ልቧ ከሷ ቀድሞ ዝሎ ነበር! የራሂማ ታሪክ
- Zebeaman Tibebu
- Mar 18
- 4 min read
ልጅነት ተጫውቶ ፣ ተሯሩጦ ከ እድሜ እኩዮች ጋር ተሳስቆ የሚታለፍ እጅጉን ደስ የሚል ጊዜ ቢሆንም ፤ ሁሉም ልጆች ለዚህ አልታደሉም።
እንደ ማንኛውም ሴት ልጅ በትምህርት፣ በሳቅ እና በጨዋታ ታሳልፍ የነበረችው ራሂማም ፤ በጊዜ በሂደት ውስጥ ቶሎ መዝለልና መጫወት አቃታት። እርምጃ ከበዳት። ትንፋሽም እያጠራት መጣ።

ከአመታት በፊት ቶንሲል አሟት ቢያቅም፤ ሀኪም ቤት ሄዳ አልታከመችውም ነበር።
ህመሙ ድንገት የጀመረበት የሚታወቅ ቅጽበት የለም። በአመታት ውስጥ ችግሩ በዝምታ እያደገ የመጣ ነበር። ህክምና ሄዳ ስትመረመር የግራ ልቧ ቧንቧ (ሚትራል ቫልቭ (Mitral Valve)) ከባድ ጉዳት ላይ እንዳለ ተነገራት።
ገና በአስራ አራት አመቷ የልቧ ቧንቧ ስራውን በስርአት መስራት ተስኖት ነበር።
የራሂማም ታሪክ የብዙ ኢትዮጵያውን ህጻናት ታሪክ ነው። እሷ ብቸኛ አይደለችም። ብዙዎች ሳይታወቅ እየተሰቃዩ ነው።
የልብ ቧንቧ በሽታ ምንድነው?
የሰው ልጅ ልብ አራት ቧንቧዎች አሉት። እነዚህ ጡንቻዎች አይደሉም፤ የደም ሥሮችም አይደሉም። እነኝህ የደም ፍሰትን የሚቆጣጠሩ በሮች ናቸው።

ልብ በመታ ቁጥር እነዚህ ቧንቧዎች በትክክለኛው ጊዜ ይከፈታሉ፣ ይዘጋሉ። ይህም ደም ወደፊት ብቻ እንዲፈስ ይረዳል።
እነዚህ ቧንቧዎች ስራቸው ሲስናከል ፤ የደም ዝውውር ይስተጓጎላል። ልብም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲለፋ ይገደዳል። በሂደትም ልብ ይደክማል። መላው አካል ይዝላል።
ይህ ሁኔታ የልብ ቧንቧ በሽታ (Heart Valve Disease) ይባላል።
የልብ ቧንቧ በሽታ ስርጭት ምን ይመስላል?
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሕክምና መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ50 ሴቶች ውስጥ አንዷ የልብ ቧንቧ በሽታ ይኖርባታል። እድሜ በገፋ ቁጥር ስርጭቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። ዕድሜያቸው ከ75 በላይ በሆኑ 10 ሴቶች ውስጥ በአንዷ ላይ ይህ በሽታ ይታያል።
ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ሌላ ገጽታ አለው።

ለምን?
በኢትዮጵያ ይህ በሽታ የሚጀምረው በለጋ እድሜ ላይ ነው። በተቀረው የአለም ክፍልይህ በሽታ የሚመጣባቸው ዋነኛ ምክንያቶች ውስጥ ከእድሜ ጋር የተያያዙ የልብ ቧንቧ ለውጦች (Age related degenerative valvular changes) ነው።
በኢትዮጵያ የዚህ ዋነኛ መንስኤ ያልታከመ የጉሮሮ ኢንፌክሽን አልያም የቶንሲል በሽታ ነው። የኢትዮጵያ የልብ ማዕከል (Cardiac Centre of Ethiopia) ከተመዘገቡ የልብ ቧንቧ ታካሚዎች መሀከል ከፍተኛ መጠኑን (59.2%) የሚወስዱት ሴቶች ናቸው።
ስለ በሽታው ሂደት እና አመጣጥ በደንብ ለመረዳት ከዚህ በፊት የጻፍነውን እዚህ ያንብቡ።
የሚትራል ቧንቧ ችግር ምንድነው?
ከሁሉም የልብ ቧንቧ ችግሮች መካከል አንዱ በተለይ በሴቶች ላይ ጎልቶ ይታያል። ይህም የሚትራል ቧንቧ ችግር ነው።
ይህ ቧንቧ በግራ የልብ ክፍል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ የላይኛውን የልብ ክፍል (Atrium) ከታችኛው (Ventricle) የሚለይ ነው። ከሳንባ ኦክስጅን ይዞ የመጣው ደም፣ ወደ ዋናው ደም መርጫ ክፍል የሚያደርገውን ፍሰት ይቆጣጠራል።

የዚህም ቧንቧ ችግር በሴቶች ላይ በይበልጥ ይታያል። የሚትራል ቧንቧ መጥበብ (Mitral stenosis) በሴቶች ላይ ከወንዶች በ3 እጥፍ ይገኛል። የቧንቧው መላላትም (Mitral regurgitation) በሴቶች ላይ በብዛት ይታያል።
ቧንቧው ሲጠብ ፤ የደም መተላለፊያው ስለሚዘጋ/ስለሚጠብ የደም ዝውውር ይገደባል። ቧንቧው ሲላላ በበኩሉ ፤ አጥብቆ አይዘጋም። ለዚህም በትክክል ስላልተዘጋ ደም ወደ ኋላ ይመለሳል።
ለምን የሚትራል ቧንቧ ችግር በይበልጥ ሴቶችን ያጠቃል?

ሴቶች ውስጥ የሚገኘው ኢስትሮጅን (estrogen) የተባለው ሆርሞን የተጎዳው የቧንቧ ክፍል ይበልጥ እንዲወፍርና እንዲጠብ በማድረግ የበሽታውን ሂደት ሊያፋጥነው ይችላል። በተጨማሪም፣ የሴቶች የልብ ቧንቧ አነስተኛ መጠን ያለው በመሆኑ መጠነኛ የሆነ የጠባሳ መኖር እንኳ የቧንቧ መጥበብን (mitral stenosis) እና የጤና መታወክን ቀድሞ ያስከትላል።
ይህ ቧንቧ በልብ ውስጥ ከፍተኛውን የደም ግፊት የሚቋቋም ስለሆነ ፤ በበሽታው ምክንያት የሚፈጠር ጠባሳ በፍጥነት ይህንን ቧንባ ይጎዳል።
ምልክቶቹ
የልብ ቧንቧ በሽታ ሲጀምር ምልክት አያሳይም። ለውጦች በዝግመት ነው የሚመጡት። ከተለመዱ ምልክቶቹ መሀከል።
ያልተለመደ ድካም
በእንቅስቃሴ ወቅት የትንፋሽ ማጠር
የልብ ምት መዛባት
ማዞር ወይም ራስን መሳት
የእግር ወይም የሆድ እብጠት
ከእነዚህ ምልክቶች ባሻገር፣ እንደ ተጠቃው የልብ ቧንቧ ዓይነት የሚታዩ የተለዩ ምልክቶች ሊኖሩ ይችላሉ

ለምሳሌ፦
የሚትራል ቧንቧ ከጠበበ
የድምፅ መጎርነን ሊኖር (Hoarseness) ይችላል። የልብ የላይኛው ክፍል ሲያብጥ ድምፅን የሚቆጣጠሩ ነርቮችን ስለሚጫን ይፈጠራል።
ደም የተቀላቀለ አክታ (hemoptysis) ሊኖር ይችላል። ይህም ሳንባ ላይ የደም ግፊት በጣም ስለሚጨምር ጥቃቅን የደም ስሮች ፈንድተው ደም የተቀላቀለ አክታ ሊታይ ይችላል።
ጉንጮች ሊቀሉ ይችላሉ።
የሚትራል ቧንቧ ከላላ ደግሞ እነኝህን ምልክቶች ሊስተዋሉ ይችላሉ።
ሌሊት ሌሊት ለሽንት መነሳት ፦ ልብ ደምን በትክክል መግፋት ስለሚሳነው ሰውነታችን የተጠራቀመውን ፈሳሽ ለመቀነስ ሌሊት በተደጋጋሚ ሽንት እንዲመጣ ያደርጋል።
በእንቅልፍ መሃል ታፍኖ መንቃት (PND)፦ በእንቅልፍ መሀል በድንገት ትንፋሽ አጥሮዎት የሚቀሰቅስ የትንፋሽ እጥረት።
ራስን የመሳት ስሜት ፦ ደም ወደ ኋላ ስለሚመለስ ወደ ጭንቅላት የሚሄደው የደም መጠን ቀንሶ የማዞር ወይም የመሳት ስሜት ሊፈጥር ይችላል።
እንዴት ይመረመራል?

ለዚህ በሽታ ቅድመ ምርመራ ወሳኝ ነው። ሐኪሞች በመጀመሪያ በስቴቶስኮፕ ያልተለመደ የልብ ድምፅ (Murmur) መኖሩን ያዳምጣሉ። ከዚህ ባሻገር የተለያዩ ምርመራዎችን ሊያዙ ይችላሉ።
በሽታውን ለማረጋገጥ ዋነኛው ምርመራ ግን ኢኮካርዲዮግራፊ (የልብ አልትራሳውንድ) ነው።
እንዴት ይታከማል?
የዚህ በሽታ ሕክምናው እንደ ደረጃው ይወሰናል፦
በመጀመሪያ ደረጃ፦ በሽታው ያለበት ደረጃ ቀላል ከሆነ ፤ የልብ ቧንቧ ጉዳት የልብ ስራን በጣም ካላስተጓጎለ ፤ ምልክቶችን ለመቆጣጠር እና የልብ ሸክምን ለመቀነስ መድኃኒቶች ሊሰጡ ይችላሉ። መድሐኒትዎን እየወሰዱ የህክምና ክትትል ሳያቋርጡ መከታተል ይመከራል።

በከፍተኛ ደረጃ፦ ቧንቧው በከፍተኛ ሁኔታ ከተጎዳ ፤ የልብ ስራ እጅጉን ከተሰናከለ ይህን ጊዜ አማራጩ የቀዶ ጥገና ህክምና ይሆናል። ይህን ጊዜ የልብን ቧንቧ መጠገን አልያም የተጎዳውን ቧንቧ በአርተፍሻል ቧንቧ መቀየር አስፈላጊ ሆኖ ይገኛል። ይህ ህክምና ህይወት አድን ነው።
የተግባር ታሪክ
ድርጅታችን ተግባር በጎ አድራጎት (Tegbar Organization) በሚያደርገው የማያቋርጥ ጥረት ይህንን አስከፊ እውነታ ለመለወጥ እየሰራ ይገኛል። በድልም እየቀየረው ይገኛል።
ልቧ ከመቆሙ በፊት ደርሰንላታል።

ራሂማም በአጋራችን ሂሊንግ ቫልቭስ ኢትዮጵያ (Healing Valves Ethiopia)በኩል ከድርጅታችን ጋር በመገናኘቷ፤ የሚያስፈልጋትን የሕይወት አድን ቀዶ ጥገና ለማግኘት በቅታለች። በታዋቂው የልብ ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ዶ/ር ፈቀደ አግዋር የተመራውና ለ4 ሰዓታት የፈጀው አስደናቂ ቀዶ ጥገና፣ ለራሂማ ሁለተኛ የሕይወት ንጋትን ሰጥቷታል።
ይህ ስኬት ግን የኛ ብቻ ውጤት አይደለም፤ የአጋሮቻችን፣ የርኅሩኅ ለጋሾቻችን እና የሁላችንም የጋራ የድል አሻራ ነው!
እንኳን ደስ አለን!
ማሳረጊያ ምክር
ብዙዎቹ የልብ ቧንቧ በሽታዎች — በተለይም በኢትዮጵያ — መከላከል የሚቻሉ ናቸው። ለዚህም
የጉሮሮ ኢንፌክሽንን እንዲሁም ቶንሲልን ቀድመው ያክሙ።
መደበኛ ምርመራ ያድርጉ።
ያስተውሉ!
የልብ ቧንቧ በሽታ በድንገት አይጀምርም። የሚጀምረው በዝምታ፣ በትንንሽ ለውጦች እና ረቂቅ ምልክቶች ነው።
ለጤናዎ ዛሬውኑ ቦታ ይስጡ!




Comments