top of page

በህጻንነት ራሰ በራ ሊያደርግ የሚችለው ቆሮቆር በሽታ

የቆዳ ሐኪምቤቱ እንደተለመደው በታካሚዎች ተሞልቷል። ከታካሚዎቹ መካከል አንዷ እናት የ7 ዓመት ሴት ልጇን እጅ ይዛ በጭንቀት ትጠብቃለች። የመጣችው ለተለመደው ጉንፋን ወይም ትኩሳት አልነበረም... የልጇ ፀጉር መሀል ላይ ክብ ክብ ቅርጽ የያዘ ሽፍታ/እድገት ለማሳየት ነበር።


ህመሙ ከጀመረማ ሳምንታት ተቆጥረዋል። መጀመሪያ ፎሮፎር ነው ብላ የጸጉር ቅባት በደንብ ትቀባት ነበር። ሆኖም ግን ልጇ አልተሻላትም ነበር። ግራ ሲገባት ፋርማሲ ሄዳ አማክራ የሚቀባ መድሐኒት ይዛ መጣች። ለቀናት ባለሙያው እንደመከራት አደረገች። ለውጥ የለም!

እድገቱ ከመስፋፋቱም ባሻገር መግል ያዘ። ሲጀምር አንድ ብቻ እንዳልነበር ፤ አሁን ጸጉሯን ሙሉ ወረረው። ቀን በቀን ማታ ላይ ታጥባት ነበር ሆኖም ግን ለሊቱን ሙሉ መግል ይዞ ያድር ነበር። ይብሱኑ ብሎ ጸጉሯ መሳስት ጀመረ። ይህች እናት የልጇ ሁኔታ እጅጉን ጨነቃት!


አንድ ያማከረችው ግለሰብ ፤ ካልታከመች በልጅነቷ ጸጉሯ ሊመለጥ እንደሚችል ሲነግራት ሮጣ የቆዳ ሐኪም ቤት ይዛት መጣች። የሰዉ መብዛት አልተስተዋላትም። ከነበራት ጭንቅ እና ካሳለፈቻቸው ሳምንታት ፤ ይህ ምንም አይደለም።


ይህ ታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ ልጆችን ያጋጥማል። ዛሬ የምናነሳው በተለምዶ ስሙ ቆሮቆር ስለሚሰኘው በሽታ ነው።


ይህ ችላ የምንለው የልጅነት በሽታ ሳይሆን ፤ ህክምና ካልተደረገ ... ጸጉርን ራሱ ሊያሳጣ የሚችል በሽታ ነው።

ቆሮቆር ምንድነው?


ይህ በህክምና ስሙ ቲንያ ካፒቲስ (Tinea Capitis) የሚሰኝ የራስ ቅል የፈንገስ በሽታ ነው። ዋነኛ መንስኤዎቹ ትሪኮፊቶን (Trichophyton) እና ማይክሮስፖረም (Microsporum) የሚባሉ የፈንገስ ዝርያዎች ናቸው። ይህ ፈንገስ የራስ ቅል ቆዳን ከማጥቃቱም ባሻገር ወደ ጸጉር ስር ዘልቆ በመግባት ፀጉሩን ሊበላው ይችላል። ይህን ጊዜ ያሳክካል። ይህ ኢንፌክሽን ለእይታ የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያሳይ ይችላል።


  • ጥቁር ነጥብ (Black Dot): ፀጉሩን ከመሬት እኩል ስለሚበሉት እንደ ጥቁር ነጥብ ሆኖ ይታያል።

  • ግራጫማ ንጣፍ (Gray Patch): ቆዳውን ድርቅ ያለና አመድማ ያደርጉታል። ለዚህም መልኩ የገረጣ ይመስላል።


እነኝህ በሽታው መለስተኛ ሲሆኑ የሚታዩ ናቸው። በሽታው ግን ከደረጀ ኬሪዮን ኬሪዮን (Kerion) የሚሰኝ ከባድ ገጽታ ያሳያል።  ይህ ባለታሪኳ ልጅ ላይ የታየው ሲሆን ፤ ከፍተኛ እብጠትና መግል አለው። ይህም ሰውነት ፈንገሱን ለመከላከል የሚያደርገው ከፍተኛ ትግል ውጤት ነው። ታድያ ግን በአግባቡ ካልታከመ ፤ ፀጉሩ እስከመጨረሻው እንዳይበቅል ሊያደርገው ይችላል።


ባይታከምስ ምን ያመጣል?


ከካናዳ ሜዲካል ጆርናል የተወሰደ ኬርዮን የሚሰኝወን የቆሮቆር ከባድ ቁስል የሚያሳይ ምስል
ከካናዳ ሜዲካል ጆርናል የተወሰደ ኬርዮን የሚሰኝወን የቆሮቆር ከባድ ቁስል የሚያሳይ ምስል

አለመታከም ብቻ ሳይሆን ፤ በሽታው በጊዜ ካልታከመ ከቆዳ ህመም አልፎ የሚከተሉትን ችግሮች ያመጣል፦

  • የእድሜ ልክ ጠባሳ

  • በልጅነት ራሰ በራነት

  • እየተባባሰ የሚሄድ ተደራቢ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ሊያመጣ ይችላል።


ከዚህም ባሻገር የስነልቦና ጫናም ይፈጥራል። ልጆች በትምህርት ቤታቸው ይገለላሉ። በእድሜ እኩዮቻቸው መሳለቂያ ይሆናሉ። ይህም ስነልቦና ጫና ከትምህርት ገበታ እንዲቀሩ ሊዳርጋቸው ይችላል። ባህሪያቸውም ላይ ተጽእኖ ያሳድራል።



በሽታው እንዴት ይሰራጫል?



በሽታው በፈንገስ ስለሚመጣ ፤ መተላለፊያ መንገዱም ከታመመ ልጅ ወደ ጤነኛ ፈንገሱ እንዲተላለፍ እድል የሚፈጥሩ ጉዳዮች ብቻ ናቸው። ለምሳሌ፡

  1. የቀጥታ ግንኙነት፦ በትምህርት ቤት ጨዋታ ላይ ልጆች ራስ ከተነካኩ።

  2. የጋራ ቁሳቁስ፦ በተለይ በቤተሰቦች የተለመደው የጋራ ማበጠሪያ፣ ኮፍያ፣ ፎጣ እና ትራስ መጠቀም ሊያስተላልፍ ይችላል።

  3. የፀጉር ቤቶች፦ በአግባቡ ያልተጸዱ(ስቴራላይዝ ያልተደረጉ ) ቶንዶሶች/የጸጉር መቁረጫዎች በሽታውን ያስተላልፋሉ።

  4. የቤት እንስሳት፦ አንዳንዴም ቢሆን ድመቶችና ውሾች ለበሽታው ተሸካሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ ግን ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ባይሆንም ፤ እንሰሶች ሲያዙ ምልክት ላያሳዩ ስለሚችሉ መጠንቀቁ መልካም ነው።


በኢትዮጵያ ለምን ተስፋፋ?


የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ5 ልጆች አንዱ በዚህ ኢንፌክሽን ይያዛል። የዚህም ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚታሰበው የትምህርት ክፍሎች መጨናነቅ ነው። ከዚህም ባሻገር በአንድ ቤት ውስጥ ብዙ ሰው መኖር እና የንጹህ ውሃ እጥረትም ለበሽታው ስርጭት አስተዋእጾ ያደርጋሉ።



እላይ እንዳለችው እናት ሕክምናን ማዘግየት ፤ በሽታው እንዲደረጅ እድል ከመፍጠሩም በላይ ልጆች ላይ የእድሜ ልክ ጠባሳ ሊተው ይችላል።


እንዴት መመርመር ይቻላል?


ሐኪሞች በሽታውን ለመለየት ሁለት ዋና መንገዶችን ይጠቀማሉ፦

  1. የባለሙያ(ዶክተር) ምርመራ : ይህ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የፀጉሩን መርገፍ ሁኔታ፣ የቆዳውን መላጥ እና የቆሰሉ ምልክቶችን በማየት ብቻ ሊያውቁት ይችላሉ።

  2. የናሙና ምርመራ: ይበልጥ እርግጠኛ ለመሆን ጥቂት የፀጉር ዘንግ ወይም የቆዳ ቅርፊት ወስዶ በማይክሮስኮፕ በማየት (KOH) አልያም በልዩ መብራት ስር ታይቶ ሊታወቅ ይችላል።



ሕክምናውስ ምንድነው?

ቆርቆር በቤት ውስጥ በሚደረግ ጥረት ወይም በቅባት ብቻ አይድንም። ለዚህም ነው ለባለታሪኳ የጸጉር ቅባት እና የቤትውስጥ ክትትል ለውጥ ያላመጣው።


  • የሚዋጥ መድኃኒት ፦ ፈንገሱ በፀጉር ዘንግ ውስጥ ስለሚደበቅ፣ በሐኪም የሚታዘዙ የሚዋጡ ኪኒኖች ለተከታታይ ሳምንታት መሰጠት አለባቸው።

  • ፈንገስን የሚቃወም ሻምፑ፦  የፈንገሱን ስርጭትን ለመቀነስ የፈንገስ መቃወሚያ ሻምፑዎችን መጠቀም እንደ ረዳት ሕክምና ያገለግላል።

ያስተውሉ! ይህ ፈንገስ በሚቀቡ መድሐኒቶች አልያም በሻምፖዎች ብቻ አይድንም

ፈንገሱ በፀጉር ዘንግና ስር ውስጥ ስለሚደበቅ መድኃኒቱ በደም በኩል መድረስ አለበት። አለበዛ ፈንገሱን ሙሉ በሙሉ አያገኘውም። ለዚህም ነው ባለታሪኳ እናት ፋርማሲ ሄዳ የወሰደችው መድሐኒት ያላዳናት።


እንዴት መከላከል ይቻላል?

በሽታው በቤተሰብ እና በትምህርት ቤት ውስጥ እንዳይሰራጭ እነዚህን ነጥቦች መተግበር ይገባል፦

  • ቁሳቁስ አለመጋራት፦ ልጆች የራሳቸው ማበጠሪያ፣ ኮፍያ እና ፎጣ እንዲኖራቸው ማድረግ ።

  • የፀጉር ቤት ጥንቃቄ፦ ከተቻለ ልጆች ወደ ፀጉር ቤት ሲሄዱ የራሳቸው መቁረጫ/ቶንዶስ ይዞ መሄድ መልካም ነው። ይህ ካልተቻለ የጸጉር ቤቱ መሣሪያዎቹ በኬሚካል / በመሳሪያ መጽዳታቸውን ማረጋገጥ ይመከራል።

  • የቤት እንስሳት ንፅህና፦ በቤት ውስጥ ያሉ ውሾች ወይም ድመቶች የፀጉር መርገፍ ካለባቸው ወደ እንስሳት ሐኪም ወስደው ያሳክሙ።

  • ልብስን በሙቅ ውሃ ማጠብ፦ የታመመ ልጅ የሚጠቀምባቸውን አንሶላዎችና ትራሶች ሙሉ በሙሉ በሙቅ ውሃ ይጠቡ። ይህ ፈንገሱን ያጠፋል።


የባለታሪኳ ህጻን እጣ ፈንታ እንዴት ሆነ ?


ተራዋ ደርሶ የቆዳ ሕክምና እስፔሻሊስት ጋር ገባች። ባለሙያውም የበሽታውን ሁኔታ ካስተዋለ እና ከመረመረ በኋላ አስፈላጊ የላብራቶሪ ምርመራዎች አዘዘላት። ምርመራዎቹም ጥርጣሬውን ስላረጋገጡለት። ለሁለት ወር የሚወሰዱ የሚዋጡ እና የሚቀቡ መድሀኒቶች አዘዘላት።


መድሀኒቶቹን መውሰድ እንደጀመረች ወዲያውኑ ለውጦችን በደንብ አላስተዋለችም ነበር። ከሁለት ሳምንት በኋላ ግን የፈንገሱም ቁስል መድረቅ ጀመረ። እድገቶቹ ሁሉ ከሰሙ። በሁለተኛ ወር ላይም ህጻኗ ወደ ሙሉ ጤናው ተመለሰች።


ይህን ያስተውሉ!


በመዘግየትዎ ለልጅዎ የእድሜ ልክ ጠባሳ ሊተዉ ይችላሉ። ለዚህም ምልክቶቹን እንዳስተዋሉ ፈጥነው የሕክምና እርዳታ ይፈልጉ።


Comments


bottom of page