top of page

ዳማከሴ እውነት ያድናል? ሳይንስ ምን ይላል?

ስለ ዳማከሴ ምን ያህል ያውቃሉ?


እናቶቻችን.... ለዘመናት ዳማከሴ ተጠቅመዋል!


ምች መትቶዎት የሚያቅ ከሆነ አንዴም ቢሆን ዳማከሴ ወስደዋል።



በሽታውን ለማወቅም የሚያስፈልገው ዳማከሴውን መጭመቅ ነው። በባህል ላብራቶሪ .... የተጨመቀው ዳማከሴ ከጠቆረ .... የሚዘጋጅለት ሰው ምች አለበት ማለት ነው።


ከዚያም ማድረግ ያለብዎ ጭማቂውን ጠጥቶ መተኛት ነው።


አስበውታል ... ከታማሚው ጋር ንክኪ የሌለው ቅጠል በአየር ሞገድ የታካሚን ህመም ሲያመላክት ፤ አውቆም ሲያድን! ይህ ምትሀትም ይመስላል!


ምን ያህሉስ እውነት ነው?


ዳማከሴ በህክምና እይታ ምን ይመስላል?


ዳማከሴ በታሪክ በኢትዮጵያ ለረዥም አመታት ለባህላዊ ህክምና ሲያገለግል የቆየ መድሐኒት ነው። እንደ ጤናአዳም እና ሌሎች ባህላዊ መድሐኒቶች በታሪክ በአለም ዙሪያ ጥቅም ላይ አልዋለም። ዳማከሴ በምስራቅ አፍሪካ ቢገኝም፣ እንደ ኢትዮጵያ በስፋትና በስርአት ለህክምና ስራ ላይ የዋለበት አገር የለም። አብዛኛዎቹ ጥናቶችም በጎንደር፣ መቀሌ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች የተሰሩ ናቸው።



በሳይንስ ስሙ ኦሲመም ላሚፎሊየም (Ocimum lamiifolium) ይሰኛል። በባህልም ብዙ ህመሞች ለማከም አገልግሎት ላይ ውሏል ፤ እየዋለም ይገኛል።


በ 2024 የተደረገ የዳሰሳ ጥናት ዳማከሴ የሰውነት መቆጣትን ለመከላከል ፣ ህመም ለማስታገስ እንደሚውልና ፣ እንዲሁም ጸረ ኦክሲዳንት ባህሪ እንዳለው ጠቁሟል።


"በባህል ላብራቶሪ " የጭማቂው ቀለም ለምን ይቀየራል?


የዳማከሴ ጭማቂ ከታማሚው ጋር ሳይገናኝ የመጥቆር ሁኔታ በሳይንሳዊ መንገድ ከኦክሲዴሽን (Oxidation) ሂደት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ቅጠሉ በውስጡ ከፍተኛ የፊኖሊክ ውህዶች (Phenolic compounds) ይዘት አለው። ለዚህም እነኝህ ውህዶች ከአየር ጋር አልያም ከሚጨምቀው ሰው ሰውነት/ላብ ጋር ሲነካኩ የቀለም ለውጥ ሊያሳይ ይችላል። ይህም ምክንያቱ የላብ የ ፔኢች ደረጃ (pH level) አነሰተኛ ስለሆነ ነው።



ሆኖም ግን በባህል የለመድነው ፤ ለሚቆረጥለት ሰው ምች መኖር አለመኖሩን ፤ በቀለም አልያም በሽታ ጥንካሬ መለየቱ አዳጋች እንደሆነ ሳይንስ ይጠቁማል።


🧪 በቅጠሉ ውስጥ ምን አለ?


  • ኢሰንሺያል ኦይልስ(Essential Oils (Sesquiterpenes))

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት ዳማከሴ በውስጡ ያለው ኢሴንሻል ኦይልስ የተሰኙ ዘይቶች አሉት። ከእነኝህ ውስጥ ወደ 94% የሚጠጋው ሴስኩተርፔን  የሚባለው የዘይት አይነት ነው። ይህ ዘይት በባህሪው የሰውነት መቆጣትን (Inflammation) በመቀነስ የራስ ምታትንና የጡንቻ ህመምን ያስታግሳሉ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናቶች ይህንን በሰፊው አረጋግጠዋል።



ከዚህ ውህድም ባሻገር የሚከተሉት ውህዶችም ውስጡ ይገኛሉ።

  • ኢዩጀኖል (Eugenol) (በ 2007 በተደረገ ጥናት ተለይቷል)

ይህ ውህድ ባክቴሪያን የመግደልና ህመም የማስታገስ (Natural anesthetic) አቅም አለው።

  • ሮዝማሪኒክ አሲድ (Rosmarinic Acid)(በመቀሌ ዩንቨርስቲ በ 2015 በተደረገ ጥናት ተለይቷል)

በሰውነት ውስጥ ያሉ መርዛማ ነገሮችን (Free radicals) ለማስወገድ የሚረዳ ጠንካራ ጸረ-ኦክሲዳንት ነው። የሰውነት መቆጣትንም ይከላከላል።

  • ኡርሶሊክ አሲድ (Ursolic acid) (በ2020 ተለይቷል)

እጢ እድገትን ይቃወማል። የሰውነት ኡደትን ያስተካክላል።

  • አፒጂኒን(Apigenin) (በ2025 የእጽዋት ኬሚካል ጥናት በባህርዳር ተለይቷል)

የሰውነት መቆጣትን ይከላከላል። በጭንቅላት ውስጥ ያሉ የነርቭ ህዋሳትን ከጉዳት ይጠብቃሉ። ይህ ደግሞ ዳማከሴ ለከባድ የራስ ምታትና ለጭንቀት የሚሰጠውን ጥቅም ይመሰክራል።


አሁን ይህ ተአምር አይደለም። ዳማከሴ በተፈጥሮ በውስጡ በዛ ያሉ የመድሐኒትነት ባህሪ ያላቸው ውህዶች አሉት።


እነኝህ በሳይንስ የተረጋገጡት በውስጡ ያሉ ውህዶች ሲሆኑ ፤ ትልቁ ጥያቄ የሚሆነው ህመም ያስታግሳሉ ወይ? የሚለው ነው።


ይህንን ለመረዳት ከፋፍለን እንይ!


🔥 የሰውነት ትኩሳት እና መቆጣት


እ.ኤ.አ. በ2011 የተደረገው የአይጦች ጥናት ዳማከሴ የሰውነት ሙቀትን የመቀነስ (Antipyretic) አቅሙ ከፓራሴታሞል ጋር ሊቀራረብ እንደሚችል አመልክቷል።


ይህም በባህል ለረጅም ጊዜ የቆየ አጠቃቀሙን ያረጋግጣል። የሰውነት መቆጣትን ተከትሎ ለሚመጣ ራስምታት፣ ትኩሳት እና የጡንቻ ህመም ተጽእኖ አለው ተብሎ ይገመታል።


ይህንን በደንብ ለማረጋገጥ ፤ በሰው ላይ የተደረገ ጥናት ያስፈልጋል።


🩸የስኳር ቁጥጥር  


ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ የተደረጉ ጥናቶች አስደናቂ ነገር አግኝተዋል። የዳማከሴ ጭማቂዎች ለስኳር በሽተኞች ተሰጥተው ፤ የስኳር ቁጥጥር ላይ አስተዋእጾ አሳይተዋል።


ዳማከሴ በውስጡ አልፋ አሚሌዝ (Alpha-amylase) እና አልፋ ግሉኮሴድ( Alpha-glucosidase) የተባሉ ኢንዛይሞችን የማገድ ብቃት እንዳለው በጥናት ተረጋግጧል። እነዚህ ኢንዛይሞች ካርቦሃይድሬት ወደ ስኳር እንዳይቀየር ስለሚያደርጉ፣ ዳማከሴን መውሰድ ከምግብ በኋላ የሚመጣን ከፍተኛ የስኳር መጠን ለመቀነስ ይረዳል።


የዳማከሴ ጸረ-ኦክሲዳንት ባህሪ በቆሽት ውስጥ ያሉ Beta-cells (ኢንሱሊን የሚያመነጩ ህዋሳት) እንዳይጎዱ የመከላከል አቅም አለው። ይህም ተክሉ ለረጅም ጊዜ የስኳር ህመምተኞች እንደ ተጨማሪ (Adjunct) ህክምና ለመዋል የሚችል አቅም እንዳለው ይጠቁማል።  የሰውነት ኡድትን የማሻሻል አቅሙም ለስኳር ቁጥጥር ጠቅሟል ተብሎ ይገመታል።


እነኝህ ጥናቶች በላብራቶሪ እና በእንሰሳት ላይ የተደረጉ መሆኑ ሊስተዋል ይገባል። በሰዎች ላይ የተደረጉ ብዙ ጥናቶች ያስፈልጋሉ።


ሆኖም ዳማከሴ የየትኛው የስኳር መድሐኒት ምትክ አይደለም። ማገዣ ሆኖ ሊያገለግል ይችል ይሆናል።

🦠 ፀረ-ባክቴሪያ ባህሪ

እላይ እንዳየነው ዳማከሴ ውስጥ የሚገኘው ኢዩጀኖል የሚሰኘው ውህድ ባክቴሪያን የመቃወም ባህሪ አለው። ውስጡ ያሉ ኢሴንሻል ኦይልስም ለባክቴሪያ መቃወም አስተዋእጾ ያደርጋሉ።


እ.ኤ.አ. በ 2018 የተደረገ ጥናት የሽንት ቧንቧ መንስኤ የሆነው ኢ.ኮላይ (E. Coli) የተሰኘ ባክቴሪያን ይቃወማል። ዳማከሴ በውስጡ ባሉት ውህዶች አማካኝነት የባክቴሪያውን የውጭ ሽፋን (Cell wall) በማዳከም ይገድለዋል።


ባህላዊ ጥቅሙ ምናልባትም ትክክል ይሆናል!

ይበልጥ የሚገርመው

የዳማከሴ ጭስ ወይም ሽታ የትንኞችን የነርቭ ሥርዓት በማወክ አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ያደርጋል። ይህ በገጠር ለሚኖሩ ማህበረሰቦች የወባ በሽታን ለመከላከል ቀላልና ተመጣጣኝ መንገድ ነው።


🦟 የፀረ-ወባ ባህሪ

እ.ኤ.አ. በ 2016 በላብራቶሪ የተደረገ የወባ ህዋስ (ፕላዝሞዲየም) ጥናት እስከ 35.53% የሚደርስ የወባ ተህዋስን ዳማከሴ እንደቀነሰ ጠቁሟል።

ታድያ ለወባ መድሀኒትን ሊያገለግል ይችላልን?

አይ! በአሁኑ ወቅት የምንጠቀመው ፍቱኑ የወባ መድሐኒት አርተመንሲንን አይተካም።


ሆኖም ግን እነኝህ ባህሪያት ይህ ተክል አስፈላጊው ጥናትን ምርምር ቢደረግበት ከውስጡ ብዙ መድሐኒት መውጣት እንደሚችል ይጠቁማሉ።


🧻ለሆድ ያለው ጥቅም


 የምግብ  መፈጨት እና ፀረ-ተቅማጥ ባህሪም እንዳለው የሚጠቁም ጥናት በ 2022 ተደርጓል። ይህ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ዳማከሴ የአንጀትን መሸማቀቅ (Muscle contraction) በመቀነስ ተቅማጥንና ቁርጠትን ያስታግሳል። ይህም ተክሉ ቁርጠትን የመከላከል (Antispasmodic) ባህሪ እንዳለው ያሳያል።


⚖ ጤናማ አጠቃቀሙ እንዴት ነው?



ዘመናዊ ሳይንስ ከባህላዊ ሳይንስ አንጻር ያለው ልዩነት ይህ ነው። በግምት በዘፈቀደ ሳይሆን ለሰውነት ክብደት እና ቁመና የተሰላ አጠቃቀም ነው መኖር ያለበት።


እ.ኤ.አ በ 2023 የተደረገ የመርዛማነት ጥናት እንደሚያመላክተው ለረዥም ጊዜ የሚወስዱ ከሆነ ከ400 mg/kg ማለፍ የለበትም። ከዚህ ካለፈ የጉበት እና ኩላሊት ላይ ተጽእኖ ያሳድራል።


በጽንስ ላይ ተጽእኖ እንደሌለው በ 2022 የተደረገ ጥናት ጠቁሟል።


በውስጡ ያለው ሊድ እና ክሮሚየም መጠንም የዓለም ጤና ድርጅት በሚፈቀደው ገደብ ውስጥ መሆኑ ተረጋግጧል። ይህም ለመጠቀም ጤናማ መሆኑን ፤ ተጓዳኝ ጉዳቱ የተገደበ መሆኑን አመላካች ነው።


ዳማከሴ ከባህል ባለፈ ሳይንስ የመስከረለት እጽዋት ነው! በውስጡ የያዛቸው ተፈጥሮአዊ ውህዶች ለጤናችን ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ጥናቶች ያረጋግጣሉ። ስለሆነም፣ የዚህን ተክል ፈዋሽነት ተረድተን በዕውቀት እንጠቀምበት




 

Comments


bottom of page