top of page

117 results found with an empty search

  • ለልጅ ስልክ መስጠት ኦቲዝም ያመጣ ይሆን?

    በብዙዎቻችን ቤቶች ውስጥ ህጻናት እና ስልክ ያላቸው ቁርኝት እየጨመረ መጥቷል። ከአንድ ስፍራ ተቀምጦ ለሰአታት በስልክ ስክሪኖች ላይ ተተክሎ የሚያሳልፍ ህጻን ጥቂት አይደለም ክፍሉ በድምጾች ተሞልተው፤ እናት ስትጠራ፣ ወንድም እና እህቶች ሲስቁ ፤ ስልኩ ላይ ተደፍቶ ህጻኑ ዘወር አይልም። እንደዚህ አይነት ትዕይንት በከተሞች ከተለመደ ሰንበትበት ብሏል። በአለም አቀፍ ደረጃ እንኳን 2 አመት ያልሞላቸው ህጻናት መካከል ከ60% በላይ የሚሆኑት በየቀኑ ስክሪን ይጠቀማሉ። ይህ አሳሳቢ ነው! ወላጆችማ በረዥም ጊዜ ውስጥ የለመዱትን ቴክኖሎጂ ፤ በስርአት ማውራት ያልቻሉ ህጻናት አቀላጥፈው ሲጠቀሙ ይገረማሉ። ጠቋሚ ሳያስፈልጋቸው የህጻናት መዝሙሮችን፣ የካርቶን ቪድዮዎች እንዲሁም አስቂ ቪድዮዎች በራሳቸው እየቀያየሩ ሲያዩ "ከእኛ በላይ ዘመናዊ ናቸው" ብለው አድናቆት ይቸራሉ። አንዳንድ ወላጆች ይህንን የአእምሮ ብሩህነት አድርገው ይወሰዳሉ። በተለይ ደግሞ ስራ ለበዛባቸው ፣ የቤት ውስጥ ኃላፊነት ላጨናነቃቸው ወላጆች ስልኩን ሰጥቶ እርፍ ማለት ይመርጣሉ። ስልኩ እንደ "ነጻ ሞግዚት" ሆኖ ያገለግላል። ህጻኑ ሳይረብሽ፣ ሳያለቅስ፣ ከቤት ሳይወጣ ባለበት ተተክሎ ለሰዓታት ሲቆይ ፤ ወላጅ የራሱን ስራ ለመከወን ትልቅ እረፍት ያገኛል። ስልኩ የልጁን ትኩረት ሰርቆ በማቆየቱ ወላጅነትን የቀለለ ያደርገዋል። ለመሆኑ ይህ ለወደፊት ዕድገታቸው ጠቃሚ ነው ወይስ ዋጋ ያስከፍላል? በአንዳንድ ማህበራዊ ድህረ ገጾች እንደሚነሳው ፤ ገና በለጋ ዕድሜ ስክሪን/ስልክ አብዝቶ መጠቀም ለኦቲዝም (ASD) ይዳርግ ይሆን?"  በዚህ ጽሑፍ ውስጥ እነዚህን ጥያቄዎች በጥልቀት እንመረምራለን። ስለ ስክሪኑ ተፅዕኖ ከማውራታችን በፊት ስለ ኦቲዝም መረዳት አለብን። ኦቲዝም ምንድን ነው? ምስሉ ላይ እንደተመለከተው ኦቲዝም ያለባቸው ህጻናት ከማህበራዊ ቁርኝት ርቀው ብቻችውን መሆን ይመርጣሉ። ኦቲዝም ከአንጎል እድገት ጋር የተያያዘ የጤና እክል ነው። ይህም በዘላቂነት አንድ ህጻን ዓለምን የሚረዳበትን መንገድ የሚቀይር ነው። በሽታው ያለባቸው ህጻናት የሚከተሉትን ባህሪያት ይስተዋልባቸዋል። በማህበራዊ ግንኙነት እና ተግባቦት ላይ ይቸገራሉ። ተደጋጋሚ ድርጊቶችን ሲያደርጉ ይስተዋላሉ። የለመዱትን የዕለት ተዕለት ተግባር የመምረጥ ዝንባሌ አላቸው። እነዚህ ህጻናት አካባቢያቸውን የሚያዩበት፣ የሚሰሙበት እና የሚያስተውሉበት መንገድ የተለየ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ100 ሕፃናት መካከል አንዱ የኦቲዝም ምልክት ይታይበታል ተብሎ ይገመታል። ምልክቶቹ አብዛኛውን ጊዜ ከ2 እስከ 3 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ መታየት ይጀምራሉ። በቂ ድጋፍ እና ክትትል ከተደረገላቸው ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች ውጤታማ ሕይወት መምራት ይችላሉ። ስለ ኦቲዝም በይበልጥ ለመረዳት ይህንን ጽሁፍ ያንብቡ። ስልኩ ኦቲዝም አምጥቶበት ይሆን? እንደ The Lancet  እና JAMA Pediatrics  ያሉ የሕክምና መጽሔቶች ያወጧቸው ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት፣ ኦቲዝም ከዘረመል (genetics) እና በጽንስ ወቅት ከነበረ የጭንቅላት ዕድገት ጋር የተያያዘ ነው። ይህም ማለት ኦቲዝም ህጻኑ ስልክ ከመንካቱ ከረጅም ጊዜ በፊት የሚወሰን ነው። ለዚህም ከዩቲዩብ /ቲክቶክ ቪድዮ አጋር ኦቲዝም አይያዝም። ዲጂታል ሚዲያ ኦቲዝምን አያመጣም። ታድያ ይህ እውነት ከሆነ ታድያ ኦቲዝም እና ስልክን የሚያቆራኙ ጥናቶች ከየት መጡ? እዚህ ጋር ያስተውሉ ፤ ስልክ መጠቀሙ ኦቲዝም ባያስከትልም ፤ ከመጠን ያለፈ የስልክ አጠቃቀም የኦቲዝምን ምልክቶች "ሊመስል" ይችላል። ይህንንም መመሳሰሉን አስከትሎ ስልክ አጠቃቀምን ተከትሎ የሚመጣው ለውጥ የዲጂታል ኦቲዝም ይሰኛል። ሆኖም ግን ይህ እንደ ትክክለኛው ኦቲዝም ከዘረመል/ከባዮሎጂ ግንኙነት የለውም። ፈጽሞ የተለያየ ነው! ምልክቶቹ ለምን ከኦቲዝም ጋር ተመሳሰሉ? የሕፃን አእምሮ በመጀመሪያዎቹ 1,000 ቀናት ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት ያድጋል። ይህ ዕድገት የሚፋጠነው ህጻን ልጅ ከአከባቢው ጋር በሚያደርገው መስተጋብር/ግንኙነት ነው። ይህም ከእናት እና ከቤተሰብ ጋር የሚኖር የአይን ለአይን ግንኙነት፣ የእናት ፈገግታ , የሚያደርገው ንግግር እንዲሁም ከእድሜ እኩዮቹ ጋር የሚኖረው ቁርኝት እድገቱን ይወስናል። በቤተሰብ ፋንታ ልጁ ከስልክ ጋር ብዙ ሰአት ሲያሳልፍ ይህ ወሳኝ ግንኙነት ይቋረጣል።  የስልክ ስክሪን የህጻኑ ዋነኛ ጓደኛ ይሆናል። ከሰው ፊት ይልቅ ህጻኑ በፍጥነት የሚንቀሳቀሱ ምስሎችን እና ተደጋጋሚ ሰው ሰራሽ ድምጾችን ያያል/ይሰማል። ይህም እድገቱ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት በታዳጊ ህጻናት ላይ በቀን ከ2-3 ሰዓት በላይ ስክሪን መጠቀም የሚከተሉትን ሊያስከትል ይችላል፦ የንግግር መዘግየት፤ የአይን ለአይን ግንኙነት መቀነስ፤ ከሌሎች ልጆች ጋር ለመጫወት ፍላጎት ማጣት ፤ ያስከትላል። እነኝህ ባህሪያት ደግሞ ኦቲዝም ካለባቸው ህጻናት ባህሪያት ጋር ይመሳሰላሉ። ለዚህም አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ላይ "ኦቲዝም መሰል" ባህሪያትን አይተው ይደነግጣሉ። ይህ ግን ህጻኑ ኦቲዝም ኖሮበት አይደለም። ይልቁንም ማህበራዊ ክህሎትን ለማዳበር የሚያስፈልገውን የሰው ልጅ ግንኙነት በስክሪን በመተካቱ የመጣ ነው። ከመጠን ያለፈ አጠቃቀም የሚያስከተለው ችግር፡ ችግሩ ቴክኖሎጂው ሳይሆን የሰው ልጅ ግንኙነት መተካቱ ላይ ነው። ከመጠን ያለፈ ተጋላጭነት (በተለይ ከ3 ዓመት በታች) የህጻን ልጅ እድገት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ከ1 አመት እስከ 2 አመት እድሜ ያሉ ህፃናት በቀን 30 ደቂቃ ተጨማሪ የስክሪን ጊዜ ካሳለፉ የንግግር መዘግየት እድላቸው በ 49% ከፍ ይላል። ይህ ደግሞ ሊያሳስበን ይገባል። ከዚህም ባሻገር አብዝቶ ስልክ/ስክሪን መጠቀም የሚከተሉትን ችግሮች ያስከትላል፦ የወላጅ እና የልጅ ትስስር ያዳክማል፦ ስክሪን በልጁ እና በወላጆቹ መካከል ያለውን ተፈጥሯዊ ግንኙነት እና የመጫወቻ ጊዜን ይቀንሳል። ለዚህም ከወላጅ ጋር ያለ ቅርበትን ይቀንሳል። የእንቅልፍ መዛባት ያመጣል፦ ከስክሪን የሚወጣው ብርሃን እና የሚያነቃቁ ምስሎች ህፃናት በቀላሉ እንቅልፍ እንዳይወስዳቸው ወይም ጥራት ያለው እንቅልፍ እንዳያገኙ ያደርጋል። ከፍተኛ ብስጭት እና ባህሪ መለዋወጥ ያመጣል፦ ከመጠን ያለፈ ተጋላጭነት ለብስጭት፣ ለትኩረት ማጣት፣ እና ለባህሪ መለዋወጥ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ለዚህም በሳይንስ የሚከተሉት ገደቦች ይመከራሉ። የልጅዎ ዕድሜ ከ0-18 ወራት ከሆነ ፤  ምንም አይነት ስክሪን አይፈቀድም። ቢበዛ የሚፈቀደው የቪድዮ ስልክ ጥሪ ብቻ ነው። የልጅዎ እድሜ ከ 2-5 ዓመት ከሆነ ፤ በቀን የሚፈቀደው ቢበዛ አንድ ሰዓት ነው። ያውም ትምህርታዊ መሆን ይኖርበታል። ይህንንም የስልክ አጠቃቀም ጥራቱ እና በውስጡ ያለው ይዘትን ለማረጋገጥ ወላጅ መከታተል/መቆጣጠር ይኖርበታል። የእርስዎ ልጅ አጠቃቀምስ ምን ይመስላል? እውቀት በተግባር ሲታገዝ ነው ጤና መጠበቅ የሚቻለው። እናስ ምን አሰቡ!? የተሳሳተ አስተሳስብ እዚህ ጋር ቴክኖሎጂን እንደ ጠላት ብቻ ማየት ስህተት ነው! ቴክኖሎጂ ለህጻናትም ሆነ ለአዋቂዎች ብዙ መልካም ጎኖች አሉት። ኦቲዝም ላለባቸው ልጆች እንደ ድልድይ ሊያገለግል ይችላል። ዲጂታል መሳሪያዎች ዓለምን የሚያዩበት መስኮት ሊሆኑ ይችላሉ። ብዙ ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች በምስል በመማር ጎበዝ ናቸው። ለዚህም በምስል አማካኝነት ሃሳባቸውን የሚገልጹባቸው አፕሊኬሽኖች ወይም ስሜታቸውን እንዲቆጣጠሩ የሚረዱ ጨዋታዎች ትልቅ እገዛ ያደርጋሉ። በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለም የህጻናትን ምህዳር የማስፋት ፣ ከቋንቋ ጀምሮ ብዙ መልካም ነገሮች የማስተማር አቅም አለው። መፍትሔው ምንድን ነው? የመፍትሄው ቁልፍ ቴክኖሎጂውን መከልከል አይደለም። ስልክን የልጅዎን እድገት በሚደግፍ መልኩ መጠቀም ላይ ነው። ለዚህም የሚከተሉትን ያድርጉ። 1. ከልጅዎ ጋር ላሎት ግንኙነት ቅድሚያ ይስጡ። ማንኛውም አፕሊኬሽን የማህበራዊ ግንኙነት ክህሎትን ሊያስተምር አይችልም። ከልጅዎ ጋር አብረው ያውሩ፣ ይዝፈኑ፣ ፊት ለፊት ይተያዩና ይጫወቱ። እነዚህ አፍታዎች የልጅዎን ማህበራዊ የአእምሮ እድገት ለመገንባት ከማንኛውም የስልክ ስክሪን በላይ ይረዳሉ። 2. ልጅዎን ትተው አይሂዱ። ልጅዎ ስክሪን የሚጠቀም ከሆነ ብቻውን አይተዉት። አብረው ይቀመጡ፤ የሚያየውን ነገር አብረው ይጠቁሙ፤ ድምፆችን አብረው ይከተሉ። ይህ ብዙ ጠቀሜታ አለው። በአንድ በኩል ልጅዎ ብቻውን የሚያደርገውን ድርጊት ወደ ማህበራዊ ግንኙነት ይለውጠዋል። በሌላ በኩል ልጅዎ የሚያየውን ነገር ትምህርታዊነቱን፣ ጥራቱን እና መልካምነቱን እንዲያረጋግጡ ያስችልዎታል። 3. ሳይንሳዊ የጊዜ ገደቦችን ያክብሩ እላይ የተጠቀሱትን የህፃናት ህክምና ባለሙያዎች ምክር ይከተሉ! 4. ቀድሞ መድረስ ትልቁ መሳሪያ ነው ልጅዎ ማንኛውንም የእድገት መዘግየት ካሳየ ፈጽመው አይጠብቁ። እድገቱ ከእድሜ እኩዮቹ አንጻር ከዘገየ ፣ ቃላት ለማውጣት፣ ለመራመድ እንዲሁም አንዳንድ ድርጊቶችን ለማድረግ ረዘም ያለ ጊዜ ከወሰደ፤ የጤና ባለሙያ ያማክሩ። ቀድሞ የሚደረግ ድጋፍ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። ስለ ሕፃናት የዕድገት ደረጃዎችና የለውጥ ምልክቶች ይበልጥ ለመረዳት ይህንን ትምህርታዊ ቪድዮ ይመልከቱ። እወነታው ይህ ነው! አእምሮ የሚገነባው በስልክ ላይ በሚታዩ ምስሎች ሳይሆን በሰዎች ነው። አንድ ህጻን ኦቲዝም ይኑርበትም አይኑርበትም፣ የሚፈልገው አንድ አይነት ነገር ነው፦ የሰው ድምጽ፣ በፍቅር የተሞላ እንክብካቤ እና ወደ እሱ የሚመለከቱ የፍቅር አይኖች። ዛሬውኑ ልጅዎ ዝም እንዲል ስልክ መስጠት ያቁሙ። በልጅዎ እድገት ዙሪያ የሚያሳስብዎት ነገር አለ? ወይም በአካባቢዎ የሚገኙ የልዩ ፍላጎት ድጋፍ ሰጪ ማዕከላትን ለማወቅ ይፈልጋሉ?

  • ስለ ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ ማወቅ ያለብሽ?

    ይህንን ሁኔታ በልቦናሽ አስቢው... ምሽት ነው። ከፍቅረኛሽ ጋር መልካም ጊዜ እያሳልፈሽ ፤ ድንገት ኮንዶም ተቀደደ። ሁልጊዜ የምትወስጂውን የእርግዝና መከላከያ ኪኒን ዛሬ አልወሰድሽም ነበር። ድንገት ያላሰብሽው እና ያልተዘጋጀሽበት ክስተት ተፈጠረ! ምን ተሻለሽ? ፖስት ፒል መውሰድ አልያስ....? እሱንስ መቼ እና እንዴት መውሰድ እንዳለበሽ ታውቂያለሽ? ዛሬ በብዙዎች ዘንድ ፖስት ፒል በመባል ስለሚታወቀው የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ መንገድ እናነሳለን። ፖስት ፒል የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ መድሀኒቶች ውስጥ የአንዱ የብራንድ (የፋብሪክ ምርት) ስም ስለሆነ ፤ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ የሚለውን ስያሜ ብቻ እንጠቀማለን። ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ምንድን ነው? ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ደህንነቱ ያልተጠበቀ የግብረ ሥጋ ግንኙነትን ተከትሎ የሚመጣ እርግዝናን ይከላከላል።ለዘወትር አገልግሎት የሚውል ሳይሆን እንደ “ተጠባባቂ እቅድ”  የሚያገለግል ነው። እንዴት ይሠራል? ድንገተኛ መከላከያ የሚሠራው እርግዝና ከመጀመሩ በፊት ነው። እርግዝና እንዳይፈጠር ይከላከላል እንጂ ፤ እርግዝና ከተፈጠረ በኋላ ጥቅም አይኖረውም።እርግዝናን የሚከላከለው በሚከተሉት መንገድ ነው። 1️⃣ የእንቁላል መውጣትን ያዘገያል፦  ድንገተኛ መከላከያው ሲወሰድ በመደበኛ ሁኔታ የሚወጣውን የሴት ልጅ እንቁላል ዘግይቶ እንዲወጣ ያደርገዋል። እንቁላል በጊዜ ካልወጣ ደግም የወንድ ዘር ፈሳሽ የሚያገኘው ነገር ስለሌለ እርግዝና አይፈጠርም። 2️⃣ የወንድ ዘር ከእንቁላል ጋር እንዳይገናኝ እንቅፋት ይሆናል፦  የወንድ ዘር በሴት አካል ውስጥ እስከ 5 ቀናት ሊቆይ ይችላል። ድንገተኛ መከላከያው ደግም የማህፀን በርን በወፍራም ፈሳሽ በመዝጋት የወንድ ዘር እንቁላል ጋር እንዳይደርስ ያሰናክላል። እንዲሁም የወንድ ዘር እንቅስቃሴን በመቀነስ ጽንስ እንዳይፈጠር ያደርጋል። 🚫 ይህ ሲሆን ግን ያስተውሉ! ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ የሚከተሉትን አያደርግም። ❌ በማህፀን ግድግዳ ላይ ያረፈን እርግዝና አያሰናክልም።   ❌ ውርጃ አያስከትልም።   ❌ ነባር እርግዝናን አይጎዳም። የሚሰራው እርግዝና ከመፈጠሩ በፊት እንጂ በኋላ አይደለም! ሦስቱ ዋና ዋና ዓይነቶች (አማራጮችሽን እወቂ) እንደ ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያነት የሚያገለግሉ ሦስት አማራጮች አሉ። እያንዳንዱን በዝርዝር እንመልከት፦ 1️⃣ ሌቮኖርጀስትሬል (Levonorgestrel) ኪኒኖች - ይህ በብዛት በኢትዮጵያ የሚገኝ አማራጭ ሲሆን እንደ ፓስት ፒል ፣ ላና እና ፒል 72 በሚባሉ ስሞች ሊገኝ ይችላል። ይህ መድሀኒት በ72 ሰዓታት (በ3 ቀናት) ውስጥ ቢወሰድ ይመረጣል። ውጤታማነቱም በመጀመሪያ 3 ቀናት ላይ ከፍ ያለ ነው። ሆኖም ግን እስከ 5 ቀን ቢወሰድ ሊሰራ ይችላል። 2️⃣ ዩሊፕሪስታል አሴቴት (Ulipristal Acetate) ኪኒኖች ይህ እስከ 120 ሰዓታት (5 ቀናት) ድረስ ውጤታማ የሆነ አማራጭ ነው። ውጤታማነቱ ከሌቮኖርጀስትሬል የላቀ ነው። ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ፋርማሲዎች በስፋት አይገኝም። 3️⃣ ሉፕ /የመዳብ አዩዲ (Copper IUD - ሉፕ) ይህ የረጅም ጊዜ የወሊድ መከላከያነት የሚያገለግል ሲሆን ፤ እስከ 5 ቀናት ከተደረገ ውጤታማ ይሆናል።  ማህጸን ላይ ካለው ተጽእኖ ባሻገር ፤ ለወንድ ዘር መርዛማ የሆነ ከባቢን በመፍጠር እርግዝና እንዳይፈጠር ያደርጋል። ሴት ልጅ ማህጸን ውስጥ የሚቀመጥ ሲሆን ፤ እስከ 10 አመት ድረስ ሊያገለግል ይችላል። ውጤትማነቱስ ምን ያህል ነው? ውጤታማነቱ እንደ አወሳሰድ ሰዓቱ ይወሰናል፦ በ1 ቀን ውስጥ ከተወሰደ → እስከ 95%  ውጤታማ ሊሆን ይችላል። በ 3 ቀን ውስጥ ከተወሰደ → ከ 75–89%  ውጤታማ ነው። ከ 3 ቀን በኋላ ግን → ውጤታማነቱ ዝቅተኛ ነው። ነገር ግን እስከ 5 ቀን ድረስ የመከላከል ዕድል ሊኖረው ይችላል። ⚠️ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እንደ ፖስትፒል ያሉ ኪኒኖች የሰውነት ክብደታቸው ከፍተኛ በሆኑ ሴቶች (BMI ከ30 kg/m² በላይ) ላይ ውጤታማነታቸው ሊቀንስ ይችላል። ለዚህም የሰውነት ክብደታቸው ከፍ ያሉስ ሴቶች እላይ የጠቀስነውን የመዳብ መከላከያ (Copper IUD) ቢወስዱ ይመረጣል። መቼስ ጥቅም ላይ መዋል አለበት? ድንገተኛ መከላከያ በሚከተሉት ሁኔታዎች ውስጥ ይመከራል፦ ያለ ምንም መከላከያ ግንኙነት ሲደረግ፤ ግንኙነት ላይ ኮንዶም ሲቀደድ ወይም ሲወልቅ ፤ መደበኛ የእርግዝና መከላከያ ኪኒን ሲረሳ፤ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ሲደርስ፤ መደበኛ መከላከያዎችን በተሳሳተ መንገድ ሲጠቀሙ፤ ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ በ 72 ሰዓታት ውስጥ እንዲወስዱ ይመከራል። ይህ የመጨረሻ አማራጭ እንጂ የሁልጊዜ ዘዴ አይደለም። የተለመዱት የጎንዮሽ ጉዳቶች የትኞቹ ናቸው? ድንገተኛ መከላከያዎች በአጠቃላይ ደህንነታቸው የተጠበቀ ነው። ይህ ማለት ግን የጎንዮሽ ጉዳት የላቸውም ማለት አይደለም። መድሀኒቱን ሲወሰድ የሚከተሉት የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊስተዋሉ ይችላሉ፦ ማቅለሽለሽ ወይም ማስመለስ ኪኒኑን እንደወሰድሽ በ2 ሰዓት ውስጥ ካስመለሰሽ ሌላ ተጨማሪ መውሰድ ይኖርብሻል። የድካም ስሜት እና የጡት ህመም ከዚህም ባሻገር የወር አበባ ኡደት ላይ ባለው ተጽእኖ ፤ የሚቀጥለው የወር አበባሽ፦ ቀድሞ ሊመጣ ወይም ሊዘገይ ይችላል። መጠኑ ሊቀንስ ወይም ሊጨምር ይችላል። 👉 አስተውይ! እነዚህ ምልክቶች ጊዜያዊ እንጂ አሳሳቢ አይደሉም። ፈጽሞ ማድረግ የማይችላቸው ነገሮች ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ ብዙ መልካም ጎኖች ቢኖሩትም የሚከተሉትን አስተውይ።   ❌ ለዘወትር አገልግሎት አይሆንም፦ ከመደበኛ መከላከያዎች ያነሰ ውጤታማነት ስላለው ፤ ለዕለት ተዕለት ጥቅም እንዲውል አይመከርም። ❌ በጊዜ ይወሰናል፦ ውጤታማ የሚሆነው እርግዝና ከመፈጠሩ በፊት ሲወሰድ ስለሆነ ፤ በመጀመሪያዎቹ ቀናት/ሰአታት ውስጥ ቢወሰድ ይመከራል። መዘግየት ውጤታማነቱን ይቀንሳል። ❌ ከአባላዘር በሽታ አይከላከልም፦  እርግዝናን ብቻ ነው የሚከላከለው። ከኤችአይቪ (HIV) ወይም ከሌሎች የአባላዘር በሽታዎች የመከላከል አቅም የለውም። መታረም ያለባቸው አመለካከቶች በኢትዮጵያ ስለ ድንገተኛ መከላከያ ያለው ግንዛቤ እየተሻሻለ ቢመጣም ፤ አሁንም የግንዛቤ ክፍተት ይስተዋላል። አወሳሰዱ ወጥ አይደለም። ብዙ ሴቶች ዘግይተው ይወስዳሉ። በተሳስተ አስተሳሰብ የተነሳ ፤ ያልታሰበ እርግዝና የሚያጋጥማቸው ጥቂቶች አይደሉም። እዚህ ጋር ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ነው። የተለመዱ የግንዛቤ ክፍተቶች የሚከተሉት ናቸው። ስህተት፦  “ውርጃ ያስከትላል።” → እርማት ፦  የሚሠራው እርግዝና ከመጀመሩ በፊት ነው። ስለዚህ ውርጃን አያመጣም። ስህተት፦  “መሃንነት ያመጣል።” → እርማት፦  ይህንን የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም። ያለው ተጽእኖ ጊዜያዊ ነው። ስህተት፦  “አደገኛ ነው።/ከፍተኛ የጎንዮሽ ጉዳት ያስከትላል። ” → እርማት፦  የዓለም ጤና ድርጅት ለማንኛውም ሴት ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን አረጋግጧል። ስህተት፦  “የዘወትር መከላከያን ይተካል።” → እውነት፦  እንደ ድንገተኛ አማራጭ እንጂ እንደ መደበኛ አይወሰድም።ለዚያ ሌሎች አማራጮች አሉ። ከተወሰደስ በኋላ? የድንገተኛ የወሊድ መከላከያ ከወሰድሽ በኋላ የሚከተሉትን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ይመከራል። መደበኛ የእርግዝና መከላከያሽን ወዲያውኑ ጀምሪ ወይም ቀጥዪ። እስከሚቀጥለው የወር አበባሽ ድረስ ግንኙነት ስታደርጊ ኮንዶም ተጠቀሚ። የወር አበባሽ ከአንድ ሳምንት በላይ ከዘገየ የእርግዝና ምርመራ አድርጊ። ከፍተኛ የሆድ ህመም ካጋጠመሽ በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ተቋም ሂጂ። አስተውይ! የድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ውጤታማነቱ በአወሳሰድሽም ላይ የተመሰረተ ነው። ዛሬውኑ ግንዛቤሽን አስተካክይ።

  • የማይታወቁት የታይሮይድ በሽታ ምልክቶች

    የዕለት ተዕለት ድካምዎን “ውጥረት ነው” ብለው አልፈውታል? ልብዎ ሲመታስ “ደክሜ ስለሆነ ነው” በሚል ሰበብ ችላ ብለውታል? ክብደትዎ ያለ ምክንያት ሲቀንስስ “ታድዬ” ብለው ተደስተዋል? ነገር ግን… እውነታው ከዚህ የተለየ ሊሆን ይችላል! በአንገትዎ ስር የምትገኝ አንዲት ትንሽ እጢ መላ ሕይወትዎን ልታመሰቃቅል እንደምትችል ያውቃሉ? ብዙ ሴቶች ከፍተኛ ድካም ሲሰማቸው “ሥራ በዛብኝ”፣ ሲጨነቁ ደግሞ “ኑሮ ከበደኝ” በማለት ምልክቶቹን ያስታክካሉ። ይሁን እንጂ ራስዎን አይውቀሱ፤ ዋናው ጥፋተኛ የእርስዎ ደካማነት ሳይሆን የታይሮይድ ሆርሞን መዛባት ሊሆን ይችላል። ይህንን ለመረዳት ስለ ታይሮይድ እጢ እና ስለ ተያያዥ ችግሮቹ በጥልቀት እናንሳ። የታይሮይድ እጢ ታይሮይድ በአንገታችን የፊት ለፊት ክፍል ላይ የምትገኝ ትንሽ እጢ ነው። ስራውም ሰውነታችን ሃይልን እንዴት መጠቀም እንዳለበት መቆጣጠር ነው። ይህም እጢ ሁለት ዋና ዋና ሆርሞኖች (T3 እና T4) ያመርታል። እነዚህም ሆርሞኖች የልብ ምትን ፣ የሰውነት ሙቀትን ፣ የሃይል መጠንን እንዲሁም የወር አበባ ዑደትን ይቆጣጠራሉ። ሰውነት ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ሆርሞኖች ላይም ተጽእኖ ያሳድራሉ። ለዚህም የታይሮይድ ስራ ሲዛባ መላው ሰውነት ትርምስ ውስጥ ይገባል። ሴቶች ለምን በብዛት ይጠቃሉ? የታይሮይድ እጢ በሽታ የተለመደ ነው። ይህም በሽታ በይበልጥ በሴቶች ላይ ይታያል። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ሴቶች ከወንዶች ይልቅ በታይሮይድ ችግር የመጠቃት እድላቸው ከ5 እስከ 8 እጥፍ የላቀ ነው። ከስምንት ሴቶች አንዷ በሕይወት ዘመኗ የታይሮይድ ችግር ያጋጥማታል ተብሎ ይታሰባል። ይህ በሽታ በሴቶች ላይ በብዛት የሚታይባቸው ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡- የሆርሞን ለውጥ ፦ የሴቶች የታይሮይድ ዕጢ ከ ሴት ልጅ ኢስትሮጅን (Estrogen) ሆርሞን ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለው። ለዚህም በጉርምስና፣ በወር አበባ ዑደት፣ በእርግዝና እና ማረጥ (Menopause) ወቅት የሚፈጠሩ ከፍተኛ የሆርሞን መለዋወጦች ለታይሮይድ መዛባት መንስኤ ይሆናሉ። የሰውነት መከላከያ ሥርዓት ፦ ሴቶች በተፈጥሮ ጠንካራ የመከላከያ ሥርዓት ቢኖራቸውም፣ ይህ ሥርዓት ተሳስቶ የራሳቸውን አካል የሚያጠቃበት ዕድል በሴቶች ላይ ይበልጣል። ለዚህም ሀሺሞቶ (Hashimoto's) እና ግሬቭስ (Graves') የተባሉት የታይሮይድ በሽታዎች ተጋላጭነታቸው ያየለ ነው። ከወሊድ በኋላ የሚመጣ ለውጥ፦ በእርግዝና ወቅት የታይሮይድ ስራ ይጨምራል። ብዙ ሴቶች ከወለዱ በኋላ ባለው አንድ ዓመት ውስጥ የታይሮይድ ዕጢ እብጠት ወይም መዛባት (Postpartum thyroiditis) ሊያጋጥማቸው ይችላል። በዘር መተላለፍ፦ በሴቶች ላይ የሚገኘው የኤክስ ክሮሞሶም (X chromosome) ከሰውነት መከላከያ ሥርዓት ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ ለታይሮይድ ችግር የመጋለጥ እድላቸውን ከወንዶች የበለጠ ያደርገዋል። የታይሮይድ ሆርሞን መዛባት ችግሮች ታይሮይድ እጢ የሚያመርተው የታይሮይድ ሆርሞን ምርት በተለያዩ በሽታዎች እና እክሎች የተነሳ ሊዛባ ይችላል። የዚህም ሆርሞን ማነስ ወይም መብዛት መላ ሰውነት ላይ የሚያሳድረው ከፍተኛ ተጽእኖ አለው። ለዚህም ምልክቶቹም ይለያያሉ። የታይሮይድ ሆርሞን ማነስ ካጋጠመ በህክምናው ሃይፖታይሮይዲዝም (Hypothyroidism) ይባላል። ይህ ካለብዎ የሚከተሉት ምልክቶችን ሊያዩ ይችላሉ።  ከፍተኛ ድካም፣ የሰውነት ክብደት መጨመር፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ቅዝቃዜን አለመቻል፣ የምግብ መፈጨት መዘግየት እና የመደበት ስሜት ሊያስተውሉ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ብዙ ጊዜ "ከእድሜ ጋር የመጣ ድካም" ተብሎ በቸልታ ይታለፋል። ይህ ሊስተካከል ይገባል። የታይሮይድ ሆርሞን ሲበዛ ፤ ሃይፐር ታይሮይዲዝም (Hyperthyroidism) ይባላል። ይህን ጊዜ   ሰውነታችን ብዙ ኃይል ስለሚኖረው/ስለሚያገኝ አለልክ ሊፈጥን ወይም ሊሮጥ ይችላል። በሽታው ካለብዎ፦  ያለምክንያት ክብደት መቀነስ፣ የልብ ትርታ መጨመር፣ ሙቀት አለመቻል ከፍተኛ ላብ እና ጭንቀት ሊስተዋል ይችላል። ይህም ብዙ ጊዜ እንደ "ተራ የኑሮ ውጥረት" ተደርጎ ይወሰዳል። ታማሚዎችም ቢያርፉ እንደሚሻላቸው ሰው አብዝቶ ይመክራቸዋል። እውነታው ግን ከዚህ የራቀ ነው። የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ የታይሮይድ በሽታ የራሱ የሆነ መልክ አለው። በኢትዮጵያ የታይሮይድ ዕጢ (እንቅርት) እና የአዮዲን እጥረት አሁንም ድረስ በከፍተኛ ደረጃ የሚታዩ የጤና እክሎች ናቸው። በቅርብ ጊዜ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ዕድሜያቸው ከ6 እስከ 12 ዓመት ከሆኑ 10 ሕፃናት አራቱ ላይ የእንቅርት በሽታ ይስተዋላል። ይህም ችግሩ “በጣም አሳሳቢ” ደረጃ ላይ እንደሆነ ጠቋሚ ነው። ችግሩ በተለይ በኦሮሚያ (46.7%)፣ በደቡብ (44.22%) እና በአማራ (41.86%) ክልሎች በስፋት ይታያል። ይህም ከአፈር መሸርሸር እና ከአመጋገብ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው። ከሚታከሙ ታካሚዎች መሀከል ወደ 61 በመቶ የሚጠጉት የሆርሞን መብዛት ችግር ሲኖርባቸው 34.3% ሆርሞን ማነስ ችግር አላቸው። ባይታከምስ? የታይሮይድ ችግር የመልክ ወይም የክብደት ጉዳይ ብቻ አይደለም። የታይሮይድ እክክሎች በአካልም ሆነ በስነ-ልቦና ላይ የሚያደርሱት ተፅዕኖ በጣም ሰፊ ነው። ሳይንሳዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ካልታከመ፦ ለልብ እና ለኮሌስትሮል ችግር ያጋልጣል፦ በተለይ የታይሮይድ ሆርሞን ማነስ የልብ ምትን በመቀነስ እና "መጥፎ" የተባለውን ኮሌስትሮል (LDL) በመጨመር ለልብ ድካም እና ለደም ቧንቧ መጥበብ ምክንያት ሊሆን ይችላል። የአጥንት ጤናን ያውካል፦ በተቃራኒው ደግሞ የታይሮይድ ሆርሞን ከመጠን በላይ መመረት ባለው እጅ አዙር ተጽእኖ አጥንት እንዲሳሳ ያደርጋል። ለስነ-ልቦና ቀውስ ይዳርጋል፦ የታይሮይድ ሆርሞን መዛባት በአንጎል ውስጥ ያሉ ስሜትን የሚቆጣጠሩ ውህዶችን (Neurotransmitters) ስለሚያዛባ፣ ለከፍተኛ ጭንቀት፣ ለድብርት እና ለትኩረት ማጣት ይዳርጋል። ይህም የእለት ተእለት ኑሮን እና ማህበራዊ ቁርኝትን ያስተጓጉላል። ከእነዚህም በተጨማሪ የታይሮይድ ችግር ካልታከመ ፤ ለመሃንነት ወይም በእርግዝና ወቅት ፅንስ ለመቀነስ አደጋ ሊያጋልጥ ይችላል። መፍትሄው ምንድነው? የሚያስገርመው ነገር፣ ለዓመታት ለተሰቃዩበት ጥያቄ መልሱ አንድ ቀላል የደም ምርመራ ነው። ይህም የቲኤስ ኤች ወይም የታይሮይድ ምርመራ (TSH Test) ነው። ይህ ምርመራ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በስፋት ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ ሐኪምዎ የአንገት አልትራሳውንድ እና ሌሎች የደም ምርመራዎችን ሊያዝልዎት ይችላል። በእነዚህ ምርመራዎች ላይ ተመስርቶ ፤ የሚዋጥ መድሀኒት እንዲሁም የቀዶ ጥገና ሕክምና ሊያስፈልግዎ ይችላል። ያስተውሉ! የሚደክምዎ አልያም ውጥረት የሚያሰቃይዎ በእርስዎ ጉድለት ላይሆን ይችላል። የታይሮድ እጢዎን ይመርመሩ። ምልክቶቹን ካዩ የህክምና እርዳታ ይፈልጉ። ሕክምናውም ቀላል እና እጅጉን ውጤታማ ነው። ዛሬውኑ እርምጃ ይውሰዱ። ለጤናዎ ቅድሚያ ይስጡ!

  • ልቧ ከሷ ቀድሞ ዝሎ ነበር! የራሂማ ታሪክ

    ልጅነት ተጫውቶ ፣ ተሯሩጦ ከ እድሜ እኩዮች ጋር ተሳስቆ የሚታለፍ እጅጉን ደስ የሚል ጊዜ ቢሆንም ፤ ሁሉም ልጆች ለዚህ አልታደሉም። እንደ ማንኛውም ሴት ልጅ በትምህርት፣ በሳቅ እና በጨዋታ ታሳልፍ የነበረችው ራሂማም ፤ በጊዜ በሂደት ውስጥ ቶሎ መዝለልና መጫወት አቃታት። እርምጃ ከበዳት። ትንፋሽም እያጠራት መጣ። ከአመታት በፊት ቶንሲል አሟት ቢያቅም፤ ሀኪም ቤት ሄዳ አልታከመችውም ነበር። ህመሙ ድንገት የጀመረበት የሚታወቅ ቅጽበት የለም። በአመታት ውስጥ ችግሩ በዝምታ እያደገ የመጣ ነበር። ህክምና ሄዳ ስትመረመር የግራ ልቧ ቧንቧ ( ሚትራል ቫልቭ (Mitral Valve) ) ከባድ ጉዳት ላይ እንዳለ ተነገራት። ገና በአስራ አራት አመቷ የልቧ ቧንቧ ስራውን በስርአት መስራት ተስኖት ነበር። የራሂማም ታሪክ የብዙ ኢትዮጵያውን ህጻናት ታሪክ ነው። እሷ ብቸኛ አይደለችም። ብዙዎች ሳይታወቅ እየተሰቃዩ ነው። የልብ ቧንቧ በሽታ ምንድነው? የሰው ልጅ ልብ አራት ቧንቧዎች አሉት። እነዚህ ጡንቻዎች አይደሉም፤ የደም ሥሮችም አይደሉም። እነኝህ የደም ፍሰትን የሚቆጣጠሩ በሮች ናቸው። አራቱ የልብ ቧንቧዎች፡ ብርማ መልክ ያላቸው የልብ ቧንቧዎች ናቸው። ልብ በመታ ቁጥር እነዚህ ቧንቧዎች በትክክለኛው ጊዜ ይከፈታሉ፣ ይዘጋሉ። ይህም ደም ወደፊት ብቻ እንዲፈስ ይረዳል። እነዚህ ቧንቧዎች ስራቸው ሲስናከል ፤ የደም ዝውውር ይስተጓጎላል። ልብም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲለፋ ይገደዳል። በሂደትም ልብ ይደክማል። መላው አካል ይዝላል። ይህ ሁኔታ የልብ ቧንቧ በሽታ (Heart Valve Disease) ይባላል። የልብ ቧንቧ በሽታ ስርጭት ምን ይመስላል? በዓለም አቀፍ ደረጃ የሕክምና መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ50 ሴቶች ውስጥ አንዷ የልብ ቧንቧ በሽታ ይኖርባታል። እድሜ በገፋ ቁጥር ስርጭቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። ዕድሜያቸው ከ75 በላይ በሆኑ 10 ሴቶች ውስጥ በአንዷ ላይ ይህ በሽታ ይታያል። ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ሌላ ገጽታ አለው። ለምን? በኢትዮጵያ ይህ በሽታ የሚጀምረው በለጋ እድሜ ላይ ነው። በተቀረው የአለም ክፍልይህ በሽታ የሚመጣባቸው ዋነኛ ምክንያቶች ውስጥ ከእድሜ ጋር የተያያዙ የልብ ቧንቧ ለውጦች (Age related degenerative valvular changes) ነው። በኢትዮጵያ የዚህ ዋነኛ መንስኤ ያልታከመ የጉሮሮ ኢንፌክሽን አልያም የቶንሲል በሽታ ነው። የኢትዮጵያ የልብ ማዕከል (Cardiac Centre of Ethiopia) ከተመዘገቡ የልብ ቧንቧ ታካሚዎች መሀከል ከፍተኛ መጠኑን ( 59.2%) የሚወስዱት ሴቶች ናቸው። ስለ በሽታው ሂደት እና አመጣጥ በደንብ ለመረዳት ከዚህ በፊት የጻፍነውን እዚህ ያንብቡ ። የሚትራል ቧንቧ ችግር ምንድነው? ከሁሉም የልብ ቧንቧ ችግሮች መካከል አንዱ በተለይ በሴቶች ላይ ጎልቶ ይታያል። ይህም የ ሚትራል ቧንቧ ችግር ነው ። ይህ ቧንቧ በግራ የልብ ክፍል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ የላይኛውን የልብ ክፍል (Atrium) ከታችኛው (Ventricle) የሚለይ ነው። ከሳንባ ኦክስጅን ይዞ የመጣው ደም፣ ወደ ዋናው ደም መርጫ ክፍል የሚያደርገውን ፍሰት ይቆጣጠራል። በስተ ግራ በኩል የላላል የሚትራል ቧንቧ ፤ በስተቀኝ በኩል የጠበበ የሚትራል ቧንቧ ይታያል የዚህም ቧንቧ ችግር በሴቶች ላይ በይበልጥ ይታያል። የሚትራል ቧንቧ መጥበብ (Mitral stenosis) በሴቶች ላይ ከወንዶች በ 3 እጥፍ ይገኛል። የቧንቧው መላላትም (Mitral regurgitation) በሴቶች ላይ በብዛት ይታያል። ቧንቧው ሲጠብ ፤ የደም መተላለፊያው ስለሚዘጋ/ስለሚጠብ የደም ዝውውር ይገደባል። ቧንቧው ሲላላ በበኩሉ ፤ አጥብቆ አይዘጋም። ለዚህም በትክክል ስላልተዘጋ ደም ወደ ኋላ ይመለሳል። ለምን የሚትራል ቧንቧ ችግር በይበልጥ ሴቶችን ያጠቃል? ሴቶች ውስጥ የሚገኘው ኢስትሮጅን (estrogen) የተባለው ሆርሞን የተጎዳው የቧንቧ ክፍል ይበልጥ እንዲወፍርና እንዲጠብ በማድረግ የበሽታውን ሂደት ሊያፋጥነው ይችላል። በተጨማሪም፣ የሴቶች የልብ ቧንቧ አነስተኛ መጠን ያለው በመሆኑ መጠነኛ የሆነ የጠባሳ መኖር እንኳ የቧንቧ መጥበብን (mitral stenosis) እና የጤና መታወክን ቀድሞ ያስከትላል። ይህ ቧንቧ በልብ ውስጥ ከፍተኛውን የደም ግፊት የሚቋቋም ስለሆነ ፤ በበሽታው ምክንያት የሚፈጠር ጠባሳ በፍጥነት ይህንን ቧንባ ይጎዳል። ምልክቶቹ የልብ ቧንቧ በሽታ ሲጀምር ምልክት አያሳይም። ለውጦች በዝግመት ነው የሚመጡት። ከተለመዱ ምልክቶቹ መሀከል። ያልተለመደ ድካም በእንቅስቃሴ ወቅት የትንፋሽ ማጠር የልብ ምት መዛባት ማዞር ወይም ራስን መሳት የእግር ወይም የሆድ እብጠት ከእነዚህ ምልክቶች ባሻገር፣ እንደ ተጠቃው የልብ ቧንቧ ዓይነት የሚታዩ የተለዩ ምልክቶች ሊኖሩ ይችላሉ ለምሳሌ ፦ የሚትራል ቧንቧ ከጠበበ የድምፅ መጎርነን ሊኖር (Hoarseness) ይችላል። የልብ የላይኛው ክፍል ሲያብጥ ድምፅን የሚቆጣጠሩ ነርቮችን ስለሚጫን ይፈጠራል። ደም የተቀላቀለ አክታ (hemoptysis) ሊኖር ይችላል። ይህም ሳንባ ላይ የደም ግፊት በጣም ስለሚጨምር ጥቃቅን የደም ስሮች ፈንድተው ደም የተቀላቀለ አክታ ሊታይ ይችላል። ጉንጮች ሊቀሉ ይችላሉ። የሚትራል ቧንቧ ከላላ ደግሞ እነኝህን ምልክቶች ሊስተዋሉ ይችላሉ። ሌሊት ሌሊት ለሽንት መነሳት ፦ ልብ ደምን በትክክል መግፋት ስለሚሳነው ሰውነታችን የተጠራቀመውን ፈሳሽ ለመቀነስ ሌሊት በተደጋጋሚ ሽንት እንዲመጣ ያደርጋል። በእንቅልፍ መሃል ታፍኖ መንቃት (PND)፦ በእንቅልፍ መሀል በድንገት ትንፋሽ አጥሮዎት የሚቀሰቅስ የትንፋሽ እጥረት። ራስን የመሳት ስሜት ፦ ደም ወደ ኋላ ስለሚመለስ ወደ ጭንቅላት የሚሄደው የደም መጠን ቀንሶ የማዞር ወይም የመሳት ስሜት ሊፈጥር ይችላል። እንዴት ይመረመራል? ለዚህ በሽታ ቅድመ ምርመራ ወሳኝ ነው። ሐኪሞች በመጀመሪያ በስቴቶስኮፕ ያልተለመደ የልብ ድምፅ (Murmur) መኖሩን ያዳምጣሉ። ከዚህ ባሻገር የተለያዩ ምርመራዎችን ሊያዙ ይችላሉ። በሽታውን ለማረጋገጥ ዋነኛው ምርመራ ግን ኢኮካርዲዮግራፊ (የልብ አልትራሳውንድ) ነው። እንዴት ይታከማል? የዚህ በሽታ ሕክምናው እንደ ደረጃው ይወሰናል፦ በመጀመሪያ ደረጃ፦ በሽታው ያለበት ደረጃ ቀላል ከሆነ ፤ የልብ ቧንቧ ጉዳት የልብ ስራን በጣም ካላስተጓጎለ ፤ ምልክቶችን ለመቆጣጠር እና የልብ ሸክምን ለመቀነስ መድኃኒቶች ሊሰጡ ይችላሉ። መድሐኒትዎን እየወሰዱ የህክምና ክትትል ሳያቋርጡ መከታተል ይመከራል። በከፍተኛ ደረጃ፦ ቧንቧው በከፍተኛ ሁኔታ ከተጎዳ ፤ የልብ ስራ እጅጉን ከተሰናከለ ይህን ጊዜ አማራጩ የቀዶ ጥገና ህክምና ይሆናል። ይህን ጊዜ የልብን ቧንቧ መጠገን አልያም የተጎዳውን ቧንቧ በአርተፍሻል ቧንቧ መቀየር አስፈላጊ ሆኖ ይገኛል። ይህ ህክምና ህይወት አድን ነው። የተግባር ታሪክ ድርጅታችን ተግባር በጎ አድራጎት (Tegbar Organization) በሚያደርገው የማያቋርጥ ጥረት ይህንን አስከፊ እውነታ ለመለወጥ እየሰራ ይገኛል። በድልም እየቀየረው ይገኛል። ልቧ ከመቆሙ በፊት ደርሰንላታል። ራሂማም በአጋራችን ሂሊንግ ቫልቭስ ኢትዮጵያ (Healing Valves Ethiopia)በኩል ከድርጅታችን ጋር በመገናኘቷ፤ የሚያስፈልጋትን የሕይወት አድን ቀዶ ጥገና ለማግኘት በቅታለች። በታዋቂው የልብ ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ዶ/ር ፈቀደ አግዋር የተመራውና ለ4 ሰዓታት የፈጀው አስደናቂ ቀዶ ጥገና፣ ለራሂማ ሁለተኛ የሕይወት ንጋትን ሰጥቷታል። ይህ ስኬት ግን የኛ ብቻ ውጤት አይደለም፤ የአጋሮቻችን፣ የርኅሩኅ ለጋሾቻችን እና የሁላችንም የጋራ የድል አሻራ ነው! እንኳን ደስ አለን! ማሳረጊያ ምክር ብዙዎቹ የልብ ቧንቧ በሽታዎች — በተለይም በኢትዮጵያ — መከላከል የሚቻሉ ናቸው። ለዚህም የጉሮሮ ኢንፌክሽንን እንዲሁም ቶንሲልን ቀድመው ያክሙ። መደበኛ ምርመራ ያድርጉ። ያስተውሉ! የልብ ቧንቧ በሽታ በድንገት አይጀምርም። የሚጀምረው በዝምታ፣ በትንንሽ ለውጦች እና ረቂቅ ምልክቶች ነው። ለጤናዎ ዛሬውኑ ቦታ ይስጡ!

  • ታመው ካልተኙ ሆስፒታል አይሄዱም?

    አያድርገውና ! ድንገት ያላሰቡት ቀን... በሩን ሳይሰበር ፣ ድምጽ ሳያሰማ አንድ ሌባ መኖርያ ቤትዎ ገብቶ ቢደበቅስ? እርስዎ በተኙበት ፤ አልያም ቤት በሌሉበት ሰአት ንብረትዎን ለመስረቅ ፤ እርስዎን ሊያጠቃ ይህ ሌባ አድብቷል እንበል። እድለኛ ሆነው ድንገት ካላዩት በስተቀር ፤ መኖሩን የሚጠቁም ምንም ምልክት የለም። ምንም ድምጽ የለም። እርስዎ የሆነ ነገር መበላሸቱን የሚረዱት ንብረትዎ ሲጎድል ፤ አልያም ጥቃት ሲደርስብዎ ብቻ ነው። እና ምን ተሻሎት!? "ኧረ አንድ በሉት ይሄ ሰው ተነሳ!" ብለው ባለቅኔ እና ገጣሚ ከበደ ሚካኤል ግጥማቸውን እንዳሳረጉት ፤ እርሶም አርፍደው ቢያውቁ ምን ይበጅዎ!? ቢሆንማ.... ቀድሞ ቢነቁ ፤ ሌባውን ቢይዙ ፤ ንብረቶን ባላጡ እርሶም ባልተጎዱ ነበር። ዛሬ የምናወራው ስለ ቅድመ ምርመራ ነው። ብዙ ከባድ በሽታዎች የመጀመሪያው የህመም ምልክት ከመታየቱ በፊት ለዓመታት በሰውነት ውስጥ በዝምታ ይኖራሉ። እንደሌባው ያደባሉ። ተደብቀው ጊዜ ይጠብቃሉ። ሕመሙን ያስተዋሉ ጊዜ ግን ቀድሞውኑ ጉዳቱ የከፋ ሊሆን ይችላል። በሕክምናው ይህንን በሽታው አድብቶ የሚቆይበትን ጊዜ ምልክት የለሽ ምዕራፍ (Asymptomatic phase)  እንለዋለን። በአለም ዙሪያ ብዙሀን ለረዥም ጊዜ ሆስፒታል ለመሄድ ፤ ሕመሙ ከአቅም በላይ እስኪሆን ይጠብቁ ነበር። በቅርብ አመታት ግን ለውጥ ይታያል። ሆኖም ብዙ ኢትዮጵያውያን ህክምና ፍለጋ የሚሄዱት ፤ በሽታው ከደረጀ ፤ ከባድ ጉዳት ካደረሰ በኋላ ነው። ለዚህም በኢትዮጵያ ስር ሰደድ ህመሞች እና ካንሰሮች የሚገኙት አስጊ ደረጃ ላይ ነው። የቅድመ ምርመራ ታሪክ ፡ ከፍርሃት ወደ አርቆ አስተዋይነት ዘመናዊው የቅድመ ምርመራ ሀሳብ የተጀመረው በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ነው። ይህን ጊዜ ላይ ሳይንቲስቶች በሽታ የሕመም ምልክት ከመሳየቱ በፊት ሊታወቅ እንደሚቻል ተገነዘቡ። ለዚህም ቀድሞ በሽታውን ማግኛ ዘዴዎችን መመራመር ጀመሩ። ከመጀመሪያዎቹ ስኬቶች አንዱ በ ዶክተር ጆርጅ ፓፓኒኮላው የተዘጋጀው የ ፓፕ ስሚር (Pap smear) ምርመራ ነበር። ይህ ቀላል ምርመራ የማህጸን ጫፍ ካንሰር ከመፈጠሩ በፊት ለመያዝ አስቻለ። የማህጸን ጫፍ ህዋሳት የሚያሳዩትን ቅድመ ካንሰር ለውጦች በምርመራ ለመለየት ተቻለ። ይህም በዓለም ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን አድኗል ፤ የጤና ምህዳራቸውንም አሻሽሏል። ከጊዜ በኋላ ቅድመ ምርመራ ወደ ሌሎች የጤና ሁኔታዎች ተስፋፋ። ለምሳሌ ፦ ለደም ግፊት ለስኳር በሽታ ለስር የሰደደ የኩላሊት ህመም ለጉሮሮ ካንሰር አዲስ ለተወለዱ ሕፃናት የሚደረጉ ሜታቦሊዝም(ሰውነት ኡደት) ምርመራዎች፣ ወ.ዘ.ተ... ይውል ጀመር። የማህበረሰብ ጤና ሳይንስም እጅጉን ተለወጠ። ሕመም እስኪመጣ ከመጠበቅ በሽታን ቀድሞ ወደ መፈለግ ተቀየረ። ከተሰረቁ በኋላ ከማወቅ ሌባውን ቀድሞ ወደ መያዝ ተሸጋገረ። ኢትዮጵያም ይህንን በከፍተኛ ሁኔታ እየተገበረች ትገኛለች። ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እጅጉን በመስፋፋታቸው ፤ ጤና ጥበቃ እና ባለድርሻ አካላትም ቅድመ ምርመራ ላይ በትጋት እየሰሩ ይገኛሉ። ለምሳሌ በማህጸን ጫፍ ካንሰር ዙሪያ ኢትዮጵያ ታላላቅ ዘመቻዎች አካሂዳለች። በ 3 ወራት ጊዜው ስጥ ብቻ ከ275,000 በላይ ሴቶች ተመርምረው፤ ከ13,000 በላይ የቅድመ ካንሰር ምልክቶች የታዩባቸው ሴቶች ወዲያውኑ ሕክምና እንዲያገኙ ተደርጓል። ይህም የአስራ ሶስት ሺ ሴቶችን ህይወት ማዳን ተችሏል ማለት ነው። ከማህጸን ጫፍ ካንሰር ባሻገርስ? ከካንስር ህመሞች ባሻገር ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ (CKD) እየተስፋፋ ይገኛል። ስሙን ለይተው ባያውቁትም ፤ መቼም ስለ እርሱ ሰምተዋል። ለብዙዎች የኩላሊት ድክመት መሰረት ነው። በየቀኑ በግምት ከ150 ሊትር በላይ ደም የሚያጣሩ እና ቆሻሻን የሚያስወግዱ ኩላሊቶች ፤ በመታት ውስጥ እየተዳከሙ ይመጣሉ። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ፤ ኩላሊቶች ምንም አይነት ምልክት ሳያሳዩ እስከ 90% የሚሆነውን ተግባራቸውን ሊያጡ ይችላሉ። ይህ ማለት ብዙ ሰዎች ኩላሊታቸው እጅጉን እየተጎዳ ቢሆንም ፤ ሙሉ በሙሉ ጤናማ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ኩላሊት ስራው እስኪሰናከል ድረስ ምንም ምልክት አያስተውሉም። ለዚህም በሽታ መስፋፋት በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ዙሪያ ዋነኛ መንስኤ ተደርገው የሚጠቀሱት በሽታዎች እነዚህ ናቸው። ፦ ከፍተኛ የደም ግፊት (Hypertension) የስኳር በሽታ (Diabetes mellitus) አንዳንድ ኢንፌክሽኖች እና ያልታከሙ ስር የሰደዱ በሽታዎች ይህንን በሽታ ቀድሞ ለማወቅና ኩላሊትን ለማትረፍ ቅድመ ምርመራ እጅጉን አስፈላጊ ነው። ያለ ቅድመ ምርመራ፣ የኩላሊት በሽታ ብዙ ጊዜ የሚታወቀው የኩላሊት ሥራ እጅጉን ከተዳከመ በኋላ ነው። ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የኩላሊት ቅድመ ምርመራ የሚያደርገው የማህበረሰብ ክፍል አነስተኛ ነው። እናስ ምን ተሻለ? "ጤነኛ ነኝ" ከሚል ስሜት በትክክል ጤነኛ ወደ መሆን ለመሸጋገር ፤ የጤና አገልግሎት ወደ ማህበረሰቡ መዳረስ ይኖርበታል። ይህንንም ለማዳረስ የቅድመ ምርመራ ዘመቻዎች ያስፈልጋሉ። እነዚህ ዘመቻዎች ካልታመመ ለማይሄደው ፤ "ኩላሊቴ ጤናማ ነው!" ብለው አስበው ለሚቀመጡት ብዙሀን እጅግ ያስፈልጋሉ። ይህንንም ለማዳረስ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እየሰሩ ይገኛሉ። ያለፈው መጋቢት 3 የተግባር በጎ አድራጎት ድርጅት ከ ኢትዮጵያ ኪድኒ ኬር (Ethipian kidney Care) ከጊቭ ሶሳይቲ ኢትዮጵያ (GIV Society Ethiopia)፣ ከ አደይ ሮታራክት ክለብ (Rotaract Club of Adey) እና ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የኩላሊት ቅድመ ምርመራ ዘመቻ አካሂዷል። እንዲህ ዓይነቱ መርሐ ግብር ኩላሊትን ጤና ከመመርመር ባሻገር ፤ ቀደምት የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ለመለየት የሚያስችሉ አስፈላጊ ምርመራዎችን ያቀርባል። እንደ ደም ግፊት እና ስኳር ያለባቸው ፤ እንዲሁም የኩላሊታቸው የማጣራት አቅም እየተዳከመ ያሉ ግለሰቦችንም ለመለየት ተችሏል። ተጋላጭነት ያለባቸው ሰዎች የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ እንዲያሳዩ ተመክረዋል። ኩላሊታቸው ለውጥ ላሳዩት ደግሞ ፤ ከአኗኗር ምክር ባሻገር አስፈላጊው የህክምና እርዳታ እና ክትትል እንዲጀምሩ ተደርገዋል። ያስተውሉ! ቅድመ ምርመራ ለታመሙ ሰዎች ብቻ አይደለም ፤ ለአስተዋዮችም ነው። ምርጡ የህክምና አማራጭ ቀዶ ጥገና ወይም መድኃኒት አይደለም። ብዙ ጊዜ ቅድመ ምርመራ ማድረግ ይሻላል። የኩላሊት ቅድመ ምርመራ ለነማን ያስፈልጋል? ምንም እንኳን ሁሉም ሰው መመርመሩ መልካም ቢሆንም፣ የሚከተሉት ሰዎች ግን በየዓመቱ ምርመራ ቢያደርጉ ይመከራል፦ የስኳር ሕመምተኞች፦ ስኳር የኩላሊት ትንንሽ የደም ስሮችን ስለሚጎዳ። የደም ግፊት ያለባቸው፦ ከፍተኛ ግፊት ኩላሊት ላይ ጫና ስለሚፈጥር። ከመጠን በላይ ውፍረት ያላቸውና የልብ ሕመም ያለባቸው። በቤተሰባቸው ውስጥ የኩላሊት ሕመም ያለባቸው። ዕድሜያቸው ከ60 በላይ ለሆነ ። የህመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን (NSAIDs እንደ Ibuprofen/Diclofenac ያሉ) አዘውትረው የሚጠቀሙ። እንዴት የቅድመ ምርመራ ማድረግ ይችላሉ? ኩላሊት መጎዳቱን ለማወቅ ውድና ውስብስብ ምርመራ ሁልጊዜ አያስፈልግም። ይህንን በሁለት ቀላል መንገዶች ማረጋገጥ ይቻላል፦ የሽንት ምርመራ (Urine Test)፦ በሽንት ውስጥ ፕሮቲን (Albumin) መኖሩን ማየት። ፕሮቲን በሽንት መውጣቱ የኩላሊት ማጣሪያዎች መጎዳታችውን/መሳሳታቸውን የሚያሳይ የመጀመሪያው ምልክት ነው። የደም ምርመራ (Creatinine/eGFR)፦ በደም ውስጥ ያለውን የቆሻሻ መጠን በመለካት ኩላሊት በምን ያህል አቅም እያጣራ እንደሆነ ያሳያል። ከቅድመ ምርመራ ባሻገርስ ምን ላድርግ? ሌባው እንዳይገባ በሩን መቆለፍ እንደሚቻለው ሁሉ፣ ኩላሊትንም በእነዚህ መንገዶች መጠበቅ ይቻላሉ፦ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መድኃኒቶችን አይውሰዱ፦ በተለይ የህመም ማስታገሻዎች (እንደ Diclofenac, Ibuprofen ያሉ) በብዛት መውሰድ ኩላሊትን ክፉኛ ይጎዳል። ጨው መቀነስና ውኃ አብዝቶ መጠጣት ይመከራል፦ ይህ የደም ግፊትን ለመቆጣጠርና ኩላሊት ስራውን እንዲያቀላጥፍ ይረዳል ። ስኳርንና ግፊትን መቆጣጠር ይኖርብዎታል፦ ይህ ለኩላሊት ጉዳት የሚያጋልጡ ዋናዎቹን መንስኤዎች በማከም ኩላሊት ያለበት ጉዳት እንዳይባባስ ያደርጋል። በኢትዮጵያ የዲያሊሲስ (Dialysis) ወይም የኩላሊት ንቅለ ተከላ (Transplant) ወጪና ተደራሽነት እጅግ አስቸጋሪ መሆኑ፣ ቅድመ ምርመራ ብቸኛውና አስተማማኙ አማራጭ ያደርገዋል። አሁን ተራው የእርስዎ ነው! እስቲ ራስዎን ይጠይቁ 'የመጨረሻ ጊዜ የደም ግፊት፣ ስኳር ወይም የኩላሊት ምርመራ መቼ አደረጉ?' ምርመራውን ዛሬውኑ በማድረግ ራስዎን እና ቤተሰብዎን ከከፍተኛ የሕክምና ወጪ እና ከሥነ-ልቦና ስብራት ይታደጉ። "ቅድመ ምርመራ ለአስተዋዮች ነው!"

  • ሰዎች በድንገት ለምን ይሞታሉ?

    " ትላንት ደህና ነበር… " ይህ አረፍተ ነገር በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ብርቅ አይደለም። የብዙዎቻችንን ቤት ያንኳኳ፣ በሐዘንና በግራ መጋባት መሃል የምንደጋግመው መርዶ ነው። ትዕይንቱን በዓይነ ሕሊናዎ ይሳሉት፦ አንድ ሰው ውሎውን እንደወትሮው በሥራ ያሳልፋል። ከጓደኞቹ ጋር በሳቅ ተጫውቶ ይለያያል። ማምሻውን ደግሞ ከቤተሰቡ ጋር እራት ተመግቦ፣ መልካም ሌሊት ተመኝቶ ወደ አልጋው ያመራል። በማግስቱ ግን ዓለም ትገላበጣለች። በመንደሩ ውስጥ መርዶው እንደ ሰደድ እሳት ይሰራጫል፦ “አልጋው ላይ እንደሞተ ተገኘ!” ምንም ዓይነት አደጋ አልደረሰም። የሚታወቅ ሕመምም አልነበረም። አስቀድሞ የሰጠው ማስጠንቀቂያም ሆነ የተናዘዘው ኑዛዜ የለም። በቃ፣ በድንገት “ተወሰደ።” ለቤተሰቦች ይህ ቅጽበት ልብ ሰባሪ ነው። ለማኅበረሰቡ ደግሞ አንድ የሚያስጨንቅ ጥያቄ ይጭራል፦ ትላንት ጤነኛ መስሎ የታየ ሰው፣ ዛሬ እንዴት በድንገት ሊሞት ይችላል? ከሰማይ የወረደ ድንገተኛ መቅሰፍት ወይስ የጤና ቀውስ? ብዙዎቻችን ይህንን ክስተት ከዕጣ ፈንታ ወይም ከማይታወቁ ምስጢራት ጋር እናያይዘዋለን። በሕክምናው ዓለም ይህ ክስተት “ድንገተኛ ሞት” (Sudden Death) ይሰኛል። ይህም አንድ ጤነኛ የሚመስል እና የተረጋጋ ግለሰብ በ24 ሰዓታት ውስጥ፣ ወይም ምልክቶች በታዩ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የሚከሰት ያልተጠበቀ ሞት ነው። እውነታው ይሄ ነው፦ ይህ ክስተት ምስጢራዊ አይደለም። ሳይንስ ከጀርባው ያሉትን መንስኤዎች ጠንቅቆ ያውቃቸዋል። እነዚህን መንስኤዎች መረዳት ደግሞ ይህንን ለመታደግ ብቸኛው መንገድ ነው። በምን ይከሰታል? ድንገተኛ ሞት ያለ ምክንያት አይመጣም። “ደህና ነበር” ያልነው ሰው ከጀርባ ለሞት የሚያጋልጡ መንስኤዎች ይኖሩታል። ሆስፒታል ሄዶ አይመርመር እንጂ ፤ የማይታወቅ በሽታ ኖሮበት ሊሆን ይችላል። እነኝህ መንስኤዎች በዝምታ ተከስተው ፤ ህይወትን ይነጥቃሉ። ይህንን ከሚያስከትሉ መንስኤዎች ውስጥ ዋነኛ የሚባሉት አምስቱን እንመልከት። 1. ድንገተኛ የልብ መቆም ይህ በጣም የተለመደ ምክንያት ሲሆን ፤ አዋቂዎች ላይ ከሚከሰቱ ድንገተኛ ሞቶች ውስጥ ከ80–90% ለሚሆኑት ምክንያት እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ይህንም ከልብ ቧንቧዎች መጥበብ/መዘጋት እስከ ልብ አመታት ለውጥ/፣መዛባት (arrhythmia) ሊያመጡት ይችላሉ ። ልብም በድንገት ደምን የመርጨት ሥራውን ያቆማል። ይህን ጊዜ በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ ፤ ወደ አንጎል የሚሄደው የደም ፍሰት ይቆማል።ለዚህም ራስዎን ይስታሉ። ካልታከመ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሞት ይከተላል። ይህ በድንገት እስኪከሰት ድረስ ግለሰቡ ምንም ዓይነት ግልጽ ምልክት ላያሳይ ይችላል። 2 . ያልታወቀ የልብ ሕመም አንዳንድ ሰዎች የልብ ጡንቻ ችግሮች (Cardiomyopathy) ወይም የተፈጥሮ የልብ ቅርጽ መዛባት ሊኖርባቸው ይችላል። አንዳንዶች ይህን ችግር ይዘው ይወለዳሉ። ይህ ችግር እንደ ተቀበረ ፈንጂ ነው። ለዓመታት ምንም ዓይነት ሕመም ሳያሳይ ይቆያል። ታድያ አንድ ቀን በድንገት ለሞት ይዳርጋል። በተለይ በወጣቶች ላይ ለሚከሰት ድንገተኛ ሞት ዋነኛው ምክንያት ይሄው ስውር ጠላት ነው። የካሜሮን ተጫዋቹ ፎኤ (Foe) እናሌሎች አትሌቶችም ለዚህ ተጠቃሽ ሊሆኑ ይችላሉ። 3. ስትሮክ ወይም በአንጎል ውስጥ የደም መፍሰስ አንዳንድ ጊዜ ድንገተኛ ሞት የሚከሰተው በአንጎል ውስጥ ያለ የደም ሥር ሲፈነዳ ወይም ሲደፈን ነው። ቁጥጥር ያልተደረገበት ከፍተኛ የደም ግፊት በአንጎል ውስጥ ያለን የደም ሥር በድንገት እንዲፈነዳ ሊያደርገው ይችላል። ይህም በአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ አስከትሎ ሊገድል ይችላል። ስኳር እና የስብ መዛባት ችግሮች በበኩላቸው ወደ አንጎል የሚሄዱ ደምስሮችን በድንገት እንዲደፈኑ ሊያደርጉ ይችላሉ። በዚህም ምክንያት አንጎል ኦክስጅንና ምግብ በማጣቱ ሕዋሳቱ በደቂቃዎች ውስጥ ይሞታሉ። ይህም ግለሰቡን ለህልፈት ይዳርገዋል። 4. የሳምባ ደም መርጋት (Pulmonary Embolism) ይህ ድንገተኛ የሳምባ ደም ስር መዘጋት ነው። ይህ መንስኤ ብዙ ጊዜ አይጠበቅም። በአደጋ፣ በሕመም ወይም ረጅም ሰዓት ባለመንቀሳቀስ ምክንያት በእግር ውስጥ የደም መርጋት (Clot) ሊፈጠር ይችላል። ይህ የረጋ ደም ተላቆ በደም ሥር ውስጥ በመጓዝ ሳምባ ላይ ይደርሳል። እዚያም ዋናውን የደም መተላለፊያ በድንገት ይዘጋዋል። ይህን ጊዜ ሳምባ ኦክስጅን መሳብ ያቅተዋል። ስራውን ያቆማል። ሰውነት ይታፈናል። ልብም ስራዋን ታቆማለች። ይህ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የሚከሰት አደጋ ነው። ህይወትንም በቅጽበት ይነጥቃል። 5. የሰውነት ማዕድናት/ ስኳር ሚዛን መቃወስ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ድንገተኛ ሞት የሚከሰተው የሰውነት ማእድናት መዛባት ጋር ተያይዞ ሊሆን ይችላል። ሰውነታችን እንዲሠራ የደም ውስጥ ማእድናት ሚዛን ያስፈልገዋል። በተለያዩ ምክንያቶች የእነኝህ ማእድናት መጠን ከተቃወሰ ለድንገተኛ ሞት ይዳርጋል። ለዚህም አጋላጭ ምክንያቶች መሀከል ፣ ያልታወቅ ኢንፌክሽን እና ያልታወቀ ኩላሊት በሽታ ሊጠቀሱ ይችላሉ። ከዚህም ባሻገር ሰውነት ውስጥ ያለ የስኳር መጠን በድንገት ሊወርድ/ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል። ይህም ካልተስተካከለ በደቂቃዎች ውስጥ ለሞትሊዳርግ ይችላል። በኢትዮጵያስ ? ከፍተኛ ገቢ ካላቸው አገራት በተለየ በኢትዮጵያ ስለ ድንገተኛ ሞት ያለው የአገራዊ መረጃ ውስን ነው። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የአስከሬን ምርመራ ባህላችን ዝቅተኛ መሆኑና የሞት ምዝገባ ሥርዓታችን አሁንም ድረስ በጅምር ላይ በመሆኑ ነው። ነገር ግን የቅርብ ጊዜ ሳይንሳዊ ጥናቶችና የጤና ባለሥልጣናት ሪፖርቶች ይህንን ይነግሩናል። “ትላንት ደህና የነበረው” ሰው፣ ለዓመታት በዝምታ ሲገነባ የቆየ የጤና ቀውስ ሰለባ ቢሆንስ? ለዚህም ተጠቃሽ ከሚሆኑት ምክንያቶች መሀከል የሚከተሉት ዋነኞች ናቸው። በሀገር አቀፍ ደረጃ የተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እየጨመሩ ነው፦ ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት በኢትዮጵያ የደም ግፊት፣ የልብ ሕመም፣ ስኳር እና ውፍረት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከሚከሰቱ ሞቶች መካከል 43% የሚሆኑት በእነዚህ በሽታዎች ሳቢያ የሚከሰቱ ናቸው። በየሰዓቱ 25 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በልብ ሕመም፣ በስኳርና በደም ግፊት ምክንያት ሕይወታቸውን ያጣሉ የደም ግፊት የተለመደ ቢሆንም ብዙ ጊዜ አይታወቅም፦ ብዙ ኢትዮጵያውያን የደም ግፊት እንዳለባቸው ሳያውቁ ይኖራሉ። ይህም ለድንገተኛ የልብ ሞት ዋነኛው መንስኤ ነው። ለድንገተኛ ስትሮክ ሞትም ተጠያቂ ነው። ትላንት ደህና ነበር” የተባለው ግለሰብ፣ ለዓመታት ያልታወቀ እና ቁጥጥር ያልተደረገበት የደም ግፊት ሰለባ ቢሆንስ? የድንገተኛ ጊዜ እርዳታ ተደራሽነት ውስንነት፦ አንድ ሰው ልቡ በድንገት ሲቆም፣ ሕልውናው በሰከንዶች ውስጥ ይወሰናል። በበለጸጉት አገራት ፈጣን የመጀመሪያ እርዳታ ( CPR ) እና አምቡላንስ ሕይወትን ይታደጋሉ። በኢትዮጵያ ግን አብዛኛው ድንገተኛ ሞት የሚከሰተው ከሆስፒታል ውጭ ነው። አምቡላንሶች እስኪደርሱ ወይም ግለሰቡ ሆስፒታል እስኪገባ ድረስ የሚጠፋው ወርቃማ ጊዜ፣ የመትረፍ ዕድሉን እጅግ አነስተኛ ያደርገዋል። እነኝህ ግለሰቦች ለምን ጤነኛ ይመስላሉ? ድንገተኛ ሞት ግራ የሚያጋባው ሰውየው ከዚያ በፊት ፍጹም ደህና ስለሚመስል ነው። በሕክምና “ጤነኛ መምሰል” እና “በእርግጥም ጤነኛ መሆን” የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ይህ ከሚሆንባቸው ምክንያቶች መሀከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ። የተደበቀ በሽታ፦ ብዙ የልብ ሕመሞች በዝምታ ነው የሚከሰቱት። የመጀመሪያው ምልክት ሞት ሊሆን ይችላል፦ በአንዳንድ ሰዎች ላይ የልብ ሕመም መኖሩን የሚጠቁም ምንም ዓይነት ቅድመ ማስጠንቀቂያ አይኖርም። ይልቁንም የመጀመሪያውና ብቸኛው የበሽታው ምልክት ድንገተኛ የልብ ትርታ መዛባት ይሆናል። ይህም በድንገት ሕይወት ይነጥቃል። የመደበኛ ምርመራ እጥረት፦ ያለ ምርመራ እንደ ከፍተኛ ደም ግፊት ወይም ስኳር ያሉ ችግሮች ተደብቀው ይቆያሉ። እነዚህ በሽታዎች በሰውነት ውስጥ ጉዳት እያደረሱ ለረጅም ጊዜ ምንም ምልክት አያሳዩም። በኢትዮጵያ ደግሞ ሕመም ሳይሰማን የመታየትና የመመርመር ባህላችን ደካማ በመሆኑ፣ ብዙዎቻችን በውስጣችን ያለውን ስጋት ሳናውቅ እንቀራለን። ያለ ምርመራ በውስጣችን ያለውን እውነተኛ የጤና ሁኔታ ማወቅ አይቻልም፤ ይህም ሞት ሲከሰት “ያለ ምክንያት የመጣ” እንዲመስል ያደርገዋል። ማስተዋል ያለብዎ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ድንገተኛ ሞት ያለ ማስጠንቀቂያ ሊከሰት ቢችልም፣ አንዳንድ ምልክቶች አስቀድመው ሊታዩ ይችላሉ፦ ምንም ዓይነት ግልጽ ምክንያት ሳይኖር (ለምሳሌ፦ ረሃብ ወይም ድካም ሳይኖር) በድንገት ራስን መሳት አልያም ሰውነት መቅለል ስሜት ካለ በአፋጣኝ ምርመራ ያድርጉ። የልብ ችግር ሊሆን ይችላል። በደረትዎ ላይ የመጫን፣ የመጨመቅ ወይም የማቃጠል ስሜት ከተሰማዎት፤ በተለይም ሕመሙ ወደ ትከሻዎ፣ ወደ አንገትዎ ወይም ወደ እጅዎ የሚሰራጭ ከሆነ የሕክምና እርዳታ ይፈልጉ። ይህ ሕመም ተከስቶ ቢጠፋ እንኳ “ደህና ነኝ” ብለው ችላ ሊሉት አይገባም። የልብ ችግር ሊኖር ይችላል። ደረጃ ሲወጡ ወይም ትንሽ ሲራመዱ ከወትሮው በተለየ ትንፋሽዎ ቁርጥ ቁርጥ የሚል ከሆነ፣ ድካም ከተሰማዎ ያስተውሉ። ይህ የልብ ወይም የሳምባ ችግር ምልክት ሊሆን ይችላል። የአንዱ እግርዎ ባት/ታፋ በድንገት አብጦና ቀልቶ ካዩት፣ ይህ የእግር ደም ስር መርጋት ምልክት ሊሆን ይችላል። ወደ ሳምባዎ ከመጓዙ በፊት በአስቸኳይ ወደ ሕክምና መሄድ ይኖርብዎታል በበድንገት ለመሳቅ ሲሞክሩ የፊትዎ አንድ ወገን ካልታዘዘልዎት ወይም እጅዎን ወይ እግርዎ ድንገት ከሰነፈ ይፍጠኑ። ከዚህም ባሻገር ድንገተኛ የባህሪ ለውጥ የንግግር ለውጥ ካዩም በአፋጣኝ ወደ አቅራቢያዎ ወዳለ ጤና ተቋም ይሂዱ። ያለምንም ሙቀት ወይም እንቅስቃሴ በድንገት የሚመጣ ላብና የሰውነት መንቀጥቀጥ፣ በሰውነት ውስጥ የስኳር መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ማነሱን ሊያመለክት ይችላል። ይህም በፍጥነት ካልተስተካከለ ራስን ወደ መሳትና ለህልፈት ይዳርጋል። ለዚህም ችላ እንዳይሉ እንዴት ይከላከላሉ? ድንገተኛ ሞትን አስቀድሞ መከላከል ይቻላል። እነዚህን ቀላል የአኗኗር ዘይቤዎች በመከተል የራስዎንና የወዳጅዎን ሕይወት ይታደጉ፦ የደም ግፊትን በየጊዜው መለካት፦ የደም ግፊት "ጸጥተኛ ገዳይ" በመሆኑ፣ ምልክት ባይሰማዎትም እንኳ በየጊዜው በመለካት ይቆጣጠሩ። ይህም ለድንገተኛ ስትሮክና ለልብ ሕመም ያለዎትን ተጋላጭነት በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። ለስኳር በሽታ መመርመር፦ በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን መዛባት ለልብና ለደም ሥር ጤና ጠንቅ ነው። በሽታው መኖሩን አስቀድሞ ማወቅና ተገቢውን ሕክምና መጀመር ድንገተኛ አደጋዎችን ይከላከላል። ከአልኮልና ከሲጋራ መራቅ፦ ሲጋራ የደም ሥሮችን በማጥበብና በማደደር ለልብ ድንገተኛ መቆም ዋነኛው መንስኤ ነው። አልኮልን ማቆም ወይም መቀነስ ደግሞ የልብን ሥራ ያቀልላል። ጤናማ አመጋገብና እንቅስቃሴ፦ በምግብ ውስጥ የጨው መጠንን መቀነስ፣ አትክልትና ፍራፍሬን ማዘውተር እንዲሁም በቀን ቢያንስ ለ30 ደቂቃ በእግር መጓዝ የልብን ጤንነት ይጠብቃል። እላይ የተዘረዘሩትን ምልክቶች ካዩ ቀጠሮ ሳይሰጡ በአስቸኳይ ወደ ሕክምና ይሂዱ። ያስታውሱ! ከብዙ ድንገተኛ ሞቶች በስተጀርባ የተደበቁ በሽታዎች፣ ያልታወቁ የጤና እክሎች አሉ። መከላከል ያለዎት ብቸኛ አማራጭ ነው!

  • ከባድ የወር አበባ ህመም ባይሆንስ?

    ጸሀይ ብርሀኗን ከፈነጠቀች ሰአታት ተቆጥረዋል። ስራ ለመሄድ ጓጉታ በጠዋት የተነሳች ቢሆንም ፤ አልቻለችም። በታችኛው የሆድ ክፍሏ ላይ እንደ ስለት የሚቆርጥና የሚጠዘጥዝ ህመም ቀስፎ ይዟታል። ከቤት ለመውጣት ህመሙን ማስታመም ጀመረች። ብርቱ ቢሆንም ፤ " የወር አበባ ህመም ነው " ብላ ለራሷ ነገረችው። ወር አበባዋ ከመጣ ሁለተኛ ቀኗ ነው። ህመሙ ከባሰባት ግን አመታት ተቆጥረዋል። ሆኖም ማንም ሊረዳት አልቻለም። "ይሄ የሴት ልጅ እዳ ነው! አይዞሽ ጠንከር በይ" የሚላት እንጂ ፤ ምናልባት ሌላ ችግር ይኖራል ብሎ የጠረጠረም የለም። ህመሙን አሸንፎ ለመውጣት ትግሉን ተያያዘችው። ለመጠርጠርስ የሚያበቃ ምን አለ? ሁሉም ሴት አንድአይነት ወርሃዊ ኡደት ያካሂድ እንጂ ህመሙ ለየቅል ነው። ብዙም ህመም ሳይሰማቸው የሚያሳልፉ ጓደኞች አሏት። በየቀኑ ሁለት ህመም ማስታገሻ ካልዋጡ ህመሙን የማይችሉም ታውቃለች። የሷንም በተፈጥሮ ጸና ከሚልባቸው መሀል አድርጋ አስባለች። ህመሙ አቅም የሚያሳጣ ነው። ፊቷ በላብ ተጥለቅልቋል። የድካም ሸክም እየተጫጫናት ነው። ስራ ካልሄደች ልትባረር ትችላለች። እናስ ምን ተሻላት? እሷን ያጋጠማት ተራ ምቾት ማጣት አይደለም፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን በዝምታ የሚያሰቃየው፣ ነገር ግን ብዙም የማይነገርለት “ኢንዶሜትሪዮሲስ” የተሰኘው በሽታ ነው። ኢንዶሜትሪዮሲስ ምንድን ነው? በተፈጥሮ በሴት ልጆች ላይ የማህጸን ግድግዳ የተለያዩ ለውጦችን ያካሂዳል። የወርሃዊ ኡደቱ የሚያልቀው ፤ ጽንስን ለመቀበል ተዘጋጅቶ የነበረው የማህጸን ግድግዳ ፈርሶ ፤ በወር አበባ መልክ ሲወጣ ነው። ሂደቱም መልሶ እንደ አዲስ በቀጣይ ወር ይጀምራል። የማህጸን ግድግዳ ህዋሳት ከማህጸን ውጭ ቢያድጉስ ምን ይፈጠራል? የኢንዶሜትሪዮሲስ ምስል፡ ምስሉ ላይ የሚታዩት ቀያይ እድገቶች ከማህጸን ውጭ ያደጉ የማህጸን ህዋሳት ናቸው። በማህፀን ውስጥ የሚገኘው ህብረ ህዋስ (Endometrium) ከማህጸን ውጭያለቦታው በኦቫሪ (እንቁላል ማቀፊያ)፣ በማህፀን ቱቦዎች፣ በአንጀት ወይም በሽንት ፊኛ ላይ ሊያድግ/ሊጣበቅ ይችላል። ይህም ያለቦታው ያደገ የማህጸን ህዋስ በየወሩ የሴት ልጅ ሰውነት ኡደትን ተከትሎ ለውጥ ያካሄዳል። ታድያ ችግር የሚፈጥረው የወር አበባ ሲታይ ነው። ያለቦታው ስላደገ ፤ ይህ የማህጸን ህዋስ ሲፈርስ በወር አበባ መልክ ወደ ውጭ አይወጣም። አጠገብ ያሉ አካላት ላይ ደሙ ይፈሳል። ይህም ስር ለሰደደ ሰውነት መቆጣት ፣ ለኢንፌክሽን ፣ እና ለጠባሳ ህመም ይዳርጋል። ህመሙም ከወር አበባ እጅጉን ያየለ ነው። ስርጭቱ ምን ይመስላል? እንደ ዓለም አቀፍ የጤና መረጃዎች ከሆነ፣ በመውለጃ ዕድሜ ላይ ከሚገኙ 10 ሴቶች መካከል አንዷ በዚህ ስውር በሽታ ትጠቃለች። ይህ ማለት በዓለም ዙሪያ ወደ 190 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች እንደ ባለታሪኳ በዝምታ ይማቅቃሉ። በኢትዮጵያ ደግሞ ፈተናው ይበልጥ ይበረታል። በሀገራችን ካለው ማህበራዊ እይታ አንጻር፣ ከባድ የወር አበባ ህመም እንደ “ተፈጥሯዊ” ወይም “የሴትነት እጣ ፈንታ” ተደርጎ ብቻ ነው የሚወሰደው። ህመሙ ቢበረታም ብዙዎች በዝምታ እንዲታገሱት ይገፋፋሉ። በዚህም ምክንያት አንዲት ኢትዮጵያዊት ሴት ትክክለኛውን የህክምና ምርመራ ለማግኘት ከ5 እስከ 10 ዓመታት ሊፈጅባት ይችላል። በቃላት ለመግለጽ የሚያስቸግሩት ምልክቶቹ ኢንዶሜትሪዮሲስ ህመም ብቻ አይደለም ፤ ሕይወትን በማይታዩ መንገዶች ያውካል። ሰውነታችን ይህ ችግር እንዳለ የሚገልጽባቸው ቁልፍ ምልክቶች የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፦ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ  የሚሄድና በተራ ማስታገሻ የማይታገስ የወር አበባ ህመም። ከወር አበባ ውጭ ያለ የዳሌ ህመም — በእንቁላል መውጫ (ovulation) ወቅት የሚብስ አልያም በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጊዜ በዳሌ አከባቢ የሚሰማ ህመም። በግንኙነት ወቅት የሚሰማ ህመም። ለመውለድ መቸገር፦  ያለ ምንም ግልጽ ምክንያት ለማርገዝ መቸገር ወይም መካንነት። ከፍተኛ ድካም፦  ከህመሙ ጋር ተያይዞ የሚመጣ አቅም የማጣት ስሜት፣ ማቅለሽለሽ ወይም የምግብ መፈጨት ችግር ይጠቀሳሉ። እነዚህ ምልክቶች ብዙውን ጊዜ እንደ "ተራ የወር አበባ ህመም" ወይም እንደ ጭንቀት ተቆጥረው ችላ ይባላሉ። ህመሙም ከወር አበባ ህመም ሊያይል ይችላል። አስተውይ! ህመሙ የድክመት ምልክት ሳይሆን የጤና እክል ነው። በምን ምክንያት ይከሰታል? ምንም እንኳን የኢንዶሜትሪዮሲስ ትክክለኛ መንስኤ አሁንም ድረስ ጥናት እየተደረገበት ያለ ምስጢር ቢሆንም፣ ለበሽታው መከሰት የሚከተሉትን አራት መላምቶች ይሰጣሉ። የወር አበባ ወደ ኋላ መመለስ (Retrograde menstruation) ፦ ይህ በጣም የታወቀው መላምት ነው። በወር አበባ ወቅት ደም በማህፀን በኩል ወደ ውጭ ከመወጣት ይልቅ ፤ ወደ ሌላ አቅጣጫ ሄዶ ይህን ችግር ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል። በዚህ ደም ውስጥ የሚገኙ ህዋሳት በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ በመጣበቅ ማደግ ይጀምራሉ። በሽታ የመከላከል ሥርዓት መዳከም ፦ በተለምዶ ሰውነታችን የተሳሳተ ቦታ ላይ ያሉ ህዋሳትን ቢያስወግድም ፤ ይህን በሽታ የሚያመጡትን ህዋሳት ለማስወገድ ይሳነዋል። ጄኔቲክስ (ዘረመል) ፦ እናታቸው ወይም እህታቸው ኢንዶሜትሪዮሲስ ያለባቸው ሴቶች በችግሩ የመያዝ ዕድላቸው ከ7-10 እጥፍ ይጨምራል። ሆርሞኖች፦ ኢንዶሜትሪዮሲስ በኤስትሮጅን ሆርሞን ላይ ጥገኛ የሆነ በሽታ ነው። ይህ ሆርሞን ለህብረ ህዋሱ እድገትና ለመቆጣት ምክንያት ይሆናል። ምርመራ፡ እንዴት ማወቅ ይቻላል? ኢንዶሜትሪዮሲስ ከሰውነት እይታ ውጭ ተደብቆ የሚቆይ "ስውር በሽታ" በመሆኑ፣ ትክክለኛውን ምርመራ ለማግኘት ከፍተኛ ጥንቃቄና የባለሙያ ክትትል ይጠይቃል። ባለሙያዎች በሽታውን ለመለየት የሚከተሉትን ዋና ዋና መንገዶች ይጠቀማሉ፦ 1. በዶክተር የሚወሰድ የህክምና ታሪክ ምርመራው የሚጀምረው በንግግር ነው። ዶክተር ስለ የወር አበባ ዑደት ፣ ስለ ህመሙ ጽኑነት እና በቤተሰብ ውስጥ (ለምሳሌ እናት ወይም እህት ላይ) ተመሳሳይ ችግር መኖሩን ይጠይቃል። ህመምዎን ደብቀሽ ሳይሆን በዝርዝር ማስረዳትሽ ለትክክለኛው ምርመራ ቁልፍ እርምጃ ነው። 2. የላቀ የምስል ምርመራ (Imaging) በሽታው በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማየት ዶክተሮች የሚከተሉትን ሊጠቀሙ ይችላሉ፦ አልትራሳውንድ (Ultrasound)፦ በተለይ በማህፀን በኩል የሚደረግ አልትራሳውንድ በእንቁላል ማምረቻ ላይ ያሉ እድገቶችን/መቆጣቶችን ለመለየት ይረዳል። ኤምአርአይ (MRI)፦ በሽታው ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ተሰራጭቶ እንደሆነ ለማወቅ ጥልቅና ዝርዝር ምስል ይሰጣል። 3. የላፓሮስኮፒ ምርመራ “የመጨረሻው ማረጋገጫ” እስከ ዛሬ ድረስ ኢንዶሜትሪዮሲስ መኖሩን 100% ለማረጋገጥ የሚረዳው ዋነኛው መንገድ ይሄ ነው። ይህ በሆድ ውስጥ ትንሽ ቀዳዳ ፈጥሮ ፤ በዛ ካሜራ በማስገባት በቀጥታ የሚደረግ ምርመራ ነው። ዶክተሩም በሽታውን በአይኑ ከማየት ባለፈ፣ ያለ ቦታው ያደገውን ህዋስ/አካል ለማስወገድ ይችላል። ለዚህም ህክምናውንም ጭምር እንዲያከናውን ያስችላል። ሕክምና አማራጮቹስ ምንድን ናቸው? ኢንዶሜትሪዮሲስ በአሁኑ ጊዜ ፍጹም መፍትሄ የለውም። ሙሉ በሙሉ አይድንም። ግን በሽታው ሕይወትዎን እንዳይቆጣጠረው የሚያደርጉ ውጤታማ የህክምና አማራጮች አሉ። የህክምናውም ዋነኛ ዓላማ ህመምን መቀነስ፣ የመውለድ ዕድልን መጨመር እና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን እንዳይሰናከል ማድረግ ነው። ዋነኛ የህክምና አማራጮቹም የሚከተሉት ናቸው። 1. የመድኃኒት ህክምና ሁለት አይነት የመድሀኒት አማራጮች አሉት። የህመሙን ብርታት ለመቀነስ ፤ ስሜቱን ለማስታገስ ፤ የህመም ማስታገሻዎች ን መውሰድ ይችላሉ። ከዚህም ባሻገር በኪኒን ወይም በመርፌ የሚሰጡ የሆርሞን መድኃኒቶች የወር አበባ ዑደትን በማስተካከል በሽታውን ያክማሉ። 2. ቀዶ ጥገና፦ ይህን መፍትሔ እላይ በምርመራ ስር አንስተነዋል። 3.የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ በሽታውን ለመቆጣጠር መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይመከራል። በሳምንት ጥቂት ቀናት ቀለል ያለ እርምጃ ወይም ስፖርት መስራት ህመሙን ይቀንሳል። እላይ በምስሉ እንደሚታየው የሞቀ ውሃ በእቃ አድርጎ ሆድ ላይ (ከእንብርት በታች) ማድረግ ፤ ህመሙን እንዲቀንስ ያደርጋል። አመጋገብስ ለውጥ ያመጣል? ምንም እንኳን አመጋገብ በሽታውን ሙሉ በሙሉ ባይፈውስም፣ በሰውነት ውስጥ ያለውን የኤስትሮጅን መጠን በመቀነስ እና ቁስለትን (inflammation) በመከላከል ህመሙን በእጅጉ ሊያቃልል ይችላል። ለዚህም የሚከተሉትን ይመገቡ። ኤስትሮጅንን የሚቀንሱ ምግቦችን ተመገቢ። ለዚህ ከፍተኛ ፋይበር ያላቸው ምግቦች ተመራጭ ናቸው። ትርፍ ኤስትሮጅን ከሰውነት እንዲወጣ ያግዛሉ ። እንደ ባቄላ፣ አተር፣ ገብስ ፣ አጃ እና አረንጓዴ ቅጠላቅጠሎችን መመገብ ይመከራል። የሰውነት መቆጣትን/ ቁስለትን የሚቀንሱ ምግቦችን ተመገቢ። እንደ ተልባ እና ለውዝ ያሉ ቅባታማ ምግቦች እንዲሁም አሳ ውስጣቸው ሰውነት መቆጣት የሚቃወም ውህድ ስላላቸው ህመሙን ሊቀንሱ ይችላሉ። እነዚህን ምግቦች ቀንሺ። አኩሪ አተር ፣ ቀይ ስጋ፣ አልኮል እና ካፊን ያሉ ምግቦች በአንድ ሆነ በሌላ መንገድ በሽታውን ስለሚያባብሱ መቀነስ ይመረጣል። ባይታከምስ ምን ችግር አለው? ብዙ ሴቶች ህመሙን “የሴትነት ጽናት” አድርገው በዝምታ ለመጋፈጥ ቢመርጡም፣ ሳይታከም ከቆየ የከፋ ዋጋ ያስከፍላል። ችላ ማለቱ የሚያስከትላቸው ዋና ዋና አደጋዎች ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፦ 1. መካንነት ያመጣል። በሽታው ካለባቸው ሴቶች መካከል ከ30 እስከ 50 በመቶ የሚሆኑት ለማርገዝ ይቸገራሉ። በሽታው በማህፀን ቱቦዎች እና በእንቁላል ማምረቻዎች ላይ በሚፈጥረው ጠባሳ ምክንያት፣ የፅንስ መፈጠርንና እድገትን ያደናቅፋል። 2. የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሕይወት ያቃውሳል። ስር የሰደደው ህመም ሴቶችን ከመደበኛ ትምህርታቸው እንዲስተጓጎሉ ፤ ከሥራ ገበታቸው በተደጋጋሚ እንዲቀሩ ያደርጋል። ማህበራዊ ቁርኝታቸው ላይም ተጽእኖ ያሳድራል። 3. የስነ-ልቦና ጫና ያሳድራል። ለዓመታት የሚዘልቅ ማንም የማይረዳው ህመም ከመሆኑም በላይ በዙሪያ ያሉ የሰዎች አለመረዳት፣ ለጭንቀትና ለድብርት ያጋልጣል። ቀደም ብሎ ማወቅ ግን ያድናል! አትታገሽ ! ተመርመሪ የወር አበባ ህመምሽ እየባሰ ከመጣ አሁኑኑ ወደ ማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት በመሄድ መፍትሄ ፈልጊ። ቀደም ብሎ ሕክምና ማግኘት ህመምን ይቀንሳል፣ የአካል ክፍሎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳትን ይከላከላል እንዲሁም የመውለድ ዕድልን ያሻሽላል። እና ምን ትጠብቂያለሽ?

  • ሰው ወድቆ ሲያገኙ ምን ማድረግ አለብዎት?

    በምናብዎ ይሳሉት... በጠራራ ጸሀይ ፤ በተጨናነቀ መንገድ ላይ እየተጓዙ ሳለ ድንገት አንድ ሰው እያዩት ይደናቀፋል። ይወድቃል። ከዛም አይንቀሳቀስም። ሰዎች ይሰበሰባሉ። አንዳንዱ በትኩረት ይመለከታል። አንዳንዱ “ምናልባት ሰክሮ ይሆናል” ሲል ሌላኛው "ስኳር እንዳይኖርበት"ብሎ ያንሾካሹካል። ሌሎች ደግሞ በፍርሃት ወደ ኋላ ያፈገፍጋሉ። በዚያች ቅጽበት እርስዎ ምን ያደርጋሉ? ዝም ብለው የሚመለከቱ መንገደኛ ነዎት!? ወይስ በሕይወትና በሞት መካከል ያለ ድልድይ ይሆናሉ። ልብ ከቆመ እና ኦክስጅን ካጣ በቀጣይ 5 ደቂቃ ውስጥ (ከ 4–6 ደቂቃዎች) ውስጥ የአእምሮ ጉዳት ይጀምራል። በእነዚህ ደቂቃዎች ውስጥ ሆስፒታል አይደርስም። አምቡላንስ አይደርስለትም። ምን ማድረግ እንዳለብዎ ካወቁ ህይወቱን የሚያድኑ ደጉ ሳምራዊ ይሆናሉ።በእነኝህ ደቂቃዎች ውስጥ በአቅራቢያው ያለ ማንኛውም ሰው ፤ ከሐኪሞች በላይ ፋይዳ አለው። ለዚህም ይህ መመሪያ ለ እርስዎ ነው። የበሽታውን ዓይነት ማወቅ አያስፈልግዎትም። ምን ማድረግ እንዳለብዎት ማወቅ ብቻ ነው የሚጠበቅብዎት። በመጀመሪያ እርስዎም ሁለተኛ ተጎጂ አይሁኑ ወደ ፊት ከመሮጥዎ በፊት፣ ለጥቂት ጊዜ ቆም ይበሉ። አካባቢውን ይመልከቱ። ትራፊክ አለ? የኤሌክትሪክ ገመዶች? እሳት? ግጭት? የጋዝ መፍሰስ? አድናለው ብለው እርስዎ ከተጎዱ፣ ከአንድ አደጋ ይልቅ ሁለት አደጋ ይፈጠራል። ይህ ምንም ትርጉም የለውም። መጀመሪያ እራስዎን ይጠብቁ። ከአደጋው እራስዎን ያርቁ! አካባቢውን ደህንነቱ የተጠበቀ ያድርጉ። ከዛም፦ የሕይወት ምልክት ይፈልጉ አከባቢዎ አደጋ ከሌለው ፤ወደ ሰውየው ይቅረቡ። ትከሻውን በደንብ ይያዙ። በግልጽ ድምፅ ጮክ ብለው ይጥሩት/ያናግሩት፦ “ደህና ነህ/ሽ?” "የሚታወቅ ህመም አለ ወይስ የለም" ይበሉት። ካወራ፣ ከተንቀሳቀሰ ወይም ካቃሰተ ፤ ደም ወደ አእምሮ እየደረሰ ነው ማለት ነው። ምንም ምላሽ ከሌለ ግን እንደ ከባድ አደጋ ይቁጠሩት። ይጣሩ! ዝምታውን ይሰብሩ! በአደጋ ጊዜ ብዙ ሰው መኖሩ ጥቅም የለውም። እንደውም አደገኛ ነው። ምክንያቱም “ሁሉም ሰው ሌላ ሰው ይደውላል” ብሎ ያስባል። ስለዚህ ለይተው ይዘዙ። አንዱን ጠቁመው፦ “ አሁኑኑ ወደ ድንገተኛ አምቡላንስ ደውል!” ይበሉ። ግልጽ ትዕዛዝ ጊዜን ይቆጥባል። ትንፋሽ ይመርምሩ። አይገምቱ! ይመልከቱ! ደረታቸውን ይመልከቱ። ደረቱ በመደበኛ ሁኔታ ይነሳል፣ ይወርዳል? ምላሽዎ አዎ ከሆነ እና ሰውየው ራሱን የሳተ ከሆነ ፤ ቀስ አድርገው በጎኑ ያስተኙት። ራሱን በመጠኑ ወደ ኋላ ዘመም ያድርጉት። አፉ እና ጉሮሮ ውስጥ ምንም ነገር አለመኖሩን ያረጋግጡ። እርዳታ እስኪመጣ ይቀጥሉ። ታካሚውን በምስሉ ላይ እንደሚታየው ወደጎን ይገልብጡት ይህ አተኛኝ አፍ ውስጥ የሚገቡ ነገሮች/ ምግቦች / ፈሳሾች ወደ ሳንባ እንዳይገቡ ያደርጋል። ቢያስታውክ እንኳን ወደ ሳንባ እንዳይገባ እና እንዳይታፈን ይረዳል። ትንፋሽ ከሌለ ግን ወዲያውኑ እርምጃ መውሰድ አለብዎት። አፍ ውስጥ ያለ ትንፋሽን የደፈነ አካል ካለ ይፈልጉ። ምላስ ወደ ኋላ ተኝቶ ጉሮሮን አለመድፈኑን ይመልከቱ። አፍን የደፈነ አካል ከሌለ እና እየተነፈሰ ካልሆነ ለወደቀው ሰው እርስዎ መተንፈስ ይኖብዎታል። አፍ ለአፍ ትንፋሽ ለመስጠት ይዘጋጁ። ልብን ያዳምጡ። ልብ ከቆመ፣ ኦክስጅን ወደ አእምሮ አይደርስም። ደሙን እርስዎ በእጅዎ መግፋት/ ማዘዋወር አለብዎት። እጅዎትን በምስሉ ላይ እንደሚታየው በደረቱ መሀል ላይ አነባብረው ይግፉ። ዘዴው፦ የአንዱን እጅዎን መዳፍ ደረት መሃል ላይ ያድርጉ። ሌላኛውን እጅ በላዩ ላይ ያድርጉ። ክንድዎን ሳያጥፉ፤ በጥልቀትና በፍጥነት ይጫኑ። መጠኑ፦ እየቆጠሩ 30 ጊዜ ደረቱን ይጫኑ።ከዛም ሁለት ጊዜ ትንፋሽ አፍ ለአፍ ይስጡ። ይህ በህክምናው ሲ ፒ አር (CPR) ይሰኛል። እርዳታ እስኪመጣ ይህን ይቀጥሉ። አፍ ለአፍ ትንፋሽ መስጠት ካልቻሉ የደረት መጫኑን ብቻ በየ 30 ዙር እያረፉ ይቀጥሉ። ያስተውሉ! የጎድን አጥንት ቢሰበር እንኳ ይድናል፤ የሞተ አእምሮ ግን አይድንም። ለዚህም እንዳያቆሙ! ከባድ የደም መፍሰስ ካለስ? በምስሉ እንደምታዩት አንገት ላይ የተስካው እንጨት እንዳይነቀል ደግፈውታል እንጂ አልነቀሉትም። ደም በከፍተኛ ሁኔታ እየፈሰሰ ከሆነ ቁስሉን በጨርቅ ተጭነው ይያዙት። በሰውነቱ ውስጥ የተሰካ ነገር ካለ (ጩቤ፣ ቢላ፣ መስታወት፣ሆነ ማንኛውም አካል) በፍጹም አይንቀሉት ! ብዙ ደም እንዳይፈስ ዘግቶ የያዘው እርሱ ይሆናል። ከነቀሉት ከባድ ደም መፍሰስ ሊያጋጥም ይችላል። የሚጥል በሽታ ካለ/እየተንቀጠቀጠ ከሆነስ? አንድ ሰው በሚጥል በሽታ (Seizure) ምክንያት ራሱን ሊስት፣ ሊወድቅ ወይም ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የሰውነት መንቀጥቀጥ ሊያጋጥመው ይችላል። እዚህ ላይ ማስታወስ ያለብዎት ዋናው ነገር አንዴ የጀመረን መንቀጥቀጥ ማቆም እንደማይችሉ ነ ው። የእርስዎ ብቸኛ ኃላፊነት ንቅናቄው እስኪያበቃ ድረስ ሰውየው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መጠበቅ ነው። በመሆኑም ይረጋጉ ፤ አካባቢውን ከጠንካራ ወይም ከሹል/ከሚጎዱ ነገሮች ያጽዱ። እናም ጃኬት/ልብስ /ለስላሳ ጨርቅ አጥፈው ከራሳቸው ስር ያድርጉላቸው። አንተራሷቸው። መንቀጥቀጡ ሲቆም፣ አየር በደንብ እንዲያገኙና ራሳቸውን እስኪያዉቁ ድረስ በቀላሉ እንዲተነፍሱ ቀስ አድርገው በጎናቸው ያስኝቷቸው። በፍጹም አፋቸው ውስጥ ምንም ነገር አይክተቱ ። ምላሳቸውን እንዳይነክሱ አፋቸው ውስጥ የሚከቷቸው ነገሮች ጥርሳቸውን ሊሰብር ወይም የመተንፈሻ ቱቦአቸውን ሊዘጋ ይችላል። በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ሰውየውን ለመያዝ ወይም እጅና እግራቸውን እንዳይንቀሳቀስ ለማድረግ አይሞክሩ፤ የንቅናቄው ኃይል ከእርስዎ ግፊት ጋር ሲጋጭ የአጥንት መሰበር ወይም የጡንቻ መበጠስ ሊያስከትል ይችላል። በመጨረሻም፣ ሙሉ በሙሉ ነቅተው በግልጽ መናገር እስኪጀምሩ ድረስ ውሃ ወይም ምግብ አይስጧቸው። ምክንያቱም ገና በትክክል መዋጥ ሊያስቸግራቸው ይችላል። ለዚህም የሚሰጣቸው ምግብ ወደ ሳንባ ገብቶ ሊያፍናቸው/ ትን ሊላቸው ይችላል። ኪሳቸው ውስጥ የሚጥል በሽታ መድሀኒት ካለ እንዲውጡ ይስጧቸው። የአካል ጉዳት እንዳለ ከተጠረጠረ ሰውየው፦ ከከፍታ ላይ የወደቀ ከሆነ በተሽከርካሪ የተገጨ ከሆነ ግልጽ የሆነ የአካል ጉዳት ካሳየ ያለ አስፈላጊ ምክንያት አያንቀሳቀሷቸው። የአከርካሪ አጥንት ጉዳት ደርሶባቸው ቢሆን ፤ ማንቀሳቀስዎ ለዘላቂ ሽባነት (Paralysis) ሊዳርግ ይችላል። ከዚህም አልፎ ሲያንቀሳቅሷቸው ፤ የተጎዳ የአንገት አከርካሪ አጥንትን ሊሰብሩ/ሊቀጯቸው ይችላሉ። ሰውየውን ማንቀሳቀስ የሚገባው ፤ እዚያው ባለበት ቢቆይ የከፋ ጉዳት ሊደርስበት የሚችል ከሆነ ብቻ ነው (ለምሳሌ እሳት ካለ፣ አስፋልት መሀል ከወደቀ፣ ወ.ዘ.ተ...)። 🚫 እነኝህን አያድርጉ! ❌ ፊት ላይ ውሃ አይርጩ፦ የቆመ ልብን አያስነሳም፣ ጥቅም የለውም። ❌ መጠጥ፣ ምግብ ወይም መድኃኒት በአፋቸው አይክተቱ፦ ካልነቁ ሳንባ ውስጥ ገብቶ ለሞት ይዳርጋል። ❌ የሚጥል በሽታ ሲነሳባቸው አፋቸው ውስጥ ምንም ነገር አይክተቱ፦ ምላሳቸውን አይውጡም፤ ነገር ግን ጥርሳቸውን ሊሰብሩ ወይም ትንፋሽ ሊዘጉ ይችላሉ። ❌ ሰክሯል ብለው አይገምቱ፦ የስኳር መውረድ፣ ስትሮክ እና የልብ አደጋ ሁሉም ከስካር ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ስክሯል ብለው ችላ ብለው እንዳይሄዱ። የተቻሎትን አድርጉላቸው። 🥤ሚሪንዳ፣ ለስላሳ መጠጦች እና ክብሪትስ? ሰው ወድቆ ሲያገኙ ፤ ብዙ ሰዎች ሚሪንዳ ወይም ጣፋጭ መጠጥ አልያም ውሀ ያሰጣሉ። ይህ የሚደረገው በቅንነት ቢሆንም ፤ የራሱ አደጋ ይኖረዋል። ራሱን የሳተ ሰው መዋጥ አይችልም፤ ፈሳሹ ወደ ሳንባው ይገባል። ልቡ ለቆመ ሰው ስኳር ቢሰጠው ፤ በሰውነት ውስጥ አይዘዋወርም። ችግሩ ስኳር ሳይሆን የደም ዝውውር መቆም፤ ኦክስጅን ማነስ ነው። ለዚህም ሚሪንዳ፣ ለስላሳ መጠጦች እና ውሀ ከመስጠትዎ በፊት ይህንን ያረጋግጡ! ሰወየው ነቅቶ ያወራል ወይ? ምላሹ አይ ከሆነ ፈጽሞ አይስጡ! ይህን ይጠንቀቁ! ራሱን የሳተ ሰው መዋጥ አይችልም አንድ ሰው ራሱን ሲስት ፤ የመዋጥ ስሜቱ ስለሚስተጓጎል ፤ የመተንፈሻ ቱቦው ምንም መከላከያ አይኖረውም። ያለው ፈሳሽ ወደ ጨጓራ መሄድ ሲገባው ወደ ሳንባ ይገባል ። ይህም አደገኛ ነው። ስለዚህም መንቃቱን እና መጠጣቱን ሳያቅ ምግብ እና ፈሳሽ አይስጡ! ክብሪት ማሽተትስ? ይህ የራሱ የሆነ ባህላዊ ትርጉም ቢኖረውም ፤ ፋይዳ የሌለው ተግባር ነው። የቆመ ልብን አያስነሳም፤ ይልቁንም ወርቃማውን ጊዜ ያባክናል። ⏳ ያስተውሉ እያንዳንዱ ሰከንድ ዋጋ አለው! ልብ ሲቆም አእምሮ ኦክስጅን ወዲያውኑ ያጣል። ከ4-5 ደቂቃ በኋላ የአእምሮ ሕዋሳት በኦክስጅን እጦት መሞት ይጀምራሉ። በእያንዳንዱ ደቂቃ የመተርፍ እድል በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። እርስዎ ሲፒአር (CPR) ሲጀምሩ ግን ፤ የደም ዝውውር ወደ አእምሮ እንዲደርስ ያደርጋሉ። ለዚህ ጊዜ እየገዙለት መሆኑን ይወቁ። የመኖር ተስፋ እየሰጡት ነው። ሆኖም ግን በእኛ ማህበረሰብን ጨምሮ በብዙ ቦታዎች ምንም እርዳታ ሳያገኝ ይህ ሰአት ይባክናል። ለምን? ሰዎች የህግ ተጠያቂነትን ይፈራሉ። ሰዎች የማያውቁትን ሰው ለመንካት ይቸገራሉ። አፍ ለአፍ ትንፋሽ ለመስጠት ይፈራሉ። አንዳንዶች ከመርዳት ይልቅ በስልክ መቅረጽን ይመርጣሉ። ነገር ግን ራስዎን ጠብቀው የሌላን ሰው ህይወት ማዳን ይችላሉ። ባይችሉ ደውለው አምቡላንስ ይጥሩ! ሰውን በደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ መርዳት የሰብአዊ ክብር መገለጫ ነው። ❤️ ማስተዋል ያለብዎ ነገር! አንድ ቀን የወደቀው ሰው እንግዳ ላይሆን ይችላል። አባትዎ፣ እህትዎ ወይም ልጅዎ ሊሆን ይችላል። ያን ጊዜ በህይወት እና በሞት መሀከል ያለው ለውጥ ፤ እንደርስዎ ለመርዳት በወሰነ ሩህሩህ ሰው ላይ ይወሰናል። ይህ ሰው ምን ማደረግ እንዳለበት ባያውቅስ ? ለዚህም ይህን ትምህርታዊ ጽሁፍ ለብዙዎች እንዲዳረስ ያጋሩ። ህይወት ያድኑበታል!

  • 🔥ስለ ጨጓራ ቁስለት ማወቅ ያለብዎ ነገሮች?

    በብዙዎች ዘንድ ከእንብርት በላይ ያለ የሚቃጠል የሆድ ህመም ይህን ያህልም ቦታ አይሰጠውም። “ቡና አብዝተህ ይሆናል” “ጭንቀት ነው” ተብሎ ይታለፋል። የበላሁት ምግብ ነው ብለውም የሚበሉትን የምግብ አይነት የሚለውጡም አሉ። ለእንደዚህ አይነት ህመም ደግሞ ፤ ሽሮ ፍትፍትማ ፍቱን ነው! እነኝህ አስተሳሰቦች እውነታ ቢኖራቸውም ፤ ከዚህ ተራ ከሚመስል ምቾት ማጣት በስተጀርባ ፣ ጠለቅ ያለ ነገር እየተፈጠረ ቢሆንስ? ጨጓራ እየቆሰለ ሊሆን ይችላል! በጨጓራ ወይም በትንሹ አንጀት ግድግዳ ላይ በዝምታ የሚፈጠር ቁስል ሊሆን ይችላል። ይህ ቁስል በህክምና "ፔፕቲክ አልሰር" (PUD) ይባላል። ስለ እርሱ ማወቅ ለጤናዎ እጅግ ጠቃሚ ነው። ለመሆኑ የጨጓራ ቁስለት ምንድን ነው? በሰውነታችን ውስጥ ጨጓራ ስጋን ማድቀቅ የሚችል ጠንካራ አሲድ ያመነጫል። ይህ አሲድም በጨጓራ ውስጥ የሚገባውን ምግብ ዱቄት ያደርጋል፤ ያልማል። አሲዱም ምግቡን እያላመ ከጨጓራም ባሻገር ፤ ወደ ትንሹ አንጀት የመጀመሪያ ክፍል (ዱዎዲነም) ይደርሳል። ስጋን የሚያደቅ ፤ ይህ ጠንካራ አሲድ ለምን ራሱን ጨጓራን አይበላውም? ይህ ኃይለኛ አሲድ ከምግቡ አልፎ እራሱን እንዳይበላው  ሰውነታችን በተፈጥሮ ራሱን የሚከላከለበት ብልሀት አለው። ይህም ፦ ጨጓራችን በወፍራም ንፍጥ በመሰለ (Mucus) ሽፋን የተከለለ ነው። ይህም አሲዱ የጨጓራ ግድግዳ ጋር እንዳይደርስ ይከልለዋል። አንጀት ጋር ደርሶ አንጀትን እንዳይበላ ደግሞ አንጀት አከባቢ ያሉ ህዋሳት ባይካርቦኔት የሚባል አሲዱን የሚቃረን ውህድ ያመነጫሉ። ከዚህም ባሻገር ጨጓራ አከባቢ ያሉ ህዋሳትን ቶሎ ማደስ እንዲቻል በአከባቢው ተገቢ የደም ዝውውር አለ። ታድያ ቁስል የሚፈጠረው ፤ ይህ የመከላከያ ሥርዓት ሲፈርስ ነው። አሲዱ የጨጓራን ግድግዳ በቀጥታ ሲያገኘው ያስቆጣዋል። ከመቆጣትም አልፎ ይቆስላል። ይህን ጊዜ የጨጓራ ቁስለት አጋጠመ ይባላል። ይህ ቁስል በሁለት ዋና ቦታዎች ይከሰታል፦ በጨጓራ ግድግዳ ውስጥ → የጨጓራ ቁስለት(Gastric ulcer) ይባላል። በትንሹ አንጀት መጀመሪያ ክፍል → የዱዎዲነም(ልዩ ስሙ) ቁስለት (Duodenal ulcer) ወይም "የአንጀት ቁስል" ይባላል። ሁለቱም በአንድ ላይ የጨጓራ አሲድን ተከትሎ የሚመጣ ቁስለት(peptic ulcer disease/ pud) ይሰኛሉ። በተለምዶ በወል የጨጉራ ቁስለት ይባላሉ። ጨጓራ ወይስ የትንሹ አንጀት ቁስለት? የቱ ነው ያለብኝ? ሁለቱም በአሲድ ጉዳት ቢከሰቱም፣ በሰውነት ላይ ያላቸው ባህሪ ይለያያል። የጨጓራ ቁስል (Gastric ulcer)፦ ምግብ እንደበሉ ወዲያው ያማል። ምግብ መብላት አሲድ እንዲመነጭ ስለሚያደርግ የቆሰለውን የጨጓራ ግድግዳ ያቃጥለዋል። ታካሚዎች ምግብ ከበሉ ከ30 ደቂቃ በኋላ ህመሙ እንደሚብስባቸው ይገልጻሉ። ምግብ መብላት ህመም ስለሚያመጣባቸው፤ ምግብ መመገብ ይቀንሳሉ። ለዚህም የክብደት መቀነስ የተለመደ ምልክት ነው። የትንሹ አንጀት ቁስል (Duodenal ulcer)፦ በተቃራኒው ጨጓራ ባዶ ሲሆን (ከተመገቡ ከ2-3 ሰዓት በኋላ ወይም እኩለ ሌሊት ላይ) ያማል። ምግብ ሲበሉ ህመሙ ለጊዜው ይጠፋል። አንዳንድ ታካሚዎች ህመሙን ለማስታገስ በተደጋጋሚ ስለሚበሉ ክብደት ሊጨምሩ ይችላሉ። ምን ያህል የተለመደ ነው? በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ5-10% የሚሆኑ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ በሆነ ወቅት ለጨጓራ ቁስለት ይጋለጣሉ። በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በበሽታው ይጠቃሉ። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የአፍሪካ አገሮች የበሽታውን ጫና ከፍ ያለ ነው። ይህም የጨጓራ የባክቴሪያ ስርጭት ከፍተኛ ከመሆኑ ፤ ያለ ሀኪም ትእዛዝ የህመም ማስታገሻዎች በስፋት ጥቅም ላይ ከመዋላቸው እና የጨጓራ ኢንዶስኮፒ ምርመራ አገልግሎት በቀላሉ ካለመገኘቱ ጋር የተያያዘ ነው። መንስኤዎቹ ለብዙ አሥርተ ዓመታት የጨጓራ ቁስለት በጭንቀትና በሚያቃጥል ቅመም ብቻ ይመጣል ተብሎ ይታመን ነበር። ዘመናዊ ሕክምና ያንን ግንዛቤ ቀይሮታል። ለብዙ ታማሚዎች ሁለት ዋና መንስኤዎች አሉ፦ 1. የጨጓራ ባክቴሪያ (H. pylori) ይህ ባክቴሪያ በጨጓራ ግድግዳ ላይ ይኖራል። የጨጓራን መከላከያ ሽፋንን በመብላቱ፤ ጨጓራ በቀጥታ ለአሲድ ጥቃት ያጋልጣል። ይህንን ባክቴሪያ ኢንፌክሽን በማከም ጨጓራ ቁስለትን በቋሚነት መፈወስ ይቻላል። 2. የህመም ማስታገሻዎች (NSAIDs) እንደ ኢቡፕሮፌን (Ibuprofen) ፣ ዲክሎፌናክ (Diclofenac) እና አስፒሪን (Aspirin) ያሉ መድኃኒቶች የጨጓራን ግድግዳ የሚጠብቁ ንጥረ ነገሮችን (Prostaglandins) ያግዳሉ። በዚህ ጊዜ አሲድ በቀላሉ ቁስል ይፈጥራል። ለዚህም እነዚህን መድኃኒቶች ለረጅም ጊዜ መጠቀም ለጨጓራ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ይህ ቁስለት ምን ዓይነት ስሜት አለው? ዋነኛው ምልክት በሆድ የላይኛው ክፍል ላይ የሚሰማ የሚቃጠል ስሜት ነው። ህመሙ አንዳድ ጊዜ ትከሻ ላይ አልያም መሀል ጀርባ ላይ ሊሰማ ይችላል። ከዚህም ባሻገር የሚከተሉት ምልክቶችም ሊኖሩት ይችላሉ፦ የሆድ መነፋት ማቅለሽለሽና ትውከት ቶሎ የመጥገብ ስሜት ቀላልክ ክብደት መቀነስ ምክንያቱ ያልታወቀ ድካም እላይ እንዳየነው ፤ ምልክቱ እንደ ቁስለቱ አይነት ሊለያይ ይችላል። ቁስሉ መቼ እጅጉን አሳስቢ ይሆናል? ያልታከመ ቁስል ወደ ሦስት ዋና አደጋዎች ሊያመራ ይችላል፦ ደም መፍሰስ፦ ቁስሉ ሲደማ የሚከሰት ነው። ምልክቶቹም ጥቁር ሰገራ ፣ እንደ ቡና የጠቆረ ትውከት እና ራስን መሳት ናቸው። የጨጓራ መበሳት (Perforation)፦ ቁስሉ ሲብስ የጨጓራ ግድግዳን ሊበሳ/ሊሸነቁር ይችላል። ይህ አስቸኳይ ቀዶ ጥገና የሚያስፈልገው የሕክምና ድንገተኛ አደጋ ነው። ይህን ጊዜ ድንገተኛ እና ከፍተኛ የሆድ ህመም ይሰማል። የምግብ መንገድ መዘጋት (Obstruction)፦ በቁስሉ ምክንያት የሚፈጠር ጠባሳ ምግብ የሚያልፍበትን መንገድ ሊዘጋው/ሊያጠበው ይችላል። ይህ ሲያጋጥም ምልክቶቹ የበሉትን ምግብ እንዳለ መልሶ ማስታወክ ፣ ትንሽ እንደበሉ መጥገብ እና የሆድ መነፋት ናቸው። ከ አምስት ታማሚዎች አንዱ ችግሩ እጅጉን እስኪባባስ አነስተኛ ምልክቶች ብቻ ሊኖረው ይችላል። ለዚህም ችላ ይባላል። ይህ ደግሞ አደገኛ ነው! እንዲሁም የጨጓራ ቁስለት ተደጋግሞ የሚያጋጥም ከሆነ ፤ በአመታት ውስጥ ለ ጨጓራ ካንሰር ሊያጋልጥ ይችላል። ለዚህም አሁኑኑ መፍትሔ ይፈልጉለት! እንዴት ማወቅ ይችላል? የጨጓራ ቁስለት በተለያዩ ምርመራዎች ሊታወቅ ይችላል። በዶክተር አካላዊ ምርመራ ጨጓራ ላይ ቁስለት መኖሩ ሊታወቅ ይችላል። ባክቴሪያ መኖሩንም በደም ወይም ሰገራ ምርመራ መለየት ይቻላል። እየደማ መሆኑን ለማወቅ የሰገራ የደም ምርመራ ሊታዘዝ ይችላል። ከዚህም ባሻገር ቁስለቱን በቀጥታ ለመመልከት እና ጨጓራ ላይ ያለውን ለውጥ በአይን ለማየት የ ኢንዶስኮፒ (Endoscopy) ምርመራ ማድረግም ግድ ሊል ይችላል። ሕክምናው ምንድነው? የጨጓራ ቁስለትን በሚዋጥ መድሀኒቶች ማከም ይችላል። እነኝህም መድሀኒቶች ቁስለቱ እንዳይባባስ እና ጨጓራ እንዲድን አሲዱን የሚቀንሱ ናቸው። ከዚህም ባሻገር ባክቴሪያው ከተገኘ ባክቴሪያውን የሚቃወሙ መድሀኒቶች ሊጨመሩ ይችላሉ። እንዴት መከላከል ይቻላል? የጨጓራ ቁስለትን ለመከላከል የሚከተሉትን ያድርጉ። ያለ አስፈላጊ ምክንያት የህመም ማስታገሻዎችን አይውሰዱ። የህመም ማስታገሻዎችን መጠቀም ካለብዎ በዝቅተኛው መጠን ይጠቀሙ። አብዝተው አይጠቀሙ። ሲጋራ አያጭሱ። አልኮል ይቀንሱ/ያስወግዱ ። የማያቋርጥ የሆድ ህመም ካለ በፍጥነት ምርመራ ያድርጉ። ያስተውሉ! የ ሚያቃጥል ቅመም (ቃሪያ/በርበሬ) በራሱ ለጨጓራ ቁስለት መንስኤ አይሆንም። ጭንቀት ብቻውን ለጨጓራ ቁስለት መንስኤ አይሆንም። ይህ ሊታከምና ሊከላከል የሚችል የውስጥ ቁስል ነው። ምልክቶቹን ይወቁ! ይከላከሉ! ጤናዎን ይጠብቁ !

  • ቡና ለጤናችን መርዝ ወይስ መድሐኒት? ሳይንሱ ምን ይላል?

    ለኢትዮጵያ ህዝብ ቡና መጠጥ ብቻ አይደለም። ባህል ነው! ሥርዓት ነው! መጨዋወቻ ፤ መተዋወቂያ እና መግባቢያ ነው! ከዚህም አልፎ የቡና ኤክስፖርት የኢኮኖሚያችን መሰረት በመሆኑ " የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ብና የሚሉ.... " ዜማዎችም አሉን። የቡና ስርአታችንም ለየት ያለ ነው። ታድያ ግን አንዳንድ ጥናቶች ቡና ለጤና ጠቃሚ ነው ሲሉ ፤ ሌሎች ቡና ያለውን የጤና አደጋ ያነሳሉ። ይህ ደግሞ ብዙዎችን ግራ ያጋባል። አንዳንዶች " የጤና ጠንቅ ስላለው ባልጠጣስ" ሲሉ ፤ ሌሎች ደም ግፊት እያለባቸው እንኳን ቡና አብዝተው ይጠጣሉ። ታድያ የትኛው ትክክል ነው? እነኝህ ጥናቶች ተሳስተው ይሆን? ይህን ለመመለስ መጀመሪያ ቡና በውስጡ ካፊን (caffeine) ጨምሮ ብዙ ንጥረ ነገሮች እንዳሉት ማወቅ አለብዎ። ቡና አንቲኦክሲዳንትስ (Antioxidants) እና ፖሊፊኖልስ (Polyphenols) የተባሉ ለጤና ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን ይዟል። ይህንን በጥልቀት እንመልከት! ከቡና መጠጣት ጀርባ ያለው ስሌት የኢትዮጵያ ቡና እንብለው እንጂ አብዛኛው በኢትዮጵያ መሬት ላይ የሚበቅለው የቡና ዝርያ ኮፊ አረቢካ (Coffee Arabica) ይሰኛል። የላብራቶሪ ምርመራዎች እንደሚያሳዩት፦ አረቢካ ቡና ዝርያ በደረቅ ክብደቱ ከ1.2%–1.5% ካፊን ይይዛል። ይህ ማለት በአንድ ግራም ቡና ውስጥ ከ12–15 ሚሊግራም (mg) ካፊን ማለት ነው። አሁን ይህንን ወደ ሲኒ እንለውጠው። አንድ በባህላዊ መንገድ የሚፈላ ቡና በአንድ ጊዜ ከ10–14 ግራም ቡና ሊጠቀም ይችላል። ይህ ማለት፦ የኢትዮጵያ ቡና አፈላል ስርአት ለየት ያለ በመሆኑ ፤ ሶስት ጊዜ ስለሚጠጣ ፤ እንዲሁም ለረዥም ጊዜ ስለሚፈላ ፤ አንድ በባህላዊ መንገድ የሚፈላ የቡና ሲኒ ጠንከር ያለ ተጽእኖ ያሳድራል። ለዚህም ከፍተኛውን መጠን ብንወስድ በአንድ ሲኒ ጠንካራ የኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ከ120–210 mg ካፊን ይገኛል። ይህ ግምት አይደለም ፤ የኬሚስትሪ ሳይንስ ነው። ይህ ለጤና ከሚቀመጡ ገደቦች ጋር ሲነጻጸር እንዴት ይታያል? የሕክምና ሳይንስ እንደሚጠቁመው፦ ✅ ለጤናማ አዋቂ ሰው በቀን የሚፈቀደው ከፍተኛ መጠን በቀን 400 mg ማለፍ የለበትም። ✅ ለነፍሰ ጡር ሴቶች ደግሞ ከ 200 mg ቢያንስ ይመከራል። አሁን በጥንቃቄ እናስብ። አንድ ባህላዊ ሲኒ ከ120–210 mg ካን ከያዘ ፤ ከአንድ እስከ ሁለት ሲኒ (እንደ ቡናው ጥንካሬ) ለአብዛኛው አዋቂ ሰው ጤናማ ነው። ከዛ በላይ ከጠጡ ግን ገደቡን ሊያልፉ ይችላሉ። ሆኖም ግን በባህላችን መሰረት ቤት ውስጥ የሚፈላ ቡና ፤ እስከ ሶስተኛ ነው የሚጠጣው። አቦል ጦና በረካን ሳይደርስ መሄድ አይወደድም። ምንም እንኳን የኋለኞቹ ዙሮች ቢቀጥኑም፣ ድምር ውጤቱ ለጤናማ ሰው ከሚፈቀደው ሊበልጥ ይችላል። ሳይንስ ከባህል ጋር የሚገናኘው እዚህ ጋር ነው። ይህ የካፊን መጠን ለምን ተቀመጠ ? አንጎላችን ውስጥ በተፈጥሮ እንቅልፍ እንዲመጣ የሚያደርጉ አዴኖሲን  (adenosine) የተሰኙ ውህዶች አሉ። ቡና ውስጥ ያለው ካፊንም በአንጎል ውስጥ አዴኖሲኖች እንዳይሰሩ ይዘጋባቸዋል። ይህም ንቁ እንዲሆኑ ያደርጋል። ለዚህም ደምዎ ውስጥ ያለው የካፊን መጠን ያለውን ተጽእኖ ይወስናል። በ100–200 mg መጠን ካፊን ከጠጡ ፤ ንቁ ይሆናሉ። ፈጣን ምላሽ መስጠት ይችላሉ። በመጠነኛ ደረጃ የልብ ምትዎ ይጨምራል። የደም ግፊትዎ በመጠኑ ከፍ ይላል። በ300–400 mg መጠን ካፊን ከጠጡ ፤ ከፍተኛ መነቃቃት ይኖርዎታል። አድሬናሊን የሚሰኘው የአደጋ ጊዜ ሆርሞን እና ኮርቲሶል የተሰኘው ከጭንቀት ጋር የሚያያዘው ሆርሞኖች መጠን እንዲጨምር ያደርጋሉ። ለዚህም ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ላይ ጭንቀት ይፈጥራል። ከ400–500 mg በላይ ካፊን ከጠጡ ፤ የልብ ትርታዎ በደንብ ይጨምራል። መቅበዝበዝ እና እንቅልፍ ማጣት ሊኖርዎት ይችላል። የደም ግፊትዎ በከፍተኛ መጠን ይጨምራል። የጨጓራ መቆጣትም ሊያመጣ ይችላል። ይህ ገደብ የተቀመጠውም ከማንቃቱ ይልቅ ጉዳቱ እንዳይብስ ለማድረግ ነው። እዚህ ጋር ያስተውሉ! ቡና ላይ የሚደረጉ ጥናቶች በሲኒ ሲገልጹ ለብዙዎች አሳሳች ይሆናል። ቀጭን ቡና 3 ሲኒ እና አንድ ጠንካራ ቡና 1 ሲኒ ውስጣቸው ያለው ውህድ መጠን እኩል ሊሆን ይችላል። ለዚህም አንዳንድ ጥናቶች 3 ሲኒ ቡና ሲሉ ፤ እስከአሁን ያነሳነውን ስሌት ክደው ሳይሆን ፤ ቡናው ቀጭን ሆኖ ሊሆን እንደሚችል ማስተዋል አለብዎ። በባህላዊ መንገድ የተዘጋጀ ቡና አንድ ሲኒ በቂ ሊሆን ይችላል። ❤️ መልካሙ ዜና፡ ቡና ለብዙ ሰዎች ጤናማ ነው ጥናቶች እንደሚያሳዩት በቀን መጠነኛ ቡና መጠጣት ከሚከተሉት ጥቅሞች ጋር የተያያዘ ነው፦ ✅ እድሜን ማራዘም፦ አዘውትረው ቡና የሚጠጡ ሰዎች ካልጠጡት ጋር ሲነጻጸሩ ያለጊዜው የመሞት እድላቸው ዝቅተኛ መሆኑን የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ። ✅ የልብ ጤና፦ መጠነኛ ቡና ጠጪዎች ለልብ ሕመም እና ለስትሮክ የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ ነው። ✅ የስኳር በሽታ፦ መጠነኛ ቡና መጠጣት ፤ ኢንሱሊን የተባለው ሆርሞን ላይ ባለው ተጽእኖ ፤ ለ ስኳር በሽታ የመጋለጥ እድልን እንደሚቀንስም የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ።   ✅ የአንጎል ጤና፦ ቡና አንጎል ላይ ባለውም ተጽእኖ ፤ እንደ ፓርኪንሰን (Parkinson’s) እና አልዛይመር (Alzheimer’s) ያሉ በሽታዎችን የመከላከል አቅም እንዳለውም አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ✅ የጉበት መድኃኒት፦   ቡና ውስጥ ያሉት አንቲ አክሲዳንት እና ፌኖልስ የጉበትን ጤና ይደግፋሉ። ጉበት በስብ እንዳይወረርና ለካንሰር እንዳይጋለጥ የመከላከል አቅም አላቸው። ⚠️አሳሳቢው ጉዳይ፡ ቡና ለብዙዎች ጎጂ ሊሆን ይችላል "ከመጠን ያለፈ ማር ይመራል" እንደሚባለው ሁሉ፣ ቡናም መጠኑ ሲበዛ ወይም አጠጣጡ ሲዛባ አደገኛ ይሆናል። ለዚህም የጭንቀት ቀስቃሽ (Anxiety Trigger) ነው።  ካፊን አድሬናሊንና ኮርቲሶል ሆርሞን ላይ ባለው ተጽእኖ ጭንቀት ሊቀሰቅስ ይችላል። ከመጠን በላይ ሲሆን የልብ ትርታን ያፋጥናል፣ እጅን ያንቀጥቅጣል፣ እንዲሁም ለከፍተኛ መረበሽና ጭንቀት ይዳርጋል። የእንቅልፍ ሌባ ነው።  ካፊን በደም ውስጥ እስከ 6 ሰዓት ይቆያል። ከሰዓት በኋላ የሚጠጣ ቡና የሌሊት እንቅልፍዎን ጥራት ይዘርፈዋል። ጥልቅ እንቅልፍ ማጣት ደግሞ ለደም ግፊትና ለሰውነት መቆጣት (Inflammation) መንስኤ ይሆናል። ለዚህም ከ ቀኑ 9 ሰአት በኋላ ቡና ባይጠጡ መልካም ነው። የጨጓራ ጠላት ነው።  ቡና የጨጓራ አሲድ እንዲመነጭ ያግዛል። የጨጓራ ቁስል ወይም ቃር ያለባቸው ሰዎች ቡና ሲጠጡ ህመሙ እንዲባባስ ያደርጋል። ለነፍሰ ጡር ሴቶች ስጋት ነው።  ከፍተኛ ካፊን በፅንሱ እድገት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ስለዚህ ነፍሰ ጡር እናቶች በቀን ከ1 ሲኒ በላይ እንዳይጠጡ በጥብቅ ይመከራሉ። ❗ቡና አብዝቶ መጠጣት ለስኳር በሽታም ይዳርጋል! ይህ እላይ ካልነው ጋር ፈጽሞ አይቃረንም! ለምን? ብዙዎች ቡና በስኳር አጣፍጠው ነው የሚጠጡት። በአማካይ በአንድ ሲኒ 2 የሻይ ማንኪያ ስኳር ሲጨምሩ ወደ 8 ግራም ስኳር ከቡናው ጋር አብረው ይጠጣሉ። በቀን 3 ሲኒ ቡና ከጠጡ፣ 24 ግራም ስኳር እያገኙ ነው። ይህ በጊዜ ሂደት ሰውነት ኡደትን ያሰናክላል። ለስኳር በሽታም ይዳርጋል። ሰዎች "ቡና ለስኳር ህመም ያጋልጣል" ሲሉ ፤ ብዙ ጊዜ የሚጠጡት በስኳር የጣፈጠ ቡናን መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም። ይህ ልዩነት በህክምናው ረገድ እጅግ አስፈላጊ ነው። ጥንቃቄ ማድረግ ያለባቸው እነማን ናቸው? የሚከተሉት ሁኔታዎች ካሉብዎት ቡና ሲጠጡ ጥንቃቄ ያድርጉ፦ ነፍሰ ጡር ከሆኑ ፤  በቀን ከ200 ሚ.ግ ካፊን (1 ሲኒ) አይለፉ። ቁጥጥር ያልተደረገበት የደም ግፊት ካለብዎት ፤ ቡና ባይጠጡ ይመከራል። የጭንቀት (Anxiety) ወይም ድንገተኛ ፍርሃት (Panic) ችግር ካለብዎት ፤ ዶክተርዎን ያማክሩ። ከፍተኛ የቃር (Reflux) ችግር ካለብዎት ቡና አይጠጡ። የልብ ምት መዛባት ካለብዎት ቡና አይጠጡ። ቡና ለሁሉም ሰው እኩል ጠቃሚ ወይም ጉዳት የሌለው ላይሆን ይችላል። ለማጠቃለል… ቡና ጥሩ ነው ወይስ መጥፎ? ትክክለኛው መልስ — ያለ ስሜት እና ያለ ማጋነን — እንደሚከተለው ነው፦ ለአብዛኛው ጤነኛ አዋቂ ሰው በቀን ከ አንድ እስከ ሁለት ሲኒ ባህላዊ ቡና የጤና ጉዳት የለውም። በጥናት መሰረትም ለረጅም ጊዜ ጤንነት ጠቀሜታ አለው። ቁልፉ ነጥብ መፍራት ሳይሆን ፤ መረዳት ነው። ቡናዎን በእውቀት ይጠጡ። ቡናዎን በመጠን ይጠጡ ።

  • በህጻንነት ራሰ በራ ሊያደርግ የሚችለው ቆሮቆር በሽታ

    የቆዳ ሐኪምቤቱ እንደተለመደው በታካሚዎች ተሞልቷል። ከታካሚዎቹ መካከል አንዷ እናት የ7 ዓመት ሴት ልጇን እጅ ይዛ በጭንቀት ትጠብቃለች። የመጣችው ለተለመደው ጉንፋን ወይም ትኩሳት አልነበረም... የልጇ ፀጉር መሀል ላይ ክብ ክብ ቅርጽ የያዘ ሽፍታ/እድገት ለማሳየት ነበር። ህመሙ ከጀመረማ ሳምንታት ተቆጥረዋል። መጀመሪያ ፎሮፎር ነው ብላ የጸጉር ቅባት በደንብ ትቀባት ነበር። ሆኖም ግን ልጇ አልተሻላትም ነበር። ግራ ሲገባት ፋርማሲ ሄዳ አማክራ የሚቀባ መድሐኒት ይዛ መጣች። ለቀናት ባለሙያው እንደመከራት አደረገች። ለውጥ የለም! እድገቱ ከመስፋፋቱም ባሻገር መግል ያዘ። ሲጀምር አንድ ብቻ እንዳልነበር ፤ አሁን ጸጉሯን ሙሉ ወረረው። ቀን በቀን ማታ ላይ ታጥባት ነበር ሆኖም ግን ለሊቱን ሙሉ መግል ይዞ ያድር ነበር። ይብሱኑ ብሎ ጸጉሯ መሳስት ጀመረ። ይህች እናት የልጇ ሁኔታ እጅጉን ጨነቃት! አንድ ያማከረችው ግለሰብ ፤ ካልታከመች በልጅነቷ ጸጉሯ ሊመለጥ እንደሚችል ሲነግራት ሮጣ የቆዳ ሐኪም ቤት ይዛት መጣች። የሰዉ መብዛት አልተስተዋላትም። ከነበራት ጭንቅ እና ካሳለፈቻቸው ሳምንታት ፤ ይህ ምንም አይደለም። ይህ ታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ ልጆችን ያጋጥማል። ዛሬ የምናነሳው በተለምዶ ስሙ ቆሮቆር ስለሚሰኘው በሽታ ነው። ይህ ችላ የምንለው የልጅነት በሽታ ሳይሆን ፤ ህክምና ካልተደረገ ... ጸጉርን ራሱ ሊያሳጣ የሚችል በሽታ ነው። ቆሮቆር ምንድነው? ይህ በህክምና ስሙ ቲንያ ካፒቲስ (Tinea Capitis) የሚሰኝ የራስ ቅል የፈንገስ በሽታ ነው። ዋነኛ መንስኤዎቹ ትሪኮፊቶን (Trichophyton)  እና ማይክሮስፖረም (Microsporum)  የሚባሉ የፈንገስ ዝርያዎች ናቸው። ይህ ፈንገስ የራስ ቅል ቆዳን ከማጥቃቱም ባሻገር ወደ ጸጉር ስር ዘልቆ በመግባት ፀጉሩን ሊበላው ይችላል። ይህን ጊዜ ያሳክካል። ይህ ኢንፌክሽን ለእይታ የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያሳይ ይችላል። ጥቁር ነጥብ (Black Dot):  ፀጉሩን ከመሬት እኩል ስለሚበሉት እንደ ጥቁር ነጥብ ሆኖ ይታያል። ግራጫማ ንጣፍ (Gray Patch):  ቆዳውን ድርቅ ያለና አመድማ ያደርጉታል። ለዚህም መልኩ የገረጣ ይመስላል። እነኝህ በሽታው መለስተኛ ሲሆኑ የሚታዩ ናቸው። በሽታው ግን ከደረጀ ኬሪዮን ኬሪዮን (Kerion) የሚሰኝ ከባድ ገጽታ ያሳያል።  ይህ ባለታሪኳ ልጅ ላይ የታየው ሲሆን ፤ ከፍተኛ እብጠትና መግል አለው። ይህም ሰውነት ፈንገሱን ለመከላከል የሚያደርገው ከፍተኛ ትግል ውጤት ነው። ታድያ ግን በአግባቡ ካልታከመ ፤ ፀጉሩ እስከመጨረሻው እንዳይበቅል ሊያደርገው ይችላል። ባይታከምስ ምን ያመጣል? ከካናዳ ሜዲካል ጆርናል የተወሰደ ኬርዮን የሚሰኝወን የቆሮቆር ከባድ ቁስል የሚያሳይ ምስል አለመታከም ብቻ ሳይሆን ፤ በሽታው በጊዜ ካልታከመ ከቆዳ ህመም አልፎ የሚከተሉትን ችግሮች ያመጣል፦ የእድሜ ልክ ጠባሳ በልጅነት ራሰ በራነት እየተባባሰ የሚሄድ ተደራቢ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ሊያመጣ ይችላል። ከዚህም ባሻገር የስነልቦና ጫናም ይፈጥራል። ልጆች በትምህርት ቤታቸው ይገለላሉ። በእድሜ እኩዮቻቸው መሳለቂያ ይሆናሉ። ይህም ስነልቦና ጫና ከትምህርት ገበታ እንዲቀሩ ሊዳርጋቸው ይችላል። ባህሪያቸውም ላይ ተጽእኖ ያሳድራል። በሽታው እንዴት ይሰራጫል? በሽታው በፈንገስ ስለሚመጣ ፤ መተላለፊያ መንገዱም ከታመመ ልጅ ወደ ጤነኛ ፈንገሱ እንዲተላለፍ እድል የሚፈጥሩ ጉዳዮች ብቻ ናቸው። ለምሳሌ፡ የቀጥታ ግንኙነት፦ በትምህርት ቤት ጨዋታ ላይ ልጆች ራስ ከተነካኩ። የጋራ ቁሳቁስ፦ በተለይ በቤተሰቦች የተለመደው የጋራ ማበጠሪያ፣ ኮፍያ፣ ፎጣ እና ትራስ መጠቀም ሊያስተላልፍ ይችላል። የፀጉር ቤቶች፦ በአግባቡ ያልተጸዱ(ስቴራላይዝ ያልተደረጉ ) ቶንዶሶች/የጸጉር መቁረጫዎች በሽታውን ያስተላልፋሉ። የቤት እንስሳት፦ አንዳንዴም ቢሆን ድመቶችና ውሾች ለበሽታው ተሸካሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ ግን ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ባይሆንም ፤ እንሰሶች ሲያዙ ምልክት ላያሳዩ ስለሚችሉ መጠንቀቁ መልካም ነው። በኢትዮጵያ ለምን ተስፋፋ? የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ5 ልጆች አንዱ  በዚህ ኢንፌክሽን ይያዛል። የዚህም ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚታሰበው የትምህርት ክፍሎች መጨናነቅ ነው። ከዚህም ባሻገር በአንድ ቤት ውስጥ ብዙ ሰው መኖር እና የንጹህ ውሃ እጥረትም ለበሽታው ስርጭት አስተዋእጾ ያደርጋሉ። እላይ እንዳለችው እናት ሕክምናን ማዘግየት ፤ በሽታው እንዲደረጅ እድል ከመፍጠሩም በላይ ልጆች ላይ የእድሜ ልክ ጠባሳ ሊተው ይችላል። እንዴት መመርመር ይቻላል? ሐኪሞች በሽታውን ለመለየት ሁለት ዋና መንገዶችን ይጠቀማሉ፦ የባለሙያ(ዶክተር) ምርመራ : ይህ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የፀጉሩን መርገፍ ሁኔታ፣ የቆዳውን መላጥ እና የቆሰሉ ምልክቶችን በማየት ብቻ ሊያውቁት ይችላሉ። የናሙና ምርመራ: ይበልጥ እርግጠኛ ለመሆን ጥቂት የፀጉር ዘንግ ወይም የቆዳ ቅርፊት ወስዶ በማይክሮስኮፕ በማየት (KOH) አልያም በልዩ መብራት ስር ታይቶ ሊታወቅ ይችላል። ሕክምናውስ ምንድነው? ቆርቆር በቤት ውስጥ በሚደረግ ጥረት ወይም በቅባት ብቻ አይድንም። ለዚህም ነው ለባለታሪኳ የጸጉር ቅባት እና የቤትውስጥ ክትትል ለውጥ ያላመጣው። የሚዋጥ መድኃኒት ፦  ፈንገሱ በፀጉር ዘንግ ውስጥ ስለሚደበቅ፣ በሐኪም የሚታዘዙ የሚዋጡ ኪኒኖች ለተከታታይ ሳምንታት መሰጠት አለባቸው። ፈንገስን የሚቃወም ሻምፑ፦   የፈንገሱን ስርጭትን ለመቀነስ የፈንገስ መቃወሚያ ሻምፑዎችን መጠቀም እንደ ረዳት ሕክምና ያገለግላል። ያስተውሉ! ይህ ፈንገስ በሚቀቡ መድሐኒቶች አልያም በሻምፖዎች ብቻ አይድንም ፈንገሱ በፀጉር ዘንግና ስር ውስጥ ስለሚደበቅ መድኃኒቱ በደም በኩል መድረስ አለበት። አለበዛ ፈንገሱን ሙሉ በሙሉ አያገኘውም። ለዚህም ነው ባለታሪኳ እናት ፋርማሲ ሄዳ የወሰደችው መድሐኒት ያላዳናት። እንዴት መከላከል ይቻላል? በሽታው በቤተሰብ እና በትምህርት ቤት ውስጥ እንዳይሰራጭ እነዚህን ነጥቦች መተግበር ይገባል፦ ቁሳቁስ አለመጋራት፦ ልጆች የራሳቸው ማበጠሪያ፣ ኮፍያ እና ፎጣ እንዲኖራቸው ማድረግ ። የፀጉር ቤት ጥንቃቄ፦ ከተቻለ ልጆች ወደ ፀጉር ቤት ሲሄዱ የራሳቸው መቁረጫ/ቶንዶስ ይዞ መሄድ መልካም ነው። ይህ ካልተቻለ የጸጉር ቤቱ መሣሪያዎቹ በኬሚካል / በመሳሪያ መጽዳታቸውን ማረጋገጥ ይመከራል። የቤት እንስሳት ንፅህና፦ በቤት ውስጥ ያሉ ውሾች ወይም ድመቶች የፀጉር መርገፍ ካለባቸው ወደ እንስሳት ሐኪም ወስደው ያሳክሙ። ልብስን በሙቅ ውሃ ማጠብ፦ የታመመ ልጅ የሚጠቀምባቸውን አንሶላዎችና ትራሶች ሙሉ በሙሉ በሙቅ ውሃ ይጠቡ። ይህ ፈንገሱን ያጠፋል። የባለታሪኳ ህጻን እጣ ፈንታ እንዴት ሆነ ? ተራዋ ደርሶ የቆዳ ሕክምና እስፔሻሊስት ጋር ገባች። ባለሙያውም የበሽታውን ሁኔታ ካስተዋለ እና ከመረመረ በኋላ አስፈላጊ የላብራቶሪ ምርመራዎች አዘዘላት። ምርመራዎቹም ጥርጣሬውን ስላረጋገጡለት። ለሁለት ወር የሚወሰዱ የሚዋጡ እና የሚቀቡ መድሀኒቶች አዘዘላት። መድሀኒቶቹን መውሰድ እንደጀመረች ወዲያውኑ ለውጦችን በደንብ አላስተዋለችም ነበር። ከሁለት ሳምንት በኋላ ግን የፈንገሱም ቁስል መድረቅ ጀመረ። እድገቶቹ ሁሉ ከሰሙ። በሁለተኛ ወር ላይም ህጻኗ ወደ ሙሉ ጤናው ተመለሰች። ይህን ያስተውሉ! በመዘግየትዎ ለልጅዎ የእድሜ ልክ ጠባሳ ሊተዉ ይችላሉ። ለዚህም ምልክቶቹን እንዳስተዋሉ ፈጥነው የሕክምና እርዳታ ይፈልጉ።

  • ዳማከሴ እውነት ያድናል? ሳይንስ ምን ይላል?

    ስለ ዳማከሴ ምን ያህል ያውቃሉ? እናቶቻችን.... ለዘመናት ዳማከሴ ተጠቅመዋል! ምች መትቶዎት የሚያቅ ከሆነ አንዴም ቢሆን ዳማከሴ ወስደዋል። በሽታውን ለማወቅም የሚያስፈልገው ዳማከሴውን መጭመቅ ነው። በባህል ላብራቶሪ .... የተጨመቀው ዳማከሴ ከጠቆረ .... የሚዘጋጅለት ሰው ምች አለበት ማለት ነው። ከዚያም ማድረግ ያለብዎ ጭማቂውን ጠጥቶ መተኛት ነው። አስበውታል ... ከታማሚው ጋር ንክኪ የሌለው ቅጠል በአየር ሞገድ የታካሚን ህመም ሲያመላክት ፤ አውቆም ሲያድን! ይህ ምትሀትም ይመስላል! ምን ያህሉስ እውነት ነው? ዳማከሴ በህክምና እይታ ምን ይመስላል? ዳማከሴ በታሪክ በኢትዮጵያ ለረዥም አመታት ለባህላዊ ህክምና ሲያገለግል የቆየ መድሐኒት ነው። እንደ ጤናአዳም እና ሌሎች ባህላዊ መድሐኒቶች በታሪክ በአለም ዙሪያ ጥቅም ላይ አልዋለም። ዳ ማከሴ በምስራቅ አፍሪካ ቢገኝም፣ እንደ ኢትዮጵያ በስፋትና በስርአት ለህክምና ስራ ላይ የዋለበት አገር የለም። አብዛኛዎቹ ጥናቶችም በጎንደር፣ መቀሌ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች የተሰሩ ናቸው። በሳይንስ ስሙ ኦሲመም ላሚፎሊየም ( Ocimum lamiifolium ) ይሰኛል። በባህልም ብዙ ህመሞች ለማከም አገልግሎት ላይ ውሏል ፤ እየዋለም ይገኛል። በ 2024 የተደረገ የዳሰሳ ጥናት ዳማከሴ የሰውነት መቆጣትን ለመከላከል ፣ ህመም ለማስታገስ እንደሚውልና ፣ እንዲሁም ጸረ ኦክሲዳንት ባህሪ እንዳለው ጠቁሟል። "በባህል ላብራቶሪ " የጭማቂው ቀለም ለምን ይቀየራል? የዳማከሴ ጭማቂ ከታማሚው ጋር ሳይገናኝ የመጥቆር ሁኔታ በሳይንሳዊ መንገድ ከኦክሲዴሽን (Oxidation) ሂደት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ቅጠሉ በውስጡ ከፍተኛ የፊኖሊክ ውህዶች (Phenolic compounds) ይዘት አለው። ለዚህም እነኝህ ውህዶች ከአየር ጋር አልያም ከሚጨምቀው ሰው ሰውነት/ላብ ጋር ሲነካኩ የቀለም ለውጥ ሊያሳይ ይችላል። ይህም ምክንያቱ የላብ የ ፔኢች ደረጃ (pH level) አነሰተኛ ስለሆነ ነው። ሆኖም ግን በባህል የለመድነው ፤ ለሚቆረጥለት ሰው ምች መኖር አለመኖሩን ፤ በቀለም አልያም በሽታ ጥንካሬ መለየቱ አዳጋች እንደሆነ ሳይንስ ይጠቁማል። 🧪 በቅጠሉ ውስጥ ምን አለ? ኢሰንሺያል ኦይልስ( Essential Oils (Sesquiterpenes) ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት ዳማከሴ በውስጡ ያለው ኢሴንሻል ኦይልስ የተሰኙ ዘይቶች አሉት። ከእነኝህ ውስጥ ወደ 94% የሚጠጋው ሴስኩተርፔን  የሚባለው የዘይት አይነት ነው። ይህ ዘይት በባህሪው የሰውነት መቆጣትን (Inflammation) በመቀነስ የራስ ምታትንና የጡንቻ ህመምን ያስታግሳሉ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናቶች ይህንን በሰፊው አረጋግጠዋል። ከዚህ ውህድም ባሻገር የሚከተሉት ውህዶችም ውስጡ ይገኛሉ። ኢዩጀኖል (Eugenol) (በ 2007 በተደረገ ጥናት ተለይቷል) ይህ ውህድ ባክቴሪያን የመግደልና ህመም የማስታገስ (Natural anesthetic) አቅም አለው። ሮዝማሪኒክ አሲድ ( Rosmarinic Acid ) (በመቀሌ ዩንቨርስቲ በ 2015 በተደረገ ጥናት ተለይቷል) በሰውነት ውስጥ ያሉ መርዛማ ነገሮችን (Free radicals) ለማስወገድ የሚረዳ ጠንካራ ጸረ-ኦክሲዳንት ነው። የሰውነት መቆጣትንም ይከላከላል። ኡርሶሊክ አሲድ ( Ursolic acid )  (በ2020 ተለይቷል) እጢ እድገትን ይቃወማል። የሰውነት ኡደትን ያስተካክላል። አፒጂኒን( Apigenin ) (በ2025 የእጽዋት ኬሚካል ጥናት በባህርዳር ተለይቷል) የሰውነት መቆጣትን ይከላከላል። በጭንቅላት ውስጥ ያሉ የነርቭ ህዋሳትን ከጉዳት ይጠብቃሉ። ይህ ደግሞ ዳማከሴ ለከባድ የራስ ምታትና ለጭንቀት የሚሰጠውን ጥቅም ይመሰክራል። አሁን ይህ ተአምር አይደለም። ዳማከሴ በተፈጥሮ በውስጡ በዛ ያሉ የመድሐኒትነት ባህሪ ያላቸው ውህዶች አሉት። እነኝህ በሳይንስ የተረጋገጡት በውስጡ ያሉ ውህዶች ሲሆኑ ፤ ትልቁ ጥያቄ የሚሆነው ህመም ያስታግሳሉ ወይ? የሚለው ነው። ይህንን ለመረዳት ከፋፍለን እንይ! 🔥 የሰውነት ትኩሳት እና መቆጣት እ.ኤ.አ. በ2011 የተደረገው የአይጦች ጥናት ዳማከሴ የሰውነት ሙቀትን የመቀነስ ( Antipyretic ) አቅሙ ከፓራሴታሞል ጋር ሊቀራረብ እንደሚችል አመልክቷል። ይህም በባህል ለረጅም ጊዜ የቆየ አጠቃቀሙን ያረጋግጣል። የሰውነት መቆጣትን ተከትሎ ለሚመጣ ራስምታት፣ ትኩሳት እና የጡንቻ ህመም ተጽእኖ አለው ተብሎ ይገመታል። ይህንን በደንብ ለማረጋገጥ ፤ በሰው ላይ የተደረገ ጥናት ያስፈልጋል። 🩸የስኳር ቁጥጥር   ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ የተደረጉ ጥናቶች አስደናቂ ነገር አግኝተዋል። የዳማከሴ ጭማቂዎች ለስኳር በሽተኞች ተሰጥተው ፤ የስኳር ቁጥጥር ላይ አስተዋእጾ አሳይተዋል። ዳማከሴ በውስጡ አልፋ አሚሌዝ (Alpha-amylase) እና አልፋ ግሉኮሴድ( Alpha-glucosidase) የተባሉ ኢንዛይሞችን የማገድ ብቃት እንዳለው በጥናት ተረጋግጧል። እነዚህ ኢንዛይሞች ካርቦሃይድሬት ወደ ስኳር እንዳይቀየር ስለሚያደርጉ፣ ዳማከሴን መውሰድ ከምግብ በኋላ የሚመጣን ከፍተኛ የስኳር መጠን ለመቀነስ ይረዳል። የዳማከሴ ጸረ-ኦክሲዳንት ባህሪ በቆሽት ውስጥ ያሉ Beta-cells (ኢንሱሊን የሚያመነጩ ህዋሳት) እንዳይጎዱ የመከላከል አቅም አለው። ይህም ተክሉ ለረጅም ጊዜ የስኳር ህመምተኞች እንደ ተጨማሪ (Adjunct) ህክምና ለመዋል የሚችል አቅም እንዳለው ይጠቁማል።  የሰውነት ኡድትን የማሻሻል አቅሙም ለስኳር ቁጥጥር ጠቅሟል ተብሎ ይገመታል። እነኝህ ጥናቶች በላብራቶሪ እና በእንሰሳት ላይ የተደረጉ መሆኑ ሊስተዋል ይገባል። በሰዎች ላይ የተደረጉ ብዙ ጥናቶች ያስፈልጋሉ። ሆኖም ዳማከሴ የየትኛው የስኳር መድሐኒት ምትክ አይደለም። ማገዣ ሆኖ ሊያገለግል ይችል ይሆናል። 🦠 ፀረ-ባክቴሪያ ባህሪ እላይ እንዳየነው ዳማከሴ ውስጥ የሚገኘው ኢዩጀኖል የሚሰኘው ውህድ ባክቴሪያን የመቃወም ባህሪ አለው። ውስጡ ያሉ ኢሴንሻል ኦይልስም ለባክቴሪያ መቃወም አስተዋእጾ ያደርጋሉ። እ.ኤ.አ. በ 2018 የተደረገ ጥናት የሽንት ቧንቧ መንስኤ የሆነው ኢ.ኮላይ (E. Coli) የተሰኘ ባክቴሪያ ን ይቃወማል። ዳማከሴ በውስጡ ባሉት ውህዶች አማካኝነት የባክቴሪያውን የውጭ ሽፋን (Cell wall) በማዳከም ይገድለዋል። ባህላዊ ጥቅሙ ምናልባትም ትክክል ይሆናል! ይበልጥ የሚገርመው የዳማከሴ ጭስ ወይም ሽታ የትንኞችን የነርቭ ሥርዓት በማወክ አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ያደርጋል። ይህ በገጠር ለሚኖሩ ማህበረሰቦች የወባ በሽታን ለመከላከል ቀላልና ተመጣጣኝ መንገድ ነው። 🦟 የፀረ-ወባ ባህሪ እ.ኤ.አ. በ 2016 በላብራቶሪ የተደረገ የወባ ህዋስ (ፕላዝሞዲየም) ጥናት እስከ 35.53% የሚደርስ የወባ ተህዋስን ዳማከሴ እንደቀነሰ ጠቁሟል። ታድያ ለወባ መድሀኒትን ሊያገለግል ይችላልን? አይ! በአሁኑ ወቅት የምንጠቀመው ፍቱኑ የወባ መድሐኒት አርተመንሲንን አይተካም። ሆኖም ግን እነኝህ ባህሪያት ይህ ተክል አስፈላጊው ጥናትን ምርምር ቢደረግበት ከውስጡ ብዙ መድሐኒት መውጣት እንደሚችል ይጠቁማሉ። 🧻ለሆድ ያለው ጥቅም  የምግብ  መፈጨት እና ፀረ-ተቅማጥ ባህሪም እንዳለው የሚጠቁም ጥናት በ 2022 ተደርጓል። ይህ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ዳማከሴ የአንጀትን መሸማቀቅ (Muscle contraction) በመቀነስ ተቅማጥንና ቁርጠትን ያስታግሳል። ይህም ተክሉ ቁርጠትን የመከላከል (Antispasmodic) ባህሪ እንዳለው ያሳያል። ⚖ ጤናማ አጠቃቀሙ እንዴት ነው? ዘመናዊ ሳይንስ ከባህላዊ ሳይንስ አንጻር ያለው ልዩነት ይህ ነው። በግምት በዘፈቀደ ሳይሆን ለሰውነት ክብደት እና ቁመና የተሰላ አጠቃቀም ነው መኖር ያለበት። እ.ኤ.አ በ 2023 የተደረገ የመርዛማነት ጥናት እንደሚያመላክተው ለረዥም ጊዜ የሚወስዱ ከሆነ ከ400 mg/kg ማለፍ የለበትም። ከዚህ ካለፈ የጉበት እና ኩላሊት ላይ ተጽእኖ ያሳድራል። በጽንስ ላይ ተጽእኖ እንደሌለው በ 2022 የተደረገ ጥናት ጠቁሟል። በውስጡ ያለው ሊድ እና ክሮሚየም መጠንም የዓለም ጤና ድርጅት በሚፈቀደው ገደብ ውስጥ መሆኑ ተረጋግጧል። ይህም ለመጠቀም ጤናማ መሆኑን ፤ ተጓዳኝ ጉዳቱ የተገደበ መሆኑን አመላካች ነው። ዳማከሴ ከባህል ባለፈ ሳይንስ የመስከረለት እጽዋት ነው! በውስጡ የያዛቸው ተፈጥሮአዊ ውህዶች ለጤናችን ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ጥናቶች ያረጋግጣሉ። ስለሆነም፣ የዚህን ተክል ፈዋሽነት ተረድተን በዕውቀት እንጠቀምበት

bottom of page