነት ጊዜ እንደዲዲቲ ያሉ ፀረ-ተባዮች ሲረጩ የታይፈስ ስርጭት ቀንሷል።

በመጽሐፍት ውስጥ በሹክሹክታ የተጠቀሰው ይህ በሽታ አሁንም በአለማችን ውስጥ አለ!

 

አብዛኞቻችንም እናውቀዋለን!

 

ይህ ታሪክ አንድ ዋና እውነትን ያሳያል።


ታይፈስ በችግር ጊዜ የሚበረታ በሽታ ነው። ክፉ ቀናቶችን ጠብቆ ፤ በትሩን ሰዎች ላይ የሚያነሳ ፤ ብዙዎችን ህይወት የሚነጥቅ ነው። ከጦርነት፣ ከረሃብ፣ ከመፈናቀልና ከድህነት ጋር ተያያዥነት አለው።


ለምን?


ስያሜውም ከበሽታው ምልክት ጋር ቁርኝት አለው። በሽታው ሲደረጅ የሚያሳየውን ድብርት ስሜት፣ግራ መጋባትና የሀሳብ መንፈዝ ለመግለጽ ስሙም ታይፈስ ተባለ። ታይፈስ የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙም መንፈዝ/ሞኝነት አልያም ጭጋግ (ሲታመሙ የአስተሳስብ ጭጋግ/መንፈዝ ስላለ) ነው።

 

 

ታይፈስ ምንድን ነው?

 

በመጀመሪያ ታይፈስ አንድ በሽታ ብቻ አይደለም። ሪኬቲስያ እና ኦረንሺያ የሚባሉ የባክቴሪያ ዝርያዎች የሚመጣ የኢንፌክሽን በሽታ ነው።  እነኝህ ባክቴሪያዎችም በቅማል ፣ ቁንጫና ቅንቅን ውስጥ መቆየት ስለሚችሉ ፤ በተባዮች የተነሳ ከታማሚ ወደ ጤነኛ ይተላለፋል።

ree

 

በባክቴሪያው አይነትና በመተላለፊያ መንገዱ ስንመልከት 3 አይነት ታይፈስ አለ። ከ እነኝህ ውስጥ ሁለቱ በኢትዮጵያ ላይ በብዛት ይስተዋላሉ።


ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት የሚታዩ ታይፈሶች

ታይፈስ ከሚያመጡ ተባዮች ውስጥ አንዱ የሆነው ቅማል
ታይፈስ ከሚያመጡ ተባዮች ውስጥ አንዱ የሆነው ቅማል

  • ወረርሽኝ የሚያመጣው ታይፈስ - ይህ ታይፈስ ሪኬቲስያ ፕሮዋዜኪ በሚባል ባክቴሪያ አይነት የሚመጣ ነው። በቅማልም ይተላለፋል። በባህሪውም ወረርሽኝ የማምጣት አቅም አለው።  


ታይፈስ ከሚያመጡ ተባዮች ውስጥ አንዱ የሆነው ቁንጫ
ታይፈስ ከሚያመጡ ተባዮች ውስጥ አንዱ የሆነው ቁንጫ
  • ከአይጥ ጋር ግንኙነት ያለው ታይፈስ- ይህ ታይፈስ አይጥንም ሊያጠቃ የሚችል ሲሆን ሪኬትሲያ ታይፊ በሚባል ባክቴሪያ ይመጣል። የሚተላለፈውም በቁንጫ ነው። የታመሙ ሰዎች/አይጦችን የበላ ቁንጫ በሽታውን ሊያስተላልፍ ይችላል።


 

ኢትዮጵያ እምብዛም የሆነው ታይፈስ

ታይፈስ ከሚያመጡ ተባዮች ውስጥ አንዱ የሆነው ቅንቅን
ታይፈስ ከሚያመጡ ተባዮች ውስጥ አንዱ የሆነው ቅንቅን
  • ይህ በቅንቅን አማካኝነት የሚተላለፍ ታይፈስ ሲሆን ፤ በህክምና ስሙ ስክረብ ታይፈስ ይባላል። ይህ ታይፈስ ኦሪየንታ በሚባለው ባክቴሪያ አይነት የሚመጣ ሲሆን በአለም ላይ  በእስያ ፓስፊክ ክልል (ከምስራቅ ኢስያ በደቡብ ምስራቅ ኢስያ እስከ ኦሽንያ ባሉ ሀገራት ) ብቻ ይታያል። በቅንቅን አማካኝነትም ሊተላለፍ ይችላል።


እንዴትስ ይተላለፋል?


ለመተላለፉ በመጀመሪያ የታመመ ሰው/ የአይጥ ዝርያ ያስፈልጋል።


ተባዮቹ በታይፈስ የተያዘውን ሰው ሲበሉ ፤ ባክቴሪያው ወደ ሰውነታችው ይገባል። እነኝህ ባክቴሪያውን የተሸከሙ ተባዮች ጤነኛ ሰው ሲበሉ የማሳከክ ስሜት ይፈጥራሉ። ይህን ጊዜ ጤነኛው ሰው አኮ ሲገድላቸው ፤ ተባዮቹ ውስጥ ያለው ባክቴሪያ ሲታከክ በተፈጠረው የቆዳ ክፍተት ወደ ጤነኛ ሰው ደም ይገባል።


ree

ደም ውስጥ ገብቶ ሲራባ ፤ ሰውየው የኢንፌክሽን ምልክት ማሳየት ይጀምራል። ትኩሳት ይኖረዋል። ሽፍታም ያሳያል።



ምልክቶቹን በደንብ ይለዩ!

 

እንዲህ ያስቡማ....ዛሬ ጤናማ ነዎት.... ጤናዎ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዳለ በተወሰኑ ቀናት ልዩነት ውስጥ

 

ree
  • ከባድ ትኩሳት ይኖርዎታል። ትኩሳቱ ከ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ  ሊያልፍ ይችላል። 

  • ራስ ምታት(ከባድ ሊሆን ይችላል)

  • ብርድ ብርድ ማለት

  • የጡንቻ ህመምና

  • የሰውነት ድካም ሊያሳዩ ይችላሉ። 

የታይፈስ ሽፍታ
የታይፈስ ሽፍታ
  • ትኩሳቱን ባዩ በቀናቶች ውስጥ ሽፍታ ሊኖርዎት ይችላል። ሽፍታው ሲጀምር ከደረትዎ/ ሆድዎ/ ጀርባዎ ተነስቶ ፤ ወደ እጅዎ መዳፍ እና ውስጥ እግርዎ ሊስራጭ ይቻላል።

  • ከዚም ባሻገር ከምግብ ቱቦ ጋር የተያያዙ ምልክቶች ሊያስተውሉ ይችላሉ። ለምሳሌ

    • የ ማቅለሽለሽ ስሜት

    • ማስታወክ፣

    • እንዲሁም የሆድ ህመም አይነት  ምልክቶች ሊያሳዩ ይችላሉ። 

  • ሳልም ሊኖርቦት ይችላል። 


ህመሙ ከባሰ ግን ፡

ree
  • ድብርት

  • እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት

  • ግራ መጋባት

  • የአስተሳሰብ ለውጥ /መንፈዝ ሊኖርብዎት ይችላል።  

 

 

ታድያ ታይፈስን አስቸጋሪ የሚያደርገው... ከሌሎች የትኩሳት ህመሞች ጋር መመሳሰሉ ነው። የኢንፌክሽን ህመም ስርጭት በበዛባት ኢትዮጵያ ታይፈስ በሽታ እስኪለይ ትንሽ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል።


እርስዎ እርስዎ ግን ለተባይ መጋለጥዎን መለየት ቢያቅትዎ እንኳን...

  1. በአቅራቢያዎ/በጎረቤትዎ ታይፈስ የታመመ ሰው ከነበረ ወይም እነኝህን ምልክቶች የሚያሳይ ሰው ከነበረ እና

  2. እርስዎ ከእነኝህ ምልክቶች ውስጥ ብዙዎችን ካሳዩ በአፋጣኝ ጤና ተቋም ሄደው ምርመራ ያድርጉ።


 

 

ታይፈስ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ እድሉ አነስተኛ ነው። ብዙ ጊዘ አስተላላፊ የሆኑ ተባዮች ያስፈልጋሉ።


ree

ለዚህ አጋላጭ ምክንያቶች ተብለው የሚጠቀሱት እነኝህ ተባዮች እንዲሁም አይጦች እንዲራቡ የሚያስችል አከባቢዊ ሁኔታዎችን ነው። ለዚህም

  • የተጨናነቀ አኗኗር ካለ (በትንሽ ቦታ ላይ ብዙ ሰው መኖር)

  •  የንጽህና ጉድለት ካለ

  • ቅማል እና ቁንጫ በመኖሪያ/በመቆያ ስፍራ ከበዛ

  • አይጦች በአከባቢው ከበዙ ተጋላጭነት ይጨምራል።


ድመቶች ያሏቸውም ሰዎች ፤ ድመቶች ከአይጦች ጋር ንክኪ ስለሚኖራቸውና ቁንጫ ስለሚያመጡ እቤት ውስጥ ጸረ ተባይ ካልረጩ ፤ ሳያውቁት ሊጋለጡ ይችላሉ።


እላይ በጠቀስናቸው ምክንያቶች የተነሳ የታይፈስ ወረርሽኝ በእስር ቤቶች ውስጥ፣ በስደተኞች ማቆያ ካምፖች ፣ በጦር ካምፓች ፣ በተጨናነቁ ሰፈሮች ፣ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ተሰብስበው በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ይታያል።

 

ሕክምናውስ ምን ይመስላል?

መልካሙ ዜና... ታይፈስ ሊታከም ይችላል። ታክሞም ይድናል!
ree

ታይፈስን የሚያመጡ ባክቴሪያዎችን የሚቃወም አንቲባዮቲክ (የባክቴሪያ መቃወሚያ) በመውሰድ ከ ታይፈስ መዳን ይቻላል።


ክዚህም ባሻገር የድጋፍ ህክምና ያስፈልጋል። ለዚህም

  • ትኩሳቱን ፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ ሆድ ህመም ካለ እሱን ማከም

  • ፈሳሾት መውሰድ ፤

  • እረፍት ማድረግ ፤

  • የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ይመከራል።


ታይፈስ በሰውነትዎ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት መከታተል ያስፈልጋል። በሽታው ከደረጀ ኩላሊትን፣ ሳንባ እና አንጎልዎትን ጨምሮ ሊያጠቃ ይችላል።

 

ያሰተውሉ! ቶሎ ህክምና ከተደረገ ፤ የህክምናው ውጤት እጅጉን መልካም ነው።  ካልታከመ ግን ሞት ሊያደርስ ይችላል።

በታሪክ እንዳየነው የብዙዎችንም ህይወት ይቀጥፋል።

 

እንዴት መከላከል ይቻላል?

 

መከላከል ከፈውስ በላይ ነው! ለመከላከል እነኝህን ያድርጉ፡


በሁለተኛ የአለም ጦርነት ጊዜ ታይፈስን ለመከላከል የተለቀቀ ማሳሰቢያ
በሁለተኛ የአለም ጦርነት ጊዜ ታይፈስን ለመከላከል የተለቀቀ ማሳሰቢያ
  • የአከባቢዎን እና የመኖሪያ ቤትዎን ንጽህና ይጠብቁ። 

  • ለተባዮች ያሎትን ተጋላጭነት ይቀንሱ። ተባይ በቤትዎ ከበዛ ጸረ ተባይ ይጠቀሙ። 

  • የግል ንጽህናዎን ይጠብቁ። ልብሶችዎን በአግባቡ ያጽዱ።

  • አይጥ ከቤትዎ ያጥፉ።

  • ቁጥቋጦዎች ከአከባቢዎ ያስወግዱ።

  • የቤት እንሰሳ ካለ ተባዮች እንዳይኖሩባቸው ንጽህናቸውን ይጠብቁ።

  • በተጨናነቀ ስፍራ የሚኖሩ ከሆነ ቅማል እና ቁንጫ ስርጭት እንዳይኖር ይጠንቀቁ።

  • ከዚህም በላይ ብዙዎች በቅማል እና በቁንጫ እንደሚመጣ አያውቁምና ግንዛቤን ያስጨብጡ ። ይህንን ትምህርታዊ መረጃ ለሌሎች ያጋሩ።

 


ስርጭቱ ምን ይመስላል?


የታይፈስ ወረርሽኝ ባዳጉ ሀገራት አይታይም። በተቃራነው ጦርነት፣ ድህነት ፣ ረሀብ በተንሰራፋባቸው ሀገራት ስርጭቱ ከፍ ያለ ነው። በኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ስርጭቱን የሚያሳይ በቅርብ የተደረገ ጥናት ባይኖርም ፤ እ.ኤ.አ 1981-1990 ውስጥ 14,078 የታይፈስ በሽተኞችን መኖራቸውን ኢትዮጵያ ሪፖርት አድርጋ ነበር። ይህ መጠን በወቅቱ በአፍሪካ ከተመዘገብው ሁለት ሶስተኛውን ይወስዳል።


እ.ኤ.አ ከ 2008 እስከ 2012 ባሉ አራት አመታት በአዲስ አበባ ቃሊት እስር ቤት ውስጥ የተደረገ ጥናት በበኩሉ ፤ አንድ አራተኛ የሚሆኑ እስረኞች የታይፈስ ኢንፌክሽን ምልክት ደማቸው ውስጥ ታይቷል።


በአሁኑ ጊዜስ ምን ያህል ይሆን?


ማጠቃለያ

 

በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ካላት አንገብጋቢ ሁኔታዎች አንጻር ፤ ታይፈስ በሽታ አርዕስተ ዜና ሊሆን ባይችልም ፡ ትኩረት ሊሰጥው ይገባል።


ቀድሞ ማወቅ ህይወት ያድናልና። ፈጠን ብለው አውቀው አፋጣኝ ህክምና ያድርጉ።

ቀድመውም ይከላከሉ። 

የእርስዎን ጤና ጠበቁ ማለት የማህበረሰብዎን ጤና ጠበቁ ነው። 


በቀጣይ ከታይፈስ ጋር አብዝቶ የሚነሳው ታይፎይድ ህመም ዙሪያ ትምህርታዊ ጽሁፍ ስለምንለቅ ይከታተሉ።

Comments


bottom of page