top of page

ታመው ካልተኙ ሆስፒታል አይሄዱም?

አያድርገውና ! ድንገት ያላሰቡት ቀን...


በሩን ሳይሰበር ፣ ድምጽ ሳያሰማ አንድ ሌባ መኖርያ ቤትዎ ገብቶ ቢደበቅስ?


እርስዎ በተኙበት ፤ አልያም ቤት በሌሉበት ሰአት ንብረትዎን ለመስረቅ ፤ እርስዎን ሊያጠቃ ይህ ሌባ አድብቷል እንበል።



እድለኛ ሆነው ድንገት ካላዩት በስተቀር ፤ መኖሩን የሚጠቁም ምንም ምልክት የለም። ምንም ድምጽ የለም። እርስዎ የሆነ ነገር መበላሸቱን የሚረዱት ንብረትዎ ሲጎድል ፤ አልያም ጥቃት ሲደርስብዎ ብቻ ነው።


እና ምን ተሻሎት!?

"ኧረ አንድ በሉት ይሄ ሰው ተነሳ!" ብለው ባለቅኔ እና ገጣሚ ከበደ ሚካኤል ግጥማቸውን እንዳሳረጉት ፤ እርሶም አርፍደው ቢያውቁ ምን ይበጅዎ!? ቢሆንማ.... ቀድሞ ቢነቁ ፤ ሌባውን ቢይዙ ፤ ንብረቶን ባላጡ እርሶም ባልተጎዱ ነበር።


ዛሬ የምናወራው ስለ ቅድመ ምርመራ ነው። ብዙ ከባድ በሽታዎች የመጀመሪያው የህመም ምልክት ከመታየቱ በፊት ለዓመታት በሰውነት ውስጥ በዝምታ ይኖራሉ። እንደሌባው ያደባሉ። ተደብቀው ጊዜ ይጠብቃሉ። ሕመሙን ያስተዋሉ ጊዜ ግን ቀድሞውኑ ጉዳቱ የከፋ ሊሆን ይችላል።


በሕክምናው ይህንን በሽታው አድብቶ የሚቆይበትን ጊዜ ምልክት የለሽ ምዕራፍ (Asymptomatic phase) እንለዋለን።



በአለም ዙሪያ ብዙሀን ለረዥም ጊዜ ሆስፒታል ለመሄድ ፤ ሕመሙ ከአቅም በላይ እስኪሆን ይጠብቁ ነበር። በቅርብ አመታት ግን ለውጥ ይታያል።


ሆኖም ብዙ ኢትዮጵያውያን ህክምና ፍለጋ የሚሄዱት ፤ በሽታው ከደረጀ ፤ ከባድ ጉዳት ካደረሰ በኋላ ነው። ለዚህም በኢትዮጵያ ስር ሰደድ ህመሞች እና ካንሰሮች የሚገኙት አስጊ ደረጃ ላይ ነው።


የቅድመ ምርመራ ታሪክ ፡ ከፍርሃት ወደ አርቆ አስተዋይነት


ዘመናዊው የቅድመ ምርመራ ሀሳብ የተጀመረው በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ነው። ይህን ጊዜ ላይ ሳይንቲስቶች በሽታ የሕመም ምልክት ከመሳየቱ በፊት ሊታወቅ እንደሚቻል ተገነዘቡ። ለዚህም ቀድሞ በሽታውን ማግኛ ዘዴዎችን መመራመር ጀመሩ።


ከመጀመሪያዎቹ ስኬቶች አንዱ በዶክተር ጆርጅ ፓፓኒኮላው የተዘጋጀው የፓፕ ስሚር (Pap smear) ምርመራ ነበር። ይህ ቀላል ምርመራ የማህጸን ጫፍ ካንሰር ከመፈጠሩ በፊት ለመያዝ አስቻለ። የማህጸን ጫፍ ህዋሳት የሚያሳዩትን ቅድመ ካንሰር ለውጦች በምርመራ ለመለየት ተቻለ። ይህም በዓለም ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን አድኗል ፤ የጤና ምህዳራቸውንም አሻሽሏል።



ከጊዜ በኋላ ቅድመ ምርመራ ወደ ሌሎች የጤና ሁኔታዎች ተስፋፋ። ለምሳሌ ፦

  • ለደም ግፊት

  • ለስኳር በሽታ

  • ለስር የሰደደ የኩላሊት ህመም

  • ለጉሮሮ ካንሰር

  • አዲስ ለተወለዱ ሕፃናት የሚደረጉ ሜታቦሊዝም(ሰውነት ኡደት) ምርመራዎች፣ ወ.ዘ.ተ... ይውል ጀመር።


የማህበረሰብ ጤና ሳይንስም እጅጉን ተለወጠ። ሕመም እስኪመጣ ከመጠበቅ በሽታን ቀድሞ ወደ መፈለግ ተቀየረ። ከተሰረቁ በኋላ ከማወቅ ሌባውን ቀድሞ ወደ መያዝ ተሸጋገረ። ኢትዮጵያም ይህንን በከፍተኛ ሁኔታ እየተገበረች ትገኛለች።


ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እጅጉን በመስፋፋታቸው ፤ ጤና ጥበቃ እና ባለድርሻ አካላትም ቅድመ ምርመራ ላይ በትጋት እየሰሩ ይገኛሉ። ለምሳሌ በማህጸን ጫፍ ካንሰር ዙሪያ ኢትዮጵያ ታላላቅ ዘመቻዎች አካሂዳለች። በ 3 ወራት ጊዜው ስጥ ብቻ ከ275,000 በላይ ሴቶች ተመርምረው፤ ከ13,000 በላይ የቅድመ ካንሰር ምልክቶች የታዩባቸው ሴቶች ወዲያውኑ ሕክምና እንዲያገኙ ተደርጓል። ይህም የአስራ ሶስት ሺ ሴቶችን ህይወት ማዳን ተችሏል ማለት ነው።


ከማህጸን ጫፍ ካንሰር ባሻገርስ?


ከካንስር ህመሞች ባሻገር ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ (CKD) እየተስፋፋ ይገኛል። ስሙን ለይተው ባያውቁትም ፤ መቼም ስለ እርሱ ሰምተዋል። ለብዙዎች የኩላሊት ድክመት መሰረት ነው።



በየቀኑ በግምት ከ150 ሊትር በላይ ደም የሚያጣሩ እና ቆሻሻን የሚያስወግዱ ኩላሊቶች ፤ በመታት ውስጥ እየተዳከሙ ይመጣሉ።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ፤ ኩላሊቶች ምንም አይነት ምልክት ሳያሳዩ እስከ 90% የሚሆነውን ተግባራቸውን ሊያጡ ይችላሉ።


ይህ ማለት ብዙ ሰዎች ኩላሊታቸው እጅጉን እየተጎዳ ቢሆንም ፤ ሙሉ በሙሉ ጤናማ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ኩላሊት ስራው እስኪሰናከል ድረስ ምንም ምልክት አያስተውሉም።


ለዚህም በሽታ መስፋፋት በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ዙሪያ ዋነኛ መንስኤ ተደርገው የሚጠቀሱት በሽታዎች እነዚህ ናቸው። ፦

  1. ከፍተኛ የደም ግፊት (Hypertension)

  2. የስኳር በሽታ (Diabetes mellitus)

  3. አንዳንድ ኢንፌክሽኖች እና ያልታከሙ ስር የሰደዱ በሽታዎች


ይህንን በሽታ ቀድሞ ለማወቅና ኩላሊትን ለማትረፍ ቅድመ ምርመራ እጅጉን አስፈላጊ ነው።


ያለ ቅድመ ምርመራ፣ የኩላሊት በሽታ ብዙ ጊዜ የሚታወቀው የኩላሊት ሥራ እጅጉን ከተዳከመ በኋላ ነው።

ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የኩላሊት ቅድመ ምርመራ የሚያደርገው የማህበረሰብ ክፍል አነስተኛ ነው።


እናስ ምን ተሻለ?


"ጤነኛ ነኝ" ከሚል ስሜት በትክክል ጤነኛ ወደ መሆን ለመሸጋገር ፤ የጤና አገልግሎት ወደ ማህበረሰቡ መዳረስ ይኖርበታል። ይህንንም ለማዳረስ የቅድመ ምርመራ ዘመቻዎች ያስፈልጋሉ። እነዚህ ዘመቻዎች ካልታመመ ለማይሄደው ፤ "ኩላሊቴ ጤናማ ነው!" ብለው አስበው ለሚቀመጡት ብዙሀን እጅግ ያስፈልጋሉ።


ይህንንም ለማዳረስ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እየሰሩ ይገኛሉ።



ያለፈው መጋቢት 3 የተግባር በጎ አድራጎት ድርጅት ከ ኢትዮጵያ ኪድኒ ኬር (Ethipian kidney Care) ከጊቭ ሶሳይቲ ኢትዮጵያ (GIV Society Ethiopia)፣ ከ አደይ ሮታራክት ክለብ (Rotaract Club of Adey) እና ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የኩላሊት ቅድመ ምርመራ ዘመቻ አካሂዷል። እንዲህ ዓይነቱ መርሐ ግብር ኩላሊትን ጤና ከመመርመር ባሻገር ፤ ቀደምት የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ለመለየት የሚያስችሉ አስፈላጊ ምርመራዎችን ያቀርባል።


እንደ ደም ግፊት እና ስኳር ያለባቸው ፤ እንዲሁም የኩላሊታቸው የማጣራት አቅም እየተዳከመ ያሉ ግለሰቦችንም ለመለየት ተችሏል።

ተጋላጭነት ያለባቸው ሰዎች የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ እንዲያሳዩ ተመክረዋል። ኩላሊታቸው ለውጥ ላሳዩት ደግሞ ፤ ከአኗኗር ምክር ባሻገር አስፈላጊው የህክምና እርዳታ እና ክትትል እንዲጀምሩ ተደርገዋል።

ያስተውሉ! ቅድመ ምርመራ ለታመሙ ሰዎች ብቻ አይደለም ፤ ለአስተዋዮችም ነው።

ምርጡ የህክምና አማራጭ ቀዶ ጥገና ወይም መድኃኒት አይደለም። ብዙ ጊዜ ቅድመ ምርመራ ማድረግ ይሻላል።


የኩላሊት ቅድመ ምርመራ ለነማን ያስፈልጋል?

ምንም እንኳን ሁሉም ሰው መመርመሩ መልካም ቢሆንም፣ የሚከተሉት ሰዎች ግን በየዓመቱ ምርመራ ቢያደርጉ ይመከራል፦


  • የስኳር ሕመምተኞች፦ ስኳር የኩላሊት ትንንሽ የደም ስሮችን ስለሚጎዳ።

  • የደም ግፊት ያለባቸው፦ ከፍተኛ ግፊት ኩላሊት ላይ ጫና ስለሚፈጥር።

  • ከመጠን በላይ ውፍረት ያላቸውና የልብ ሕመም ያለባቸው።

  • በቤተሰባቸው ውስጥ የኩላሊት ሕመም ያለባቸው።

  • ዕድሜያቸው ከ60 በላይ ለሆነ ።

  • የህመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን (NSAIDs እንደ Ibuprofen/Diclofenac ያሉ) አዘውትረው የሚጠቀሙ።


እንዴት የቅድመ ምርመራ ማድረግ ይችላሉ?


ኩላሊት መጎዳቱን ለማወቅ ውድና ውስብስብ ምርመራ ሁልጊዜ አያስፈልግም። ይህንን በሁለት ቀላል መንገዶች ማረጋገጥ ይቻላል፦

  • የሽንት ምርመራ (Urine Test)፦ በሽንት ውስጥ ፕሮቲን (Albumin) መኖሩን ማየት። ፕሮቲን በሽንት መውጣቱ የኩላሊት ማጣሪያዎች መጎዳታችውን/መሳሳታቸውን የሚያሳይ የመጀመሪያው ምልክት ነው።

  • የደም ምርመራ (Creatinine/eGFR)፦ በደም ውስጥ ያለውን የቆሻሻ መጠን በመለካት ኩላሊት በምን ያህል አቅም እያጣራ እንደሆነ ያሳያል።


ከቅድመ ምርመራ ባሻገርስ ምን ላድርግ?

ሌባው እንዳይገባ በሩን መቆለፍ እንደሚቻለው ሁሉ፣ ኩላሊትንም በእነዚህ መንገዶች መጠበቅ ይቻላሉ፦

  • ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መድኃኒቶችን አይውሰዱ፦ በተለይ የህመም ማስታገሻዎች (እንደ Diclofenac, Ibuprofen ያሉ) በብዛት መውሰድ ኩላሊትን ክፉኛ ይጎዳል።

  • ጨው መቀነስና ውኃ አብዝቶ መጠጣት ይመከራል፦ ይህ የደም ግፊትን ለመቆጣጠርና ኩላሊት ስራውን እንዲያቀላጥፍ ይረዳል ።

  • ስኳርንና ግፊትን መቆጣጠር ይኖርብዎታል፦ ይህ ለኩላሊት ጉዳት የሚያጋልጡ ዋናዎቹን መንስኤዎች በማከም ኩላሊት ያለበት ጉዳት እንዳይባባስ ያደርጋል።


በኢትዮጵያ የዲያሊሲስ (Dialysis) ወይም የኩላሊት ንቅለ ተከላ (Transplant) ወጪና ተደራሽነት እጅግ አስቸጋሪ መሆኑ፣ ቅድመ ምርመራ ብቸኛውና አስተማማኙ አማራጭ ያደርገዋል።


አሁን ተራው የእርስዎ ነው!


እስቲ ራስዎን ይጠይቁ


'የመጨረሻ ጊዜ የደም ግፊት፣ ስኳር ወይም የኩላሊት ምርመራ መቼ አደረጉ?'


ምርመራውን ዛሬውኑ በማድረግ ራስዎን እና ቤተሰብዎን ከከፍተኛ የሕክምና ወጪ እና ከሥነ-ልቦና ስብራት ይታደጉ።


"ቅድመ ምርመራ ለአስተዋዮች ነው!"



Comments


bottom of page