የማይታወቁት የታይሮይድ በሽታ ምልክቶች
- Zebeaman Tibebu
- 1 day ago
- 3 min read
የዕለት ተዕለት ድካምዎን “ውጥረት ነው” ብለው አልፈውታል?
ልብዎ ሲመታስ “ደክሜ ስለሆነ ነው” በሚል ሰበብ ችላ ብለውታል?
ክብደትዎ ያለ ምክንያት ሲቀንስስ “ታድዬ” ብለው ተደስተዋል?

ነገር ግን… እውነታው ከዚህ የተለየ ሊሆን ይችላል!
በአንገትዎ ስር የምትገኝ አንዲት ትንሽ እጢ መላ ሕይወትዎን ልታመሰቃቅል እንደምትችል ያውቃሉ? ብዙ ሴቶች ከፍተኛ ድካም ሲሰማቸው “ሥራ በዛብኝ”፣ ሲጨነቁ ደግሞ “ኑሮ ከበደኝ” በማለት ምልክቶቹን ያስታክካሉ። ይሁን እንጂ ራስዎን አይውቀሱ፤ ዋናው ጥፋተኛ የእርስዎ ደካማነት ሳይሆን የታይሮይድ ሆርሞን መዛባት ሊሆን ይችላል። ይህንን ለመረዳት ስለ ታይሮይድ እጢ እና ስለ ተያያዥ ችግሮቹ በጥልቀት እናንሳ።
የታይሮይድ እጢ

ታይሮይድ በአንገታችን የፊት ለፊት ክፍል ላይ የምትገኝ ትንሽ እጢ ነው። ስራውም ሰውነታችን ሃይልን እንዴት መጠቀም እንዳለበት መቆጣጠር ነው። ይህም እጢ ሁለት ዋና ዋና ሆርሞኖች (T3 እና T4) ያመርታል። እነዚህም ሆርሞኖች የልብ ምትን ፣ የሰውነት ሙቀትን ፣ የሃይል መጠንን እንዲሁም የወር አበባ ዑደትን ይቆጣጠራሉ። ሰውነት ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ሆርሞኖች ላይም ተጽእኖ ያሳድራሉ። ለዚህም የታይሮይድ ስራ ሲዛባ መላው ሰውነት ትርምስ ውስጥ ይገባል።
ሴቶች ለምን በብዛት ይጠቃሉ?
የታይሮይድ እጢ በሽታ የተለመደ ነው። ይህም በሽታ በይበልጥ በሴቶች ላይ ይታያል። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ሴቶች ከወንዶች ይልቅ በታይሮይድ ችግር የመጠቃት እድላቸው ከ5 እስከ 8 እጥፍ የላቀ ነው። ከስምንት ሴቶች አንዷ በሕይወት ዘመኗ የታይሮይድ ችግር ያጋጥማታል ተብሎ ይታሰባል።

ይህ በሽታ በሴቶች ላይ በብዛት የሚታይባቸው ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡-
የሆርሞን ለውጥ ፦ የሴቶች የታይሮይድ ዕጢ ከ ሴት ልጅ ኢስትሮጅን (Estrogen) ሆርሞን ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለው። ለዚህም በጉርምስና፣ በወር አበባ ዑደት፣ በእርግዝና እና ማረጥ (Menopause) ወቅት የሚፈጠሩ ከፍተኛ የሆርሞን መለዋወጦች ለታይሮይድ መዛባት መንስኤ ይሆናሉ።
የሰውነት መከላከያ ሥርዓት ፦ ሴቶች በተፈጥሮ ጠንካራ የመከላከያ ሥርዓት ቢኖራቸውም፣ ይህ ሥርዓት ተሳስቶ የራሳቸውን አካል የሚያጠቃበት ዕድል በሴቶች ላይ ይበልጣል። ለዚህም ሀሺሞቶ (Hashimoto's) እና ግሬቭስ (Graves') የተባሉት የታይሮይድ በሽታዎች ተጋላጭነታቸው ያየለ ነው።
ከወሊድ በኋላ የሚመጣ ለውጥ፦ በእርግዝና ወቅት የታይሮይድ ስራ ይጨምራል። ብዙ ሴቶች ከወለዱ በኋላ ባለው አንድ ዓመት ውስጥ የታይሮይድ ዕጢ እብጠት ወይም መዛባት (Postpartum thyroiditis) ሊያጋጥማቸው ይችላል።
በዘር መተላለፍ፦ በሴቶች ላይ የሚገኘው የኤክስ ክሮሞሶም (X chromosome) ከሰውነት መከላከያ ሥርዓት ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ ለታይሮይድ ችግር የመጋለጥ እድላቸውን ከወንዶች የበለጠ ያደርገዋል።
የታይሮይድ ሆርሞን መዛባት ችግሮች
ታይሮይድ እጢ የሚያመርተው የታይሮይድ ሆርሞን ምርት በተለያዩ በሽታዎች እና እክሎች የተነሳ ሊዛባ ይችላል። የዚህም ሆርሞን ማነስ ወይም መብዛት መላ ሰውነት ላይ የሚያሳድረው ከፍተኛ ተጽእኖ አለው። ለዚህም ምልክቶቹም ይለያያሉ።
የታይሮይድ ሆርሞን ማነስ ካጋጠመ በህክምናው ሃይፖታይሮይዲዝም (Hypothyroidism) ይባላል።

ይህ ካለብዎ የሚከተሉት ምልክቶችን ሊያዩ ይችላሉ።
ከፍተኛ ድካም፣
የሰውነት ክብደት መጨመር፣
ብርድ ብርድ ማለት፣
ቅዝቃዜን አለመቻል፣
የምግብ መፈጨት መዘግየት እና
የመደበት ስሜት ሊያስተውሉ ይችላሉ።
ይህ ደግሞ ብዙ ጊዜ "ከእድሜ ጋር የመጣ ድካም" ተብሎ በቸልታ ይታለፋል። ይህ ሊስተካከል ይገባል።
የታይሮይድ ሆርሞን ሲበዛ ፤ ሃይፐር ታይሮይዲዝም (Hyperthyroidism) ይባላል።

ይህን ጊዜ ሰውነታችን ብዙ ኃይል ስለሚኖረው/ስለሚያገኝ አለልክ ሊፈጥን ወይም ሊሮጥ ይችላል። በሽታው ካለብዎ፦
ያለምክንያት ክብደት መቀነስ፣
የልብ ትርታ መጨመር፣
ሙቀት አለመቻል
ከፍተኛ ላብ እና
ጭንቀት ሊስተዋል ይችላል።
ይህም ብዙ ጊዜ እንደ "ተራ የኑሮ ውጥረት" ተደርጎ ይወሰዳል። ታማሚዎችም ቢያርፉ እንደሚሻላቸው ሰው አብዝቶ ይመክራቸዋል። እውነታው ግን ከዚህ የራቀ ነው።
የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ
በኢትዮጵያ የታይሮይድ በሽታ የራሱ የሆነ መልክ አለው። በኢትዮጵያ የታይሮይድ ዕጢ (እንቅርት) እና የአዮዲን እጥረት አሁንም ድረስ በከፍተኛ ደረጃ የሚታዩ የጤና እክሎች ናቸው። በቅርብ ጊዜ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ዕድሜያቸው ከ6 እስከ 12 ዓመት ከሆኑ 10 ሕፃናት አራቱ ላይ የእንቅርት በሽታ ይስተዋላል። ይህም ችግሩ “በጣም አሳሳቢ” ደረጃ ላይ እንደሆነ ጠቋሚ ነው።

ችግሩ በተለይ በኦሮሚያ (46.7%)፣ በደቡብ (44.22%) እና በአማራ (41.86%) ክልሎች በስፋት ይታያል። ይህም ከአፈር መሸርሸር እና ከአመጋገብ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው። ከሚታከሙ ታካሚዎች መሀከል ወደ 61 በመቶ የሚጠጉት የሆርሞን መብዛት ችግር ሲኖርባቸው 34.3% ሆርሞን ማነስ ችግር አላቸው።
ባይታከምስ?
የታይሮይድ ችግር የመልክ ወይም የክብደት ጉዳይ ብቻ አይደለም። የታይሮይድ እክክሎች በአካልም ሆነ በስነ-ልቦና ላይ የሚያደርሱት ተፅዕኖ በጣም ሰፊ ነው።

ሳይንሳዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ካልታከመ፦
ለልብ እና ለኮሌስትሮል ችግር ያጋልጣል፦ በተለይ የታይሮይድ ሆርሞን ማነስ የልብ ምትን በመቀነስ እና "መጥፎ" የተባለውን ኮሌስትሮል (LDL) በመጨመር ለልብ ድካም እና ለደም ቧንቧ መጥበብ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
የአጥንት ጤናን ያውካል፦ በተቃራኒው ደግሞ የታይሮይድ ሆርሞን ከመጠን በላይ መመረት ባለው እጅ አዙር ተጽእኖ አጥንት እንዲሳሳ ያደርጋል።
ለስነ-ልቦና ቀውስ ይዳርጋል፦ የታይሮይድ ሆርሞን መዛባት በአንጎል ውስጥ ያሉ ስሜትን የሚቆጣጠሩ ውህዶችን (Neurotransmitters) ስለሚያዛባ፣ ለከፍተኛ ጭንቀት፣ ለድብርት እና ለትኩረት ማጣት ይዳርጋል። ይህም የእለት ተእለት ኑሮን እና ማህበራዊ ቁርኝትን ያስተጓጉላል።
ከእነዚህም በተጨማሪ የታይሮይድ ችግር ካልታከመ ፤ ለመሃንነት ወይም በእርግዝና ወቅት ፅንስ ለመቀነስ አደጋ ሊያጋልጥ ይችላል።
መፍትሄው ምንድነው?

የሚያስገርመው ነገር፣ ለዓመታት ለተሰቃዩበት ጥያቄ መልሱ አንድ ቀላል የደም ምርመራ ነው። ይህም የቲኤስ ኤች ወይም የታይሮይድ ምርመራ (TSH Test) ነው። ይህ ምርመራ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በስፋት ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ ሐኪምዎ የአንገት አልትራሳውንድ እና ሌሎች የደም ምርመራዎችን ሊያዝልዎት ይችላል።
በእነዚህ ምርመራዎች ላይ ተመስርቶ ፤ የሚዋጥ መድሀኒት እንዲሁም የቀዶ ጥገና ሕክምና ሊያስፈልግዎ ይችላል።
ያስተውሉ!
የሚደክምዎ አልያም ውጥረት የሚያሰቃይዎ በእርስዎ ጉድለት ላይሆን ይችላል።
የታይሮድ እጢዎን ይመርመሩ። ምልክቶቹን ካዩ የህክምና እርዳታ ይፈልጉ።
ሕክምናውም ቀላል እና እጅጉን ውጤታማ ነው።
ዛሬውኑ እርምጃ ይውሰዱ። ለጤናዎ ቅድሚያ ይስጡ!





Comments